ከ ወልደማርም ዘገዬ
የቀድሞው ኢትዮጵያዊ የአሁኑ ኤርትራዊ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድኃኔ “ኤርትራ እንደ እናት አገር፤ ችግሮችና ፈተናዎች ትናንትም ዛሬም” በሚል ርዕስ በአውሮጳውያኑ የዘመን አቆጣጠር ጥር ወር 2013 የጻፉትን ጥናታዊ ዘገባ በፍላሼ አሰንብቼ ዛሬ ጧት ቁርሴን አወራረድኩበት፡፡ ኤርትራ ለእርሳቸው የምታስጨንቀውን ያህል ኢትዮጵያም – ባለቤት ያጣችዋ ከርታታዋ ኢትዮጵያም ለእኔ እንደእናት ሀገር ታስጨንቀኛለችና የተሰማኝን ልናገር ብዕሬን አነሳሁ፡፡
ግን በዚህች የተረገመች ሀገር – በዚህ የዜጎች መብት ክፉኛ በሚረገጥባት ሀገር የመብራት መጥፋት በየደቂቃው ስለሚከሰት በምፈልገው ፍጥነት መጨረሴን እጠራጠራለሁ፡፡ አንዳንዴ በቀን ለቁጥር ለሚያታክት ጊዜ ያህል መብራት ይቆራረጣል፤ አሁን ድርግም ይልና ከደቂቃዎች በኋላ ሊመጣ ይችላል፤ የምትሠራውን ቅጥ ያሳጣብሃል – በልጆቼ አነጋገር ‹ሙድህን ይሠርቅብህ›ና ልትሳነፍ ባስ ሲልም ልትጽፍ ያሰብከውን ከነጭራሹ ልትተወው ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ በኛ መንደር በቀደም ዕለት የጠፋ ከ27 ሰዓታት በኋላ ትናንት ማታ ነው መብራት የመጣልን፡፡ ስልኩም ውኃውም እንደዚሁ ነው፡፡ የቤት ስልክ ከሚሠራበት ጊዜ የማይሠራበት ይበልጣል፡፡ የአንዱን ሊጠግኑ ሲመጡ የሌላውን አበላሽተው ሊሄዱ ይችላሉ – ጠርተሃቸው በመቁሽሽ እንድታሠራቸው፡፡ ውኃ ወር እስከወርም ላታገኝ የምትችልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ማንን ትጠይቃለህ? በየቢሮው አናት ‹የዚህና የዚህ የሥራ ሂደት ባለቤት› የሚል ጽሑፍ ተለጥፎ ብታይም ማንም ጉዳይህን ከቁብ የሚጥፍልህና የሚያነጋግርህ ሰው የለም፡፡ ስቃይ ነው ልጄ፡፡ የዴሞክራሲው ነገር እዬዬም ሲዳላ ነውና አታስበውም፡፡ አሁን በአንጻራዊነት ከሚታዩ መልካም ነገሮች ውስጥ ዋናው የመንገዶች መስፋፋት ነው፡፡ ይህም ቢሆን በየቀኑ በመቶዎችና በሺዎች ከሚጨምረው የተሸከርካሪዎችና የእግረኞች ብዛት ጋር በጭራሽ ሊጣጣም ባለመቻሉ ችግሮች ሲወሳሰቡ እንጂ ሲፈቱ አታይም፤ የሕዝቡን ብዛት በየሥፍራው እንደጉንዳን ሲርመሰመስ ስታይ ሰው ነገር ዓለሙን እርግፍ አድርጎ ትቶ ከመፈላፈል ውጪ ሌላ ሥራ ያለው ላይመስልህ ይችላል፤ የሀገሪቱ ዋና ራስ ምታት የራሴ ነው የምትለው ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆር፣ ሁሉንም እኩል በሚያሣትፍ የዕቅድና የበጀት ምደባ ሀገሪቱን በተገቢው የዕድገት ጎዳና የሚያራምድ ተቆርቋሪ መንግሥት ማጣት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ቁጥር በአደገኛ ሁኔታ መጨመርም ነው – እኔ ራሴ ባለቤቴ ዘጠንኛውን ልጃችንን ልትገላገል ጥቂት ሣምንታት ይቀሯታል፤ ይህን የምናደርገው ተስፋ ከመቁረጥና በነሱ ለመጦር ከማቀድ አንጻር ነው – ሌላ መዝናኛም ከማጣት ጭምር(እንዴ! ምን ማለታችሁ ነው – እስከግማሽዋ በአረፋ የተሞላች አንዲት ብርጭቆ ድራፍት እንኳን ባቅሟ በሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከብር 2.20 ሽቅብ ተወንጭፋ አሥር ብር ስትገባ! – ታዲያ መራባት ይነሰን?)፡፡ ሰው ተስፋ ሲቆርጥ ከ‹መብላት› እና ‹መጠጣት› ውጪ ያሉትን አብዛኞቹን የ‹መ›ሕጎች ያከብራል፡- መናደድ፣መበሳጨት፣መሰደድ፣መጠጣት፣መዋለድ፣መእንትን…፤ “ጠጪነትና የሕዝብ ብዛት በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመር የተስፋ መቁረጥ ምልክቶች ናቸው” የሚባለው አዲስ ምሳሌያዊ አባባል ለካንስ እውነት ነው! ምን ልበልህ ወንድሜ! የሀገርህ ነገር እጅግ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሁለተኛና ሰባተኛ ዜጋ ሆነህ ከመኖር አውሮፓ ውስጥ ውሻና ድመት ሆነህ ብትፈጠር በእጅጉ ይሻልሃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የወያኔ ተለማማጭ ሀብታም ከምትሆን የጓንታናሞ የፍርድ እሥረኛ ብትሆን ላንተ ሉተሪ ነው፡፡ ብሬቪክ የሚባለው ሰባ ምናምን ሰው የገደለው ስዊድናዊ ታራሚ ከእሥር ስወጣም ገና ብዙ ሕዝብ እፈጃለሁ እያለ መስፈራርቾውን በቀጠለበት ወቅት ‹ክፍሌ በሰዓቱ አልጸዳልኝም› ወይም ‹ክፍሌ በቂ ብርሃን ስለሌለው በአስቸኳይ ይለወጥልኝ!› በሚል የማያዳግም ቃል (‘ultimatum’) የማረሚያ ቤቱን ባለሥልጣናት እያሽቆጠቆጠ መብቱን በሕግ ማስጠበቁን ስትሰማ ከጫካ የመጣ ወሮበላ እንደፈለገው የሚደፈጥጥብህን የአንተን ኢትዮጵያዊነት ያሻው ቀቅሎ እንዲበላው ከአእምሮህ መንትገህ ለመጣል ልትዳዳ ትችላለህ፡፡ ጊዜው የፈተና ነው ወንድሜ፡፡ እናም ይህችን ጊዜ እንደምንም ታገላትና ሳትበለሻሽ ተወጣት፡፡ ታሪክ እንደሆን ይቅርታ ማድረግን አያውቅም፡፡ ጽጌረዳን በቀላል አናገኝም፤ እሾኋ ውድነቷን ሳይጨምርላት አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ አይደለም፡፡ ዛሬ በስሟ የነገዱና ሕዝቧን የዶጋ ዐመድ ያደረጉ ዱርዬ ልጆቿ ሁሉ አይቀጡ ቅጣት ሲያገኙ ዳፋው እንዳይደርስህ ተጠንቀቅ! ለአንድ እንጀራ ብለህ እንደዔሣው ብኩርናህን ለሆድህ አትሽጥ፡፡ የሰው ወርቅ አያደምቅምና የጠፋህ ወገኔ በጊዜ ተመለስ!!
አንተ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ እያልክ በየሰው ሀገር አደባባይ ትጮሃለህ፡፡ እዚህ ሰዎች ከሰውነት ተራ እየወጡ ተንቀሳቃሽ በድን እየሆኑልህ ነው፡፡ ያንተን ጩኸት ራሱ አይሰሙም – ብዙዎቹ የሚሰሙበት ፍላጎትና መንገድም የላቸውም፤ደንበኛ ሰሜን ኮሪያውያን ሆነንልሃል፡፡ ‹ወንድሞቼንና እህቶቼን ነጻ አወጣለሁ› ብለህ ብትመጣ እንኳን፣ ነጻነት የሚገባው(የሚያስፈልገው) መሆኑን የሚረዳ ዜጋ ለማግኘት ይቸግርሃል፤ የሚመጣውን ቁጣና መቅሰፍት ሁሉ በቀላሉ እየተለማመደ ለሁሉም የግፍ አገዛዝ ተንበርካኪ ትውልድ እየተበራከተ ነው፡፡ ግዴለህም አንዳች የተደገመብን ነገር መኖር አለበት፡፡ ፈዘንና ደንግዘን በመተታዊ የአንደርብ ሥራ ወደ ጋንነትና እንሥራነት የተለወጥን ግዑዛን ነገሮች መስለንልሃል ወንድምዬ፡፡
አንድ ለአንድ አካባቢ እንግዳ የነበረ ሰው መንገድ ይጠፋውና አንዱን መንገደኛ ይጠየቀዋል፡፡ “የኔ ወንድም እንደዚህ የሚባል መንደር ልሄድ ፈልጌ ነበር፡፡ እስኪ እንዴት እንደምደርስ ጠቁመኝ ወዳጄ” ያም ሰው “ ይሄን መንገድ ቀጥ ብለህ ትሄድና እመስቀልኛው መንገድ እዚያ ወዲያ ስትደርስ ግራህን ይዘህ ትታጠፋለህ፤ ከዚያም ጥቂት እንደሄድክ ግራና ቀኝ የሚገኙ ሠፈሮችን ታገኛለህ፡፡ አንደኛው ግን የቡዳዎች ሠፈር ስለሆነ ሰው ጠይቅና ተጠንቅቀህ እለፍ፡፡” ይለዋል፡፡ እዚያ ጠንቀኛ መስቀልኛ መንገድ ላይ ሲደርስ ቀድሞ የተነገረውን ያስብና በቡዳነት ይታማ ከነበረው ሠፈር የመጣ አንድ ሰው እዚያ አካባቢ ስለነበር በየዋህነት “ አንቱ ጋሼ – የቡዳው ሠፈር የትኛው ነው?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ ያም ሰው ምንተፍረቱን “እኛም እነሱን እንላለን፤ እነሱም እኛን ይላሉ” ይለውና ወዶ እንዲገባብት ምርጫውን ለጠያቂው ትቶ ንዴቱ እንዳይታወቅበት ለማድረግ በመጣር ይለየዋል፡፡ “እነሱም እኛን ይላሉ፤ እኛም እነሱን እንላለን!”
‹ኤርትራውያን› የኛ የ‹ኢትዮጵያውያን› ችግሮች መባቀያ እንደሆኑ የምናምን ወገኖች ጥቂቶች አይደንለም፡፡ በተገላቢጦሹም እኛ የነሱ ችግሮች ምንጭ እንደሆንን የሚያምኑ ኤርትራውያን አሉ፡፡ የሁለታችንም ችግሮች አንድ መሆናቸውን ግን እያጤንን መጥተናል – ለዐይን ይበጃል ያሉት ኩልም ዐይንን ሊያጠፋ መቃረቡን እየተረዳን ነው – ‹ናጽነት› ወይ ‹ባርነት›፤ ዕድሜ ደጉ የነጻነትንም የባርነትንም አዲስ ፍቺዎች እየተገነዘብን ነው፡፡ በዕንቆቅልሾች ታጥረናል ማለት ይቻላል፡፡ ለቅጣት በተላኩ ሁለት የአክስትና የአጎት ልጆች ጦስ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እየታመሰና የቁም ስቅሉን እያዬ ነው፡፡ ‹ዘይገርም ሻሸመኔ ትብስ ኮፈኔ› ይላሉ ወንድሞቼ የሚደንቅ ነገር ሲገጥማቸው፡፡
ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ ውኃ ጣዕሙ አንድ ነው፡፡ መለስና ኢሳይያስ – የአንድ ሣጥናኤል ሁለት ገጽታዎች – ከአንድ የጥፋት ወንዝ የተቀዱ በመሆናቸው በሃሊዮ በገቢር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የበሰበሰና የገማ የገለማ ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማፈራረስ ሕዝብንም ከሕዝብ ማቃቃርና ማፋጀት በውጤቱም የራሳቸውን ሰይጣናዊ ተልእኮ ማሣካት ስለሆነ እነዚህ ሁለት የሥጋ ዝምድናና የዓላማ ቁርኝት ያላቸው ሰዎች በሁሉም ነገር አንድ ናቸው፡፡ የተረገሙና ከእግዚአብሄር መንገድ የወጡ – ለቅጣት የመጡ እንደመሆናቸው መጨረሻቸው ቀርቶ መነሻቸውና መገባደጃቸው ራሱ የሚያምር አልሆነም፡፡ መለስ በ‹ለጋነት› ዕድሜው ሊቀጭ የቻለው በሕዝብ ፍቅር ምክንያት እንዳልሆነ እንኳን ፈጣሪ ሰይጣን ካቦኣቸውም(Foreman) ያውቃል፡፡ በቀላል ትዝብት መለስ ትዳርና ልጅ ሊወጣለት ያልቻለው በሕዝብ እርግማንና በሕዝብ ዕንባ ምክንያት እንጂ የመልካም ሥራ ተፈጥሮ ኖሮት ያንን ደግነቱን ፈጣሪ ዋጋ አሳጥቶበት እንዳልሆነ አሁንም እንኳንስ እግዚአብሔር ዲያብሎስ ራሱም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ኢሳይያስ አፈወርቂ እንደጎረምሳ ትዳሩን እያመናቀረና ባለቤቱ በሽማግሌዎች ብርታት እየለዘበች እሱ የመጠጥና የቁማር ሱሰኛ ሆኖ የቀረው፣ የረባ ግለሰብኣዊና ማኅበራዊ ሕይወት ሳይመራ ዕድሜውን በከንቱ እየጨረሰ ያለው፣ የበሽታና የጋንጩሮች ዋሻ ሆኖ እንዳበደ ውሻ እየተቅበዘበዘ የሚኖረው በሕዝብ እርግማን እንጂ በጽድቅ ሥራው ምክንያት አይደለም(ልብ አድርጉ! አማሮችን ለተዋጊዎቹ የዒላማ ማለማመጃ እያደረገ የነበረ የሉሲፈር ቀኝ እጅ ነው! To be honest, I was not there in any form of presence, but I can assume as if I were there; my instinct tells me that he and his protégé, His Crookedness Meles Zenawi, have been doing every crime that men can do against the so called Amharas! And it is my sincere conviction that their karmatic uncleanliness will never let them go without punishment, possibly here or probably there, or maybe in both realms until the time they become as immaculate as a newborn sinless babe!)፡፡ የእንጨት ሽበቶቹ ስብሃት ነጋ፣ ሞራ-ራስ የኑስ፤ ሥዩም መስፍን … በልዩ ልዩ ሱሶችና የበሽታ መርዞች ተለክፈው ባብዛኛው እንደነሱው ሰካራምና ሀሺሻም በስተቀር እዚህ ግባ የሚሉት አንድም ቁም ነገረኛ ልጅ ሳይወጣላቸው ዕድሜያቸውን በመንዘላዘል እንዲሁ በከንቱ እየጨረሱ የሚገኙት በእርግማን እንጂ በምርቃት በረከት አይደለም – ጎበዝ በደንብ እንደማመጥ! የእርግማን ጦር ሲወጋ እንጂ ሲወረወር አይታይም የሚባለውን ነባር ሥነ ቃል አንርሣ! ከጥንትም ቢሆን ሕዝብ ያለቀሰበት መቅኖ የለውም – በተለይ በኢትዮጵያ፡፡ ለዚህም ነው አሁን ማንም በማንም ላይ እንትኑን እንትን ይበል በሂደት ግን ‹በሠፈረው ቁና ይሠፈርለታል› በሚለው ነባር መለኮታዊና ተፈጥሯዊ ሕግ መጽናት የሚገባ መሆኑን በጥብቅ የምሰብከው፡፡ የቻለ እንዲያውም በክፉዎች አይቅና – ብድራታቸውን ያገኛሉና፡፡ ክፉዎች ለጊዜው የተሳካላቸው ቢመስልም የማታ ማታ ተጎጂዎች ናቸው፡፡ ሁለት ስህተቶች አንድን የተበላሸ ነገር ሊያስተካክሉ ወይ ሊያቃኑ እንደማይችሉም መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ስህተት ስህተትን ይወልዳል እንጂ የተዛነፈን አያቃናም፡፡ (Two wrongs don’t make a right.) ለዚህም ነው ወያኔን ሳይወለድ እንደጨነገፈ ሽል መቁጠር የሚገባን፡፡ ግርፋቱ ግን ከባድ ነው!
እውነት መስሎ የታየኝን እናገራለሁ፤ እጽፍማለሁ፡፡ በእንትን የተጥለቀለቀ የንግግር ዘይቤያችንን የምጥሰው ሆን ብዬ ነው፡፡ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን መጥፎ ድርጊት ላለማድረግ እንጂ ቋንቋ በማሳመር እውነትን ለመሸፈን መሆን የለበትም፡፡ ባለፈው ሰሞን የላክሁትን አንድ ጽሑፍ አንብቦ አንድ ወዳጄ በስልክ እንዲህ አለኝ፡፡ “አንተ ወልዴ! ምን ነካህ? አበድክ እንዴ? እንዴት በስሜት ውስጥ ሆነህ ትጽፋለህ? ለምን ቀዝቀዝ ስትል አትጽፍም? ተናደህ ከጻፍክ እኮ ሰው ይቀየምሃል፤ተናደን የምንቀጣው ልጅ ሊጎዳብን እንደሚችል አታውቅምን? የምትለው ነገር እውነትነት ቢኖረው እንኳን በቃላት መረጣ ተጠምዶ አንዱ የሌላኛውን ስሜት ላለማጎፍነን እርስ በርስ ሲሞከሻሽ በኖረ ማኅበረሰብ ውስጥ ይህን ያህል ግልጽነት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ድረ ገጽ ያን ጽሑፍህን ለጥፎት ሲያበቃ ከሁለት ቀናት በኋላ ከውጪ ዐዋቂ ይሁን ከውስጥ ዐዋቂ አስተያየት በመነሳት ገንጥሎ ጣለው፤ አንድ ቦታ ደግሞ ስሜታቸውን እንዴት እንደነካህባቸው ባልገባኝ ሁኔታ መርቅነህ እንደጻፍከው አስተያየት የጻፉብህ አሉ፤ ለምን …” ሲለኝ ብልጭ አለብኝና “ኦ!ኦ! የኔ ወንድም ዝም ብለው ካዳመጡህ ብዙ ትቀባጥራለህ፤ አንተ ራስህም የፈለግኸውን ልትለኝ ትችላለህ፡፡ የፈለጋችሁትን በሉ ሃሳቡ አይበላኝም፡፡ እኔ ካልተናደድኩ አልጽፍም፡፡ ስናደድ የምጽፈው ለእኔ እውነትነት አለው፡፡ ያልተበረዘና ያልተከለሰ – እከሌን ላስቀይም ወይም ላስደስት የማልልበት እንደወረደ ዓይነት ሃሳብ የማገኘው ተናድጄ ስጽፍ ነው፡፡ አንባቢም ያሻውን የማለት መብት አለው፡፡ የሚዲያ መድረኮችም ሲፈልጉ ይለጥፉ ሳይፈልጉ ቀድደው ይጣሉት – በኔ የቁጣ ንግግር ሰማይና ምድር አያልፉም፡፡ ሰለጠነ በሚባለው ዓለም የአሜሪካ ሴኔትና ኮንግረስ፣ የእንግሊዝ ፓርላማ፣ የእስራኤል ክነሴት፣ የራሽያ ዱማ… በስብሰባዎቻቸው ‹f**k off, idiot, son of a bitch, …› እየተባባሉ ተሰዳድበው ሲያበቁ ከስብሰባው ሲወጡ ሁሉንም ረስተው አብረው ይጫወቱ፣ ይበሉና ይጠጡስ የለምን? እኔስ ምን አጠፋሁ? ‹የትግሬ ወያኔ እንትን አለብን፤ እነእንትና ከፈለጉ እንትን ይሁኑ፤ እንትኔ መጥቶብኝ ወደ እንትን ቤት ልሄድ ነው፣እንትንህ ተከፍቷልና እንትንህ ሳይታይብህ እንትንህን ዝጋ…› እያልኩ ሁሉን ነገር በግድ በእንትን ጀምሬ በእንትን መጨረስ አለብኝ? ለምን? ከፈለግህ አንተም እንደነእንትና መሆን ትችላለህ፣ የእንትን አቀንቃኝ ሁላ! ለካንስ አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ‹እንትን›ን እንደጠላና ስም አይጠሬዎችን(taboo words) እነእንትንንና እንትንን በቁልምጫ ሳይቀር እንደጠራ የሞተው ማፈንገጥ አምሮት ሳይሆን እውነትን እንዳለች መግለጽ ፈልጎ ኖሯል?” አልኩና በንዴት ፎግልቼ ስልኩን ጆሮው ላይ ጠረቀምሁበት፤ የታባቱንና፡፡ ነገር ግን የራሽያው ዱማ በቦሪስ የልሲን የደረሰበት የመድፍና የታንክ እሩምታ ትዝ አለኝና ከጠቀስኩለት ዝርዝር ውስጥ እንዲያወጣልኝ ሳልነግረው ስልኩን በመዝጋቴ ቆጨኝ፡፡ ራሺያና እኛ ለካንስ በአንዳንድ ነገሮች እንመሳሰላለን፡፡ ፑቲን – መድቬዴቭ፤ መለስ – ደሳለኝ፡፡ አይይይ፣ የኛዎቹ ቲያትር እንኳን የነዚያኞቹን ያህል ወዝ ያለው አይደለም፡፡ በምን ተገናኝቶ ልጄ!
እንትን ስል አንድ እንትን ትዝ አለኝ ይልቁናስ – ፈገግ በሉ እንጂ – ግንባርን አኮሳትሮ እስከመቼ ይዘለቃል፡፡ በአንድ መንደር ውስጥ ኃይለኛ ርሀብ ይገባል አሉ፡፡ ከመንደሩ አባውራዎች አንዱ ውሻውን ይዞ አንዳች የሚታደን ነገር ባገኝ ይልና በቅርብ ወደሚገኝ ጫካ ይሄዳል – ወደ ደደቢት በረሃ፡፡ ጉድጓድ ይቆፍርና ወጥመዱን አዘጋጅቶ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ወደ ወጥመዱ ዝር የሚል ሰስና ሚዳቋ ይጠፋል፡፡ ከዚያ እግሩን አፍታትቶ ለመመለስ ከሄደበት ዘወርወር ብሎ ሲመጣ ያጠመደው ጉድጓድ ውስጥ አንድ አውሬ ገብቶ ያገኛል፡፡ ይሄኔ በመደሰትና ዘመኑ የችግር በመሆኑ ግዳዩን ሌላ ሰው እንዳይካፈለው በመሥጋት በኮድ የታሰረ መልእክቱን ለሚስቱ እንዲህ ሲል ጮክ ብሎ ያስተላልፋል፡-
እንትናችን ውስጥ እንትን ገብቶበት፤
እንትን አምጭልኝ እንትን እልበት፤
አንቺም ነይልኝ እንትን ትይልኝ፡፡
ነገሩ ቢላዎ ይዘሽልኝ ነይ ነው፡፡ ሁሉም አልፎ ፣ የቀኒቱ ርሀብም ለጊዜው ጠፍታ ጧት ላይ ቆዳና ጭንቅላት ሲታይ በጨለማ የተበላችው ለካንስ ቡችዬ ናት፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነው እንግዲህ ‹ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን› የሚል ሥነ ቃላዊ ብሂል በቋንቋችን የተዘነቀውና አሁን ድረስ እየተጠቀምንበት የምንገኘው ይባላል፡፡
ለማንኛውም አካፋን አካፋ ማለት ጥሩ ነው፡፡ በመሠረቱ ኢትዮጵያ ሳይጠጡ የሚሰክሩባት፣ ሳይቅሙ የሚመረቅኑባት፣ ጠብ ከመነሳቱ አቧራ የሚጨስባት፣ በጠብ ያለሽ በዳቦ የስድብ ውርጅብኝና የአግቦ ውሽንፍር አየሩ የሚሞላባት የለየላቸው አማኑኤሎች ሀገር እየሆነች በመምጣቷ ብዙ ነገሮች ሊያስገሩሙን አይገባም፡፡ አምባጓሮ በሽበሽ ነው፡፡ መነቃቀፍ የሠርክ ልማድ ነው፡፡ ሌብነትና ውሸት፣ ሙስናና ንቅዘት አያስነውሩም፡፡ የሚያሾምና የሚያስሞግስ ተግማምቶ መገኘት እንጂ የኅሊናና የሞራል ንጽኅናን መጠበቅ አይደለም – ንጽሕና እንዲያውም ሊያስቀጣና ሊያደኸይ ቤተሙከራ ውስጥ በተፈለሰፈ ወንጀል አስከስሶም በዕድሜ ይፍታህ ዘብጥያ ሊያወርድ ይችላል – ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ መቅረቱ ከፋ እንጂ በዚህ ረገድ ስንትና ስንት የምነግራችሁ ነበረኝ! እናም ወደተነሳሁበት ስመለስ… የወያኔዎች የከረፋ ተፈጥሮና በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ሰይጣናዊ ድርጊት እያናደደኝ እውነትን ባለማለሳለስ እንዳለ እጽፋለሁ እንጂ በምንም ዓይነት ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ ንጥረ ነገር ተመርቼ አልጽፍም፡፡ በሀብት ብዛትና ኅሊናን በሚያዛቡ የአልኮል መጠጦች እየሠከሩ እንደዕንቁላል የገማ አስተሳሰባቸውን በጉልበት በተቆጣጠሩት ሚዲያ አማካኝት ሕዝብ ላይ የሚያስታውኩና የሚቀረሹ ስብሃትን የመሰሉ ዘረኞች ሞልተውናል፡፡ “አሜሪካ ቀርቶ መንግሥተ ሰማይም ብትሆን አታመልጠንም! አምጥተን እናስርሃለን” የሚሉ ልበ ድፍን የወያኔ ሰካራሞችና ቅዠታሞች እያሉ እኔ እውነትን ለመጻፍ ጫትም ሆነ መጠጥ አያስፈልገኝም፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ውቅያኖሶች ቀለም፣ ሰማይና ምድር ብራና ሆነው የወያኔን ታሪክ ብንጽፍ አያልቅም፡፡
ከዚህ በላይ እስካሁን ምን እንዳልኩ አላውቅም – የምርቃና ነገር – ቂ…ቂ…ቂ… ሣቅ አምሮኝ ነበር እንደጉድ ተንከተከትኩላችሁ፡፡ ቢሆንም ትርጉም ሰጠም አልሰጠም ነገሬን መቋጨት አለብኝና ወደዚያው ወደሚወስደኝ ጎዳና ላዝግም፡፡ ኤርትራውያን ችግር ላይ እንደሚገኙ ከፕሮፌሰሩ ጽሑፍ በኛና በነሱ የነገሮች ግጥምጥሞሽና ምስስሎሽ እያዘንኩ ተረድቻለሁ፡፡ የኛም የነሱም ችግር አንድ ነው ማለት ነው፡፡ እኛ፣ ኤርትራውያኑ እነበረከትና ስብሃት ገደሉን እንላለን፤ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን ደግሞ ‹ትግራውያኑ› እነስብሃትና በረከት እነሱን ኤርትራውኑን ገደሉን እያሉን ነው፡፡ ማን ማንን መግደሉ ለጊዜው ለውጥ አያመጣም – ትኩረት ሊሰጠውና ሊቆምም የሚገባው ግድያው ነው፡፡ ይህን የተቀናበረ ታሪካዊ የሀገርና የሕዝብ ግድያና ጭፍጨፋ ማን ነው የሚያቆመው? እነዚህ ታሪካዊ የጋራ ጠላቶቻችን ቅጥረኞች(mercenaries) ምን እስኪያደርጉን ነው የምንጠብቀው? በኛ ስም እየማሉና እየተገዘቱ እስከመቼ ነው ግድያቸውን የሚቀጥሉት? ዐይጥ በበላ እስከመቼ ነው ዳዋ እየተጨፈጨፈ የሚዘልቀው? እንደኔ እንደኔ ሥጋዊ ሞት ከመንፈሳዊ ሞት በጣም ተመራጭ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ታላላቅ ሰዎች የሚፈሩት ሞትን ሳይሆን አሟሟትን ነው፡፡ ነገሩ ‹ከሞቴ አሟሟቴ ያስፈራኛል› እንደሚባለው ነው፡፡ የፕሮፌሰሩ አባባል እውነት ከሆነ የሞተችው ኢትዮጵያና ሕዝቧ ብቻ ሳይሆኑ ሳትወድ በግዷ የተለየቻት ልጇ ኤርትራም ናት ማለት ነው፡፡ ያሳዝናል፡፡
በእኔ እምነት እናትና ልጅ እንደተለያዩ አይቀሩም – በግሌ ያን ጊዜ ልደርስበት ወይ ላልደርስበት እችል ይሆናል – ግን ላምና ጥጃ በርግጥ ይገናኛሉ! ይህን ስል – ማለትም ‹እደርስበት ወይ አልደርስበት ይሆናል› ብዬ በኩራት ስናገር የስድስተኛውን ስሜቴን ‹ትንቢት› ለመግለጽ ያህል እንጂ የአንድ ትንኝ ወደ አንድ ታሪካዊ ኹነት(An historic event which really is inevitable!) መድረስ ወይ ያለመድረስ ጉዳይ አሳስቦኝ አይደለም፡፡ ስትፈልጉ ቅዠት ወይም ቅብዥር በሉት ኢትዮጵያና ልጇ ኤርትራ በአዲስ መልክ ይዋሃዳሉ፡፡ የተበለሻሹ ነገሮች ተቃንተው ይስተካከላሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ቂም በቀልና ጥላቻ፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ተወግደው ሰው እንደውሻ ደምና አጥንት እያነፈነፈ ሳይሆን በሰውነቱ ብቻ ሲሳሳብና ሁሉም ዜጎች በአንድ የወል ሀገራዊ ስሜት ሲተሳሰሩ ነው – የመለስ-ኢሳይያስ የትግራይ ትግሪኝ ዘፈን ቅኝት ወረቱን በመጨረስ ከስሞ የኢትዮጵያዊነት ሥልት ሲናኝ፡፡ ይህን የተቀደሰ ትውልዳዊ ኃላፊነት በብቃት የሚወጡ ዜጎች በቅርብ ይሾማሉ፡፡ በቤተ ሙከራ ተሠርተው እንደዕርዳታ ስንዴ ለየጎጡ የተከፋፈሉ ባንዲራዎች ይቃጠላሉ፤ የዚህ መሠሪ ተንኮል ጠንሳሾች፣ አስጠንሳሾችና አራማጆችም በገሃድ መሞት እንደጀመሩ አንድ ባንድ ግን ሁሉም ተራቸውን ጠብቀው ያልቃሉ፤ በሰማይም በምድርም ተረግመዋልና – በደም ባህር የሚዋኙ ናቸውና – በሕዝብ የምሬት ዕንባ ዶፍም በስብሰዋልና ዘር አይወጣላቸውም፤ ለነሱ የተፈቀደችዋ ዘመን ይህቺ የአሁኗ ጊዜ ብቻ ናት – ባለቻቸው ጊዜ ይደሰቱ፤ ይጠጡ፤ አንዳቸው በሌላኛቸው ቤት ይሸራሞጡ፤ አንዳቸው የሌላኛቸውን ልጅ ያሳድጉ – ከእርጉማን የሚጠበቅ የልክስክስነት ባሕርይ ነውና፤ ዳንኪራና ጮቤም ይርገጡ (የዐዋጁን በጆሮ ባትሉኝ እነዚህ የታሪክ ጉዶች እኮ አልጋንም የሚጋሩና ‹የተቀደሰውን ለውሾች አውጥተው የሚጥሉ› ጋጠወጦች ናቸው! አንዳችም ማሠሪያና የሚፈሩት ነገር የሌላቸው ከሃይማኖትም ከባህልም ማዕቀፎች የወጡ ስዶች እኮ ናቸው!)፡፡ ታዲያን እነሱ ሰይጣንን ይዘው ይህን ያህል ተዓምር የሠሩ እኛ እግዚአብሔርን ይዘን ከነሱ የበለጠ ልዩ ተዓምር እንዴት አንሠራ!? “እመን እንጂ አትፍራ!” መባሉም ለዚህ ነው፡፡ አይዞን ምዕመናን!!
ነጻነትን እንደቀድሞው የሙሤ ዘመን በኅብስተ መና መልክ ከሰማይ መጠበቅ ግን የዋህነት መሆኑን እንረዳ፡፡ ፈረንጆች “There is no free lunch!” ይላሉ፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባንና እንደሚቻለንም እናስብ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን ከክፋት ሥራ ተጠብቀን ወደፈጣሪ መዞር እንደሚገባን እንወቅ፡፡ ፈጣሪን ግማሽ መንገድ ድረስ ሄድን እንቀበለው፡፡ የሞተን ለመርዳት የሚተጋ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ኃይል እንደሌለ እንገንዘብ፡፡ እናም ሕይወት እንዳለን፣ እንዳልሞትን፣ ለዲያብሎስ መንጋ እንዳልተንበረከክን የምናሳውቅበት የመነሳሳት ቅጽበት እንዲፈጠር እንትጋ፡፡ ያ ጊዜ ደግሞ አሁንና ዛሬ ነው፡፡ የኛን የቤት ሥራ ከሠራን ቀሪው ቀላል ነው፡፡ ለመሆኑ አሁን ፈጣሪ ምን እየሠራ እንደሆነ እናውቃለን? አዎ፣ ሁሉንም ባናውቅም ይህችን ያህል የምናውቅ ግን አለን፡- ‹ቁናውን እየሰፋ ነው› ወይም ‹ሰፍቶ ጨርሷል›፡፡ መሥፈር ሲጀምርስ? እሱን አያድርስ!ሦርያን ያየ፣ ሊቢያን ያዬ፣ የመንን ያዬ፣ ሩዋንዳን ያዬ፣ማሊን ያዬ፣ቱኒዚያን ያዬ… በእሳት ሊጫወት ማሰብ የለበትም፡፡ ግን ግን ‹የዱባ ጥጋብ ካለስንቅ ያዘምታል› መባሉ ለካንስ እውነት ነው? ውድ ወያኔዎች – መጥፊያችሁ ደርሷል! መጥፋታችሁ እንጂ እንዴት እንደምትጠፉ ግን እኛም እናንተም አናውቅም – ከፈጣሪ በስተቀር፡፡
በመሠረቱ ገዢዎች ይሳሳታሉ፡፡ እንዲያውም የማይሳሳት ገዢ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በዚህች ምድር ፅድቅን ስለማንጠብቅ ለምሳሌ ባገራችን የመንግሥትን ሥልጣን የሚይይዘው ከበደም ይሁን ሐጎስ ወይም ዘበርጋም ይሁን ሂርጳሳ በአንጻራዊነት እገሌ ከእገሌ በዚህ ወይ በዚያ ጉዳይ ይሻላል ማለት እንችል እንደሆን እንጂ በአስተዳደር ረገድ ፍጹም እንከን የለሽ የመንግሥት አካል አናገኝም፡፡ ከዚህ አንጻር የአሁኑን የወያኔ አገዛዝ ካለፉትም ሆነ ወደፊት ይመጣሉ ብለን ከምንጠብቃቸው ጋር ስናወዳድረው በጥፋት ተልዕኮው ወደር የማይገኝለት መሆኑን መገንዘብ አያዳግተንም፡፡ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን – የውጭ ሀገር ሰው በመሆናቸው ፕሮፌሰር መድኃኔ ልበልና ባባታቸው ስም ልጥራቸውና – ፕሮፌሰር መድኃኔ በጥናታቸው እንደጠቆሙት የአንድ ሀገር አመራር ትልቁ የሞራል ዝቅጠት በሚያስተዳድረው ሕዝብ መሀል ግርድና አመሳሶ እያወጣ ራሱንም ወደ አንድ ሸጥና ጎጥ እየወተፈ ሌሎችን በወርቅነትና በኩበትነት እየፈረጀ ሲያንጓልል ነው፡፡ ይህ በታሪካችን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ መቅሰፍት – በምንም መንገድ ሊሽር የማይችል ጠባሳ መሆኑ ሳይረሳ – ምን ያህል መሪዎቻችንን ከስብዕና በታች እያወረደና በመዘዙም እኛን ከመኖር ወዳለመኖር እየለወጠን እንደሚገኝ ከተረዳን ቆይተናል፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉንም የሀገሪቱን የመንግሥት ሥልጣን በቀጥታና በተዛዋሪ ከያዘ የአንድ ሀገር የፖለቲካ አመራር ቡድን ውስጥ 3.6% ብቻ ኢትዮጵያን እንደእናት ሀገር የሚቀበል ሆኖ ሲገኝ ሌላውና 96.4% የሚሆነው በትግራይ እናት-ሀገርነት ሲጸና ከዚህ በላይ ማፈሪያ የታሪክ አንጓ የለም – በጭራሽ! ትግራይ ውስጥ በናሙናነት ከተወሰደ የሕዝብ ክፍል መሀል 82.1% የሚሆነው ‹ቀንደኛ ጠላትህ ማን ነው?› ተብሎ ሲጠየቅ ‹አማራ ነው› ካለ አስታራቂ የሚያስፈልገው ግን ቀን ሊሰጠው የማይገባ ችግር አለ ማለት ነውና ሀገር ሰላም ብለን መተኛት የለብንም፡፡ እነዚህን ዘግናኝ መረጃዎች በዝርዝር ለማንበብና በሃዘን ለመቆራመድ የፈለገ ሰው የተጠቀሰውን የፕሮፌሰሩን ጽሑፍ ማንበብ ነው፡፡ የአጻጻፍ ሥልታችንና የይዘታችን ድምፀት (style and tone) ይለያይ እንጂ እኔን መሰሎች ዘባራቂ የብዕር ‹ጦረኞች›ም የምንለው ይሄንኑ ነው፡፡ ችግር አለ! (‹ነገ እዚህ አካባቢ ቤት ይቃጠላል!› ነበር ያለችው የደሴዋ ዕብድ ሴት በማግሥቱ ራሷ ልታጋየውና ጉድ ልትሠራቸው?) ችግሩ ታዲያ እንደሌሎች ሀገሮች ችግር ሳይወሳሰብና ጥርስ ወደሌለው የተቃቃሩት መንግሥታት(DN/Disunited Nations) መሮጥ ሳይመጣ ከአሁኑ እንፍታው ነው እያልን ያለነው፡፡ ሦርያ ላይ የሚጮህ ጅራፍ ጊዜውን ጠብቆ ኢትዮጵያ ውስጥ አይጮህም ብሎ ማሰብ የለየለት ድንቁርናና ትዕቢት ነው፡፡ ትብታብም ይፈርሳል፤ ፍርሀትም ይጠፋል እያልን ነው የምንገኝ፡፡ አሁን ዓለምን የገዙ የመሰላቸው የትግሬ ወያኔዎች በሕዝብ ላይ መፈንጠዛቸውንና ጥሬ እንትናቸውን በጭቁኑ ወልደማርያም ላይ መጣላቸውን ትተው ወደኅሊናቸው ይመለሱ ማለት ኃጢኣት አይደለም፤ ትርፍ እንጂ ኪሣራም የለውም፡፡ ችግሩስ ቁስልን እየሸፋፈኑ ይብስ እንዲነፈርቅ ማድረግ ነው፡፡ በጭቁን ዜጎች ላይ ፋንድያን ማለትም እንትንን እዬጣሉ ለስንት ዘመን መኖር እንደሚቻል የጋዳፊንና የኢዳሚንን የሙት መንፈስ በጠንቋዮቻቸው አማካይነት ያስጠይቁና ከጥጋብ መንገድ በአፋጣኝ ይውጡ ነው እያልን ያለነው፡፡ በተረቱ ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ መባሉ የጥጋብን መዘዝ ለማጠየቅ ነው፡፡ ሰከርክም ልባል መረቀንህ – አሁንም እደግመዋለሁ፡- እነዚህ ዋልጌ የዲያብሎስ ውላጆች ባስከተሉት መዘዝ ኢትዮጵያ በ‹ጥቂት› ትግሬዎች እጅ ገብታ በወለድ አገድ እየተመጠመጠች ናትና ይህ ታሪክ ይቅር ሊለው የሚከብደው አሰቃቂ ድርጊት ተጨማሪ ጥፋት ሳያስከትል በአስቸኳይ ይቁም፤ ብሔራዊ ዕርቅ ይፈጠር፤ ፖለቲካችን ሰው ሰው ይሽተት፤ በዘረኝነት ከርፍቷል፤ በጎጠኝነት ገምቷል፤ በሙስና ጠንብቷል – የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ መጥፎ ጠረን የዚህችን ዓለም አድማሳዊ ድንበር አልፎ ጽርሐ አርያምን እያጥነገነገ ነውና በቶሎ መፍትሔ ካልተፈለገለት ጦስ ጥንቡሱ ከኢትዮጵያ ድንበሮችም ይሻገራል እያልን የምንገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል የሚል ግንዛቤ ወስደናል እያልን ነው – በበረከት ስምዖን አማርኛ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግራችን ዋናው መፍትሔ ‹አማራ ገዳይ! ትግሬ ገዳይ!…› የሚለው የጅሎች ፉከራና ሽለላ ሳይሆን መደማመጥና መግባባት ብቻ ነው፡፡ ይሄኛው የሃያና ሠላሳ ዓመት አበቅቴ ለነዚህ ቢሆን ያኛው የሠላሣና ዐርባ ዓመት አበቅቴ ደግሞ ለነዚያኞቹ ይሆናል፤ የዚህች ምድር ነገር የጽዋ ማኅበር ዓይነት ነው – ማንም የማንንም ዝክር ቀፈቱ እስኪያብጥ ሰልቅጦ ሰልቅጦ ሲያበቃ በ‹ጨዋታው ፈረሰ – ዳቦው ተገመሰ› የልጆች ጨዋታ የበላ የጠጣትን ሳይከፍል ከማኅበሩ ልሰናበት ሊል አይችልም – በየትኛው ሒሳብ! ዛሬ ለተቀናጀ መንግሥታዊ የበቀል ጥማት ማርኪያ የሆነ ሕዝብ በቀል አርግዞ በተራው በዳዮቹን ለመቅጣት ምቹ ቀንን የሚጠብቅ እንዳይሆን የክፋት ምንጭን እናድርቅ እያልን ነው – አንዳንድ “የሩቅ ተመልካቾች”፡፡ ማሰብ በተሳናቸው የትግሬ ወያኔዎች፣ ይሉኝታንና ሀፍረትን ሸጠው በበሉ ወንድምና እህቶቻችን እያየነው ያለነው አበሳ የሰቆቃችን የመጨረሻ ምዕራፍ ይሁንና ከዚህ መጥፎ ታሪክ ትምህርት ቀስመን የወደፊቱን ትውልድ ከመርዘኛ ፖለቲካና ፖለቲካው ካበሰበሰው አጠቃላይ ማኅበረሰብኣዊ ቀውስ ነጻ እናውጣው፡፡ በሎሚ ተራ ተራ ዜጎች ለማያባራ ስቃይ መዳረግ የለባቸውም፡፡ መለስ በስብሶ የሞተው፣ ኢሳይያስ ለያዥ ለገራዥ አስቸግሮ ሞትን በሚያስመርጥ የቁም መቅበዝበዝ ላይ የሚገኘው አላንዳች ብልሃት አይደለምና ዜጎች ወደጤናማ ኅሊናቸው ባፋጣኝ ይመለሱ – ቢያንስ ከነዚህ ሁለት የጠፉ ዜጎች እንማር፡፡ በሀገር ዕርቅ ይውረድ፡፡ ቂም በቀል ይወገድ፡፡ የጠገበ ይስከን፤ የተራቡና የተጨቆኑ ወገኖቹንም ያስብ፤ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባም ሆነች አሥመራ(I can imagine,) የሎጥን የሶዶምና ገሞራ የእሳት ዝናብ የሚጠሩ የሲዖል ከተሞች ሆነዋል ብንል አልተሳሳትንም – ብዙኃን በርሀብ አለንጋ እየተገረፉ ጥቂቶች በሚመዘብሩት የሕዝብና የሀገር ሀብት ይሠሩትን አጥተው በነውረኝነት ጎዳና መትመምን መርጠዋል…እኛም እነሱም አናሳዝንም? – በሬ ካራጁ ጋር ይውላል፡፡ ቂም በቀል ቂም በቀልን ይወልዳል፡፡ አመፅ አመፅን ይወልዳል፡፡ ፍቅርና መተሳሰብ ግን የበቀል ቁርሾን አስወግዶ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመሠረት ያደርጋል፡፡ ዛሬ አንድ የሚፏልል ጥጋበኛ የወያኔ ካድሬ በቢሊዮን የሚገመት ሀብትና ንብረት ቢያከማች – እመኑኝ – አይበላውም፤ መቼምና የትምም አይጠቀምበትም፡፡ ‹እባካችን› ልብ እንግዛ፡፡ እርግጥ ነው ሀብታምና ፖለቲከኛ በአብዛኛው ደናቁርት ስለሆኑ ዛሬን እንጂ ነገን ማሰብ አይቻላቸውም – ለማሰብ የሚጠቀሙበት ሆዳቸውን እንጂ ጭንቅላታቸውን አይደለም፡፡ አንጎላቸው የተቃኘው በሶስት ነገሮች ብቻ ነው፤ እነሱም ሥልጣን፣ ገንዘብና ወሲብ ናቸው – አንቀሳቃሽ ሞተሮቻቸው እነዚህ ናቸው፤ የእነዚህን ፍላጎቶቻቸውን ጥሪ ለመመለስ ሲሉ ከሰማይ በታች ከምድር በላይ የማይሠሩት ወንጀልና ኃጢያት የለም፡፡ በእነዚህ ሦስት ፈታኝ ነገሮች ያልታወረ ሰው ግን ብፁዕ ነው – አእምሮውንም በአግባቡ ይጠቀማል፤ ከቅሌትና ውርደትም ይድናል፡፡ አቅሉን ስቶ ለነዚህ ነገሮች የሚንበረከክ ከሰውነት ተራ ይወጣል – በመጨረሻው መጨረሻ ላይ ታዲያ ውድ ዋጋ ይከፍላል፡፡
በተረፈ ትግሬ፣ አማራ ፣ ኦሮሞ የምንለው ነገር የቋንቋ ፈሊጥ እንጂ ተጨባጭ የሆነ አመክንዮኣዊ ልዩነት የላቸውም፡፡ በነዚህ የጎሣና የብሔር ስሞች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ሌቦች በሏቸው – አጭበርባሪዎች፡፡ ለአብራኩ ክፋይ ለልጁ ግድ የሌለው – ሚስቱን በወጣ በገባ ቁጥር የሚነተርክ – ከጎረቤቱ ጋር ዐይንና ናጫ ሆኖ የሚኖር፣ ለቸገረው ወንድሙ አምስት ሣንቲም የማያቀምስ፣ ለተጨነቀ ጓደኛው አሥር ብር የማያበድር… ስግብግብና ፍቅርን የማያውቅ ዜጋ ለሥልጣን አራራውና ለግል ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ሲል የዚህን ወይም የዚያኛውን ብሔረሰብ ስም በታፔላነት አንስቶ ቢጮህ እውነት አይምሰላችሁ፡፡ ለማያውቅህ ታጠን በሉት፡፡ በአባቱ ኦሮሞ በእናቱ አማራ የሆነ ለማን ሊታገል ነው የጎሣ ቡድን ውስጥ የሚገባው? ለምሳሌ ስብሃት ነጋ ኤርትራዊነቱንም ኢትዮጵያዊነቱንም ትቶ ለትግራይ የበላይነትና ለወያኔ ንግሥና ቆሜያለሁ የሚል ሰው ነው ይባልለታል፡፡ ይህ ሰው፣ እውን ለትግራይ ይጨነቃል? ለትግራይ ሕዝብስ እንቅልፍ አጥቶ ያድራል? እንዲያ ከሆነ ስንትና ስንት ትግራውያን በርሀብ ሲሰቃዩ እንደማንኛውም ወገናቸው ሲለምኑና ሲቸገሩ በምዝበራና በሕገወጥ የገንዘብ ክምችት ብዙ ቢሊዮን ብር አለው ከሚባልለት ኤፈርት ትንሽ ገንዘብ ቆንጠር አድርገው ለምን አይረዱም? አዎ፣ ብዙ ነገሮች የታይታ ናቸው፤ ብዙ ነገሮች የብልጭልጭ ናቸው፡፡ የእንትና ብሔረሰብ ይልና በቁስልህ ሊገባ ይፈልጋል – ቁስልህን ተገን አድርጎ ወደልብህ ለመግባት ከሞከረ በኋላ ግን የርሱን ቁስል ባንተ ሀብትና ጥሪት ፈውሶና የድህነት ጭቅቅቱን አራግፎ ያንተን ቅስል ይብስ ያነግልብሃል፤ አንተም ከነድህነትህ እህህ እያልክ ትኖራለህ – ለሌላ ዙር እንግልትም ትጋለጥና የራበው አዲስ ተኩላ ከጫካም ይሁን ከከተማ መጥቶ በአዲስ መልክ ይግጥሃል፡፡ ሕይወት እንዲህ ናት፡፡ አንዱ መሰላል ነው – ሌላው በመሰላሉ የሚወጣ ነቀዝና ተምች ነው፡፡ ታችኛው ግን ሞኝና እንደነዱሽ እንደሆነ ይቀራል፡፡ እነገሌ መጡብህ ካሉት እየደነበረ ከየሽርንቁላው ይወጣና አሰለጦች ባዘዙት መሠረት በንጹሓን ላይ ጦሩን ሰብቆ መሰል ወገኖቹ ላይ ይዘምታል፤ ብዙኃኑ ታችኛው የጥቂቶች ላይኞች መጠቀሚያ ጎጋ ነው፡፡ ከስቅሎ ስቅሎ በፊትም ሆነ በኋላ የዓለም ታሪክ እንደዚሁ ነው፤ ጥቂት ብልጦች ብዙኃንን ዕቃ’ቃ እንደተጫወቱባቸው ዓለም ‹ፍጻሜዋ ደረሰ›፡፡ አንዳንዱ እንደተሸወደ የሚገባውና ዐይኑን የሚገልጠው ራሱ ችግር ውስጥ ከገባ በኋላ ነው፡፡ እነመለስ፣ እነኢሳይያስ በዚህ መልክ ሲጫወቱብን ከቆዩ በኋላ ነው እንግዲህ እነሱም በፋንታቸው የማይቀርላቸውን መሪር ጽዋ ሊጎነጩ የመጨረሻው ፊሽካ ብቻ እንደቀረው አምነን ያቺን የፍርድ ቀን በጉጉት እየተጠባበቅን የምንገኘው፡፡ በቃ፡፡
የነስብሃትና መሰሎቹ አገርና ወገን ሆዳቸው ነው፤ ሃይማኖታቸው ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ወሲብና መጠጥ ነው፡፡ የሚሉት ሁሉ ለማደናገሪያነት እንጂ የአንጀታቸውን አይደለም፡፡ ትዳርን የማያከብር ዘልዛላ፣ የክፉ ቀንን የትዳር ጓደኛና የልጆቹን እናት ሲያልፍለት አስወጥቶ የሚጥል ጉደኛ፣ ልጆቹን የማይሰበስብ የሌሊት አውሬ ዳንኪረኛ፣ በሽምግልና ዕድሜው ከልጅ ልጆቹ ጋር የሚማግጥ ሠካራም ነውረኛ… በምን ሒሳብ ለሀገር ጠቃሚና ለወገን ተቆርቋሪ ሊሆን እንደሚችል አስቡት፡፡ ይቅርታ – ባደጉ ሀገሮች ከሕጻንነት ጀምሮ የሚመዘገብ የግል ሕይወት ይዞታ ለሥልጣን ዕጩነት ታላቁ መለኪያ በመሆኑ ይህን ስለባለሥልጣኖቻችን ዋልጌነትና እንስሳነት የምላችሁን ነገር በምን አገባህ አናንቃችሁ አትመልከቱት – በኛ ሀገር ደግሞ በተገላቢጦሹ ባለጌ ባለጌው እየተመረጠ ይመስላል ለሥልጣን የሚበቃው – አልጋውና ወንበሩ የሚወደው ጥፍራሞችንና መደዴዎችን መሆን አለበት፡፡
ሀገር ወዳድነት ላግጣ አይደለም – ሀገርን የመምራት ጠንካራ ጎን ደግሞ ከቤተሰብና ከራስ ጤናማ ኑሮ ይመነጫል፤ በሽተኛ ሰው እንኳንስ ሀገርን ራሱንም መምራት አይችልም፤ ሠካራምና እንደልቡ ተናጋሪ ሰው ደግሞ ከዕብድ ተለይቶ አይታይም፡፡ አሁንም ከዚህ ከምለው ነጥብ አኳያ እነስብሃትን ‹ለማያውቋችሁ ታጠኑ!› በሉልኝ፡፡ መቆሚያቸውን ለማደላደል የትግራይን ሕዝብ ‹ያንተዎቹ ነን፤ ከኛ ወዲያ ላንተ የተሻለ አማራጭ የለም፤ አማሮች ከመጡ ሥጋህን ዘልዝለው ይበሉሃል…› በማለት ሊያስፈራሩበት እንጂ በውነት የትግራይነት ስሜት ኖሯቸው አይደለም፡፡ ቀደም ካለ የትግላቸው ወቅት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሠሯቸው ወንጀሎች ይህን የሚሉትን ነገር አያረጋግጡላቸውም፡፡ ብሎም ቢሆን ለትግራይ ምድርና ሕዝብ የሠሩት የልማትና የዕድገት እመርታ የለም ለማለት እንዳልሆነ በትህትና ላስታውስ እወዳለሁ፡፡ ሀገራችን ለሚሉት ብዙ ሠርተዋል – ይሁን፡፡ ጥጃ ጠባ እሆድ ገባ ነው፡፡ ቦዕ ጊዜ ለኩሉ ፤ ሌሎቹም በጊዜያቸው ይለማሉ፡፡
ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም፡፡ ቀጥሎ በቅንጭብ ያመጣሁትን የፕሮፌሰርን ንግግር አዳምጡ፡-
ኤርትራ ዛሬ በሁሉም መስፈርት አስጠሊና የተገለለች አገር ሆናለች። ሕዝባችን ባሁኗ ወቅት ደቃቃዋ የፖለቲካ መብት እንኳ የሌለው፡ ሰብኣዊ መብቱ ፈጽሞ ያልተጠበቀ፡ እጅግ ከባድ ድህነት ያጐሳቈለው፡ ማህበራዊ ኑሮው ሰብኣዊነት የራቀው፡ የህላዌው ሁኔታ በፍርሃትና ስጋት ተበክሎ የደህንነትና የዋስትና ጭላንጭል እንኳን የሌለው ነው፡፡ የወጣቶቹ ሁኔታ በተለይ እጅግ የሚያሳዝን የከበደ ትራጀዲ ሆኗል፡፡ ወጣቱ ሊደሰትበት በሚገባ አፍላ ዕድሜው በግድ እየታፈሰ ሳዋ ወይም አገልግሎት ለሚባለው ባርነት እየተዳረገ ነው። ወጣቶቹ ከዚያ ገሃነማዊ ሁኔታ ለማማምለጥ ሙከራ ሲያደርጉ፡ ከስደት ወደ ስደት አገር ለመሸጋገር ሲሞክሩ አንዳንዱ ባሕር ውስጥ እየሰጠሙ ለምህረት-የለሽ ዓሳ ሲሳይ እየሆኑ ነው፣ አንዳንዱ ደግሞ በአረሜኔዎች ተጠልፈው እንደ እንስሳ እየታረዱ ኩላሊታቸውና ሌላ ውስጣዊ አካላቸው እየተነጠቀ ሬሳቸው በሳሃራና በሲናይ ምድረ-በዳዎች እየበሰበሰ ነው፡፡ ይህ መከራ በጣም የሚዘገነን፡ ስትሰማውም እጅግ የሚያስደነግጥ ነው።
ለመሆኑ ዜጎች ለዚህ አሰቃቂ መከራ ሲጋለጡ አስመራ ውስጥ ያለው መንግሥት ምን እየሰራ ነው? የሚል የዋህ ጠያቂ አታጣም። አስመራ ውስጥ ያለው አምባገነን ኢሳያስ የሚመራው መንግሥት እውነትም ኤርትራዊ መንግሥት አይደለም፣ በኤርትራውያን ላይ የጥላቻና የቂም በቀል ቁርሾ በያዙ፡ ድብቅ ሴራ ባላቸው አካላት የቆመ ቡድን (ካባል) ነው። እነኚህ ሴረኞች በትውልድ ትግሬዎች ቢሆኑም ኤርትራዊያን ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ፡ ሆኖም ግን ምንነቱ ባልተመረመረ ችግር ምክንያት፡ ሕዝባችንን በሚያጠቃ መልኩ የ“ትግራይ-ትግርኚ” ንድፍ አዝማቾች ለመሆን የመረጡ ናቸው።
ከዚህ ጋር በተዛመደ ሊነሳ የሚገባው አሳዛኝ ነገር አለ። ለብዙ ዓመታት ከበረሃ ትግል ጀምሮ እስከ ህግዲፍ መንግሥትነት ድረስ ኢሳያስን ያገለገሉ፡ እንደ እነ ሃይለ ወልደትንሳኤ፡(ድሩእ)፡ማሕሙድ ሸሪፎ፡ እስጢፋኖስ ስዩም፡ ጴጥሮስ ሰለሞን፡ ጀርማኖ ናቲ፡ ኣስቴር ፍስሓጽዮን፡ በራኺ ገብረስላሴ፡ ዑቕበ ኣብርሃ፡ ብርሃነ ገረዝጊሄር የመሳሰሉ፡ በዛ ገሃነማዊ የዒራዒሮ እስር ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው አንዳንዶቹ ሞተው፤አንዳንዶቹ ደግሞ እየተሰቃዩ ሞታቸውን ይጠባበቃሉ። እነኚህ ታጋዮች የፈጸሙት ወንጀል የለም። ኤርትራ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲጀመር ጥገናዊ የሆነ ለውጥ በመጠየቃቸው ብቻ ነው ለዚሁ አበሳ የተዳረጉት። እነዚህንና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን የምትመለከት አንዲት አንገብጋቢ ነጥብ አለች፤ እርስዋም እኚህ በኢሳያስ የሚታሰሩና በተለያየ ዘዴ እየተገደሉ ያሉት ዜጎች በሙሉ ንጹሃን “ኤርትራዊያን” መሆናቸው ናት። በተቀረ፡ ብዙ ሰዎች እንደነገሩኝ ከሆነ፡ በትውልዳቸው ትግሬዎች የሆኑ ኤርትራውያን በኢሳያስ መንግስት እንዲገደሉ ወይንም እንዲታሰሩ የተደረጉ የሉም። ይህ አሳሳቢ የሆነ ትዝብት ነው!!
***
በጥያቄው የተሳተፉት የዛሬው የትግራይ ፖለቲከኞች (ወይም የፖለቲካ ተዋንያን – ማለት ኤሊት) እናት አገራችሁ ማነች ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ በመንፈስም በአስተሳሰብም ኤርትራውያን ፖለቲከኞቹ ከሰጡት መልስ አሳሳቢ በሆነ መጠን ይለያል። ከተሳተፉት የትግራይ ፖለቲከኞች መሃል እናት አገራችን ኢትዮጵያ ነች ብለው የመለሱ 3.6% ብቻ ናቸው። አብዛኛዎቹ በጥያቄው የተሳተፉ የትግራይ ፖለቲከኞች ግን እናት አገራችን ትግራይ ነች ነበር ያሉት። ኢትዮጵያ አላሉም። አቶ ስብሓት ነጋ ይህንን ጥያቄ ሲመልስ፡ ላንዳፍታ “ዝግ ካለና ካመነታ በኋላ”፡ እናት አገር ሲባል በአእምሮው ውስጥ ድቅን የምትልበት “ትግራይ“ መሆኗን ገልጿል። አንደዚሁም አቶ ጸጋይ በርሄ – እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትግራይ ክልል ፕረዚደንት የነበረና፡ ዛሬ ግን የሕዝባዊ ወያነ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆነው – ይህ ጥያቄ ቀርቦለት ሲመልስ ሳያመነታ በቀጥታ “እናት አገሬ ትግራይ ነች“ ነው ያለው። ኢትዮጵያ ነች አላለም። “ብትግሬነቴ በኩል አድርጌ ነው ኢትዮጵያዊ የምሆነው“ በማለት ግን መልሷን ስስ በሆነች ኢትዮጵያዊነት ሸፋፍኗታል።
ይህ እናት አገራችን ትግራይ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም የሚል መልስ ከታወቁ የሕዝባዊ ወያኔ አመራር አካሎች ሲደመጥ የሚያሳስብ ክስተት ነው። (ለምሳሌ አንድ በኤርትራዊ የፖለቲካ ድርጅት አመራር ውስጥ ያለ ሰው እናት አገሬ ብሎ ኤርትራን ከመጥቀስ ይልቅ ባርካን ወይም ቢለንን ወይም ኩናማን ቢጠቅስ፡ ወይንም ደግሞ ከደጋማው አውራጃዎቻችን – ማለትም ሓማሴን፡ አከለጉዛይ – ብሎ ቢጠቅስ፡ ለኛ ለኤርትራውያን እጅግ የሚያሳስበን ይመስለኛል!!