Health: ጽንስ ያለጊዜው እንዲወለድ የሚያስገድደው ደም ግፊት ለእናቶች ሞትም 14 በመቶ ድርሻ አለው ተባለ

– እርግዝናን ተከትሎ የሚከሰተው ደም ግፊት
– ለኩላሊት ሥራ ማቆም፣ ለደም መርጋት፣ ለልብ፣ ለአዕምሮ ህመም፣ ለጽንስ መቀጨትና ለሞት የሚያጋልጥበት ምስጢር ምንድን ነው?

የዶክተሩ ገጠመኝ 1
ቦታው በአንድ ክፍለ ሀገር ነው፡፡ አንዲት የሶስት ልጆች እናት፣ አራተኛ ልጇን አርግዛ ከገጠር ወረዳዎች እየመጣች በአንድ ሆስፒታል የወሊድ ክትትል ታደርጋለች፡፡ በሁለተኛው የእርግዝና ወቅት ላይ የደም ግፊት ይታይባታል፡፡ ዶክተሩ የበሽታውን አስከፊነት በመግለፅ ህክምና እንድትጀምር ሙያዊ ምክር ይሰጣታል፡፡ ሴትየዋ ግን ‹‹ህክምናው ልጄን ሊያሳጣኝ ይችላል›› በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት ወደመጣችበት የገጠር መንደር እምቢ ብላ ትመለሳለች፡፡ በወሯ ተመልሳ ስትመጣ ዶክተሩ የደም ግፊቱ ጊዜ በጨመረ ቁጥር እየተባባሰ እንደሚመጣ በመግለፅ ህክምና እንድትጀምር ለማግባባት ይሞክራል፡፡ ሴትየዋ ግን ፈቃደኛ ሆና አልተገኘችም፡፡ ከወር በኋላ ወደ ሆስፒታሉ ተመልሳ ስትመጣ ግን የደም ግፊቱ ከሚጠበቀው በላይ ጨምሯል፣ መተንፈስ አቅቷታል፣ ሳንባዋ ውስጥ ውሃ ቋጥሯል፣ በአጠቃላይ ግፊቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በህክምና ለማገዝ ከፍ ያለ ጥረት ተደረገ፡፡ ነገር ግን ሴትየዋ ሳንባዋ ውስጥ በተጠራቀመው ውሃ በመታፈኗ ምክንያት፣ በሆስፒታሉ አቅም ልትረዳ የምትችልበት ተስፋ ጠፋ፡፡ በዚህም ምክንያት ከ30 ደቂቃ በላይ ሳትቆይ፣ አራተኛ ልጅ ለማግኘት ብላ ሶስት ልጆቿን ጥላ ሞተች፡፡

የዶክተሩ ገጠመኝ 2
አንዲት ሴት፣ እርግዝናን ተከትሎ በሚከሰት ደም ግፊት አንድ የመንግሥት ሆስፒታል ትመጣለች፡፡ ነገር ግን ህመሙ ተባብሶ ጽንስ ከመቀጨጩ ባሻገር በማህፀኗ ውስጥ እያለ ሞቷል፤ የጉበትና የኩላሊት ጤና እንዲሁም የሚጥል በሽታ ገጥሟታል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል ጽንሱ በቀዶ ህክምና እንዲወጣ ተደረገ፡፡ የተለያዩ መድሃኒቶችን በመስጠት፣ የእናትየዋን ጤና ለመመለስ ጥረት ተደረገ፡፡ ይሄም ሆኖ ከማህፀነው የሚደማው ደም አልቆም ይላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የደም መርጋት ችግርም ያጋጥማታል፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ ሲመጣ፣ በሐኪሞች ውሳኔ የሴትየዋ ማህፀን ተቆርጦ እንዲወጣ ተደረገ፡፡ የፈሰሰውን ደም ለመተካት ተጨማሪ ደም ተሰጣት፤ ይህ በሆነ በሶስተኛው ቀን ግን በሽታው እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ ሊሄድ አልቻለም፡፡ ኩላሊቷ ስራውን አቆመ፡፡ በዚህም ሳቢያ በሽንት አማካኝነት መወገድ የሚገባው በሰውነቷና በደሟ ውስጥ መጠራቀም ጀመረ፡፡ የቆሻሻውን ደም ተከትሎ የሚከሰት የአዕምሮ ህመም ተከሰተባት፡፡ አጠቃላይ የሴትየዋ ጤና እየተወሳሰበ መጣ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን የጤና ባለሙያዎች ተስፋ ባለመቁረጥ ጥረታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የኩላሊት ጤና ለመመለስ፣ ለተከታታይ 10 ቀናት የዲያሌስስ ህክምና እንድታገኝ ተደረገ፡፡ በሂደት በጤናው ላይ መሰረታዊ ለውጥ መምጣት ቻለ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሞት ተርፋ ጥሩ ትዳር አላት፣ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ህይወቷ የተስተካከለና አገርን መጥቀም የምትችልበት ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡

ከዶክተሩ ገጠመኞች መገንዘብ እንደሚቻለው እርግዝናን ተከትሎ የሚከሰት የደም ግፊት መዘዙና ውስብስብነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ 5 የጤና ችግሮች መካከል የደም ግፊት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ለመሆኑ ለምንድን ነው እርግዝናን ተከትሎ የደም ግፊት የሚከሰተው? ለምንስ ገዳይ በሽታ ሆነ? በእነዚህና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮ ዙሪያ፣ አንድ የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

ጥያቄ፡- የደም ግፊት በሽታ በሴቶች ላይ ለምን እርግዝናን ተከትሎ ይከሰታል?
ዶ/ር፡- ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰበውና አሁን እየተደረጉ ያሉ ምርምሮች የሚያጠነጥኑት፣ በእርግዝና ወቅት በሚታዩ አዳዲስ ክስተቶች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ የጽንስ መምጣት፣ የእንግዴ ልጅ መኖር፣ በጽንሱና በእንግዴ ልጁ መካከል የሚኖረው የሆርሞኖች ለውጥ ጋር ይያያዛል ወይ- የሚሉ መላምቶች በተደጋጋሚ በህክምናው ዘርፍ ይነሳሉ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥናቶች አተኩረው እየተካሄዱ ነው፡፡ ነገር ግን በእርግዝና ወቅት በተለየ ሁኔታ፣ ለምን የደም ግፊት እንደሚመጣ ከእርግዝናው ውጭ በውል ተለይቶ የታወቀ ምክንያት የለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአጥንት መሳሳትን ለመከላከል (በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም)

ጥያቄ፡- እስኪ ስለ ደም ግፊት በሽታ ምንነት ጠቅለል ያለ ሐሳብ ያካፍሉን?
ዶ/ር፡- በአጠቃላይ የደም ግፊት በሽታ የምንለው፣ በማንኛውም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችልና የደም የግፊት መጠን መጨመር በሽታ ነው፡፡ በሽታው ፕራይመሪና ሰከንደሪ የደም ግፊት ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ ፕራይመሪ የደም ግፊት 90 በመቶ የሚከሰት ሲሆን ምክንያቱ (መንስኤው) ይሄ ነው ተብሎ በውል አይታወቅም፡፡ ሰከንደሪ የሚባለው የደም ግፊት 10 በመቶ የመከሰት ዕድል ያለውና የተለያዩ የጤና ችግሮችን ተከትሎ የሚመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ የስኳር፣ የኩላሊት፣ የደም ስፍርና የልብ ጤና ችግር ያለባቸው እንዲሁም ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት ባለባቸው ሰዎች ላይ ለሁለተኛው አይነት የደም ግፊት በሽታ የተጋለጡ ናቸው፡፡
ዛሬ የምንነጋገርበት እርግዝናን ተከትሎ የሚመጣው የደም ግፊት በሽታ፣ በሁሉም ማህበረሰብ ላይ ከሚከሰተው ደም ግፊት ጋር በስም ረገድ አንድ አይነት ይመስላል እንጂ በሽታው ግን የተለየ ነው፡፡ በሴቶች የእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የደም ግፊት በሽታ፣ እናቶችን ለሞት ከሚያበቁ 5 የጤና ችግሮች ቀዳሚው ነው፡፡ በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ የደም ግፊት በሽታዎች 4 አይነት ናቸው፡፡ ለዛሬ የምናተኩርበት ግን በተደጋጋሚ በሚከሰተው ፕሪለምሽያ በሚባለው ላይ አተኩራለሁ፡፡ ይህ የጤና ችግር የሚከሰተው በ2ኛው የእርግዝና ወቅት አጋማሽ ነው፡፡ የበሽታው ዋነኛ መገለጫ የደም ግፊት መጨመርና በሽንት ውስጥ ፕሮቲን የሚባለው ንጥረ ነገር በብዛት መገኘት ነው፡፡

ጥያቄ፡- የዚህ ጤና ችግር ስርጭት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶ/ር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ እርግዝናን ተከትሎ የሚከሰተው ደም ግፊት ከ7 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑትን እርግዝናዎችን ያጠቃልላል፡፡ በእኛ ሀገር ያለውን ስርጭት በተመለከተ እውነት ለመናገር፣ የችግሩን አገራዊ ስፋት የሚያሳይ የተጠና ጥናት የለም፡፡ ነገር ግን ተቋምን መሰረት አድርገው የተጠኑ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የበሽታው ስርጭት ከዓለም አቀፉ ጋር ተቀራራቢ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን አንድ የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም በዕለት ተዕለት የቀን ውሎው ላይ ከሚያጋጥመው፣ የእናቶች ጤና ችግሮች መካከል እርግዝናን ተከትሎ የሚከሰተው ደም ግፊት አንዱና ቀዳሚው ነው፡፡

ጥያቄ፡- መንስኤው ምንድን ነው?
ዶ/ር፡- እስካሁን በአለው ሳይንሳዊ ጥናት፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ደም ግፊት የሚያመጣው ተጨባጭ ምክንያት አይታወቅም፡፡ ምክንያቶቹ በመላምት ደረጃ ያሉ እንጂ በምርምር የተረጋገጡ አይደሉም፡፡

ጥያቄ፡- አጋላጭ ምክንያቶችስ የሉም?
ዶ/ር፡- አሉ!

ጥያቄ፡- ዋና ዋና የሚባሉትን ብናያቸው?
ዶ/ር፡- ለጤና ችግሩ ተጋላጭ የሚያደርጉ ምክንያቶች በግልጽ ይታወቃሉ፡፡ ዋና ዋና የሚባሉት አጋላጭ ምክንያቶች፣ የመጀመሪያ እርግዝና (የመጀመሪያ እርግዝናቸው የሆኑና ደጋግመው የወለዱ እናቶችን ስናነፃፅር፣ የመጀመሪያ እርግዝናቸው የሆኑ እናቶች ለጤና ችግሩ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው) በቀደመው እርግዝና የደም ግፊት ከነበረ ቀጥሎ በሚመጣው የእርግዝና ወቅት የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ዕድሜ (ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሁነው የሚያረግዙና ከ40 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች የሚያረግዙ ከሆነ ለደም ግፊት በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው)
እንዲሁም የኩላሊትና የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የሰውነት ክብደት ያላቸው፣ መንታ እርግዝና፣ የዘር ተጋላጭነትና ከእርግዝና በፊት የነበረ የደም ግፊት በሽታ ለጤና ችግሩ ተጋላጭ የሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Health: የሰውነት መቆጣት (አለርጂ)

ጥያቄ፡- ከአመጋገብና ከአኗኗር ዘይቤ ጋር በተያያዘ፣ እርግዝናን ተከትሎ በሚከሰተው ደም ግፊት የሚያጋልጡ ምክንያቶች የሉም?
ዶ/ር፡- አመጋገብን በተመለከተ እርግዝናን ተከትሎ ለሚመጣው ደም ግፊት፣ በተለየ ሁኔታ ያመጣሉ ተብለው የሚጠቀሱ ምግቦች የሉም፡፡ ነገር ግን የጤና ችግሩ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው ብለን የገለጽናቸው ማለትም ለስኳር፣ ለኩላሊትና ለደም ግፊት በሽታዎች የሚያጋልጡ አመጋገቦችና የአኗኗር ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለሆነም አመጋገባችንና የአኗኗር ሁኔታችን በቀጥታ መንገድ እርግዝናን ተከትሎ፣ ለሚመጣ ደም ግፊት የሚያጋልጥ ቢሆንም በተዘዋዋሪ መንገድ ግን ለጤና ችግሩ የመጋለጥ ዕድልን ሊጨምር ይችላል፡፡

ጥያቄ፡- የበሽታው ምልክቶችስ የትኞቹ ናቸው?
ዶ/ር፡- በሽታው ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ በእርግዝና ወቅት የደም ግፊት መጨመር፣ ግፊት በነበረባቸው ሴቶች ላይ ደግሞ የደም ግፊት መባባስ፣ ለቀናት የሚቆይ የራስ ምታት፣ የእይታ መደብዘዝ፣ የብርሃን ማንጸባረቅ፣ የላይኛው የሆድ ክፍል ህመም፣ የከፋ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ የሽንት መጠን መቀነስ፣ የደረት ህመም፣ የአየር ማጣት ስሜት፣ ሳል፣ የፅንሽ መቀጨጭ፣ የሽርት ውሃ መቀነስ፣ የፅንስ እንቅስቃሴ መቀነስ፣ የፅንስ ሆ ውስጥ መጥፋት፣ ሰውነትን ማንቀጥቀጥና ራስን ስቶ መውደቅ፣ በተጨማሪም የላይኛው የሰውነት ክፍል እብጠትና አንዲት ሴት በሳምንት ከ2 ኪሎ በላይ መጨመር ለሽታው መከሰት መሰረታዊ ምልክቶች ናቸው፡፡

ጥያቄ፡- የጤና ችግሩ ከእርግዝና በኋላ የመቀጠል ዕድል ይኖረዋል?
ዶ/ር፡- እርግዝናን ተከትሎ የሚመጣው ደም ግፊት፣ ከእርግዝና በኋላ በሁሉም ላይ ባይሆን በአንዳንድ ሴቶች ላይ አልፎ አልፎ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን ግፊቱን ለመቆጣጠር ከእርግዝና በኋላ የተለያዩ ህክምናዎች ይደረጋሉ፡፡ ሕክምናው ተደርጎ እናትየዋ ከወደለች ከ12 ሳምንት በኋላ ደም ግፊቱ ከቀጠለ እንደማንኛውም ሰው የሚከሰት መደበኛ የደም ግፊት ሁኖ የመቀጠል ሁኔታ አለ፡፡ ሆኖም አብዛኛው በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ደም ግፊት ተገቢው የህክምና ክትትል ከተደረገ ከወሊድ በኋላ ይጠፋል፡፡

ጥያቄ፡- በእናትየዋ ላይ የታየው ደም ግፊት ወደ ልጅ ይተላለፋል?
ዶ/ር፡- የመተላለፍ ዕድሉ ጠባብና የለም ሊባል በሚችል ደረጃ ያለ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በአግባቡ ያልታከመ ደም ግፊት በሽታ፣ በእናትየዋና በፅንሱ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው?
ዶ/ር፡- በእርግዝና ወቅት የሚከሰት ደም ግፊት፣ በእናትየዋ ላይ ብዙ አይነት ጉዳቶችን ያስከትላል፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትን አለፍ አለፍ ብለን እንያቸው፡፡ በቀዶ ህክምና የመውለድ ዕድልን ያሰፋል፣ ያለጊዜ መውለድ፣ የኩላሊት ሥራ መዳከም፣ የመጣል በሽታ፣ የሳንባ ውስጥ ውሃ መቋጠርና በስተመጨረሻም በእናትየዋ ላይ የሞት አደጋ ያመጣል፡፡ ፅንሱን በተመለከተ ያለ ጊዜ መውለድ፣ የመተንፈሻ ችግር፣ በከፍተኛ ደረጃ ለኢንፌክሽን መጋለጥ፣ በሰውነት ውስጥ የስኳር መጠን መቀነስ፣ የሰውት ሙቀት መጠን አለመጣጣም፣ ቀጭጮ መውለድ፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነትና በኋላም ሞትን ያመጣል፡፡ ከእነዚህ ሁኔታዎች መገንዘብ የሚቻለው፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰትን የደም ግፊት በሽታ በአግባቡና በወቅቱ መታከም ካልተቻለ፣ በእናትየዋም ሆነ በህፃኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የጤና ችግሩን መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚደረገው ምርመራ ምንድን ነው?
ዶ/ር፡- በእርግዝና ወቅት የተከሰተ ደም ግፊት በሽታ መኖር፣ አለመኖሩን ለማወቅ የተለየ እውቀትና ቴክኖሎጂ አይጠይቅም፡፡ ሁላችንም በምንለካበት የደም ግፊት መለኪያ ችግሩ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በእርግጥ የበሽታውን ሙሉ ገጽታ ለማወቅ የደም ግፊት መጠንን መለካት ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ግፊት መኖሩን ግን ያረጋግጣል፡፡ ግፊት መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ በሽታው ያለበት ደረጃናንና ሌሎች የጤና ችግሮችን ማምጣት አለማምጣቱን ለማረጋገጥ የጉበት፣ የኩላሊት፣ የደም ፕሮፋይል፣ የልብ፣ የአዕምሮና የመሳሰሉ ምርመራዎች እንደየአስፈላጊነቱ ይካሄዳሉ፡፡ የፅንሱን ጤንነት ለማረጋገጥም የአልትራሳውንድ ምርመራ ይካሄዳል፡፡ በእነዚህ መንገዶች የበሽታውን መኖር ብቻ ሳይሆን በሽታው ያለበትን ደረጃና ያስከተለውን ጉዳት በዝርዝር ማወቅ ይቻላል፡፡ በሀገራችን ደረጃም አቅሙ አለ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትዳር ለምን ሰላም አልባ ይሆናል? መፍትሄውስ...

ጥያቄ፡- ህክምናውስ?
ዶ/ር፡- ሶስት ዋና ዋና የህክምና አይነቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ህክምና መድሃኒትን በመጠቀም የግፊት መጠንን መቆጣጠር እና በቂ የሚባል ደረጃ ላይ ማድረስ ነው፡፡ ሁለተኛው አንቀጥቅጦ ወደሚጥል በሽታ እንዳትገባ ማከም ወይም ተከስቶ ከሆነ ወደተባባሰ ደረጃ እንዳይሸጋገር ማድረግ ነው፡፡ ሶስተኛውና የህክምናው ማጠንጠኛ የሚባለው ልጁ ጊዜው ሳይደርስ እንዲወለድ ማድረግ ነው፡፡ እንግዲህ ለዚህ ጤና ችግር የሚሰጡ ዋና ዋና ህክማዎች ከላይ የተገለፁት ናቸው፡፡ ደም ግፊቱ በተጓዳኝ ያመጣቸው ሌሎች የጤና ችግሮች ካሉ እነሱን የማከም ሥራ ይሰራል፡፡

ጥያቄ፡- እንደገለፁልኝ፣ በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የደም ግፊት በሽታን ለማከም ጥቅም ላይ የሚውሉት መድሃኒቶች ናቸው፣ በእርግዝና ወቅት መድሃኒት መሰጠት ጉዳት የለውም?
ዶ/ር፡- በእርግዝና ወቅት ዝም ብሎ የተገኘውን አይነት መድሃኒት መስጠትም ሆነ መጠቀም አይቻልም፣ አደገኛም ነው፡፡ ነገር ግን በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊትን ለማከም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መድሃኒቶች ውስጥ በእናትየዋም ሆነ በፅንሱ ላይ ምንም አይነት የከፋ ጉዳት የማያስከትሉ መድሃኒቶች አሉ፤ እነሱን ነው የምንጠቀመው፡፡

ጥያቄ፡- ይሄን የጤና ችግር መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?
ዶ/ር፡- በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ደም ግፊት አስቀድሞ መከላከል አይቻልም፡፡ ነገር ግን አጋላጭ ምክንያቶች ብለን ከላይ የዘረዘርናቸውን መሰረታዊ ጉዳዮች ማስወገድ ከቻልን በተዘዋዋሪ የጤና ችግሩን መከላከል እንችላለን፡፡ በሌላም በኩል በሽታው ከተከሰተ በኋላም በወቅቱ ህክምና ማድረግ ከተቻለ በሽታው ሊያመጣቸው የሚችላቸውን ውስብስብ የጤና ጉዳቶች መከላከል ይቻላል፡፡ የእናቶችን ሞትንም መቀነስ ያስችላል፡፡

ጥያቄ፡- በማህበረሰቡ ውስጥ ከጤና ችግሩ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው የሚሉት ካለ ቢያነሱት?
ዶ/ር፡- በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ደም ግፊት በሽታ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ከሚከሰተው አጠቃላይ ደም ግፊት ጋር አንድ አድርጎ ማሰብ ይስተዋላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ደም ግፊት አለብሽ ተብላ ሲነገራት፣ አጠቃላይ የህክምና ፓኬጅን ከመውሰድ ይልቅ የደም ግፊት መድሃኒት ብቻ ነጥሎ በመውሰድ፣ ግፊቱ ወርዷል ብሎ የማሰብ አዝማሚያ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በህክምና ተቋማት በኩል በእርግዝና ወቅት የሚከሰተውን ደም ግፊት፣ እንደማንኛውም ግፊት በመቁጠር በዘፈቀደ መድሃኒት የማዘዝ ድርጊትም ይስተዋላል፡፡ ግፊት መጨመር የበሽታው አንዱ መገለጫ እንጂ የበሽታው ሁለንተናዊ ማለት አይደለም፡፡ ስለሆነም የደም ግፊቱን መጠን ቀነስን ማለት ሴትየዋን አከምን ማለት አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- መልክትዎን ልውሰድና ውይይታችንን እናጠቃለው?
ዶ/ር፡- በአጠቃላይ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ደም ግፊት የከፋ ጉዳትን የሚያስከትል ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በሽታውን በቀላሉ ለማወቅና ለማከም የሚያስችለው አቅም በአቅራቢያችን ያለ ነው፡፡ ስለሆነም ነፍሰጡር ሴቶች በየጊዜው የደም ግፊት መጠናቸውን በምርመራ የማረጋገጥ ልማዳቸውን ቢያሳድጉ፣ ችግሩ ሲከሰትም በፍጥነት ህክምናውን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እናቶች በጤና ተቋም ክትትል የሚወልዱበትን አቅም እና ልምድ በአገር ደረጃ ለማሳደግ ሁላችንም ድርሻ አለን የምንል አካሎች ትኩረት ሰጥተን መስራት ይኖርብናል ብዬ አምናለሁ፡፡

Share