ኤርያልን የገደለው!!!! ………

(ቴዲ ከአትላንታ)

ኤርያል ካስትሮ ከአስር ዓመት በፊት ሶስት አሜሪካውያን ወጣት ሴቶችን አፍኖ ቤቱ አስቀመጠ። ለ 10 ዓመት ያህልም የፈለገውን እያደረገ ሲያሰቃያቸው ኖረ። ዋጋ የማይተመንለትን ወጣትነታቸውን ወሰደባቸው (ሰረቃቸው)፣ በዚያ ጨለማ በምድር ቤቱ ውስጥ አስቀምጧቸው አስር ዓመት ያህል ሲቆዩ ፣ እንወጣለን ብሎ ማሰብ ረስተው ነበር። ቦ ጊዜ ለኩሉ (ለሁሉም ጊዜ አለውና) አንድ የተመረጠች ቀን ምክንያት ተፈጥሮ ነጻ ወጡ።

ከዚያ ኤርያል ካስትሮ ተያዘ፣ አሜሪካም የቀረውም ዓለም ጉድ አለ ! ጨካኙ ካስትሮ ፍርድ ቤት ቀረበ፣ የገዛ ወንድሞቹና ልጁ ሳይቀሩ አይንህን ላፈር አሉት፣ የሰው ዓይንና ርግማን ሳይገድለው ቀረና፣ ፍርድ ቤት ቀርበ ውሳኔ ተሰጠው፣ የፍርድ ቤቱም ውሳኔ – ሞትን አስቀረና ዕድሜ ይፍታህ ፈረደበት። እዚያም ሞትን አመለጠ። ከዚያ እስር ቤት ገባና የ እስር ኑሮውን ሀ ብሎ ጀመረ። ለካ ከዚህ ሁሉ ከውጭ ሊመጣ ይችል ከነበረው የሞት ፍርድ ያምልጥ እንጂ፣ ህሊናው ፈርዶበት ነበር። ከሁሉም የህሊናው ፍርድ፣ ጸጸቱ፣ የጥፋተኝነት ስሜቱ፣ የበደለኝነት ግለቱ አላስቀምጥ ቢለው …..፣ የ እስር ቤት ምግብ እየበላ፣ ቴሌቪዥን እያየና ካርታ እየተጫወተ መኖር ሲችል ዛሬ ንጋት ላይ ራሱን አንቆ የራሱን ህይወት አጠፋ ተባለ።

…. በምንሰራው ግፍና በደል ከሌላው ዓለም ፍርድ እናመልጥ ይሆናል፣ ከራስ ህሊና ግን የት እናመልጣለን? ሰዎች ላይ ግፍና በደል ሰርተን ፣ አገር በመቀየር ፣ በገንዘብ ፍርድ በመግዛት፣ ስማችንን በመቀየር፣ በትልቅ ግንብ በመከለል የምናመልጥ ይመስለን ይሆናል፣ ትልቁ ፈራጅ ህሊናችንን ግን የትም አናመልጠውም። በደል፣ ግፍ፣ ተንኮል፣ ምቀኝነት …. ይቅርብን። ነገ የሚጸጸተንን ዛሬ ለምን እናደርጋለን ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰሞነ-ሕማማት የበረታ፣ በተንሳኤ ይሽራል! - ሙሉዓለም ገ/መድኀን ከሁመራ-ጎንደር

1 Comment

Comments are closed.

Share