ከሊሊ ሞገስ
የተለያዩ አጋጣሚዎች ለምሳሌ በት/ቤት ለተማሪዎች፣ በስራ ቦታ ለሠራተኞች፣ ሰዎች እንዲለወጡ የሚያስችላቸውን መልዕክት ከማስተላለፍ አንፃር፣ የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳዎችን በሞቀ ሁኔታ ለማድረግ (ኦባማን ልብ ይሉዐል)፣ የተለያዩ ጥፋቶችን ያጠፉ ሰዎችን ለማረም ሰብስቦ ቀጥተኛ የእርምት እርምጃ በመውሰድ ላይ ያተኮረ ንግግር የመሳሰሉትን መሰረት በማድረግ አድማጩን ወደ አንድ ነገር የሚያመጡ አሳማኝ ንግግሮችን እናደርጋለን፡፡ እነዚህ ንግግሮች ታዲያ የራሳቸው የሆነ የሚያስተላልፉት የተለያየ መልዕክት እንደመኖሩ መጠን የራሳቸውን አላማ ከማሳካት አንፃርም የሚጠቀሙበት ቴክኒክ የተለያየ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም ላይ እንደ ጋራ ልናገኛቸው የምንችላቸው ወሳኝ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህን በንግግራችን ውስጥ እያዳበርናቸው ስንመጣ በየትኛውም አጋጣሚ አሳማኝ ንግግሮችን ማድረግ እንችላለን፡፡ አሳማኝ ንግግሮችን ማድረግ የንግግርን የተቀናጀ አካሄድ ከመያዝ ጋር ብቻ በተገናኘ ሳይሆን ውጤታማ ሊያስብለው የሚችለው የሚነገረው (የሚተላለፈው) መልዕክት በምን መልኩና ምን አይነት ሆኖ ነው አድማጩ ጋር መድረስ ያለበት የሚለው ነው፡፡ አድማጮች ምን አይነት ናቸው፤ የንግግር ሀሳቦች እንዴት ታማኝነት ኖሯቸው ይተላለፋሉ፤ መረጃዎች ያላቸው ተቀባይነት፣ ለምክንያታዊነት የተጠቀምንባቸው ዘዴዎች፣ የአድማጩን ስሜት የምንረዳበት መንገድ የመሳሰሉት መሰረታዊ በሆነ መልኩ ከእንደዚህ አይነት ንግግር ጋር ሊነሱ የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡ እነዚህን አጠቃላይ በሆነ መልኩ እያነሳናቸው እንመጣና በውስጣቸው ሊይዙት የሚችሉ ነጥቦችን እየዘረዘርን በማየት የሚያሳምኑ ንግግሮችን ለማድረግ የሚጠቅሙ ነጥቦችን እንደሚከተለው እናነሳቸዋለን፡፡
1. የአድማጩን ማንነት መለየት
አሳማኝ የሆኑና ሰዎች ሳያስቡት ነገር ግን ንግግሩን የራሳቸው ፍላጎት አካል አድርገው እንዲቀበሉት የሚያደርጉ ንግግሮችን ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ አድማጩ ምን አይነት እንደሆነ መለየት ነው፡፡ አድማጩን በደንብ መለየት ከቻን በኋላ ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው የሚለውን አይተን በሚፈለገው የሃሳብ ተልዕኳችን በየአድማጩ ጫማ ውስጥ ራሳችንን አቁመን እነሱ በሚያዩት እይታ ውስጥ እኛም እያየን የምንፈልገውን መልዕክት በውስጣቸው ማስረፅ እንችላለን፡፡ አስቀድመን ንግግራችን እያንዳንዱ ነገሮችን እነሱ ከሚያዩበት አቅጣጫ በመነሳት የራሳችንን የምንፈልገውን ሀሳብ ማስረፅ ይገባል፡፡ የአድማጩን ማንነት ለመለየት ከምንጠቀምባቸው መንገዶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-
– አድማጩን መገምገም (Abalyze listeners)፡- ስለ አድማጩ በቂ የሆነ መረጃ አስቀድሞ ማግኘት፡፡ ከራሳቸው ከአድማጮቹ በመነሳት ቀድሞ በሚሞላ መጠይቅ ወይም አጠቃላይ ስለማንነታቸው ከሚናገሩ የተለያዩ ምንጮች የተነሳ ይህንን ማድረግ ይቻላል፡፡ ወይም አድማጩ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ፕሮግራም ያለው ሁኔታ ወይም አቀራረብ ምን እንደሚመስል መረጃ በመጠያየቅ ሊሆን ይችላል፡፡
– የማሳመኛ የስኬል መጠንን መጠቀም (use a persuasion scale) የተለያዩ አድማጮች ከየት እንደመጡ፣ ምን አይነት ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚችል፣ ምንስ አይነት ነገር እደሚፈልጉ የሚያሳይ የቅድሚያ ግምትን የሚያሳዩ ስኬልን ነድፎ በማዘጋጀት የአድማጩን አጠቃላይ ሁኔታ ማግኘት ይቻላል፡፡
– ራሱን የቻለ ስትራቴጂ ማዘጋጀት (Plan strategy)፡- አጠቃላይ ሁኔታዎችን የሚገልፅ የአንተን ንግግር ከአድማጮቹ አንጻር ሊያመጣ የሚችለውን የቅድመ ትንበያ ግምት በመውሰድ ስትራቴጂ አውጥቶ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከአድማጮቹ ውስጥ የአንተን ሀሳብ የሚደግፈው፣ የሚጠላውን፣ ግራ ሊገባው የሚችለው የትኛውና ምን ያህሉ እንደሆነ በመገመት የሁሉንም ሀሳብ ሊዳስስ በሚችል መልኩ ለንግግሮቻችን አጠቃላይ ስትራቴጂ ማውጣት ይገባል፡፡ ስትራቴጂ አውጥተን ንግግራችንን ስናዘጋጅ የእያንዳንዱን አድማጭ ስሜት ከመንካት ጋር በተያያዘ ልንቆጣጠራቸው የምንችላቸውን ነገሮች ምን አይነት እንደሆኑ ያሳየናል፡፡ በየትኞቹ አድማጮችስ ላይ ብዙ ጊዜና ኢነርጂ ልናባክን እንደሚገባን ይጠቁመናል፡፡ በእነዚህ መሰረታዊ መነሻዎች የተለያዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ በተለይም አድማጩ ላይረዳው የቻለው፣ የሚረዳው ሆኖ ተቃውሞ የሚያስነሳበት፣ የሚረዳው ግን ጉዳዩ እንዳልሆነ የሚያስበው፣ መረጃው ያለው ነገር ግን ከሃሳቡ መራቅ የሚፈልግ፣ ከንግግር ሀሳቦቹ ጋር ተሳስቦ መጓዝ የሚችለው፣ ወደ እርምጃዎች ለመጓዝ የተዘጋጀው የመሳሰሉትን በተቀናጀ መልኩ በመለየት ንግግሩ አላማዬ ያለውን መልዕከት ማስተላለፍ አለበት፡፡
2. ተአማኒነትን መፍጠር
ንግግሮቻችን ራሳችንን የመግለፅ ኃይል ስላላቸው ሁልጊዜም ምን አይነት ተአማኒነት ሊያገኙ ይችላሉ ብለን ልናስብ ይገባል፡፡ ራሳችን ንግግር ማድረግ በፈለግን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በዛ ውስጥ አብሮ ሊገኝ የሚችል ተአማኒነትን የመፍጠር ብቃታችን ንግግር ስናደርግ ከመልዕክታችን አላማ ጋር የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ መልዕክታችን ህይወት እንዳለው የምንገነዘበው በምናስተላልፈው መልዕክት ውስጥ አድማጩ ሊሰጠን ከሚችለው ምላሽ በመነሳት ለእኛ ያለውን ተአማኒነት ሲያንፀባርቅ ነው፡፡ ተአማኒነትን የመፍጠር ሃይል ያለው ንግግር በቂ ጊዜ ወስደን ስናዘጋጅ ሰዎችን በንግግራችን የማሳመን ኃይላችን ከፍተኛ እየሆነ እንደሚመጣ አውቀን ልንዘጋጅ ይገባል፡፡
ንግግራችን ተአማኒነትን እያገኘ በመጣ ቁጥር መልዕክታችን ትክክለኛ እንደሆነ ከማሳየቱም ባሻገር የእኛንም ስብዕና በመገንባት የተሻለ እውቀት እንዳለን፣ ከአድማጭ ጋር መግባባት እንደምንችል፣ ብዙ ክህሎት ያላቸው ሰዎች እንደሆንን እንዲገነዘቡ ማድረግ እንችላለን፡፡ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ሌላኛው ንግግራችንን አሳማኝ የምናደርግበት መንገድ ይሆንልናል፡፡
3. በቂ መረጃ መስጠት
(Providing enough evidence)
አድማጮቻችን በእኛ ንግግር ላይ መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን በሚፈልጉት መልኩ የማቅረብ ችሎታችን የንግግራችንን ተፈላጊነት የበለጠ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ የንግግራችንን አሳማኝነት የበለጠ ያጎላዋል፡፡ ንግግራችን ምን አይነት መረጃዎችን መያዝ አለበት ስንል፡-
– ትክክለኛነታቸው በሰፊው ሊታወቅ የሚችል
– ወቅታዊና የቅርብ ጊዜ መረጃዎች መሆን አለባቸው
– መረጃዎቻችን አንፃራዊ መሆን አለባቸው
– መረጃዎቻችን በተለያዩ ምንጮች በግልፅ መቀመጥ የሚችሉ መሆን አለባቸው
– የተለያዩ ምሳሌዎችን በመያዝ የተለያዩ አቅጣጫዎችን የሚያሳዩ መሆን አለባቸው
– መረጃዎቻችን በራሳቸው መገለፅ የሚችሉና ሌላ መንዛዛት ውስጥ የማይከቱ ወጥነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል
– ከአጠቃላይ ወደ ዝርዝር ወይም ከዝርዝር ወደ አጠቃላይ እንደየቦታቸው እና እንደአስፈላጊነታቸው የሚያስኬዱ የመረጃ አቀራረቦችን መተግበር እነዚህን በመሳሰሉት ላይ መረጃዎቻችን ምን ያህል በቂ መሆናቸውን በመገንዘብ አድማጩ የሚረዳበትንና እንደ ፍላጎቱ በምናቀርብለት መንገድ ለንግግራችን አሳማኝነት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
4. ተነሳሽነትን የሚፈጥር ንግግር ማቅረብ
(Appealing motivation)
ንግግራችን በራሱ ሙሉ ኃይል ያለው አድማጩን የሚያነቃና የሚያነሳሳ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉ ከሆነ በእያንዳንዱ የንግግራችን ክፍሎች የአድማጩን ተነሳሽነት በማግኘት ሁሉ ነገሩን ከእኛ ጋር እንዲያደርግ በመሳብ ወደ አሳማኝ ንግግር ውስጥ ራሳችንን መክተትና እነሱም የዚህ ክፍል ተቀባይ ተዋናይ እንዲሆኑ ማድረግ እንችላለን፡፡ አድማጩን ልናነሳሳበት ከምንችለው መንገዶች መካከል፡-
– አድማጩ እንድትወደውም እንድታከብረው ይፈልጋል፡፡ ታዲያ ይህን የሚያሳዩ ንግግሮችን ስናደርግ አድማጩ ራሱ ንግግር አድራጊውንም እየወደደውና እያከበረው ይመጣል፡፡ ተነሳሽነቱንም ከእሱ ጋር በመሆን ይገለፃል፡፡
– አድማጩ ከድካሙና ከህመሙ እንዲነቃቃና እንዲፈወስም መፍትሄ ላይ በማተኮር ነገሮችን በማስረሳት የሚያበረታቱ ንግግሮችን ማድረግ
– አድማጩን ከንግግሩ ውስጥ አንድ ማንነቱን ሊያስጠብቅለት የሚችል ነገር ከመፈለጉ ይህን የሚያሳውቁ አበረታች ንግግሮችን ማድረግ
– የተጎዳበትን መንገድ ለምሳሌ የገንዘብ እጦቱን የሚቀርፍበት መንገድ የመሳሰሉትን እንደ መፍትሄ ሊያገኝበት የሚያስችለውን መንገድ የሚያሳየውና ለዚህም የሚያነሳሳው ንግግር ማድረግ
– ንግግር የሚያደርገው ሰው አድማጩን በማነሳሳት ራሱ በራሱ ለመለወጥና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ የሚጋብዝ ማድረግ
– ንግግራችን ዘና የሚያደርግና (የተለያዩ ሰዎችን ፍላጎት ባማከለ መልኩ) ነፃነትን የሚያሳይ ማድረግ
እኒህን መሰል ሀሳቦችን በንግግራችን ውስጥ ስናካትታቸው በተለይም የአድማጩን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ስናደርገው አድማጩን ወደ ራሳችን የማምጣት ኃይል ይኖረናል፡፡ ሁል ጊዜ ግን ልናስብበት የሚገባው አድማጩን የሚያነሳሱና ውስጡን ወደ አንድ ነገር ወይም ወደ ንግግሩ አላማ የሚያመጣ እንዲሆን የንግግር ዝግጅታችንና አላማው ላይ ልናተኩር ይገባል፡፡ እዚህ ላይ የባራክ ኦባማን የንግግሩን አላማና አካሄዱን እንደ ምሳሌ ልናይ እንችላለን፡፡
5. ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮችን ማድረግ
(Arousing Emotions)
የተለያዩ ምርጥ ቃላትን በንግግራችን ውስጥ በመጠቀም፣ የሌሎችን ቀልብ የሚገዛ ስብዕናም በመላበስ አድማጩን ለበለጠ ስሜት ማነሳሳት እንችላለን፡፡ የቋንቋችን ጥንካሬ የሚለካባቸው አጠቃላይ ነገሮች የአድማጩን ስሜት የሚያነቃቁ እስከሆኑ ድረስ የማሳመን ሃይላቸውም የዛኑ ያህል እየጬመረ ነው የሚመጣው፡፡ ታዲያ ንግግሮችን በሙሉ በቂ የሆነ ምክንያታዊነትን በመያዝ ከቀስቃሽ አቀራረቦች ጋር ካያያዝነው የአድማጩን ጆሮ የማግኘት እድል ብቻ ሳይሆን የአድማጩን ፍላጎት ከእኛ ፍላጎት ጋር በማጣመር ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ ልናመጣው እንችላለን፡፡ በንግግራችን ብቃት የእኛን ማንነት ልናሳውቀውና ንግግራችንን በግድ ልናግተው ሳይሆን በንግግራችን ምን ያህል እያሰብንለትና እየረዳነው እንደሆነ የሚሰማው አይነት ስሜት በውስጡ ማስረፅ የሚያስችል መሆን አለብን፡፡ ለንግግሮቻችን ስርዓትና ወጥነትን ባላበስነው ቁጥር ከተአማኒነቱ ጋር የአድማጩን ስሜት መቀስቀስ እንችላለን፡፡
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው መሰረታዊ ነጥቦችን የንግግር ክፍሎቻችን አካል አድርገን ስናቀርባቸው ንግግራችን በደረቁ መልዕክት የሚያስተላልፉ ብቻ ሳይሆን በራሱ ህይወት ኖሮት የሚናገርና አድማጩን ወደ ምንፈልገው የለውጥ መንገድ እንዲመጣ የምናደርገው ነው፡፡ ይህ ደግሞ አድማጩን የሚያሳምኑ ንግግሮችን ማድረግ የእኛው የተፈጥሯችን እስኪመስል ድረስ የራሳችን መለያ ማድረግ የሚያስችለን ዘዴ ነው፡፡ የትኛውንም አድማጭ የሚያሳምኑ ንግግሮችንም በዚህ መልኩ በቀላሉ ማድረግ እንችላለን፡፡