የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚያከናውኑ ሰዎች ቆጠራ ከመጀመራቸው በፊት ሊምሉ ነው

መንግስት አሁን ቆጠራውን ከሚያደርግ ሃገር በማረጋጋት ሥራ ላይ ቢጠመድ ይሻለዋል – የቆጠራውን ውጤት ተከትሎ ሊከሰት ለሚችል ግጭት አልተዘጋጀም እየተባለ አስተያየት በሚሰጥበት በዚህ ሰዓት  ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራው ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ገለፀ፡፡ ቆጠራውን በተመለከተ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታወቀ፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=bsEiZlueJBA

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርና የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ፀሐፊ አቶ ቢራቱ ይገዙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በቆጠራው የሚሳተፉ ባለሙያዎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡ እንደ አቶ ቢራቱ ገለጻ ቃለ መሃላ እንዲደረግ የተፈለገው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የየራሱ እምነት ያለው በመሆኑ መረጃውን የሚሰበስበው ትክክለኛ መረጃ እንዲሰበስብ ነው፡፡ በቆጠራ ሥራው ላይ የሚሰማሩትና ተቆጣጣሪዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ የጠቆሙት አቶ ቢራቱ ወደ 150 ሺ የሚገመት የቆጠራ ቦታ ካርታ እንዲሁም ከ37 ሺ በላይ የመቆጣጠሪያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን እና በእያንዳንዱ ቦታም አንድ ተቆጣጣሪ እንደሚመደብ ገልጸዋል፡፡

አቶ ቢራቱ እንዳስረዱት በቆጠራው የሚሳተፉት የመንግሥት ሠራተኞች ሲሆኑ፣ በአብዛኛው ከመምህራን የሚመለመሉ ናቸው፡፡ ከእነርሱ በተጨማሪ የግብርና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችም በምልመላው የሚካተቱ ይካተታሉ፡፡የመመልመያ መስፈርትም ተዘጋጅቷል፡፡ ከመስፈርቶቹ መካከል በቴክኖሎጂው እውቀት ያላቸው፣ በሥራ ምስጉን የሆኑ እንዲሁም በሥነ ምግባርም ችግር የሌለባቸው የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ አራተኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ከቀደምት ሦስት የህዝብና ቤት ቆጠራዎች በተሻለ ሁኔታ ቆጠራውን ለማካሄድ እና ውጤቱም የበለጠ ጥራትና በህዝብ ዘንድም ተዓማኒነት እንዲኖረው ሰፊ ሥራ በመሠራት ላይ ነው፡፡ ተደራሽነቱም ሁሉም ቦታ የሆነ፣ መረጃ አሰባሰቡ ላይም እያንዳንዱ ሰው ሳይቆጠር እንዳይታለፍ በሚያስችል መልኩ ዝግጅቶች በመገባደድ ላይ ናቸው፡፡ ቆጠራው ከተካሄደ በኋላም ውጤቱ በእያንዳንዱ ክልል ከቀበሌ ጀምሮ ያለውን የህዝብ ብዛት በትክክል ሊያሳይ በሚችል መልክ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "በቤተክርስቲያን ውስጥ አፈና አለ" - አቡነ መቃርዮስ

በቴክኒክ ረገድ ያለውን ግብዓት ውጤታማ ለማድረግ በመስክም ፍተሻ ተደርጓል በዚህም ለቆጠራው ስኬታማነት ጥሩ ግብዓት መገኘቱን አቶ ቢራቱ አመልክተዋል፡፡ በቆጠራ ላይ ይከሰታል ተብሎ የሚገመተው የቁጥር ስህተትና አይነቱን ቀድሞ ማስወገጃ ሥርዓትም ተነድፏል፡፡

በርካታ መረጃዎችን መሰረት በማድረግ ኤጀንሲው የሠራው ትንበያ እንዳመለከተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 98 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ተቆጥሮ ሲመጣ ግን ሊቀንስ አሊያም ሊጨምር እንደሚችል መታሰቡን አቶ ቢራቱ ገልጸዋል፡፡ ቃለ መሃላው ቀደም ሲል በተካሄዱ ሦስት ቆጠራዎች ተግባራዊ እየተደረገና በአራተኛው ቆጠራ ላይ የሚጀመር እንደሆነም ታውቋል፡፡

ዘ-ሐበሻ በፌስቡክ ገጹ ባሰባሰበው ድምጽ 61% ድምጽ ሰጪዎች ሕዝብና ቤት ቆጠራው አሁን ባይደረግ ይመርጣሉ::

2 Comments

  1. የሀገራችን ፖለቲካ ቅኝት በኣብዛኛው ጎሳ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የጎሳዎች / ዘሮች ቁጥር እና ኣባላቶቹ በዚህ ሀገር ኣቀፍ ቆጠራ ትኩረት ሊሰጥባቸው እንደሚገባ እሙን ነው ።
    በዚህ ሂደት የዜጎችን ማንነት መጫን ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
    ለምሳሌ ከትግራዊ ኣባት ፣እና ከኣኙዋክ እናት ተወልዶ የናቱ ሀገር ያለ ኣባት ያደገና ; ያደገበትን ኣካባቢ ባህል የተላበሰ ዜጋ ኣባትህ ትግራዊ ስለሆነ ብሄርህ ትግራዊ ነው ብሎ መጫን ትርጉም የለሽ ነው ።
    ስለዚህ በቆጠራው በእናቱም በኣባቱም ካንድ ጎሳ/ብሄር (ethnic origin ) ከሆነ የዛ ጎሳ ኣባል ነው ተብሎ ቢወሰድ ችግር ኣይታየኝም ፣ ግን በእናቱ ከኣንድ ጎሳ ፣ በኣባቱ ከሌላ ጎሳ ለሚወለድ መመዝገብ ያለበት ከሁለት ጎሳዎች የተገኘ መሆኑን በሚያሳይ መልኩ ፣ ” ቅይጥ ” መባል ይገ ባዋል ፣ ወይም በዜጋው ነጻ ፍላጎት መሰረት የእናቱን ወይም የኣባቱን ጎሳ እንዲመርጥ መብት ሊሰጠው ይገባል።
    እንዲሁም ባንድ ክልል ለተወሰነ ኣመት የኖረ ከሌላ ክልል የመጣ ዜጋ የክልሉን ቁዋንቁዋ እስከቻለ እና ስነ ምግባር በስራ እስካዋለ ድረስ በትውልድ ሳይሆን በምርጫው የዛ ጎሳ ፣ ወይ ክልል ኣባልነቱ ተክብሮለት ሙሉ መብት ሊሰጠው ይገባል።
    በሌላው ሀገር የሀገር ዜጋ ኣይደለም ፣የውጭ ሃገር ዜጋ የተወሰነ ኣመት በሌላ ሀገር እስከኖረ ድረስ ከተውላጆቹ እኩል የዜግነት መብት ይሰጠዋል።
    የኛ ኣክቲቪስቶች በኣሜሪካ እና በሌሎች ሃገሮች የዚህ መብት ተጠቃሚዎች ሆነው ፣ በሀገር ቤት መጤ፣ ሰፋሪ ወዘተርፈ ፤እያሉ ሲጮሁ ማየት እጅግ ልብ ይሰብራል።ያሳፍራልም።

Comments are closed.

Share