ሰላማዊ ሠልፍን እንደ ትግል ስልት – በ ሰለሞን ጎሹ

ተጻፈ በ  ሰለሞን ጎሹ

ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አንደበት የማይጠፋ አንድ አባባል አለ፡፡ ‹‹ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አላሠራ አለን!›› እንደ ፓርቲ ያለባቸውን ግዴታ ለመወጣትና መብታቸውን ለመጠቀም ከሕዝቡ ጋር መገናኘት አለባቸው፣

ስብሰባ ማድረግ አለባቸው፣ ለቆሙለት ዓላማ ሌሎች ደጋፊዎችን የመመልመል ሥራ መሥራት አለባቸው፣ ቢሮ ከፍተው በቋሚነት መሥራት መቻል አለባቸው፣ ፓርቲዎቹ ሥራቸውን በነፃነት ያለመንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጫናና ጣልቃ ገብነት ሕጉን ብቻ አክብረው መሥራት አለባቸው፡፡ ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት ኢሕአዴግ ከሕዝቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሁለት መንገድ እያወከው ነው፡፡ ሕዝቡ በፍርኃት ውስጥ እንዲወድቅና ከፓርቲዎቹ ጋር ግንኙነት እንዳይፈጥር ማድረግ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ የፍርኃት ደመናውን ለመገላለጥና ሕዝቡ በነፃነት የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ የሚሠሩትን ሥራ እያስተጓጎለ እንደሆነ ይከሳሉ፡፡

ኢሕአዴግ በበኩሉ ለስንፍናቸው ሁሉ ማምለጫ ያደረጉት ኢሕአዴግ ‹አላሠራ አለን› ቢሆንም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ክሳቸውን በማስረጃ ለማረጋገጥ እንዳልቻሉና ሕጋዊ መብቶቻቸውን ለመጠቀም የታገዱበት አጋጣሚ እንደሌለ በመግለጽ ራሱን ይከላከላል፡፡ በአባላት ምልመላ ረገድ የተሳካ ሥራ መሥራት የልቻሉት የሕዝቡን ፍላጎት የሚወክሉ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የፓርቲ አወቃቀር እንዲሁም የአመራር ብቃትና አንድነት ስለሌላቸው እንደሆነም ይጠቁማል፡፡

እነዚህ ሁለት ተፃራሪ ድምፆች በተለያዩ መገለጫዎቻቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዕለት ከዕለት ሕይወት ግብዓቶች ቢሆኑም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሰላማዊ ሠልፍን እንደ ሌላ አማራጭ የትግል ስልት የማየት አዝማሚያ እያዩት ይመስላል፡፡ በሰማያዊ ፓርቲ አዲስ አበባ ላይ፣ በአንድነት ፓርቲ በጎንደርና በደሴ የተደረጉት ሰላማዊ ሠልፎች በሌሎች ተጨማሪ ሰላማዊ ሠልፎች እንደሚቀጥሉ ፓርቲዎቹ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ እንዴት የፖለቲካ መሣሪያ ሊሆን ይችላል? የሰላማዊ ሠልፍ አሉታዊ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላማዊ ሠልፍ ሕጋዊና ፖለቲካ አንድምታው ምንድን ነው? ጠባቡን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ሰላማዊ ሠልፍ ምን ሚና ይኖረዋል? ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰላማዊ ሠልፍ ተሳታፊዎች ቁጥር ላይ የሚፈጥሩት የቁጥር ጨዋታ ከምን የተነሳ ነው? የሕዝቡን የፖለቲካ ነፃነትና ፍርኃት በምን መለካት ይቻላል? ከብሔራዊ ምርጫው በሁለት ዓመት ርቀት ላይ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሰላማዊ ሠልፎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች እንድናነሳ የሚያስገድደን ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሠልፎችን የተረጎሙበት የሰሞኑ አተያይ ነው፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ እንደ ትግል ስልት 
ከተለመዱት የትጥቅ ትግልና የምርጫ ውድድር ውጪ ሰላማዊ ሠልፎች እንደ ሌላ አማራጭ የትግል ስልት ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ በሰላማዊ ሠልፎች ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ወይ ድጋፉን ወይ ተቃውሞውን የሚገልጽበትን ስሜት ያንፀባርቃል፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ በአብዛኛው ጥቅም ላይ የሚውለው ሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ኃይል በአካሄዱ ላይ ለውጥ እንዲያመጣ ለማነሳሳት ነው፡፡ በተለይ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የተገቡ ጉዳዮች መፈጸም አለመፈጸማቸውን በማስመልከት የሚካሄዱ ሰላማዊ ሠልፎች ሌላ ምርጫ እስኪመጣ ድረስ በአመራሩ ላይ ጫና ለማድረግ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

ሰላማዊ ሠልፎች በአብዛኛው ለተወካዮች ደብዳቤ በመጻፍ፣ ለመንግሥት ቅሬታ በማቅረብ፣ በፕሬስ ላይ ጉዳዩን በማንሳትና የውትወታ ቡድኖች ጉዳዩን አጀንዳቸው እንዲያደርጉ በመገፋፋት የተደረጉ ጥረቶች ውጤት ሳያመጡ ሲቀሩ ነው ሥራ ላይ የሚውሉት፡፡

ተቃውሞ ለማሰማት ሰላማዊ ሠልፍን መጠቀም መብት ቢሆንም፣ በሌላ በማንኛውም መብት ላይ የሚደረጉ ገደቦች ለሰላማዊ ሠልፍም ተፈጻሚ ናቸው፡፡ በብዛት ከብጥብጥና ከፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር የተያያዙ የደኅንነት ጉዳዮች ሰላማዊ ሠልፎችን አስመልክቶ መንግሥታት የሚሰጉበት ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በርካታ ሕዝብ የሚታደምበትን ሰላማዊ ሠልፍ ለመጠበቅ የፖሊስና የደኅንነት ተቋማት ቅድሚያ ዝግጅት የማድረግ ፍላጎታቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመላው ዓለም እየጨመረ መምጣቱን የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በአንዳንድ ሰላማዊ ሠልፎች የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም መከሰቱም መንግሥታት ሰላማዊ ሠልፎችን በጥንቃቄ እንዲያዩት ማድረጉም ይገለጻል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ ሰላማዊ ሠልፎች እንደ መብት ማንኛውም ሐሳብ እንደሚገለጽባቸው ጠቁመው፣ ከደኅንነት አኳያ ግን ገደብ እንደሚያስፈግልጋቸው ይገልጻሉ፡፡ በተለይ የደኅንነት ሥጋትና የሰላማዊ ሠልፍ ግንኙነት ላይ ያሉት የተለያዩ አተረጓጎሞች የክርክር ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በታሪክም ቢሆን ሁሉም አብዮቶች የተነሱት ከሰላማዊ ሠልፍ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰሜን ኢትዮጰያው ጦርነት ድርድርና የአደራዳሪዎቹ ማንነት ያስከተለው ተስፋና ስጋት - አክሊሉ ወንድአፈረው

ሰላማዊ ሠልፍ እንደ ሕዝባዊ አለመታዘዝ
በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መንግሥት ሕዝቡ ተቃውሞውን በነፃነት እንዲገልጽ ማበረታታት  አለበት፡፡ የጎደሉና ሊታረሙ የሚችሉ ጉዳዮችን ወደ መንግሥት ትኩረት የማድረስ መብት ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ገደቡን እስካላለፈ ድረስ ሕዝባዊ አለመታዘዝም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የደኅንነት ተንታኙ የሚቀርበው ቅሬታ የዕለት ዕለት ሕይወትን በሚያደናቅፍ ሁኔታ ሊፈጸም እንደማይገባ ይገልጻሉ፡፡ “ሕዝባዊ አለመታዘዝ መብት ስለሆነ ብቻ መስቀል አደባባይ ሄደን ለሦስት ቀናት እንተኛ አትልም፡፡ በብዙ የዓረብ አገሮች እንደሆነው ሰላማዊ ሠልፎችን ቅሬታ የማሰሚያ መድረክነት ከመጠቀም ዘለህ መንግሥት ለመለወጥ መጠቀም ፖለቲካ ተቀባይነት ቢኖረውም ሕጋዊና ሕገ መንግሥት የተከተለ አካሄድ ግን አይደለም፡፡ አንዱ የመንግሥት አዎንታዊ ግዴታ የሰላማዊ ሠልፎችን አሉታ ገጽታዎች ጉዳይ መቆጣጠር ያስችለዋል፤” ይላሉ፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ ጥቅም ላይ የሚውለው አንድን ፖሊሲ ወይም የመንግሥት ዕቅድ ለመቃወም ከሆነ የተቃውሞ ሠልፍ ተብሎም ሊጠራ ይችላል፡፡ ነገር ግን በተቃውሞ ሠልፍ ጽንፈኛ ኃይሎችም ብጥብጥና የኃይል ጥቃትን ስለሚጋብዙ ለሌላ የፖለቲካ ጥቅም ተሳታፊዎች ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሠልፍ ቅሬታ ከማቅረብ በመዝለል የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ለተሰማሩ ለፀጥታ ኃይሎች ከቁጥጥር ውጭ እስከ መሆን ይደርሳል፡፡

የተቃውሞ ሠልፎች በብዛት በሚስተናገዱባቸው አገሮች የተለያዩ ተቋማት የተለያዩ ውጤቶችን በመጠበቅና የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ከተለያዩ የኅብረተሰብ  ክፍሎች ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ሠራተኛኞች፣ ወጣቶች፣ ሲቪክ ድርጅቶች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሃይማኖታዊ ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን በመጠበቅ፣ ጥያቄ በመጠየቅና የትግል ስልቶች በመቅረፅ ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ መንገድ በተቃውሞ የተራራቀ ድምፅ በሚያሰሙበት ሁኔታ ድጋፍ ያጣው መንግሥት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ድጋፍ  ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በአብዛኛው የዓረብ አገሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት የሆነውም ይኼው እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡

ፋቢያና ማቼዳ፣ ካርሎስ ስካርታሲኒና ማሪያኖ ቶማስ “Political Institutions and Street Protests in Latin America” በተሰኘ ሥራቸው ጠንካራ ተቃውሞ በተገነባባቸው አገሮች ሕዝቡ ተሳትፎ የሚያደርገውና የድጋፍና የተቃውሞ ስሜቱን የሚገልጸው ተቋማዊ አሠራሮችን ተከትሎ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ተቋማዊ ባሕል በሌለባቸው አገሮች ሕዝቡ ለአደባባይ ተቋውሞ የመውጣት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የላቲን አሜሪካ አገሮችን ምሳሌ በመጠቆም አስረድተዋል፡፡ አጥኚዎቹ ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ጠንካራ ተቋማት ባሉባቸው አገሮች ጭምር ለተቃውሞ የመውጣት አዝማሚያ እንዳላቸው ገልጸው፣ ደካማ ተቋማዊ ባሕል ባለባቸው አገሮች ግን ጽንፈኞቹ ከለዘብተኛ ዜጐች ጋር ለተቃውሞ እንደሚወጡ አመልክተዋል፡፡

ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነት በኢትዮጵያ
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 30 ላይ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሠልፎች በሚደረጉባቸው ቦታዎች በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር እንዳይፈጥሩ ለማድረግ፣ ወይም በመካሄድ ላይ ያለ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሠልፍ ሰላምን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና የሕዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥስ ለማስጠበቅ አግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡ ሆኖም ሕገ መንግሥቱ የወጣቶችን ደኅንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስምን ለመጠበቅ፣ የጦርነት ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ለመከላከል ሲባል ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነት በሚወጡ ሕጎች ሊገደብ እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡

ከሕገ መንግሥቱ ቀደም ብሎ የወጣው የሰላማዊ ሠልፍና የሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባዎች ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1983 ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባዎችን ለማድረግ ከፈለገ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎችን ሊፈጽም እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ ፖለቲካዊ ስብሰባ ከመደረጉ ከ48 ሰዓት በፊት ለተገቢ የመንግሥት አካላት የማሳወቅ ግዴታ ነው፡፡ ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ሰላማዊ ሠልፎችና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባዎች ከኤምባሲዎች፣ ከቤተ ክርስቲያኖች ወይም ከመስጊዶችና ከገበያ ቦታዎች በ100 ሜትር ርቀት ላይ የማድረግ ግዴታ ነው፡፡ ቅድሚያ የማሳወቅ ግዴታው ስለ ስብሰባው ተፈጥሮ፣ ጊዜ፣ የሚጠበቅ የተሳታፊ ቁጥርና ቦታ እንዲሁም ዓላማን መግለጽ የሚጠይቅ ቢሆንም ሕጉ ፈቃድ የመጠየቅን ግዴታ በምንም ሁኔታ አይጠይቅም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወገኖቻችንን ለዘመናተ የጨረሰው አደገኛው ዘንዶ፡-የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት - ሰርጸ ደስታ

ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 እና ከአዋጅ ቁጥር 3/1983 ውጪ የሰላማዊ ሠልፍ መብትና ግዴታዎችንና ገደቦችን የሚተነትን ሕግ የለም፡፡ እርግጥ በረቂቁ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ውስጥ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ የሚቀርብ የፈቃድ ሥነ ሥርዓት ተቀምጦ ይገኛል፡፡ መሠረታዊ የሕግ ድንጋጌ በሥነ ሥርዓት ሕግ ሊሻር ይችላል ወይ የሚለው የሕግ ክርክር እንዳለ ሆኖ፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 3/1983 ፈቃድ ሳይሆን የማሳወቅ ግዴታ ብቻ ይጥላል፡፡

ይሁንና በተግባር ግን የመንግሥት የሰላማዊ ሠልፍ የማሳወቅ ግዴታ አተረጓጎም ወደ ፈቃድ የተቀየረ ሲሆን፣ መንግሥት የፈቃድና ማሳወቂያ ቢሮ እስከ መክፈት ደርሷል፡፡ በፈቃድና ማሳወቂያ መካከል ያለው ልዩነት መንግሥትንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለዓመታት ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡ እስካሁን ድረስ የታቀዱ ሰላማዊ ሠልፎች ያለ ለውጥ የተካሄዱበትን ቀን ማስታወስ ይከብዳል፡፡ የደኅንነት ተንታኙ መንግሥት ፓርቲዎቹ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ማስታወቂያው ላይ የሚገልጿቸውን ዝርዝር ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የስብሰባ ቀኑን መቀየሩ አስገዳጅ ከሆነ ከአሳማኝ ምክንያት ጋር ያን ማድረጉ ችግር እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ወደ ፈቃድ መጠየቅ የቀየረው አሠራር ሕገወጥና ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፣ በሥራ ላይ ያለውን ሕግ መቀየር በመንግሥት እጅ ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከአወዛጋቢው ምርጫ 97 በኋላ ባለፈው ግንቦት ወር ሰማያዊ ፓርቲ ያካሄደው ስብሰባ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን በመጋበዝ የመጀመሪያው ነው፡፡ በያዝነው በሐምሌ ወር ደግሞ አንድነት ፓርቲ በጎንደርና በደሴ ሰላማዊ ሠልፍ አካሂዷል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲና አንድነት ፓርቲ የመጀመሪያው ዕቅዳቸው ለሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድ ባለማግኘታቸው ለመቀየር ተገደዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ አስራት ጣሴ ፓርቲያቸው ፈቃድ ለመጠየቅ በሕግ ባይገደድም፣ ለሰላማዊ ሠልፍ ፈቃድና ማሳወቂያ ክፍል በማለት ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዳቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ ከፈለግን በሕጉ መሠረት መከልከል አይችሉም፤ የሚፈለገው ማሳወቅ ነው፤›› በማለት አቶ አስራት በሕጉና በተግባር መካከል ያለውን ልዩነት ይገልጻሉ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሠልፍ የተላለፈው በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የተነሳ ሲሆን፣ የአንድነት የጎንደር ሰላማዊ ሠልፍ ደግሞ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምረቃ ስለነበረበት የጥበቃ ኃይል ያጥረናል፣ ያለአግባብ ግርግር ሊፈጠር ይችላል በሚል ምክንያት ነው፡፡ የደኅንነት ተንታኙ በቅን ልቦና ጉዳዩ ከታየ እነዚህ ምክንያቶች አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕግም ቢሆን አሳማኝ ማስተላለፊያ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ሆኖም ሕጉ በቋሚነት ወደ ፈቃድ ከተለወጠ ግን የመንግሥት አካላት አሳማኝ ባልሆነ የደኅንነት ሥጋት ጭምር በመከልከል ሥልጣናቸውን ያላግባብ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ በማውሳት ያላቸውን ሥጋት አመልክተዋል፡፡ የዚያኑ ያህል በሠልፎቹ አማካይነት ሌላ አጀንዳቸውን የሚያራግቡ አካላት ስብሰባዎቹን ያላግባብ እንዳይጠቀሙ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት
በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ምርጫ 97 ለአጭር ጊዜ የቆ ሰፊ ነፃነትን ለዜጎች ቢያጎናጽፍም ውጤቱ ዘላቂ ተፅዕኖ ያለው የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብን ማስከተሉን ይጠቅሳሉ፡፡ በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች፣ ተቋማትና አሠራሮች ሰፊ ነፃነቶችን የማያበረታቱና ነገሮችን ሁሉ በሥጋት የሚያዩ መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠቧል የሚል ተከታታይ ቅሬታ ከማቅረብ ውጪ ተጨባጭ የሆነ ሥራ በመሥራት ምኅዳሩን ለማስፋት አለመሞከራቸው ተወቃሽ አድርጓቸው ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ በሰላማዊ ሠልፎቹ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ እንዲሰረዝ፣ የታሰሩ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም፣ የሙስሊም አመራሮች እንዲፈቱ፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ነፃነት እንዲከበር፣ የፖለቲካ መረጋጋት እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲገታ፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እንዲቆም፣ አምባገነናዊ ሥርዓቱ እንዲሻሻል፣ ፍርድ ቤቶች ነፃ እንዲሆኑ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የሕዝብ አመኔታ እንዲፈጠር፣ ከባለድርሻዎች ጋር የውይይት መድረክ እንዲፈጠርና ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍን በመጠየቅ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት እንቅስቃሴው ሰፊው ሕዝብ እንዲሳተፍ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸው በመንግሥት አካላት ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸው፣ ቢሮዎቻቸው እንደሚዘጉና በሚገባ ሥራ እንዳይሠሩ እንደሚደረጉ፣ ስብሰባዎቻቸው እንደሚደናቀፉ፣ የሕዝብ ንብረትን እንዳይጠቀሙ እንደሚከለከሉና በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ሥራዎችን መሥራት እንዳልቻሉ በ2002 ዓ.ም. ሒዩማን ራይትስዎች “One Hundred Ways of Putting Pressure፡ Violations of Freedom of Expression and Association in Ethiopia” በተሰኘ ሪፖርቱ ገልጾ ነበር፡፡ የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ አስራት ጣሴ ፓርቲያቸው ሰላማዊ ሠልፍን እንደ ትግል አማራጭ የወሰደው ሌሎች ሕዝብ የማንቀሳቀሻ ዕድሎችን መንግሥት በማጥበቡ መሆኑን በመናገር፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት ሊጠቀሙበት እንደቻሉ በመጠቆም ከሪፖርቱ ጋር ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለሻለቃ ዳዊት - ሰለሞን ሥዩም ሲያትል፣ ዋሽንግተን

የቁጥር ጨዋታዎች
በግንቦት ወር በሰማያዊ ፓርቲ በተጠራው ሰላማዊ ሠልፍ የተገኙትን ተሳታፊዎች ቁጥር ፓርቲው በ15,000 እና በ20,000 መካከል የገመተው ሲሆን ኢቲቪ ወደ 2,000 የሚጠጉ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ነው የዘገበው፡፡ በደሴና በጎንደር የአንድነት ሰላማዊ ሠልፍ የተገኙት ሰዎች ብዛት በፓርቲው በቅደም ተከተላቸው በ50 ሺሕና በ40 ሺሕ አካባቢ ሲገምት፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሁለቱን ሰላማዊ ሠልፎች ተሳታፊዎች ቁጥር ከ1,000 የማይበልጥ ሲሉ ዘግበዋል፡፡

የደኅንነት ተንታኙ የቁጥር ልዩነቱ እጅግ ሰፊ መሆኑን ጠቁመው፣ ገዢው ፓርቲና መንግሥት በአንድ ወገን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላ ወገን ከትክክለኛው ቁጥር ወጥተው እያጋነኑ በቁጥር የሚጫወቱት ተቀባይነት ለመጨመርና የሌላኛውን ተቀባይነት ለማሳጠት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

አቶ አስራት በተመሳሳይ ብዙ ሕዝብ ከተገኘ ለፓርቲያቸው ትልቅ የፖለቲካ ትርጉም እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ዋነኛው ጉዳይ ሕዝቡ በመብቱ የመጠቀም መብትን እንዲገነዘብ በመሆኑ፣ የቁጥር ጉዳይ ለፓርቲያቸው በሁለተኛ ደረጃ እንደሚታይ አመልክተዋል፡፡

ፍርኃትን መግፈፍ
ሕዝቡ በፍርኃት እንዲሸበብ ኢሕአዴግ አድርጓል በማለት የሚከሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝቡ ፍርኃትን ከራሱ ላይ በመግፈፍ በነፃነት እንዲቀላቀላቸው በተለያዩ መድረኮች ጥሪ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሰላማዊ ሠልፍ ሌላኛው አስፈላጊነት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑም ይገልጻሉ፡፡ አቶ አስራት፣ ‹‹ሕዝቡ ከገባበት የፍርኃት ቆፈን እንዲወጣ ወደ ሕዝቡ ሄደን ሊከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ከፍለን መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ሕዝቡ በብዛት ወጥቶ ያለውን ችግር በመግለጽ ያለውንም ድጋፍ ለተቃዋሚዎች ካላሳየ መጪው ጊዜ አስቸጋሪ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ በቀጣይ ጊዜያት በደቡብ እስከ ጂንካ፣ በሰሜን እስከ መቀሌ እንዲሁም በምሥራቅ እስከ ሐረር ድረስ የተለያዩ ሰላማዊ ሠልፎችን የማድረግ ዕቅድ የያዘ ሲሆን፣ ዜጎች በተለያዩ ክልሎች ጥሪ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡ አበረታች የተሳታፊ ቁጥር መገኘቱም የሚያስቀጥል ምቹ ነገር መፍጠሩን ገልጾ፣ የፍርኃቱ ሲገፈፍ የተሻለ ቁጥር በቀጣይነት እንደሚጠብቅ አመልክቷል፡፡

የምርጫ ቅስቀሳ?
ቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ ሊካሄድ ከሁለት ዓመት ጥቂት ወራት ያነሱት ጊዜ ይቀራል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአብዛኛው ምርጫን ተገን አድርገው ብቅ የሚሉና ከምርጫ በኋላ ድምፃቸው የሚጠፉ ተቋማት ተደርገው ይወሰዱ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግን በመወዳደር ረገድ ጎልቶ የሚታይ ፓርቲ በአገሪቱ የለም፡፡ አገሪቱ የአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነት የሰፈነባት አገር ናት፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰላማዊ ሠልፎች ላይ የተነሱት መሠረታዊ ጥያቄዎች የምርጫ ቅስቀሳው ከአሁኑ ተጀመረ እንዴ የሚያስብሉ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አላችሁ ወይ ሲባል፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፀረ ሽብርተኝነት ሕግን ማውጣት ማለት መኪና በሌለበት አገር የትራፊክ ደንብ እንደማውጣት ይቆጠራል፤›› በማለት መመለሱ ፓርቲዎቹ አሁንም የአማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ እንዲሁም የፖለቲካ እውነታዎቹን በጥሞና ያለማየት ችግር ዛሬም እንዳለባቸው የሚጠቁም መሆኑን የሚተቹ አሉ፡፡

የዛሬ ስምንት ዓመት በተካሄደው ድኅረ 97 ምርጫ የተቃውሞ ሠልፍ ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ከመሆናቸው አኳያ ሰላማዊ ሠልፎቹ በሰላም ማለቃቸው የሚበረታታ ነው፡፡ ሆኖም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን ሥራ ለመሥራት አባሎቻቸው እንደተንገላቱና አንዳንዶችም በእስር ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የስብሰባውና የሰላማዊ ሠልፉ ተሳታፊዎች ሙስሊሞች መሆናቸውን በመጠቆም ጉዳዩን ከሽብርተኝነትና ከአክራሪነት አጀንዳ ጋር ማገናኘታቸውም አዋጭነቱ አጠያያቂ መሆኑን የጠቆሙት የደኅንነት ተንታኙ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የተገኙት የእስልምና አማኞች ቁጥር በርካታ መሆን ከዚህ ቀደም መንግሥት ‹ጥቂት አክራሪዎች› በማለት ከሚገልጸው ጋር የሚጋጭ መሆኑን ጠቁመው የሃይማኖት ጉዳይ የቀጣዩ ምርጫ አንድ አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

 

Share