ድሬዳዋ ዛሬ በጎማ ጭስ ስትታጠን ዋለች

በዛሬው እለት ከጠዋቱ አራት ሰአት ጀምሮ በድሬደዋ ከፍተኛ ተቃውሞ ተደርጓል፡፡ ከንቲባው ያነጋግሩን ያሉ ወጣቶች መንገድ ዘግተው ጎማ በማቃጠል ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የዋሉ ሲሆን በፖሊስ ላይም ድንጋይ ወርውረዋል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=pJpzsue5H3c&t=917s

ተቃውሞው ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ መከላከያ ገብቶ የማረጋጋት ስራ መስራቱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡ የተቃውሞው መነሻ በጥምቀት በአል አከባበር ወቅት የተፈጠረው ረብሻ ነው፡፡ የድሬዳዋ ፖሊስ ትላንት ባወጣው መግለጫ በጥምቀት በአል ማግስት ጥር 13 ቀን 2011አ.ም የእግዚአብሔር አብ ታቦትን አስገብተው በሚመለሱ ምእመናኖች ላይ የተወረወረ ድንጋይን ተከትሎ በተፈጠረው ግጭትና ሁከት ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን መግለፁ ይታወቃል፡፡ፖሊስ 84 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ቢናገርም በዛሬው ተቃውሞ የታሰሩት ይፈቱ የሚል መፈክርም ተሰምቷል፡፡

በተጨማሪም በከተማው ውስጥ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ስላለ አስተዳደሩ መፍትሄ እንዲሰጥም ተጠይቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከፍተኛ የስራ አጥነት በመኖሩ የሚመለከተው አካል በተለይም ከንቲባው በዚህ ዙሪያ እንዲሰሩ ወጣቶቹ ጠይቀዋል፡:

የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሰራሁ ነው ብሏል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን ባንተአለም ግርማ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጥር 12/2011 ፖሊስ የችግሩ ቀስቃሾች ናቸው ብሎ የጠረጠራቸውን ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ ነው፡፡
በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃና ማስረጃ አሰባስቦ ለፍርድ ለማቅረብ  የተቀናጀ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡
ግጭቱ ከየትኛውም ብሔር ሆነ እምነት ጋር ግንኙነት እንደሌለው ኃላፊው ተናግረዋል።
አንድ መድኃኒት ቤት በከፊል ቃጠሎ እንደደረሰበትም አስታውቀዋል፡፡
በአስተዳደሩ የሕዝቡን ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስና የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው እርምጃ እንደሚወስዱ ዋና ሳጂን ባንተዓለም  ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያጎለብት  ጠይቀዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መግለጫው የማነው ለሚለው የፋኖ ቃል አቀባዩ :ዶ/ር አብደላ መልስ
Share