December 26, 2018
6 mins read

አርበኛ መሳፍንት ‹‹በወልቃይት ጠገዴ ያልተነገረና የኢትዮጵያ ህዝብ በውል ያላወቀው መጠን የለሽ በደል ተፈፅሟል›› አሉ

93364

አርበኛ መሳፍንት ተስፉ ህወሀት በትጥቅ ትግሉ ወቅት በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ ሲፈፅም የነበረውን ግፍ በመቃወም በረሃ ገብተው ህወሃትን ሲፋለሙ በትግራይ የጉድጓድ እስር ቤት ታስረው ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባቸዋል፡፡ ይሁንና እስር ቤቱን ሰብረው በመውጣት እድሜያቸውን ሙሉ ሲፋለሙ የቆዩት እኚህ አርበኛ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ሰምተው በቅርቡ ከበረሀ ወጥተዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግል ጓዶቻቸውን ይዘው ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ወደጎንደርና ባህር ዳር መምጣታቸውን ከዚህ ቀደም በዘሃበሻ ዜናዎቻችን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አርበኛ መሳፍንት ዛሬ ለንባብ ከበቃውና በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ከሚዘጋጀው በረራ ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ አድርገው ነበር፡፡

በዚህ ቃለምልልስ ትግል ስለጀመሩበት ምክንያት ሲገልፁ ‹‹የህወሃት ሰዎች ለአካባቢው ህዝብ ያላቸው እይታ ገና ከጠዋቱ ጀምሮ በጥላቻ የተሞላ ነበር፡፡ በአማራ ላይ የነበራቸው ጥላቻ ጫፍ የደረሰ ስለነበር አንተ የመሳፍንት ዘር፣ የጨቋኝ ቤተሰብ ስለሆንክ ነው መሳፍንት የተባልከው እያሉ በጥላቻ ያዩኝ ነበር›› ካሉ በኋላ በዚህ መልኩ በእሳቸውና በአማራው ህዝብ ላይ የሚደርሰው በደል ሲበዛ በ22 አመታቸው ወደትግል መውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡ በትግል ትንሽ ከቆዩ በኋላ በህወሀት እጅ ወድቀው የስቃይና የመከራ ጊዜ እንዳሳለፉ የተናገሩት አርበኛ መሳፍንት መስከረም 17 ቀን 1981 ከለሊቱ ስምንት ሰአት አምልጠው እንደወጡም ገልፀዋል፡፡

ከእስር አምልጠው ዳባት ርቀው እየኖሩ እያለ ህወሀቶች በ1983 አገሪቱን እንደተቆጣጠሩና መሳሪያቸውን እንዲያወርዱ ተስማምተው የግብርና ኑሯቸውን ጀምረው እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ግብርና እንደጀመሩ የቢሮክራት ልጅ ተብለው እርሻቸው እንደተቀማባቸው የተናገሩት አርበኛው ይህን በደል ችለው በመኖር በ1997 ቅንጅትን ወክለው ምርጫ መወዳደራቸውንም ያወሳሉ፡፡ በምርጫው በዳባት ሙሉ በሙሉ ምርጫውን ማሸነፉን ተከትሎ አፈሙዝ ሲነሳባቸው በድጋሚ ለትግል ወደበረሃ መግባታቸውን ገልፀዋል፡፡ በረሃ ከገቡ በኋላም በህዳር ወር 1999 ህወሀት ሽፍታ በመላክ ልታስገድላቸው እንደሞከረችና በተአምር እንደተረፉ ያስረዱት አርበኛ መሳፍንት ሲናገሩ ‹‹ህዳር 19 ቀን 2009 ይፋዊ ውጊያ በህወሃት ተከፍቶብኝ ከእነሱም ከእኛም ወገን በርካታ ሰው ሞቷል፡፡ በዚያ ውጊያ የምወደው አባቴ ተታኩሶ በኋላም ተገድሎብኛል፡፡ እኔም ከብዙ ጡርነት ነው ያመለጥኩት›› ብለዋል፡፡ በዚህ ውጊያ ህወሃት ዲሽቃና ከባድ መሳሪያ ሁሉ ተጠቅሞ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

አሁን በምን ስምምነት ከበረሃ ወጥተው ከተማ እንደገቡ ሲጠየቁ በሰጡት ምላሽ ደግሞ ‹‹መሬት የያዘ ነገር የለም፡፡›› ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል አመራሮች ከውጭ አገር እስኪመለሱ እየጠበቁ መሆኑን የተናገሩት አርበኛው ከበረሃ የመጣው ወጣት ሀይል እየተንገላታ በመሆኑም ቅሬታቸውን አሰምተው ‹‹ወደፊት በምን አይነት መልኩ ህዝብና አገር ሊጠቅም በሚችል ተግባር ላይ ልንሰማራ እንደምንችል በዝርዝር ተወያይተን ለህዝባችን እንገልፃለን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይ በወልቃይት ጠገዴ ህወሃት የፈፀመውን ሲገልፁ ደግሞ ‹‹በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ወጣቱን አጥፍተውታል፡፡ ነባሩን ህዝብ እያሰሩ፣ እያሳደዱና እየገደሉ ከርስቱ አፈናቅለው የራሳቸውን ህዝብ አስፍረውበታል፡፡ ያልተነገረና የኢትዮጵያ ህዝብ በውል ያላወቀው መጠን የለሽ በደል ተፈፅሟል›› ብለዋል፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=52FOcaxcCwo

93358
Previous Story

ለኢትዮጵያ ኢንቨንስትመንት ኮሚሽን ዳይሬክተር ጄኔራል ተሾመ

93367
Next Story

በአፋር ብሔራዊ ክልል ከሰኞ ጀምሮ በተነሳ ግጭትአራት ሰዎች ሲገደሉ 13 ደግሞ ቆሰሉ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop