ይህ ፁሑፍ ልብ ወለድ አይደለም። ይህ ፁሑፍ ፖለቲካዊ ትንታኔም አይደለም። ወይም በምናብ የተፃፈ የይሆናል መላምታዊ ትረካም አይደለም። ይልቁንም በሰሜን ኦሞ ጀግኖች ማፍለቂያ በሆነ ግዙፍ ወታደራዊ ካምፕ ዉስጥ የሆነ እና እየሆነም ያለ የሰራዊቱ እዉነተኛ ለሀገር የመሞት ዝግጅት ታሪክ ነዉ። በቦታዉ እኔም ነበርኩና እዉነቱን ልመሰክር ወደድኩ።
እንደጋዜጠኛ አልያም እንደ ፀሐፊ ሳይሆን እኔም ለሀገሬ ስል ወያኔን ጥዬ ለመዉደቅ ምልምል ሰልጣኝ ነበርኩና ሁሌም የምኮራበትን መከላከያ እና ሕይወቱን በምናብ ላሳያችሁ ዛሬ ፈለኩ።
ሞቱ ብቻ ሳይሆን የመሞት ዝግጅቱም መራራ ነዉ። በርካታ ፈታኝ ዕለቶችና ወራቶች አሉት። ብዙ ኖሬ ሕዝቤን ከመከራና ምርኮ እታደጋለሁ ፤ የሀገሬንም ክብርና ሉዓላዊነት አስጠብቃለሁ የሚለዉ ተስፋ በብዙዎቻችን አዕምሮ ዉስጥ በርቀት የሚያቃጭል እዉነት ቢሆንም ለሀገር ሲባል በበረሃ ወድቆ የአሞራ ሲሳይ የመሆኑ እዉነታ ግን ዘወትር ገዝፎ ፊት ለፊት ይደቀናል። የመስዋዕትነቱ ግዝፈት ግን ብዙ ከመኖርና ሀገርን ከመታደግ ፍላጎት እንጂ ከመሞት ፍራቻ አይደለም። የሀገሬ ኢትዮጵያ ወታደር ልቡ ራርቶ በአታላዮች ሲታለል እንጂ መቼም ዉጊያን ሲፈራ አይቼም ሰምቼም አላዉቅም።
የብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ የሚገኘዉ በቀድሞዉ ሲዳሞ ክፍለ ሀገር በሰሜን ኦሞ አስተዳደር ዉስጥ ነዉ። ግዙፍ የሆነና ኢትዮጵያ አለኝ ከምትላቸዉ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ግንባር ቀደሙ ነዉ። አስፈላጊ ከሆነ በአንድ ጊዜ እስከ አምሳ ሺህ ቀይ ለባሽ አየር ወለድ ጀግኖችን ማሰልጠን የሚችል ድንቅና ግዙፍ ማዕከል ነዉ። በብዙ መቶ አየር መቃወሚያዎችን፣ ታንኮችን፣ አዉሮፕላኖችን ማስተናገድ የሚችል ራሱን የቻለ ከተማ ነዉ። በሕይወቴ ከምኮራባቸዉ አጋጣሚዎች መካከል የእኔም ታሪክ በአንድ ወቅት የዚህ ጀግና ታሪክ አካል መሆኑ ነዉ።
“አየር ወለድ ነኝ ዘላይ ከአንቶኖፍ ላይ” ብለን አብረን በቆጠራ ሜዳ፣ በተኩስ ወረዳ፣በቡቄሳ ኮረብታ እና በመሳሰሉት በሞራል ከተንቦጎቦግነዉ የኢትዮጵያ ልጆች መካከል ዛሬ በሕይወት ያሉም እንዲሁም መስዋዕት የሆኑም ቢኖሩ ትዉልድ ግን እንደ ጅረት ዉሃ ይቀጥላልና የጀግኖቹ ማዕከል ዛሬም አዳዲስ ጀግኖችን እያፈራች አለች። ነገም ከእናት ኢትዮጵያ ጋር ትኖራለች።
ዛሬ በትግራይ ወገኔ ላይ አልተኩስም ብሎ አፈሙዙን በራሱ ጭንቅላት ላይ የሚደቅነዉን የሀገሬ ጀግና ታሪክ ብዙዉ ሰዉ ሲሰማ ሊደንቀዉ ወይንም ሊጠራጠር ይችላል። ስለዚህም በራሴዉ ዓይን ያየሁትን የደጀን የመስዋዕትነት ገድል ልመስክር ግድ አለኝ።
ከቀትር በኃላ ነበር ሰዓቱ። የዕለቱ ወታደራዊ ትምህርት ስለ ቦንብ ገለፃ እና ልምምድ ነበር። መቶ አለቃ በዛብህ ከምንሰለጥነዉ ምልምል ወታደሮች ራቅ ብሎ በሚመስጥ አንደበት ስለ ተለያዩ ቦንቦችና ፈንጂዎች ያስረዳን ነበር። አር ጂ ዲ አምስት ስለሚባልና ከአርባ እስከ አምሳ ሜትር እስከሚወረወረዉ የማጥቂያ ቦንብ፣ ኤፍ አንድ ስለሚባል የመከላከያ እና ሃያ ስድስት ጊዜ ስለሚፈናጠር የእጅ ቦንብ፣ እንዲሁም አር ጂ አርባ ሁለት ስለሚባል ቦንብ ይተርክልን ነበር።
መቶ አለቃ በዛብህ በንግግሮቹ መሐል ደጋግሞ የሚናገር የነበረዉ የጀግንነት እና ስለ ሀገር ፍቅር የሚከፈል መስዋዕትነት መቼም አይረሳኝም። ኢትዮጵያን የሚወድ፣ የሀገሩን ልጆች የሚያፈቅር፣ በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ጀግና ወጣት ነበር።
መቶ አለቃ በዛብህ ዛሬ ዉስጤ እየተናወጠ እንዳስታዉሰዉ ያደረገኝ አባባሉ በወቅቱ የእሱ ብቻ ልዩ ስብዕና መስሎኝ ነበር። እያደር ግን የመላዉ ሰራዊቱ ኢትዮጵያዊ እሴት መሆኑን ተረድቻለሁ። በንግግሮቹ ከሚያዘወትረዉ አባባል የማልረሳዉ እንዲህ ይላል “እኛ ኢትዮጵያዊ ነን። በምንም መልኩ ሲቪል ላይ አንተኩስም። ባሕላችን አይደለም። የጀግናም መገለጫ ሰዉ መግደል አይደለም” የሚለዉ ነዉ።
መቶ አለቃ በዛብህ ቦንብን እና ፈንጂን ሲያስተምር ሀገሩን ከወንበዴና ወራሪ ለመከላከያ እንጂ ሌላን ለማጥፊያ እንዳይሆን የሚመክር ልበ ቀና የአየር ወለድ አባል ነበር። የወታደር ጀግንነትና ሞት ግን የትም ሊሆን ይችላልና በዚያችዉ ዕለት ምሽት በቡቄሳ ኮረብታ ላይ በፈንጂ ስለመከላከልና ማጥቃት ለማስተማር በገለፃ ላይ እንዳለ ተሰዉቷል። የእሱ የጀግንነት ታሪክ ግን በቡቄሳ ኮረብታ ላይ መሰዋቱ መሆኑ አይደለም፤ ይልቁንም በጣር ድምፁ የተወልን አደራ ነዉ።
መቶ አለቃ በዛብህ ያቀጣጠላት ሶቪየት ሕብረት ሰራሽ ባለ አራት መቶ ሃያ ግራም የፈንጂ ፊዉዝ ችግር ነበረባትና ሳይታሰብ ተቀጣጥላ በፍጥነት ፈንጂዉን ትለኩስበታለች። በቅፅበትም እጁ ላይ እንዳለች በመፈንዳት በደም ታጥበዋለች። እጆቹን እና እግሮቹንም እንደ ሮኬት በየቦታዉም ትሰዳለች።
የቡቄሳ ኮረብታ በቅፅበት በሆነዉ በመደናገጥ ፀጥ እረጭ አለች። ወዲያዉ በደም የተጨማለቀዉ ሰዉነቱን ጓደኞቹ በቃሬዛ አድርገዉ ከኮረብታዉ ሲያወርዱት አንድ በሴቃ የታጀበ ድምፅ ደጋግሞ ይሰማ ነበር፡ …… “አይዟችሁ ….ኢትዮጵያን አደራ ….. አይዟችሁ ….ኢትዮጵያን አደራ” ይላል ያ ድምፅ እየደጋገመ።
ብዙዎች ሰልጣኞች በድንጋጤ ዉስጥ የነበሩ ቢሆኑም ደጋግመዉ ሰሙት። እኔም ሐዘን ዉስጤን ቢያጥለቀልቀዉም ደጋግሜ ሰማሁት። ሁላችንም ግን ቀድሞም የኢትዮጵያ ፍቅር ነበርና እዚያ በርሃ ዉስጥ ያሰባሰበን የእሱ በሴቃ ዉስጥ የነበረ አደራ ይበልጥ አፀናን።
ከጥንት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ወታደር ዉስጥ ያለዉ ወኔ ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር አብሮ የሚወለድ የሀገር ፍቅሩ መገለጫ ነዉና ሁሌም ይኖራል። ርዕራኤዉን ፍርሃት፤ አስተዋይነቱን ሞኝነት በማድረግ ብዙ ባንዳዎችና ከሃዲዎች በየዘመናቱ ብቅ እያሉ ያልተገባ መስዋዕትነት ቢያስከፍሉትም ሀገሩን በነፃነት ጠብቆ እስከዛሬ ኖሯል። ወደፊትም በጀግንነቱ ሀገሩን እየጠበቀ ይኖራል።
ዛሬ የሀገሬን አዛዉንትና ሕፃን ከምገድል በሀገሬ ልጅ ምርኮኛ ልሁን ባለ እንደ ሌባና ቀማኛ ከተማ ማዕል እያንገላቱ ሲሳለቁበት ሳይ የወታደር መስዋዕትነት ግዝፈቱ ይበልጥ ያኮራኛል። አልገድለዉም ይቅር ያለዉ የሀገሩ ልጅ ባንዳና ወንበዴ ሆኖ ምርኮኛ በማድረግ ሲሳለቅበት መመልከት ሽንፈት ሳይሆን ሰዉ መሆንና ጀግንነት ነዉ።
ንፁሑ ሕፃን አልገድልም ብሎ መማረክን መፍቀድ ኩራት እንጂ ዉርደት አይደለም።“አይዞን” ሲል የሰማሁት ያ የሴቃ ድምፅም የሚነግረኝ በመከራና ስቃይ ዉስጥ ስለሌላና ሀገር ማሰብ እንጂ እርኩስ መሆንን አይደለም። ጀግና ሩኸሩህ ነዉ። ጀግና በገደለዉ ሳይሆን ከሞት ባዳነዉ የሚኩራራ ሰዉ ነዉ።…. አይዞን ወገኔ።
ኢትዮጵያ ትቅደም።
ዶ/ር መኮንን ብሩ