ደም ብዛት የያዘህ ጨው አብዝተህ በመመገብህ ነው ተባልኩ፤ እውነት ይሆን?

ለምን እንደሆነ አላውቅም ጨው የበዛበት ነገር እወዳለሁ፡፡ በቅርቡ ታምሜ አንድ የግል ሆስፒታል ስመረመር ጨው ስላበዛሁ ደም ብዛት ይዞሃል ተባልኩ፡፡ ከመቼ ወዲህ ነው ጨው ደግሞ የደም ብዛት የሚያስይዘው? እባካችሁ እውነት መሆን አለመሆኑን አስረዱኝ፡፡
የዘ-ሐበሻ የዘወትር አንባቢ ሳምጆ
የዶክተር ዓብይ ዓይናለም ምላሽ፦ ጥያቄህ ሚዛን ደፍቶ አገኘነውና መልስ ልንሰጥበት ወሰንን፡፡ ባለፈው የዘ-ሐበሻ ጋዜጣ እትማችን ላይ በስፋት ስለጨው ጽፈን ነበር። አሁንም እስኪ ስለዚህ በአጠቃላይ በደምብዛትና በጨው ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል ተከታተለን፡፡
በአንድ ወቅት በስራ ላይ በነበርኩበት ወቅት አንድ የደም ግፊት ታማሚ የሆኑ ተጫዋች አዛውንት አጋጥመውኝ ነበር፡፡ አንዴ ስለህመማቸው እያዋየኋቸው እያለሁ ‹‹ሰማህ ልጄ?›› አሉኝና ት/ቤት ያላገኘሁትን ‹‹ሌክቸር›› ሰጡኝ፡፡ ‹‹አየህ? ደም ግፊት ማለትኮ የሚጥም ምግብ ማለት ነው›› አሉኝ፡፡ ግራ ገባኝና ‹‹እንዴት አባቴ?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹እንዴት ማለት ጥሩ! የሚጥም፣ ጣት የሚያስቀረጥም ምግብ ስበላ ከከረምኩ ደም ግፊትህ ተነስቷል ትሉኛላችሁ፡፡ የናንተን ምክር ሰምቼ ጨውም፣ ቅባትም፣ ምኑም ምኑም ያልገባበትን እህል ውሃ የማይል ምግብ የበላሁ ሰሞን ደግሞ ደም ግፊት የለብህም ትሉኛላችሁ፡፡ ታዲያ ደም ግፊት ማለት የሚጥም ምግብ ማለት አይደል›› ሲሉ ሃሳባቸውን አብራሩልኝ፡፡
ጨዋታ አዋቂው አዛውንት በየዋህ አገላለፅ ያስተላለፉት ታላቅ ቁም ነገርን ነው፡፡ ሁል ጊዜ ግራና ቀኝ ሲነገር የምናዳምጠው ነው- የደም ግፊት ህሙማን ጨው፣ ቡናና ሌሎችንም ነገሮች ከምግባቸው እንዲያስወግዱ የመከሩን ነገር፡፡ አሁን አሁን ይህ ህመም በአገራችን በሚገርም ፍጥነት ተስፋፍቶ ‹‹የተለመዱ›› ከሚባሉት ህመሞች ጎራ ተመድቧልና ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡
ውድ ጠያቂያችን የደም ግፊት ህመም (hypertension) በደም ቧንቧዎች መጥበብ ወይም በግድግዳዎቻቸው እንደልብ መለጠጥ አለመቻል የሚመጣ ህመም ነው፡፡ የደም ቧንቧዎች ይህን አይነቱ ገፅታ ሲኖራቸው ደም በውስጣቸው የሚጓዝበት ኃይል ይጨምርና አይነትና ከፍታቸው ለተለያዩ የጤና አደጋዎች ይዳረጋሉ፡፡ የደም በአንጎል ውስጥ መፍሰስ፣ የልብ የደም ቧንቧዎች መዘጋትና መጥበብ፣ ስር የሰደደ የኩላሊት መዳከም በጣም የተለመዱትና ለህልፈት ሊያበቁ የሚችሉት የደም ግፊት መጨመር መዘዞች ናቸው፡፡
መጀመሪያ ነገር የደም ግፊት እንዲመጣ የሚያደርገው ምክንያት እስካሁን በውል አይታወቅም፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮች ግን ተለይተዋል፡፡ እንደ ስኳር ህመም ሁሉ ደም ግፊትም በከፊል በዘር፣ በከፊል ደግሞ በአኗኗር ዘይቤ የተነሳ ይመጣል፡፡ የዘር ስሪቱ ሲታይ በደም ግፊት ህመም የመያዝ ዕድሉ ከፍ ያለ ሰው (ለምሳሌ ወላጆቹ የደም ግፊት ህሙማን የሆኑ) የአኗኗር ዘይቤው ለዚህ ህመም የተመቻቸ ከሆነ በደም ግፊት ህመም ይያዛል እንደማለት ነው- በግርድፉ ሲቀመጥ፡፡ የዘር ስሪትን ማስተካከል የማይታሰብ ነው፡፡ ነገር ግን የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል በበሽታው አለመያዝም፣ ከተያዙ በኋላ ማስተካከልም ይቻላል፡፡
ለደም ግፊት የተመቻቸ የአኗኗር ዘይቤ ስንል ምን ማለታችን ነው? ከልክ ያለፈ ውፋሬ፣ በጣፋጭነት ቅባታማ ምግቦች ተሞልቶ በፍራፍሬና አትክልት ያልተደገፈ አመጋገብ፣ የማያንቀሳቅስ የስራና የኑሮ ገፅታ፣ በዕድሜ መግፋት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የእነዚህ ነገሮች መኖር በደም ግፊት የመያዝ ዕድልን ይጨምራል፡፡ አንዴ በህመሙ ከተያዙ በኋላ ደግሞ ከእነዚህ በተጨማሪ ጨው በብዛት መመገብ፣ ሲጋራ ማጤስ፣ የስኳር ህመም፣… ወይ የደም ግፊቱን ከፍ ማለት ያባብሱታል፣ ወይ ደግሞ በሱ የተነሳ የሚመጡትን መዘዞች ይበልጥ ያከፏቸዋል፡፡ እንግዲህ በደም ግፊት የተያዘ ሰውም ከሌሎቹ እርምጃዎች በተጓዳኝ ምግቡ ውስጥ የሚኖረውን የጨው መጠን እንዲቀንስ የሚመከረውም ለዚህ ነው፡፡ ጨው መመገብ የደም ግፊቱ ከፍታ እንዲባባስ ከማድረግ በተጨማሪ ለደም ግፊት የሚወሰዱት መድኃኒቶችም በቅጡ እንዳይሰሩ ያደርጋል፡፡
ህመሙ ያለበት ሰው ላይ ጨውን በጥቂቱ ብቻ መመገብ የሚኖረው ጠቀሜታ አያጠያይቅም፡፡ ገና ባልተያዘው ሰው ላይስ? በጨው ይዘቱ ያየለ ምግብ መመገብ በደም ግፊት ሊያስይዘው ይችላል? ጥናቶች ለዚህ ያላቸው ምላሽ በከፊል አዎንታዊ ነው፡፡ እላይ የዘረዘርናቸው የአኗኗር ገፅታዎችና በዘር የመጠቃት እድል እያሉበት ጨው አብዝቶ የሚመገብ ሰው መጠነኛ ወይም ጥቂት ጨው ከሚወስደው ጋር ሲነፃፀር ቀድሞ በደም ግፊት የመጠቃት ዕድሉ ከፍ ይላል፡፡ ተመራማሪዎቹ ለዚህ እንደማስረጃ የሚያቀርቡት ምዕራባውያኑ በምግባቸው ውስጥ የሚጨምሩት ጨው ከፍ ያለ መሆኑን፣ የታዳጊ አገር ነዋሪዎች ግን የሚወስዱት የጨው መጠን መጠነኛ ከመሆኑ ባሻገር አብዛኛው በቀጥታ ከምግቡ ከራሱ የሚገኝ እንጂ ምግብ ላይ የሚጨመር አለመሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ሌሎቹ የዘርና የአኗኗር ገፅታዎችን ልዩነት አውጥተንም ከጨው ጋር በተያያዘ ብቻ ስናወዳድር ምዕራባውያኑ ይበልጥ በደም ግፊት እንደሚጠቁ እናስተውላለን፡፡
መልዕክቱስ? የጨው መብዛት ከምላስ ያለፈ ፋይዳ የለውም፣ ማነሱ ግን ሊጠቅመን ይችላልና የጨዋችንን ነገር ልብ እንበለው፡፡ ያለበለዚያ እንደአዛውንቱ ‹‹ደም ግፊት ማለት የሚጥም ምግብ ነው›› ለማለት እንበቃለን፡፡
ውድ ጠያቂያችን ከቀረበው ፅሑፍ በቂ ማብራሪያ እንዳገኘህ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ያለፈው አንዴ አልፏል፡፡ ተገቢው ጥንቃቄ አይለይህ፡፡
ማንኛውንም ነገር በመጠኑም ቢሆን አይጎዳምና የጨው መጠናችንንም በአግባቡ ብንወስድ ይመረጣል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የነጭ ሽንኩርት የጤና ጥቅሞች

2 Comments

  1. Ete Lamote…she lived with me for 40 years and more than that.mOST OF THE TIME she said sickness happened only when we weat alone-sickness comes
    comes when we eat engera and meat alone== now 70 years ago–hodamenet= hypertension–

  2. ኦኔ በጣም የምወዳት ልጅ አለች ታዲያ ችግሩ እኔና እሷ ተቀራርበን ወይንም ተታይተን አናዉቅም
    እኔ ከእሷ ፍቅር ይዞኛል ስለ እሷ ወሬና ጨዋነት ስለ ሰማሁኝ ብቻ?
    እናንተስ ምን ምክር ትሰጡኝ ኣላሁ?

Comments are closed.

Share