ከዳንኤል ገዛክኝ አትላንታ
መቼም እንደ አሜሪካ ባለ ሃገር ከአንድ ሃገር ወደሌላ… በተለይም ከ ስቴት ስቴት ለመጉዋዝ ሲያስቡ እክሎች አይጠፉም እና ባጋጠመኝ መለስተኛ የመኪና አደጋ ሳቢያ ጉዞዬ ጥቂት በመስትጓጎሉ የተነሳ አንዳንድ ዝግጅቶች ላይ በወቅቱ እናበሰዓቱ ለመድረስ ሳልችል ቀርቻለሁ። የሆነው ሆኖ ከዝግጅቶች ሁሉ ቀልቤን ወደ ሚሰበው ወደ ኢሳት ዝግጅት ሜሪ ላንድ ደብል ትሪ ሆቴል ለመታደም ሞክሬያለሁ። ምንም እንኳን እንዳሰብኩት ሙሉውን ዝግጅት ባልታደምም ወደ መገባደጃው አካባቢ ደርሻለሁ። እናም እንደገባሁ ነበር የአትላንታውን የኢሳት ድጋፍ አስተባባሪ የማክብረውን አቶ ጌታቸውን አገኘሁት። ለጥቆም ከኢሳት ጋዜጠኛዎች ደረጀ ደስታን… ተወልደ በየነን… ብሩክ ይባስን እንዲሁም በርቀት የማውቃቸውን የአትላንታ አንድነት ፓርቲ አስተባባሪዎች እና አባላትን የአንገት ሰላምታ እያቀረብኩ ወደ አዳራሹ የመጭረሻ ጥግ ስደርስ አዳራሹ ከሚጠበቀው በላይ ሞልቶ አስተዋልኩኝ።
እንደምንም በሰዎች መሃል እየተጋፋሁ በደረስኩበትም ሰአት ቢሆን ከዝግጅቱ ለመታደም ስዘልቅ ከምንወደው እና ከሚወደን አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ጋር አይን ለአይን ተጋጨን። ታማኝ ለሰላምታ በዘረጋሁት እጄ አጠፌታ እየመለሰልኝ ቀድም በወቀሳ ወጋ አድደረገኝ። “አንድ ሁለት ጊዜ ጽፈህ በነገር ወጋግተኽኛል…” ሲል እሱም ወጋ አደረገኝ። እኔም እሱን ለመንካት እንዳልጻፍኩ እና የጽሁፌ አላማ ምን እንደነበረ ለማስረዳት መናገር ስጀምር ታማኝ ተመልሶ ወሌላ ቁም ነገር ሲገባ “ለነገሩ በርታ ጻፍ ብትጽፍ ነው የሚሻልህ…ግን በቃ እኔ እና አንተ የምንገናኘው ለኳስ ብቻ ነው ማለት ነው…” ሲል ሃሳቡን ሰነዘረ። ለነገሩ አዎ ታማኝ እውነት አለው በመጽሐፌ ዙሪያ ባለፈው አመት እንደዚሁ ለኢሳት ዝግጅት አድናቆቱን እና አክብሮቱን ብቻ ሳይሆን የገለጸልኝ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢሳት አድናቂ እና ቤተሰቦች በተገኙበት የክራውን ሆቴል ዝግጅት ላይ ከመድረክ ስለ እኔ አስቦ እና አስታውሶ ተነስቼ ህዝቡን እንድተዋወቅ ብሎም ስለ እኔ ቀንጨብ አድጎ በመናገር ታማኝ ልቤን እንደነካኝ እና እንዳስደሰተኝ መሸሸግ አልፈልግም። እናም ተገናኝተን ማውራት አለብን ብዙ ቁም ነገሮችን እናወጋለን ብሎኝ ነበር። ታማኝ እውነት አለው። በተለይ በ አትላንታ በነበሩት ሁለት ጉዞዎች በተለያዩ ያልተመቻቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሳ ታማኝን ሳላገኘው ቀርቻለሁ።
የታማኝ ንግግር ታዲያ በተለይ በጻፍኩት ጽሁፍ እንደነካሁት የጠቆመኝ ጉዳይ ግን ስህተት ነው። በእኔ በኩል ታማኝ የሚተች ጎን ቢኖረው እንኳን በዚያ ጽሁፍ ግን አክቲቪስት ታማኝ በየነን እና ጋዜጠኛ አበበ ገላውን የሚያወድስ ነጥብ ነበረ ያነሳሁት፤ ታማኝ ከምን አንግል እንደተመለከተው ባላውቅም። ዞሮ ዞሮ ግን ታማኝ ሊተች ቢችል እንኳን ጠንካራ ጎኑ ሚዛን እንደሚደፋ ስለማስብ ያንን አላደረግኩም። የታማኝን በርካታ ብዙ ተጠቅሰው የማያልቁ ጥንካሬዎቹ እንዳሉ አውቃለሁ፤ እነዚያን አልዘረዝርም። በኢትዮጲያዊነቱ ለአንድነት ባለው አቋም ጸንቶ መቆየቱ ለትግሉ የሚያዋጣው አስተዋጾ ብቻ ለታማኝ የታማኝነቱ ጎን ነው፤ ስለዚህ እኔ በምን ሂሳብ ታማኝን በነገር ልወጋው እችላለሁ ?
በደብል ትሪ የ ኢሳት ዝግጅት ከሚጠበቀው በላይ እንደነበረ በ እለቱ የተካሄዱት መርሃግብሮች የታዋቂ ሰዎች ንግግሮች ታዳሚውን ያረኩ እንደነበሩ ለማስተዋል ችያለሁ። ይህንኑ ሂደት የተለያዩ ሚዲያዎች ስለዳሰሱት መድገም አልፈልግም። ዞሮ ዞሮ…ያም ሆነ ይህ ኢሳት ዝግጅቱን በስኬት አከናውኗል። ወደፊት እንዲጓዝ አክቲቪስት እና አርቲስት አለም ጸሃይ ወዳጆ እንደዚሁም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የ ግንቦት 7 ፕ/ት እንደተናገሩት “ኢሳትን ወደ ተቁዋምነት ለመለወጥ የሁሉም ርብርቦሽ ያስፈልጋል…”፤ ትክክል ነው ኢሳት የማይናወጥ፣ በስራው ጸንቶ ኢትዮጲያውያንን በመረጃ አቅርቦት የሚያገለግል ተቁዋም መሆን አለበት። ሁሉም በ ኢሳት መገልገል ብቻም ሳይሆን ኢሳት አቅም እንዲኖረው በሚችለው ሁሉ ማገዝ እንዳለበት እኔም በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ።
ከኢሳት ዝግጅት በኋላ በዚያው እለት ማለትም ጁላይ 4 አመሻሹን ያመራሁት ወደቀድሞው የ ኢትዮጵያ የአየር ሃይል አባላት ያዘጋጁት ታላቅ ዝግጅት ላይ ነበር። በዚህ የ ኢትዮጲያ የቀድሞው የ አየር ሃይል አባላት ዝግጅት ላይም እንደዚሁ ለመታደም ገና ወደ በር ላይ አስተናባሪዎች አጠገብ ካለው ካውንተር ስደርስ የቀድሞው አየር ሃይል አባላት በብሉ ብላክ ሙሉ ሱፍ አሸብርቀዋል። ከአስተናባሪዎች ደማቅ ሰማያዊ ክራቫት እየተቀበሉ አንገታቸው ላይ እያሰሩ ከክራቫቱ ላይ በደረታቸው መሃል ለመሃል የአየር ሃይልን አርማ እየሰኩ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ተመለከትኩ። ከዚሁ ጋር ጎን ለጎን የአየር ሃይል አባላት ከአመታት በኋላ ሲገናኙ በፍቅር እየተጠራሩ በማዕረግ ስማቸው ጭምር እየተጠራሩ ሰላምታ ሲለዋወጡ በፍቅር ሲተቃቀፉ ፍቅራቸው የሚያስቀና እና የሚያስደስት ዓይነት ነበረ።
አሰብኩት እነዚህ ለአመታት ሃገራቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ በራሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች በስደት ሰው ሃገር ከከተሙም በኋላ አለመረሳሳታቸው፣ መሰባሰባቸው እና ያለፈውም ሃገራዊ ህይወታቸው ወደኋላ ሄደው በማስታወስ መገናኘታቸው የሚያስመካ እና ውስጥን በሃገር ፍቅር ስሜት የሚያላውስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ውጤቱ ታዲያ የፌዴሬሽኑ ተመስርቶ እዚህ መድረሱ ነው። በር ላይ የሚጠበቅብኝን አድርጌ እኔም ወደ አዳራሹ የሪሴፕሽን ስፍራ ሳመራ በአዳራሹ ፊት ለፊት ካለው መድረክ ላይ የተሰቀሉ ሁለት ፎቶዎች ተመለከትኩኝ። የቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ የነበሩት የሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ እና የሜጀር ጄኔራል አምሃ ደስታ ፎቶ ከነማዕረግ ልብሳቸው በጉልህ ስፍራ ተሰቅለዋል። ቅኝቴን አላቁዋረጥኩም። ከዋናው መድረክ ወረድ ብሎ ደግሞ ብሄራዊ ጀግናችን በተለይም ሃገራችን ኢትዮጲያ በጄኔራል መሃመድ ዚያድ ባሬ /አፍ-ወይኔ/ መሪነት ወቅት በ 1977 እ.ኤ.አ በተወረረችበት ጊዜ በተዋጊ ጄት አብራሪነት ለሃገሩ ዳር ድንበር መከበር ትልቅ ወታደራዊ ተጋድሎ በማድረግ በኋላም በሶማሊያ ጦር ተማርኮ ለ 11 ዓመታት በላንተቡር ወታደራዊ የምርኮኞች እስር ቤት የቆየው ፤ በሁዋላም በፕ/ት መንግስቱ ሃይለማርያም እና ዚያድ ባሬ መካከል በተደረገ ድርድር ተለቆ ለሃገሩ መሬት የበቃው ጄኔራል ለገሰ ፎቶ በደማቁ ተሰቅሎዋል።
የጄኔራል ለገሰን ፎቶ ስመለከት አንድ ግጥምጥሞሽ ትውስ አለኝ። ጄኔራሉ በጸይም ገጽታቸው በዚያ አኩሁዋን ጥቁር የዓይን መነጽራቸውን እንዳደረጉ ያንን ፎቶ የተነሱበት ስፍራ የነበርኩበት ጊዜ ታወሰኝ። 1981 ዓ.ም ከድሬ ዳዋ ከተማ በጥቂት ኪሎ ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ሁርሶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የወቅቱ የ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም እና ሚኒስትሮቻቸው ይህንን ብሄራዊ ጀግና እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደራዊ ምርኮኛዎችን በተቀበሉበት ወቅት ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ለጄኔራል ለገሰ አንገታቸው ላይ ካጠለቁላቸው የአበባ ጉንጉን እና ሰማያዊ የሃገሪቱ ከፍተኛ ሚኒስትሮች እና የፓርቲ አባላት የክብር ልብስ ጋር የፎቶ ካሜራ ባለሞያዎች ያነሱዋቸው ፎቶ። የጄኔራሉን ገጽታ ፎቶዋቸውን ሳይ እዚያ የታደምኩበትን ታሪክ በ እዝነ ልቦናዬ መልሼ ተመለከትኩት። በስፍራው የተገኘሁበት ሂደት ደግሞ ለሃገራቸው ዳርድንበር ከወራሪው የሶማሊያ ጦር ጋር ሲፋለሙ ከተማረኩት የሰራዊቱ አባላት መካከል የኔም ወላጅ አባት የአስር አለቃ ገዛኽኝ ወንድሙ /ሬገን/ አንዱ ነበረ እና ከ እናቴ ጋር የታደምኩበት ሂደት ነበረ። አስታውሳለሁ ጄኔራሉን በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁዋቸው በዚያ ወቅት ነበረ። ለጥቆም የቀድሞው መንግስት ለዘማች ልጆች ባመቻቸው ወደኩባ ሃቫና ሄዶ ትምህርት የመከታተል እድል አንዱ ተጠቃሚ እንድሆን እድሉ ከተመቻቸላቸው ወጣት ታዳጊዎች መሃል አንዱ ሆኜ ተመርጬ ጉዞው ሊከናወን ሲል በደገሃቡር አውራጃ ኢሰፓ ጽ/ቤት ውስጥ በርካታዎች ሆነን አንድ ፊልም እንድናይ ተጋብዘን ነበር። የ ኢትዮ-ሶማሊያን ጦርነት የሚያሳይ በኩባ የፊልም አንሺዎች የተቀረጸ በፕሮጄክተር በቀረበ ፊልም ውስጥ ጄኔራሉ ከረዳት አብራሪዎቻቸው ጋር ሆነው በቅጠልያ የአብራሪዎች ቱታ እና ጃኬት ልብስ ጥቁር መነጽራቸውን አድርገው ያየሁበት ሂደት ነበር። ይሄኛው የፎቶ ት ዕይንት እንግዲ ሶስተኛው መሆኑ ነበር። እናም በዚያ እሳቸውን ባየሁበት ገጽታ አለባበስ እና አኩሁዋን የተነሳውን ፎቶ ሳይ አይኖቼ በ እምባ ዘለላ ተሞላ ሰው እንዳላየኝ አረጋግጬ ምንተ-እፍረቴን እምባዬን ካሜራ በያዝኩበት እጄ እንደ ዘበት ጠረግ አደረግኩኝ እና አዳራሹን መቃኘቴን ቀጠልኩ።
አዳራሹ በቀድሞው የአየር ሃይል አርበኛ የጦር ባለ ማዕረግተኛዎች፤ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች ተሞልቶዋል። የግንቦት 7 ፕረዚዳንት የበክኔል ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ የኢሳት ከፍተኛ ማኔጅመንት የጥምረቱ መሪ አቶ ነአምን ዘለቀ፤ ልባሙ ደፋሩ እና የ እውነት ተሙዋጋቹ ጋዜጠኛ አበበ ገላው፤ እንዲሁም የ ኢሳት ጋዜጠኛዎች ሂደቱን በፊልም ለማስቀረት ከቦታ ቦታ ተፍ ተፍ ሲሉ አየሁዋቸው። ብራቮ ጋዜጠኛዎቻችን አልኩኝ። አክቲቪስት ታማኝ በየነ ከብዙዎቹ ሲቪል ታዳሚያን ለየት ባለ መልኩ የአየር ሃይል አርማን ደረቱ ላይ ከከረቫቱ ጋር ለጥፎ አምሮበት ሣየው ታማኝ ያስገርመኝ ከነበረው ይበልጥ አስገረመኝ። ለነገሩ ታማኝ ከዚህ የሰራዊት አባላት ጋር የራሱ የሆነ ቁርኝት አለው።
የቀድሞው የአየር ሃይል አባላት ዝግጅት የተሰናዳበት አዳራሽ ጢም ብሎ ሞልቶዋል። በዝግጅቱ መርሃ ግብር መሰረት በአክቲቪስት ታማኝ በየነ የተቀናበረው የኢትዮ-ሶማሊያን ጦርነት በተለይም የሰራዊቱን ብቃት የአየር ሃይል ሰራዊታችንን ተጋድሎ፤ አጠቃላይ ሂደትን ከመረጃ ጋር በሚያሳይ መልኩ የተዘጋጀው ጥናታዊ ፊልም ለ እይታ ቀረበ። የሚገርም ፊልም ነበረ። በነገራችን ላይ እነ ጄኔራል ለገሰን ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳን እና መሰል የሰራዊቱ አባላትን ባከበረው በ አሜሪካን ሃገር በተዘጋጀ አንድ የ አክብሮት ስነ-ስርዓት ላይ ታማኝ በየነ የራሱ ትልቅ ሚና እንደነበረው ለማስታወስ እወዳለሁ።
ዝግጅቱ በድምቀት ቀጥሎ በስደት የሚገኙ የቀድሞ የኢትዮጲያ አየር ሃይል አባላት ፕረዚዳንት ፍላይት ኢንጂነር ብርሃኑ በአጠቃላይ የማህበሩ የሃያ አመታት ጉዞ በተለይም ደግሞ አሁን ባለው የሃገራችን ገዢ ሃይል ጫና ሃገር ለመልቀቅ ተገደው በሁለተኛ ሃገር በስደት በከተሙበት ጊዜ ከማህበሩ ስለተደረገላቸው ድጋፍ፤ ወደ ሶስተኛ ሃገር እንዲሰፍሩ እና የተሻለ የደህነነት ጥበቃ እንዲያገኙ ስለተሰራው ስራ እና እንቅስቃሴ ፕረዚዳንቱ በመረጃ የተደገፈ ንግግር አድርገዋል።
ታዲያ በሊቀመንበሩ ንግግር ውስጥ ሁለት ነገሮች ከ እኔ እና ከሙያ ባልደረባዎቼ ጋር ያለውን ቁርኝት አስታወስኩኝ። ወደ ቤላሩስ ለትምህርት የተላኩ 8 የኢሃዴግ ዘመን የ እየር ሃይል አባላት ጊዜው የምርጫ 97/2005 ወቅት ነበረ እና አብራሪዎቹ ስርአቱን ተቃውመው ጥገኝነት ሲጠይቁ የሞራል ኪሳራ የደረሰበት የ ኢህአዴግ መንግስት እነዚህን ብርቅዬ ኢትዮጲያውያን ወደ ሃገር ቤት አስሮ ለመመለስ በርካታ ገንዘብ መድቦ ሲንቀሳቀስ የነበረበትን ሂደት እኔ እሰራባት የነበረችው ሞገድ ጋዜጣ በማጋለጥዋ የተነሳ ተከስሼ እስር ቤት የገባሁበትን ሂደት የሚያስታውስ ሁኔታ ነበረ በ እለቱ ንግግር ሲደረግ ያስታወስኩት።
ሁለተኛው ሁኔታ እና ትውስታዬ በዚያው የምርጫ 97 ወቅት ሁለቱ የበረራ ባለሞያዎች አብዮት ማንጉዳይ እና ባልደረባው ለስራ ይዘዋት የወጡትን ሂሊኮፕተር ይዘው ጅቡቲ በማረፍ የፖለቲካ ጥገኝነት ሲጠይቁ የጅቡቲ መንግስት ሁለቱንም አሳልፎ የሰጠበትን ሁኔታ ከጅምሩ ማህበሩ የታገለውን ትግል ሊቀመንበሩ አስታወሱ። እኔም አስታወስኩ ሁሉም የነጻው ፕሬስ አባላት ጉዳዩን አስመልክተው ከሂደቱ ጅማሮ አንስቶ ይዘግቡ የነበረውን ታሪክ አስታወስኩ እና ግጥምጥሞሹ አስደነቀኝ።
በመለጠቅ ቢኬ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የ አየር ሃይሉ አባል ኮሎኔል ብርሃኑ ከበደ ሰፊ እና መሳጭ በተለይም ደግሞ ከ አየር ሃይል አባላት ጋር ቁርንት ያላቸውን በስደት ሃገር ተጋድሎ የፈጸሙ የሚመሰገኑ ግለሰቦችን ስም በመትራት ታላቅ እስውና የሰጠ ሰፊ ንግግር አደረጉ። በመሃል ታዳሚውን ያረካ የሪሴፕሽን ግብዣ ተከናወነ። በነገራችን ላይ እኔም ሆንኩኝ ሌሎችም ጋዜጠኛ ባልደረቦቻችን የተገኘነው በኮክቴል ጋዜጠኝነት ደንብ ሳይሆን ይህንን ማንም ኢትዮጲያዊ ሊያወደሰው እና ሊያሞግሰው የሚገባን ተግባር ልመታደም እና በሞያችን በምንችለው መልኩ ለህዝብ ለማድረስ መሆኑ ልብ እንዲባል እፈልጋለሁ።
ከዚህ በሁዋላ ነበረ የ አየር ሃይል አባላቱ ካሰናዱት ዝግጅት መካከል በሙዚቀኛዎች መሪነት ለታዳሚው ባንዲራ ታድሎ ሙሉው አዳራሽ በ አረንጉዋዴ ቢጫ ቀዩ ባንዲራችን አሸብርቆ…
ኢትዮጲያ ሃገሬ መከታ ጋሻዬ
ለ እኔ መመኪያ ነሽ የህይወቴ መኩሪያዬ
የሚለው የማያረጅ ዘለ አለማዊ ዜማ በአንድነት ባንዲራ እየተውለበለበ የተዜመው። ሁሉም በፍቅር መስ ዋ ዕትነት ስሜት በጋራ ተደሰተ በጋራ ዘመረ በጋራ ተወዛወዘ። ግን ከዚህ በሁዋላ ነበረ በስፍራው የተገኙት የነጻነት ትግሉን ወደፊት እየገፉ ያሉት ተቃዋሚዎች ይህንን ሃይል እንዴት ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆን? ብዬ ለራሴ ጥያቄ ያቀረብኩት።
በማግስቱ በሜሪላንድ በርድ ስታድየም የሚከናወነው የኢትዮጲያ ባህል እና ስፖርት ፌዴሬሽን ከሚወደስባቸው እና ከሚመሰገንባቸው አመታዊ የ እንድ ሳምንት ዝግጅቶች ውስጥ ትልቁ እና ኢትዮጲያውያንን በጋራ የሚያገናኘው የኢትዮጲያውያን ቀን ዝግጅት ነበር። ጁላይ 5 ስታድየሙ ገና ከቀትር በሁዋላ በጊዜ ነበረ መሙላት የጀመረው። እንዳውም ጸሃይ ዝቅ ማለት ስትጀምር ስታድየሙ ሞልቶዋል ተብሎ ህዝብ መመለስ ጀመረ። እዚህ ጋ ግን ስለፌዴሬሽኑ የምለውን ልበል።
በመጀመሪያ ይሄ ላለፉት 30 ዓመታት ከነችግሮቹ በመሪ መርሁ መሰረት ኢትዮጲያውያንን አንድ ቦታ በማገናኘት ሲሰራ የቆየው የ ኢትዮጲያ ስፖርት እና ባህል ፌዴሬሽን የሚወደድበት እና የሚወደስበት ተግባሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጲያውያንን በ አመት አንድ ጊዜ ማሰባሰቡ ብቻም ሳይሆን ሁሉም እንደየ አመለካከቱ እና ፍላጎቱ ድርጅቱን ተቁዋሙን ወዘተርፈ ጉዳዩን የሚያስተዋውቅበት ሂደትን እየመራ መቆየቱ አስመስጋኝ እና ጠንካራ ጎኑ ነው። ፌዴሬሽኑ በየአመቱ የተለያዩ ድክመቶች አሉት። በዘንድሮው ግን በተለይም እኔ ከታደምኩባቸው ሶስት አመታቶች የ ሜሪላንድ 2013 ዝግጅቱ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነበር።
ድንኩዋን ተከራይተው የራሳቸውን ቢዝነስ እና ስራ ከሚሰሩ ነጋዴዎች ሮሮ ስነሳ ጥቂት ነጋዴዎች ድንኩዋን ለማግኘት ተመዝግበው እና አስፈላጊውን ፎርማሊቲ አሙዋልተው ድንኩዋን ሳያገኙ የቀሩበት መጉላላት እና ኪሳራ ውስጥ የገቡበት ሂደት ይጠቀሳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የ ኤሌክትሪክ ሃይል የመቆራረጥ ሮሮ ያሰሙም ነጋዴዎችን ሮሮ ሰምቻለሁ። በመግቢያ አሰራር መሰረት አንድ የቆየ አሰራር ነበረ። ይኽውም ሲኒየር የሚባሉ በተለይም ከ 60 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ዝግጅቱን ለመታደም የሚመጡ ኢትዮጲያውያን ነጻ እንዲገቡ እንደሚደረግ ነገር ግን የኮሚቴ አባላቶች የሚፈልጉዋቸውን በተለይም እነሱ ኮሜቴዎቹ ከመጡባቸው ቦታዎች የመጡ ሰዎችን በጥቅሻ መርጠው ሲያስገቡ እና ሌሎችን ሲከለክሉ ተመልክቻለሁ። ከተከለከሉት ውስጥም አንዳንዶችን ለመረጃ አነጋግሬያለሁ።
ለጋዜጠኛዎች/የሚዲያ ሰዎች/ እንዲሁም ለነጋዴዎች የሚሰጠውን የመግቢያ ማለፊያ መታወቂያ የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዴስክ ስራ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ቡድኑ ስራውን በአግባብ ከመስራት ይልቅ ተግባሩን የሚቃረኑ ሁኔታዎችን ታዝቤያለሁ። ምንም እንኩዋን ጥቂቶች ኮሚቴዎቹ ባረፉበት ዲሲ ሸራተን ድረስ በመሄድ መታወቂያ ቢያገኙም እኔ እና መሰል የሞያ ባልደረባዎቼ ፌዴሬሽኑ በሚያመቻቸው የይለፍ የሚዲያ መታወቂያ እድል መጠቀም ሳንችል ቀርተን በየዝግጅቶቹ ሁሉ እየከፈልን ለመግባት ተገደናል። በተለመደ አሰራር መሰረት የሚዲያ ሰዎች በተለይ የኢትዮጲያ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኛዎች በተወካያችን በጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ አማካኝነት ፎቶዋችንን ለፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ብንልክም መታወቂያችንን ለማግኘት በስታድየሙ ተገኝተን ብንጠይቅም እንዳልተሰራ መናገር ብቻም ሳይሆን የኮሚቴ አባላቶች ሲያመናጭቁን እና ሲያንጉዋጥጡን ተመልክቻለሁ።
እጠቅሳለሁ የ ኢትዮጲያውያን ቀን ሲከበር የቢዝነስ ማናጀሩን አቶ መላኩን አነጋግሬው ነበር የመለሰልኝ መልስ ቢዚ መሆናቸውን ነው። ይልቅም በዘየድነው መንገድ ሁላችንም መግቢያ ያላገኘን ጋዜጠኛዎች ስማችንን በዝርዝር በመጻፍ ለኮሚቴዎች በመስጠት በር ላይ ማለፍ እንድንችል ብንሞክርም አልሆነም። ስም ዝርዝራችንን ግን ለኮሚቴዎቹ ብንሰጥም በዚያ መንገድ መጠቀም እንድንችል ማድረግ አልቻሉም።
በመዝጊያው ቀንም እንደዚሁ የሚተባበሩን ከሆነ ከኮሚቴ አባላት መካከል በሃገራችን የ እግር ኩዋስ ታሪክ ውስጥ አሻራውን ማሳረፍ የቻለው የምናከብረው አቶ ፍሰሃ ወልደ አማኑኤልን እና አቶ አብይ ኑርልኝን ትብብራቸውን በግሌ ብጠይቃቸውም አቶ ፍሰሃ ቃል በቃል “የምን ሚዲያ ነው ሚዲያ ምናምን የለም… ለመለፍለፍ ነው በቃ መለፍለፍ ብቻ ነው… አሁን ቢዚ ነን ጊዜ የለንም” በማለት አዋርዶኛል አንጉዋጦኛል። በተመሳሳይ አቶ አብይንም ሁኔታውን ባስረዳውም… “አዝናለሁ ምንም ላደርግ አልችልም” ሲለኝ ሁኔታውን በዝርዝር በማስረዳት ችግሩ የነሱ መሆኑን ብነግረውም ከግልምጫ በስተቀር መልስ እንኩዋን ሊመልስልኝ አልቻለም። እኔም እንዲያው ለአሰራሩ ያህል እንጂ ሃያ ብር ከፍሎ መግባት ከባድ ሆኖ አልነበረም ነገር ግን ዋናው ስነ-ስርአት የሚካሄድበት ቦታ ለማለፍ ፊልም እና ፎቶ ለማንሳት አስቸጋሪ ስለሚሆንብኝ ነው ትብብር መጠየቄ። ምክንያቱም ከፌዴሬሽኑ ውጪ የሆኑ የቦታው አስተናባሪ ሰራተኛዎች ያለ መታወቂያ ስለማያሳልፉኝ ነበር ግን አልሆነም።
የፌዴሬሽኑ አንዳንድ የኮሚቴ አባላት ስራቸውን ከመስራት ይልቅ በመጠጥ ሰክረው በአሳፋሪ ሁኔታ በየ ድንኩዋኑ ሲንጎማለሉ ለመመልከት ችያለሁ። ይሄ ብቻም አይደለም በመግቢያ ሰአት ታዳሚያን በወቅቱ ቲኬት የሚሸጥላቸው አጥተው በረጅም ሰልፎች ሲጉላሉ ተመልክቻለሁ። በተመሳሳይ ፌዴሬሽኑ ባዘጋጃቸው የሜዳ ውስጥ እና የመዝጊያ የተለየ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የመግቢያ ሰዓት ካለ ማክበር አንስቶ በመግቢያ በሮች ላይ የተቀላጠፈ አሰራር ያለመኖር ይልቅም የፌዴሬሽኑ አመራራ ሚስቶቻቸውን ዘመድ አዝማዶቻቸውን የበር አስተናባሪ አድርገው የማስተናበር ልምድ አንሶዋቸው ግራ ሲጋቡ ታዜቤያለሁ የምጸፈው በመረጃ ነው የፕረዚዳንቱን ሚስት አይቻለሁ አነጋግሬያታለሁም። በነዚህ ሂደቶች ውስጥ በሃላፊነት ስራቸውን ሲወጡ ያስተዋልኩት ጋዜጠኛዎችን ብቻ ነው። ፌዴሬሽኑ መግቢያ ከልክሎዋቸው እንኩዋን ከፍለው እየገቡ ፊልም አንሺዎች ፎቶ ካሜራ ማኖች ለሬድዮ፤ ለድረ ገጽ እንዲሁም ለተለያዩ ሚዲያዎች የሰሩዋቸውን ስራዎች ከሜዳ አንስቶ እስካረፉበት ሆቴል ድረስ ያለ እረፍት ሁኔታውን ሲዘግቡ እና ሲያሳውቁ ነው የሰነበቱት። ነጋዴዎች ያለ ተቆጣጣሪ አንድ ምግብ ከ 13 ዶላር እስከ 20 ዶላር ሲሸጡ፤ የሚጠጣ ነገር እስከ 8 ዶላር ሲቸበችቡ ያለ አግባብ ሊከብሩ ሲሩዋሩዋጡ ታይተዋል። የፌዴሬሽኑ አመራሮች እንደተጠቀሰው፤ አርቲስቶች መድረክ ላይ ከወጡ በሁዋላ “የተጋበዝኩት እዚህ አልመሰለኝም…”በማለት እየተዝናና ባለው ህዝብ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሲደፉ አስተውለናል። እናም ቪቫ ጋዜጠኛዎች ብያለሁ።
ከዚህ ባሻገር በመዝጊያው ፕሮግራም ላይ የተቀናጀ እና ገንዘብ ከፍሎ የገባውን ታዳሚ ህዝብ ያላከበረ ደርዙ የጠፋ አጀማመር ታይቶዋል። በዚህ የዘንድሮው ዝግጅት ትዝብቴ ውስጥ ታዲያ የተለያዩ ድምጻዊያን ስራቸውን ያቀረቡ ሲሆን እንደ ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ብርሃኑ ተዘራ የህዝቡን ሃገራዊ ስሜት በመያዝ እና በማስደሰት አስመስጋኝ ስራ መስራታቸውን ሳልገልጽ አላልፍም።
በመጨረሻም በዘንድሮ የሜሪላንዱ ዝግጅት አስደሳችም ማራኪም ግን ደግሞ ስሜት የሚነኩ ህዝቡ እንዳማረረው የአንድ ሃይማኖት ሰዎችን አግዝፎ የማቅረብ እና መድረክ የመስጠት አዝማሚያ ተመልክቻለሁ። ይህ አግባብ እንዳልሆነ ልጠቁም እወዳለሁ። በተረፈ እንደበርካታዎቹ እምነት እና አስተያየት “ይህ ፌዴሬሽን በጽናት የቆየ እንደስያሜው ኢትይጲያውያንን በማሰባሰብ እዚህ ደርሶዋል አሁንም ዘላለማዊ እድሜ ለፌዴሬሽናችን እንመኛለን። ነገር ግን የፌዴሬሽኑ የአመራር አባላት ግን ስራቸውን ህዝቡን ከማገልገል አኩዋያ መስራት የማይችሉ ብቃት የሌላቸው በመሆናቸው ተርማቸውም ባይደርስ ሊቀየሩ ይገባቸዋል” ሲሉ አአስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በተረፈ በተለይ በተለይ በዋሽንግተን ዩ ስትሬት እና መሰል ስፍራዎች የታዘብኩዋቸውን ልቤን የሰበሩትን አሳዛኝ ታሪኮች በቀጣይ አሜሪካንን ጠላሁዋት + አሜሪካንን ወደድኩዋት በሚለው ቀጣይ ርዕስ እመለስበታለሁ፤ ሰላም።