Sport: የማን.ዩናይትዱ ዴቪድ ሞዬስ ሩጫ ተጀመረ!!

August 2, 2013

ዓርብ ከሰዓት በኋላ አሰልጣኙ ስብስብ ያሉ የጃፓን ቱሪስቶችን አስከትለው ኦልድትራፎርድ ደረሱ፡፡ በማንቸስተር ዩናይትድ ፈፅሞ የማይቀየሩ እውነቶች አሉ፡፡ በክለቡ ውስጠኛ ክፍል ግን እንግዳ ነገሮች ይታያሉ፡፡ የክለቡ ስታፎች በጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ለብሰውት የተገኙት ዘመናዊ ሙሉ ልብስ በአይነቱ አልተለወጠም፡፡ በ10፡00 ሰዓት የጋዜጣዊ መግለጫውን ትኩረት የሳቡት ሰው ግን አዲስ ናቸው፡፡ ቦታው ባለፉት 27 ዓመታት ያሳየውን ለውጥ ለሌሎች አሳየ፡፡

ለዴቪድ ሞዬስ እና በፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኖች አዲሱ የስራ ዘመን የጀመረው በፀሐያማ ከሰዓት ነው፡፡ ሆኖም የሰር አሌክስ ፈርጉሰኑ ምትክ ስራቸውን ሲጀምሩ ለሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ ተገቢ መልዕክት ነበራቸው፡፡

‹‹እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም እድለኛ ነኝ›› አሉ ሞዬስ፡፡ ‹‹ሁኔታው ሁሉ እንግዳ ሆኖብኝ ነበር፡፡ ስለሆነው ሁሉ ምንም እውቀት አልነበረኝም፡፡ ሰር አሌክስ ስልክ እስኪደውሉልኝ ድረስ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም ወደ ቤታቸው እንድመጣ በስልክ ጠየቁኝ፡፡ ከተጨዋቾቼ መካከል አንዱን ሊወስዱ መፈለጋቸውን እንደሚነግሩኝ ገመትኩ፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ በቀጣዩ ሳምንት ጡረታ ልወጣ ነው አሉኝ፡፡ ቀጥለውም እነዚህን ቃላት አስከተሉ፡፡ ቀጣዩ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ አንተነህ ይህንን ስሰማ እሺ ወይም እምቢ ለማለት እድሉ አልነበረኝም፡፡ ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ መሆኔ ተነገረኝ፡፡ ይህ በቂ ነበር፡፡ የሚታመን ግን አልነበረም፡፡

‹‹በግማሽ ሰዓት ውስጥ ሰር አሌክስ ስለ ቡድኑ፣ ስለ ተጨዋቾቹ እና ስለ ስታፉ ያወሩልኝ ጀመር፡፡ የሚሆነውን ሁሉ አምኖ መቀበል ቸግሮኝ ነበር፡፡ ጉዳዩን በምስጢር ለመጠበቅ ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ስለ ክለቡ ብዙ ነገር ነገሩኝ፡፡ ምን ያህል ታላቅ ክለብ እንደሆነም አብራሩልኝ፡፡ ይህንን ሁሉ ለመሸከም እንደምችል አምነውብኝ ነበር››

ሞዬስ ቀጠሉና ባለፈው ሳምንት ስራቸውን ሲጀምሩ ስለተፈጠሩ አጋጣሚዎች ማስረዳት ጀመሩ፡፡ በአንደኛው ቀን በልምምድ ማዕከሉ የሚገኘው የሞዬስ ቢሮ ተንኳኳ፡፡ በር ላይ የቆሙት ትልቅ ሰው ነበሩ፡፡ ሰር ቦቢ ቻርተን ወደ ውስጥ ዘልቀው ለሞዬስ መልካሙን ሁሉ ተመኝተው ሄዱ፡፡

ቀጣዩ የሞዬስ እንግዳ በአካል አልመጣም፡፡ ሆኖም ለሁለት ሰዓታት በስልክ አወሩት፡፡ ፖል ስኮልስ ነበር፡፡ የቀድሞው የዩናይትድ አማካይ በአዲሱ አሰልጣኝ ስታፍ ውስጥ ቦታ እንዲወስድ የቀረበለትን ግብዣ ውድቅ ቢያደርግም ስለ ቡድኑ ተጨዋቾች ያስተዋላቸውን እና የሚያውቃቸውን ዝርዝር መረጃዎች ለሞዬስ አብራርቷል፡፡

ሞዬስ ከጉዲሰን ፓርክ በቀጥታ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ሲመጡ ማንቸስተር ዩናይትድ ከእግር ኳስ ክለቦች በዓለም እጅግ አስደናቂው መሆኑን ሳያስቡ አልቀሩም፡፡ ባለፉት ቀናት ደግሞ በአካል የተመለከቷቸው የክለቡ ውስጣዊ እውነቶች መደነቃቸውን አብዝተውባቸዋል፡፡ ሰውዬው ከ15 ዓመታት በፊት በፕሪስተን ኖርዝ ኢንድ የተጫዋች አሰልጣኝ ሆነው ስራ ሲጀምሩ ሁኔታው ሁሉ ከአሁኑ የተለየ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በጊዜው የ34 ዓመት ተከላካይ የነበሩት ዴቪድ የእግርኳስ ህይወታቸው አዲስ የህይወት አቅጣጫ መጀመር እንደሚገባው አውቀው ነበር፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወት ብዙ ተራምደው በትልቁ ፕሪሚየር ሊግ በኤቨርተን በታማኝነት ስኬታማ ሊባል የሚችል ረጅም ጊዜ ካሳለፉ በኋላ አሁን ወደ ሌላ ከፍታ መጥተዋል፡፡ ሆኖም የአሁኑ እርምጃቸው ፈታኝ ነው፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ትልቅ ስም የተከሉትን ሰር አሌክስን የመተካት ከባድ ስራ ከፊታቸው ቆሟል፡፡

ሞዬስም ይህንን ይገነዘባሉ፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ይህንን ኃላፊነት ሲወስድ የቀደሙት አሰልጣኝ የሰሩትን ያውቃል›› ይላሉ፡፡ ‹‹የሰር አሌክስ ስኬት አምሳያ የለውም፡፡ እዚህ መስራት የምፈልገው ዴቪድ ሞዬስ ቀድሞ ይሰራው የነበረውን ነው፡፡ የማንቸስተር ዩናይትድን ልማዶች ሁሉ ያለምንም ጥያቄ አስቀጥላለሁ፡፡ ሆኖም በክለቡ የራሴን አሻራ ልተው ይገባል፡፡ የእንግሊዝ ሻምፒዮን የሆነን ቡድን በመረከቤ እድለኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ ይህ ጅማሬዬን ያሳምረዋል፡፡ ይህ ብዙ አሰልጣኞች የማያገኙት ጥሩ ዕድል ነው፡፡

‹‹ሰር አሌክስ ጠንካራ እና የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በድጋሚ ሊያነሳ የሚችል ቡድን አስቀርተውልኛል፡፡ የመጣሁት ሻምፒዮንነትን እንደ ንቅሳት በሁሉ ምልክቶቹ ላይ ወዳኖረ ክለብ ነው፡፡ ዩናይትድ ማለት አሸናፊነት ነው፡፡ እኔም ይህንን ለማስቀጠል መጥቻለሁ፡፡ በዚህ አልቀየርም፡፡ የመጀመሪያውን ዋንጫዬን ለማንሳት ቆርጫለሁ፡፡ ይህንን ኃላፊነት ለመረከብ ብቁ የሆኑ ብዙ ታላላቅ አሰልጣኞች ነበሩ፡፡ ሆኖም ለእኔ ትልቁ በራስ መተማመን ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቀጣዩ የክለቡ አሰልጣኝ እንድሆን መፈለጋቸው ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ለምክር ወደ እርሳቸው ስልክ ደውዬ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ለቦታው መረጡኝ፡፡ በኋላም ቦቢ ቻርተን ሊመለከቱኝ ሲመጡ እጅግ ተደስቻለሁ››

ሞዬስ ለ26 ደቂቃዎች በጋዜጠኞች ፊት ንግግር ሲያደርጉ ብዙ ነጥቦች አንስተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የክለቡን ቅርፅ ከሰጡት ሰዎች የረጅም ጊዜ እቅድ ሳያፈነግጡ ራሳቸው ባመኑበት መንገድ ለመስራት መነሳታቸውን አብራርተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ከጎናቸው እና በዙሪያቸው የሚሆኑትን ሰዎች ማንነት ለይተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአዲሱ አሰልጣኝ ዋነኛ ረዳት የሚሆኑት ሰውም ታውቀዋል፡፡

አሁን ጉዞው ተጀምሯል፡፡ ስቲቭ ራውንድ ዋና ምክትል አሰልጣኝ እና ጂሚ ሉምስዳን አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኦልድትራፎርድ የአሰልጣኙ አይን እና ጆሮ ሆነው ይሰራሉ፡፡ ቀጥሎ አሰልጣኙ አስቀድመው የተዘጋጁበትን እና ብዙዎች የጓጉለትን ጥያቄ ተቀበሉ፡፡ በዌይን ሩኒ ዙሪያ ከ10 በላይ ጥያቄዎችን አስተናገዱ፡፡ ሞዬስ በማንቸስተር ዩናይትድ የሚዲያ ሰዎች ትብብር ጣልቃ እየገባባቸው እንዳይጠቀዩ ሆነው በነፃነት መለሱ፡፡ ብዙዎች እንደገመቱት ዌይን አይሸጥም›› አሉ፡፡ ይህ የሞዬስ ንግግር ተጫዋቹ ራሱን ጨምሮ ሌሎችም ሰፊ ማብራሪያ የሚፈልጉበት መሆኑ እርግጥ ነበር፡፡ ሞዬስ ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡

እውነተኛው ነገር ዌይን የማይሸጥ መሆኑ ነው፡፡ አሁን የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ነው፡፡ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ከእርሱ ጋር ብዙ አውርተናል፡፡ ቀደም ሲል የተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ አልፈዋል፡፡ አሁን አብረን እየሰራን ነው፡፡ አይኖቹን አንብቤያቸዋለሁ፡፡ ደስተኛ ይመስላል፡፡ ሁሉን ነገር ትቶ በትክክለኛው ጎዳና ላይ መገኘት መፈለጉ ይነበብበታል፡፡ ከእረፍቱ በጥሩ ሁኔታ እና አቋም ተመልሷል፡፡ አብሬው ለመስራት ጓጉቻለሁ፡፡

ዌይን አብሯቸው ቆየም አልቆየ አሰልጣኙ ነገሮቹን እና አዳዲሶቹን ተጨዋቾቻቸውን ይዘው ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ያውቃሉ፡፡ ማንቸስተር ዩናይትድ ፈርጉሰን የመጀመሪያ ዋንጫቸውን እስኪያገኙ ያሳየውን ትዕግስት ለእርሳቸውም እንደሚደግም አይጠብቁም፡፡ ፈርጉሰን በደጋፊዎች ዘንድ እንዲሰናበቱ መጠየቅ ከተጀመረ በኋላ የ1990 ኤፍኤ ካፕ ዋንጫውን አሀዱ ብለው ለማንሳት ሶስት ዓመት ተኩል ወስዶባቸዋል፡፡ አሁን ግን ዘመኑ ሌላ መሆኑን ሞዬስ ራሳቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹በዚህ ዘመን አሰልጣኞች ጊዜ እንዲሰጣቸው መጠየቅ የሚችሉ አይመስለኝም›› ይላሉ ኤቨርተንን ለ11 ዓመታት ያገለገሉት አሰልጣኝ፡፡ ‹‹አሁን ማንም አይታገስህም፡፡ መጠየቅ የምትችለው እየሰራኸው ያለኸው በፍትሀዊ መልኩ እንዲመዘንልህ ነው፡፡ አሰልጣኞች አሁን እጅግ የሚቸገሩበት ነገር ጊዜ ማጣት ነው››

ሞዬስ ይህንን በአዕምሯቸው ይዘው የመጀመሪያ ሳምንታት ጨዋታቸውን ከቼልሲ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ከሊቨርፑል ጋር ለማድረግ ይጠብቃሉ፡፡ ‹‹ከባድ ጅማሬ ነው›› ይላሉ ሞዬስ፡፡ ሆኖም ዩናይትድን በራሳቸው መንገድ ለመምራት የተዘጋጁት ሞዬስ የፈርጉሰንን ቀጣይ እገዛ መፈለጋቸው እንደማይቀር ይመሰክራሉ፡፡ ‹‹በስራው አንድ ነገር አስጨንቆ ወደ ፈርጉሰን ሄዶ መጠየቅ የማይፈልግ ማን አለ? በስራው እርሱ ታላቅ አርአያ መሆኑን ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ ስለዚህ የእርሳቸውን አስተያየት የምጠይቅበት ጊዜ ይኖራል፡፡ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ እርሳቸው ቢሆኑ የማያደርጉትን ነገር አድርጎ ይሆናል፡፡ የዴቪድ ሞዬስን አሻራ በስራዬ ላይ ማሳረፍ መፈለጌ ለዚህ ነው፡፡ በጊዜው ቡድኑ የእኔ ሊሆን ይገባል፡፡

ከባለቤታቸው ጋር ለሸመታ በወጡበት ወቅት ከፈርጉሰን የስልክ ጥሪ ደረሳቸው፡፡ ኃላፊነቱንም የተቀበሉት በዚሁ ወቅት ነው፡፡ ከጀርባቸው አዲስ የሾሟቸው አምስት ሰዎች አሉ፡፡ ከምክትላቸው ስቲቭ በተጨማሪ የክለቡ ታሪካዊ ተጨዋቾች ፊል ኔቭል እና ሪያን ጊግስ ያግዟቸዋል፡፡ የቅድመ ውድድር ዘመኑ ልምምድ እየተጠናከረ ሲመጣ ሞዬስ የዩናይትድን ትኩሳት ይበልጥ ይገነዘቡታል፡፡ የዩናይትድ አሰልጣኝ መሆን ማለት ጨዋታዎችን ከማሸነፍም በላይ መሆኑን ይረዳሉ፡፡

‹‹እንደቀደሙት ቡድኖች እንደምንጫወት ተስፋ አለኝ፡፡ ተመሳሳይ ልማድ እና የማዝናናት ባህሪይ ያለው አስደሳች እግርኳስ መጫወት ይኖርብናል፡፡ ለእኔ በእግርኳስ ትልቁ ነገር ማሸነፍ ነው፡፡ እዚህም ትልቅ ስራ ማሸነፍ ነው፡፡ እኔ ሁልጊዜም ለአሸናፊነት ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ ሰር አሌክስም እንደዚያው ነበሩ፡፡ ሆኖም ሚዛናዊ መሆን ይኖርብኛል፡፡ ይህንን ማድረግ እንደምችል አስባለሁ፡፡ በማንቸስተር ዩናይትድ ሁልጊዜም ማሸነፍ አለብህ፡፡ አንዳንድ ጊዜ አይሳካልህም ይሆናል፡፡ ሆኖም ሁሉንም ዋንጫዎች ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ አለብህ››

የሞዬስ እና የዩናይትድ የሜዳ ላይ ፍልሚያ በኦገስት አጋማሽ በፕሪሚየር ሊግ ወደ ስዋንሲ ሲሄዱ ይጀመራል፡፡ ከዚያም በኦልድትራፎርድ ቼልሲ እና ወደ ሊቨርፑል ሄዶ ይጫወታሉ፡፡ ሞዬስ የማንቸስተር አሰልጣኝነታቸው እስካሁን በቅጡ ካልተሰማቸው ሴፕቴምበር ላይ ይታወቃቸዋል፡፡

 

1 Comment

Comments are closed.

speec
Previous Story

Health: ሰዎችን የሚያሳምን ንግግር እንዴት ማድረግ ይቻላል?

Next Story

ከፌደራል ፖሊስ ማስጠንቀቂያ በኋላ ሙስሊሞች በመላው ሃገሪቱ የጠሩትን ተቃውሞ ሰረዙ

Latest from Blog

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት

የኢካን ዓላማ በኔዘርላንድ የሚኖረውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ኮምዩኒቲይ የማሰባሰብ ሳይሆን የመከፋፋልና የማዳከም ተልኮን ያነገበ ነው።

አገር ! ለየአንድ ሠው ቋንቋው፣ ልማዱ፣ ባሕሉ፣ እምነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ወጉና በአጠቃላይ እሱነቱና ማንነቱ የሚከበርበት ብቸኛ ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያውያንም በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሁሉ እነኝህን በስደት ያጧቸውን የግልና የጋራ ማንነቶቻቸውን በአንድ ላይ ሆነው ለመዘከር

ፋኖ ምሽጉን ደረመሰው ድል ተሰማ | ” ስልጣን እለቃለሁ ” ፕረዚዳንቷ | ህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ | “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ

-966+9-የኦህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ – ስልኩ ተጠለፈ “እኛ የምን’ዘጋጀው ለፋኖ ሳይሆን ለኤር-ትራ ነው” አበባው|”በጊዜ ቦታ አዘጋጁልኝ” አረጋ

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ሰኔ 4፣ 2016 (ሰኔ 11፣ 2024)   በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት አብይና ዳንኤል ክብረት ጉድ አሰሙ-|ጀነራሉ በቁ*ጣ ተናገሩ-‘ህዝቡ ጉድ ሰራን’-|“ብልፅግናን ራ*ቁቱን አስቀርተነዋል”-|ታዳሚው ባለስልጣናቱን አፋጠጠ
Go toTop