በአርቲስት ፈቃዱ ተክለማሪያም ስም የተሰበሰበው ገንዘብ ኮሚቴውንም ለሁለት ከፈለው

በአርቲስት ፈቃዱ ተክለማሪያም ስም የተሰበሰበው ገንዘብ ኮሚቴውንም ለሁለት ከፈለው፡፡  በእነ ሀይሉ ከበደ የሚመራው በአገር ውስጥ ገንዘብ ሲያሰባስብ የቆየው ኮሚቴ ከቴዎድሮስ ተሾመ ጋር ውዝግብ ውስጥ ቆይቶ እንደነበር ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል፡፡ ምንጮቻችን እንደገለፁልን አሁን ደግሞ ይህ ኮሚቴም በሀሳብ ለሁለት ተከፍሏል፡፡

https://youtu.be/J8BZqY2t65c

የኮሚቴው አባላት አቶ ኃይሉ ከበደ፣ አርቲስት መቅደስ ጸጋዬ፣ አቶ ሳምሶን ብርሃኑ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ አርቲስት መሠረት መብራቴ እና አቶ ውድነህ ክፍሌ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህ ኮሚቴ በአገር ቤት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያምን ከመሞቱ በፊት ለሕክምና ወጪ ተብሎ የተሰበሰበ ገንዘብ ብር 1 ሚሊየን 200 ሺ 895 ብር ከ65 ሳንቲም በባንክ አካውንቱ የሚገኝ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ 

ይህን ገንዘብ በተመለከተ ሰሞኑን ኮሚቴው ባደገረው ስብሰባ ለአርቲስት ፈቃዱ ሀውልት ይሰራበት በሚል በቀረበው ሀሳብ ከፍተኛ ጭቅጭቅ ተፈጥሮ እንደነበር ምንጮቻችን ገልፀውልናል፡፡ ሀውልት ይሰራ የሚለውን ሀሳብ ደግፈው የተከራከሩት አቶ ሳምሶን ብርሃኑ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ አርቲስት መሠረት መብራቴ እና አቶ ውድነህ ክፍሌ እንደነበሩ የገለፁት ምንጮች አቶ ሀይሉ ከበደና አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ግን ሀውልት ከሚሰራ ለበጎ አድራጎት ድርጅት መሰጠት ይኖርበታል ብለው ሃሳብ ማቅረባቸውን ጠቁመውናል፡፡ 

ከብዙ ክርክር በኋላም በድምፅ ብልጫ ሀውልት ይሰራ የሚለው ሀሳብ እንዳለፈ ለማወቅ ችለናል፡፡ በዚህ መሰረትም ሀውልቱ በኮሚቴው እጅ ባለው ብር ተሰርቶ የተረፈውን ብር ህጋዊ ወራሾች በፍርድ ቤት ከተረጋገጡ በኋላ ለማከፋፈል ተስማምተዋል፡፡ ሃውልቱን በታወቁ ባለሙያዎች ለማሰራትም ጨረታ እንዲወጣ በተወሰነው መሰረት እስከ ጥር 12 ክፍት የሆነ ጨረታ ወጥቷል፡፡-

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጃ ሉድን ምን ነካው? (ቪድዮ)
Share