March 19, 2013
8 mins read

በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞውን በድል ጀመረ

ከአሰግድ ተስፋዬ

ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በአንደኛው ዙር ከማሊው ጆሊባ እግር ኳስ ክለብ ጋር ያደረገውን ጨዋታ በድል ተወጥቷል።
ትናንት በአዲስ አበባ ስቴዲየም ሁለቱ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቱን የማሸነፊያ ግቦች በመጀመሪያውና በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠሩት አስር ቁጥሩ ዮናታን ብርሃነና በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አስራ አምስት ቁጥሩ ፍጹም ገብረማርያም ናቸው።
በጨዋታው የአምናው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ሻምፒዮና የዋንጫ ተፋላሚ የነበረው የማሊው ጆሊባ እግር ኳስ ክለብ ጥሩ ቢጫወትም ከመሸነፍ አልዳነም። ክለቡ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ከባለሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሽሎ የተጫወተ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊስ ድክመቶቹን አስተካክሎ በመግባት ጥሩ ሊንቀሳቀስ ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ኳስና መረብ ያገናኘው ጨዋታው እንደተጀመረ በስድስተኛው ደቂቃ ነበር። ለቅዱስ ጊዮርጊስ አስራ አንድ ቁጥር ለብሶ በቋሚ አሰላለፍ የገባው ኡመድ ኡኩሪ ከመሀል ሜዳ ኳስ እየገፋ በመምጣት ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ለአዳነ አቀብሎት አዳነ የሞከራትና የግቡ አግዳሚ የመለሰበትን ኳስ ዮናታን ብርሃነ መልሶ አክርሮ በመምታት ግብ ሊያስቆጥር ችሏል።
ከግቧ በኋላ ማሊን ወክሎ በሻምፒዮናው በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ጆሊባ በተጋጣሚው ላይ የበላይነት ወስዶ ተጫውቷል። ክለቡ ያገኘውን የጨዋታ የበላይነት ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል። ከሙከራዎቹ መካከል ተጠቃሹ 14 ቁጥሩ 19ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ አስደንጋጭ ነበረች።
በእዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቀኝ መስመር ተመላላሹ አሉላ ግርማ በግሩም ሁኔታ ተከላካዩን አልፎ ወደግብ ሞክሮ ወደውጪ የወጣችበት ኳስ በስቴዲየም የተገኘውን ተመልካች ያስቆጨች ነበረች።
የመጀመሪያው አጋማሽ በማሊው ጆሊባ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወስድም በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለባዶ መሪነት እረፍት ወጥተዋል።
በእረፍት ሰዓት የጣለው ከባድ ዝናብ « አንድ ለእናቱ » የሆነው ስቴዲየም ለጨዋታ ምቹ እንዳይሆን አድርጎታል። ሜዳው ቢጨቀይም የታክቲክ ለውጥ አድርገው የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተጋጣሚያቸው ላይ ፍጹም የበላይነት መውሰድ አልተሳናቸወም። ቅዱስ ጊዮርጊሶች የጨዋታ የበላይነት ቢወስዱም አስራ አምስት ቁጥሩ ፍጹም ገብረማርያም ተቀይሮ እስኪገባ ድረስ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ቆይተዋል።
ከሙገር ሲሚንቶ እግር ኳስ ክለብ በ2005ዓ.ም ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን የተቀላቀለው ፍጹም ገብረማርያም በቀኝ ክንፍ ከሽመልስ በቀለ የተሻገረችለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎ ክለቡ ሁለት ለባዶ እንዲመራና የሜዳ ተጠቃሚነቱን እንዲያስጠብቅ አስችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው አጋማሽ የነበረውን የጨዋታ የበላይነት በሚገባ መጠቀም ቢችል ተጨማሪ ግቦችን ለማከል ሰፊ ዕድል የነበረው ቢሆንም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ጀርመናዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ከለብ ዋና አሰልጣኝ ማይክል ክሩገር በሰጡት አስተያየት ፤ጨዋታው ከባድ እንደነበር ተናግረዋል። ጨዋታው ከባድ ቢሆንም ክለባቸው ሁለት ለባዶ አሸንፎ አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ማግኘት በመቻሉ ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል። የማሊው ክለብ በአፍሪካ ውድድሮች መድረክ ከፍተኛ ስምና ዝና ያለው እንደሆነ ጠቁመው፤ተጫዋቾቻቸው ድል በማስመዝገባቸው ደስታቸው ከፍተኛ እንደሆነ አብራርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ዝናብ ከጣለ በኋላ ሁሉም ነገር ለተጫዋቾቻቸው ከባድ እንደነበር የተናገሩት አሰልጣኙ፤ ቡድናቸው የሜዳውን ምቹ አለመሆን ተቋቁሞ ውጤት ይዞ ጥሩ ብቃት ማሳየቱን ተናግረዋል። በመልሱ በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ በሚያደርጉት ጨዋታ ከተጨዋቾቻቸው ተመሳሳይ ተነሳሽነትና የማሸነፍ ወኔ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ በመልሶ ማጥቃት ዘዴ ሊጫወቱ እንደሚችሉም ፍንጭ ሰጥተዋል።
ጆሊባ እግር ኳስ ክለብ ላይ ግብ ማስቆጠር በጣም አስቸጋሪ ነው ያሉት አሰልጣኙ፤ ተጫዋቾቻቸው ሁለት ግቦች ማስቆጠራቸውና ሳይቆጠርባቸው መውጣት መቻላቸው ለማሊው ክለብ የመልሱ ጨዋታ ከባድ ሊያደርግበት እንደሚችል ተናግረዋል።
የማሊና የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተለያየ ደረጃ የሚገኝ እንደሆነ ያስታወሱት አሰልጣኝ ክሩገር፣ክለባቸው አገሩን ወክሎ ያደረገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ደረጃ እንደሚያመለክት አብራርተዋል። በጨዋታው ሁሉም ተጫዋቾቻቸው እንደ ቡድን ጥሩ መንቀሳቀሳቸ ውንም አሰልጣኙ ገልጸዋል።
የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ ከሁለት ሳምንት በኋላ በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

Latest from Blog

እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ። የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ የሐዘን መግለጫ ታጋይ ይሰዋል ትግል ይቀጥላል !

January 22, 2025
Go toTop