በአማራ ህዝብ ላይ የተደነቀሩ ከፀጥታ ጋ የተያያዙ ችግሮችና መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦች – ከመሰረት ተስፉ

April 26, 2019
71 mins read

እንደሚታወቀው ባለፉት 27 አመታት የአማራ ህዝብ እንደህዝብ በቀደሙት ስርዓቶች ሳይጠቀም እንደተጠቀመ፣ ሳይገዛ እንደገዛ፣ ሳይጨቁን እንደጨቆነ፣ የበላይ ሳይሆን የበላይ ፣ ነፍጠኛ ሳይሆን ነፍጠኛና ትምክህተኛ ሳይሆን ትምክህተኛ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ ያደረጉ በርካታ ልሂቃን አሉ። በዚህም ምክንያት ይህ ህዝብ እንደህዝብ ትኩረት ተነፍጎትና አልፎም ግፍና መከራ ሲፈራረቅበት ቆይቷል። በዚህ ረገድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የስልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጀመሪያው የመፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ መጥፎ አጋጣሚ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ እንደሆነ ማንሳት ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብኛል። በማንነቱ ምክንያት እድሜ ልኩን ከኖረበት አከባቢ ሲፈናቀልም እንዲፈናቀል የተደረገው ደን ስለጨፈጨፈ ነው በሚል የተቀለደበትም የአማራ ህዝብ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ለዚህ የአማራ ህዝብ ስቃይ ደግሞ ኢህአዴግ ከፍተኛ የሆነ ድርሻ አለው። ኢህአዴግ ስል ደረጃው ይለያይ እንጅ ሁሉም የኢህአዴግ አመራር ማለቴ ነው። በእርግጥ የኢህአዴግን ስርዓት እንዳሻቸው በሁሉም አቅጣጫዎች ሲያሾሩ የነበሩት የህወሃት ሰዎች ዋና ደንጋይ ወርዋሪዎች መሆናቸው አልጠፋኝም። እዚህ ላይ እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ግን የህወሃት ሰዎች ስል የምጠቅሳቸው ስግብግብና ቀንደኛ የሆኑ የህወሃት አመራሮችን እንጅ ለትክክለኛ ዓላማ የሚታገሉ የህወሃት አባላትንና የአማራ ህዝብ ወንድምና እህት ሆኖ ለረጅም ጊዜ ሲሻው ተጋብቶና ተዋልዶ ሲፈልግ ደግሞ ተጎራብቶ የሚኖረውን ውዱን የትግራይ ህዝብ ማለቴ በፍፁም አይደለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የብአዴን፣ የኦህዴድ እንዲሁም የደኢህዴን ሰዎችም ቢሆኑ አንድም ዋና ደንጋይ ወርዋሪ ሆነው ከህወሃት ሰዎች ጋ ሰርተዋል ካልሆነም ደንጋይ ተሸካሚና አቅራቢዎች ሆነው አገልግለዋል። ስለዚህ የፍትህ ስርዓቱን ተከትሎ ተጠያቂነት ይስፈን የሚባል ከሆነ ደረጀው ሊለያይ ይችል እንደሆነ እንጅ ሁሉም የኢህአዴግ አመራር አባላት ተጠያቂዎች መሆናቸው አይቀርም። በዚህ ረገድ ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል እንዲሉ ተመርጦ ነፃ የሚወጣና ተመርጦ ጥፋተኛ ሊባል የሚችል ሃይል ወይም አካል አይኖርም።

ይሁንና ላለፉት ጥፋቶች ሁሉ አሁን ያለውን የፍትህ ስርዓት በመጠቀም ተጠያቂነትን የማስፈን መንገድ ኢትዮጵያ ላለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የሚሰራ መስሎ አልታይህ ብሎኛል። ምክንያቱም ማን አሳሪ ማን ታሳሪ፣ ማን መስካሪ ማን አስመስካሪ፣ ማን ፍርድ ሰጭ ማን ተከሳሽ ሊሆን እንደሚችል መለየት በማይቻልበት የህወሃት መራሹ የኢህአዴግ የተበለሻሸ “የስልጣን” ዘመን ለተፈፀመ ግፍና በደል ከዚሁ ከኢህአዴግ ውስጥ የወጣ ሃይል ፍትህ አሰፍናለሁ የሚል እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ “ያሸናፊዎችና የተሸናፊዎች” የቂም በቀል መወጣጫ ድራማ እንጅ እውነተኛና ስር ነቀል የሆነ ፍትህን ለማረጋገጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን ስለማይችል ነው። “አሸናፊዎች” ነን በሚሉና “ተሸናፊ” በሚሏቸው መካከል የሚደረግ “የፍትህ ሂደት” ደግሞ ባብዛኛው ህዝብ ተዓማኒነት ሊኖረው አይችልም። በነገራችን ላይ አሁን እያየን ያለነው አንዳንድ የፍትህ ስርዓቱን የመጠቀም ሂደት ሲታይ ልክ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው “አሸናፊ” ነኝ የሚለው አካል “ተሸናፊ” ነው በሚለው ሃይል ላይ እየወሰደ ያለውን ፖለቲካዊ ቂም በቀል የመወጣት እርምጃ የሚያመላክት እንጅ ትክክለኛና ፍትሃዊ የሆነ ሁሉንም ጥፋተኞች በእኩል የሚያይ ተጥያቂነትን የማስፈን ሂደት አይመስልም።
እዚህ ላይ አሁን ባለው የፍትህ ስርዓት ተጠያቂነትን ማስፈን አይቻልም ከተባለ ሌላ ምን አማራጭ ሊኖር ይችላል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በእኔ እምነት ሁለት አማራጭጮች አሉ ብዬ አስባለሁ። አንደኛው ከፍ ብዬ ለመግለፅ እንደሞከርኩት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከጥፋት ነፃ ሊሆን የሚችል የኢህአዴግ አመራር ሊኖር አይችልም ከሚል እሳቤ የሚነሳ ነው። በመሆኑም ሁሉም ለፈፀመው ጥፋት ከልብ ይቅርታ ጠይቆ በአዲስ መንፈስና ወኔ አገር ለመገንባት በቁርጠኝነት መነሳት ቢቻል ጠቃሚ ነው እላለሁ።

በይቅርታና እርቅ ሂደት የማይፈቱ ማናቸውም አይነት ጉዳዮች ካሉ ደግሞ መጭውን ምርጫ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ በማድረግ እንደ አዲስ በሚቋቋም ነፃና ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ስርዓት ተጠያቂነትን ማስፈን ሁለተኛው መንገድ መሆን አለበት ብየ አምናለሁ። በዚህ ረገድ እንደ አዲስ የሚመሰረቱት የህዝብ ተወካዮችና የክልል ም/ቤቶች ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባቸዋል። እነዚህ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና የክልል ም/ቤቶች በተለይ በዳኝነት የሚሾሟቸውን ዜጎች ልክ እንደስካሁኑ ለማለት ብቻ ሳይሆን እውነትም ከፖለቲካና ከሌሎች ተፅዕኖዎች ነፃ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል። በተቻለ መጠን ገለልተኛ ያልሆነ አንድም ሰው ቢሆን ተጣልፎ እንዳይገባ ምክር ቤቶቹ በየሰልጣን ወሰናቸው ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የት ሄድክ እንዳትሉኝ ብቻ። ያው ሃገራችን ውስጥ ያሉ ችግሮች ተዝቀው የማያልቁ በመሆኑ ሌላ ቦታ ረገጥኩ እንጅ የተነሳሁበትን ነጥብ አልረሳሁም። እንዳልኩት ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የአማራ ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጳያ ህዝብ ምናልባትም በከፋ ሁኔታ ብዙ ግፍና መከራ ደርሶበታል። ይህን እሳክሁን የተፈፀመ ግፍና መከራ አንድም በይቅርታና እርቅ መንገድ ካልሆነም ከመጭው ምርጫ በኋላ በሚቋቋም ነፃና ገለልተኛ የሆነ የፍትህ ሂደት እንዲታይ በማድርግ ችግሮችን መሰረታዊ በሆነ መንገድ መፍታት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
ይህም ሆኖ አሁንም ከአማራ ህዝብ ጋ የተፋጠጡ ከፀጥታ፣ ከህግ የበላይነት፣ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋ የተያያዙ በርካታ ችግሮች መኖራቸው አይቀርም። በ’ኔ አምነት እነዚህ ችግሮች በተናጠልም ሆነ በመሰናሰል የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ቢሆንም የቅደም ተከተል ጉዳይ ነውና ሌሎቹን አብይ ጉዳዮች በሌላ ጊዜ የምመለስባቸው ሆኖ በዚህ ፅሁፌ ላነሳ የፈለኩት ግን ከፀጥታ ጋ የተያያዙ ችግሮችንና መፍትሄ ይሆናሉ ብየ የማስባቸውን ነጥቦች ነው።
በዚህ የፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ አምስት መሰረታዊ ችግሮችን ማንሳት ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ።
1. በህወሃትና በአዴፓ ሰዎች መካከል ያለው ፍጥጫ:
ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው የህወሃት ሰዎች ከአስራ ሰባት አመታት የበርሃ ትግል በኋላ የሃገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ያላቸውን የትግል ልምድና በመሳሪያ የተደገፈ ጡንቻ ተጠቅመው በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው እንዲሁም በማህበራዊ ጉድዮች ላይ በርካታ ግፎች ፈመዋል። በተለይ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ በሙስናና እንዲሁም አድሎዋዊ በሆኑ አሰራሮቻቸው ሻምፒዮን ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በህወሃት ሰዎች አጋፋሪነት የተፈፀመ ግፍና መከራ ሊካድ የማይችል ሃቅ ቢሆንም በተለይ ደግሞ ከአማራ ክልል ጋ ባሉ አዋሳኝ ቦታወች የፈፀሙት ተጨማሪ ደባ የለየለት ስግብግብነታቸውን ያሳዩበት አሳፋሪ ድርጊት መሆኑ ግልፅ ነው። ገና ከበርሃ ትግላቸው ጀምረው የትግራይ ድንበር “ከአልውሃ ምላሽ” ነው የሚል ያልተፃፈ እቅድ ነድፈው ሲንቀስቀሱ ከቆዩ በኋላ ልክ የሃገሪቱን ስልጣን በተቆጣጠሩ ማግስት የወልቃይትን፣ የራያንና የሁመራን አካባቢዎች የኛ ነው ወደሚሉት አስተዳደር እንዲካለሉ አደረጉ። ይህን ሲያደርጉ በየአከባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር በግልፅ ይታወቃል። ግን የነዚህን ነዋሪዎች ጩኸት የሚሰሙ ጆሮዎች አልነበሯቸውም።
የሚገርመው ነገር የህወሃት ሰዎች የውሳኔዎቻቸው ሁሉ ማጠንጠኛ ህዝባዊነት እንደሆነ አድርገው አሳምረው በመናገር የሚያህላቸው የለም። በተግባር ግን እንደነሱ አይነት ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ፍጡር ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። አበክረው እንደሚገልፁት መመሪያቸው ህዝባዊነት ቢሆንማ ኖሮ ቦታዎቹን የኛ ነው ወደሚሉት አስተዳደር እንዲካለሉ ከማድረጋቸው በፊት በቦታው የነበሩ ነዋሪዎች ህዝበ-ውሳኔ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ሊያመቻቹላቸው በተገባ ነበር። አላማቸው ግን በስግብግብነት ላይ የተመሰረተ የግዛት መስፋፋት ስለነበር በቦታው ለነበሩ ነዋሪዎች ፍላጎት ምንም አይነት ደንታ አልነበራቸውም። ይህ በስግብግብነት የሰሩት ጥፋታቸው ነው እንግዲህ አሁን ላይ ፈንድቶ በነሱና በአዴፓ ሰዎች መካከል ለተፈጠረው ፍጥጫ መሰረት ሆኖ ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ተከባብሮ የመኖር ሂደት ላይ ጠባሳ እየጣለ የሚገኘው።
ለማንኛውም ከላይ በተገለፁት መልክ የሚታዩት የህወሃት ሰዎች ግትርነት፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊና አንባገነናዊ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው የአዴፓ ሰዎችም ቢሆኑ በቦታዎቹ ወደ ትግራይ መካለል ሂደት ላይ ምንም አይነት ጥፋት የለብንም በሚል ራሳቸውን ከደሙ ለማፅዳት እያደረጉት ያለው ጥረት አይናችሁን ጨፍንኑና እናሞኛችሁ አይነት የሞኝ ብልጠት እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል። በግልፅ ለመናገር ያህል ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የድርጅት አባላት እና የአከባቢው ነዋሪዎች የተጠቀሱት ቦታዎች ወደትግራይ የተካለሉበት ሂደት ፍትሃዊም ሆነ ህጋዊ አይደለምና ህዝበ-ውሳኔ መካሄድ አለበት ብለው ሲከራከሩ አሁን የለውጥ ሃዋሪያ ነን የሚሉት አብዛኛዎቹ የአዴፓ አመራር አባላት አንድም ትምክህተኞች ካልሆነም ግትሮች እያሉ ሲያሸማቅቁ እንደነበር ራሳቸው ያውቁታል። መቸም እነዚህ አመራሮች ወትሮም የድንበሩን ማካለል ኢፍትሃዊነትና ህገወጥነት በፅናት ታግለናል ብለው ደፍረው ለመናገር የሚዳዱ አይመስለኝም። እንዲያውም የሚታወቀው እነዚሁ አብዛኞቹ አመራሮች ወደስልጣን ማማ ለመውጣት በአድርባይነት ሲሽሎኮሉኩ እንጅ ድንበሮቹ የተካለሉበት መንገድ ትክክል አይደለም ብለው ሲከራከሩ አልነበረም። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ አሁን “ጊዜ ሰጠን” በሚል ሁሉንም ችግሮች ጠቅልለው ለህወሃትና ብአዴን ውስጥ ለነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ማሸከም ከግፍም በላይ ግፍ ነው።
ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ቡዙዎቹ የአዴፓ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት ውስጥ ተዋናይ ካልሆነም አጎብዳጅ ሆነው ቆይተው አሁን የህዝቡ ጥያቄ ሲበረታ ከሃላፊነት ለመሸሽ ሲሉ የጦርነት ፍጥጫ ውስጥ መግባት ለአማራ ህዝብ የሚያስከብረው ዘለቄታዊ መፍትሄ ይኖረዋል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ጦርነት በባህሪው የማያቀልጠው ነገር የለምና። ጦርነት ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን እንዲሁም ማህበራዊ ግንኙነቶችን ያቀልጣል። ከዚህ አልፎም የሰውን ህይወትም ሆነ ንብረት ያቀልጣል። በመጨረሻም የሁለቱን ወንድምማች ህዝቦች ህይወት ምስቅልቅል አውጥቶ እንዳልሆነ በማድረግ ለሌሎች መጫዎቻ የመሆንን እድል ይጋብዛል። ይህን ደግሞ ከህወሃትና ከአዴፓ ሰዎች በላይ ሊመሰከር የሚችል ሰው ይኖራል ብየ አላስብም። ስለዚህ በሁለቱ ህዝቦች መካከል አሸናፊ ሊኖረው የማይችል ጦርነት ሊቆሰቆስ ቀርቶ ሊታሰብም አይገባም። በመሆኑም የአዴፓ ሰዎች ሌሎች መፍትሄዎችን መቃኘት ይጠበቅባቸዋል።
በእኔ እይታ ከላይ ለተገለፅው ችግር እልባት በመስጠት ረገድ ለጊዜው የሚታየኝ መፍትሄ በነዚህ በተጠቀሱ አካባቢዎች ህዝበ-ውሳኔ ሊካሄድ ይችል ዘንድ ሰላማዊ፣ ፖለቲካዊና ህጋዊ መንገዶችን ሁሉ ተከትሎ መታገል ነው። ይህን መሰል ትግል በመምራት ደግሞ የአዴፓ ሰዎች ትልቁን ድርሻ መውሰድ አለባቸው የሚል የፀና አቋም አለኝ። የአዴፓ ሰዎች ይህን ትግል በሚመሩበት ጊዜ አሁን እያደረጉት ባለው ጣት የመቀሰር መንገድ ሳይሆን በረጋና በሰከነ እንዲሁም መርህንና ህግን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊሆን ይገባል እላለሁ። የእልህ መንገድ ሊታሰብ ከቶ አይገባም። የኢትዮጵያን አንድነት ለአንድ ቀን እንኳ ከማይመኘው ከኤርትራው መሪ ጋ በወዳጅነት ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው ለሚሉን የአዴፓ መሪዎች ከህወሃት ሰዎች ጋ መተክላዊ የሆነ ግንኙነት ለመመስረትና ለመገንባት የሚችሉትን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይከብዳቸዋል ብየ አላስብም። ስለዚህ በተጠቀሱት አከባቢዎች ያሉ ችግሮች በህዝበ-ውሳኔ ሊፈቱ ይችሉ ዘንድ የአዴፓ ሰዎች ምርጫ ሰላማዊና ሰላማዊ ሊሆን ይገባል እላለሁ። የህወሃት ሰዎችም ቢሆኑ ይህንኑ ሰላማዊ መንገድ ተከትለው ችግሩ እንዲፈታ ቢጥሩ ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች አብሮነትና ከዚህም አልፎ ለጠንካራ ኢትዮጵያ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸው መገንዘንብ ይገባቸዋል።
እዚህ ላይ ህዝበ ውሳኔ ሲባል የትኛው ህዝብ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ምክንያቱም ቦታወቹ ወደትግራይ ከተካለሉ በኋላ በታቀደም ሆነ በሌላ መንገድ እንደ አዲስ መኖር የጀመሩ ሰዎች አሉና ነው። በእኔ እምነት በህዝበ-ውሳኔው ሊሳተፉ የሚገባቸው ሰዎች ቦታዎቹ ወደትግራይ ከመካለላቸው በፊት ይኖሩ የነበሩ ብቻ ሊሆኑ ይገባል እላለሁ። በሌላ በኩል እነዚህን ሰዎች እንዴት ማወቅና መለየት ይቻላል የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። በርግጥ ሰዎቹን ለመለየት ብዙ ስራ ሊጠይቅ ይችላል። ይሁንና ካለው ጠቀሜታ አንፃር የወሰደውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ወስዶ ከዚህ በፊት የተደረጉ የህዝብ ቆጠራ ሰንዶችን፣ የግብር ከፋይ ደረሰኞችን እንዲሁም በየአካእባቢው የሚገኙ መዛግብቶችን በማገላበጥ የሰዎቹን ማንነት መለየት ይቻላል። ይህ የህዝብ ወሳኔ ፍትሃዊና ግልፅ በሆነ መንገድ ከተካሄደ በኋላ ነዋሪው አሁንም ባለሁበት መቀጠል እፈልጋለሁ የሚል ውሳኔ ካስተላለፈ ውሳኔው ሊከበርለት ይገባል። በአካባቢው ያሉ የአማራም ይሁኑ የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች አባላት ካሉ ህገመንግስታዊ መብታቸው ተጠብቆላችው መኖራቸውን ይቀጥላሉ። ህዝቡ በአብላጫ ድምፅ አማራ ክልል ጋ መካለል እፈልጋለሁ የሚል ውሳኔ ካሳለፈ ደግሞ ቦታዎቹ ወደአማራ ክልል ይካለሉና በቦታው የሚኖሩ የትግራይም ይሁኑ የሌላ ብሄር ብሄረሰቦች አባላት ህገመንግስታዊ መብታቸው ተጠብቆላቸው ይኖራሉ።
ይህ ይደረግ እያልኩ ያለሁት ህዝበ-ውሳኔ በተገቢው መንገድ ቢከወን ሁኔታዎችን ወደነበሩበት ስለሚመልሳቸው የተፈጠሩ ችግሮችን ሊያርም ይችላል የሚል እምነት አለኝ። ቅርብ ጊዜ የተፈጠረ ችግር በመሆኑም ማስረጃ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። በሌላ በኩል የወሰን ማካለሉ ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲከወን ያደረጉት የህወሃት ሰዎች አሁንም ቦታዎቹን እያስተዳደሩ በመሆኑ ራሳቸው የፈጠሩትን ኢፍትሃዊነት በራሳቸው ፍትሃዊ እንዲሆን ቢያደርጉት የበለጠ መተማመንን እንደሚፈጥር አያጠራጥርም።
በእርግጥ ህዝበ-ወሳኔው ተካሂዶም ቢሆን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ያለው አካል ካለ ታሪካዊም ሆኑ ሌሎች ማስረጃዎችን በማቅረብ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ተጠቅሞ ፍትህን መሻት ይችላል። በዚህ አግባብ የአዴፓ ሰዎች የሚመሩት የአማራ ክልል መንግስት የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የማቅረብ ፍላጎት ካለው አሉ የሚባሉትን ህጎች ሁሉ በአግባቡ በመጠቀም ጥያቄውን የማቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው። የአማራ ክልል መንግስት ይህን ማድረግ ይችል ዘንድ ግን በዘፈቀደ መንቀሳቀስ የለበትም። ይልቁንም ታሪካዊና ህጋዊ ሁኔታዎችን መሰረት ያደረገ ጥናት ማካሄድ ይኖርበታል። ጥናቱ ደግሞ የይስሙላ ሳይሆን ጥልቀት ያለውና ሁሉንም ሁኔታዎች ያብላላ መሆን አለበት። ይህ ሊሆን ይችል ዘንድ የታሪክና የህግ ምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው። ስለዚህ የአዴፓ ሰዎች የታሪክም ሆነ የህግ እውቀት ያላቸውን ምሁራን አስተባብረው ጥናቱ እንዲካሄድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የጥናቱ ውጤቶች እውነትም የሚባለውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚያስረዱ ከሆነ የአማራ ክልል መንግስት ሁለት አማራጮች አሉት።
የመጀመሪያውና እጅግ ተመራጩ መንገድ የጥናቱን ውጤቶች እንደማስረጃ በመያዝ ከትግራይ ክልል መንግስት ጋ በሰከነና በተረጋጋ እንዲሁም ሰላማዊ በሆነ መንፈስ ተነጋግሮ ችግሮቹ እንዲፈቱ ማድረግ ነው። ይህ መንገድ የትግራይ ክልል መንግስትን ማሳመን የማይችል ከሆነ ሌላው መንገድ አሁንም በጥናት ላይ የተመሰረተውን ማስረጃ በመያዝ ሌሎች ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የጠበቁ የመፍትሄ መንገዶችን መጠቀም አግባብነት አለው። በዚህ ረገድ ዋነኛ የሚባለው ህገመንግስታዊ የሆነ የመፍትሄ አካል የፌዴሬሽን ም/ቤት ነው። ሌሎች ህጋዊ መንገዶች ካሉም እነሱን መጠቀም አግባብነት አለው። ይህ ሆኖም የትግራይ መንግስት ለፌዴራል መንግስቱ ውሳኔዎች አልገዛም የሚል ከሆነ ይህን ተመርኩዞ የአማራ ክልል መንግስት ወደ አልተፈለገ ግጭት ሳይገባ የፌዴራል መንግስቱ የራሱን ውሳኔዎች እንዲያስፈፅም ግፊትና ትግል ማድረግ ይኖርበታል። ይህን በማድርግ ፍርሃትን ሳይሆን ስልጡንነትን ማሳየት ይቻላል።

2. በአማራ ክልል በኩል ካለው የኢትዮ – ሱዳን ድንበር ጋ ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ:
በዚህ ዙሪያ በርካታ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ ይታያሉ። ብዙ ሰዎች በአማራ ክልል በኩል ያለው የኢትዮጵያ ድንበር የሱዳን መጫወቻ ሆኗል የሚል ስሞታ ያቀርባሉ። የአዴፓ ሰዎችም እንዲሁ ሱዳን ታሪካዊ ዳራውን ባልጠበቀ መንገድ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ያለውን ድንበር ጥሳ ገብታለች የሚል ቅሬታ እያቀረቡ እንዳለ እየሰማን ነው።
የአዴፓ ሰዎች አሁን ላይ ይህን ይበሉ እንጅ ጉድዩን አስመልክቶ የተለያዩ አካላት እሮሮ ያሰሙ በነበረበት ወቅት ትንፍሽ ለማለት እንኳን አልደፈሩም ነበር። እንዲያውም በዚህ ረገድ ድንበራችን አሳልፈው ለሱዳን እንዲሰጥ ወስነዋል በሚል ይወቀሱ የነበሩት የአሁኑ የአዴፓ ሊቀመንበር እንደነበሩ እናስታውሳለን። ከዚህ አንፃር የአሁኑ የአዴፓ መሪ በወቅቱ ሁኔታውን አጣርተው ለህዝብ ለማቅረብ ምን ገደዳቸው ተብለው ቢጠየቁ ውሃ የሚቋጥር መልስ የሚሰጡ አይመስለኝም። ይህ በሆነበት ሁኔታ እኛ ከደሙ ንፁህ ነን፤ ችግሩን የፈጠሩት ሌሎች አካላት ብቻ ናቸው ብሎ ራስን ከተጠያቂነት ለማውጣት መሞከር ሁሌም ገዥው ሁኔታ እውነት ሳይሆን “የዘመን ባለቤት” ነኝ ብሎ ማሰብ እንደሆነ የሚያሳብቅ ነገር ያለው ይመስለኛል። በእኔ እምነት ይህ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት ጠቃሚ ነው ብየ አላስብም። ከዚህ ይልቅ ገንቢና አብሮነትን ሊያዳብር የሚችለው አብይ ቁመነገር በመጀመሪያ የራስን ጥፋት በግልፅ ማየትና በቅንነት ለማረም ጥረት ማድረግ ነው። ይህን በማድረግ ሌላውንም መርህ ላይ በመመስረት በፈርጅ በፈርጁ መታገል ደግሞ መግባባትን ፈጥሮ ለህዝብና ለሃገር የሚጠቅም ስራ መከወን ያስችላል። ካለበለዚያ እሽቅድድሙ ለራስ ጥቅምና ዝና መሯሯጥ ይሆንና ሌላ የባሰ ጥፋት ፈፅሞ የሃገርንም ሆነ የህዝብን ህልውና አደጋ ላይ በመጣል የታሪክ ተወቃሽ ሆኖ ማለፍን ያስከትላል።
በዚህም አለ በዚያ ግን የድንበሩ “በሱዳን የመጣስ” ጉዳይ የአማራን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ መንግስት የሚያሳስብና የሚያውክ በጣም ትልቅ የሆነ አጀንዳ ነው። ስለዚህ እንደቀላል ሊታይ የሚገባው ስሞታ አይደለም። ምክንያቱም የአገር ሉአላዊነት ለምንም አይነት ድርድር የሚቀርብ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በአከባቢው በሚኖሩ ዜጎች ተረጋግቶ የመኖር መብት ላይም አሉታዊ ተፅእኖው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ስለሚገመት ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ በተጠቀሰው አከባቢ ያለው ሁኔታ መሰረታዊ መፍትሄ የሚያስፈልገው ከባድ የፀጥታ ችግር ነው ማለት ይቻላል።
ይህን ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ አዴፓ እየመራው ያለው የአማራ ክልላዊ መንግስት ተነሳሽነቱን ወስዶ በአከባቢው ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት እንዲካሄድ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህን ጥናት በታሪክና በህግ እንዲሁም በህዝብ አሰፋፈር ጥልቅ ሙያ ያላቸው ዜጎች እንዲያካሂዱት ቢደረግ ውጤቱ የጎላ ይሆናል። እነዚህ ዜጎች ቢችሉ በትርፍ ጊዚያቸው ያለምንም ክፍያ ካልቻሉ ደግሞ ተከፍሏቸውም ቢሆን ከሱዳን ድንበር ጋ ተያይዞ ያለውን ችግር ከስር መሰረቱ ጀምረው ከታሪክና ከህግ አንፃር እየቃኙ እንዲያጠኑት ማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ይህን ጥናት መሰረት በማድረግ እንደተባለው ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር መጣሷን መገንዘብ የሚቻል ከሆነ የአማራ ክልል መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋ ሊያደርግ ከሚችለው ሰላማዊ ድርድር በተጨማሪና ምን አልባትም በተጠናከረ መንገድ ጉዳዩን ለፌዴራል መንግስቱ ማስረዳትና ፌዴራል መንግስቱም አምኖ የራሴ ጉዳይ ነው እንዲል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
የፌዴራል መንግስት በበኩሉ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ጉዳይ የአለም አቀፍ ህጎችን መሰረት አድርጎ ቢቻል በድርድር ካልሆነ ደግሞ በህግ አግባብ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህ ሆኖ የሱዳን መንግስት ከያዛቸው የኢትዮጵያ ቦታዎች የማይለቅ ከሆነ ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል መብቷን ተጠቅማ የምታምንበትን ህጋዊ አፀፋዊ ርምጃ መውሰድ የምትችልበት ሁኔታ ይኖራል። በዚህ ሂደት የአማራ ክልል መንግስት ሊኖረው የሚገባው ሚና ፌዴራል መንግስቱ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠው በሰላማዊ መንገድ መታገል ሊሆን ይገባል። ይህን በተመለከተ የአማራ ክልላዊ መንግስት ሊገነዘበው የሚገባ አብይ ጉዳይ አለ። ይህም ምንጊዜም ቢሆን ፍትሃዊ የሆነ ነገርን መከተል ሽንፈት አለመሆኑንና እንዲያውም ድልን መቀዳጀት የሚያስችል ቀና መገድ መሆኑን ነው። የአማራ ክልል መንግስት ይህን ፍትሃዊ የሆነ መንገድ ስቶ መብቴን አስከብራለሁ በሚል ዘው ብሎ ጦርነት ውስጥ የሚገባ ከሆነ በጦርነቱ ሊደርስበት ከሚችለው ጉዳት በተጨማሪ ዘላቂ የሆነ ሌላ ጠላት ሊያፈራ የሚችልበት ሂደት ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባዋል።
3. በክልሉ ውስጥ ከሚኖሩ አንዳንድ ከአማራ ብሄር ውጭ ካሉ ብሄርሰቦች ጋ ያለ እሰጥ አገባ:
ይህን ጉዳይ በተመለከተ እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን እውቅና የሰጠ ክልል ጥራ ብባል ከደቡብ ቀጥሎ ያለው ጥሪዬ አማራ ክልል እንደሚሆን አልጠራጠርም። ይህም ሆኖ ግን በአንዳንዶቹ ብሄረሰቦች ውስጥ ያሉ ሰዎች ጥቅማችን አልተከበረም ወይም ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥያቄያችን በሚገባ አላስተናገደም በሚሉ ምክንያቶች እየተፈጠሩ ባሉ ግጭቶች የሰው ህይወት እየተቀጠፈና ንብረት እየወደመ ከዚህ በላይም በክልሉ ነዋሪዎች መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አብሮ የመኖርና የመቻቻል ታሪክ ላይ ትልቅ ጠባሳ እየጣለ እንዳለ እየተመለከትን ነው።
ይህ ከሚሆን ይልቅ ጥያቄዎቹ ሲቀርቡ ቅንነት በተሞላበትና ክሴራ ነፃ በሆነ መንገድ ቢሆንና የሚቀርቡ ጥያቄዎች ሁሉ መርህን መሰረት ባደረገ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት እንዲሁም ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ መልስ እንዲያገኙ ቢደረግ ችግሮቹ ከመሰረታቸው ሊቀረፉ የሚችሉበት እድል በጣም ሰፊ ነው። በዚህም መሰረት ጥያቄዎቹ፣ ሃሳቦቹ ወይም ችግሮቹ ሲቀርቡ ከሁለቱም ወገን ያሉ ምሁራን ያገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶችና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት እንዲያጠኑት ተደርጎ የመነሻ ሃሳብ ቢቀርብና ጥናቱን መሰረት በማድረግ ደግሞ የክልሉ ም/ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት ቢደረግ የተሻለ ይሆናል። እነዚህን አግባቦች ተከትሎ ክልሉ መፍታት ባይችል ወይም ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር እንኳ ወደ ቃላት ስንዝርና ንትርክ ከመሯሯጥ፤ እንዲሁም አጥፊና ለማንም ጠቃሚ ወዳልሆነ ግጭት ውስጥ ከመግባት ይልቅ የክልሉንም ሆነ የፌዴራሉን ህገመንግስታዊ ስርዓቶች በተከተለ አግባብ ጥያቄዎች ቢቀርቡና መፍትሄ የመሻት አቅጣጫን መከተል ቢቻል ሂደቱ ሁሉ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል።
ከዚህ ጎን ለጎን የመፍትሄው አካል ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችንም ልጨምር። አንደኛ በማንኛውም ጊዜ አንዱ የሌላውን ስሜት ሊጎዱ የሚችሉ ፀብ አጫሪ የሆኑ ንግግሮችን እንዳያደርግ የሚከለክል ደንብ መመሪያና አሰራር ቢኖር ሁኔታዎች እንዳይጋጋሉ ያግዛል። እነዚህን ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች ተላልፈው የሚገኙ አካላትም ይሁኑ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ ቢደረግ ደግሞ የበለጠ ይሆናል።
ሁለተኛ በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚቀርቡ ጥያቄዎችና ሃሳቦች የተለያየ ስም እንዳይሰጣቸው ቢደረግ ችግሮች እንዳይሳቀሉ ሊያደርግ ይችላል። ይህም ማለት የሆነ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም የህብረተሰብ ክፍል ያሳከከውን ጥያቄ ወይም ሃሳብ ባነሳ ቁጥር ከጀርባ እገሌ አለ፣ ሌላ ገፊ ምክኒያት ሊኖር ይችላልና የመሳሰሉ መላምቶች እየተደረደሩ ጥያቄ ያቀረቡትን አካላት እከክ እንዳይድን እንዲያውም እንዲነፈርቅ የሚያደርግ አካሄድ ሊገታ ይገባል ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ገንቢና ሊያቀራርብ የሚችለው ተግባር ጥያቄዎችን ከማንም ጋ ሳያገናኙ ራሳቸውን አስችሎ (On their own merits) ማየትና መልስ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነው። በዚህ መንገድ ተሂዶ እውነትም ችግሮች ካሉ ቀና፣ በጥናትና በመርህ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን መስጠት ተገቢ ይሆናል። የተባሉት ችግሮች ከሌሉ ደግሞ አለመኖራቸውን በሚያሳይ መንገድ በመግለፅ ሁሉም በተገቢው መንገድ እንዲረዳው ማድረግ መተማመንን ይጨምራል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። ከኋላ ገፊ ሃይል ወይም አካል አለ የሚል ጥርጣሬ ቢኖር እንኳን ጥናት አድርጎ በተጨባጭ ማስረጃ በማስደገፍ ለህዝብ መግለፅ እንጅ በስሜት መፈረጅ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዳልሆነ መረዳትም ይጠቅማል። አሁንም በዚህ ረገድ ችግሩን ለመከላከል አሰራር ቢዘረጋለት የተሻለ ይሆናል የሚል ሃሳብም አለኝ።
4. የስርዓት አልበኝነት መበራከት፡
ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ቀበሌም ሆነ ክልል ላይ ስርዓት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ስርዓት ከሌለ ሰላም የለም። ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት አይቻልም። ስርዓት በሌለበት አከባቢ ህግ አይከበርም። የህግ አለመከበር በበኩሉ መተራመስን ይፈጥራል። ይህ መተራመስ ደግሞ እንደሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ መኖርን ያስከትላል። ከሰወነት የወጣ ባህሪ ደግሞ አገርን በታትኖ ህዝብን ያፋልሳል። የዚህ አይነቱ የስርዓት አልበኝነት ችግሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተከሰቱ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ሆኗል። አማራ ክልልም ቢሆን በተለያየ መንገድ የሚገለፁ የስርዓት አልበኝነት ችግሮች እየተከሰቱ ነው። አንዳንዴ ሰዎች በደቦ ተገደሉ የሚል ዜና ሲነገር እንሰማለን። ሌላ ጊዜ ንብረት ዝውውር እንዳይኖር በደቦ እገዳና ዘረፋ እየተደረገ መሆኑን የሚገልፁ ወሬዎች ይበረክታሉ። ከዚህ አልፎም የፍትህ አካላት በደቦ ጫና ምክንያት ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ ሲደረጉና በዚህም ዜጎች መብቶቻቸውን ሲነፈጉ እንታዘባለን። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ግን እነዚህን የመሳሰሉ የደቦ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ የክልሉ የመንግስት አካላት አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ማለፋቸው ነው። ችግሮች በዚህ ከቀጠሉና በአስቸኳይ ካልታረሙ ሁኔታዎች ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ይሆኑና የክልሉንም ሆነ የሃገሪቱን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ስጋት ላይ መጣላቸው አይቀርም። ስለዚህ የአዴፓ ሰዎችም ሆኑ እነሱ የሚመሩት የአማራ ብሄራዊ ክልልዊ መንግስት በህግና ስርዓት መከበር ላይ የማያወላውል አቋም ሊወስዱ ይገባል። በማስከተልም ማንም ይሁን ማን ስርዓትንና ህግን ያልተከተለ መንገድን ሲመርጥ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን መደረግ ይኖርበታል። አሁን ርካሽ የፖለቲካ አላማን ለማሳካት ሲባል ስርዓት አልበኝነትን መደገፍ ካልሆነም አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ወደማይቆጣጠሩት ሁኔታ ያደርስና በመጨረሻም “በእንቁላሉ በቀጣሁት” እንዲሉ አይነት ፀፀት እንዳያስከትል ጥብቅ የሆነ ግንዛቤ መውሰድ ይጠይቃል።
5. በአዴፓና በኦዴፓ ሰዎች መካከል ያለው መርህን መሰረት ያላደረገ የሚመስል ግንኙነት:
እንደሚታወቀው ኦዴፓ የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን ለመያዝ የነበረውን ፍላጎት ተግባራዊ ለማድረግ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ጨምሮ በጣም በርካታ በሚገባ የተጠኑና የታቀዱ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል። ከነዚህ የኦዴፓ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ከአዴፓ ጋ የመሰረተው ግንኙነት ነበር። ይህ ከተለመደው የኢህአዴግ ባህል ያፈነገጠ የሚመስል የቡድነኝነት እንቅስቃሴ አላማው መርህን መሰረት ያደረገ ሳይሆን በወቅቱ አፋኝ፣ አንባገነንና ሙሰኛ ከሆኑት የህወሃት ሰዎች ተፅዕኖ ለመላቀቅ ማንኛውንም መንገድ የመከተል ስልታዊ ግንኙነት ነበር ማለት ይቻላል።
እንደታሰበዉም የሁለቱ ቡድኖች ጥምረት የህወሃትን ሰዎች የጀርባ አጥንት ሰብሮ መቀሌ ላይ እንዲመሽጉ በማድረግ የኦዴፓ ሰዎች የፌዴራል መንግስቱን ስልጣን እንዲቆጣጠሩ አስቻለ። የአዴፓ ሰዎችም ይህን ንግስና አሜን ብለው ተቀበሉ። ከዚህ በኋላ የኦዴፓ ሰዎች ዋና ዋና የሚባሉ የፌዴራል መንግስት ተቋማትን ከመቆጣጠር ጀምሮ በርካታ ኢ-ፍትሃዊ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መግባት ጀመሩ። ይህ ጉዳይ ቀድሞውንም ቢሆን በመርህ ላይ ያልተመሰረተውን የአዴፓና የኦዴፓ ሰዎችን ግንኙነት ማሻክሩ አልቀረም።
በዚያ ላይ ደግሞ ኦዴፓ ውስጥ ያሉ ጽንፈኛ የሆኑና “ዘመኑ የኛ ነው” የሚሉ ሃይሎች በአንድ በኩል ኦነግ ደግሞ በሌላ በኩል በደኦዴፓና በአዴፓ ሰዎች መካከል ያለው ማንኛውም ግንኙነት የሚያስደስታቸው አይመስልም። ምክንያቱም ከዚህ ቀደምም አንዳንድ ፀሃፍት በተደጋጋሚ እንዳሉት እነዚህ ኦዴፓ ውስጥ ያሉ ጽንፈኛ የሆኑ ሃይሎች የአዴፓን ሰዎችና ምን አልባትም የአማራን ህዝብ ከተለያየ አቅጣጫ በመነሳት እንደሚጠራጠሩት ይታወቃል። ይህ በመሆኑም እነዚህ ኦዴፓ ውስጥ ያሉ ፅንፈኞች አዴፓንም ሆነ ሌሎች አማራን እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ብሎም የአማራ ሃዝብ እንደህዝብ ተዳክሞ ቢያዩት እንደሚመርጡ መገመት ይቻላል። ይህ ሊሆን እንዲችል ደግሞ እነዚህ ኦዴፓ ውስጥ ያሉ ፅንፈኛ የሆኑ ሃይሎች ህወሃት ውስጥ ካሉ ፅንፈኞች ጋ ዞረው ዞረው ግንኙነት ለመመስረት የሚፈልጉበት ሁነታ ሊኖር እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም። እነዚህ ሃይሎች ከተሳካላቸው በጋራ ሆነው ተጀምሮ ያለው የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነት እንዳይቀጥል ለማድረግ መሞከራቸው አይቀርም። በትግራይና በአማራ ህዝቦች መካከልም መቃቃር እንዲሰፋ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ይህ ደግሞ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ለአማራ ህዝብ የፀጥታ ችግር መፍጠሩ አይቀርም።
አንዳንድ የአዴፓ እና ብብዛት ደግሞ የአብን ሰዎችም ቢሆኑ ከኦዴፓ ሰዎች ጋ ያለውን ግንኙነት ሊያሻክርና እዛው ሳለም በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያዛባ አልፎም የፀጥታ ችግር መነሻ ሊሆን የሚችል አስተሳሰብ በተለያየ አግባብ እያራመዱ እንደሆነ እየተስተዋለ ነው። አንዳንዱ ከኛ በላይ ላሳር የሚል መፈክር የሚያነሳበት ሁኔታ አለ።። ለምሳሌ ከኛ በላይ ኢትዮጵያዊ ላሳር ነው፤ ትምክህተኛና ነፍጠኛ መሆናችን ያኮራናል የሚሉ የአብን አመራሮች ሞልተዋል። የአብን አመራሮች ይህን ሲሉ የአዴፓ አመራሮች በፅናት አለመንቀፋቸው የሚያሳየው እነሱም በአስተሳሰቡ አለመጠለፋቸውን ማረጋገጥ የማይቻል መሆኑን ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የአብን አመራሮች አይን ያወጣ ትምክህትና የአዴፓ ሰዎች ዝምታ የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መርህ መጓደል እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ይህ አይነት አስተሳሰብ ደግሞ አንድም ቀድሞውንም በአማራ ህዝብ ላይ ጥርጣሬ ያላቸውን ኦዴፓ ውስጥ ያሉ ፅንፈኞች እንዲሁም ኦነግን የበለጠ ያስደነብራል፤ ሌላም እስካሁን እንኳ ጥርጣሬ ያልነበራቸው ካሉም እነሱኑ ጨምሮ ጥርጣሬ ውስጥ ማስገባቱ አይቀርም።
በሁሉም መመዘኛ ሲታይ የአዴፓ ሰዎች ከኦዴፓዎች ጋ ያላቸውን ተገቢ ያልሆነ መተሻሸት፣ መላላስና መፋተግ እንደቀላል ሊያዩት አይገባም። ምክንያቱም የዚህ መተሻሸትና መፋተግ ጦስ የአማራን ህዝብ ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ማወኩ የሚቀር አይሆንም። ስለዚህ የአዴፓ ሰዎች ግልፅና የማያሻሙ የመፍትሄ ሃሳቦች መንደፍ አለባቸው ስል እመክራለሁ። በእኔ እይታ የአዴፓ ሰዎች ከኦዴፓዎች ጋ እያደረጉት ያለውን መተሻሸትና መገፋፋት በተመለከተ ከዚህ በታች ባለው የፅሁፌ ክፍል የማስቀምጣቸው የመፍትሄ ሃሳቦች እዛው ሳሉም ከሌሎች አካላት ጋ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶችች ቢጠቀሙባቸው ጥቅም ይኖራቸዋል ብየ አስባለሁ።
በመጀመሪያ ደረጃ የአዴፓ ሰዎች ከኦዴፓም ይሁን ከሌሎች አካላት ጋ ያሏቸውን ግንኙነቶች መምራት ያለባቸው በተወሰኑ የስራ ሃላፊዎች መልካም ፈቃድ ሳይሆን ፍትሃዊ በሆነ ህግ፣ በመርህና በተቋም ሊሆን ይገባል። ግንኙነቱ ፍትሃዊ በሆነ ህግ፣ በመርህና በተቋም ላይ የተመሰረተ የሚሆነው ደግሞ አንድም እስካሁን እንደነበረው የኢህአዴግ አባል የሆኑ አራቱም ፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ መጥተው አሁን ባለው የኢህአዴግ ፕሮግራም፣ ህገደንብና አሰራር ተገዝተው መቀጠል ሲችሉ ነው። አሁን ያለው ህገደንብና አሰራር አልተመቸንም የሚሉ ከሆነ ደግሞ አሁንም በጋራ ውይይት ማሻሻያ በማድረግ ተስማምተው ስራዎቻቸውን መስራት ሌላው መንገድ ነው። ካልሆነ በግልፅ ተለያይተው ግን ደግሞ መንግስቱን ለመምራት ተስማምተው እስከሚቀጥለው ምርጫ መቆየት አንድ አማራጭ ነው። ይህን ሁሉ ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ደግሞ እነሱም በየፊናቸው ሄደው ጊዚያዊ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም በሩን መክፈት ይገባቸዋል የሚል እምነት አለኝ።
ኢህአዴግን አፍርሰን አዲስ አገራዊ ፓርቲ እንመሰርታለን የሚሉት እውነት ከሆነም በግለሰቦች ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አባል ፓርቲዎችና አብዛኛውን የየፓርቲዎቻቸውን አባላት አሳምነው ያድርጉት። ለዚህ ደግሞ አዲሱን ፕሮግራማቸውን፣ ህገደንባቸውንና የአሰራር መመሪያቸውን ይቅረፁ። ይህም ቢሆን ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ የሆነ፣ አብዛኛውን የድርጅቶቻቸውን አባላት የሚያሳትፍና በመርህ ላይ የተመሰረተ ቢሆን ይመረጣል። ይህ ሆኖ በሚቀጥለው ምርጫ ካሸነፉ አሁንም በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነታቸውን እያዳበሩ ይቀጥሉ። ካላሸነፉም መርህን መሰረት አድርገው ለሚቀጥለው ዙር ምርጫ ይስሩ። የሚያዋጣው ይሄው ነው። ከዚህ ውጭ በአምስት ወይም በስድስት ሰዎች መካከል ያለ ግንኙነት የፓርቲውን/ የግንባሩን ዘላቂነት ሊያረጋግጥ አይችልም። መርህ በሌለው የግለሰቦች ዲስኩርም ረዘም ላለ ጊዜ አገር መምራት የሚቻል አይመስለኝም።
የአዴፓ ሰዎች ከኦዴፓም ይሁን ከሌሎች አካላት ጋ ሊኖራቸው ይገባል የሚባለው መርህን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ቀጣይነት ሊኖረው ይችል ዘንድ ደግሞ ሁኔታዎችን እየተከታተለ የመፍትሄ መንገድ ሊያሳይ የሚችል ሃሳብ አፍላቂ ክንፍ (Think Tank) ቢኖራቸው እጅግ በጣም ተመራጭ ይሆናል። ይህ ሃሳብ አፍላቂ ክንፍ መዋቀር ያለበት በዋነኛነት በወጣት ምሁራን ሆኖ የሌላውን ህብረተሰብ ጥንቅርም ግምት ውስጥ ያስገባ ቢሆን ይመረጣል እላለሁ። የዚህ ክንፍ ተልዕኮ መሆን ያለበት ከላይ እንደተጠቀሰው የአዴፓ ሰዎች ከማንኛውም አካል ጋ የሚያደርጉት ግንኙነት መርህን መሰረት ያደረገ መሆኑን መከታተልና መዛነፎች ሲኖሩ በጥናት ላይ የተመሰረቱ የማስተካከያና የመፍትሄ ሃሳቦች ለአመራሩ ማቅረብ ይሆናል። ይህ ሃሳብ አፍላቂ ክንፍ እዛው ሳለም ወቅታዊ የሆኑ ክልላዊና ሃገራው ጉዳዮችን እየተከታተለ ጥልቅ ጥናት በማድረግ ለአመራሩ የሃሳብ ግብዓት ሊያቀርብ ይችላል። ይህ ሂደት አመራሩ ያለበትን አርቆ የማሰብና አስፍቶ የማየ ችግሮች ለጊዜውም ቢሆን የመቅረፍ እድሉ ሰፊ ነው።
እነዚህና ሌሎች ችግሮች በቋሚነት ሊቀረፉ የሚችሉት ግን አዴፓዎች ያለባቸውን የአቅም ውስንነት አስወግደው ስልታዊም ይሁን ስትራቴጅያዊ የሆነ አመራር መስጠት ሲችሉ ብቻ ነው። ይህ ይሳካ ዘንድ ደግሞ በስራቸው የተመሰገኑ፣ በስነምግባር የታነፁ፣ ለመርህና ለመተክላዊ አሰራር የሚቆሙ፣ በህዝቦች እኩልነት በፅናት የሚያምኑና በአጠቃላይም ለሌሎች አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣት ምሁራን፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በአዴፓ አባልነት መመልመልና መደራጀት ይኖርባቸዋል። በዚህ መንገድ የሚመለመልና የሚደራጅ አባል እዛው ሳለም የአመራሩን አቅም በማጎልበት አማራ ክልል ውስጥ ያሉ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችንና አፍራሽ አመለካከቶችን በማረቅ ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ቀድሞ ለማስወገድ ያግዛል።
ሌላው መፍትሄ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ማጎልበት ነው። በርግጥ ብሄርተኝነት በጥሬው ሲታይ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ይሁን እንጅ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ በቀላሉ ሊጠፋ የሚችል ተቋም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አብይ ጉዳይ ብሄርተኝነት በምን መልኩ ቢያዝ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ በጎ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል የሚለው ነው። ለዚህም ነው ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት መጎልበት አለበት የሚል ጠካራ እይታ ያለኝ፡
ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ማለት ለራስ ጥቅም ብቻ መቆም አይደለም። ሁሉም ለኔ፣ የኔና ከኔ በላይ ላሳር ማለትም ሊሆን አይችልም። ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ማለት ለራስ ፍትሃዊና አግባብ ያለው ጥቅም በመቆም የሌሎቹም ፍትሃዊና ተገቢነት ያለው ጥቅም እንዲከበርላቸው መታገል ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ሲባል የራስን ተገቢ የሆነ ጥቅም ከማስከበር አልፎ ያለአግባብ መጠቀም የሚፈልግን የራስን ብሄር አባል አምርሮ መታገልና ማስተካከል ማለት ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ መከባበርና አብሮ መኖር እየጎለበተ መምጣቱ አይቀርም። በዚህ መንገድ እየጎለበተ የሚሄድ መከባበርና አብሮነት ሲኖር መዋሃዱ ይጠነክርና አገራዊ እሳቤው የቀደመ ቦታ እንዲሰጠው ያደርጋል። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን የማጎልበት ያለማጎልበት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የአዴፓ ሰዎች ሊገነዘቡት ይገባል። ይህን ተገንዝበው በውስጣቸውም ይሁን በህዝቡ ውስጥ ያለ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ የብሄርተኝነት ስሜት አመለካከት እንዲወገድ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። አዴፓዎች ከራሳቸው አልፈው ሌሎቹ አጋሮቻቸውም በዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው ጠንካራ ትግል ሊያደርጉ ይገባል። ይህን በማድረግም በክልሉ ሊፈጠር የሚችልን የፀጥታ ችግር ማክሰም ካልሆነም መቀነስ ይቻላል።
በአጠቃላይ ሲታይ የአማራ ህዝብ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተደቀኑበት የፀጥታ ችግሮች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል። እነዚህን ችግሮች የመፍታት ያለመፍታት ጉዳይ ደግሞ የአማራን ህዝብ ህልውና የማስቀጠል ወይም ያለማስቀጠል ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ችግሮችን ለመፍታት መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች አንዱ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን በሚያጎለብት መልኩ ህጋዊ፣ ተቋማዊና በመርህ ላይ የተመሰረተ አሰራርን ማዳበር ነው። ምክንያቱም በግለሰብ የስራ ሃላፊዎች መልካም ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ አሰራር ዘላቂነት ሊኖረው አይችልምና ነው። እነዚህ ግለሰብ አመራሮች እንደሰው ሁሉ በሆነ ምክንያት ቢፈራቀቁ አገር እንዳይሆኑ ልትሆን የምትችልበት እድል በጣም ሰፊ ነው። ለዚህም ነው አዴፓዎች ከኦዴፓዎችም ጋ ሆነ ከህወሃቶችና ከደኢህዴኖች ብሎም ከሌሎች ማናቸውም አካላት ጋ ያላቸው ግንኙነት ህጋዊ፣ ተቋማዊና በመርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድርገ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ሊጠብቁና ሊያስጠብቁ ይገባል የሚል ጠንካራ እምነት ያለኝ።
ለዚህ አጋዥ የሆኑ ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድም እጅግ ተመራጩ መንገድ ነው። በዚህ ረገድ ሊጠቀስ የሚችለው አንዱ ጉዳይ ከክልሉ ውጭም ይሁን በክልሉ ውስጥ ያሉ በተለይም ወጣት ሙህራን ነፃና ግልፅ በሆነ መመዘኛ ወደ አዴፓ እንዲቀላቀሉና እንዲደራጁ የማድርግ አስፈላጊነት ነው። ይህ የተማረ የወጣት ሃይል ወደ ድርጅቱ ተቀላቅሎ በመደራጀት እውቀትና ክህሎቱን ለህዝብ ጥቅም እንዲያውል ቢደረግ ባጭር ጊዜ ውስጥ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም የወጣት ሃይሉ በብዛትና በጥራት ድርጅቱን የሚቀላቀል ከሆነ ይህ ሃይል ሙህራዊ እውቀቱንና ክህሎቱን ተጠቅሞ አሰራሮች ሁሉ ተቋማዊና በመርህ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይሆንም። ይህ እዛው ሳለም የክልሉን ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት የማስጠበቅ ሚናው ከፍተኛ ነው።
ተጨማሪ አጋዥ እርምጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ደግሞ ጎላ ጎላ ያሉ ውሳኔዎች በሚተላለፉበት ጊዜ ጥልቅ የሆኑ የጥናት ውጤቶችን መሰረት አድርገው ቢሆን ከተለያዩ አካላት ጋ የሚያግባባ ስራ መስራት ይቻላል። ጥናቱን ለማድረግ የሚቋቋመው ሃይል ሙህራንን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ቢሆንና ተልዕኮውም ጊዜያዊ ቢሆን ይመረጣል። ይህ አካሄድ ከሱዳን፣ ከህወሃትና ከኦዴፓ ሰዎች እንዲሁም አማራ ክልል ውስጥ ካሉ የብሄረሰብ አባላት ጋ ያለውንና ሊኖር የሚችለውን ከልክ ያለፈ መፋተግ ሊቀንሰው ካልሆነም ሊያስወግደው ስለሚችል ለሰላምና ፀጥታ መከበር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው።
በሌላ በኩል የአማራን ህዝብ ተገቢና ፍትሃዊ የሆኑ መሰረታዊ ጥቅሞች በቀጣይነት ለማስጠበቅ ይቻል ዘንድ ቅድመ ጥናት እያደረገ ለአዴፓ ሰዎችም ሆነ ለክልሉ አመራሮች በግብአት መልክ የሚያቀርብ ቋሚ የሆነ የጥናት ክፍል (Think Tank) ቢኖር አመራሩ የተጠናወተውን ስትራቴጅያዊ በሆነ መንገድ የማሰብ (Strategic Thinking) ከፍተኛ እጥረት ሊያቃልል ይችላል። በዚህ ረገድ ጥናት የሚደረግበት አንዱ ዘርፍ ሰላምን የማስፈን ጉዳይ ስለሚሆን የጥናት ክፍሉ ፀጥታን በማስከበር ረገድ ሊጫወተው የሚችለው ሚና የጎላ መሆኑ አይቀርም።
እነዚህ ከላይ የተገለፁት የመፍትሄ ሃሳቦች ሁሉም ተገምደውና ተሰናስለው ተከታታይነትና ቀጣይነት ባልው መልኩ የሚፈፀሙ ከሆነ የአማራ ህዝብ የተጋረጡበትን የፀጥታ ችግሮች ለማለፍ የከፋ መላላጥ አይገጥመውም የሚል አጠቃላይ እምነት አለኝ።

Previous Story

ይቅርታ እና ይቅር ባይነት – በዲያቆን ዳንኤል ክብረት

Next Story

ትንሣኤ ለኢትዮጵያ “አርጋጅነትን “ለማሶገድና ” አልጫ ፍቅርን” ለመቀነሥ ፣  የባህል አብዮት ያስፈልገናል

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop