August 20, 2019
27 mins read

ናጫቃማ  – በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

አጭር ልብ ወለድ
    የናዝሬት ጫት ቃሚዎች ማህበርን ለመመስረት ከሁሉም ቀበሌዎች ፣ በአቃቃማቸው አግባብ የተመረጡ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ጫት ቃሚዎች ግር ብለው ወደ “በለጬ”አዳራሽ እየገቡ ነው።
   በአብረቅራቂ ወዛም ፊት- በደማቅ፣ፈገግታ -በልዩ አቅል ና ምድራዊ ባልሆነ ስሜት ተሞልተው ።ዐይኖቻቸውን እያጉረጠረጡ – እጆቻቸውን እንደክንፍ እያርገበገቡ –  ሰውነታቸውን እስክስታ እንደሚወርድ እያውረገረጉ- አንዳንዶችም ምድርን ለቀው -በሰማይ ለመብረር እንደሚፈልጉ ሁሉ፣ እጆቻቸውን በአየር ለይ እያርገበገቡ – በቄንጠኛ አረማመድ ፣ “ሽው ! እልም ! “እያሉ – ምድርን ለቀው – ወደሰማይ ለመብረር  ያኮበኮቡ መስለው –  ወደሰፊው “በለጬ” አዳረሽ በሐሴት ተሞልተው ፣ በጥድፊያ፣ሽው እልም እያሉ ወደማይሞላው አዳራሽ ሲገቡ ማየት ፣በእውነት አንድ አሥገራሚ ትዕንግርት እንደማየት ይቆጠራል።
     እኔም “ወሬ ቲቪን” ወክዬ ፣ወደ አዳራሹ   ሲገቡ ፣ ስብሰባውን በስፈራው ተገኝተው ለመዘገብ ጥሪ ከተደረገላቸው ጋዜጠኞች ጋር ሆኜ-  ሙያዬ የጣለብኝን ሐላፊነት ለመወጣት – መቅረፀ ምሥልና ድምፅ ይዤ – ይህንን ጉደኛ ትንግርት እና የምሥረታ ፕሮግራም  ሂደት ፣  ለታሪክ ቀርጬ ለማሥቀረት  ተፍ፣ተፍ እያልኩ ነው ።
   “የናጫቃማ“  መስራች ጉባኤ አባላቶች በሙሉ ወደ አዳራሹ ገብተው በተዘጋጀላቸው ወንበር ላይ በስማቸው ትይዩ እንደተቀመጡ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ጋዜጠኞች ወደ አዳራሹ ገብተን የተያዘልንን ስፍራ እንድንይዝ ተፈቀደልን፡፡
  በወንበሬ ቁጭ ብዬ ገና  ሳልደላደል፣ ምንነቱን ያለወቅሁት ጢስ በአራቱም ማዕዘን በትልልቅ የዕጠን ማጤሻ ሲንቦሎቦል አየሁ፡፡እናም ደነገጥኩ፡፡ ጢሱ የዕጣን ሽታ የለውም፡፡ይህ ጢስ በዕፀ ፋርስ የተቀላቀል እጣን ሳይሆን አየቀርም፤ ብዬ ጠረጠርኩና ‘መድሃኒዓለም አውጣኝ፡፡‘በማለት አማተብኩ፡ ና የአዳራሹን ጫፍ ና ጥግ መቃኘት ጀመርኩ።
   አምስት ሽህ አምስት መቶ ሰው የሚይዘው ” በለጬ አዳራሽ” ጉንጩ በጫት በተወጠር ቃሚ ጢም ብሏል፡፡ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀልን በዛ ከፍታ ሥፍራ ላይ ሆኜ ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላውን አዳራሽ እና ቤቱን የሞለውን ጢስ አሥተዋልኩት።
   ሁሉም ተሰብሳቢ የሞቀ ወሬ ይዟል፡፡አዳራሹም በሳቅና በሁካታ ተሞልቷል፡፡ ተገረምኩ፡፡ ‘አሃ !አንድም ያልመረቀነ ተሰብሳቢ የለም ማለትነው? ‘በማለት እያሰላሰልኩ ሳለ ፣ድንገት ልቤ ተረበሸ፡፡ ወዲያው ድብልቅልቅ ያለ ስሜት በአእምሮዬ መጣ፡፡
   የድፍረትና የግዴለሽነት ስሜት ከመቅስፈት ሲጠናወተኝ ተሰማኝ፡፡ነገሮችን እደወትሮው በአሉታዊና በአዎንታዊ ጎናቸው ለማሰላሰል ተሳነኝ፡፡ ህሊናዬ በመጠኑ የተዛባ ኢ _መደበኛ መሆኑ ታወቀኝ፡፡ከዚህ ቀደም ነገሮችን በጥድፊያና በወከባ እንዳከናውን አይጎተጉተኝም ነበር፡፡ ዛሬ ግን አንዱን ሃሳብ በቅጡ አስቤ ሳልጨርስ፣ ወደሌላኛው ሃሳብ ከመቅስፈት ያሸጋግረኛል፡፡
   የአዕምሮዬ መናጋት ሰበብ ግልፅ ነው፡፡ያ ጢሲ እና የ5500 ጫት ቃሚ ትንፋሽ እኔንም አመርቅኖኛል፡፡በጢሱ ውሰጥ ባለው ጋንጃ የተነሳም አእምሮዬ በቅጡ ማሰብ አልቻለም።
   በአእምሮዬ የሚመጣው ሃሳብ ሁሉ ከገሃዱ ዓለም ሰው ማህበራዊ መስተጋብር ውጪ ነው፡፡ከሞራል ከመልካም ሥነ -ምግባር ከደንብና ከሥርዓት ያፈነገጠ ነው፡፡ ስብሰባውን ለመዘገብ መጥቼ አእምሮዬ የስብሰባውን መሪዎች ጥያቄ እንድጠይቅ ይገፋፋኛል፡፡
   ‹‹ሁሉንም ተሰብሳቢ በአንድ ጊዜ ኢንተርቪው  ( ቃለመጠይቅ  ) ለምን አታደርግም ? ምን ጣጣ አለው ?! የስብሰባውን አስተባባሪዎች ፈቃድ መጠየቅና መድረኩ ላይ ፊጥ ማለትነው፡፡ ከዛም በየጠረጴዛው ፊት ለፊት ያለውን ስም እያነበብክ በጥያቄ ማጣደፍ ነው፡፡የጥያቄ መዓት ማዥጎድጎድ ነው፡፡ጥያቄ መጠየቅ የጋዜጠኛ ሥራ እንደሆነ የታወቀ ነው። ደሞ ለመጠየቅ ማን ይጨነቃል ? ለመልስ ሰጪው ይብላኝ እንጂ!
   “ሂድና የስብሰባውን አዘጋጆች አስፈቅዳቸው፡፡ደግሞም ፈቃደኞች አይሆኑም ብለህ አትፍራ ።የአንተ ጥያቄ እንደ ካሌ ጉላ  ” የቢሆንልኝ ምኞትን” የያዘ  ለፈጣሪ የቀረበ አሥጠሊ ጥያቄ እንደማይሆን ይታወቃል።   ካሌ ጉላ እኮ የሮማ ህዝብ አንገት አንድ ብቻ እንዲሆንለት የተመኘው በአንድ ጊዜ ቀንጥሶ በመጣል ከሚጠላው የሮም ህዝብ ለመገላገል ስለ ፈለገ ነው፡፡በዚህ ፀረ -ህዝብ አቋሙ ለዓለም ህዝብ ያሳየው፣ ለሰው ልጆች የለውን የንቀት ጥግ ብቻ ሣይሆን እብደቱንም ጭምር ነው።
   የአንተ ምኞት ግን፣ የተደማጭነት የተባቢነት እና በቴሌቪዥን መስኮት የሚመለከቱህን ታዳሚዎች ከማብዛት የዘለለ አይደለም፡፡እንድትጠይቅ ቢፈቀድልህ ተሰብሳቢውን  ‘ጫት ለምን እንደሚቃም ና ከጫት ቅሚያ በኋላ ጫት ቃሚው የሚጎናፀፈውን ልዩ እርካታና፤ህሊናዊ እና ሥጋዊ ጥቅም ፣’እንዲገልፅልህ ልትጠይቅ ትችላለህ ። ምናልባት ጥያቄህ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል፡፡ቃሚው በአንድ ድምፅ አነደብራቅ ሊጮኽበህ ይችላል።…
   —አፍህን ዝጋ !ያልበላህን አትከክ!!
   —ያለሰፈርህ የመጣህ ዝንብ ነህ!!
   —ኡኡቴ ! ጠይቀህ ሞተሃል……??
  __ ወያላ !አፍህን ዝጋ!…
   በማለት ሊሰድብህና ሊያንጓጥጥህ ይችላል፡፡ ቃሚው ጠቅላላ ቢያሾፍብህና ቢያንጓጥጥህ አንተ ሞያዊ ስራህን እየሰራህ ነውና ከቁብም አትቆጥረውም፡፡ ደግሞም ፣እውነትን አሳዋቂ  ና በዴሞክራሲ ፅንስ ሃሣብ የምታምን  ጋዜጠኛ በመሆንህ፣ ሰዎች የፈለጋቸውን ቢናገሩ ፣“መናገር ተፈጥሮአዊ ስጦታ ነው፡፡“ብለህ ስለምታምን ፣ ሰምተህ ከማለፍ ውጪ ፣ቁጣና ብስጭት ሲያልፍም እንደማይነካህ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የጋዜጠኝነት ተልኮህን ለማሳካት የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ልታስመሰክር ይገባል፡፡
   አእምሮዬ ከዚህ በፊት እንዲህ በሃሳብ ኖህልሎብኝ እና ዘባርቆብኝ  አያውቅም። ዛሬ ግን የቃሚ መሃት በታጨቀበት አዳራሽ ውስጥ ቁጭ ብዬ እንዲህ አይነቱን  ጎትጎች ና ፋታ ነሺ ሃሣብ  አእምሮዬ እያሥተናገደ ነው።   ‘በጠጪዎች የተከበበ ጠጅ  ቀጂ መስከሩ አይቀሬ ነው። ‘የተባለው እውነት ኖሮአል ለካ ! ” እያልኩ በማሰብ ላይ እያለሁ “የናቃማ” መስራች ጉባኤ ሰብሳቢ ሁካታውን ለማስቆም ከፊት ለፊታቸው ከተቀመጡት ባለከበሮ ና ባለመድፍ ድምፅ ጠረንጴዛ ባለከበሮውን በአጥንታማ እጃቸው ደጋግመው ፣በደቃቃ እጃቸው በኃይል ነረቱት፡፡ በጠረንጴዛው የከበሮ ድምፅ ሙዱ የተቀየረ ቃሚ ፣በአንድ ድምፅ አጉረመረመ። ከጥቂት ደቂቃ ጉርምርምታ በኋላ ፀጥታ ሰፈነ፡፡የስብሰባው አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡
   “ክቡራንና ክቡራት!! ናቃማን ለመመስረት በዚህ አዳራሽ የተሰባሰባችሁ የናጫቃማ አባላቶች !! እንዲሁም በጥሪያችን መሰረት በዚህ አዳራሽ የተገኛችሁ ከአጎራባች ከተሞች የመጣችሁ የተጨበጨበላችሁ ቃሚ እንግዶች !! ፣አንኳን ደህና መጣችሁ፡፡
  እንዲሁም  የተከበራችሁ፣ የምትቅሙና የማትቅሙ ይህንን ታላቅ ስብሰባ ለመዘገብ ፣ከመንግስትና ከግል መገናኛ ብዙሃን የተገኛችሁ፣ ጋዜጠኞች…ከሁሉ አስቀድሜ በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ በንቃት ለመሳተፍና የስብሰባውን ዲሞክራሲያዊ ሂደት ለመከታተል በሰዓቱ ስለተገኛችሁልን፣ በዝግጅት ኮሚቴውና በራሴ ስም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ !!
   አዳራሹን ባነቃነቀው ፣ ፉጨት ና ጭብጨባ ንግግራቸው ለጥቂት ደቂቃ ተቋረጠ፡፡ ፉጨቱ ና ጭብጨባው እንዳባራ ንግግራቸውን ቀጠሉ::
   “ውድ  ‘የናጫቃማ ‘ ዓባላት! ይህንን ማህበር በዛሬው ዕለት እንድንመሰርት ሦሥት ዋና ዋና ምክንያቶች ገፍተውናል። 1ኛው  በየወቅቱ እየዋዠቀ ያስቸገረንን የጫት ዋጋ ሲሆን ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመቅረፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፣የሁላችንንም አቅም ያገናዘበ ዋጋና ስርጭት በመላው ኢትዮጵያ አንዲኖር የሚያሥችል አቅም ለመፍጠር ነው። ሦስተኛው የገፋን ምክንያት የጫት   አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ፣ በማህበር መደራጀት አማራጭ የሌለው የትግል ስልት መሆኑንን በመገንዘባችን ነው። ” … ፉጨቱና ጭብጨባው ንግግራቸውን አቋረጠው፡፡ከአፍታ በኋላ ንግግራቸውን ቀጠሉ።
   “ ከዚህ ዋንኛ ቆስቋሽ ሃሳብ በተጨማሪ፣ በማህበር መደራጀት ጠቃሚ የሚሆነው በጣም ተፈላጊ የሆኑ የጫት ዓይነቶችን በማህበራችን አማካኝነት ለመቆጣጠር እንዲያመቸን ነው፡፡
    “ሁላችሁም እንደምታውቁት ‘ ከገለምሶ፤ ከአሰበ ተፈሪ ወይም ጪሮ፤ ከሂርና፤ ከአወዳይ ወዘተ ፤ ውጪ በተለየ መልኩ ከደቡብ ክልል የሚመጣው ‘ የወንዶና የበለጬ ጫት’ ሥርጭት በናዝሬት የተረጋጋና የተደላደለ እንዲሆን በተለያየ ጊዜ በቡድንና በግል ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እስከዛሬ ባለመገኘቱ በምፅሀረ ቃል ‘ናጫቃማ’ የተባለ፣  ሲተነተን ደግሞ ናዝሬት ጨት ቃሚዎች ማህበር የሚሰኝ፣ የህልውናችን ወኪል የሆነ ድርጅትን ለመመስረት እነሆ ተሰብስበናል፡፡“
   ጭብጨባውና ፉጨቱ ለደቂቃዎች ቀጠለ:: አዳራሹ በጭብጨባና በፉጨት ተነቃነቀ ፡፡ለሩሲያዊው አንባገነን መሪ፣ ለእስታሊን እንኳን ፣በዘመኑ እንዲህ አይነት ጭብጨባ አልተደረገለትም:: ጭብጨባው እጅግ የረዘመና በአልልታ የታጀበ ነበር፡፡ናጫቃማዎች የስብሰባ አዳራሹን በእነሱ ቋንቋ ቀወጡት:: ማለት ይቀላል፡፡
   “ናጫቃማ ይበቃል ! ይበቃል !” በማለት አጠገባቸው ያለውን እንደመድፍ የሚጮኸውን ጠረንጴዛ ደጋግመው በቡጢ ነረቱት፡፡በአዳራሹ ያለ ቃሚ በድምፁ ተደናግጦ ፀጥ እረጭ አለ፡፡
      “አሁን ቀጥታ ወደዋናው አጀንዳችን እንገባለን፡፡ በቅድሚያ አስመራጭ ኮሚቴ ከእናንተ መሃከል ይመረጣል፡፡ ኮሚቴውን ካስመረጥን በኋላ እኛ ከእናንተ ጋር ተቀላቅለን እንቀመጣለን፡፡ ቃሚው ለመሪነት ከጠቆመንና የቤቱን አብላጫ ድምፅ ካገኘን ግን የማህበሩን አመራር እንይዛለን፡፡…
      “ክቡራን ና ክቡራት !! ይህንን ምርጫ የምናካሂደው ፍፁም በሆነ ዲሞክራሲያዊ አግባብ  መሆኑ ለሁላችሁም ግልፅ መሆን አለበት፡፡ በሉ አሁን ለአስመራጭ ኮሚቴ ሰባት ሰዎችን ስለምንፈልግ አስር ሰዎችን ጠቁሙና በድምፅ ብልጫ ሰባቱ አስመራጭ ሆነው መድረኩን ይረከቡናል፡፡” በማለት ወደ ምርጫው ሥነ ሥርአት ለመግባት ሲዘጋጁ ፣አንድ ፂሙን በአብዮተኘው ሌኒን ቅርፅ የተሰተካከለ የስብሰባው ታዳሚ፦”ከዛ በፊት  !……..”ብሎ ጣልቃ ገባና ሳይፈቀድለት ንግግሩን ቀጠለ፡፡
   “አሰመራጭ ኮሚቴ ፣ቆጣሪና ተቆጣሪ፣ ወዘተርፈ፡፡ የምትሉት ሥርዓት ለኔ ፈፅሞ አይገባኝም፡፡ ለመሰሎቼም አይገባቸውም፡፡የምን ተአብ ማብዛት ነው? እንዲህ አይነቱ ሥርአት በእኛ በቃሚዎች ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
   ለመሆኑ ሃሳቡን አፍልቀው ፣ጉዳዩን ወደኛ በማውረድ ፣ይህንን ሁሉ ቃሚ በዚህ አዳራሽ እንዲሰበሰብ ያደረጉት፣ በመድረኩ ቁጭ ብለው እያየናቸው ምንም አስተዋፅኦ ያላደረጉ ቃሚዎችን በምርጫ ሰበብ የማህበራችን መሪ ማድረግ በራሱ ትልቅ ጭቦ ነው፡፡
 “ስለሆነም ፣ያለአንዳች ጭቦ መሪዎቻችንን መምረጥ ስለሚገባን ፣ለዚህ  የናጫቃማ ‘ ምስረታም ያበቃችሁን እናንተ ናችሁና በዛሬው ዕለትም የመሪነቱን ወንበር መያዝ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ፡፡በበኩሌ መድረኩን በአሁኑ ሰዓት እየመራችሁ ከምትገኙት ከሰባታችሁ ውጪ ሌላ ቃሚ አመራሩን እንዲይዝ ከቶም አልፈልግም፡፡
   “በመድረኩ የማያችሁ፣ ሰባታችሁም ፣  በማንኛውም መስፈርት ፣ ከኛ በእጅጉ የተሻላችሁ ናቸው፡፡  ሁላችሁንም  አውቃችኆለሁ ፣ በጠዋት የጀበና ቅሚያ ጀምራችሁ ፣ሌሊት ስድስት ሰዓት ላይ ነው መቃምን የምታከትሟት። ከጫት ጋር እሰኪ ነጋ የማትለያዩትን መሪ ማድረግ የዚህ ጉባኤ ታሪካዊ ኃላፊነት ይመሥለኛል፡፡ ከእናንተ  በላይ በጫት ፍቅር የተነደፈ ቃሚ በድፍን ኢትዮጵያ ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡
    “እኔ በበኩሌ  ይህንን ከኛ ሙድ ጋር የማይገጥም፣  ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚሉት አሰልቺ  አካሄድ ፣የህ መድረክ ከተከተለ በትዕግሥት መቀመጥ አልችልም።የቅሚያ ሰዓትን እየገደሉ  በትዕግሥት ተጎልቶ ማንም ቃሚ ዴሞክራሲ  ገለመሌ እያለ  ቁጭ ብሎ ዓለማዊውን ሥርዓት አይከታተልም፡፡ናጫቃ _ዎችም አይፈልጉም፡፡እባካችሁ ባልኩት እንሰማማና በግዜ ወደቅሚያችን እንመለስ፡፡አመሰግናለሁ !!  ” ንግግሩን ያበቃ መስሎኝ ነበር፡፡አመሰግናለሁ ! ሲል፡፡ሰውየው ግን ንግግሩን ቀጠለ፡፡
   “ወንድሞቼና እህቶቼ ምረቃናችን ተኖ ድብርት ውሰጥ ከመግባታችን በፌት፣ ይህ ስብሰባ በአስቸኳይ መቋጨት ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁላችንም አቋም የእኔ ሃሳብ መሆኑን በጭብጨባ መግለፅ ይኖርባችኋል̋ ፡፡”በማለት ቁጭ ከማለቱ አዳራሹ በድጋፍ ጭብጨባ ተናጋ።
      ቿ!ቿ!ቿ!ቿ!ቿ!ቿ …… ከድጋፍ ጭብጨባው ጋር የተቀናጀ  “ይገባቸዋል!…..   ይገባቸዋል! …… ይገባቸዋል  !…… ይገባቸዋል !….ይገባቸዋል ! …..ይገባቸዋል !… ቿ!ቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿቿ!!!!!!!!!………”በማለት እየደጋገመ ጉባኤተኛው በዜማ ድጋፉን ገለፀ፡፡
   “በእንደዚህ አይነት ወከባ ለስልጣን የበቁት ሰብሳቢ የፊታቸው ፈገግታ እንደባውዛ እያበራ፣ያንን ፣እንደ መድፍ የሚጮህ ጠረንጴዛ ደጋግመው በቡጢ ሲነርቱት፣ በአዳራሹ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ከፌታቸው ላይ ፈገግታ ሳይጠፋ በሃሴት ቃና…
   “ከዚህች ደቂቃ ጀምሮ ናጫቃማ ተመስርቷል፡፡ በሊቀመንበርነትም እኔ እራሴ እመራዋለሁ::የተቀረውን የስልጣን ክፍፍል በየጫት ቤቱና በየመቃሚያ ቤቱ በመለጠፍ እናሳውቃችኋለን፡፡በዚህ አጋጣሚ ከእናንተ መካከል አነድ ሰው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዲሆን ወስኛለሁ፡፡ ይህንንም ግለሰብ አሁኑኑ አሣውቃችኆለሁ።ክብር ለሱ ይሁንና  ሥብሰባችን ሳይንዛዛ  በአጭሩ አንዲጠናቀቅ  በጣም የተሸለና ሁለችንንም የምያግባባ ሃሰብ ያቀረበው የመጨረሻውን ተናጋሪ ነው።     የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አድርጌ የሾምኩት።  ይህንን አእምሮ ብሩህ ሰው፣የናጫቃማ የህዘብ ግንኙነት ኃላፊ አደርጌ፣ በዚህ ታለቅ ጉባእ ፊት ሥሾም ታለቅ ደስታ ና ክብር ይሰማኛል። ሁላችሁም “ናጫቃማ“ እውን እንዲሆን ላበረከታችሁት ታላቅ አስተዋፅዖም ከልብ ፣ከልብ  አመሰግናለሁ !!
   “እነሆ በትግላችን የናጫቃማ እውን ሆኖአልና ደስ ይበላችሁ !! ስለመረጣችሁን በናጫቃማ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴእና በራሴ  ሥም በእጅጉ አመሰግናለሁ!! … ስብሰባችንን ጨርሰናል፡፡ “
  ተሰብሳቢው በጩኸትና በፉጨት አዳራሹን እያናጋ ሰብሳቢውን እና ካቢኔያቸውን ሸኛቸው፡፡ከእነሱም ኋላ ሁሉም ሰው ግር ብሎ ፣እየተገፋፋ ፣ከአዳራሹ መውጣት ጀመረ፡፡ከአዳራሹ እንደወጣሁ ከአዳራሹ ፊት ለፊት ካለው የመኪና ማቆሚያ ሰፊ አስፋልት ላይ ፣ብዙ ሰው ተሰባስቦ ተመለከትሁ::
   ብዙዎቹም ፀጉራቸው የተንጨፈረረ ! ፊታቸው የገረጣ ! አለባበሳቸው ቅጥ ያጣ ! ነበር፡፡
ከአንድ የጥበቃ ሰራተኛ እንደተረዳሁት፣ የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ በአዳራሹ ፊትለፊት የተሰባሰቡት የናዝሬት ገራባ ጫት ቃሚዎች ወይም ‹‹ናገጫቃ ››የሚባሉት ነበሩ፡፡
በቱሪማንቱሪ ዛፍ ቀርንጫፍ ላይ የተንዥጎረጎረ ካርቶን በምስማር መተው፣ በክሠል የሰላማዊ ሰልፋቸውን አላማ የሚያንፀባርቅ መፈክር ይዘው  ነበር፣አዳራሹ ፊት ለፊት የተሰደሩት፡፡
   —የጫት ገራባን ለማገዶነት የሚሰበስቡ አንዳንድ ምቀኞችን አጥብቀን እንቃወማለን  !!
   —የጫት ገራባን ለማገዶነት የሚሰበስቡትን “ናጫቃማ” ሃይ ይበልልን  !! “
   —የጫት ዋጋ በማሻቀቡ፣ ገራባ ቃሚዎች እየተበራከቱ ስለመጡ፣ የጫት ዋጋ እንዲቀንስ  የናጫቃማ አባለት መታገል ይኖርባቸዋል!!”
  — የናጫቃማና የናገጫቃ አንድነት ይጠንክር!!”
   —ናጫቃማ ለዘላለም ይኑር!!”
   እነዚህን መፈክሮች እያሰሙ ባሉበት ሰዓት ከአዳራሹ በመውጣት ላይ ያሉትን “የናጫቃማ” አባላትን “ናገጫቃ” እንዳዩአቸው፤ መፈክር ማሰማታቸውን አቁመው፣የአንድ እጅ መዳፋቸውን ወደ ላይ ዘርግተው እየተንደረደሩ መዳፋቸውን ከናጫቃማ አባለት ጋር እያጮሉ በምርቃና አባዜ ትከሻ ለትከሻ በመገጫጨት ፣ሰላምታ ሲለዋወጡ በመመልከት ላይ ሳለሁ፤ አንድ እረጅም፣ወፍራም አና ጠይም መልክ ያለው፤የገጠጠ ብልዝ የፊት ጥርሱ የሚየስፈራ፣  የተንጨበረረ እና የጎፈረ ጥቁር ፀጉሩ የዱር አውሬ የሚያስመስለው፣ በምረቃና ብዛት ዐይኑ ወደውጪ ፈጦ ፣ስለታም ጥረሱን አግጦ፣ በገራባ ጫት የግራ ጉንጩን እንደ ተነፋ ፊኛ ወጥሮ፣ እጆቹን እንደአሞራ ክንፍ እያርገበገበ፣በሩጫ ወደ እኔ ሲመጣ ፣በፍርሃት ጮኬ ፣ከእንቅልፌ ብንን አልኩ፡፡
2002 የተጸፈ በ2011 የታደተ።

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop