” የእኛ አገር ዋና ችግር በድህነታችን ሰበብ አቅም ማጣት ነው ። አቅም በማጣታችን የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን መጠቀም አልቻልንም ። የተፈጥሮ ሀብታችንንም ባለመጠቀማችን ፣ ለመበልፀግ አልቻልንም ። ሥለ አልበለፀግንም በሥልጣኔ ከፍ ለማለት አዳጋች ሆኖብናል። በመበልፀጋቸው በሥልጣኔ ከፍ ያሉት ሁለንተናዊ ኃይላቸው ከእኛ በመቶ እጅ በመብለጡ ፣ በታጠቁት ኃይል ተጠቅመው ፣ የጥሬ ሀብተ (የልዩ ልዩ ማዕድናት ሀብታችንን ለመበዝበዝ ) ፍላጎታቸውን ለማርካት እኛን በጎሣ ፣ በቋንቋና በኃይማኖት በቀላሉ በመከፋፈል ፣ አንዱን ጎሣ የበለጠ ተጠቃሚ ቀሪውን ጎሣ የበለጠ ተጎጂ አድርጎ በመተከል ፣ ሌላውን ዘውግ ተነቃይና ተሳዳጅ በማድረግ ፣በጥቂት ተጠቃሚ ቡድኖች አማካኝነት ፣ የሚቀነቀን የሤራ ፖለቲካን በመላ አገራችን በመዘርጋት… እኛ በለማወቅ እርስ በእርስ ሥንጠፋፋ እነርሱ ብዝበዛቸውን በማጧጧፍ ባለፀጋ አገራቸውን የበለጠ ተፈሪና ተከባሪ ለማድረግ ሲጥሩ ይሥተዋላሉ። በተቃራኒው ደግሞ በእኩል ተጠቃሚነት የሚያምኑ ኃያላን መንግስታት የሉም ማለት አይቻለም። በቅንነት ፣ በግልፅ የንግድ ህግ፣በሰጥቶ መቀበል ፣ ከአገራችን የብልፅግና ራእይ ጎን የተሠለፉ መኖራቸው አይካድም።
(ቻይና እና ሩሲያ እናመሰግናለን፡፡ )
ከእነዚህህ ቅን የበለፀጉት አገራት በተቃራኒ የተሠለፉ የበለፀጉት አገሮች ፤ቱጃሮቻቸውን የበለጠ ቱጃር የማድረግ ፤ በአፍሪካ ሌባና ዘራፊ መንግስት ዘላለም እንዲገዛ ነው የሚፈልጉት ፡፡ ምክንያቱም በማንኪያ እየሰጠ በእንቅብ የሚዝቅ ይሉንታ ቢስ ሆዳምነታቸው ዛሬም እንደ ቅኝ ግዛት ዘመናቸው እንደተጠናወታቸው ነውና !
እነዜህ የቱጃር አገር መሪዎች ከቶም ስለዴሞክራሲ ፣ ስለሰብአዊ መብት ፣ሰለሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት መሞላት የማይገዳቸው ፣ በስግብግብነት ህሊናቸው የታወረ ፤ ፀረ ክርስቶሶች መሆናቸውን መረዳት የምትችሉት ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በሶሪያ ፣በሊቢያ ፣በኢራቅ እና በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት እየፈጸሙ ያሉትን ነውር ስታስተውሉ ነው፡፡
ቱጃሮቹ ሲጀመር የበለጸጉት በጥቁር ህዝብ ጭንቅላትና ፣ ጉልበት ነው፡፡ ይህንን እውነት ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ዛሬ በ21 ኛው ከ/ዘ እንኳን በቀደመው የቅኝ ገዢነት አስተሳሰብ ፣ ፍትሃዊ ባልሆነ ተጠቃሚነት አፍሪካን እንዝረፍ ባዮች ናቸው፡፤ መንግስቶቻቸው የቱጃሮቻቸውን ጥቅም አስጠባቂ በመሆናቸው ፣ ዛሬም በገፍ የሚመርቱትን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ፣ ለምስኪኖቹ አፍሪካዊያን መጨራረሼ ከመሸጥና አፍሪካን ሰው አልባ ከማድረግ የዘለለ ህልም ከቶም እንደሌላቸው ዳቢሎሳዊ ተግባራቸው ያሳብቃል፡፡
እንዚህ በተግባራቸው ዳቢሎስን የሚመስሉ ሰው መሳይ በሸንጎዎች ፣ በማንኛውም መንገድ በመሄድ ፣ የበለጠ ተጠቃሚ ብቻ ሣይሆን በጉልበታቸው ተጠቅመው ነፃ በዝባዥ ለመሆን የሚፈልጉ ናቸው። ይህንንም በኢራን ፣ በሊቢያ ፣ በአፍጋኒስታን፣ ጥቂት በማይባሉ የአፍሪካ አገራት ዛሬም እያሳዩ ነው፡፡ እነዚህ ፣ ለአፍሪካ ደሃ ህዝቦች ደንታ ቢስ የሆኑ ፣ ብዝበዛን ለልጅ ልጆቻቸው ያወረሱ ግፈኛ የኃያላኑ መንግሥታት ቱጃሮች የሚፈፅሙት የሴራ ፖለቲካ ና እኩይ ተግባር ፣ በሚኒሊክ ና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይህን ያህል የደመቀ አልነበረም ።
የደመቀ ችግራቸው ፈጦ የወጣው በደርግ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡በደርግ ዘመነ መንግስት የአሜሪካ ና የሩሲያ ገመድ ጉተታ እጅግ በመድመቁ በኤርትራ ፣ በትግራይ ና በአሶሳ እንዲሁም በኡጋዴን አካባቢ ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች አገር የማፍረሥ ጥንሥሥ የጀመሩት በአሜሪካኑ ሲ አይ ኤ አማካኝነት ነው፡፡ ይህንን ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳም እስከ ዛሬ ከእንጊሊዝና ከአሜሪካ ነጮች ጥገኝነት ያልተላቀቀቸው የጥቁሩ ፈርዖን አገር በግንባር ቀደምትነት ታስፈፅም ነበር፡፡ ዛሬም እያስፈጸመች ነው፡፡ ( ዛሬም በወንዛችና በአባይ ተጠቅመን እንዳንበለፅግ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም ፡፡ ዛሬም የሱዳን ሽግግር መንግስትን እንደ አንድ የህዳሴ ግድብን አደናቃፊ ዲንጋይ አድርጋ መጣሁባችሁ በማለት ለማስፈራራት ትሞክራለች፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ከፈጣሪችን በቀር በአገራችን የሚመጣብን ጠላትን ፈርተን እነደማናውቅ ግን አሳምራ ታውቀለች፡፡ እናም ፣ የሱዳን መንግስትን ሆይ ጨው ለራሱ ሲል እነደሚጣፍጥ ሁሉ ፣ አንተም ለራስህ ሥትል ልብ ግዛ እንለዋለን ፡፡ )
የኒኩላር ጦር መሳርያ ባለቤቶቹ ባለጸጋ አገራት ፣ ደሃ አገራትን እጅ በመጠምዘዘ በግድ ተመፅዋች ሆነው እንዲኖሩ እንዳደረጓቸው የታወቀ ነውና ከላይ በጠቀስኩት አስቀድሞ በተጠና እና በታሪክ በታወቀ መንገድ ፣ ለኢትዮጵያ ቋሚ ጠላት ግብፅን በመፍጠር ቀደኛውን የሰው ጠላት ወያኔን የአጀንዳቸው ዋነኛ ፈጻሚ አደረጉት ፡፡…
አገራችን በወያኔ አማካኝነት እንድትበታተን ያቀዱት ሴራም ፈር ይዞላቸው ነበር፡፡ እነ ጎሹ ወልዴ የዛሬ 29 ዓመት አሜሪካኖች ወያኔን ሥልጣን እንዲዝ ሲያደርጉ ፣” ኢትዮጵያን የመሰለች ታላቅ አገር የራሳቸውን ቤተሰብ እንኳን በቅጡ ማስተዳደር ለማይችሉ ለአልባንያ ኮሚኒስቶች መስጠት እብደት ነው ፡፡ ” ቢሉም ፣ የእቅዳቸው ግብ ፣ አገሪቱን ማፈራረስ ነበርና ወያኔን ወደ ሚኒልክ ቤተመንግስት አስገቡት፡፡…
አገሪቱም ፣በአሜሪካ ፊት አውራሪነት ፣ የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች ኢጣሊያን እና እንግሊዝ በጠነሰሱት የከፋፍለህ ግዛ አክሳሪ ፖለቲካ ውስጥ ተመልሳ ተዘፈቀች። 20 ኛው ክ / ዘመንም ኢትዮጵያን ቀስ ፣ በቀስ ገዝግዘው ለማፈራረስ በሚጥሩ የእናት ጡት ነካሾች ተሞላ ። ደርግ በወቅታዊው የታደጊ ዓለም ፋሽን በሆነው የኮሚኒዝም ሥርዓት በመመራቱ ፣ ኢፔሪያሊስት የተባሉ ኃይላት ከደርግ በተቃራኒ ቆሙ ። በዳቦ ችግሩም ገብተው፣ የተለያዩ የጎሣ ቡድኖች የኢኮኖሚ ኃይልን በሚሲዮናዊያን እና በረጂ ድርጅቶች አማካኝነት እንዲያገኙ አደረጉ ። ከህዝቡ ጉሮሮ ነጥቀው በቢሊን የሚቆጠር ዳቦ በምራብአዊያን ባንክ አከማቹ፡፡ በህቡም ነቅቻለው ባዩን እና የዳቦ ችግር ያለበትን በተራ ዘረኝነት ቅሥቀሣ እየሰበኩ ና ፍርፋሪ እየሰጡ ፣ በአገር አውዳሚ ዓላማቸው ዙሪያ አሰለፉት ።
(ታሪክ እንደሚነግረን እውነት በ 1983 ዓ/ም ፣ ወያኔዎች አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ሻቢያ ደግሞ ኤርትራን ከኢትዮጵያ በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ኃያላን ፈቃድ ከእናት አገሯ ገነጠለ ። ወያኔም ” በዲፋክቶ መንግሥትነቱ ” ኤርትራ እንድትገነጠል መፍቀድ እንደማይችል እየታወቀ ፣ የሽግግሩ መንግሥት ፕሬዝዳንት የእናት ጡት ነካሹ መሪ ” ኤርትራን አንፈልጋትም ፡፡ ከእናት አገሯ ትቆረጥ ፡፡ ” በማለት የመጀመሪያውን የይሁንታ ፊርማ በተባበሩት መንግሥታት መዝገብ ላይ ያለሐፍረት ኤርትራን መንገዱን ጨርቅ ያደርግልሽ አላት ። ኤርትራ ግን ለእነ አሜሪካ ተንበርካኪ የሆነ መሪ አልነበራትም እና አሜሪካንን እዛው በጸበልሽ አቻ ወዳጅነት እንጂ ቅኝ አልገዛም አለቻት ፡፡ ኢሳያስም በዚህ አቋሙ የአሜሪካ ቱጃሮች ጥርሳቸውን ነከሱበት ፡፡ በዚህ የተነሳም የኤርትራ ህዝብ ሥቃይ ደረሰበት ፡፡ ይገርማል ራሳቸው እርስ በእርስ እንድንጠፋፋ እያደረጉን እና እያጫረሱን ዳር ቆመው ይስቁብናል ፡፡ አይገርምም ?)
የዲፋክቶው መንግሥቶ ወያኔ (… ) በወቅቱ ቤተ መንግሥቱን ብቻ ሳይሆን ፣ ቤተ እምነቱንም ጭምር ተቀጣጥራ የዜጎችን አፍ በጠመንጃ በማስፈራራት ለጎመች ፡፡ በናዝሬት ፣ በሻሸመኔ ፣በአዋሳ ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች በ1983 ዓ/ም ከግንቦት 20 በኋላ ወያኔ ሌባነው እያለችና እያስባለች በጠራራ ፀሐይ ራስዋ ፍርድ ቤትና ፍትህን ሆና ፣ ግድግዳ አስደግፋ ስንቱን እንደ ረሸነች ቤቱ ይቁጠረው፡፡
በወቅቱ የዜጎች አፍ የተለጎመው መሳሬያው ህግ እንደማያከብር ፣ ፍትህን ደፍጣች እንደሆነ በማወቁ ና ድንገተኛ ክሥተቱ ፣ በፈጠረበት በዢታ ነው ። ከነበረበት ከኮሚኒስት ሥርዓት ተላቀሃል ቢባልም ወያኔ በኃይማኖቱ ላይ ሾሚ ፣ ፈላጭና ቆራጭ ሆና መምጣትዋን ፣ያለሲኖዶሱ እውቅና ፣ፍላጎት ፣ዶግማም ሆነ ቀኖና የፈለገችውን የመላው ኦርቶዶክስ አማኝ አባት ማድረጓንም በማስተዋል ፈጣሪን የተገዳደረን ሴጣን መዳፈር ምን እንደሚያስከትል ህዝብ በመገንዘቡ ለሁሉም ግዜ አለው በማለት አድፍጦ መቀመጥን ምርጫው አድርጎም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ፡፡
ወያኔ በማንአለብኝነት ፣ በአይን አውጣነት ና በእምነተ ቢስነት በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ውሥጥ የፖለቲካ ሹመኛን መደበች። ከፓትርያርኩ ጀምሮ በተዋረድ የራስዋን ፖለቲካ አራማጆች በኃላፊነት እነዲቀመጡ አደረገች፡። የምእመናኑንም የእምነት ጥንካሬ ዝቅ ለማድረግ በብርቱ ጥራች ። ባይሳካላትም።
ወያኔ አማኙን አሥመሳይ አማኝ ማድረግ ሙሉ፣ ለሙሉ ባይሳካላትም ፣ የጎሤ እምነት በመፍጠር እግዜርን የአማራ ፣ የኦሮሞ ፣ የትግሬ ፣ የጉራጌ ወዘተ ። ለማድረግ ጥራለች፡፤ በአንድ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጥላ ሥር ያለውን አማኝ በልቡ በጎሳው እንዲጠረነፍ አድርጋው እንደነበር ይታወቃል። …ጦሱም ጃዋር ዘብጥያ እሥከወረደበት ጊዜ ድረስ መቀጠሉን አትረሱትም። ( ዛሬም ብዙዎቹ ንስሃ እንደገቡና የሁላችንም ፈጣሪ ይቅር እንዲላቸው ተንበርክከው ለፈጣሪ መፀለያቸውን ፣ ውንድምና እህታቸውን በቋንቋ ልዩነታቸው ብቻ ማስቀየማቸው ስህተት እንደሆነ ግብቷቸው መፀፀታቸውን ግን አላውቅም፡፡)
ወያኔ ለብዝበዛ የሚያመቻትን የአፓርታይድ ሥርዓት ዘርግታ በዘረኝነት መንገድ ላይ እየጦዘች ፣ የብዝበዛ ተባባሪዋን ቅንጣቢ እየሰጠች አገርን መጋጦ ብቻ ሳይሆን የሚቆጨው፣ ወያኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብቻ አያሌ ምሁራንን ሥልጣን እንደያዘች በማግስቱ በማባረር፣ጥራት የሌለው የትምህርት ሥርዓትን አንበራ ትውልድን የመግደል ሥራዋን ” ሀ ” ብላ መጀመሯ አይረሳም።
ይህ ብቻ አይደለም ። የወያኔ ግፍ ። ወያኔ ቋንቋ የመግባብያ መሣሪያ እንዳልሆነ ሁሉ ፣ የመጨቆኛ መሣሪያ ነው ፡፡ ብላ ፣ እራሷ ትግራይን በቋንቋ ጠቅልላ በመያዝ፣ በየአገሩ ተሰባጥሮ የሚኖረውን አጥር የሌለውን ዜጋ እንደቅኝ ተገዢ ሆኖ እንዲኖር ለአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድን ብቻ መብትን በመሥጠት ኢትዮጵያዊያንን በዓለም ላይ በሌለ ና ፍፁም በሚወገዝ በአፖርታይድ ሥርዓት ረገጣ ስትገዛ ነበር ። አንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ሌላውን በቋንቋው ብቻ እንዲጨቆን በማድረግም ፣ በዜጎች በደል እያላገጠች ለ27 ዓመት በሚኒሊክ ቤተመንግሥት ውሥጥ በእንከን በተሟላው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲዋ እየተመፃደቀች ኖራለች።
የወያኔ የከፋፍለህ ግዛ ፣ ፖለቲካዊ ሥርዓቷ ብቻ አልነበረም በእንከን የተሞለው ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚው ና የማህበራዊ መሥክ ፖሊሲዋ ፣ከጥቂት ቡድኖች ብዝበዛ ጋር የተቆራኘ ነበር ። ዛሬም አንዳንድ ወያኔ ሰራሽ ፖሊሲ በለውጥ አራማጁ መንግሥት እየተተገበረ አይደለም የሚል ማነው ? በቀለሉ የትምህርት ፖሊሲውን ማየት ይቻላል።
እነዚህ ወያኒያዊ ፖሊሲዎች ናቸው የአገሪቱ በሽታዎች ። እነዚህ ፖሊሲዎች መላውን ዜጋ በሚጠቅም ፣ አገርን አበልፃጊ ፖሊሲ እሥካልተቀየሩ ጊዜ ድረስ አገሪቱ በህመም ብዛት ክፉኛ እያቃሰተች ፣ ቅኑው ዓለም በአዘኔታ ከንፈሩን እየመጠጠላት ፣ ጠላቶቿም ” ያሰቡክት ተሳካ ፣ ያለምኩት ደረሰ…” እያሉ ፤ በውድቀቷ ተደሥተው ” አሸሼ ገዳሜ ” ማለታቸውን ይቀጥላሉ። የኢትዮጵያ ህመም መንስኤ እሥከነ ሰንኮፉ እሥካታልተነቀለ ጊዜ ድረስም ይኸው ዜማቸው ይቀጥላል፡፡ …
ህገ መንግሥቱ ውሥጥ የተሰነቀሩት ከፋፋይ ና ዘረኛ ሃሳቦችን ያዘሉ ህጎች ፣በጥልቀት ተፈትሸው እንዲሰረዙ እሥካልተደረገ ጊዜ ድረሥ የአገራችን በሽታ እሥከነሰንኮፉ መንቀል አይቻልም። …
ዛሬ የአገርን ችግር በጥልቀት አስተውሎ እሰከሰንኮፉ መንቀል ኢትዮጵያን ለማበልፀግ ወደሚረዳው መንገድ ይወስደናል ብየየ አምናለሁ፡፡ ለዚህም እነዲረዳን ጠንካራ ህግ አስከባሪ እንዲኖረን መስራትና የድህንነት ሃይላችንን ማጠናከርና የጠላቶቻችንን የፋይናንስ መዋቅር በመበጣጠስ ኃይል ማሳጣት ይኖርብናል ፡፡ በዚ ሀገር ጥቂት የማይባሉ ከተከፈላቸው ለሴጣን ለማገልገል ወደኋላ የማይሉ ሰዎች እዚህና እዝያ መኖራቸውም መታወቅ አለበት፡፡ አገር የሚመራበት ፖሊሲ፣ በወረቀት ደረጃ ቢቀየር እንኳ ፣በተቋማቱ ውሥጥ ያሉ በወያኔ የአፓርታይድ ርዕዮት የተጠመቁ ፣በንስሃ ጸበል ተረጭተው በእውነት ያልተቀየሩም ሞልተዋል፡፡ … እነዜህ ልበ ደንዳኖችና ህሊና ቢሶች ፣ ከወያኔ ውድቀት ያልተማሩ በመሆናቸው ታሪክን በመድገም መፀፀታቸው እነደማይቀር ከወዲሁ ይወቁት፡፡
ወያኔ፣ ትላንትና ራሷ በሰፈረቸው መስፈርያ ተሰፍሮላት ከሥልጣን ከመወገዷ በፊት ፣ በኢትዮጵያ ዜጎች ትብብርና ይሁንታ በግንቦት 20 /1983 ዓ/ም ሚኒሊክ ቤተመንግሥት መግበቷንም ያስታውሱ ። ህዝብ በዝመታ ውሥጥ ይሁንታ ባይሰጣት ኖሮ አዲስ አበባ የወያኔ መቀበሪያዋ ይሆን እንደነበር ሳንዘነጋ !
ወያኔ፣የህዝቡን ዝመታ እና ለአሥገንጣይነቷ ያለውን ንቀት እንደፍራቻ በመቁጠር እግሯ የሚኒሊክን ቤተመንግሥት ከረገጠበት አንሥቶ የከፋፍለህ ግዛ ርእዮቱን ማራመድ ጀመረች።
ይህ የከፋፍለህ ግዛ ርእዮት ነው፣ ዛሬም ለአገራችን ፖለቲካ ያለመረጋጋት ሰበብ የሆነው ። ወያኔ ትላንት ያልገባው ና ዛሬ ደግሞ ይሄ የለውጥ መሪ መንግሥት ገብቶት ትኩረት ያለስጠው አንድ ቁምነገር አለ፡፡
ወያኔ ፣አዲስ አበባ ሥትገባ ህዝብ ይሁንታውን የሰጣት ወንድም ወንድሙን የሚገድልበት የእርሥ ፣ በእርሥ ጦርነት አንገሽግሾት፣ “ጦርነት ይበቃል !”።በማለት እንደሆነ አልገባትም ነበር ። ሥለ አገሩ ዳር ድንበር ልጁን በመገበሩ ፣ ኢትዮጵያዊው ኩራት እንጂ ፀፀት እንደማይሰማውም ፈፅሞ አልተገነዘበችም ነበር ። ወያኔ በመላው ዜጎች ትብብር ፣ በታላቋ አሜሪካ አንቀልባ ታዝላ ፣ በሚኒሊክ ቤተ መንግሥት እንደገባች እርሷ ብትረሳ ታሪክ አይረሳም ። እንዲህ አልጋ ፣ በአልጋ በሆነ ፣ የጨርቅ መንገድ ለሥልጣን ብትበቃም ፣ ለዚህ ኩሩና በፈሪሃ እግዛብሔርነቱ ለታወቀ ህዝብ ያላትን ንቀት በማሳየቷ ፣ ፈጣሪ በቃሽ ስላላት ዜጎች በሙሉ፣ ” ወረጅ ከጫንቃዬ ” ብለው ሥለተነሱባት ሥልጣኗን አጥታለች ። ያውም ፣ በሰፈረችው መሥፈሪያ በፈጣሪያችን እግዚአብሔር ተሰፍሮላት፡፡
ወያኔ፣በቆፈረችው የግፍ ጉድጎድ የገባችው እንደደርግ የነቃና የተደራጀ ህዝብ የለም በማለት የይስሙላ የሽግግር መንግሥት አቋቁማ ምርጫ በሌለው ምርጫ፣ ህዝብ መረጠኝ ብላ በተከታታይ አምሥት ምርጫዎች የአሸናፊነቱን ዋንጫ በማንሣት ዓፄ በጉልበቱ ሥለሆነች ነው። ይህንን እውነት ” የለውጡ መሪ ነን ” የሚሉ ብዙዎቹ የሚገነዘቡት ቢሆንም በቅጡ ያስተዋሉት እና ነገ በእኔ ያላሉት አብይ ቁምነገር መሆኑን ልብ እንዲሉት ዛሬ ላይ ሆኜ በትህትና አስታውሳቸዋለሁ፡፡
ወያኔ እኮ ፣ የዛሬ ሦሥት ዓመት ፣በመጋቢት ወር መጨረሻ ሥልጣኑንን በህዝባዊ አመፅ እሥከተነጠቀች ግዜ ድረሥ ” የከፋፍለህ ግዛን ” ርእዮት በግልፅ የምታራምድ እጆ በንፁሐን ደም የተጨማለቀ ግፈኛ ገዢ ነበረች ። ተቋማቷም የጭካኔ እና የግፍ ተግባሯን ጨምሮ ፣ ምዝበራን ፣ ዘረፋናን መንግስታዊ ሌብነትን አራማጀች ና ህጋዊ ከለላ ሰጪዎች ነበሩ።
እነዚህን አሣፋሪ የሆኑ የግፍና የመከራ አሥቀጣይ ተቋማት ፣ከጎሣና ቋንቋ አራማጅ የአፓርታይድ ሥርዓት ለማላቀቅ በመጋቢት 24/ ቀን 2010 ዓ/ም ወደ ሥልጣን የመጣው የህዝባዊ አመፅ ትሩፋት የሆነው አብይ መራሹ መንግሥት ቃል ገብቶ ነበር ። ይሁን እንጂ፣ የአገሪቱን ህመም በቅጡ መርምሮ ትክክለኛውን ምክንያት በመረዳት፣ ለማከም ለ3 ዓመት ያለ እረፍት ቢሰራም ፣ወያኔዎች ፣ተላላኪዎቻቸውና የጥቅም አጋሮቻቸው የምዕራብውያኑ ቱጃሮች እንዲሁም ” የአባይ አስቀያሚ የውሃ ፖለቲካ ” በየጊዜው በሚሰጡት አጀንዳ ብዛት በመዋከቡ ፤ ኢትዮጵያዊያንን በተገቢው መልኩ ሊያስደስት እና ይህንን የዘውግ ፖለቲካ በጣጥሶ በአሸናፊነት ለመውጣት አልቻለም፡፤ ይሁን እንጂ ዛሬም ትክክለኛውን ግዜ ፣ ሥፍራና ሁኔታን በማገናዘብ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ተግባርን በመፈጸም ዜጎችን ሁሉ በአድናቆት እንደሚያስጨበጭብ ፤ ባንዳዎችን ፣ ሥግብግቦችን እና ሌቦችን እንደሚያሳፍር ፣ ተስፋ አድረጋለሁ ፡፡