(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ወጣት ክንፍ ድርጅት (ኢሕአፓ ወክንድ)”ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ጎን እንቁም !!” ሲል ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። “ወያኔ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ መቃብር ጉድጎድ እየወረደ ባለበት በአሁኑ ወቅት በጣአረ ሞት እንደእብድ ውሻ ከግራና ቀኝ ያገኘውን ሁሉ መናከሱ የሚጠበቅ ነው ። በዚህ የአምባገነኖች ሁሉ መገለጫ በሆነው የመጨረሻ ሰዓት መፈራገጥ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመመከት ሁሉም የህዝብ ወገን ፣ በተለይም ወጣቱ ሐገርና ሕዝብን በማስቀደም የድርጅትን አጥር ጭምር ሰብሮ ፣ ዘር ፣ ሀይማኖት ፣ጾታ ፣ወዘተ ሳይገታውና ሳይከፋፍለው በተጠናከረና በተቀናጀ ትግል የዘረኛውን ወያኔ ውድቀት ማረጋገጡ የግድ ነው።” ያለው የኢወክንድ መግለጫ “በወያኔ መቃብር ላይም ሕዝብ ወሳኝ የሚሆንበት፣ ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የሚከበሩባት የሕግ የበላይነት የሰፈነባትና ሕዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆንባትን እትዮጵያን ለመገንባት የወጣቱ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ኢሕአፓ ወክንድ ያምናል።” ብሏል።
መግለጫው ቀጥሎም “ይህንንም እውን ለማድረግ ሁሉም ወጣት ክንዱን አስተባብሮ የሚሰነዘርበትን ጥቃት በጋራ መመከት አማራጭ የማይገኝለት የታሪክ ግዴታ ነው። ኢሕአፓ ወክንድ የወያኔን ወያኔነት በሚገባ የተገነዘበና በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ የሕብረተሰባችን ክፍሎች ላይ የሚፈጽመው ግፍና ጥቃት ወያኔ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ካለው አኩይ ራእይ የሚመነጭ ለመሆኑ ቅንጣትም ብዥታ የለውም።” ካለ በኋላ ከሕብረተሰቡ የሚጠበቀውንም ጠቁሟል።
“በመሆኑም ወያኔ ባሰማራቸው እርጉም መልእክተኞቹና አባሎቹ አማካኝነት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ውስጥ ባሉ የትግራይና የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች መሃከል ግጭት አንዲፈጠር ካደረገ በሗላ ሆን ብሎ ታጣቂዎቹ በዩኒቨርስቲው ግቢ ገብተው የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎችን አንዲደበድቡ አድርጎል። በዚህም የትግራይ ተወላጆችን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በማጋጨት የስልጣን አድሜውን ለማራዘም የሚጠቀምበት ሴራ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። እንደትላንት ሁሉ ኢሕአፓ ወክንድ ይህን ተራ የወያኔ ተንኮል ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ነቅቶ አንዲያከሽፈው አበክሮ ይጠቁማል። በዚሁ የወያኔ ተንኮል መነሻነት አስር የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃንም ኢሕአፓ ወክንድ አጥብቆ ያወግዛል። የገንጣዮች ማርከሻው ኢትዮጵያዊ አንድነት ነውና በማናቸውም አካል የሚቃጣብንን ማነቆና ሴራ በጣጥሰን ወጣቶች ሁሉ በጋራ ሁለገብ ጸረ ወያኔ ትግላችንን በማፋፋም ሕዝባችንን አና አገራችንን ነጻ አናውጣ።” በማለት ኢሕአፓ ወጣት ሊግ ሁለገብ ጸረ ወያኔ ትግሉ እንዲፋፋም ጥሪውን አቅርቦ መግለጫውን አጠናቋል።