January 25, 2018
22 mins read

ሕዝብ ፍርሃትን እያሸነፈ፤ የወያኔም ጀንበር እየጠለቀች ነው! – ያሬድ ኃይለማርያም

 

ጥር 25 ቀን 2018 እ.ኤ.አ

ከብራስልስ፣ ቤልጂየም

ፍርሃትን እያሰረጸና እያነገሰ የኖረው ፖለቲካችን ነጻነታችንን፣ ክብራችንን፣ ታሪካችንን፣ ስብዕናችንን እና አብሮነታችንንም ጭምር ሲያኮስስና ሲያረክስ፤ እንዲሁም የወደፊት ተስፋችንም ላይ ጥላውን ሲያጠ እያየን ነው።  የማንኛውም አንባገነናዊ ሥርዓት ሥነ-ልቦናዊ መሰረቱ ፍርሃት ነው። አንባገነኖች ያላቸውን ኃይል ሁሉ የሚያሟጥጡት ሕዝብን በማሸበር የፍርሃት ቆፈን ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ ነው። ለዚህም አራት ነገሮችን በዋነኝነት ይጠቀማሉ። የመጀመሪያው የጡንቻቸውን ልክ ለማሳየት ዱላና ጠመንጃን በመጠቀም የይጭካኔ በትራቸውን በሕዝብ ላይ ያሳርፋሉ። ለመቀጣጫም ከማህበረሰቡ ውስጥ የነቁና ሥርዓቱን በአደባባይ የሚተቹ እና የሚያሳጡ ሰዎችን ዒላማ በማድረግ ያስራሉ፣ ይገርፋሉ፣ ያሰቃያሉ፣ አልፎም ይገድላሉ። ሁለተኛው ፍርሃት የሚያሰርጽበት መንገድ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በመቆጣጣር ማባሪያ በሌለው ፕሮፓጋንዳ ሥርዓቱን እያገዘፉ እና ሕዝብና ተቃዋሚዎችን እያንኳሰሱ፣ እያሳነሱ፣ እየወነጀሉና እያብጠለጠሉ ሽብር መንዛት ነው።

ሦስተኛው መንገድ በአገሪቱ ውስጥ ነጻና ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት እንዳይኖሩ ማድረግ ነው። የፍትህ ተቋማትን፣ የምርጫ አስፈጻሚውን አካል፣ ሕግ አውጪውን፣ የሲቪል ሰርቪሱን እና ሌሎች መንግስታዊ ተቋማትን ሙሉ በሙሉ በአገዛዝ ሥርዓቱ ካድሬዎች ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ ነው። ይህ አይነቱ አደረጃጀት እንደ አንባገነኑ ስጋት መጠን ከወረዳና ቀቤለዎች አልፎ እስከ አንድ ለአምስት የጥርነፋ መዋቅር ይወርዳል።  በእነዚህ በሁለቱ (ጠመንጃና ፕሮፓጋንዳ) ተጠቅሞ ፍርሃትን ማስረጽ የቻለ አንባገነናዊ ሥርዓት አንድን ሕዝብ ሰጥ ለጥ አድርጎ እየገዛ ለሞቆየት ይችላል። ሕዝብም በእነዚ ተቋማት ላይ እምነት እንዲያጣ ይደረጋል። ቀደም ያሉት ሦስቱ የማፈኛ ስልቶች በጊዜ እየተረቱ ሲመቱ አቅም እያነሳቸውና የማሸበር አቅማቸውም እየሳሳ ይሄዳ። ያኔ ወደ አራተኛው መንገድ ይገባል። አራተኛው መንገድ ሕግ የማፈኛ መሳሪ ማድረግ ነው። አፈናን የሚፈቅዱና የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የሚገድቡና የሚጥሱ ሕጎችን አጽድቆ በማውጣት የመብት ጥሰት ተግባራትን ሕጋዊ ማደረግ ነው። እነዚህን ሁሉ መንገዶች ሄዶና አቅሙን ሁሉ አሟጦም ሕዝብን በፍርሃት ማንበርከክ ያቃተው ሥርዓት ግን አንድ ሃሙስ የቀረው አንባገነን ነው የሚሆነው።

ብዙን ጊዜ እነዚህ ሁሉ ስልቶች አላዋጣ ያሏቸው አፋኝ ስርዓቶች የመጨረሻውን ሴይጣናዊ መንገድ ይያያዙታል። ይህውም ሕዝብ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭቶች እንዲከሰቱ ማድረግ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በቋንቋና በጎሳ የተሰበጣጠረን ማህበረሰብ እርስ በእርሱ ለማጋጨት ቀላል እና ሰፊ የሆኑ እድሎች ስላሉ የሞት አፋፍ ላይ የቆሙ አንባገነናዊ ሥርዓቶች በአሥራ አንደኛው ሰዓት የሚመዙት ሰይፍ ይህ በሕዝቦች መካከል የእርስ በእርስ ግጭቶች እንዲነሱ የሚያደርገውን ‘ግጭቶችን የማራባት ስልት’ በእንግሊዘኛ ‘distributive conflict model’ ነው። ይህ ሰይጣናዊ ግጭትን የማራባት ስልት የአንድ አገር ሕዝብ ጎሳውን፣ ቋንቋውን፣ ኃይማኖቱን ወይም ሌሎች ልዩነቶቹን መሰረት አድርጎና በታሪክ ሂደት የተፈጠሩና የሻሩ ቁርሾዎችንም ሳይቀር እየቆሰቆሱ አንዱ ሌላውን በጠላትነት እንዲፈርጅ፣ እርስ በርሱም እንዲጋጭና እንዲጨራረስ የሚያደርግ እኩይ የሆነ ፖለቲከኞች የሚቀምሩት መርዝ ነው። በዚህ አይነት ስልት በርካታ አገራት ተፈረካክሰዋል፣ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ እርስ በራሱ ተጋድሏል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ ኑሮአቸው ተናግቷል፣ አገር አልባም ሆነዋል።

ወያኔ ከላይ የተጠቀሱትን የማፈኛ መንገዶች ሁሉ፤ አፈሙዙን፣ ፕሮፓጋንዳውንም፣ የአፈና መዋቅሩንም ሆነ ሕግን የማፈኛ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም 26 ዓመታት እየተንገጫገጨም ቢሆን ሕዝብ እያስፈራራና እያሸበረ ከዚህ ደርሷል። ዛሬ የወያኔ ጀንበር ላትመለስ እየጠለቀች ነው። ሁሉም የማፈኛ ስልቶች አቅም ያጡ መሆኑን በአገሪቱ ውስጥ ላለፉት ሁለት አመታት ያለማቋረጥ የታዩት ሕዝባዊ መነቃቃቶችና እንቢተኝነቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። በዚህም ተስፋ የቆረጡት የህውሃት ባለሥልጣናት የመጨሻውንና ሴይጣናዊ የሆነውን ግጭትን የማራባቱ ሥራ ውስጥ ተጠምደዋል። በቅርብ ግዜ የተከሰተው እና ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው፣ በመቶ ሺዎችን ያፈናቀለው በኦሮሚያና ሶማሊያ ክልሎች አዋሳኝ ላይ የተቀሰቀሰው የጎሳ ግጭት፣ በተለያዩ ዩንቨሪሲቲዎች የታየው ዘር ተኮር ጥቃትና መቧደን፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልል በአማሪኛ ተናጋሪዎች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት፣ በእስፖርት ሜዳዎች ላይ የታየው ዘር ላይ ያነጣጠረ ዝልፊያና ግጭት፤ እንዲሁም ቀደም ሲል በኢሬቻ ባህል ላይ የተፈጸመውን አይነት አሳፋሪና የጭካኔ እርመጃ በዚህ ሳምንትም በጥምቀት ባዕል ላይ የመከላከያና የፖሊስ አካላት በወልዲያ የፈጸሙት አስነዋሪ የጥቃት እርምጃ ከብዙ በጥቂቱ የሚገለጹ ናቸው። ወያኔ የጎንዮሽ ወይም የእርስ በእርስ ግጭቶችን ስማፋፋት የፈለገባቸውን ምክንያቶች መገመት ከባድ አይደለም። ዋና ሊሆኑ የሚችሉትን ብናነሳ፤

  • ከሕዝብ ዘንድ ከተቀሰቀሰበት ቁጣ በተጨማሪ እንደ ፈረስ ይጋልባቸው ከነበሩት አባል ድርጅቶች መካከል አውራ የሆኑት ብአዴን እና ኦህዴድ አፍንጫህን ላስ ብለውታል። የጀመሩትም መርህ አዘል መሳሳብ ከህውሃት መንደር ሽብር ፈጥሯል።
  • ለ26 አመታት ድፍን ኢትዮጵያን በማን አለብኝነት ሲፈነጭባት፣ ያሻውን ሲያስር፣ ሲገድልና ሲያሳድድ የነበረው ወያኔ ዛሬ በተወሰኑ ክልሎች ይህን ማድረግ አልቻለም። ቄሮን ከኦሮሚያ ክልል አጠፋለው የሚለው የወያኔ ዛቻ ውኃ በልቶታል። ኮ/ል ደመቀን እንዳሻቸው ከቦታ ቦታ ማዛወር አልቻሉም። ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል።
  • አገሪቱ ከሁለት አመታት በላይ በተቃውሞ እየተናጠች ነው። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚሰሙት ድምጾች ‘የወያኔ የግፍ አገዛዝ በቃን፣ ለውጥ እንፈልጋለን’ የሚል ነው።
  • ይህን የህዝብ ቁጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያስቆመው አልቻለም። የመከለከያ ሥራዊትም ሊመልሰው አልቻለም። የወያኔ ‘የጥልቅ ተሃድሶ’ ኑዛዜም አድማጭ አላገኘም።
  • በጥቅሉ ሕዝብ ፍርሃትን አሸንፎ ሥርዓቱ በመሳሪይም፣ በፕሮፓጋንዳም፣ በአፋኝ ሕጎችም ሆነ በደህንነት መዋቅሩ የሚሰነዝረበትን ጥቃት ሁሉ ተቋቁሞ አደባባይ ለተቃውሞ ከመውጣት አልቦዘነም።

እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው ወያኔ ሁለት ብቸኛ አማራጮች እንዲኖት አስገድደውታል። አንዱ የማይዋጥለት፤ ሌላኛው ባያዋጣውም እድሜን የሚገዋለት። እነሱም፤

1ኛ/ የማይዋጥለት፤ ወያኔ ጡንቻው የዛለ መሆኑና ከፍለፊቱ ደግሞ ፍርሃትን አሸንፎ ወደሱ እየገሰገሰ ያለ ሕዝብ መኖሩን ማየት አልቻለም። ፍርሃትን ድል የነሳ ሕዝብ ደግሞ ነጻነቱን ሳይቀዳጅና የሥልጣኑና የአገሩ ባለቤት ሳይሆን አርፎ እንደማይተኛ የተረዳ አይመስለኝም። ይህን ከተረዳ በተሸናፊነት ስሜትም ይሆን ከልብ በመነጨ ቅንነት የፌዝ ሳይሆን ሁሉንም የአገሪቱን የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ (ነፍጥ ያነሱትን ኃይሎች ሁሉ ጨምሮ) አገራዊ መግባባትና በእውነተኛ ፍትህ ላይ የተመሰረተ እርቅ ማካሄድ ይኖርበታል። ለእዚህም እንደቅድመ ሁኔታ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅደ ሁኔታ መፍታት፣ አፋኝ የሆኑትን ሕጎች ሙሉ በሙሉ ማንሳት፣ የደህነነት መዋቅሩን ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆንና ከአንድ መንደር ልጆች እጅ እንዲዋጣ ማድረግ፤ እንዲሁም የእርቅና የሽግግር ጉባኤ ማካሄድ ይጠበቅበታል። ለዚህም ከሚዲያ ልፈፋ ባለፈ የተግባር እርምጃዎችንም ማሳየት የግድ ይላል። ይሁንና ወያኔ ለዚህ ዝግጁ ስላልሆነ በቅሩቡ ካደረገው ጥልቅ ግምገማ በኋላ መልሶ ድጥ ውስጥ መዘፈቁ ለእንዲህ ያለ ታላቅና ታሪካዊ ሊሆን ለሚችል የፖለቲካ ገድል አልታደለም ወይም ብቃቱ የለውም። እንግዲህ ወያኔ ይህን ታላቅ እድል ካቃጠለ የሚቀረው ሁለተኛውና የመጨረሻው ሴጣናዊው መንገድ ነው።

2ኛ/ ሴጣናዊው መንገድ ይህ መንገድ ከላይ የጠቀስኩት የአንባገነኖች የአፈና ስልቶች አልሰራ ሲሉ የሚመረጥ የመጨረሻው እድል ነው። ይህውም የሲቪል አስተዳደሩን ሙሉ በሙሉ ሊተካ ወደሚችል ወታደራዊ አንባገነናዊ ሥርዓት መቀየር ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና የተሰባጠረ ሕዝብ ባለባቸውና እራሳቸውን የሚያስተዳድሩና የራሳቸው ታጣቂና አስተዳደራዊ መዋቅር ባለባቸው አገሮች ቀላል ስለማይሆን እንደ መንደርደሪያ አንባገነኖቹ የሚጠቀሙት ከላይ ሴጣናዊ ብዮ የገለጽኩትን የጎንዮሽ ግጭቶችን የማራባትና በየስፍራው እንዲነሱ ማድረግ ነው። የግጭቶቹ ስፋትና መደጋገም የክልሎችን ሰላምና ጸጥታ የማስከበር አቅም ስለሚፈታተን የማዕከላዊው መንግሥት የአገር ደህንነት፣ ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅ በሚል ሽፋን የመጀመሪያውን ደረጃ እርምጃ ለመውሰድ በር ይከፍትለታል። ይኽውም በፌዴራሉ መንግሥት የሚመራ የመከላከያ ሠራዊት ማስፈር፣ የክልሎችን የጸጥታ መዋቅርም ተጠሪነት በቀጥታ ለማዕከላዊው መንግስት እንዲሆን ማድረግ ነው። ወያኔ እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ከዛም አልፎ የአገሪቱ ዋና ዋና አውራ መንገዶች ለአመጽ እየተጋለጡ ነው በሚል ከክልሎች እጅ ወጥተው በመከላከያ ሠራዊት እጅ እንዲወድቁ ተደርጓል። እነዚህ በየሥፍራው ሆነ ተብሎ በተከታታይ በመከላከያ ሰራዊት በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የዚህ ደባ አካል ናቸው። በዚህ ባሳለፍናቸው ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ በበደኖ፣ በወልዲያ፣ በሞያሌና በሌሎች የኦሮሚያ ክፍሎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት የተሰነዘሩትን ጥቃቶች ስንመለከት ከአንድ የአገሪቱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ድረስ ችግሩ ጎልቶ እንዲታይና አገሪቱም የአደጋ ቀጠና ውስጥ መውደቋን ማሳያ ነው። የሥርዓቱን እኩይ እርምጃ ከማስቆም ይልቅ ኢትዮጵያን የግጭት ቀጠና ውስጥ ካሉ አገሮች ጎን አሰልፈናታል የሚለው የምዕራባዊያን ‘አዛኝ መሳይ አንጓችነትም’ የእዚሁ ደባ አካል ይመስለኛል።

 

ይህ ሁኔታ ወዴት ያመራናል፤

‘የዘፈን ዳርዳርታ …’ እንደሚባለው ይህች የወያኔ ግጭቶችን የማራባት፤ በተለይም ዘር ላይ እንዲያነጣጥሩ በማድረግ የተጀመረው እኩይ ተግባርና የምዕራባዊያኑም አይን ያወጣ ድጋፍ እና በአፍሪቃ ቀንድ እየታየ ያለው የኃይል መሳሳብና ውጥረተ ተደማምረው በቅርቡ አገሪቱ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በምን ሁኔታ ልትቆይ እንደምትችል የሚያውጅ ዜናን እንድንጠብቅ የሚያደርግ ነው። ይኽውም ‘የኃይለማሪያም ደሳለኝ የሲቪል አስተዳደር በአገሪቱ ሰላም ለማስጠበቅና ዜጎችን ከጥቃት ለመታደግ አቅም ስላጣ ካቢኔው ፈርሶ ወይም ዋና ዋና ሥልጣኖቹ ተነስተው አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት እንደነበርው በልዩ ኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ተውላለች’ የሚል ይሆናል ብዮ እገምታለሁ። ይህ ደግሞ የክልሎችን እራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ሙሉ በሙሉ ከመገደብ አልፎ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል መስተዳድሮች ውስጥ ያለውን አዲስ የተነሳሸነትና ከሕዝብ ጋር የመቆም ስሜት በእንጭጩ ለመቅጨት ለህውሃት እድል ሊሰጥ ይችላል። የወያኔ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ወደ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት መቀየር ይችላል ወይ? በዚህ ውሳኔ ክልሎች ምን ድርሻ ይኖራቸዋል? የሕዝብስ ተቃውሞ ይዳፈናለ ወይስ ተጠናክሮ ይቀጥላል? በአገር ውስጥ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች እጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ይችላል? ኢትዮጵያስ ወዴት ታመራለች? የሚሉትን ጥያቄዎች አብሮ አንስቶ ማጤንና መወያያት የሚገባበት ወቅት ይመስለኛል።

 

ይህ እንዳይሆን ምን ይደረግ፤

ይሄ እጅግ ከባድ የሆነ ጥያቄ ቢሆንም ከወዲሁ ምላሽ ልንፈልግለት ግድ ይለናል። ለእኔ የሚታዩኝ መፍትሔዎች፤

  • በብአዴን እና በኦህዴድ የተጀመረው መርህ አዘል መሳሳብ ተጠናቅሮ እንዲቀጥልና ሌሎች በአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ሕዝቦችንም ባሳተፈ መልኩ እንዲንጸባረቅ ማድረግ። እነዚህ ድርጅቶችና አመራሮች ለራሳቸውና ለሚወክሉት ሕዝብ፤ በዋነኝነትም ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማቆየትና ያንጃበበውን የእልቂት አደጋ ለማስቀረት ህውሃት ያልደፈራቸውን የሰላምና የእርቅ መንገዶች በመድፈር በጀመሩት የመሳሳቢያ በመድረኮቻቸው ላይ ተቃዋሚ ኃይሎችን ማሳተፍና የውይይት በሩን መክፈት፤
  • ተቃዋሚዎች ከእነዚህ ሁለት ድርጅቶች በመማር እናንተም እርስ በእርሳችው መርህ አዘል መሳሳብ ማድረግ።
  • ሕዝብም የወያኔን እኩይ ተለዕኮና ተንኮል በቅጡ በመረዳት ከእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ዘርና ኃይማኖት ተኮር ከሆኑ ቅራኔዎች ተቆጥቦ የጀመረውን ከአንባገነናዊ ሥርዓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል የጀመረውን የነጻነት ጉዞ አጠናክሮ ቢቀጥል፤

እርስ በእርስ ሳንተላለቅ ነጻ የምንወጣበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትበቃናለች። ሃብቷንም በአግባቡ ካበለጸግነው ከራሷም አልፎ ለሌሎች ይተርፋል። የአንዱ ብልጽግና የሌላው ሞትና ውድቀት የሚሆንበት ታሪክም ያከትማል።

 

ለሰማዕታት ቤተሰቦች መጽንናቱን ይስጥ!

እግዚያብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop