በኖርዌ ኦስሎ ከተማ የኢጣሊያ ግዛት በሆነችው ላምፔዱሣ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የሻማ ማብራት ሥነሥርአት ተካሄደ

ሄለን ንጉሴ / ከኖርዌ

በኦክቶበር 20, 2013 የኢትዮጵያ ሥደተኞች ማህበር በኖርዌ የኢጣሊያ ግዛት በሆነችው ላምፔዱሣ ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያና ኤርትራዊያን ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን አስመልክቶ በኖርዌ ኦስሎ ከተማ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃዘናቸውን ለመግለፅ የሻማ ማብራት ሥነስርአት ተካሂዷል።

ሥነስርአቱ በኖርዌጅያን የሰዓት አቆጣጠር 16፡00 ላይ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን በመቀጠል በኖርዌ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበር የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን በመግለፅ አጭር ንግግር አድርገዋል። እንዲሁም ከተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት፦ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፤ ከፕሮቴስታንት የሐይማኖት ተከታዮች እና ከእስልምና እምነት ተከታዮች ተወክለው የመጡ አባቶች በየተራ ንግግር በማድረግ የስደትን አስከፊነት በመግለፅ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማቸውን ልባዊ ሐዘን በመግፅ እና ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝተው ፀሎትም አድርገዋል።

እንዲሁም የተለያዩ የፓለቲካ አክቲቪስቶች በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ያጡትን ወገኖቻችንን አስመልክቶ የተላያየ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የስደት መንስኤው ምን እንደሆን ሲጠቁሙ በሐገራችን ያለው ብልሹ አስተዳደር መሆኑንና የሰብአዊ መብት ጥሰቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፤ እንዲሁም የፖለቲካውና የኑሮ ሁኔታ ዜጎች ሐገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ እንደሚያስገድዳቸው ተናገረዋል። በተጨማሪም መታሰቢያነቱ በአደጋው ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን የሚሆን አጫጭር ግጥሞች፤ መዝሙር እና እንጉርጉሮ በሥነስርዓቱ ላይ ቀርበዋል።

በመጨረሻም ከተናጋሪዎቹ በአብዛኛው ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ ሰዎች ከሐገራቸው እንዳይሰደዱ የስደት ምንጭ የሆነውን የወያኔ ጨቋኝና አረመኔ ግፈኛ አገዛዝ በፍጥነት ማስወገድ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመው በሐገር ቤትም ሆነ በውጭ ሐገር የተጀመረውን ትግል በመቀላቀል ለመጨረሻ ጊዜ ሥደትን ከምንጩ ማድረቅ እንዳለብን አሳሥበዋል።

ባጠቃላይ የሻማ ማብራቱ ሥነስርዓት ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ በሐዘን ድባብ የተዋጠ እና በለቅሶ የታጀበ እንዲሁም የብዙ ሰዎች ልብ ያሳዘነ ሥነስርአት የነበረ ሲሆን በ16:00 የተጀመረው ዝግጅት ከምሽቱ 18፡00 ሰዓት ላይ ተጠናቋል። ሙሉውን ዝግጅት ከዚህ ቪዲዮ ይመልከቱ

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይጋብዟል እንግዳ እንደ መልካም ሞላ!

1 Comment

Comments are closed.

Share