አገርና ድንበር ሳይወስነው በሰው ልጆች ሁሉ የሚፈፀመውንና የትልቅ ጉድኝት መገለጫ የሆነውን ወሲብ አስቸጋሪ የሚያደርጉ እና የደስታና እርካታ ምንጭ እንዳይሆን የሚያደርጉትን የጤና ችግሮች ከነመፍትሄያቸው የቅርብ ጊዜ ጥናቶችን ዋቢ አድርገን አሁን እንቃኛለን፡፡
– ጥናቶቹ ምን አሉ?
– ስኳር ህመም እና ሴክስ
– ከፍተኛ የደም ግፊት ከወሲብ ይገፋዎታል
– ከፍተኛ የደም ግፊት ሴቶችንም ከእርካታ ያርቃል
– ኮሌስትሮል የሴክስ ጠር ይሆን?
– የህይወት ውጣ ውረዶች እና የወሲብ ህይወትዎ
‹ጤንነት› ሲባል የሁሉንም የሰውነት ስርዓት እና አካላቶቻችን እንደመሆኑ የወሲብ ህይወታችን ጤንነትም ገሸሽ የሚደረግ አይደለም፡፡ የተሰካ የወሲብ ህይወት የሌላቸው ጥንዶች ደስታቸው ሙሉ ይሆናል ማለት አስቸጋሪ መሆኑም ሀቅ ነው፡፡ የሰዎችን የወሲብ ህይወት አስቸጋሪ የሚያደርጉና ከተጣማሪያቸው ሊያራርቋቸው የሚችሉ በርካታ የጤና ችግሮችን ባለሞያዎች ያነሳሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች አዕምሮ መልካም ሁኔታ ላይ ካለመገኘቱ አሊያም በአካላዊ ህመሞች ምክንያት የሚመጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በርከት ላሉ ሰዎች የተቃና የወሲብ ህይወት ማጣት እና እርካታ የለሽ ጉድኝት በሚዳርጉት ችግሮች ላይ ትኩረት አድርገናል፡፡
ጥናቶቹ ምን አሉ?
‹‹የበርካቶችን የወሲብ ህይወት የሚያናጉ በርካታ የጤና ችግሮች በመላው ዓለም የታወቁ ቢሆንም ችግሩን ወደ ሐኪም ቀርበው የሚያስረዱና መፍትሄው የሚፈልጉላቸው ሰዎች በጣም ጥቂት በመሆናቸው የየሰዉ የጓዳ ችግር ሆነው ቀርተዋል›› ይላሉ በኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦፍ ሜዲስን ይህንን በተመለከተ ጥናታቸውን ያሰፈሩት ዶ/ር ስቴሊ ቴስለር፡፡
በዚህ የምርምር መፅሔት በቀረበው ጥናት 3 ሺህ ሰዎች ላይ በተደረገ ምልከታ በወሲብ ህይወታቸው ላይ ጤናቸው ችግር ማስከተሉን ከሐኪም ጋር ለመወያየት የፈቀዱ ወንዶች 38 ከመቶ ያህሉ ሲሆኑ 22 በመቶ ሴቶችም ወንዶቹን ተቀላቅለዋል፡፡ ‹‹ችግር አለ›› ሲሉም ምክር ፍለጋ ሄደዋል፡፡
በተለያዩ ጥናቶች ከተገኙና የአብዛኛዎቹ ሰዎች አስደሳች ወሲብ የመፈፀም ብቃት ከፈተኑ የጤና ችግሮች መካከል በደም ቧንቧ ላይ የሚከሰቱ ህመሞች፣ የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከመጠን ያለፈ ኮሌስትሮል፣ ድብርት እንዲሁም የሴቶች ማህፀንን የሚያጠቁ የካንሰር አይነቶች በበርካቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ለተለያዩ በሽታዎች ተብለው የሚወሰዱ መድሃኒቶችም ከሚያስከትሏቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል አንዱ ወሲብን አስቸጋሪ ማድረጋቸው በባለሞያዎቹ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከእነዚህ ሌላ በስራ የተወጠረ እና ለትዳር አሊያም ፍቅር ጓደኛ ጊዜን የማይሰጥ ሰው በወሲብ የመደሰት እድሉ ዝቅተኛ ነው ተብሏል፡፡ ሰላም የሌለው እና በጭቅጭቅ የተሞላ ጉድኝትም የወሲብ ህይወትዎ ፀር ተደርጓል፡፡
ስኳር ህመም እና ሴክስ
የስኳር ህመም በተለይ ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመምን ተከትለው ከሚመጡ ተያያዥ ችግሮች መካከል የልብ ህዋሳትን መጉዳቱ፣ አይን፣ ኩላሊት እና የሌሎች አካላት ነርቮችን ማጥቃቱ በዋናነት ይነሳሉ፡፡ የወሲብ ህይወትዎስ ላይ? አዎን ችግር ያመጣል፡፡ በስኳር ህመም ምክንያት በደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን በሚጨምርበት ወቅት በሚመጣው የነርቮች ጉዳት የወሲብ አካላትም የችግሩ ቀማሽ ይሆናሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ለወንዶች በቂ የደም አቅርቦት ወደ ብልት እንዳይደርስ ይሆናል፡፡ ብልት በደም ካልተሞላ ደግሞ ሊወጠርና ሊቆም አይችልም፣ ለወሲብም አይዘጋጅም፡፡ በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹ኤሬክታይል ዲስፊንክሽን›› ተብሎ የሚጠራው የብልት መወጠርና መቆም አለመቻል ችግር የስኳር ህመም ባለባቸው ወንዶች ላይ በበለጠ መታየቱን በርካታ ጥናቶች ማውሳታቸውም ይህን ያስረዳል፡፡
በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የዩሮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ዴቪድ ፔንሰን የጤና ችግሮች በወሲብ ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ ለወንዶች በመንገር ለጤናቸው የተሻለ እንክብካቤ እንዲያደርጉ መምከር ጥረታቸውን የበለጠ ውጤታማ እንዳደረገላቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ወሲብ መፈፀም መከልከል ወይም ደባሪ ሴክስ መፈፀም የሚፈልግ ወንድ የለም፡፡ ስለሆነም ይህን ለማስቀረት ሲል የምትመክሪውን ሁሉ ይቀበላል›› ይላሉ፡፡ ‹‹ስኳር ህመም የአይን ብርሃንህን ሊያጠፋው ይችላል፣ ኩላሊትህ ይጎዳል የሚል ማስጠንቀቂያ ከሰጠኸው ታማሚ ይልቅ የስኳር መጠንህን ካልተቆጣጠርክ ከአሁን በኋላ ወሲብ መፈፀም አትችልም ብትለው ደንግጦ ጥንቃቄውን መተግበር ይጀምራል›› ሲሉ አክለዋል፡፡
የስኳር ታማሚ ከሆኑ በደምዎ የሚገኘውን ስኳር መጠን ከሐኪም ምክር ጋር ይቆጣጠሩ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ይመገቡ፣ የአካል እንቅስቃሴም ያደርጉ፡፡ በሐኪም የተከለከሉትን ምግብም አይውሰዱ፡፡ ያለዚያ የወሲብ ህይወትዎ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ የወሲብ እርካታ በረከትንም መቋደስ አይችሉም፤ ያስቡበት፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት ከወሲብ ይገፋዎታል
ከመደበኛው በላይ የሆነ የደም ግፊት ለልብ ህመምና ስትሮክ አጋላጭ መሆኑን መቼም ያውቃሉ ብለን እንገምታለን፡፡ ወሲብ ከመፈፀም ጋር በተያያዘ ችግር ያመጣብኛል ብለው አስበውስ ያውቃሉ? በዚህ ዙሪያ ጥናቶችን ያደረጉ ባለሞያዎች ግንኙነታቸውን ይተነትናሉ፡፡ ‹‹ከፍተኛ የደም ግፊት የወሲብ ህይወትዎን ጤናማ ፍሰት ያደናቅፋል››
ከፍተኛ የደም ግፊት በወንዶች በሚኖርበት ጊዜ በሂደት የደም ቧንቧዎችን ግድግዳ ሽፋን በማጥቃት ቧንቧዎቹ (አርተሪዎች) እንዲጠጥሩ እና እንዲጠቡ ደም የማሳለፍ ብቃታቸውም በእጅጉ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በቂ ደም ወደ ብልት ካልሄደ ብልት መቆም ይቸግረዋል፡፡ ቢቆምና ወሲብ ቢፈፀም እንኳ የዘር ፈሳሽ (ስፐርምን) በመርጨት እና እርካታ በማግኘት በኩል አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳድራል፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት በዚህ ሁኔታ ወሲብ ከፈፀሙ ከእርካታ ይልቅ የነበረው ችግር ይሆናል የሚታሰብዎት፡፡ በዚህ በመሳቀቅ ወሲብን ነፃ ሆነው ከመፈፀም ገሸሽ ይላሉ፡፡ ብዙም አይደፋፈሩም፡፡ ይህ ደግሞ በፈንታው ከፍቅር ጓደኛዎ አልያም የትዳር ጓደኛዎ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ቅሬታ ውስጥ መጣሉ አይቀርም፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት ሴቶችንም ከእርካታ ያርቃል
ከፍተኛ የደም ግፊት ሴቶችን የወሲብ ህይወት በምን መልኩ እንደሚጎዳ ጥርት ያለ የጥናት ውጤትን ማግኘት ባይቻልም እስካሁን የተደረጉ ምልከታዎች የደረሱባቸውን ውጤቶች እና ምክንያታዊ ግምቶች ያስቀምጣሉ፡፡ ከፍተኛ የደም ግፊት የደም ቧንቧዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር በቂ የደም መጠን ወደ ብልታቸው እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡ ይህ በአንዳንድ ሴቶች ላይ ለወሲብ የመነሳሳት ፍላጎታቸው እንዲቀንስ፣ ብልታቸውም እንዲደርቅ እና የእርካታ ጫፍ ያለመድረስ ችግር እንዲገጥማቸው አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
‹‹በመሆኑም›› ይላል በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሚታተመው ሃርቫርድ ኸርት ሌተር መፅሔት፡፡ ‹‹በመሆኑም ደም ግፊት ልክዎን መቆጣጠር እና በጤናማ ልኬት ውስጥ መሆኑን ማረጋገጥ የወሲብ ህይወትዎን ከችግር ያድናል፡፡ ለደም ግፊት መቆጣጠሪያ ብለው የሚወስዷቸው መድኃኒቶችም አንዳንድ ጊዜ ተመሳሳይ አሉታዊ ተፅዕኖ በወሲብ ህይወትዎ ላይ የማሳደር ዕድል ስላላቸው መድኃኒቱ ሲወስዱ የሚሰማዎትን፣ በወሲብ ፍላጎት እና አፈፃፀም ጭምር የገጠመዎትን ችግር ከሐኪምዎ ጋር ተመካክረው ለእርስዎ ተስማሚ የሆነውን መድሃኒት ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡›› ከሐኪሞች ጋር ስለ ወሲብ ማውራት በተለይ ለኛ ኢትዮጵያውያኑ በጣም ያልተለመደ እና እፍረት ላይ የሚጥል ቢመስልዎትም ከእርስዎ አይብስም፡፡ ለማን ነው የሚኖሩት?
ኮሌስትሮል የሴክስ ጠር ይሆን?
ኮሌስትሮል የቅባት ዘር የሆነ እና ለበርካታ ሆርሞኖች መስሪያነት የሚያገለግል የመሆኑን ያህል ከተገቢው መጠን በላይ በተለያዩ ‹‹መጥፎ›› የሚባለው የኮሌስትሮል አይነት በደም ውስጥ ሲጠራቀም አርተሪዎችን (የደም መተላለፊያ ቧንቧዎችን) ተጠራቅሞ በመዝጋት ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል፡፡ የልብ ድካም፣ ስትሮክ እና መሰል የደም ቧንቧ ህመሞችን ከማስከተሉ በተጨማሪ ጤናማ ወሲብ እንዳይፈፅሙ እና በእርካታውም እንዳይደሰቱ ከሚያደርጉ ችግሮች ተመድቧል፡፡ ግና የደም እና ንጥረ ነገር አቅርቦቶች ወደ ወሲብ ብልቶችና አካባቢያቸው እንዳይደርሱ በማድረግ መሆኑን ባለሞያዎች ይገልጣሉ፡፡ በመሆኑም የቅባት (ኮሌስትሮል) ልክዎን መቆጣጠር ስራዬ ብለው ይያዙት፡፡ ቅባት ነክ ምግቦች እንዲወዳጁም አይመከርም፡፡ በሴክስ ፈርደው ከሆነ ይግቡበት!
የህይወት ውጣ ውረዶች እና የወሲብ ህይወትዎ
ህይወት ሁል ጊዜ በተቃና ሁኔታ አትጓዝምና አንዳንድ ጊዜ የሚያሳስቡን እና የሚያስጨንቁን ሁኔታዎች ይከሰታሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎችን ለጭንቀት ውጥረት እና ድብርት ሊዳርጉት የመቻል እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ አዕምሯችን በዚህ ሁኔታ ባለበት ጊዜ ውስጥ ወሲብ የመፈፀም ፍላጎት አይኖረንም፡፡ የሆነ የጎደለ ነገር እንዳለ ቢሰማንም ወሲብ ካለመፈፀማችን ጋር የተያያዘ ይሆናል ብለን የምንገምት ብዙ አይደለንም፡፡ በመሆኑም ሁልጊዜም ስሜታችን ጥሩ ያልሆነ እንደሆነ እና አዕምሮአችን የተጨናነቀ ከመሰለን ምክንያቱን ፈልገን እናውጣ፣ መፍትሄ እንፈልግ፡፡ ነፃ ያልሆነ እና ዘና ያላለ አዕምሮ በወሲብ የመዝናናት እና እርካታ የማግኘት፣ የመደሰት እድሜ ዝቅተኛ በመሆኑ አዕምሮዎትን ከሚያስጨንቀው ነገር ያፅዱት፣ ለጓደኞች ሀሳብዎን ያካፍሉ፣ ባለሞያ እርዳታ ከመፈለግም አይቆጠቡ፡፡ ለተለያዩ በሽታዎች የሚወስዷቸው መድኃኒቶችም የወሲብ ህይወትዎን አጓጉል የማድረግ መጥፎ የጎንዮሽ ጉዳት ስለሚኖራቸው ይህን ያስቡበት ከባለሞያም ይመካከሩ፡፡
– See more at: http://www.tenaadam.com/amharic/archives/1930#comment-1315