ይድረስ በ’ፈረንጁ ወያላ’ ለሳቃችሁ ሁሉ፤ እኛ ማን ነን?

ከሮቤል ሔኖክ
“ዋው ኢትዮጵያ አድጋ ነጮች ኢትዮጵያ ውስጥ ዝቅ ያለ ሥራ መሥራት ጀመሩ”
“ቂቂቂቂ….”
“አሁን ተራው የነጭ ባርነት በኢትዮጵያ ነው”
“ነጮች ይህን ሥራ መሥራታቸው ይገባቸዋል”

ሌላም ሌላም አስተያየቶችን በዩቲዩብ እና በፌስቡክ ላይ አነበብኩ – አንድ ዴንማርካዊ ጋዜጠኛ ‘ሰዎች ሲያደርጉት አይቼ እስኪ ልሞክረው ብሎ በሰራው የታክሲ የወያላነት ሥራ”። ብዙዎቹ ይህ ነጭ ኢትዮጵያ ውስጥ የታክሲ ወያላ ሆኖ በመሥራቱ ሲመጻደቁ፤ የ”ሃገሪቱ እድገት” ነጮችን ኢትዮጵያ ውስጥ ወያላነት እያሠራ መሆኑን በጀብደኝነት ሲያስወራ፣ አንዳንዶቹን ደግሞ ወያላነትን ንቀው የሥራ ክቡርነትን ገደል ከተው ነጩ ‘ወሎ ሰፈር… ወሎ ሰፈር እያለ’ ሲጠራ ቆመው ሲስቁበት ይታያል። አንዳንድ ሚዲያዎችም ‘ቬሪ ፈኒ” ሲሉ ቪድዮውን እንደጉድ እያሰራጩት ነው። በራሳችን እየሳቅን እንደሆነ አልገባቸው ይሆን?
በቅድሚያ እኛ በስደት ያለን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 80 ከመቶው ኢትዮጵያዊ (ሥራ የሚንቀውን ባዶ ኪስ የአእምሮ ደሃ) ሳይጨምር ማን ነን? ምንድን እየሠራን ነው ቤተሰባችንን የምንጦረው????? ዛሬ ይህ ነጭ ያውም እኛ ላይ ለሙከራና ለዜና ዘገባው እንዲመቸው በወያላነት ሥራ ተሰማርቶ የምንስቅበት እኛ ኢትዮጵያውያን በርሱ ሃገር ምን እየሠራን ይሆን? ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ በዛ ፈረንጅ ላይ የሚስቀው ወጣት እኮ በዛ ፈረንጅ ሃገር ምናልባትም በሃገር ቤት የሥራ ክቡርነት በማይገባቸው ሰዎች ሊያስቅ የሚችል ሥራ እየሠራን መሆኑን ተረድተውት ይሆን?

እስኪ እኛ ማን ነን ብለንም እንጠይቅ!

ይልቅ ኢትዮጵያዊ ንቃ! በሥራ ላይ አይሳቅም። በሚሰራም እንዲሁ። ቆመህ ስትስቅ ጀንበር የምትጠልቅብህና ውጭ ካለ ሰው “ላንተ የተናቀ ሥራ እየሰራ ገንዘብ በሚልክህ” ሰው ትከሻ ሥር ሆነህ ራስህን አትቆልል። ገንዘብ እስካስገኘና ራስን እስካስቻለ ድረስ ሥራ ሊከበር ይገባዋል። ከዚህ ከ19 ዓመቱ ዴንማርካዊው ጋዜጠኛ ሳይስ ፌልቦርግ ግሬገሰን የምንማረው ብዙ ነገር ሊኖር ሲገባ በርሱ ላይ በባዶ ኪስ በጉራ ብቻ ተውጥረን ልንስቅበት መሞከራችን አናዶኛል። ይልቅ የሥራ ክቡርነትን ከርሱ ተማር።

እኔ ብዙ ማለት አልችልም፤ በዚህ ወጣት ዴንማርካዊ ወጣት ላይ በኛ በኢትዮፕያውያን የተሰጡ አስተያየቶች አሳፍረውኛልና። ለማንኛውም ሪፖርተር ጋዜጣ ስለዚህ ወጣት የጻፈውን እናንብብና የሚያስተውል አ እምሮ ያለን እንማርበት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሐምሌ ጨረቃ! (ክፍል አንድ) - ከአንዱዓለም አራጌ ዋለ (አንድነት ም/ሊቀመንበር ከቃሊቲ ማጎሪያ)

ይስ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የጋዜጠኝነት ትምህርትን መማር ስለመረጠ፣ ለትምህርቱ የሚረዳውን ልምድ ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ ሳይስ ኢትዮጵያ ከመጣ ሁለት ወር ከግማሽ ሲሆነው፣ በቆይታውም በዝግጅት ክፍላችን በተለማማጅ ጋዜጠኝነት የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን (በእንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ) በጽሑፍ ሲዳስስ ቆይቷል፡፡ ወጣቱ ኢትዮጵያ ሲገባ ቀልቡን ስለሳቡት የታክሲ ረዳቶች ለመጻፍ በማሰብ ከአስራ ሦስት ቀናት በፊት (ዕለተ ዓርብ) እነሱ የሠሩትን ሠርቶ ስለወያልነት ቀኑ የጻፈውን ተርጉመን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

ዕለቱ ልክ እንደአብዛኛዎቹ ቀናት ሞቃታማ፤ ፀሐዩም ሃሩር ነበር፡፡ የታክሲ ተሳፋሪዎች ከምታቃጥለው ፀሐይ ለማምለጥ፣ መጠለያ ለማግኘትና ወዳሰቡበት ቦታ ለመድረስ ታክሲ ውስጥ ለመግባት ይጣደፋሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በፍጥነት የሚነጉዱ ሚኒባሶችን በፍጥነት ማውራት ከሚችሉ ወያላዎቻቸው ጋር መመልከት የዘወትር ክስተት ነው፡፡ ይህን ክስተት ለመጀመርያ ጊዜ ለተመለከተ ሁኔታውን ለመቀበል ይከብደዋል፡፡

በከተማዋ የፈረንጅ ወያላ ማየት የተለመደ ነገር ባይሆንም፣ በእለቱ ግን ከወሎ ሰፈር ቄራና ከቄራ ወሎ ሰፈር የሚጓዙ ተሳፋሪዎች የተመለከቱት ለየት ያለ ክስተት ነው፡፡ በእለቱ ለተከታታይ ዘጠኝ ሰዓታት በወያልነት ሥሰራ ሥራው ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ከሁለት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ስመጣ፣ እዚህ ተወልጄ ባድግ ኖሮ የወያልነትን ሥራ እሠራ ነበር ብዬ አስቤ ነበር፡፡ የወያላዎቹ ወርሃዊ ክፍያ በጣም ትንሽ እንደሆነ ግን ተረድቻለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ታክሲው የሚሄድበትን ቦታ በመስኮት ብቅ ብዬ እየጮህኩ መዳረሻ ቦታዎችን በመጣራት የወያልነቱን ሥራ ለመሥራት አስቤ ነበር፡፡

ሥራውን ለመሥራት ወስኜም ስለሥራው ጥልቅ መረጃዎችን ከሰጠኝ ከይድነቃቸው ንጋቱ ጋር በመሆን ካረፍኩበት ቤት ቅርብ ወደ ሆነ ታክሲ ማቆሚያ ሄድኩ፡፡ በመጀመሪያ ያነጋገርነው የታክሲ ሾፌር አብሬው እንድሠራ ካለመፈለጉም በላይ እብድ መስዬው ነበር፡፡ አሁንም ተስፋ ሳንቆርጥ ወደሌላኛው የታክሲ ሾፌር ስንሄድ እድላቸን ቀንቶ እሺታውን ገለጸልን፡፡ የሹፌሩ ዕድሜ 35 ሲሆን ስሙም ደረጄ ንጋቱ ይባላል፡፡ ይድነቃቸውም ለቀኑ እንደወያልነት ለምን መሥራት እንደፈለኩ ለደረጄ አስረድቶት ከጥቂት ድርድር በኋላ ተቀጠርኩ፡፡ ከቄራ ወሎ ሰፈር የሚሄደው መንገድ ቀጥ ያለ በመሆኑ ቦታውን ለማጥናትና በቦታው ለመሥራት ቀላል ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተቃዋሚዎች ድክመትና ለስልጣኑ ያላቸው ርቀት (ተመስገን ደሳለኝ)

ነገር ግን የታክሲውን በር መክፈትና መዝጋት እንዲሁም ገንዘብ መቀበልና መመለስ መለማመድ ነበረብኝ፡፡ ሥራው ከጠበኩት በላይ ከባድ ነበር፡፡ በመጀመርያ ላይ በር ለመዝጋት ስሞክር በእጄ ይዤያቸው የነበሩትን ሳንቲሞች መሬት ላይ በተንኳቸው፡፡ ለሥራው ዝግጁ ያልነበርኩ ቢሆንም ከአምስት ደቂቃ በኋላ ግን መንገዱ ላይ እየተዟዟርኩ ‹‹ወሎ ሰፈር ወሎ ሰፈር›› እያልኩ መጥራት ጀመርኩ፡፡

ከወሎ ሰፈር ቄራ ደርሶ መልሶችን ስናደርግ ከመኪናው ሳንቲምና ብር ይዤ ስወርድና መዳረሻውን ስጣራ አብዛኛው ሰው ይስቅብኝ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹም ተግባብተውኝ ለመቁጠር በሚያዳግት ሁኔታ ለምን ይህንን ሥራ እንደምሠራ ሲጠይቁኝ ነበር፡፡

ሳንቲሞችን በእጄ በአግባቡ መያዝ ተቸግሬ ስለነበር መሬት ላይ ሲበተኑብኝ ለቅመው ይሰጡኝ ነበር፡፡ መልሳቸውም ስንት እንደሆነ ለማወቅ ግራ ሲገባኝ ስንት እንደምመልስላቸው ትክክለኛውን መጠን ይነግሩኝ ነበር፡፡ ደረጄም ተሳፋሪዎቹ በሥራዬ እንደተደሰቱ ሲነግረኝ ሥራውን የመሥራት ፍላጎቴ ያይል ነበር፡፡ ተሳፋሪዎቹ ሲወርዱ ‹‹አመሰግናለሁ›› እንዲሁም ‹‹መልካም ቀን›› ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም ከ ሁለት ቢያጆ በኋላ ሳንቲሞችን ከእጄ አለማንጠባጠብ፣ ሂሳብ በትክክል መቀበልና መመለስ ቻልኩበት፡፡

የታክሲ ሹፌሩ ጥሩ እንግሊዝኛ ይናገር ስለነበር ጉዞ ላይም ሆነን እንዲመቸኝ አድርጎኛል፡፡ በየጉዞው መጨረሻ ላይ ተራ ጠብቀን ጉዞ እስክንጀምር ብዙ የዕረፍት ሰዓታት ነበሩን፡፡ በእነዚያ የዕረፍት ጊዜያትም በየታክሲ ማቆሚያው የሚያገኙኝ የታክሲ ሾፌሮች፣ ወያላዎችና መንገደኞች ሰላምታና ለዕለቱ ለምን ወያላ መሆንን እንደመረጥኩ በሚያቀርቡልኝ ጥያቄ ተጠምጄ ነበር፡፡ ይህ ሂደት የኢትዮጵያውያንን የተግባቢነትና የጓደኝነት መንፈስን እንድረዳ ስላደረገኝ ሁኔታው አስደንቆኛል፡፡

ከአምስት ቢያጆ በኋላ ሥራውን በደንብ እየተረዳሁ መጣሁ፡፡ ከዛ በኋላ ስድስተኛውን ቢያጆ ደረጄ በደረስንበት የታክሲ መዳረሻ ላይ ሳይቆም መንዳቱን ቀጠለ፡፡ ታክሲው ውስጥ ማንም ተሳፋሪ ባለመኖሩ በደረጄ ድርጊት ግራ ተጋባሁ፡፡ ከዚያም ደረጄ ሁኔታውን ሲያስረዳኝ በመስኮት ወጥቼ መዳረሻችንን እየጠራሁ ተሳፋሪዎችን እየለቀምን መሄድ እንዳለብን ነገረኝ፡፡ በዚህ ሁኔታም ተደናገጥኩ፡፡ ቀድሞ በነበሩን ቢያጆዎች ሒሳብ በመሰብሰብ ተጠምጄ ስለነበር በመስኮት ወጥቼ መዳረሻችንን አልተጣራሁም ነበር፡፡ ይልቁንም ደረጄ ሰዎችን ማየቱን ተያይዞ እናሳፍር ነበር፡፡ እየተጣራሁ የሚገቡት ተሳፋሪዎች የት እንደሚሄዱ ማወቅም ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን በሚሰጡኝ ሒሳብ የት እንደሚሄዱ ይገባኛል ብዬ ተስፋ አደረኩ፡፡ በታክሲው መዳረሻ ስንደርስ አንዳንድ ሰዎች ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳልከፈሉ አውቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ያልከፈሉት ሰዎች የትኞቹ እንደነበሩ መለየት አልቻልኩም፡፡ ስለዚህ ተሳፋሪዎቹ ከታክሲው ሲወርዱ እየከፈሉ እንደሚሄዱ ተስፋ ባደረኩት መሠረት ያልከፈሉኝ በሙሉ እየከፈሉኝ ወረዱ፡፡ ከዚያ ያደረግነው ነገር ቢኖር ተሳፋሪዎችን በየመንገዱ እየለቀምን ከመሄድ ይልቅ ተራችንን ጠብቀን እየሞላን መሄድ ስለነበር በሁኔታው ተደስቼ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዴሞክራሲ በተግባር: ‘ሰላማዊ ሰልፍ መከልከል!’

ምሳ ሰዓት ሲደርስ እጅግ ተርቤና በር የምከፍትበትና የምዘጋባቸው ክንዶቼ ዝለው ነበር፡፡ በሰፊው የምሳ ሰዓት እረፍታችን በርገር በላን ቡናም ጠጣን፡፡ ይህን ጊዜ ድካሜ ጠፍቶ ጉልበቴ ሁሉ ተመለሰ፡፡ ከምሳ ሰዓት በፊት በነበረው ቢያጆ በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም ሂሳቤን ቶሎ ሰብስቤና መልስ ሰጥቼ ስለነበር ከተሳፋሪዎች ጋር የማወራበትና መንገድ ላይ ያሉ ተሳፋሪዎችን የማስገባበት ጊዜ ነበረኝ፡፡ በዚህን ጊዜ በሥራዬ ጥሩ እንደሆንኩ ሲሰማኝ፤ ደረጀም በወያልነት መሥራት ስፈልግ አንድ ቀን ቀደም ብዬ ብነግረው አብረን ልንሠራ እንደምንችል ነገረኝ፡፡ ቢሆንም ግን ወያልነቱን ለዕለቱ የሠራሁት ለልምድ ብቻ ብዬ በመሆኑ መሥራት እንደማልፈልግ ብገልጽለትም፣ ከእሱ ጋር በነበረኝ ቆይታ ሥራዬን ስላደነቀና ኢትዮጵያ ስለነበረኝ ቆይታ ለረዥም ጊዜ በማውራታችን በጣም ደስተኛ ነበርኩ፡፡

የከሰዓት በኋላው ሥራ ከጠዋቱ ይልቅ የተጣደፈ ቢሆንም ሥራውን ስለተለማመድኩት ቀለል ብሎኝ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ክንዶቼ ይበልጥ እየዛሉ ነበር፡፡ ከመኪናው መውረድና ወደ መኪናው መግባት እግሮቼን ቢያደክሙትም መሄድ የነበረብንን ብዙ ቢያጆዎች ፈጽመናል፡፡ ጊዜው ሄዶ ፀሐይዋ መጥለቅ ስትጀምር የመጨረሻውን ቢያጆ ለመሥራት ተንቀሳቀስን፡፡ ክንዶቼ ሊቀነጠሱ የደረሱ እስኪመስለኝ ድረስ ቢደክመኝም ምኞቴን ስላሳካሁ ተደስቼ ፊቴ ላይ ከሚታየው ፈገግታ ጋር ደረጀን አመስግኜና ተሰናብቼ ከመኪናው ወረድኩ፡፡ በዕለቱ በእኔ ምክንያት ለሚደርስበት ኪሳራ 400 ብር ከፍዬዋለሁ፡፡ በውሎዬም የታክሲ ረዳቶች ሥራ ምን ያህል ጥረት እንደሚያስፈልገውና እንዴት ከባድ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡ ሁኔታው ግን በጣም አስደንቆኛል፡፡

Share