ከበልዩ
የአቶ አብርሃም ደስታን ፅሁፍ ስመለከት ጆርጅ ቡሽ ልክ በ2008 ከስልጣን ሲለቁ ስለእሣቸው ሕብረተሰቡ ይገነዘብ ዘንድ አንድ ፊልም ተሰራ፡፡ይህንን ፊልም የሰራው ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ኦሊቨር ስቶን ነበር፡፡የፊልሙ ርእስ “W ” ይባላል፡፡ በዚህ ፊልም ላይ የጆርጅ ቡሽን እድገትና ወደ ስልጣን አመጣጥ የተመለከተ ሁሉ ይህ ሰው ይሄ ነው እንዴ ብሎ በቃ በእሣቸው ላይ ቂም ከመያዝ ይልቅ መተው ነው ብሎ አለፋቸው፡፡ ይህንን በመግቢያነት ለመጠቀም የፈለኩት አቶ አብርሃም ደስታ በተደጋጋሚ በፖለቲካዊ ትንታኔ ዙሪያ የሚያወጧቸውን ፅሁፎች አነባለሁ፡፡ ጥሩ አድናቂያቸውም ነኝ፡፡ ግን ምን ታዘብክ ብትሉኝ የፖለቲካ ተንታኝ ከዛ ወጥቶ ሌላ ትንታኔ ላይ ሲገባ ምናልባትም በእሱ ውስጥ ያለው አስተሳሰቡ የሚታይበትና የሚጋለጥበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡
እንደሚታወቀው ባለፈው ሰሞን “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ላይ ኢትዮጵያን ወክላ ወደዛ የተጓዘችው ቤትልሄም ተሾመ የፈፀመችው ወሲብ ለፕሮግራሙ ትልቅ ስም ሲያሰጥ ለእሷና በተለይም ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ ውርደትንና እፍረትን አከናንቧል፡፡ አቶ አብርሃም የዚህ የእሷን የተዋረደ ተግባር ያዩበት አንግል በአንድ አቅጣጫ ነው ብሎ ለመናገር የሚከብድ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያዊያን ባህል የራሣችን አስተሳሰብ፣ የራሣችን የሆነ ልማድ እንዳለም የዘነጉ ይመስለኛል፡፡ በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያዊያን በሩጫው በሚያመጡት ውጤት ባንዲራችን ከፋ ብሎ እንዲውለበለብ አድርገው ያጨበጨብንላቸው አትሌቶች ታሪክ እያለ ኢትዮጵያዊቷ በዚህ ውድድር ላይ ወሲብ ፈፀመች የሚል ስም ሲበረዝበት ምን ያህል እንደሚያሣፍርና እንደሚያሸማቅቅ የተረዱት አልመሰለኝም፡፡
አቶ አብርሃም ሁሉንም ነገር ከወሲብ ጋር የተያያዘ አድርጐታል፡፡ ከወሲብ ጋር መያያዙ አይደለም ከኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ይህቺ ሴት በዚህ ውድድር ላይ ስትካፈል እኮ ወሲብ ለመፈፀም አይደለም የገባችው፡፡ በምትቆይበት ጊዜያት ውስጥ በተመልካች ትኩረት የሚሰጥ ወይም የሚመስጥ ነገር ማድረግ ነው፡፡ አላማው የወሲብ ከሆነማ ለምን ቤቲ ወሲብ ፈፀመች ብለን እንቃወማለን፡፡ እሷ ግን ከዚህ አላማ በመውጣት ሌላ መንገድ ውስጥ ገብታለች፡፡ ይህ ማለት ለስሜቷ የተገዛች ሆናለች ማለት ነው፡፡ ትልቁ ነገር እራስን መቆጣጠር ነው፡፡ራሷን መቆጣጠር የማትችል ለስሜቷ የምትገዛ ከሆነች በዚህ ውድድር ላይ መሣተፍ ፈፅሞ የለበትም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አቶ አብርሃም በዚህ ዙሪያ ለምሣሌነት የተጠቀሟቸው ነጥቦች ደግሞ ይበልጥ ያሣቀኝና ያስገረሙኝ ናቸው፡፡ ለምሣሌ “ሀሺሽን ጠልተን የቦምባርሌን ፎቶ የሰቀልነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ለመሆኑ ቦብማርሌ በድምፃዊነቱ ነው የሚታወቀው ወይስ በሃሺሽ አጫሽነቱ ለመሆኑ ቦብማርሌ ድምፃዊ ብቻ ሣይሆን የነፃነት ታጋይም ነው፡፡አፍሪካ በቀኝ ግዛት ስር በነበረችበት ወቅትና ከዛም በኋላም የፈፀመው ነገር ትልቅ ቦታና ታሪክ ያለው ነው፡፡ ምናልባትም የአለማችን ታላቁ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን ሄደው ስለቦብማርሌ ቢጠይቁ የሚሰጠዎት ምላሽ በተመስጥኦ የታጀበና ለእሱ ያላቸውን ክብር የሚያመለክት ነው፡፡ እናም የቤቴልሄምን ተግባር ፈፅሞ ሊገናኝ በማይችል መልኩ ከቦብማርሌ ጋር ማገናኘቱ ምናልባትም ከላይ በመግቢያዬ ላይ ስለጆርጅ ቡሽ ማንነት ወይም ስብእና ለማወቅ ፊልም እንዲሰራ እንደተደረገ ሁሉ የአቶ አብርሃም ደስታን አስተሳሰብ ለመረዳት ደግሞ የቤተልሄም ጉዳይ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡
በርግጥ አንድ ችግር አለ ሁሉም ሰው የሆነ ተከታይና ደጋፊ ማፍራት ይፈልጋል፡፡ አቶ አብርሃምም እንደፖለቲከኛነቱ የሆነ የዘመናዊው ፖለቲከኛ ወይም “ዴሞክራትነታቸውን” ለማሣየት የፈለጉና ቤቲ መብቷ ነው በራሷ ምናምን እያሉ ዘመናዊ ነን የሚሉ ወገኖችን መንገድ በመከተል ስምና ዝናን ለማግኘት የፈለጉ ይመስላል፡፡ ይህ ግን የዘመናዊነት ምልክት አይደለም፡፡ ወይም በመብት ላይ ለማሣወቅ መጣርም አይደለም፡፡ ካላወቅንና ነገሩ ካልገባን ዝም ማለት ይቻላል፡፡ የፕሮሞሽን ስራ ይመስል በሁሉም ነገር ላይ ጥልቅ ካሉ ኋላ ላይ እንደቡሽ ጭንቅላት ይመረመርና ከዚህ ቀደም ይታወቁበት በነበረው ነገር ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ይህቺ ልጅ የፈፀመችው ነገር ስህተት ነው፡፡ ምናልባት አቶ አብርሃም እንደበሰለ ፖለቲከኛ ሲሆኑ የሆነው ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ግን ሆኗል መታረም ይገባዋል በማለት ቢገልፁት ምንኛ ባማረ ነበር፡፡
ግን ከዚህ በመውጣት እርስ በእርሱ የሚጣረዝና ጠለቅ ብሎ የፕሮግራሙ ወይም የውድድሩ ሂደትን በደንብ ሣይረዱ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ካልሰጡ ችግር ይገጥማል የተባሉ ይመስል ዝም ብሎ ዘባርቆ መፃፍ ግን ዝናን ናፋቂና ዘመናዊ ነኝ ባይ ከማስባል ያለፈ አይሆንም፡፡ አቶ አብርሃም ኢትዮጵያዊያን እኮ የራሣችን ባህል አለን ያልኩት በሀገራችን ወንድ ልጅ ወንድን ቢያቅፍ ችግር የለውም፡፡ አሜሪካ ግን ይሄን ቢያደርግ ሌላ ስያሜ ያሰጠዋል፡፡ በሀገራችን ሚስቱን እንኳን በአደባባይ ከንፈር ላይ የሚስም የለም ይህ የኛ ባህል አይለምና፡፡ በሌላ ሀገር ግን ይደረጋል፡፡ ቤተልሄምም ቢሆን ከዚህ አይነቱ ሕብረተሰብ ነው የወጣችው ይህን ስሜትም ይዛ ነው የኖረችው፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ የሄደ ሰው ደግሞ እዛ ላይ ኢትዮጵያዊ ሲያየው ምን አይነት ስሜት ሊፈጥርበት እንደሚችል መረዳት ይኖርብናል፡፡ እሷ እኮ መምህር ናት፡፡ ለተማሪዎቿ አርአያ የምትሆን፡፡ ከዚህ በኋላምን አይነት መምህር መሆን ትችላለች፡፡ አቶ አብርሃም ይህን ሁሉ ነገር ማሰብ ከማውራት በፊት ግራና ቀኝ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ወጣት ስለሆኑና ወጣት ስላጠፋ ማስተባበል የዘመናዊነት ምልክት አይደለም፡፡ እናም በቤቲ ጉዳይ በግልዎ ፅፈው ቢያነቡት ወይም ቢያልፉት በተሻለ ነበር፡፡ እናም አቶ አብርሃም በቤተልሄም ጉዳይ ዴሞክራት ለመባል ያሰቡት ነገር ፈፅሞ አልተሣካም፡