በአፋር ብሔራዊ ክልል ከሰኞ ጀምሮ በተነሳ ግጭትአራት ሰዎች ሲገደሉ 13 ደግሞ ቆሰሉ

ሰኞ ሌሊት ተቀስቅሶ እስከ ትላንት ማክሰኞ ረፋድ በዘለቀው ግጭትየተነሳ ወደ ትግራይና ወደ አዲስ አበባ መንገደኞችንና ጭነት የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች መንገድ ተዘግቶባቸው እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ ዛሬ እንደዘገበው ግጭቱ በአካባቢው ከሳምንት በፊት የሕዝብ የተቃውሞ ሠልፍ ከተካሄደ በኋላ እየተባባሰ የመጣ ሲሆን በወቅቱ በተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ከዚህ ቀደም ሶስት ቀበሌዎች ልዩ ቀበሌ ተብለው መሰየማቸውና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችም በሕዝቡ ተነስተው ነበር፡፡ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማርገብ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ወደአካባቢው የገባ ቢሆንም ከታጠቁ ግለሰቦች ጋር ተኩስ መለዋወጡ ታውቋል፡፡

በግጭቱ ወቅት የኢሳ ጎሳ አባላት አደይቱ፣ እንድፎ እና ገርባ-ዒሳ በተባሉ ከተሞች የአፋር ብሔራዊ ክልልን ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ የሶማሌ ክልልን ሰንደቅ ዓላማን ለመስቀል የሞከሩ ሰዎች እንደነበሩ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

እስከ ማክሰኞ ታኅሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ረፋድ ድረስ ያልተቋረጠ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እንደነበረ፣ ከቀትር በኋላ ግን ተኩሱ መብረዱንና መንገዶችም መከፈታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ መንቀሳቀስ ያልቻሉ ተሽከርካሪዎችም ጉዞ ቀጥለዋል፡፡ ይህም የሆነው ልዩ ኃይሉ ከአካባቢው ከወጣና ነዋሪዎች የዘጉትን መንገድ ለመክፈት ከፈቀዱ በኋላ እንደሆነ ሲታወቅ፣ በአፋር ክልል የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ እንዳልገባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከወራት በፊት የአፋር ክልልን የሚያስተዳድረው የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ባደረገው ጉባዔ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙትን ወ/ሮ አይሻ መሐመድን (ኢንጂነር) የፓርቲው ሊቀመንበር፣ እንዲሁም አቶ አወል አርባን ምክትል አድርጎ መሾሙ ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይም ፓርቲው የክልሉ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ሥዩም አወልን በማሰናበት በምትካቸው አቶ አወል አርባ ክልሉን እንዲያስተዳድሩ መድቧቸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ራስን እና አገርን  ካይቀሬዉ ሞት ለመታደግ በሚደረግ የህልዉና ትግል በአንድነት እና ህብረት ለነፃነት ዘብ መቆም የአሁን ግዴታ ነዉ

ሕወሓት ከአፋር ክልል የሚያገኘው ጥቅም ስለሚቀር አዲሱ አመራር ሲመረጥ በክልሉ ብጥብጥ ሊያስነሳ እንደሚችል ዘ-ሐበሻ ዘግቦ መንግስት ይህ ከመከሰቱ በፊት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ዘ-ሐበሻ ቀደም ሲል ጥቆማ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል::
https://www.youtube.com/watch?v=52FOcaxcCwo

Share