December 17, 2016
6 mins read

እንዲያው ዝም እንበል? – ግጥም

ምርቃት እርግማን፤ ደግ ክፉ ከሆነ፤
እንዲያው ዝም እንበል፤ የሞተ ካልዳነ።
እሬሳችን ቀብረን፤ ሃዘን እንቀመጥ፤
ዘመድም ተረድቶ፤ እንባውን ያሟጥጥ።
ብረቱን እንጨት ነው፤ እንጨቱን ብረት፤
ብለን ላንግባባ…አጉል መሟገት።
እያየ የማያይ፤ ሰምቶም የማይሰማ፤
አይን፤ ጆሮ፤ ከጠፋ በምን እንስማማ።
ስራውን ለሰሪው…ላድራጊው ብንተው፤
ብድር ከነወለድ…ከፋዩ እርሱ ነው።
ኢትዮጵያ ተወልደን ኢትዮጵያ ካደግን፤
የአንድ ሀገር ሕዝቦች፤ ኢትዮጵያውያን ነን።
በዓለም ዙሪያ ብትሄድ፤የምትታወቀው፤
በትውልድ ሀገርህ፤ በዜግነትህ ነው።
የመብት እኩልነት…ምህዳር እንዲሰፋ፤
በዘር መደራጀት፤ ማንነት ባልከፋ፤
ከጀርባው ያለው ነው፤ አንገት የሚያሰደፋ።
ትግሬ፤አማራ፤ኦሮሞ…በዘር ተደራጀ፤
መልካም፤ ግን ለሀገር…ለኢትዮጵያ ማን በጀ?
ከዝንጀሮ ቆንጆ…ምን ይመራርጡ፤
ነገር ዱለት ሆኖአል…ጠፍቶ መላቅጡ።
ጋዜጣ፤መድሔት…ሬድዮ፤ቴሌቪዥን፤
የወሬ ቋት በዝቶ…አቅቶአል ለማመን።
እውነትና፤ሀስት… ድብልቅልቁ ወጥቶ፤
ሀቁን፤ከውሸቱ…መለየት አቅቶ።
ሁሉም ትክክል ነኝ…በሚልበት ዘመን፤
እንዲያው ዝም እንበል፤ ቀርቶአል መተማመን።
የእሰጥ አገባው …ውይይት ክርክር፤
የህብረት፤የጥምረት…የመደረክ ድርድር፤
የአንድነት ግንባር…የሸንጎ ንግግር፤
መሆን፤ አለመሆን…ከሌለው ቁምነገር፤
ምን ጥቅም ያስገኛል …አፍ ከፍቶ መናገር።
መረጃ፤ጭብጥ ያለው… ሃቁ ከተካደ፤
ሃሰት እውነት መስሎ…ሰው ካወናበደ፤
መዳፍ፤መወያት…ምንም ካልፈየደ፤
እንዲያው ዝም እንበል…በሬ ከወለደ።
እውነቱን ከሀሰት…አውቆ ለመለየት፤
በጣም ያስቸግራአል…ያላዩትን ማየት።
ጆሮ አልሰማም አይል…ዓይንም አላነብ፤
አዕምሮ ያስጨንቃል…እውነት መገንዘብ።
ፎቶና ወረቀት…ቪድዮም ይሰራል፤
ፈጥሮ አቀናባሪ…ቆርጦ ቀጥል ሞልቶአል።
ታዲያ ምን እንበል?…ነገሩ ረቀቀ፤
ጥበብ፤ፍልስፍን…እውነት ከእኛ አራቀ።
የላስቲክ አበባ…ከተፈጥሮው በልጦ፤
በክብር ይቀመጣል…አፍክቶና አጊጦ።
አይበላ፤አይጠጣ…አይበቅል አያድግ፤
ተመስሎ ይኖራል…ሳይደርቅ ሳይጠወልግ።
በየሱቁ ያለው…የአሻንጉሊት ሰው፤
ለብሶ፤ ቢሽቀረቀር… በድን የሆነው፤
የዕቃ ማሻሻጫ… መነገጃ ነው።
አይሰማም፤ አይለማም…ተገትሮ ይውላል፤
እንደው ዝም እንበል፤ዝምታው ይሻላል።
ልክ እንደ ባቢሎን…ቋንቋ ተደባልቆ፤
መግባባት አቅቶን…ምላሳችን ደረቆ።
ከአለፈው ተምረን …ስህተትን ከማረም፤
ዛሬም ባለበት ሂድ…ጥፋት መደጋገም፤
ችግር ያባብሳል…አይሰጠንም ሠላም፤
እንዲያው ዝም እንበል…ችክ ምንም አይጠቅም።
ከጦር ሜዳው ፍልሚያ…ከጀግኖቹ ቦታ፤
የባንዳዎች ወሬ…ገብቶ ጦር ሲያስፈታ።
የተደረገውን ማወቅ…እናውቃለን፤
ከተናገርነው ግን…ጠፍተን እናልቃለን።
ብሎ እንዳለው ፈሪ…የተረት ያይደለ፤
እንቆቅልሽ መፈቻ…ሌላ መንገድ አለ።
እውነቱን ተናግሮ…የመሸበት ማደር፤
የአበው አባባል …ብሂላቸው ነበር፤
ትላንት ታሞ፤ ሞቶ…ዛሬ ባይቀበር፤
እንደው ዝም ብለን…ታሪኩን እንዘክር።
ዛር ወርዶ ጨፍሮ…ካልተካደመለት፤
አጓርቶ አያበራም…ሃጃ እስኪወጣለት።
ለይቅር ለእግዚአብሔር…መሸነፍ ካቃተን፤
የዘመናት ቁርሾ..አንቆ ከጎተተን፤
በቃ ዝም እንበል…ጠብ ማጫሩን ትተን።
በእልህ ተይዞ…ልብ ከደነደነ፤
ትርፉም ሰድብ፤ ጥላቻ…በቀል ሰለሆነ።
የሞቀው ቀዝቅዞ..የጋለው እሰኪበርድ፤
እርቅ፤ይቅርታ ሰፈኖ…ሠላምም እሰኪወርድ።
አርቆ ማስተዋል…ትዕግስት ይጠይቃል፤
የቆጥ አወርድ ካሉ…የብብት ይወድቃል።
ማዳመጥ፤መረዳት… መቻቻልን ንቀን፤
በሄድንበት መንገድ…እንዳንቀር ወድቀን፤
የዘረኝነት ጥቅም…ጉዳቱንም አውቀን፤
የያዘን አባዜ…ሰልችቶ እሰኪለቀን ፤
ሰከን፤ረጋ፤ረጋ…ማሰተዋሉን ይስጠን።
ሁሉም ለበጎ ነው…ይሄኛውም ያልፋል፤
እንዲያው ዝም እንበል…ሆድ ከሀገር ይሰፋል።
የገሃነም ደጆች ሊያጠፉ የማይችሉዋት፤
ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አንዲት ናት።
ከሽመልስ ተሊላ።
ታህሳሰ 7 2008 ዓ.ም።

Go toTop