ወቅታዊ መልዕክት ለለውጥ ኃይሉ  (ሰው ዘ ናዝሬት)

የዓፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት ነው።ቴዎድሮስ በመቅደላ  ሚያዚያ 6 / 1860  ዓ/ም  ሹጉጡን ጠጥቶ፣ ” መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ።  ” ተብሎ ለጀግና አሟሟቱ መታሰቢያ ዘመን ተሻጋሪ ግጥም ሳይገጠምለት በፊት ነበር መንግሥቱ ክፉኛ ተገዝግዞ በቅርቡ ባሉት የጦር ሰራዊት ብቻ ተደግፎ ቆሞ የነበረው…።
የመይሣው ካሣን፣ የአንድነት፣የብልፅግና እና ኢትዮጵያን ኃያል የማድረግ ህልም ለማጨናገፍ ሺ  የሥልጣን ጥመኛ ጋረዶችና ጥቂት የመሰሪ ፕሮፖጋንዳ ፋብሪኪ” አክሊሉዎች”  ወዳጅ መሥለው በሥተጀርባው እና በፊትለፊት በመውጋት የመንግሥትነት አቅሙን አሣጥተውት ነበር።
   ዓፄ ቴዎድሮስ ፣   ከመቅደላ በዓለም ከተደነቀበት የጀግንነት ሞቱ  ጥቂት ዓመት አሥቀድሞ   የተለያየ  የጥቅም  አጀንዳ ካላቸው ግለሰቦች ካደራጇቸው  ቡድኖች ጋር በመፋለም ጦሩ ተዳክሞ ነበር ።በሰው ኃይል ፣በትጥቅና ሥንቅም የተመናመነ ኃይል ነበር የነበረው።እናም ይህ ድንቅ ህልሙ በመሠሪዎች፣በሥልጣን ጥመኞችና በኢትዮጵያውያን አንድነት ሥጋት ውስጥ በሚገቡ የውጪ ሥግብግቦች፣ የተቀናጀ ፣ተንኳል፣ደባ እና ግልፅ ጥቃት የመጨረሻ የመከላከያ ምሽጉን መቅደላ  ላይ አደረገ። በመጨረሻም የገዛ ሹጉጡን ምላጭ ሥቦ ጥይቱን ጠጥቶ የኢትዮጵያ ህዝብ  ለዘላለም የሚኮራበትን የጀግና ሞት ሞተ።
  የሞቱ ሤራ ትርክት እንዲህ ነበር።
   ዓፄ ቴዎድሮሥ፣በወጣትነታቸው  በጀግንነታቸው እየታወቁ በመምጣታቸው   የራሥ አሊን ልጅ ተዋበች ዓሊን  በማግባት በደጃዝማች ማዕረግ ቋራን እንዲያሥተዳድሩ ከመደረጋቸው በፊት ። “ካሣ ኃይለጊዮርጊስ ፣ አክሊሉና ጋረድ ጓደኛሞች ነበሩ ።ይለናል ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ‘ በቴዎድሮስ እንባ ” መፅሐፉ።
    እንደእነ  አክሊሉና ጋረድ ዓይነት፣ ለአፄው ቅርበት ያላቸው  በሥልጣን ጥም እና በግል በደል ባረገዙት ቂም ያበዱ  ፣  ግለሰቦች፣የዓፄ ቴዎድሮስን ህልም ለማጨለም  ዓይነተኛ አሥተዋፆ እንዳደረጉም በመፀሐፉ ይተርካል።(በብሥለት ከፃፈው “የታንጉት ምሥጢር” መፅሐፉ በፊት  ይህ መፅሐፍ በቀዳማዊ ንጉሰ ነገሥት ኃይለሥላሴ ዘመንበ 1958  የተፃፈ ታሪክ ቀመስ አጭር ልቦለድ ነው።)
አክሊሉ  ጋረድ የተባለ የባላባት ወገን ፣ ቴዎድሮስ ለተቀመጡበት ዙፋን እንደማያንስ ፣ የጋረድን ስብእና በማግዘፍ ፣  ጀግንነቱን በማወደሥ  ፣ የዘሩን ጥራት በመጥቀስ ፣  በዓፄ ቴዎድሮሥ ላይ  የመጀመሪያው ሸፋች የዐፄው ሹመኛ እንዲሆን አድርጎታል።
     አክሊሉ በወጣትነቱ እንደ  ካሣ ኃይለጊዮርጊሥ( ሆላ ዓፄ ቴዎድሮሥ) የአንድ መስፍን  ጠመንጃ አንጋች (በዘመኑ አጠራር ሎሌ ) ነበረ።
     አክሊሉ በገና ጫወታ ወቅት ፣ቴዎድሮስ የመታት ቁር ወይም ድቡልቡል  የገና መጫወቻ  የወይራ ኳሥ ፣ የዘር ፍሬዎቹን አፍርጣ ዘሩን እንዳይተካ አድርጋው ነበር።ይህንን ግን ለማንም አልተናገረም።
     ከአክሊሉ ጋር በልጅነት ጓደኛ የነበሩት    ልጅ ካሣ ኃይለጊዮርጊሥ  ታሪክ በፃፈው  የጀግንነት ተጋድሏቸው፣  የሸዋን ምንሊክ ሳይቀር ማርከው ፣ ጎንደር በፋሲል ቤተመንግሥት በአቡነ ሰላማ ንጉሠ ነገሥት  ዘኢትዮጵያ በመሰኘት ዐፄ ቴዎድሮስ ተሰኙ።
       አክሊሉ ፣ በቅናት አረረ። በቂም በታጀበ ቅናት  ተነሳሥቶ ፣ ያለእኔ ወንድ የለም ባዩን ጋረድን በኢዮጋዊ ችሎታው በንጉሱ ላይ እንዲሸፍት አደረገው። ልጅ ጋረደ የካሣ አብሮ አደግ  ነበር።ካሣ ንጉሥ ሲሆን በደጃዝማች ማዕረግ የወገራ ገዢ አድረጎ ሾሞትም ነበር። እርሱ አይመጥነኝም ብሎ ለመሸፈት አሴረ እንጂ።
        ዓፄ ቴውድሮስ ይህንን ሲሰሙ ፣ አዘኑ። ራሴነኝ ሄጄ እመቀጣው ብለው ጦር ሲያደራጁ ምሽታቸው ተዋበች ሞቱ።
    እስቲ ጠይቁልኝ ፣እርቃ ሳትሄድ
    እቴጌ ተዋበች ሚሥት ‘ናት ገረድ።
በማለት ከባድ ሃዘናቸውን ለሙሾ ተቀባዩ ለቀሥተኛ የገለፁት ያኔ ነው። እናት ፣ሚሥት ና ገረድ አጡ። እንደ እናት ማን ይሳሳላቸው ? እንደሚሥት ማን ደጋፊና መካሪ ይሁናቸው ?እንደገረድስ(ሁሉን አቀፍ የምግብ ባለሙያ) ማን ጣት የሚያሥቆረጥም ምግብ አዘጋጅቶ ይመግባቸው?
         ሃዘናቸውን ሳይጨርሱ ፣ በትካዜ ውስጥ ሆነው ፣መካሪ አጥተው ፣ ጋረድን ለመውጋት ከገብርዬ፣ከአለሜ ና “ከሊቀመኳሥ ቤል” (የኢትዮጵያዊነት ዜግነት ተሰጥቶት  ኢትዮጵያዊት አግብቶ፣  ኃይማኖቱን ኦርቶዶክስ አድርጎ የሚኖር በዐፄው “የሊቀመኮስ “ማዕረግ የተሰጠው እንጊሊዛዊ።) ጋራ ዘመቱ።
ከጋረድ ጦር ጋር ያደረጉት ፍልሚያ በእጅጉ ከባድ ነበር።ጋረድ ንጉሡን ለመግደል ተቃርቦ ነበር። ንጉሡ ላይ ከመተኮሱ በፊት ሊቀመኳሥ ቤል በሽጉጥ ከፈረሱ ላይ ጣለው።ቤልንም የጋረድ ወንድም በጦር ወግቶ ገደለው።የጋረድ ወድምንም ዓፄ ቴዎድሮሥ በሽጉጣቸው ቀልበው፣ ከፈረሱ ላይ ተፈናጥሮ ዲንጋይ ላይ እንዲከሰከሥ አደረጉት።
       በሊቀመኳሡ መሞት የተበሳጩት ንጉሥ አንድም ሰው እንዳያመልጥ ና ምህረትም እንዳይደረግለት ጦራቸውን አዘዙ። ….
      ከጦርነቱ በኋላ መሠሪው  አክሊሉ ፣ ገዳም ገባ። ከእፎይታ  በኋላ በአንድ ደብር ላይ ፣ አንካሴውን ይዞ፣ሰንሰለት በወገቡ ታጥቆ፣ ባህታዊ በመሆን በንግሥ በዓለ ተገኘ።”በዓፄው ሰበብ ፣ ምእመናን በቂ ኃይማኖታዊ ሥርአት እንዳይፈፅሙ ተደርጓል። በአንድ ደብር  ከአምስት በላይ ካህን አያሥፈልግም ፣ በማለት ንጉሡ በኃይማኖታችን ጣልቃ ገብተዋል።  እንግዲህ ልጆቻችሁን ማን ያሥተምር ? ፍትሃት ማን ይፍታ ? ማንሥ ሥለ ኃይማኖት ያሥተምር ? ንጉሡ ፀረ ኃይማኖት ናቸው።ወዘተ።”ብሎም ሰበከ።
    በዚህ መሠሪ ቅሥቀሳ የጎንደር ህዝብ በዓፄው ላይ ሸፈተ።ዓፄ ቴውድሮስም እጅግ ተናደዱ።ምህረተ ቢሥና ጨካኝ እርምጃ በአማፅያኑ ላይ ወሰዱ። የጎንደር ከተማ ቤቶች ተቃጠሉ።ዘግናኝ እልቂትም ተፈጠረ።ዓፄውም በሁኔታው አዘኑ ለዚህ ከሆነ ፈጣሪ የፈጠራቸው፣ባይፈጥራቸው እንደሚሻል በቁጭት ለፈጣሪ ተናገሩ።ከዛ በኋላ ብዙም አልሰነበቱም።በወራሪው በእንግሊዝ ጦር አሥገዳጅነት፣መቅደላ አፋፍ ላይ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሞቱ።
     መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
     የሴቱን አላውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ።
     ገደል እንዳይሉ ፣ ሞተው አገኞቸው
     ማራክን እንዳይሉ ፣ ሰው የለ በእጃቸው
     “ተሸነፍን! አሉ  ሲገቡ አገራቸው።”
(ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው?)
      ከላይ የፃፍኩትን ሃሳብ ያገኘውት፣ በኢትዮጵያ ሥነ- ፅሑፍ ታሪክ ውሥጥ ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጠው ጋዜጠኛ ና ደራሲ   ብርሃኑ ዘሪሁን ፣ “የቴዎድሮስ እንባ” ከተሰኘ አጭር ልቦለድ ነው። በነገራችን ላይ ብርሃኑ ዘሪሁን ደጎሥ ያሉ በኩራዝ ማተሚያ ቤት የታተሙ ሁለት የአጭር ልቦለድ ሥብስብ ወይም መድብሎች አሉት ። “መድብል አንድ እና ሁለት” ተብለው የታተሙ። ወጣቶች ፈልገው ያነቧቸው  ዘንድ እጋብዛቸዋለሁ።(በበኩሌ ከታሪክ የተገነዘብኳቸውን እና ከብርሃኑ ዘሪሁን ቀደምት ሥራ “መድበል አንድ” ያነበብኩትን አካፋያችኋለሁ።)
  እርግጥ ነው፣ የዓፄ ቴዎድሮስ   ኢትዮጵያን ታላቅ የማድረግ ጥረት፣በወቅቱ በነበረው   ህዝብ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛነት እና ከግል ጥቅማቸው ውጪ የህዝብ ጥቅም ጉዳያቸው ባልሆነ የዘመኑ   መሣፍንቶች ና ባለሥልጣናት ሥግብግብነት ከሽፎል።እነዚህ ባለሥልጣናት ሥልጣን የጥቅም ማግኛ መሣሪያ ብቻ ነው።”ብለው የሚያምኑ እና ” ሹመት ለመብለት እንጂ ለማብላት እንዳልተፈጠረ …” አበክረው የሚሰብኩ ነበሩ።  የሀገርና የህዝብን ታላቅ መሆን ሣይሆን የራሳቸውን እና የዘመድ አዝማዶቻቸውን ጥቅም  በሥልጣን ሥም ለማሥጠበቅና ለማሥከበር የተሰለፉ ነበሩና የታላቁ በለራእይ መሪ ህልምን አጨናግፈዋል።
ዛሬም በሀገራችን   በታሪክ አጋጣሚ የሀገር መሪነትን   የተረከበውን  የሀገራችንን መሪ የአብይ አህመድን(ዶ/ር) “የተነሣ ተራመድ፣ክንድህን አበርታ  ፣ለሀገር ብልፅግና ለወገን መከታ። …” ወይም “የመደመር ፍልሥፍና  “(ክንድን ለማበርታትም ሆነ በብርታት ወደ ብልፅግና  ግብ ለመራመድ መደመር በእጅጉ አሥፈላጊ ነውና!)  እንደ መይሣው ካሣ ህልም  እንዳይጨናገፍ ፣ የመደመር ፀር የሆነው ከፋፋዩ፣ የቋንቋ አደረጃጀት እና አሥተዳደር መፍረሥ ይኖርበታል።
   ይህንን ለመተግበር ደግሞ፣ ከትግራይ እሥከ ቤንሻንጉል፣ከሞያሌ እሥከ መተማ፤ ከአሦሣ እሥከ ኦጋዴን፣ ማንኛውም ዜጋ ተዞዙሮ መሥራት ብቻ ሳይሆን፣መኖር፣ቤተሰብ ማፍራት በምርጫ መወዳደር ፣መምረጥ እና መመረጥ የሚያሥችል ሥርአትን የሚያነብር ፖርቲ ሥልጣን እንዲይዝ ማድረግ  ይጠበቅበታል።ለዚህ ሰው፣ሰው ለሚሸት ፖለቲካ መሥዋትነት የሚከፍል ወጣት፣ጎልማሳ፣ሽማግሌና ወርቅ የሆኑ እናቶች ኢትዮጵያ አላት።
     በቅርቡ  በአዳማና በደብረዘይት ለእውነት  መሥዋት በመክፈል ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ እንደዛፍ ከመሬት እንዳልበቀለና ሁሉም  ከተለያየ ቦታ ሰርቶ ለመኖር ወደ የከተሞች እንደመጣ ያሥመሰከሩት እነዚህ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። ዘላለማዊ ክብር ለእነዚህ ውድ ለሆኑ  ለእውነተኛ ፍትህ፣ዴምክራሲና ብልፅግና ለከፈሉ  ሰማዕታት ይሁን።…ታሪክ ለዘላለም ሲያሥታውሳችሁ ይኖራል።
   በነገራችን ላይ፣  ዛሬም ጥቂት  የጊዜው ባለሥልጣናት ፣ እሥርቤቱን እና ጠመንጃውን የሚቆጣጠሩ የፖርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሥልጣናቸው እና እሱን ተከትሎ ላገኙት ና እያገኙ ላሉት  የሌብነት ጥቅም ሲሉ   የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት የሰውነት መንፈስ በመገዳደር እኩይ ተግባር  እየፈፀሙ እንዳሉ እየተወራ ነውና አብይ  “ነግ በእኔ ” ብለህ ድርጊቱን አሥቁም። የአመፁ ቋሥቋሽ ጫፉ ሳይነካ ፣የሞቱት ሰማዕታት ደም ሳይደርቅ እንዲህ አይነት ህግን ተገን ያደረገ ዘራዊ ጥቃት ካለ መታረም የሚችለው በአንተና በሃቀኛ የለውጥ ኃይል በሆኑት ነገ ሟች እንደሆኑ አሳምረው በተገነዘቡ የትግል አጋሮችህ ብቻ እንደሆነ አምናለሁ።
     በመላው ሀገሪቱ ያሉ ፣ከመብል ያልዘለለ ራእይ ያላቸው ፣ሥልጣንን በችሎታ ሳይሆን  በቋንቋ ብቻ ያገኟት  ፣በዘር፣በኃይማኖት  ንቃተ ህሊናው ዝቅተኛ የሆነውን ዜጋ በማጋጨት ሥልጣናቸውን ማራዘምና ያልተቋረጠ  ትረፍ ማግኘት  እንደሚችሉ አሥቀድመው በማሥላት ፣ በቋንቋ ህዝቡን በማደራጀት፣ መና ከሰማይ ይወርድልሃል እያሉ ፣ሰማይ፣ሰማይ እያየ አንጋጦ እንዲራመድ የሚያደርጉትን ግን ታሪክ ይፋረዳቸዋል።
     በግልፅ አማርኛ ፣ በቋንቋው እኩይ ፕሮፖጋንዳን በመንዛት፣”ትላንት እነገሌ የአንተን ቋንቋ ተናገሪ በጭካኔ ገድለዋል ።አሰቃይተዋል። ዘርፈዋል።ወዘተ። በማለትም ፣የድርጊቱ ተካፋይ ያልነበረውን፣በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያልነበረውን ከእነሱ የተለዩ ቋንቋ የሚናገረውን በጠላትነት እንዲተያይ አድርገዋል።   መንጋ ፈጥረዋል። የሰው ሰብዓዊ ክብሩ ሳይሆን ቋንቋው ብቻ ገዝፎ እንዲታይ በማድረግ ፣ ከእሱ ቋንቋ ውጪ የሚናገረውን ጎረቤቱን በጠላትነት በመፈረጅ እና ሀገር አልባ እንደሆነ እንዲቆጥር  እና የምናገባኝነት ሥሜት እንዲገዝፍበት በማድረግ  በብጥብጥ እና በመግደል ሺ ዓመት መንገሥ እንደሚቻል የሚያሥቡ ከንቱዎች ሆነዋልና የታሪክ አተላዎች ናቸው።
  የእነዚህን የታሪክ አተላዎችና  የሴጣን ወታደሮች እኩይ ሃሳብ ለመታገል ብሎም ለማሸነፍ  ፣ የልጅ ልጆቻችንን የነገ ውድቀት በመገንዘብ ፣ “በአድር ባይነት ፣እየበላን ለመኖር ሥንል፣ እየዋሸን፣እያሥመሰልን እንዲሁም ጭራችንን እየቆላን፣ መኖራችን  ይብቃ !! “ብለን ምድር ላይ ያለውን እውነት ፊት ለፊት ተጋፍጠን ለታሪክ እና ለሰው ሁሉ ክብር ሥንል መሰዋት ለመሆን መዘጋጀት ይኖርብናል።
     በመሠሪዎች የጅል ሃሳብ በመመራት፣ እኔ ላይ ካልደረሱ  ምን ያገባኛል በማለት   ልንሞትለት የሚገባንን ከሙታን በላይ የሚያደርገንን እውነት መሸሽ የለብንም።ሜዳ እየተቃጠለ የሚሥቅ ተራራ ካለ ያ ተራራ ሞኝ ነው።ባቅራቢያዋ ያለ ቤት እየተቃጠለም እርሷ ኩሬ ውሥጥ ከባሏ ጋር በጫጉሏ ሽርሽር ላይ በተዝናኖት ላይ ያለች እንቁራሪት ላሃጫም ናት። መጨረሻዋ አሰቃቂ እንደሚሆን መገንዘብ የነበረባት እሳቱን እንዳየች ከመቅፅበት ነበር። በላሃጫምእነቷ   የሚነደው እሳት የጫጉላዋ ርችት ከመሰላት በባሊ ተጨልፋ ከነባሏ እሳት ውስጥ ሥትወረወር ያኔ ይገባታል።
      ማንም የማይከራከርበት እውነት ቋንቋ መግባብያ እንጂ የመጨቆኛ፣አድሎ ና ግፍን የመፈፀሚያ መሣሪያ ያለመሆኑን ነው።ይሁን እንጂ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አሥተዳደር በመላ ኢትዮጵያ መግባቢያ የሆነውን እና የተወካዮችም ሆነ የፌዴሬሽን ምክርቤት ውይይት ፣ የሚካሄደው በአማርኛ ቋንቋ ሆኖ ሣለ ፣ በመላው ኢትዮጵያ ከተሞች ፣ አማርኛ  ከሌሎች በአካባቢው ህዝብ  በብዛት ከሚነገረው ቋንቋ ጋር በአቻነት የሥራ ቋንቋ  መሆን ሲገባው ፣ ብዙሃኑን ወይም ድብልቅ ቋንቋ የሚናገረውን ፣ “የቋንቋ ተጨቋኝ ማድረግ ” የከፋፍለህ ግዛ ተግባር ነው።
     እንግሊዘኛ የታላቋ ብሪትን ወይም የተባበሩት ግዛቶች ፣ሀገር ቋንቋ ነው።ልብ በሉ ፣የኢንግሊዝ ቋንቋ ባዮቹ እኛ ነን።የነሱ ሀገር መጠሪያ  ግን (United kingdom ) ነው ።ወይም( Great Britain’s )
   በኢትዮጵያ ውስጥ ” አማርኛ”  የተባለ ቋንቋ መኖሩ እርግጥ ቢሆኑም ቋንቋውን የሚናገሩ ሁሉ አማራ አይደሉም።ትግርኛ ተናጋሪ ፣ኦሮምኛ ተናጋሪ፣ሱማሊኛ ተናጋሪ፣የደቡብ ብሔርና ብሔረሰብ ቋንቋዎችን ተናጋሪ ወዘተ አማርኛን በመናገሩ አማራ አይባልም። ይህንን ወደሌላው ቋንቋ ወስደን ብንመለከተውም እንደዛው ነው።(ከ ጃዋር እሥከ ፕሮፊሰር ህዘቄል ድረሥ ያሉ ፅንፈኛች ከአንድ መንዜ እና ጎንደሬ እኩል አማርኛን ይናገራሉ።እናም አማርኛ ቋንቋ ቋንቋቸው ነው።በትውልድ ኢትዮጵያዊ እሥከሆኑ ድረስ?)
    ሁሌም እንደምናገረው እኔም ሆንኩ አንተ፣አንቺም ሆንሽ እርሷ ፣ የፈለጋችሁትን ቋንቋ ብትናገሩ እናንተ ሰዎች እንጂ ቋንቋ አይደላችሁም።
    ለምን የመለአክት ቋንቋ አትናገሩም? የመለአክትም ሆነ የሴጣን ቋንቋ ብትናገሩ እናንተ  እንደማንኛውም ሰው ሰው የሚያደርገውን ተፈጥሯዊ ነገር እሥከፈፀማችሁ እና እሥከበላችሁና ደግሞም ወደሽንት ቤት እሥከሄዳችሁ ድረሥ፣ ሰው እንጂ፣ሰይጣን ወይም መልአክ መሆን አትችሉም።
     በአኗኗራችሁ ሂደት ውስጥ በየዕለቱ  የሚገለፅ የሴጣንና የመልአክት ባህሪ ና ድርጊትን ልትላበሱ ትችላላችሁ።ሆኖም ይህም አንፃራዊ ነው።
     ህዝብ በመሠሪ ቅስቀሳ፣አገራት በጥቅምና በኃይማኖት ሰበብ ተፋልመው ቢገዳደሉ የቱ ነው የጽድቅ ጦርነት?የቱሥ ነው ሤጣናዊ ጦርነት? እውነት ማለት ሰው ለራሱ እና ለሌሎች በእኩልነት ያለው ፍቅር ብቻ ነው።ሌላው ከእውነት በተፃራሪ የቆመ በራሥ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ የጥቅም ና በልጦ የመገኘት የሰው ጅልነትን የሚያረጋግጥ ከንቱ ተጋድሎ ነው።
      እና ከትላንት ጀምሮ እኛን በጅልነት እርስ በእርስ እያገዳደሉን ያሉት  ተንደላቀው የሚኖሩት በቋንቋችን የሚያወሩ ፣ቢበሉ የማይጠግቡ ህሊና ቢሶች ናቸው።
     እነዚህ ህሊና ቢሥ ሰዎች ገንዘብ እና ምላሥ አላቸው።ሥልጣን አላቸው።ከፋፍሎ ለመግዛት ለምዝበራ   የሚያመች ፣በጠመንጃ ማሥፈራርቾ የፀደቀ ፣  ህዝብ ያልተሥማማበት ህገመንግሥት አላቸው።
      ይህ ብቻ አይደለም በፖርቲ ሥም ያሰባሰቡት አብዛኛው አባላት ከራሥ በላይ ነፋሥ ባይ ሠግብግብና ሁሉን ለእርሱና ለጥቅም አጋሮቹ ብቻ አገበሥባሽ ነው።ህዝብ ደግሞ በላም አለኝ በሰማይ የሚነገድበት የቋንቋ እሥረኛ ነው።
   ዛሬ ህዝብ የላም አለኝ እሥረኛ መሆኑ ገብቶታል።የአዲሥ ሥርዓተ መንግሥት አዋላጁ ሥርዓት የለውጥ ትግልም እንዲደናቀፍ አይፈልግም።ይህንን የለውጥ አዋላጅ መንግሥት እና መከላከያ ሠራዊቱን ይደግፋል።በመላ ኢትዮጵያ ህግን የሚያሥከብሩ  ፣አገልግሎትን ያለጉቦ የሚሰጡ ፣ ሰብዓዊ መብት እንዳይጣሥ የሚያደርጉ ተቋማት በፅኑ መሠረት ላይ እንዲገነቡ የሚያደርግ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ  መንግሥት  ይፈጠራል ብሎም ያምናል።
      ዛሬ ለአንድ አምባገነን እና በእጅ አዙር ባካበተው ሀብት ሰበብ  በትዕቢት ለተወጠረ  ግለሰብ ጭራቸውን የሚቆሉ እና አሽከር የሚያቆሙ የክልል መንግሥት  ባለሥልጣናትን በማሥተዋል ቢበሳጭም ነገ ይህ እንደማይደገም ፣ ማንም ሰው ከህግ በላይ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ መንግሥት ኢትዮጵያ ይኖራታል ብሎ ያምናል።
     ግደይ በቋንቋዋ ሥም ሥልጣን ሥለያዘ  ብርክቲ ከጠላ ሻጭነት አልወጣችም።አብዲሣ ከንቲባ ሥለሆነ ኢፍቱ ከካቲካላ ኮማሪነት አልተላቀቀችም።እምሩ የክልል ፕሬዝደንት  ሥለሆነ ሙሉጎጃም  ከኮረፌ  ንግድ   ፈቀቅ አላለችም።ወዘተ። በቋንቋ  ሥም ግን ግለሰቧች ከብረዋል።ወደ ከበርቴነትም ተሸጋግረዋል። ይህንን ሃቅ የለውጥ ኃይሉ ይገነዘባል። ሲተውም የማይተውትን ሌቦች ለመቅጣትም  መከላከያ እና የለውጥ ኃይሉ በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ተጨማሪ ያንብቡ:  እልህ ያረገዘው - ያለወለደው። (ሥርጉተ ሥላሴ)

1 Comment

  1. Yes, people have the right to live in any part of the country so long as they are respecting the right of the people they live with. Insulting and dehumanizing the people they live with could cause catastrophic events on the lives of those coming from other areas and living in other parts of the country. This a good precaution for such people to respect the culture and every thing of the people they live with. Otherwise, it would be very much harmful to minority groups coming from other regions as a result of unwanted conflict that could be instigated by those wishing to return back to the older system of Ethiopian feudal system. So, the best way to prevent such conflict is to be peaceful with the people a person coming from another region.

Comments are closed.

Share