ይቅርታ እና ይቅር ባይነት – በዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለዩ አስተያየቶችን በመጠኑ ማስተናገድ መጀመር ምልክት ከሚታይባቸው መካከል አዲስ ዘመንን ያነሳሉ።ከ1933 ጀምሮ ለየዘመኑ ገዢዎች ቁጭ በል ሲሉት ቁጭ እያለ እንደ ዘመኑ እየተለዋወጠ እዚህ የደረሰው በሕዝብ ሀብት ከሚተዳደሩ የሕዝብ ያልሆነው አዲስ ዘመን ትንሽ መልኩን ቀየር ለማድረግ እየሞከረ ነው ብዙ እንደማይዘልቅ የኖረበት ልምድ ምስክር ነው። ለሁሉም የዳንኤል ክብረትን ሀሳብ ይዞ ወጥቷል። መንግስትን የሚሞግቱ አቅጣጫ የሚያሳዩ አስተያየቶችን ወደፊት በስፋት ሊስተናገዱ ይገባል። ያንብቡት ሼር ያድርጉት

ይቅርታ እና ይቅር ባይነት
April 20, 2019 21

ከሳምንት በፊት ከአንድ አንባቢያችን በኢሜይል አድራሻችን አንድ መልዕክት ደረሰን። በመልዕክቱ መሰረት በስልክ ተጨዋወትን። አንባቢያችን በመጋቤ አዕምሮ አምዳችን የምናቀርባቸው የአዕምሮ ምግቦችን በጣም እንደወደዳቸውና እርሱም በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ድረገፆች ያሰባሰባቸው የአዕምሮ ምግቦች እንዳሉት ነገረን።

ካሰ ባሰባቸው የአዕምሮ ምግቦች መካከል እርሱ ይበልጥ ከወደዳቸው ታሪኮች መካከል አንባ ቢዎቻችን እንዲማሩባቸው ያሰባቸውን የተወሰኑትን ላከልን። እኛም በአንባቢ ምርጫ ከተላኩልን የአዕምሮ ምግቦች መካከል ለዛሬ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት በአንድ መድረክ ላይ የተነገረውን የአዕምሮ ምግብ እንዲህ አቀረብነው።

ይቅርታ እና ይቅር ባይነት መገኛው የት ይሆን?

ቂም በቀል ጊዜያዊ የሆነ እርካታን ለስጋችን ይሰጠው ይሆናል እርሱም ቢሆን ቀን አልፎ ቀን ሲተካ ይፀፀታል። ያጣሁትን መልሼ ላላገኝ ይህንን ማድረጌ ምን ጠቀመኝ? ለምንስ የሰነፎችን መንገድ ተከተልኩኝ? እያለ ራሱን መውቀሱ አይቀሬ ነው። በደልን በበደል፣ ክፋትንም በክፋት፣ ተንኮልንም በተንኮል እንሸፍናለን በሚል የዋህ አስተሳሰብ ታስረን የነገሮችን ውል ከማጥፋት ይልቅ ጥፋ ትን ተራርሞ ክፍተትን በይቅርታ መሙላቱ የታላቅነትና የአስተዋይነት ብሩሕ ምልክት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ስለ ጀግናው ተዋጊ ሞላ መላኩ  ጽኑ የፋኖ ሕይወትና አይበገሬነት

ይህ ይቅርታና ይቅር ባይነት መገኛው የት ይሆን? እንደ እኔ አመለካከት ይቅርታ እና ይቅር ባይነት ምንጩ መንፈሳዊ ሕይወት ነው። ምንም እንኳን ይቅርታ መደራረግ ለስጋዊ ኑሯችንም ታላቅ ጠቀሜታ ቢኖረውም ዋናውና ከዚህ የሚበልጠው ግን መንፈሳዊው ዋጋ ነው።

ይህንን መንፈሳዊ ዋጋ ያገኝ ዘንድ ዘወትር የሚተጋ ሰው ልቡናው ለይቅርታ የፈጠነ ነው። በዚህ ምድር በበዳዩ ከተበደለው በደል ይልቅ በሰማይ የሚያገኘው ክብር ሚዛን ይደፋለታል። እዚህ ላይ ግን ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን ነገር አለ። ይቅር ባይነት ቀላል አይደለም። እንደማንኛውም ክብርን እንደሚያጎናፅፍ ተጋድሎ ሁሉ እርሱም ከፍተኛ ተጋድሎ ያሻዋል።

በአፋችን ለመናገር እንደሚቀለው ያህል ለመተግበሩ ቀላል አይደለም። ይቅር ለማለት ስናስብ ብዙ ፈተናዎች ፊታችን ይጋረጣሉ። ፈተናው ከራስ ይጀምራል የቤተሰብ ፈተናም አለው። እንዲሁም የአካባቢ ተፅዕኖም አለው።

እነዚህን ፈተናዎች በድል አድራጊነት መወጣት የሚችል ሰው ነው። ይቅር የሚለው እና ሰማያዊውን ክብር ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኘው። ቁርሾን በሆድ ይዞ ዘወትር መበላላትን፣ መጠፋፋትን እና ልኩን/ለኳን አሳያታለሁ ባይነትን የዘወትር መገለጫው የሆነውን ስጋችንን ሰማያዊውን ተስፋ አሻግራ ወደምትመልከተው ነፍሳችን ስናስገዛ መንፈሳዊነት በሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደተለኮሰ ሻማ ከሩቅ ያበራል።

የዚያን ጊዜ የበደሉንን አካላት መጥተው ይቅርታ እስኪሉን ሳንጠብቅ አስቀድመን ይቅርታ ይቅርታ ወይም ይቅር ባይነት የሰው ልጅ በዚህ ዓለም በሚኖርበት ወቅት በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስሮች ወይም ግንኙነቶች አማካኝነት ከሌሎች የማኅበረሰቡ ክፍሎች ጋር ለሚኖረው ጤናማ የኑሮ ጥምረት ትልቅ ድርሻ አለው ብዬ አምናለሁ።

ይቅር መባባል ያለፈ በደልን አጥቦና አስወግዶ ለቀሪው ህይወት አዲስ ልቡናን በመፍጠር ግንኙነታችንን ወደ ተሻለ የኑሮ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል። በአንድ ወቅት በታሪክ አጋጣሚ ተበዳድለው፣ ተቀያይመው፣ ተኮራ ርፈው ከዚያም ባለፈ ደም ተቃብተው እና ለቂም በቀል ሌት ተቀን በሃሳብም በግብርም ይሯሯጡ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በልቡናቸው የተቋጠረውን የመጠፋፋት ሕልምና ዕቅድ ወደ ጎን ትተው አንዱ ካንዱ በጋብቻ እስከ መጣመርና አንዱ ላንዱ ዋስ ጠበቃ እስከመሆን ያደርሳቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትግራይን እናቶች ከወላድ መካንነት ማዳን የጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት ታሪካዊ ሃላፊነት ነው!

በዚሁ መልካም አጋጣሚ ምክንያትም ሊጠፋ የነበረው ሕይወት፣ ሊፈስ የነበረው ደም እናሊጎድል የነበረው አካል ከጥፋት፣ ከመፍሰስና ከመጉደል ይድናል። ከዚህም ባለፈ ቂም በቀል በይቅርታ እስካልተደመደመ ድረስ ጥፋቱ መቋጫ የለውም። አንዱ ላለፈ በደሉ አዲስ በደል ሲፈፅም ሌላኛውም አፀፋውን ሲመልስ የሁለቱም ወገኖች በምድር ላይ በሕይወት እስካሉ ድረስ መጠፋፋቱ ይቀጥላል። እንዲህ ዓይነቱ ለይቅርታ ቦታ አለመስጠት በተለይ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ በእኛ በኢትዮጵያውያን ይብሳል።

ምክንያቱ ምን ይሆን? በምጣኔ ሃብት አለማደጋችን፣ በቴክኖሎጂ አለመበልፀጋችን ወይም ገና ያልደረስንበትና ያልተማርነው ዘመናዊ ትምህርት ይኖር ይሆን? ትልቁ መንስዔ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል እንዳልሆነ የምንገነዘበው እነዚህ ምክንያቶች ሞልተው የተትረፈረፉላቸው ወገኖቻችን ይባስ ብለው የችግሩ ሰለባ እነሱ መሆናቸው ነው።

ይቅርታና ያደግንበት ማህበረሰብ

ያደግንበት ማኅበረሰብም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በአትንኩኝ ባይነትና ክንዴን ሳልንተራስ እንዴት እደፈራለሁ? አስተሳሰቡ በደንብ አድርጎ አጥምቆናል። ገና ከእናታችን ማኅፀን ከመውጣታችንም ደም መላሽ ብሎ ስም ያወጣልናል።

አንደበታችን እማማ አባባ ማለት ሳይጀምር በቂም በቀል ዲፕሎማ ከቤተሰባችን እና ከአካባቢያችን በከፍተኛ ማዕረግ እንመረቃለን። ከዚያ በኋላ ልክ ግብፃውያን እናቶች ልጆቻቸውን አባይ ሕይወትህ ነው እያሉ እንደሚያሳድጉት ሁሉ ለእኛም የስማችንን ትርጓሜ ከወደፊቱ ሥራችን ዕቅድ ጋር እየተነገረን እናድጋለን።

ከዚህም በተጨማሪ ሕዝብን እናዝናና በታለን በሚል ሽፋን የሚወጡ ዘፈኖችም የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው። የአንድን ግለሰብ አስተሳሰብ ለመግለፅ እንዲሁም ለግጥሙ ቤት መድፋት እንጂ ጭብጡ በማኅበረሰቡ ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ባለማስተዋል የሚዘፈኑ ዘፈኖች አሉ።

«ተበድዬስ ይቅርታ አልልም የቀረው ይቅር እንጂ» የሚል ዘፈን ሲያዳምጥና አብሮ ሲያንጎራጉር ያደገ ሰው ለይቅርታ ያለው ቦታ ቢያንስ ኸረ እስከ ጭራሹም ባይኖረውምን ይደንቃል? ሁላችንም እንደምናስታውሰው በጀግኖች አባቶቻችን ቆራጥ ተጋዳይነት ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ የሚተርፍ የነፃነት ፋና በዓድዋ ተራሮች ተንቦግቡጎ ባልጠበቀውና ባላሰበው መልኩ ድል የተደረገው የኢጣልያ መንግሥት ይህንን በዓለም አቀፍ አደባባይ የውርደት ሸማ ያለበሰውን የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ቂም ለመወጣት በተጠቀመው የመርዝ ጋዝ እጅግ ብዙ ወገኖቻችን በመሪር ስቃይ አልፈዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ደውሉ ይጮሐል!!

እስቲ እነዚህን የነፃነታችን አምድና ለዛሬው እኛነታችን የሕይወትን መስዋዕትነት ከፍለው ስማቸውን በልባችን ፅላት ላይ በወርቅ ማኅተም ያተሙትን ወገኖቻችንን አንድ ጊዜ ቆም ብለን እናስባቸው። በዚያን ጊዜ እንደዚያ ያለውን የጭካኔ ርምጃ እንዲወሰድ ያዘዘውን አካል ብናገኘውና ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኘው።

ቁርሾን በሆድ ይዞ ዘወትር መበላላትን፣ መጠፋፋትን እና ልኩን/ለኳን አሳያታለሁ ባይነትን የዘወትር መገለጫው የሆነውን ስጋችንን ሰማያዊውን ተስፋ አሻግራ ለምትመለከተው ነፍሳችን ስናስገዛ መንፈሳዊነት በሕይወታችን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደተለኮሰ ሻማ ከሩቅ ያበራል።

የዚያን ጊዜ የበደሉንን አካላት መጥተው ይቅርታ እስኪሉን ሳንጠብቅ አስቀድመን ይቅርታን እናደርግላቸዋለን። የሰማያዊው ክብር ባለቤቶች መሆናችንን እናውቃለንና ይቅርታውን ባደረግን ወቅት ከመቼውም ይበልጥ ውስጣችን በሐሴት ይሞላል። የሰላም እንቅልፍም እንተኛለን።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 12/2011

በዲያቆን ዳንኤል ክብረት

1 Comment

  1. 4/26/19
    የተወደዳችሁና የተከበራችሁ፤ ዲን. ዳንኤል ክብረትና ዐባይ ሚዲያ እንዲሁም በመላው ዓለም የምትገኙ ክቡራን ታዳሚዎች፤

    በውድ ሐገራችን በኢትዮጵያ እጅግ ከፍ ባለ ደረጃ አስፈላጊ ሆኖ ስለሚገኘው ስለ ይቅር መባባል ጉዳይ የቀረበውን ጦማር በጥንቃቄ ተመልክቼ ከዚህ በታች ያለውን አስተያየት እንዳቀርብ ፍቀዱልኝ፤

    “ዕርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።” ማቴ. ም5/9

    ይቅር ማለትና መባባል መንፈሳዊ ግዴታ እንደ ሆነ ግልጽ ነው። በኔ በኩል ለናንተ የማቀርበው መሠረታዊ ጥያቄ ግን የፍትሕስ ሥፍራው የት ነው? የሚለውን ነው። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን እንድትመለከቱልኝ በትሕትና እጠይቃለሁ፤

    1ኛ/ ፋሺሽት ኢጣልያ፤ ባልተቆጠበ የቫቲካን ድጋፍ፤ ምንም ባልበደለች ኢትዮጵያ ላይ እጅግ አሰቃቂ የጦር ወንጀል ፈጽማ፤ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ጨፍጭፋ፤ ከዚሁ ውስጥ በየካቲት 12-14፣ 1929 ዓ/ም 30000 ሕዝብ አዲስ አበባ ውስጥ ያለምሕረት ገድላ በተጨማሪም 2000 ቤተ ክርስቲያኖች፤ 525000 ቤቶችና 14 ሚሊዮን እንስሶች ከማውደሟ በላይ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ንብረቶችን ዘርፋለች። ለዚህ ሁሉ እጅግ ከባድ የጦር ወንጀል ኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ ካሣ አልተከናወነላትም። አርኪ ይቅርታም አልተጠየቀችም።

    2ኛ/ 500000 ሕዝብ ስለጨፈጨፈው እንዲሁም እጅግ የከፋ ሌላም ጥቃትና ወንጀል የፈጸመው የደርግ መንግሥት፤ በተለይም ዋናው ተጠያቂው፤ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ተገቢው ፍትሕ አልተፈጸመባቸውም። እሱማ ዝንብም አልነካሁ እያለ ያላግጣል።

    3ኛ/ በወያኔም ዘመነ ለአስከፊ ዘረኛነትና እጅግ ብዙ አሰቃቂ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑት ግለሰቦች ለፍትሕ ሳይቀርቡ ይገኛሉ።

    4ኛ/ ሌሎችም ተጠያቂዎች አሉ።

    ታዲያ፤ ሊኖር የሚገባው አማራጭ በዓይነ ጭፍን፤ ያለአንዳች የፍትሕ ሒደት፤ ይቅር ማለት ከሆነ ላሁኑም ሆነ ለወደፊቱ አገዛዝ ወንጀለኛነትን የሚያበረታታ አይሆንም? ሚዛናዊ በሆነ መንገድ፤ በጥንቃቄ ማሰብ አያስፈልግም?

    በበኩሌ ባጭሩ የማሳስበው፤ ወንጀል የፈጸመ ከፍትሕ የማያመልጥ መሆኑን በተግባር ማሳየትና ይቅር መባባሉንም አያይዞ ማጠናከር የሚያስፈልግ መሆኑን ነው።

    እግዚአብሔር በፍትሑና በይቅርታው ሥልት ያበርታን!

Comments are closed.

Share