በህወሃት የሽብር ቡድን ህጻናትን በሃሺሽ አስክሮ የገቡበት ውጊያ

e66sobwwua0fal9“ከመቀሌ በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አቅጣጫ ወስደውን አፋር እስከምንደርስ ወዴት እንደሚወስዱን አላውቅም”

ህጻን ሄለን ሀድጉ
 ህጻን እየሩሳሌም ሃይላይም በእንባ ታጅባ ከመቀሌ መከላከያው ከወጣ በሁዋላ ታፍና ወደ ጦርነት መግባቱዋን ትናገራለች
***********************************
ከትግራይ፡ መቀሌ አስከ አፋር ድረስ ባልጠና ጉልበታቸው ተጉዘዋል። ከወንዝ ውሃና ከደረቅ ብስኩት ውጭ ለዛለ የህጻን ጉልበታቸው ያገኙት የለም። በህወሃት የሽብር ቡድን ተገደው ድንገት በገቡበት ውጊያ ብዙ እህት ወንድሞቻቸውን አጥተዋል።
“ምርኮኞቹ” ህጻናት ከእንባ ጋር እየታገሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ህወሃቶች እንዳይገድሉን ፈርተን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየተማገድን ነው ሲሉ ነው የተማረኩ ህጻናት “ወታደሮች” ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት።
ከእነዚሁ ታዳጊ ህጻናት “ወታደሮች” መካከል ኢየሩሳሌም ሃይላይ አንዷ ናት፤ እየሩሳሌም ሐምሌ 7 ቀን 2013 ከመቀሌ በድንገት ከቤቷ እንደወጣች ታፍና ወደ ጦርነት መምጣቷን ትናገራለች።
ምንም ዓይነት ሥልጠና ሆነ መሣሪያ ሳታገኝ ”አሸንፈን አዲስ አበባ እንገባለን” በሚል ባዶ የተስፋ ቃል እየሸነገሉ ወደ ጦርነት እንዳስገቧቸውም ትገልጻለች።
በመጨረሻም ጦርነቱ ሲጀመር እንደ ዕድሜ እኩዮቿ ህጻናት “ደንግጠን ራሳችንን ለማዳን ለመከላከያ ሠራዊት እጃችንን ሰጥተናል” ትላለች ኢየሩሳሌም።
ሌላዋ ህጻን ሄለን ሀድጉ በበኩሏ ከመቀሌ በመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሥመር አቅጣጫ አምጥተው አፋር ክልል እስከሚገቡ ድረስ ወዴት እየወሰዷቸው እንደሆነ ሳታውቅ መቆየቷን ታስታውሳለች።
በጦርነት ውስጥ ደረቅ ብስኩትና የወንዝ ውሃ እየጠጡ መቆየታቸውን የምትናገረው ሄለን፣ “ጓደኞቼ ራሳቸዉን ለማትረፍ በጭንቅ ላይ በነበሩበት ወቅት በአገር መከላከያ ተማርኬ ሕይወቴ በመትረፉ ተደስቼያለሁ” ብላለች።
የትግራይ ሕዝብ የህወሓት አሸባሪ ቡድን ራሱን በሥልጣን ላይ ለማቆየት ህጻናትን በግፍ ወደ ጦርነት በመማገድ እየፈጸመ ያለውን ግፍ እንዲያቆም እንዲታገለውም ጠይቃለች።
ሌላው ህጻን ኢሳያስ ዓለም በበኩሉ ጁንታዉ የትግራይ ህጻናትን በግዳጅ ወደ ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን ይመሰክራል።
እሱን ጨምሮ ሌሎች የእድሜ እኩዮቹ ተምረው ነገ የተሻለ ዜጋ ለመሆን ፍላጎትና ህልማቸው ቢሆንም፤ ጁንታው እንዳይገላቸው በመፍራት በተዋጊነት መሰለፋቸውን ይናገራል።
በጁንታው ተገድደው ወደጦርነት የገቡትና በመከላከያ ሰራዊት ጥንቃቄ የተሞላበት ርምጃ ህይወታቸው ተርፎ የተማረኩት ህፃናት “የጁንታው አመራሮች የራሳቸዉን ልጆች በውጭ አገር እያስተማሩ የእነሱና የቤተሰቦቻቸው ሕይወት ተስፋ በመደብዘዙ ተቆጭተናል” ይላሉ።
ህፃናቱ፣ የትግራይ ሕዝብ ራሱን በሥልጣን ለማቆየት ሲል ህጻናትን በግፍ ወደ ጦርነት የሚማግደውን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሊታገለው እንደሚገባ ነው በአፋር ግንባር በሀገር መከላከያ ሰራዊት የተማረኩተ ህጻናት “ወታደሮች” የገለጹት።
ጁንታዉ በኢትዮጵያ ላይ በጀመረዉ አጥፍቶ መጥፋት ዘመቻ፣ የትግራይ ህጻናትና ሴቶችን በተዋጊነት መጠቀም ከጀመረ ሰነባብቷል።
የሰሞኑን በአፋር ክልል ፈንቲ-ረሱ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በከፈተዉ ጥቃት የተማረኩት እነዚሁ ህጻናት፣ የጁንታው አሳፋሪና ከሰብዓዊነት የወጣ ባህሪን ዓለም በትኩረት ሊያየው እንደሚገባም ተናግረዋል።
የአፋር ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሺን ምክትል ኮሚሽነር መሀመድ አህመድ እንደገለጹት ጁንታው በዞኑ ያደረገዉን ወረራ የአፋር አርብቶ አደር ከመከላከያ ሠራዊትና ልዩ ሃይል ጎን በመቆም እየደመሰሰዉ ነዉ ።
ጁንታዉ ዛሬ በሀገር ላይ የከፈተዉ ጥቃት የቆየ ሀገር የማፍረስ ህልሙን እውን ለማድረግ በግልጽ የጀመረው መሆኑን ገልፀዋል።
በጦርነቱም ህጻናትን በሃሺሽ አስክሮ በማስገባት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሆኖ ከማንም በላይ የትግራይ እናቶችና ህጻናት ጠላትነቱን እያስመሰከረ ነዉ”ብለዋል
በመሆኑም የትግራይ ህዝብ ራሱን ለማቆየት ህፃናትን በጭካኔ ወደ ጦርነት እየማገደ ያለውን አሸባሪ ቡድን፣ ከመከላከያና ከሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን በመቆም እንዲታገለው ጠይቀዋል።
አሸባሪው ህወሃት ለአቅመ አዳም እና ሔዋን ያልደረሱትን ህጻናት እያስገደደ ለሦስት ቀናት ያልበለጠ ሥልጠና በመስጠት ወደ ውጊያ አስገብቶ መቋቋም በማይችሉት ጦርነት እየማገዳቸው መሆኑን መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ገልጿል።
“በጦር ሜዳ ካሰለፋቸው ህጻናት ድል አገኛለሁ ብሎ በማሰብ እያስጨረሳቸው ይገኛል” ያለው ሚኒስቴሩ፤ ይህ ሳይበቃ በውጊያ የተገደሉትን ህጻናት ሬሳ በመሰብሰብ “የኢትዮጵያ መንግስት ሠራዊት ገደላቸው” ብሎ በውጊያ ያስጨረሳቸውን ህጻናት አስከሬን መነገጃ ለማድረግ የተለመደውን የቅጥፈት ፕሮፓጋንዳ ለማሰራጨት አስከሬናቸውን ኹሓ ላይ ሰብስቦ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
(ኢ.ፕ.ድ)

1 Comment

  1. የደንቆሮ ጩኽት መልሶ መላልሶ። ወሬው ሁሉ ድግግሞሽ፤ ውሸት፤ የፈጠራ ፕሮፓጋንዳ ነው። ያልተደመሰሰው ተደመሰሰ፤ ያልተያዘው ተያዘ፤ ባጭሩ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቃሚዎች የበዙበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። Sensational media devoid of truth ዓለማችን እያዋከባት እንደሆነ ልብ ያለው ያስተውላል። ወደ ሃበሻው ምድር ችግር ስንገባ ራሱን አቁስሎ ድረሱልኝ የሚል የቁም ሙታን ክምር የሚራወጥባት ሃገር ናት። የሰሜኑን እዝ በጭካኔ የጨፈጨፈው ወያኔ ላይ ሰብአዊ መብት፤ የአለም ህግጋትን መጠበቅ፤ ወዘተ እያሉ መቀባጥር ጭራሽ አይገባኝም። ወያኔ የሚገባው አንድ መንገድ ብቻ ነው። ወያኔ በመጣበት የውጊያ ስልት ራስን አዘጋጅቶና አደራጅቶ መታገል ብቻ ነው የሚያዋጣው። 50 ዓመት የሞላው አሮጌ ክላሽን ይዞ ውጊያ የለም። እነርሱ በመነጸር የሚታገዝ አልሞ ተኳሽ እየተጠቀሙ ነው የሚገሉት። ለዚህ ይሆን ከአመታት በፊት የወያኔው ወታደራዊ ባለስልጣን በፊርማው በመቶ የሚቆጠሩ ስናይፕሮችን ወደ ትግራይ ያስተላለፈው? ወያኔ የሰሜኑን እዝ ለማጥቃት 3 ዓመት ያህል ተዘጋጅቷል ማለት ነው። ግን ማንም የነቃ ሰው አልነበረም። የኢትዮጵያ ወታደራዊ የስለላ መረብ ውሃ የማይቋጥር ስልቻ ነው። ምንም የማይነቃ። ወያኔ በፕሮፓጋንዳውም፤ በስለላውም በወታደራዊ መስኩም ብልጫ እያሳየ ይገኛል። አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው ወሬ የሚያቀብሉ፤ ስንቅና ትጥቅ ለወያኔ የሚልኩ፤ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ላይ እንቅፋት የሚያስቀምጡ በደርግ ጊዜም ነበሩ አሁንም አሉ። በዘሩና በቋንቋው የሰከረ ቢኖር ወያኔና የወያኔ ደጋፊዎች ናቸው። ለምን ይህ ሁሉ እብደት ይሆናል? ለምን የትግራይ ልጆች ያልቃሉ? እንዴትስ ነገርን ማርገብ ይቻላል በማለት በሰከነ መልኩ ቆም ብሎ የሚያስብ የለም። እንካ የአንገቴን ሃብል ሽጠህ ለወያኔ እርዳታ አድርስልኝ የሚሉ ጅሎች እንጂ። ማን እየሞተ ማን ይኖራል?
    አሁን እንደ አዲስ ነገር የሚነገረን የወያኔ ህጻናትን በጦር ሜዳ ማሰለፍና ሻሂ ነው እያሉ በሃሽሽ ሰውን አደንዝዞ ጦርነት መማገድ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ሲጠቀሙበት የነበረ ስልት እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። ህጻናትን ጦርነት ውስጥ ከተተ የሚባለውም የነበረ ያለ ነው። በድል አዲስ አበባ ሲገቡ ከወያኔ ሰራዊት ያሰናበቷቸው 30 ሺህ ተቀናሽ ተጋዳላይ ይበልጦቹ ከ 18 ዓመት እድሜ በታች ነበሩ። ስለሆነም አሁን ህጻናትን አሰለፉ ገለ መሌ ማለቱ መደንቆር ነው። ወያኔ በምንም ይሁን በምንም ወታደራዊ ስልቱ ማሸነፍ ብቻ ነው።
    በሌላ መልኩ በአዲስ አበባ አደባባዪችና በሌሎችም ከተሞች ለሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ማድረጉ መልካም ሆኖ ሳለ ሰልፍ ብቻውን ምንም ለውጥ አያመጣም። በአየር ሃይል፤ በባህር ሃይል፤ በምድር ጦር፤ በፊዴራል ሰራዊትና በክልል ሃይሎች የጸጥታ ተቋማት በመመዝገብ ስልጥና አግኝቶ ግንባር በመሄድ መፋለፍ እስካልተቻለ ድረስ ሺህ ጊዜ የድጋፍ ሰልፍ የወያኔን ግስጋሴ አይገታውም። በየመድረኩ የሚለፈልፉት የጦር አበጋዞችና የፓለቲካ ሰዎችም ይገርሙኛል። አይበቃም ዲስኩር? እንደምንሰማው ከሆነ ወያኔ ከትግራይ መሬት ወጥቶ በአማራ፤ በአፋር ሰው እየገደለና እያፈናቀለ እንደሆነ ነው። ታዲያ አዲስ አበባ እስኪገባ ነው የሚጠበቀው? ሌላው የሚያናድደኝ የዚህ ክልል ሰራዊት አሸኛኘት ተደረገለት እየተባለ ዜና መሆኑ ነው። መጣንላችሁ መንገድ ላይ ጠብቃችሁ ግደሉን እንደማለት ነው። እናንተ ጡሩንባ ሳትነፉ የወያኔ የስለላ መረብ እኮ ማን ማን ከየት ወደ የት እንደሚሄድ ያውቃል። የነበረና አዲስ የተዘረጋ የስለላ መረባቸውን ከውጭ እስከ ሃገር ቤት እንደመበጣጠስ መጣንባችሁ ጠብቁን እያሉ መለከት መንፋት ከአንድ ወታደራዊ ተቋም አይጠበቅም።
    በመዝጊያው የተማረኩ ልጆች (ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን) በእውነት ላይ በተመረኮዘ መልኩ በራሳቸው ቋንቋ በትግርኛ ያለምንም ተጽኖ በወያኔ የደረሰባቸውን ግፍና መከራ ለህዝባችን እንዲያስረድ ማድረግ ነው። የዓለም አቀፍ ህብረተሰብ በተለይም አሜሪካና ሸሪኮቿ በምንም ሂሳብ ቢሆን ወያኔን ይኮንናሉ ብሎ ማመን ጅልነት ነው። ወያኔ የአሜሪካ ባለስልጣኖችን ሰርቆ የሚያበላ ጥገት ነው የነበረው። የአለም ባንክና ሌሎችም አበዳሪና የተራ ዶ ኦ መልክ ያላቸው ድርጅቶች ሁሉ የብድርና የእርዳታውን ገንዘብ አዙረው ነው ወደ አሜሪካ ባንክ የሚከቱት። ለተበዳሪ ሃገሮችም የሚቀርላቸው ነገር ቢኖር ዝንተ ዓለም ወለድ መክፈል ነው። የዚህ ሴራ ደንበኛ አጋፋሪ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ነው። የስዬ አብርሃን ከሥር እስከ አሜሪካን ሃርቫርድ ኮሌጅ ጉዞ መመልከት በቂ ይሆናል። አሁን ደግሞ በዘረፈው ሃብት ከሚኖርበት የቦስተን ከተማ ካርቱም ድረስ የተጓዘው በአሜሪካ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማቀናጀት ነው፡፡ የሰላም አስከባሪ ጦር፤ የአሜሪካ ጦር ትግራይ ሊገባ ነው የሚባለው ሁሉ ቱልቱላ ነው። ያው በሱዳንና በግብጽ አቀናባሪነት ወያኔዎች የሃይል ማመንጫና ድልድይ እያፈረሱ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ግስጋሴ በመግታት ለአለም ህዝብ የተለመደ ኡኡታቸውን ማሰማት ይቀጥላሉ። ውጊያው ይቀጥላል፤ አረቡ ዓለም ይደግፋቸዋል፤ እኛም እንደተለመደው ስንተራመስ ዝንተ ዓለም እንኖራለን። መፍትሄው ወያኔን ላንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ከትግራይ መሬት ጠራርጎ በማጥፋት የትግራይ ህዝብ የራሱን በራሱ መሪዎች እንዲመርጥና ከቀረው የሃገሪቱ ህዝብ ጋር በፍቅርና በሰላም አብሮ መኖሩ ብቻ ነው የሚያዛልቀው። ሌላው ሁሉ የፓለቲካ ግለትና ውስልትና ለማንም አይጠቅምም። በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.