Sport: ጃክ ዊልሸር አርሰናል ሩኒን ካስፈረመ ለዋንጫ ተፎካካሪ ይሆናል አለ

ከይርጋ አበበ

እንግሊዛዊው የሃያ አንድ ዓመት የመሐል ሜዳ አንቀሳቃሽ ጃክ ዊልሸር ክለቡ ዋይኒ ሩኒን ማስፈረም ከቻለ ለዋንጫ ተፎካካሪ እንደሚሆን ገለጸ። ወጣቱ አማካይ ሰሞኑን ከዕለታዊው ዘሰን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ «ሩኒ መምጣት ከቻለ በጣም አስገራሚ ይሆናል» ብሏል። ሃሳቡን ሲቀጥልም « ሩኒ ማለትኮ ውጤት ሲያስፈልግህ በቡድንህ ውስጥ እንዲኖር የምትፈልገው ዓይነት ተጫዋች ነው። እርሱን በቡድንህ ውስጥ ማሰለፍ ደግሞ ለተጋጣሚዎችህ ሽብርን መፍጠር ማለት ነው። ይህን ማድረግ እንደምንችል ደግሞ ተስፋ አደርጋለሁ» ብሏል።
ፈረንሳዊው የአርሴናል አሠልጣኝ አርሴን ቬንገር በቀጣዩ የውድድር ዓመት የስምንት ዓመት ውጤት አልባ ጉዞ ለማቆም እንደወሰኑ የሚነገርላቸው ሲሆን፤ ለእዚህም ይረዱኛል ያሏቸውን ተጫዋቾች ወደ ክለባቸው ለማዘዋወር የተጫዋቾቹን ቀጣሪዎች ይሁንታ ለማግኘት ደጅ መጥናት ጀምረዋል።
ከእነዚህም መካከል የማንቸስተር ዩናይትዱ አጥቂ እንግሊዛዊው ዋይኒ ሩኒ፣ የሪያል ማድሪዱ አርጄንቲናዊ አጥቂ ጎንዛሎ ሂጉየን፣ የኤቨርተኑ አይደክሜ አማካይ ማሩዋን ፌይላኒ፣ ብራዚላዊው የኪውፒአር ግብ ጠባቂ ሁሊዮ ሴዛር፣ የስዋንሲ ሲቲው ተከላካይ አሽሊ ዊሊያምስና የፍዮሬንቲናው ሞንቴኔግሯዊ አጥቂ ስቴፈን ዩቮቲች ተጠቃሾች ናቸው።
ዊልሸርም የአሠልጣኙን የግዥ ዝርዝር ከተመለከተ በኋላ አስተያየቱን ሲሰጥ «እንደ ሂጉየን እና ዋይኒ ሩኒ ዓይነት ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች ወደ ክለባችን ለማምጣት ስንሞክር ታያላችሁ። የቡድናችን ስብስብ እንደ ማንቸስተር ሲቲና ዩናይትድ ሁሉ ማስፋት ይኖርብናል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ18 ተጫዋቾች የሻምፒዮንነት ዘውድን ሊደፋ አይችልም።
ሻምፒዮን መሆን እንደምንፈልግ ምንም ምሥጢር የለውም። ላለፉት ስምንትና ሰባት ዓመታት ዋንጫ አለማግኘታችን ከፍተኛ ውጥረት ላይ እንድንወድቅ አድርጎናል። ከሁለት ዓመታት በፊት ለካርሊንግ ካፕ ዋንጫ ፍፃሜ ቀርበን ዋንጫውን ማጣታችን ጫና ላይ እንደጣለን ግልጽ ነው። «አንዴ ማሸነፍ ከቻልን አከታትለን የድሉ ባለቤት እንሆናለን ብዬ አስባለሁ» በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
ልቡ ከማንቸስተር ዩናይትድ ካምፕ የሸፈተውን ዋይኒ ሩኒን ለማግኘት በርካታ ክለቦች ፍላጎታቸውን ማሳደራቸው ለአርሴን ቬንገር ከባድ ፈተና እንደሚሆን ቢገለጽም አሠልጣኙ ግን ስለ ገንዘብ አታስቡ እያሉ ነው። ለእዚህም ሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብና ከሁለት መቶ ሺህ ፓውንድ ያላነሰ ሳምንታዊ ደመወዝ ሊከፍሉት እንደሚፈልጉ ለክለባቸው ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
ሮቢን ቫንፐርሲ ከአንድ ዓመት በፊት ከአርሴናል ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ እንደተዘዋወረው ሩኒ ከማንቸስተር ወደ አርሴናል ሊዘዋወር ይችላል ብሎ ማሰብ ከባድ እንደሆነ እየተነገረ ባለበት ሰዓት አርሰን ቬንገርና ጃክ ዊልሸር የልጁን ልብ ለማሸፈት ቆርጠው ተነስተዋል ሲል ዘ ሰን ጨምሮ ገልጿል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትምህርት ሚኒስትሩ እና ፓርላማ - የፋኖወች መልእክት - የአብኑ ደሞዝ ካሴ መልእክት - ኦነግ ሸኔ ያፈናቸውን 80 ሰወች የሚያስለቅቅልን መንግስት አጣን
Share