August 17, 2019
39 mins read

ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች (Non state Actors) ሚና  ከወቅቱ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁ

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ ነሐሴ 2011

የአንዳንድ ታዋቂ ዜጎችና ተቋማት የበሰለ ወቅታዊ እንቅስቃሴ፣ በገዛ-ራሳቸው የትግልና የመስዋዕትነት ፍሬ ላይ ሳያውቁት ሻጥር ለሚፈጽሙ አንዳንድ “የቀድሞ ታጋዮች” ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ አንድ የለውጥ ኃይል፣ ለውጥ ለማምጣት ብዙ መስዋዕትነት ከከፈለ በኋላ የትግሉ ፍሬ መታየት ሲጀምር፣ ለውጡ ወደኋላ እንዳይመለስ፣ መሥመር እንዳይስት፣ ቀሪ ነገሮች እንዲሟሉና ዳር እንዲደርስ ወጥሮ መሥራትና መቀጠል ይገባዋል፡፡ እርግጥ ነው ሰው ከደከመው ማረፍ ነውር አይደለም፡፡ “ያልተጠናቀቀ ሥራ አለኝ” ብሎ የሚያምን ደግሞ ትግሉን ዛሬ ከደረስንበት ተጨባጭ ሁኔታ (ዕድሎችና ስጋቶች፣ የኃይል አሰላለፍና በተለይም ከአቅምና የኃይል ሚዛን ወዘተ) አንጻር ቃኝቶ በጽናትና በአስተዋይነት መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በአንዳንድ “የቀድሞ ታጋዮች” ዘንድ፣ ቁርጠኛ ታጋይነት የሚለካው ዛሬም እንደትላንት መንግሥትንና ባለሥልጣኖቹን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመኮነን፣ በማውገዝ፣ በማብጠልጠል፣ በማሳጣትና በማንኳሰስ (naming and Shaming) ብቻ ተደርጎ እየታየ ይመስለኛል፡፡ የተቃዋሚነት ሀሳብና ተግባር መለካትና መቃኘት ያለበት፣ በግል ስሜት (ቂምና በቀል፣ ጥላቻ፣ እልህ፣ ሂሳብ ማወራረድ) ወይም በጭፍን ምኞት አይደለም፡፡ በውነቱ የተራማጅ ኃይሎች የትግል ሥልት መቃኘት ያለበት ከወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ፣ እንደአዲስ ከታየው የኃይል አሰላለፍ በተለይም ከአቅምና የኃይል ሚዛን፣ ከመርሆ፣ ከትልቁና ከዘላቂው የሕዝብና የሐገር ጥቅም አኳያ መሆን አለበት፡፡

ከአንድና ሁለት ዓመት ወዲህ በሐገራችን ፖለቲካ ዙሪያ በርካታ ነገሮች ተቀያይረዋል፤ ከዋናዋናዎቹ አዳዲስ ተጨባጭ ሁኔታዎችና የኃይል አሰላለፎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡

  • ዋናው ገዢ – ወያኔ ከማዕከል ተገፍትሯል፤ ከየጎሣው የተሰባሰቡ ዋና ዋና ጸረ ዴሞክራሲና ጸረ አንድነት ኃይሎችም ቢሆኑ ከመድረኩ መራገፍ ጀምረዋል፤
  • ጨካኙና ገደብ የለሹ አፈና በአብዛኛው ተነስቷል፣ እየተነሳም ነው፤
  • በፍትሕ፣ በዴሞክራሲ፣ በምርጫ አስፈጻሚ፣ በሐገር መከላከያ፣ በጸጥታና ደህንነት፣ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውስጥ መሠረታዊ የሚባሉ የፖሊሲና የሕግ፣ የመዋቅር፣ የሰው ኃይል ለውጦችና ማሻሻያዎች መደረግ ጀምረዋል፤ የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚው፣ የኃይማኖቱ፣ ሀሳብን የመግለጹ፣ የዜጎች አደረጃጀቶችና አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን የሚመለከቱ ምሕዳሮች ሁሉ ከወትሮው በተሻለ ይዘትና መልክ እየሰፉ ነው፡፡ እርግጥ በርካታ ቀሪ ሥራዎች አሉ፤
  • የምሕዳሩን መስፋት ተከትሎ ሕዝቡ፣ በተለይም ወጣቱ አምቆት የቆየውን ብሶትና ጥያቄውን በመሰለው መንገድ መተንፈስና ራሱን መግለጽም ጀምሯል፤ የታፈነ ጥያቄ፣ ምሬትና ብሶት በግብታዊነት ሲገለጽ የሚያስከትለውን ፈተና እየተመለከትነው ነው፤
  • የዘረኛው ሥርዓት ሰለባ የነበሩ በተለይም ከእሥር የተፈቱ፣ የአካል፣ የሞራል፣ የኢኮኖሚና የስነ አእምሮ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ተደብቀው የከረሙና ከስደት የተመለሱ ታጋዮች አብዛኞቹ ከቁጣ፣ ምሬትና ቁጭታቸው ጋር አዲሱ ምሕዳር ባስተናገዳቸው ልክ ራሳቸውን እየገለጹ ነው፤
  • ከርቀትና ከውጭ በማህበራዊ ሜዲያና በመደበኛ የዜና አውታሮች እንዲሁም በህቡዕ ስምሪትና በውክልና ትግል ወጣቱን ያማልሉ የነበሩ ልዩ ልዩ (ብሔርተኛ፣ ጽንፈኛ …) ኃይሎች ዛሬ ሰፋ ባለው ምሕዳር ተጠቅመው ሳይረፍድ በቶሎ መሠረት ለመያዝና ለማስፋት እየሠሩ ነው፣ ነጻነትንና ግዴታን ያላገናዘበና ያልተመጣጠነ እንቅስቃሴ የሚያስከትለውን ፈተና እየተመለከትነው ነው፤
  • ከሥልጣን የተገፉት የወያኔ ጽንፈኞችና ከየጎሣው የተሰባሰቡ ጨቋኞችና መዝባሪዎችም ጥቅም ስለቀረባቸውና የማይቀር የሚመስል የተጠያቂነት አደጋ ከፊታቸው ስለተደቀነባቸው እጅግ ፈርተዋል፡፡ ስለዚህ ወደው ሣይሆን በግድ የተከፈተውን ምሕዳርም ለእኩይ ዓላማቸው ለመጠቀም ዕረፍት አጥተው ሲሯሯጡ ይታያል፤ ያለ የሌለ ኃብት፣ ልምድና መረባቸውን ተጠቅመው ምህዳሩን እየበከሉት ነው፤ በሰበብ አስባቡ ራሳቸው አጀንዳ እየፈጠሩና እየሰጡ የልዩ ልዩ ቡድኖች አጀንዳዎች ላይም ዘለው እየተሳፈሩ ሐገሪቱንና ሕዝቡን ማተራመስ ይዘዋል፡፡ ሁኔታውን የባሰ አስጊ የሚያደርገው ደግሞ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች መቀሌና በየክልሉ ከተማ ከመመሸጋቸው ባልተናነሰ በመንግሥታዊ መዋቅሩም ውስጥ ገና እንደተሰገሰጉ መገኘታቸው ነው፡፡
  • ነገሩን የበለጠ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ የዶክተር አቢይ ቡድን፣ አንደኛ ለራሱም የመለወጥ ዕምነት ታማኝ ሆኖ ለመገኘት የሚያደርገው ጥንቃቄ፣ ሁለተኛ ሕዝብና ዓለም፣ ተለውጫሁ ከሚል መንግሥት ከሚጠብቀው ፖለቲካዊ ጠባይ አፈንግጦ ላለመታየት የሚያደርገው ጥንቃቄ፣ ሦስተኛ ደግም ምናልባት የዋና ዋና ቅራኔዎችና ተግዳሮቶችን አያያዝ በሚመለከት ራሱ ከቀመረው ሥልትና ከሚያሳየው ትዕግሥት አንጻር ከላይ የተዘረዘሩት ወገኖች እዚህም እዚያም የሚፈጥሩትን ሁከትና ሥርዐት አልበኝነት ለመቆጣጠር የተሳነው መስሎ እየታየ ነው፡፡ በማናቸውም ምክንያት ይሁን የሕግ የበላይነትን የማሰከበርና ሰላምን የማስፈን መንግሥታዊ ግዴታውን በጊዜ ባለመወጣቱ ምክንያት ሕዝቡና ሐገሪቱ ራሱ መንግሥትም ጭምር ከፍተኛ ኪሣራ እየደረሰባቸው ይገኛሉ፡፡
  • በዚህ ሁሉ ላይ በራሱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያደፈጡ ጸረ ለውጥ ኃይሎች የሚፈጽሙት ዘርፈ ብዙ አሻጥር የሽግግሩን ሁኔታዎች ሁሉ ለመረዳትና ለመተንበይ አዳጋች አድርጎታል፡፡

 

ቀደም ብሎ ለማሣየት እንደተሞከረው፣ የተራማጅ ኃይሎች የትግል ሥልት መቃኘት ያለበት እዚህ ከተዘረዘሩት (እና ካልተዘረዘሩት) ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች፣ አዳዲስ የኃይል አሰላለፎች፣ የልዩ ልዩ አካላት አቅምና የኃይል ሚዛን፣ ከመርሆ፣ ከትልቁና ከዘላቂው የሕዝብና የሐገር ጥቅም አኳያ መሆን አለበት፡፡ እገሌ ይህንንና ያንን አድርጓል/አላደረገም ብሎ ችግርን ወደ ሌላ አካል (ወደ ውጭ) መግፋት (Externalize) እና የትናንት ሁነቶች ላይ ብቻ አፍጥጦ መቅረት የትም የማያደርስ “የትግል ሥልት” መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡ ይልቁንም ቀልጣፋና ውጤታማ ለመሆን የሚበጀው፣ ወደ ራስ (ወደ ውስጥ) እና ወደ ፊት ተመልካች ሆኖ የራስን ክፍተቶች ማጥበብና ጥንካሬን ጨምሮ ወደምንፈልገው ግብ የሚያደርሰንን ስልትና አቅጣጫ ተልሞ መንቀሳቀስ ነው፡፡

 

የዚህን ሃሳብ አቀራረብ በሚመለከት ያልተፈለገ የሀሳብ ብዥታ እንዳይፈጠር መነሻውን አጥርቶ ማለፍ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ የነዶክተር ዓቢይን ፍልስፍና፣ አጀማመር፣ አያያዝ፣ ውጥን፣ የሠሩትን / ያልሠሩትን (ዕቅድና አፈጻጸም) አንጠይቅ፣ አንቃወም፣ ዝም ብለን እንይ ወይም እንደግፍ የሚል አቋም ፈጽሞ ሊኖረን አይገባም፡፡ ይልቁንም፣ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በሐገራችን የለውጥ ጅማሮ አለ / የለም ወይም አጥጋቢ ነው / አይደለም ወይም አዝማሚያውና አቅጣጫው ወዴት ነው? ብሎ መጠየቅና ትክክለኛ መልስ ለማግኘት መሞከር እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በየትኛውም ሠፈር የሚቆም ኃይል መንግሥትን በሚመለከት የቀጣይ ሥራውን ዓይነት (መደገፍ/መቃወም/ዝም ብሎ መመልከት) ሊወስንና ሊከውን የሚችለው ለነዚህ ጥያቄዎች በሚሰጠው መልስ ላይ ተመርኩዞ ይመስለኛል፡፡ ግምገማ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግምገማችንን ሣይንሳዊና ቅንነት የተሞላበት ማድረጉ ላይ ነው፡፡

 

እንደሌሎች ክንዋኔዎች ሁሉ የለውጡንም ጅማሮና አካሄድ ለማየትና ሣይንሳዊ ግምገማ ለማድረግ ስንፈልግ ከብዙ ነገሮች መካከል ቢያንስ ሁለት መሣሪያዎች በቅድሚያ ሊኖሩን ይገባል፤ አንደኛው መሣሪያ የማስተያያ/የማንጸሪያ ግብ ሲሆን ሁለተኛው መሣሪያ ደግሞ የመገምገሚያ መርሆ ነው፡፡ አንደኛ፣ ለአፈጻጸም ሂደትና ለውጤት ግምገማው መነሻ የሚሆነን የተደራጀ የሥራ ዕቅድ፣ ውጥን ወይም ግብ አስቀድሞ ሊኖረን ይገባል፡፡ ዕቅዳችንንና የምንፈልገውን ውጤት (Intended Result) መሥፈሪያ አድርገን የለውጡን አፈጻጸም መገምገም ወሣኝ ነው፡፡ የስኬትና የውድቀት መለኪያችን እርሱ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍላጎትና ግባችን የሐገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት ማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ ስለዚህ በግምገማችን የምናነሳው ጥያቄ፣ እስካሁን የተሠራውና በመሠራት ላይ ያለው ሥራና የተገኘው ውጤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ፍላጎታችንን ያገናዘበ ነው ወይ? ወደ ተፈላጊው የዴሞክራሲና የአንድነት ፍላጎትና ግባችን የሚያደርሰን ነው ወይ? የሚል መሆን አለበት፡፡

ሁለተኛው መሣሪያችን ደግሞ የመገምገሚያ መርሆአችን ነው፡፡ ከመርሆ አንጻር “የግማሽ ጠርሙስ ንድፈሀሳብ” የሚባለውን የዕይታ ቅኝት፣ ቅደምተከተልና ሥልት ማጤን የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡ በ”ግማሽ ጠርሙስ ንድፈሀሳብ” መሠረት አንዳንዶች የጠርሙሱ አለመሙላት በቅድሚያ ይታያቸውና፣ እዚያ ላይ ብቻ በማተኮር ጠርሙሱ ባዶ እንደሆነ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጠርሙሱ ውስጥ ውኃ መኖሩን በቅድሚያ ያዩና እዚያ ላይ ብቻ በማተኮር ጠርሙሱ ሙሉ እንደሆነ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ አሁንም ሌሎች ደግሞ ውኃው ጠርሙሱ ግማሽ ላይ የደረሰና ለመሙላት ግማሽ የሚጎድለው መሆኑ “በአንድ ጊዜ” ይታያቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ቁምነገር የዕይታ ቅደምተከተላችንና ቅኝታችን ነው፡፡ በቅድሚያ ጠርሙስ ውስጥ ውኃ መገኘቱን ከማየት መነሳት አለብን፣ በጠርሙሱ ውስጥ ያለው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሆነ መለካት ያስፈልጋል፤ ጥራቱንም ማየት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ አካሄዳችን ላየነው ተጨባጭ ውጤት ዕውቅና በመስጠት መጀመር ይጠቅማል፡፡ ስለኛ ለውጥ ጅማሮውም ስናስብ አስቀድመን ለማየት መሞከር ወይም መገምገም ያለብን ከዴሞክራሲና ከአንድነት አንጻር የተወጠነውን፣ የተጀመረውን፣ የተኬደውን ርቀትና የተገኘውን ተጨባጭ ውጤት እንዲሁም የተያዘውን አቅጣጫ የሚያሳየውን ጠንካራ ጎኑን ነው፡፡ ይሄ ይሄ ተሠርቷል ብለን በተሳካው ሥራ ላይ ቆጠራ ስናደርግ፣ እስከዚህ ድረስ የታየው ውጤትና መሻሻል ያስደስተናል፣ ሞራላችንን ከፍ ያደርገዋል፤ በጡቡ ላይ ተጨማሪ ጡቦች በመደርደር ግንቡን የማቆም ሥራችንንና ጥረታችንን ይበልጥ አጠናክረን ለመቀጠል ትልቅ ሞራል ይሆነናል፤ የተጓዝነውን ርቀትና የደረስንበትን ነጥብ በትክክል ማወቅ ቀሪዎቹን ሥራዎች በተስፋ ለመመልከት፣ በፍጥነት ለመጀመርና ለማጠናቀቅ ፍላጎትና ጉጉት ያሳድርብናል፤ ተነሣሽነትና ብርታትም ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ለተሠራ ሥራና ለተገኘ ውጤት ዕውቅና መስጠት፣ ማድነቅ፣ ማመስገን፣ ማበረታታትና መደገፍ የሞራል ብቻ ሣይሆን ተግባራዊና ስትራቴጂካዊ ጥቅምም አለው፡፡ ቀጥሎ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ገና ያልተጀመረውን፣ ተጀምሮ በእንጥልጥል ላይ ያለውን እና ተሞክሮ ያልተሳካውን ማለትም ክፍተትና ድክመቱን በቅንነት ማየት ግድ ነው፡፡ ገና የተቀመጠን፣ የቀረውንና ያልተሠራውን ሥራ ማየት የሚጠቅመው ግን የተሠራውን ለመካድና ለማንኳሰስ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም ያልታቀደበትን፣ ሣይሰራ የዘገየበትን፣ የቀረበትን ወይም ያልተሣካበትን ምክንያቱን አውቆ እንዲሠራ ለማበረታታት፣ ለመጎትጎት፣ ለማነቃቃት፣ ለመደገፍና ይበልጥ ለመከታተል ነው መሆን ያለበት፤ ተጠያቂነት ከዚህ በኋላ ደረጃውን ጠብቆ መምጣቱ ግድ ነው፡፡ የለውጡንም ጅማሮ የምናየው በዚህ መልክ ቢሆን ይጠቅመናል እላለሁ፡፡

 

ቀደም ብለን ወደጀመርነው ጉዳይ እንመለስ፡፡ በየፊናችን የነበረን የትናንት አስተዋጽኦአችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ብዙ የደከምንለት፣ ዋጋ የከፈልንለትና የናፈቅነው የለውጥ ተስፋ መታየት ሲጀምር፣ እንደተለመደው እንዳይቀለበስና እንዳይከሽፍ ማገዝ ግድ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና እነገሌ ይህን ቢያደርጉ/ባያደርጉ ኖሮ ወይም ለምን አደረጉ/ አላደረጉም ብቻ እያልን ሁልጊዜ ጠባቂ፣ ወቃሽ፣ አጉረምራሚና ጣት ቀሳሪ ከመሆን ሁላችንም በተለይ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች (Non state Actors) በየፊናቸው እንደየአቅማቸው ለውጡን ለማስቀጠል የሚችሉትን ማድረግ ይገባቸዋል ብዩ አምናለሁ፡፡ ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ ችግሩና ድክመቱ እነዚህ ወገኖች ጥቂቶች መሆናቸው ብቻ ሣይሆን  ከሐገራዊ ቀውሱ ግዝፈትና ውስብስብነት አንጻር ጥረታቸው ጎልቶ ሊታይ አለመቻሉም ነው፡፡ የጥረታቸው ቀጣይነት መጉደልም ችግር አለ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ባለጉዳዮች ለውጡን በርብርቦሽ ለማስቀጠል መጎትጎት ይኖርባቸዋል፡፡

ሁሉም ከጠባቂነትና ከዳር ተመልካችነት ወጥቶ የድርሻውን በሙሉ-አቅሙ ማዋጣት እንዲጀምር ለመጎትጎትና ለመሞገት ኃላፊነት የሚሰማቸው የሜዲያ ተቋማትና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ቡድኖች  የማይናቅ ሚና ለመጫወት የተሻለ ዕድል አላቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮችን አንድ በአንድ ለይቶ በማወቅ፣ በመቅረብ፣ በማነጋገር፣ በየዘርፉ አንቀሳቃሽ ኮሚቴ (Stirring Committee) እንዲቋቋም በመርዳት፣ መድረክ በማመቻቸት ወይም በማገናኘት ትልቅ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፤ እነዚህ አካላት ይህን እንደ አንድ ፕሮጀክት አስበውበት ቢሠሩት በሐገር ደረጃ የሚፈጥሩት እጅግ ከፍተኛ ለውጥ ለኔ ከወዲሁ ይታየኛል፡፡ ሰፊው ሕዝብ ድምጹና አቋሙ በግልጽ እንዲሰማና እንዲታይ፣ የሚጠቅመውን በጽኑ መደገፍ እንዲችል፣ የሚጎዳውን ደግሞ “አይሆንም ተው” እንዲልና  አስገዳጅ ጫና ማሳደር እንዲችል ከመንግሥት ውጭ ባሉ ተዋናዮች አማካኝነት ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ይህ ለነገ ይደር የማይባል እጅግ አጣዳፊ ጉዳይ ነው፡፡

ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች (Non state Actors)

መንግሥት ከፖሊሲ፣ ከሕግ፣ ከመዋቅር፣ ከሰው ኃይል፣ ከሐብት ምደባና አጠቃቀም ወዘተ አንጻር ለውጡን ለማስቀጠል ማድረግ ስለሚገባውና ስለማይገባው ነገር መጎትጎት፣ ማስታወስ፣ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ፣ ሂሳዊ ድጋፍ መስጠት ግድ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች በራሳቸው በኩል ወደ ውስጥ-ተመልካች በመሆን፣ የለውጡን ሂደት ለመደገፍ የራሳቸውን ድርሻና ኃላፊነት ከመወጣት አንጻር ምን እና ምን ያህል እየሠሩ እንደሆነ መጠየቅና መሞገት፣ መደገፍም ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ያለን ይመስለኛል፤ እነዚህ ኃይሎች በዚህ ረገድ እጅግ አርፍደዋል ባይ ነኝ:; እስኪ በመንግሥት፣ በተቃዋሚዎች፣ በልዩ ልዩ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ በተማሪዎች፣ በወላጆችና በአጠቃላይ በህዝብ ላይ ሣይቀር ትልልቅና እጅግ ወሣኝ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳደር ይችሉ ከነበሩትና ነገር ግን እስካሁን በእንቅልፍ ላይ ከሚገኙት ዋና ዋና ተዋናዮች አንዱን ለማሳያ ያህል እንጠይቅ – የኢትዮጵያ መምሕራንን፤ ለኢትዮጵያ መምሕራን የምንጠይቃቸው እነዚህ ጥያቄዎች ለሌሎች ተዋናዮችም እንደየተፈጥሮና ተልእኮአቸው እየተስተካከሉ የሚጠየቁ ናቸው፡፡

  • የኢትዮጵያ መምሕራንና ነጻ ማኅበራቸው የት ነው ያሉት?
  • ዶር ዐቢይ እና ኢሕአዴግ እንዲ/እስኪያደራጇቸው ይሆን እየጠበቁ ያሉት?
  • ወይስ የገዢዎች አካልና አገልጋይ ሆኖ ራሱን ብቻ ሲያጎለብትና ሲጠቅም የነበረው ተለጣፊ ማሕበር “ተኃድሶ አካሂጃለሁና ኑ በነጻነት ላደራጃችሁና ላሸጋግራችሁ” እስኪል እየጠበቁት ነው?
  • ወይስ ወያኔና መሰል ጎጠኞች ላለፉት 30 ዓመታት እንደቀሰቀሱትና እንደቀየሱት የጎሣ ማንነትን የተሻገረ ሌላ (የሙያ ወዘተ) ማንነት እንዳይኖር በተሠራውና አሁንም በሚሠራው ሻጥር እንደተደናገሩ ናቸው?
  • ወይስ የቀድሞው ኢሕአዴግ፣ ከጥገኛ “የሕዝብ ክንፍ” አደረጃጀቶች ውጭ ነጻ የሲቪል ማሕበረሰብ አደረጃጀቶች እንዳይኖሩ በወጋቸው መርፌ ምክንያት አሁንም እንደደነዘዙ ናቸው?

 

በዚህ አጋጣሚ አንድ የግሌን የወቅታዊ ሁኔታ ጥቅል ምልከታ ልግለጽ፡፡ ዶክተር ዓቢይ ወደሥልጣን በመጡበት ጊዜና እስካሁንም ድረስ በግልጽ የሚታይ የአቅም፣ የኃይል አሰላለፍና የኃይል ሚዛን ክፍተት አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና መረጋጋትና ዕውነተኛ የምርጫ ዴሞክራሲ ወደሚረጋገጥበት የተሻለ ምሕዳር ለማሸጋገር ከዶክተር ዓቢይ ቡድን (ከነብዙ ችግሩም ቢሆን) የተሻለ ሁኔታ ላይ ያለ ወይም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊገኝ የሚችል ኃይል ገና እልተፈጠረም፡፡ ይህ በዋነኛነት የወያኔ የግፍ አገዛዝና አፈና የጣለብን መጥፎ አሻራና ዕዳ ነው፡፡ “አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መንግሥት ለመሆን የሚያበቃ ሐገር አቀፍ ድርጅታዊ ቁመናና በቂ የሕዝብ ድጋፍ አላችሁ ወይ?” በሉና ጥግና ጥግ ያሉትን ለምሳሌ ኢዜማንና ኦነግን ወይም ኦፌኮን፣ አለያም አረናንና የነዶክተር አረጋዊን ትዴት ወይም ሌሎችን ጠይቋቸው፡፡ ሕብረ ብሔራዊ የዴሞክራሲ ኃይሎችም ሆኑ ብሔረተኛ ድርጅቶችና ኃይሎች፣ ወይም ልዩ ልዩ ጽንፈኛ ኃይሎች፣ ወይም ልዩ ልዩ የሙያ፣ የኃይማኖት፣ የጎሣ፣ የጾታ፣ የዕድሜ ቡድኖችና ባጠቃላይም የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአንጻራዊ አነጋገር የተሻለ ሊያምኑት የሚችሉትና ቀርቦ ለማነጋገር ቀለል የሚላቸው፣ የጉልበቱንም ሆነ የሕዝብ ድጋፉን ሁኔታ አስልተው በጥንቃቄ ሊይዙት የሚችሉት አካል የዶክተር ዓቢይን ቡድን ይመስለኛል፡፡ በአንጻራዊ አነጋገር፣ ዶክተር ዓቢይና የለውጥ ቡድናቸው፣ በሁሉም ማዕዘን ጥግና ጥግ ይዘው በጥርጣሬ የተፋጠጡ ኃይሎችን በአማካይ ርቀት/ቅርበት ላይ ሆኖ ለማነጋገር፣ ለማረጋጋትና ለማቀራረብ የተሻለ የመታመን ዕድል ያላቸው ይመስለኛል፡፡ የወያኔ ጽንፈኛና መሰሎቹ ሐገራችን ወደትርምስ እንድትገባ ፍላጎታቸው ነው፡፡ ከነዚህ አፍራሽ ኃይሎች በስተቀር፣ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ የሚጨነቅ ወገን የነ ዶክተር ዓቢይ የለውጥ ኃይል ከመሥመር እንዳይወጣ ከመጠበቅ፣ ከመግፋትና ከማገዝ የተሻለ አማራጭ ያለው አይመስለኝም፡፡ እናም በታሪክ አጋጣሚ በነዶክተር ዓቢይ ላይ ያረፈውን የማገናኘትና የማሸጋገር ኃላፊነትና አደራ በጊዜ ለመረከብ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች (ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ) መረባረብ ይገባቸው ነበር፡፡ ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ እጅግ የሚበዙት ተኝተዋል፡፡ ያለውን ግልጽና ከፍተኛ ክፍተትና ድክመት በመሙላት የለውጡ ጅማሮ እንዳይቀለበስ ለመጠበቅም ሆነ አማራጭ ኃይል ሆኖ ለመውጣት እየተደረገ ያለው ትግልና ጥረት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ እስካሁን ከባከነው ጊዜ በላይ ማባከን ደግሞ እጅጉን የከበደ ዋጋ እንዳያስከፍለን እሰጋለሁ፡፡

 

ከዚህ አንጻር የተጀመረው ለውጥ ወደመሬት / ሕዝብ እንዲወርድና እንዲጎለብት፣ እንዲሁም ስጋቱ እየቀነሰና ተስፋው እየጨመረ እንዲቀጥል፣ የሚከተሉት ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች (Non state Actors) ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ምን የሚታይና ትርጉም ያለው ሥራ ሰሩ? ከያሉበት እየተፈለጉ ሊጎተጎቱና ሊሞገቱ ይገባል፤ ድጋፍም ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋንያን፣ ለጉድለቶችና ለጥፋቶች ሁሉ ከነሱ ውጭ የሆነ ተጠያቂ የሚሆን አካል በመፈለግ የራሳቸውንና የሐገሪቱን ውድ ጊዜ በማባከን ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች ወደ ውስጥ / ወደራሳቸው መመልከት እንዲጀምሩና ያለ-የሌለ ኃይላቸውን አውጥተው የድርሻቸውን በማበርከት በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ ያለዕረፍት መጎትጎት አለባቸው፡፡

እስኪ በዚያውም ለውይይት፣ ለመድረኮችና ለቃለመጠይቅም መነሻ ከሆኑ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እናጢናቸው፡፡ ለምሣሌ፡

  1. ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች
  • ሕዝብ የራሱን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅና የሕግ የበላይነት ለማስከበር ሊኖረው ስለሚገባ ቀጥተኛ ተሳትፎ
  • አማራጭ የመሸጋገሪያ ስልትና ኃሳቦችን ለማቅረብ፣
  • መርሐግብራቸውን ለሕዝብ ማስተዋወቅ፣
  • አባላትና ደጋፊ ለማፍራት፣ መዋቅር ለማስፋት፣ ለመጪው ምርጫ ለመዘጋጀት ምን እያደረጉ ነው?) (በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ምን ሠሩ?)
  • በፖሊሲና በመርሐግብር አንድ ዓይነት ከሆኑ ጋር ስለመዋሐድ፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከሚመሳሰሏቸው ጋር ቅንጅት ወይም ግንባር ስለመፍጠር ግንኙነትና ውይይቶችን አጠናክሮ መቀጠል (በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ምን ያህል ሠሩ?)
  1. የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና ሌሎች የሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት
  • ለሕዝብና ለመንግሥት አካላት ስለሰብዓዊ መብቶች ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት ረገድ
  • ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርባቸውን፣ ሰላም፣ እርቅ፣ አንድነት የሚጎለብቱባቸውን ልዩ ልዩ መድረኮችን ለልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተከታታይ ማደራጀት
  • አሁንም በመንግሥት አካላት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን (Violations) አጣርቶ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ፣
  • ከመንግሥት ውጭ ባሉ አካላት (ተቃዋሚዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ኢመደበኛ አደረጃጀቶች ወዘተ) የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን (Abuses) አጣርቶ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ፣(በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ምን ሠሩ?)
  • ተቀራራቢ ዓላማና ተልእኮ ያላቸው በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ለመተሣሠርና በሕብረት ለመሥራት ምን ያህል ርቀት ሄደዋል?
  1. ጋዜጠኞች ነጻ ማኅበር አቋቁመው (ጋዜጣ፣ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ የኢንተርኔት መገናኛዎችና የማሕበራዊ ሜዲያ ተዋናዮች፣ ጦማሪዎች)
  • ሀሳብን በነጻ የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብት ወደኋላ እንዳይመለስና ለውጡ እንዲጎለብት፣
  • አራተኛው መንግሥት / ነጻ ሜዲያ እንዲጠነክር
  • የሕዝብና የሐገር ሰላም፣ አንድነትና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን
  • የሙያ መብታቸው እንዲከበር … በጋራ አሻራቸውን መጣል ጀምረዋል? (በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ምን ሠሩ?)
  1. ሠራተኞች ከተለጣፊ ማሕበር ራሳቸውን ነጻ አውጥተው ነጻ ማኅበር አቋቁመው
  • ለውጡ እንዳይነጠቅና እንዲጎለብት፣
  • የሠራተኞች መብቶች እንዲከበሩ
  • የሥራ አካባቢ ሰላም፣ የሕዝብና የሐገር ሰላም፣ አንድነትና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን … በጋራ አሻራቸውን መጣል ጀምረዋል? (በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ምን ሠሩ?)
  1. መምሕራን ከተለጣፊ ማሕበር ራሳቸውን ነጻ አውጥተው በነጻ የሙያ ማሕበር ተደራጅተው
  • የሥራ አካባቢ ሰላም፣ የሕዝብና የሐገር ሰላም፣ አንድነትና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን
  • የትምህርት ጥራት ማስጠበቅ እንዲጀመር፣
  • ትውልድን ማቃናትና ማነጽ እንዲጀመር
  • የሙያ መብታቸውን ለማስከበርና የሙያ ግዴታቸውን በጥራት ለመወጣት … በጋራ አሻራቸውን መጣል ጀምረዋል? (በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ውስጥ ምን ሠሩ?)

 

ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት ተዋናዮችም፣ ለለውጡ የሚኖራቸውን ኃላፊነት፣ ድርሻና አስተዋጽዖ እንደየባህርያቸው መዘርዘር ይቻላል፣ ይገባል፡፡

  1. የኃይማኖት ተቋማትና መንፈሳዊ ማሕበራት (ማሕበረ ቅዱሳን፣ ሰንበት ት/ቤቶች….)
  2. ልዩ ልዩ የሙያ ማሕበራት (Professional Associations)
  3. የኪነጥበብ ባለሙያዎች ማህበራት
  4. የጥናትና ምርምር ተቋማት (Think Tank)
  5. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (የግሎቹን ጨምሮ)
  6. ንግድ ምክር ቤቶች
  7. የግሉ ዘርፍ ማሕበራት / የአሠሪዎች ፌዴሬሽን
  8. የወጣቶች ማሕበራት (ልዩ ልዩ የወጣቶች የበጎ አድራጎት አደረጃጀቶች)
  9. የተማሪዎች ማሕበራት
  10. የስካውት ቡድኖች፣ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማሕበር-ወወክማ/ወሴክማ፣ የሙስሊም ወጣቶች
  11. የሴቶች ማሕበራት
  12. የአካል ጉዳተኞች ማሕበራት
  13. የአርበኞች ማሕበር
  14. የቀድሞ ሠራዊት አባላት ማሕበር
  15. የተሰናባች ሠራዊት አባላት ማሕበር
  16. የአረጋውያን ማሕበር
  17. የባሕል ሕክምና አዋቂዎች/ባለሙያዎች ማሕበራት
  18. የሸማቾች ማሕበራት

 

ከነዚህ መካከል ይበልጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ ተብለው የሚታመኑት ላይ ልዩና አስቸኳይ ትኩረት ተሰጥቶ ጉትጎታውና ድጋፉ መጀመር ይኖርበታል፡፡

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop