ብሔር፣ መንግሥትና ሕዝብ – የፖለቲካ ግብ ማሰለጫ ግንዛቤነታቸው

አንዱ ዓለም ተፈራ

እሁድ፣ ጥቅምት ፲ ፮ ቀን ፳ ፻ ፲ ፪ ቀን

ሀገራችን አሁን ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ፤ ሥር መነሻ አለው። ይህ ቀውስ ትክክለኛ መፍትሔ እንዲያገኝና የተጀመረው የለውጥ ሂደት ግቡን እንዲመታ፤ መሠረታዊ የሆኑ የኅብረተሰባችን ግንዛቤዎቻችን ሊለውጡና፤ በአመራሩም በኩል ተገቢ የፖለቲካ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባቸዋል። ያለው ሀቅ፤ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሲካሄድ የነበረው ዕልቂት፤ አሁንም በየቦታው ቀጥሎ መጧጧፉ ነው። ባለፈው ወቅት፤ ይህ ዕልቂት በመንግሥት በኩል በተቀናበረ መንገድ የተከናወነ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ በየቦታው በተናጠል፤ በተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተካሄደ ነው። በርግጥ ሁላችንም እንደምንረዳው፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” ባዮቹ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች፤ ያገኙትን ያጎበደደላቸውን ሁሉ በመጠቀም፤ ሰላም በሀገሪቱ እንዳይኖር የሚያደርጉት ጥረት ነው! ማለት ይቻላል። አድር ባዮችም ይሄን አጋጣሚ ለመጠቀምና በትንሿም በትልቁም የሥልጣን ወንበር ላይ ጉብ ለማለት ተነስተው ነው! ማለትም ይቻላል። ይህ ሁሉ፤ ከመፍትሔነቱ አንጻር፤ መገለጫዎቹ ላይ ማተኮር እንጂ፤ ዋና የሆነውን ጉዳይ መንካት አይደለም። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትም ሆነ አሁን በለውጡ ሂደት ወቅት እየተገበረ ያለው ዕልቂት፤ በድምሩ ሁሉም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች የግብ ሂደት አካል ነው። አሁንም ይህ ቡድን በቀደደልን ፈሰስ እየተጓዝን፤ ይህ ቡድን ካቀደው ግብ ውጪ ሌላ ውጤት መጠበቅ፤ ሳያርሱና ሳይዘሩ ለማጨድ መዘጋጀት ነው። እናም የነበረውን መርምረን፣ አጀማመሩን፣ አተገባበሩንና ውጤቱን አጥንተን፤ እንዲከተል የምንፈልገውን በግልጥ አውጥተን፤ ምንነቱን ተረድተን፣ አፈጻጸሙን በትክክል አስቀምጠንና ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ከወዲሁ አውቀን፤ ወደፊት ልንሄድ ይገባል።

አንድ የታሪክ ወቅት፤ በጊዜ ገደብ ክልሉ፤ የራሱ የሆኑ ግንዛቤ፣ አመለካከት፣ የክንውኖች መግለጫ ቃላትና የራሱ የሆኑ እውነታዎች አሉት። የኒህን ዘላቂነት፤ እኒሁ ከአጠቃላዩ ጊዜ ከማይሽራቸው ሁሉን አቀፍ እውነታዎች ጋር ያላቸው ዝምድና ይወስነዋል። ጊዜ የማይሽራቸው እውነታዎችና ግንዛቤዎች ከምንላቸው መካከል፤ “በደል ከልኩ ሲያልፍና ተበዳዩ በቃኝ ሲል፤ አመጽ መከተሉ!” አንዱ ነው። “ሕዝብ ፍትኅንና ሰላምን ካገኘ፤ ሀገሩን ማበልጠጉና መንግሥቱን የኔ ብሎ መውደዱ!” ሌላው ነው። “ጦርነቶች፤ ትክክለኛም ሆኑ ትክክለኛ ያልሆኑ ጦርነቶች፤ ግባቸው ይለያይ እንጂ፤ ጥፋት ማስከተላቸው አሌ አለመባሉ!” ሌላው ነው። እንግዲህ እኒህን ቋሚና ጊዜ የማይሽራቸው ስል፤ “ባሪያን ለመግዛት ገበያ መውጣት!” “ሴትን ከቤት አትውጪ ብሎ ማገት!” “ጉልበት አለኝ ብሎ የሰውን ንብረት መቀማት!” ደግሞ፤ በጊዜያቸው ተቀባይነት የነበራቸው፤ ከጊዜያቸው ውጪ ደግሞ ፀያፍ ተግባር ተብለው የሚነወሩ ናቸው። ከቃላትም እንዲሁ! ሰው፣ ሰላም፣ ጦርነት፣ ግብ፣ ሂደት፣ ግንዛቤ . . .፤ የምንላቸው ቋሚነት ያላቸው ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሕዝብ፣ መንግሥት፣ ብሄር የሚሉትና ቋሚነት ካላቸው ላይ አንጻራዊ የሚል ቃል የሚጨመርባቸው ሁሉ፤ ተለዋጭ በመሆናቸው፤ ጊዜያዊ ናቸው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወዴት እየሄድን ነው! - አንዱ ዓለም ተፈራ

ብሔር፣ መንግሥትና ሕዝብ፤ የፖለቲካ ግብን ማሰለጫ ግንዛቤዎች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ስል፤ በመንግሥታት መካከል ስለሚኖረው ግንኙነትና ዝምድና የተወሰነ ግንዛቤ አለኝ። አንድነት እንደሌላቸው እረዳለሁ። በእንግሊዝኛ፤ Nations (ኔሽንስ) የሚለውን ነው፤ መንግሥታት የሚለው የሚወክለው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ይሄንኑ Nations (ኔሽንስ) የሚል የእንግሊዝኛ ቃል፤ ብሔር ብለን እንተረጉመዋለን። በአሜሪካ፤ ከእንግሊዝም ይምጣ ከደቡብ አፍሪካ፤ ከሜክሲኮም ይምጣ ከሩስያ፤ የአሜሪካን ዜግነትን ካገኘ በኋላ፤ የአንድ የአሜሪካ መንግሥት፣ የአንድ የአሜሪካ ብሔር፣ የአንድ የአሜሪካ ሕዝብ አባል ነው። ሌላ መንግሥት የለውም። ሌላ ብሔር የለውም። ሌላ ሕዝብ የለውም። የትውልድ ማንነቱንና በሰውነቱ ቧንቧዎች ውስጥ የሚፈሰውን ደም መነሻ በሚመለከት፤ ከግለሰቡ በስተቀር ማንም የሚያገባው የለም። የፈለገው ሊሆን ወይንም ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል። ያን ወሳኙ ራሱ፤ ግለሰቡ ነው። ከእንግሊዝ ሀገር መጠው ኢትዮጵያዊ የሆኑ አውቃለሁ። ከአሜሪካም እንዲሁ። ብዙ ከጃማይካ የመጡና ኢትዮጵያዊ የሆኑም አውቃለሁ።በሁኗ ኢትዮጵያ ያለው ግንዛቤ ከዚህ የተለየ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፤ ይሄን መዳሰስ ነው።

ኢትዮጵያዊነት የሀገር አለኝታ ነው። ኢትዮጵያዊ መሆን ነው። በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ክንዋኔ ውስጥ፤ ሙሉ አባል መሆን ነው። ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር ውስጥ፤ በየትኛውም ቦታና ጊዜ፤ ባለቤት ሆኖ መገኘት ነው። ከዚያ ውጪ፤ የተለየ ከፊል ኢትዮጵያዊነት የለም። በኢትዮጵያ ውስጥ፤ አንድ አካባቢ ኢትዮጵያዊ ሌላው አካባቢ ደግሞ ባዕድ የመሆን አግባብነት የለም። ታዲያ አሁን ያለው የክልልና የኢትዮጵያዊነት የተሸዋረረ ግንዛቤ መነሻው የትና ምንድን ነው?

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች፤ ፀረ-ኢትዮጵያዊነትን በኢትዮጵያዊነት ስም ለማራመድ፤ የተቀነባበረ ሂደት ዘርግተዋል። በርግጥ ጠንቋይነት ስለሌለብኝ፤ ሲነሱ ይሄን አስበው ነበር! ብሎ ማለቱ ይቸግረኛል። የማውቀው ነገር ቢኖር፤ የሀገሪቱን ሥልጣን ይዘው፤ እንደ ሀገር ከማሰብና የያዙትን ሥልጣን ሀገሪቱን በሙሉ በማስተዳደር ከማዋል ይልቅ፤ ለራሳቸው መጥፊያ የሚሆነውን የከፋፍለህ ግዛ መርኅ ሙጥኝ ብለው አራምደዋል። ለምን ይሄ ሆነ ለሚለው መልስ እንዳልሠጥ፤ አሁንም ደግሜ ጥንቆላ አላውቅም እላለሁ። ሙሉ የሀገሪቱን ሥልጣን፣ ሀብት፣ መሣሪያ፣ መንግሥታዊ መዋቅር፣ በጃቸው ይዘው፤ በትግሬነታቸው መግዛት መቀጠሉን ገፉበት። ይህ ሊሰነብት የሚችለው ደግሞ፤ “እኛ ትግሬዎች!”ና “እነሱ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን!” ብለው በገነቡት አጥር ውስጥ፤ የ“እኛ!”ነታቸው መጠንከርና፤ የ“እነሱ!”ነታችን የሚሉን መዳከም እስከቀጠለ ድረስ ብቻ ነው። ስለዚህ፤ “እኛ ትግሬዎች!” የሚሉትንና “እነሱ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን!” የሚሉንን መለያያና መቀጠያ ይሆን ዘንድ፤ የወቅቱን እውነታዎች፣ ግንዛቤዎች፣ አመለካከት፣ የክንውኖችን መግለጫ ቃላት በሚመቻቸው መንገድ መለወጥ ፈለጉ። በዚህ ሂደት፤ ሕዝብ፣ ብሔር፣ መንግሥት የሚሉት ቃላት ትርጉማቸው ተቀየረ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በበዓል የረሃብ አድማ!! - ርዕዮት ምን ልትነግረን ነው?

ቀደም ብዬ እንዳሰፈርኩት፤ የተባበሩት መንግሥታት የሚለውን ሁላችን እናውቀዋለን። ይህ ሲጠራ በአእምሯችን የሚመጣውን እናውቃለን። ወደው የተሰበሰቡ ሀገሮች፣ መንግሥታት ወይንም ብሔሮች እንደሆኑ እንረዳለን። በአብዛኞቹ መንግሥታት ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎች እንደሚነገሩ እናውቃለን። አልፎ ተርፎም መንግሥታቱ፤ ነዋሪዎቻቸው የተለያዩ ቋንቋዎችን እንዲናገሩላቸው፤ ከፍተኛ ውጪ እየመደቡ ትምህርቱን በየሀገራቸው ያስፋፋሉ። ስለዚህ፤ ቋንቋዎች ከመንግሥታትና ከማንነት ጋር ጣልቃ ገብነትም ሆነ ጠብ የላቸውም ማለት ነው። ይሄ እንዳለ ሆኖ፤ የትግሬዎቹ ነፃ አውጪ ግንባር አመራር፤ በመጠምዘዝ፤ በሀገራችን የተለያዩ ሕዝቦችና ብሔሮችን ፈጠረ። ይሄን ለማከናውን ደግሞ፤ የየብሔሮች መንግሥታትን ፈጠረ። ልታስታውሱት ይገባል፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አመራሩ ጌታቸው ረዳ፤ “ዐማራንም ሆነ ኦሮሞን የፈጠርነው እኛ ነን!” ማለቱን። በነገራችን ላይ፤ ይሄ እውነትነትም ስህተትም አለው። የፖለቲካ ዐማራና ኦሮሞ እነሱ ፈጥረዋል። በትውልድ ማንነት ግን፤ ዐማራዎችና ኦሮሞዎች ከነሱም መፈጠር ቀድመው የነበሩ ናቸው።

ታዲያ ይሄን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አመራር ክንውን ያሰለጠላቸው ምንድን ነው? በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የቆየው የገዥዎችና የተገዥዎች ግንኙነት፣ በሀገራችን ውስጥ ያለው ድህነት፣ የሀገራችን ለሥልጣኔ ክፍት አለመሆን ተደማምረው፤ ለውጥ የመፈለግ ስሜትን ወደ ላይ አጦዙት። በቦታው የመደማመጥ፣ ልዩነትን የመቀበል፣ በልዩነት አብሮ መሥራት፣ በአደባባይ የፖለቲካ ውይይቶችን የማድረግ ባህል አለመኖራቸው ደግሞ፤ የበሰለና የዳበረ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ አላመች አለ። እንግዲህ ጠቅለል ባለመልኩ፤ የዚህ ሁሉ ድምር፤ ለምንም ነገር የተመቸ የፖለቲካ አንቅስቃሴን ለማድረግ የተመቸ ሁኔታን ወለደ እላለሁ።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ እኩይ ተግባር፤ በተለይም አናሳ ክፍል፤ የብዙኀኑ አካል ሳይሆን በብቸኝነት ብዙሃኑን ለመምራት፤ የግድ ማድረግ ያለበትን ክንውን፤ መሰሪ በሆነ መንገድ ነው ማከናውን የምችለው። እናም ተቀባይነት ያለውን ሀቅ፤ መለወጡ አይቀሬ ሆነ። “እኛ ትግሬዎች!”ና “እነሱ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን!” የሚለው የሴራ ክፍፍል፤ እውነታነት አገኘ። ይሄን ከስድሳዎቹ የተማሪዎች ትግል ጋር ማቆራነቱ ለተንኮል ነው። ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ያን ለሌላ ጊዜ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የበረከትና አላሙዲ ልሳን (ከኢየሩሳሌም አረአያ)

ይህ ነው እንግዲህ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታትና አሁን ላለንበት የፖለቲካ ሀቅ መሠረቱ። በዚህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ቅድ እየተጓዝን፤ ይህ ቡድን ካስቀመጠው ግብ ውጪ ሊከተል የሚችል ውጤት የለም። አሁንም የደቡብ ክልል የተለያዩ የራስ ገዝ ብሔሮችን ይወልዳል። አይቀሬ ነው። በሂደቱ የብዙ ንፁሃን ሕይወት ይቀጠፋል። ብዙ ንብረት ያላግባብ ይወድማል። ነገ ተነገ ወዲያ ደግሞ፤ ሳሆም ሆነ ራያ፣ የየራሳቸው ብሔርነትን ቢጠይቁ፤ የትግራይ ክልል መከልከል ሊፈቀድለት አይገባም። የአዋሳ ከተማ፣ የሐረር ከተማ፣ የድሬዳዋ ከተማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ፣ ሌሎችም ትልልቅ ከተሞችና የንግድ ማዕከሎች፤ የመተላለቂያ ቦታዎች ከመሆን አይድኑም። በዚህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች በቀደዱልን ፈሰስ እየነጎድን፤ አሁን ካለው ሀቅ ሌላ ውጤት መጠበቅ፤ የየዋኅነት የዋኅነት ነው።

በአመለካከት ደረጃ፤ አንድም በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የተቀመጠውን የፖለቲካ ሀቅ ተቀብሎ በየክልሉ የመናቆር ተግባርን መቀበል ነው። አለያም ይሄ ትክክል አይደለም ብሎ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ነው። ከመካከል እግርን ማስቀመጫ ሌላ ቦታ የለም። መቆሚያ የሌለበት አጥር ነው ያለው። በተግባር አሁን ካለው ሀቅ ወደ የምንፈልገው ሀገራዊ አመለካከት የመሄዱ ጉዳይ፤ የአጭር ጊዜ ዕቅድ ነው። መነሻው ግን፤ በግልጥ የትኛው ነው ትክክለኛና መሆን ያለበት የሚለውን መለየቱ ነው። ይሄን ሳናደርግ፤ “የሽግግር ሁኔታ ላይ ነን!” እያልን ብቻ ብንከንፍ፤ አሁን እየተፈጸመ ያለውን ግድያና የንብረት ውድመት ልንቀይረው አንችልም። ምኞትና የግለሰቦች ቅንነት፤ ሀገርን ወደፊት መውሰድ አይችሉም። መሠረታዊ የሆነ ግንዛቤ፣ በዕቅድ የተቀመጠ መመሪያና የተዋቀረ ተግባሪ አካል የግድ በቦታው መቀመጥ አለበት። ኢትዮጵያ አንድ ሀገር ናት። በኢትዮጵያ አንድ መንግሥት ነው መኖር ያለበት። ኢትዮጵያ አንድ ብሔር ናት። የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው። የሌሎቻችሁን ሃሳብ ለማዳመጥና ትክክለኛውን መርጬ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።

Share