(የዘ-ሐበሻ ምንጮች ስለ 6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዛሬ የደረሱባቸው መረጃዎች) ሥርዓቱ ያዘጋጃቸው ኃይሎች “ሆን ተብሎ በሕዝብ የተመረጡ ለማስመሰል” በቡድንም ሆነ በተናጠል 6ኛው ፓትርያርክ አቡነ ሳሙኤል እንዲሁኑ ጥቆማ ማድረጋቸው በፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንና ይህን የሚያደርገው በአቶ አባይ ፀሐዬ የሚመራ ስውር ኃይል እንደሆነ የዘ-ሐበሻ የቤተክህነት ምንጮች አስታወቁ።
በተለይም ለ6ኛው ፓትርያርክነት ከታጩት 5 ሰዎች ውስጥ የ4ቱ በካድሬነት (ቡድን በማሰባሰብ ደረጃ) ከአቡነ ሳሙኤል ያነሰ እንዲሆን የተደረገው ሴራ በመንግስት የታቀደ መሆኑን ያጋለጡት እነዚሁ የዘ-ሐበሻ ምንጮች ብዙ ጊዜ መንግስትን በመተቸት የሚታወቁት አቡነ ገብርኤል በእጩነት የገቡት ምርጫውን ሚዛናዊ ለማስመሰል እንደሆነ ገልጸዋል። ሌሎቹ 3 እጩ ጳጳሳት ደግሞ እንደ አቡነ ሳሙኤል ከወያኔ ጋር ለረዥም ጊዜ በመሥራት ያገኙት የደህነትና የስለላ ሥራ ልምድ የሌላቸው እንዲሆን ሆን ተብሎ መደረጉን እነዚሁ ምንጮች ገልጸው የፓትርያርክ ምርጫው “ዓይን ባለው እና በሌለው” መካከል ነው ብለዋል። ምንጮቹ ይህን ሲያብራሩም “አቡነ ሳሙኤል በደህነነት ሥራ በቆዩባቸው ጊዜያት ቡድን በማሰባሰብና በማደራጀት አሁን ከታጩት አባቶች የላቁ ናቸው፤ ስለዚህ ዓይን ያለው ሰው ፓትርያርክ ሆኖ ይመረጣል ቢባልና ለውድድር ሁለት ዓይን ያለው፣ ዓንድ አይን ያለውና አይን የሌለው ቢቀርቡ የቱ ያሸንፋል?” ይላሉ።
በተለይ መንግስት ሆን ብሎ ባደራጃቸው ቡድኖችና ግለሰቦች አማካኝነት በሕዝብ እንደተመረጡ በማስመሰል አቡነ ሳሙኤልን እጩ 6ኛው ፓትርያርክ እንዲሆኑ በገፍ በማስጠቆም ላይ ሲሆን ይህን ጫና ተከትሎና 6ኛው ፓትርያርክ ማን እንደሚሆን ቀድሞ መታወቁ የሲኖዶሱን አባላት ወትሮም ወደነበረባቸው የዘር መከፋፈል ውስጥ ከቷቸዋል ያሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች በተለይ፦
1ኛ. ፓትርያክ ከሸዋ ፓትርያርክ መመረጥ አለበት የሚሉ ጳጳሳት(ወ እጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተብሎ ፓትርያርኩ ስለሚጠራና የአቡነ ተክለሃይማኖት መንበር ላይ ስለሚቀመጥ ከሸዋ ነው መመረጥ ያለበት በሚሉ)
2ኛ. ከወሎ ፓትርያርክ ተመርጦ አያውቅምና ከወሎ ይመረጥ በሚሉ ሊቃነ ጳጳሳት፤
3ኛ. ፓትርያርክ ከትግራይ ነው መመረጥ ያለበት በሚሉ የአቡነ ሳሙኤል ደጋፊ ቡድኖች ሲኖዶሱ ውስጥ መከፋፈል እንዳለ አጋልጠዋል።
የሲኖዶሱ አባቶች ምንም እንኳ እንደዚህ ያለ መቧደን ቢይዙም የመንግስት ባለስልጣናት በሚገኙባቸው ስብሰባዎች በፍራቻ አቋማቸውን በግልጽ ሳያሳዩ መክረማቸውን ያስታወቁት ምንጮች ከሀሙስ በኋላ ብዙ ነገሮች ጠርተው ይሄዳሉ ሲሉ የደረሱባቸውን መረጃዎች አድርሰውናል።
ይህ በ እንዲህ እንዳለ በከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዳለ የሚነገርለት የፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የካህናቱና ምእመናኑ የፓትርያርክ ጥቆማ የመስጠቱ የጊዜ ሰሌዳ በዛሬው ዕለት ከ10፡00 በኋላ መጠናቀቁንና ከነገ የካቲት 9 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ዕጩዎችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለማቅረብ አስመራጭ ኮሚቴው ውይይቱን እንደሚቀጥል ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል። ለአቡነ ሳሙኤል የተካሄደው የጠቋሚዎች ዘመቻ የኮሚቴውን አባላት በሙሉ ማስጨነቁ ተገልጿል።
ዘገባችን ይቀጥላል፤ ይከታተሉን።
በእጩነት ከቀረቡት ጳጳሳት መካከል (ፎቶ)
አቡነ ሉቃስ
አቡነ ገብርኤል