“ስብሰባው”

በፍሬው አበበ አደራ
ሞልቶ ከተረፉን ስብሰባዎች መካከል በአንዱ ውስጥ ነበርኩ፡፡ ስብሰባው ስለመንግስት የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ እና የክልሎች እንቅስቃሴ የሚወራበት ነበር፡፡ያው እንደደንቡ የተመረጡት ሹም ከአንድ ሰዓት በላይ ጊዜ ወስደው ጥናት ያሉትን አቀረቡ፡፡አወያዩ አቅራቢውን የጎንዮሽ በማየት እያደነቁ “ዌል! እጅግ በሳል ትንታኔ የተንጸባረቀበት ጹሑፍ ነው፡፡እሳቸው ያሉትን መልሼ አልደግመውም፡፡ግን መታለፍ የሌለባቸው ዋና ዋና ነጥቦችን ላንሳ” አሉንና ንግግራቸውን እየጎተቱ ልክ እንደበቀቀን ሰውየው ያሉትን ምንም ሳያስቀሩ መልሰው ደገሙልን፡፡ደግመውልን ሲያበቁ መድረኩ ለአስተያየትና ጥያቄ ክፍት መሆኑን አበሰሩ፡፡ጥቂት እጆች አየር ላይ ታዩ፡፡ሰብሳቢው ብርጭቆ የሚያህል መነጽራቸውን ግራና ቀን ሲያንከራትቱ ቆዩና “አንተ በቀኝ በኩል ያለኸው..አዎ!..ቀይ ከረባት ያሰርከው ” ብለው መነጋገሪውን አሻገሩ፡፡ተመራጩ ተናጋሪ ቀጠለ፡፡
“በቅድሚያ ክቡር አቶ እገሌ ላቀረቡልን ፕረዘንቴሽን ያለኝን ልባዊ አድናቆት ልገልጽ እወዳለሁ፡፡በእውነቱ ፕረዘንቴሽኑ በአሁኑ ወቅት በተለይ በክልሎች ያለውን ችግር አንድ በአንድ ነቅሶ ያሳየ በመሆኑ በዚህ ረገድ የምጨምረው ብዙም ነገር አይኖረኝም፡፡ክቡር አቶ እገሌ እንዳሉት ለዚህች ሳታጣ ላጣች አገራችን መደህየት ተጠያቂዎቹ ጸረ ልማት ኃይሎች መሆናቸውን የተናገሩት በትልቁ ሊሰመርበት ይገባል…. ”
ሌላኛው ቀጠለ፡፡“እኔም እንደወንድሜ ክቡር አቶ እገሌ ላቀረቡልን ጥናታዊ ጹሑፍ ያለኝን ክብር ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ጹሑፋ ብዙ ያላወኩትን ነገር ያሳወቀኝ ነው፡፡ከዚህ በኃላ የማቀርበው አንድ ሁለት ጥያቄዎች ይኖሩኛል፡፡ይኸውም የአገራችንን ዕድገትና ልማት የሚያደናቅፉ ሓይሎች እስከመቼ ነው የምንታገሳቸው?ይህ ስብሰባ አንድ ቁርጥ ያለ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ለመጠየቅ ነው፡፡አመሰግናለሁ፡፡”
ሌላኛውም ማይክሮፎኑን አስጠግተው ለመናገር ጉሮሮአቸውን ጠራረጉ፡፡“እ..እ..እ..እ….ክቡር ሰብሳቢ ለሰጡኝ ዕድል አመሰግናለሁ፡፡በእውነቱ በእንዲህ ዓይነት ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ባለው ስብሰባ ላይ በመገኘቴ የተሰማኝን ደስታ በዚህ አጋጣሚ ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ጥናት ያቀረቡትም እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ጥናቱ መሬት ላይ ያሉ ችግሮቻችን በሚገባ የዳሰሰ ነው፡፡አገራችን ለዘመናት የተጎዳችው እንዲህ ዓይነት ችግሮቻችን በሚገባ የሚዳስሱ ጥናቶች ባለመኖራቸው ነው፡፡እናም ስብሰባውን አዘጋጆች የምጠይቀው ይህ ጠቃሚ ጥናት ለሚመለከታቸው ስቴክሆልደሮች ሁሉ ተባዝቶ እንዲሰጥ መደረግ እንዳለበት ለማሳሰብ ነው፡፡አመሰግናለሁ፡፡”
ሌሎችም ሶስት ተናጋሪዎች በተመሳሳይ መንገድ አድናቆታቸውን ገለጹ፡፡የስብሰባው ተካፋዮችም ንግግሮችን ሁሉ ሳይታክቱ በጭብጨባ ከማድመቅ አልቦዘኑም፡፡ እነሆ የሻይ ዕረፍት ሆነ፡፡ ምሳ ሰዓትም ደርሶ መብልና መጠጡ ተወራረደ፡፡ በስብሰባው ማሳረጊያ ላይ የአቋም መግለጫ ወጣ፡፡ተጨበጨበ፡፡የውሎ አበል ለተሰብሳቢው በነፍስወከፍ ታድሎ የዕለቱ መርሃግብር ተጠናቀቀ፡፡
ምሽትም ላይ ኢቴቪ በዕድገትና በትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና ትግበራ ላይ ያተኮረ የአንድ ቀን አውደጥናት በሸራተን ሆቴል ሲካሄድ መዋሉን አበሰረ፡፡ “በስብሰባው ላይ የተገኙት ክቡር አቶ እገሌ ባቀረቡት ጥናታዊ ጹሑፍ የአገሪትዋን ልማትና ዕድገት በአስተማማኝ መልኩ ለማስቀጠል ጸረ ሰላም ኃይሎችን መታገል እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ተሰብሳቢዎችም ዕቅዱን ለማሳካት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ቃል መግባታቸው የሪፖርተራችን ዘገባ ያሳያል” አለ፡፡
እነሆ ወራት ተቆጠሩ፡፡ክቡር ሚኒስትሩም የመ/ቤታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ ሲያቀርቡ ያን ዓውደጥናት አልዘነጉትም፡፡ ከተለያዩ ክልሎችና ሴክተር መ/ቤቶች ለተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የአንድ ቀን አውደጥናት መሰጠቱን፤ በዕለቱም በቀረበው ጥናት መሰረት በልማት ረገድ ክልሎች ያለባቸው ችግሮች መቀረፋቸውን ለፓርላማው ተናገሩ፡፡ዓውደጥናቱን ጨምሮ ለዚህ ዓመት ከተያዘው በጀት 30 ሚሊየን ብር ጥቅም ላይ መዋሉንና የበጀት አፈጻጸማቸው ከዓመት ዓመት መሻሻል እያሳየ መምጣቱን አከሉ፡፡የፓርላማ አባላቱም ስለሪፖርታቸው አጨበጨቡ፣አደነቁ፡፡ኢቴቪም አንዱ ቃል በስድስት ሰዎች ተደጋግሞ ሲነገር ያየነውን ታሪክ የሚኒስቴሩ ሥራ አበረታች መሆኑን በምሽት ዜና እንደአዲስ ግኝት አድርጎ ነገረን፤እኛም የተደነቀውን፣የተጨበጨበለትን…. ሲመመሰጋገኑ የዋሉበትን ስብሰባ እንደልማት ቆጥረን፣ አይ ዜና ብለን ሰምተን ዝም አልን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምሕረት ሲሉ : ፍትሕ ስንል ለየቅል!!! - ከቴዎድሮስ ሃይሌ

1 Comment

Comments are closed.

Share