ጥቂት ስለድምጻዊት ነፃነት መለሰ


ከዩሱፍ ኢትዮቲዩብ

ነፃነት መለሰ ወደ ሙዚቃው አለም የተቀላቀለችው በ 1977 ዓ.ም ሲሆን በጊዜው ባሳተመችው “ይላል ዶጁ” በተሰኘው የሙዚቃ አልበሟ የበርካታ ሙዚቃ አፍቃሪዎችን ቀልብ መሳብ ችላለች፡፡

ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ በዚሁ “ይላል ዶጁ” የተሰኘው ዜማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ በርካቶች ለዚህች ባለተሰጥኦ አርቲስትከመቀመጫቸው ተነስተው አጨበጨቡላት፤ አድቆትም ጎረፈላት፡፡ የነፃነት መለሰና የሙዚቃ ትውውቅ ከዚህ አልጀመረም፡፡ ነፃነትና ሙዚቃ ትውውቃቸው የሚጀምረው ነፃነት ትምህርት ቤት እያለች ነበር፡፡ ታዲያ የዛን ጊዜ በወቅቱ ተወዳጅ የነበሩትን የእነ አሪታ ፍራንክሊንን ፤ ዊትኒ ሂውስተን እንዲሁም የእነማዶናን ሙዚቃ ማንጎራጎር ጀምራ ነበር፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ሙዚቀኞች በላይ ለነፃነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው በእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የሰንበትተማሪ እያለች የተለያዩ መንፈሳዊ መዝሙሮችን መዘመሯ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ተሰጥኦ ግን በወቅቱ በብስራተ ወንጌል ሬድዮ ጣቢያ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ክፍል ባልደርባ በነበረችው የነፃነት እህት ፅጌማርያም መለሰ አስተዋፅኦ ባይታከልበት ኖሮ ዛሬ ነፃነት የደረሰችበት ቦታ ላትደርስ ትችል ነበር፡፡ በጊዜው በብስራተ ወንጌል ሬድዮ ጣቢያ የ“እሁድን ላንዳፍታ” ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ታደሰ ሙሉነህ ፕሮግራም ላይ በእህቷ ግፊትየቀረበችው ነፃነት የእንግሊዘኛ፤ሱዳነኛ እንዲሁም የህንድ ሙዚቃዎችን በመጫወት ችሎታዋን አስመሰከረች፡፡ ይህንኑ ፕሮግራም ያዳመጡ በርካታ የሙዚቃ ባንዶች የአብረንእንስራ ጥያቄዎችን አጎረፉላት፡፡ ከበርካታ ጥያቄዎች ግን የነፃነትን ቀልብ የሳበው በወቅቱ በሂልተን ሆቴል ይጫወት የነበረው “ዋልያስ” ባንድ ነበር፡፡ከዋልያስ ባንድ ጋር በሳምንት ለስድስት ቀናት ከአህጉራችን አፍሪካ ፤ከሰሜን አሜሪካ እንዲሁም ከአህጉረ እስያ በፈለቁ በወቅቱ ተወዳጅ ዜማዎችንበመጫዎት የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ቀልብ መግዛት ቻለች፡፡

የመጀመሪያው አልበሟ ገበያ ላይ ከዋለ ከሁለት አመታት በኋላ ባሳተመችው “ምነው ጃል” በተሰኘው አልበም ነፃነት በድጋሚ ባለተሰጥኦአርቲስት መሆኗን አስመሰከረች፡፡ ከዚያም በተከታታይ በሳተመቻቸው “ተው ጀግና በለው” ከቴዎድሮስ ታደሰ ፤አረጋኽኝ ወራሽ እና ኩኩ ሰብስቤ ጋርበሰራችው “ኧረ ተይ ውቢት “ እንዲሁም በ “ትዝታ” አልበሞቿ የበርካታ የሙዚቃ አፍቃሪያን ልብ ውስጥ ገባች፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቴዲ አፍሮ ምኞቶች

ለተወሰነ ጊዜ ኑሮዋን በካናዳ መስርታ የነበረችው ነፃነት ከአስር አመታት ቆይታ በኋላ “ፍርቱና” የተሰኘውን አልበሟን ለአድማጮች አቀረበች፡፡ በፍርቱና አልበም ላይ የተካተቱት ግጥምና ዜማዎች የነፃነት ተወዳጅነት አጠናከሩት ፡፡ የፍርቱና አልበም ተደማጭነቱ ሳይቀዘቅዝ በለቀቀችው “ባይ ባይ” በተሰኘው ነጠላ ዜማዋ አድናቆትና ክብር ጎረፈላት፡፡

በአሁኑ ሰዓት ለገበያ ያዋለችው “ልቤን “ የሙዚቃ አልበሟን ለመጨረስ ሶስት አመት የፈጀባት ሲሆን በአዲካ ኮሚኒኬሽንና ኢቨንትስ አማካኝነት ለገበያ ቀርቧል፡፡በዚህ የሙዚቃ አልበም ላይ በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ከእነዚህም መካከል አስቴር አወቀ ፤ አብርሀም ወልዴ ፤ኒኒ መኮንን እንዲሁም ቶክቻው ይገኙበታል፡፡

ይሄ ሁሉ ክብርና ዝና የተቸራት ነፃነት የመጣችበትን አልረሳችም፡፡ “ልቤን” ተሰኘውን አልበሟን ከማሳተሟ በፊት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መንፈሳዊ መዝሙር የያዙ አልበሞች በማሳተም ከመንፈሳዊ ህይወቷ ጋር ያላትን ቁርኝት አጠናክራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነፃነት ወደፊት በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ በመቆየት በርካታ የሙዚቃ አልበሞችን በማሳተም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ያላትን ቦታ አጠናክራ ለመያዝ አቅዳ በርትታ በመንቀሳቀስ ላይትገኛለች፡፡

Share