(ብርሃን ከበደ (በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ መምህር የነበረ))
ግልጽ የኾነ ሎጂክ አለ፤ የኢትዮጵያ ሠራዊቱ ተብሎ ለሚጠራ አባል ሁሉ የሚተረክ፡፡ “ኢሕአዴግ የሕገ መንግሥቱ ጠባቂ ነው፡፡ ኢሕአዴግን መጠበቅ ደግሞ ሕገ መንግስቱን መጠበቅ ነው፡፡ ስለዚህም ሠራዊቱ ግንባሩን መጠበቅ ትልቁ ኃላፊነቱ ነው፡፡” ይህ ከአገር ጥቅም በላይ የገዢ ግንባሩን የሥልጣን ጥማት ለማርካት የሚነገር የሠራዊቱ መመርያ ከሁሉ የአገሪቱ ሕጎች በላቀ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ እያንዳንዱ አባልም የስሙን ያህል ያውቀዋል፡፡ ዘወትር እንዲያነበንበውም ይጠበቃል፡፡ እኔም በ1994 ዓ.ም የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅን በተማሪነት ከመቀላቀሌ መመሪያውን መተዳደርያዬ እንዳደርግ ከወታደራዊ ሳይንስ ስልጠናዎች ይልቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በሚሰብኩ ስብሰባዎች ተነገረኝ፡፡ ያንጊዜ ከልቤ ላገለግለው በፍቃደኝነት የተቀላቀልኩት ሠራዊት ዘለቂ በኾኑ ብሔራዊ ጥቅሞች አንጻር ተንሸራንቶ መገኘቱ ውሳኔዬ የተሳሳተ መኾኑን ለመገንዘብ ያስቻለኝ ነበር፡፡
ዛሬ በስደት በምኖርበት ባህር ማዶ ያሉ ወገኖችም ኾኑ የ20 ዓመታቱ የአቶ መለስ አገዛዝ ያንገፈገፋቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ስለመንግስት ለውጥ በስፋት የሚነጋገሩበት ነው፡፡ የነጻነት እጦቱ፣ መራብና መጠማቱ እንዲሁም ያለ አግባብ በእስር መንገላታቱ በቂ ምክንያቶች ቢኾኑም፤ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የተገኙት ሕዝባዊ ድሎች ለዛሬው የዜጎች መነቃቃት ግብዓት ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት ለሚችለው የኢትዮጰያ የሕዝብ የአደባባይ ተቃውሞ የሠራዊቱ ሚና ምን ይኾናል የሚለው ዋነኛ መነጋገርያ መኾኑ አልቀረም፡፡
በግብጽ እንዲሁም ሕዝባዊ ተቃውሞ ውጤት ባስመዘገበባቸው ሌሎች አገራት የታዩ የሠራዊቱ የገለልተኝነት ሚና ዛሬ የኢትዮጰያ ሠራዊት ከሚገኝበት ወታደራዊ ስነ ሥርዓት እና መዋቅር አንጻር መመልከቱ ተገቢ እንደሚኾን በማሰብ በሠራዊቱ ውስጥ በተማሪነት እንዲሁም በመምህርነት በቆየሁባቸው ሰባት ዓመታት ውስጥ ያገኘኋቸውን እውነታዎች መሰረት በማድረግ ጥቂት ነጥቦችን ለማካፈል ወደድኩ፡፡ አንድም የብሔራዊ ጥቅምን ዋጋ ከፍ ከማድረግ አኳያ በሌላም በኩልም ደግሞ ተገቢውን ወታደራዊ ሥነ ምግባር ከመጠበቅ አንጻር ዝርዝር አገራዊ ጉዳዮችን ከመተንተን ይልቅ አንኳር በሚመስሉኝ የሠራዊቱ ጉዳዮች ላይ ብቻ ለማተኮር እወዳለሁ፡፡
በፕሮፓጋንዳ ማደንዘዝ
ወታደራዊ ሳይንስ በዲሲፕሊን የታነጸ ጠንካራ ሠራዊት ለመፍጠር ዋነኛው ግብዓት ነው፡፡ እያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል ዘመኑ ከደረሰበት ወታደራዊ ብልሃት የቻለውን ያህል እንዲቀስም ሳይንሱን ያለማቋረጥ መመርመር ግዴታውም ጭምር ነው፡፡ ማወቅ ወታደሩን የበለጠ ለሕዝቡ ታማኝ እንዲኾንና የሚጠበቅበትን አገራዊ ግዴታ እንዲወጣ ይረዳዋል፡፡ እውነታው ይሄ ቢኾንም እኔ ባሳለፍኩብት የኢሕአዴግ ሠራሽ ሠራዊት ውስጥ “ማወቅ” የሚለው ቃል ብያኔው ከዚህ የራቀ ነው፡፡
ማወቅ፣ መሠረታዊ የሰው ልጆችን መብት ከመካድ እና ያለማቋረጥ በኢሕአዴግ ካድሬዎች የሚነገሩትን ፕሮፓጋንዳዎች ከማነብነብ ጋር እጅጉን የተቆራኘ ነው፡፡ ሠራዊቱ ከመብቱ ይልቅ ግዴታዎቹን እንዲያብሰለስልና እንዲፈጽም ይጠበቅበታል፡፡ ግዴታ እንጂ መብት የሠራዊቱ አካል አይደለም፡፡ ዘወትር በሚነገረውም ፕሮፓጋንዳ ተገዢ በማድረግ የህሊና እስረኛ ይኾናል፡፡ ለመጥቀስ ያህል ለተራ ወታደር ቴክኒካል ስልጠናዎች ለሶስት ወር ብቻ ያህል ሲሰጡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ እና መሰል ኢሕአዴግ ፕሮፓጋንዳ ሥራዎች እሰከ ስድስት ወር ያህል ይዘልቃሉ፡፡ በየስብሰባውም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማጥመቅ እና መደንዘዝ ይቀጥላል፡፡ ብዙ ጊዜም እንደሚስተዋለው በስብሰባዎች የብዙሃኑ የሚመስሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ትልቅ ወንጀል ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ አገራዊ አጀንዳዎችም የሠራዊቱ ያልኾኑ ያህል ከከፍተኛ ባለስልጣናት እስካልፈለቁ ድረስ አባላት በስብሰባዎች መካከል እንዲያነሱ አይፈቀድም፡፡
ቀደም ሲል እንደጠቀስኩትም የፕሮፓጋንዳዎቹ ዓላማ ሰራዊቱ መብቱን እንዳይጠይቅ፣ ኢሕአዴግን መጠበቅ ሕገ መንግስቱን መጠበቅ ነው ብሎ እንዲያምን እና የፕሮፓጋንዳቸው ተገዢ እንዲኾን ማድረግ ነው፡፡ ይህም አብዛኛው ሠራዊት መንግስት ከሚሰጠው ግዳጅ ውጪ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ውስጥ ሚና እንዳይኖረው እንዲሁም ስለብሔራዊ ጥቅም እንዳያስብ ኾን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ ሠራዊቱ ራሱን ችሎ ህልውና እንዲኖረው ማድረግ በኢሕአዴግ ሰዎች ልብ ውስጥ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ በተለያዩ ስብሰባዎች እንደሚደሰኩሩልን “ኢሕአዴግ ከሌለ ሠራዊቱ ህልውናውን ያጣል፡፡” ስልጠናዎች ሁሉ ከኢሕአዴግ ውጪ የትኛውም አካል የሠራዊቱ ወዳጅ እንዳልኾነ እና የመንግስት ለውጥ ቢመጣ ኣባላቱ ተጎጂ እንደሚኾኑ የሚሰብኩ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የኾነውን ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባ ላይ ድል ማስመዝገቡ ሲነገር በሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በሠራዊቱ ውስጥ ተደጋጋሚ እና አሰልቺ ስብሰባዎች የበዙበት፤ አይን ያወጣ ወንጀልም የተስተዋለበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱም ከተደረጉት ስብሰባዎች ውስጥ እኔ በነበርኩበት መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ውስጥ በጥቅምት 1998 ዓ.ም እንዲህ የሚል ውሳኔ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ “ሕዝቡ ተሳስቶ ሊመርጥ ይችላል፡፡ እነዚህ ሰዎች (ቅንጅቶች) ሕገ መንግስቱን ሊንዱ የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት አዲስ አበባን ለቅንጅት ሰዎች ቢያስረክብም ሠራዊቱ ግን ማስረከብ የለበትም፡፡” ይህ ኣባባል መንግስትና ሠራዊቱ የተለያየ አቋም ያላቸው ለማስመሰል እንጂ የዚህ ሐሳብ ጠንሳሽ አራት ኪሎ እንደሚገኝ ማንም የሚስተው ጉዳይ አልነበረም፡፡
ባይተዋር ወታደር
ይህ በኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ውስጥ የኾነ ታሪክ ነው፡፡ በሰኔ 1997 ዓ.ም አንዲት የሠራዊቱ አባል በላይቤሪያ የሰላም አስከባሪ ግብረ ኃይል ውስጥ መካተቷ ይነገራታል፡፡ ብዙዎች ከግቢው ለመራቅም ይኹን ዳጎስ ላለው ክፍያ ላይቤሪያ መጓዝን እንደ ልዩ ዕድል ያዩት ስለነበር ወታደሯም በአጋጣሚው ደስተኛ ነበረች፡፡ ከደስታዋ ጋር ግን ብዙ አልተጓዘችም፡፡ ለአመራሮቹ ቅርብ የኾነ የሠራዊቱ አባል በላይቤሪያው ጉዞ አልተካተተ ኖሮ በብስጭት ባለዕድለኛ ጉዞውን ሰርዛ ለእርሱ እንድትሰጠው ይጠይቃታል፡፡ እርሷም ቀድሞ ትሻው የነበረው ዕድል እንደኾነ በመግለጽ እንደማትችል ትገልጥለታለች፡፡ እርሱ አልተናደደም ይልቁንም “እኔ ቀድሜ አንቺን ላማክር ብዬ እንጂ ቢሮ ብሄድ ያንቺን ዕድል ለእኔ ይሰጡኛል” ብሎ የሚፈልገውን አደረገ፡፡ የእርሷ ጉዞ ያለፍቃዷ ተሰርዞ ለሌላ ሰው ተሰጠ፡፡
እንዲህ አይነት አድሎ ስራዎች እጅግ የተለመዱ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅትም በጥረቱ ያገኘውን የውጭ ትምህርት ዕድል የሌላ ብሔር ስለኾነ ብቻ የተከለከለ የመከለካከያ ኮሌጅ መምህር ራሱን ማጥፋቱ ብዙዎቻችን የሠራዊቱ አባላት በቁጭት የምናስታውሰው ነው፡፡
ይህ የግቢው ለአንድ ብሔር የማድላት ነገር የተለመደ ነው፡፡ ሌሎች ራሳቸውን ባይተዋር እንጂ የሠራዊቱ አካል መኾን የሚያኮራቸው ነገር የለም፡፡ የሻምበልነት ማዕረግ ያለውን ነገር ግን ከትግራይ ክልል ውጭ የመጣን የሌላ ብሔር ተወላጅ ተራ ወታደር መመርያ ሊሰጠው ይችላል፡፡ በተለይ ከ1997 ምርጫ ወዲህ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ሚና ጭራሹኑ እየጠፋ ነው፡፡ ከፍተኛ ስልጣን የያዙ ጥቂቶች አሁንም ቢኖሩም እምነት የሚጥልባቸው ባለመኖሩ በሠራዊቱ ውስጥ አሉ መባላቸው ለቁጥር ካልኾነ በቀር ፋይዳ የለውም፡፡
ላይ ላዩን ለተመለከተው የሠራዊቱ የብሔር ተዋጽኦ ምጥጥን የሚታይበት ይመስላል፡፡ ይሁንና የቁጥር መመጣጠን እና የስልጣን መጋነን ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ የትግራይ ተወላጆች ቁጥር አነስተኛ ቢኾንም የያዙት የስልጣን ድርሻ ግን እጅግ ከፍተኛውን የያዘ ነው፡፡ ለይምሰል ከሌሎች ብሔረሰቦች የተውጣጡ ስልጣን ቢይዙም ቀደም ሲል እንደተገለጸው ዋናው የስልጣን ሞተሩ ያለው በሕወሃት እጅ ነው፡፡ ሠራዊቱ ይህንን በሚገባ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ጥያቄ እንዳያነሳ በሕግና በደንቦች ቀንብበው ይዘውታል፡፡ የጋራም ኾነ የግል ጥያቄ እንዲነሳ አይፈለግምና፡፡
በዚህም ወቅት ብዙዎች አማራጭ አድርገው የወሰዱት ከሠራዊቱ ወጥቶ መኮብለልን ነው፡፡ ብዙዎች በተለያየ ምክንያት ከአገር እየወጡ መቅረትን መርጠዋል፡፡ በተለይ የትምህርት ደረጃቸው ከፍ ያሉት (የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ) በሠራዊቱ ውስጥ ያላቻው ቁጥር ከጊዜ ጊዜ እየመነመነ ነው፡፡ ብዙዎቹም እንደወጡ መቅረትን መርጠዋል፡፡
የሥርዓቱ ፈጣሪዎች ለሠራዊቱ ያላቸው ንቀት
በ1997 ቅንጅት አዲስ አበባን ማሸነፉ ሲገለጽ የመሬት መቀራመቱ ለሠራዊቱም ደርሶት ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ሩጫ ጥቂት በማይባሉ የሠራዊቱ አባላት የተወደደ ባይኾንም ከመንግስት የመጣ መመርያ ነው በማለት ብዙሃኑ አባላት በመሬት ቅርጫው ተሳትፏል፡፡ እውነታውን በወቅቱ ለታዘበ የእናት አገር መሬት ሳይኾን የባእድ ይመስል ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ታለፈ፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባን ሳይረከብ ቀረ፤ መንግስትም እፎይ አለ፡፡
መንግስት መረጋጋቱን ሲያውቅ የመጀመረያው ርምጃ በሰበብ አስባቡ ለቅንጅት አድልቷል የተባለውን አባል መቅጣት ነበር፡፡ እኔም እንደማስታውሰው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራ አንድ ስብሰባ አዋሽ አርባ ላይ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱም መንግስት ራሱ በመመሪያ የፈቀደውንና ያስፈጸመውን የመሬት መቀራመት ጉዳይ አንስቶ “ስግብግብ” የሚል ቅጥያ ለሠራዊቱ በመስጠት ቂሙን መወጣት ጀመረ፡፡ በምርጫው ሂደትም “ሕገ መንግስቱን አልጠበኩም” እንዲል እና ሂሱንም “እንዲውጥ” ተደርጎ ነበር፡፡
በጥቅምት 1998 ዓ.ም በተደረገው የአዋሽ አርባ ስብሰባ ኢሕአዴግ በግልጽ ለሰራዊቱ ያለውን ንቀት የገለጸበት ነበር፡፡ እዚህ ላይ ቢሰፍሩ ጸሐፊውንም ጭምር የሚያስገምቱ ንግግሮች ከአቶ መለስ ይደመጡ ነበር፡፡ ጉዳዩ በዚህ ብቻ አላበቃም ነበር፡፡ በቅንጅት ደጋፊነት የተጠረጠሩ ያለ ፍርድ እስር ቤት ተላኩ፡፡ “በፓርቲዎች ክርክር ወቅት የቅንጅትን አድምጠህ የኢሕአዴግ ሲመጣ ከቴሌቪዠን ክፍል ወጥተህ ሄደሃል” ተብሎ ግምገማ የተደረገበት ሁሉ ሳይቀር ለእስር ተዳረገ፡፡ 20 ሺህ ሠራዊት በአንድ ቅጽበት ተራገፈ፡፡ ታጠቅ መሙላቱን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ወቅት አፋር በረሃ ላይ ለአራት ወር ያህል በማሰር አሰቃይተው ለቀዋቸዋል፡፡
ኢሕአዴግ ለሰራዊቱ ያለው ንቀት በብዙ መልክ የሚገለጽ ነው፡፡ መብቱን ከመግፈፍ አንስቶ ብሔር ከብሔር እያጋጨ ለሥልጣን ማራዘሚያ እየተጠቀመበት ነው፡፡ ጓደኛ ለጓደኛ እንዳይተማመኑ በማድረግ እንዲሁም የበታች አለቆች የላይኞቹን እንዲያዙ በማድረግ ሠራዊቱን የብሔራዊ ስሜት አሳጥቶታል፡፡
ይህ ከላይ በወፍ በረር የተመለከትኩት እውነታ ዛሬ ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው ሠራዊት ማንነት ነው፡፡ ለነፃነት የቆመ የሚባለው ሠራዊት እንደሌላው የማህበረሰብ ክፍል ሁሉ ነጻነትን የሚሻ ነው፡፡ ድምጽ ማሰሚያ ቀዳዳ አጥቶ እንጂ የነጻነት ጥሪው ከሌሎች ቢልቅ እንጂ የሚያንስ አይደለም፡፡ .