May 31, 2014
12 mins read

በማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ፤ የሲኖዶስ ጉባኤ በፓትርያርኩና ጳጳሳቱ ፍጥጫ ተቋጨ – (አዲስ አድማስ ጋዜጣ)

ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደዘገበው፦

ጳጳሳት የፓትርያርኩን የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ማሻሻያ ቅድመ ኹኔታ አልተቀበሉትም

‹‹ቅድመ ኹኔታው የማኅበሩን አገልግሎት የሚያቀጭጭና በሒደትም የሚያስቆም ነው›› /ታዛቢዎች/

የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅን እንደ አንድ አጀንዳ የያዘው የዘንድሮው የሲኖዶሱ የርክበ ካህናት ጉባኤ ከረቂቁ ጋር በተያያዘ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል በተፈጠረ ፍጥጫ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
የፍጥጫው መንሥኤ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው የማኅበረ ቅዱሳን መተዳደርያ ደንብ አጥኚ ኮሚቴ ያዘጋጀው የማሻሻያ ረቂቅ በዝርዝር ከመታየቱ አስቀድሞ ፓትርያርኩ ለውይይቱ እንደ ቅድመ ኹኔታ ያቀረቧቸው ነጥቦች በአብዛኛው የጉባኤው አባላት የገጠመው ተቃውሞ እንደኾነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የቅ/ሲኖዶሱን ስብሰባ በርእሰ ጉባኤነት የሚመሩት ፓትርያርኩ፤ በአጀንዳው ላይ የሚካሔደውን ውይይት ቀጣይነት ይወስናል በሚል ካቀረቧቸው ቅድመ ኹኔታዎች ውስጥ÷ ለአጥኚ ኮሚቴው መመሪያ የሰጡባቸው ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› አንድም ሳይቀነሱ በደንቡ እንዲካተቱና ረቂቁ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ከጸደቀ በኋላ እንዲታይ የሚሉ እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡

ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ አስቀምጠዋቸዋል በተባሉት ነጥቦች ስምምነት ላይ ከተደረሰ ስብሰባው ሊቀጥል እንደሚችል በመጥቀስ፣ ኃይለ ቃልም ተማኅፅኖም በተቀላቀለበት አኳኋን መጠየቃቸው ተዘግቧል፡፡
ይኹንና የሚበዙት ሊቃነ ጳጳሳት በቀጥታ እንደተቃወሟቸው፣ የተቀሩትም ድጋፍ ከመስጠት እንደተቆጠቡ ታውቋል፡፡ ፍጥጫው ቀጥሎ አቡነ ማትያስ ‹‹አቋሜ ይኽው ነው፤›› በሚል አጀንዳውን መዝጋታቸውን ሲያስታውቁም፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ እንዲህ ተብሎ የሚተው አይደለም፤›› በሚል ከኹሉም ሊቃነ ጳጳሳት ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ምንጮች ይገልፃሉ፡፡

የቅ/ሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባ የሚካሔደው ምልዓተ ጉባኤው ከጅምሩ ተስማምቶ ባጸደቃቸው የመነጋገርያ አጀንዳዎች መሠረት እንደኾነ በሊቃነ ጳጳሳቱ ተቃውሞ ተጠቅሷል፡፡

የማኅበሩ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ እንዲቀርብ ከታዘዘበት ከጥቅምት 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እየተንከባለለ ለኹለት ዓመታት መዘግየቱን ሊቃነ ጳጳሳቱ አስታውሰው፣ የተጓተተው አጀንዳ ‹‹የማኅበሩን አገልግሎት ያቀጭጫሉ፣ በሒደትም ያስቆማሉ›› በሚል በተተቹት የፓትርያርኩ ቅድመ ኹኔታዎች ሊዘጋ እንደማይችልና ተጨማሪ ጊዜ ሳይወስድ ቅ/ሲኖዶሱ ሊወያይበት እንደሚገባ በአጽንዖት በመናገራቸው፣ ጉዳዩ ሳይቋጭ ለቀጣዩ ቀን በይደር ተላልፏል፡፡

አጀንዳው ሰኞ፣ ግንቦት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ጥዋት መታየት ሲጀምር፣ አጥኚ ኮሚቴው በ37 አንቀጾችና በ34 ገጾች አሻሽሎ ያዘጋጀው የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብና የኮሚቴው ቃለ ጉባኤ በንባብ መሰማቱም ታውቋል፡፡ ፓትርያርኩ ‹‹ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች›› በሚል ራሱን በቻለ ርእስ በደንቡ እንዲካተት ለአጥኚ ኮሚቴው ጥብቅ መመሪያ የሰጡበት ባለ24 አንቀጽ ሰነድም አብሮ እንዲነበብላቸው መጠየቃቸው የመጀመሪያው ቀን የፍጥጫ መነሻ እንደነበር ታውቋል፡፡

በ24 አንቀጾችና በአምስት ገጾች የተዘረዘሩት የፓትርያርኩ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችና ግዴታዎች÷ በአባላቱ በጎ ፈቃድ ተቋቁሞ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘውን ማኅበር፤ ከሕገ ተፈጥሮው ውጭ የሚያደርግ፣ በቅ/ሲኖዶሱ ፈቃድ ከሚመራበት ደንብ በተፃራሪ ተቋማዊ ህልውናውን፣ የአመራር ምርጫውን፣ የአባላት አያያዙንና የሥራ ቦታውን ለውጭ ተጽዕኖ አሳልፎ የሚሰጥና አጣብቂኝ ውስጥ የሚያስገባ፣ በአርኣያነት የሚጠቀሰውን የፋይናንስ አሠራሩን ወደ ኋላ የሚጎትት መኾኑን እንደተረዱ ያብራሩ አንድ የቅ/ሲኖዶሱ አባል፣ ‹‹ቀጣዩ ቀንም የከበደ ነገር ይዞ እንደሚመጣ ግልጽ ነበር፤›› ይላሉ፡፡
በይደር የተያዘው አጀንዳ በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ጥዋት ተጀምሮ ለግማሽ ቀን የቀጠለ ቢኾንም ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ የመተዳደርያ ደንብ ማሻሻያውን በዝርዝር ለመመልከት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡

‹‹ፓትርያርኩ በቅድመ ኹኔታ ያስቀመጧቸውን ነጥቦችና በአጀንዳው ቀጣይነት ላይ የያዙትን አቋም አልቀየሩም፤ ሊቃነ ጳጳሳቱም ባጸደቅነው አጀንዳ መሠረት ቅድሚያ ሰጥተን መነጋገር ያለብን የሠየምነው አጥኚ ኮሚቴ አዘጋጅቶ ባቀረበው ረቂቅ ላይ ነው፤ መካተት ያለበት ነገር ካለም ማኅበሩን በሚያሠራ መልኩ እያገናዘብን በሒደት እናየዋለን እንጂ አጀንዳው በቅድመ ኹኔታ መታሰር የለበትም በሚል ለማስረዳት ጣሩ፤ በመጨረሻም ፓትርያርኩ “እንግዲያውስ ስብሰባውን ለመምራት አልችልም” በማለታቸው የስብሰባው መቋጫ ኾኗል፤›› ይላሉ- ሒደቱን ለአዲስ አድማስ የገለጹ የስብሰባው ምንጮች፡፡
የማኅበሩ ደንብ በመጀመሪያ ረድፍ ከሰፈሩት የቅ/ሲኖዶሱ መነጋገርያ ነጥቦች አንዱ እንደነበር ያስተዋሉ ሌሎች የስብሰባው ተከታታዮች በበኩላቸው፤ አጀንዳው ከቅደም ተከተሉ ወጥቶ እየተገፋ በመጨረሻ መነሣቱ በፓትርያርኩና በሊቃነ ጳጳሳቱ መካከል ይህ ዓይነቱ አለመግባባት ሊነሣ እንደሚችል ጠቋሚ ነበር ብለዋል፡፡

ተከታታዮቹ አክለውም፣ ፓትርያርኩ ስብሰባውን ለመምራት ፈቃደኛ ባይኾኑም በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ በተደነገገው የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት መሠረት፣ ምልዓተ ጉባኤው በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያዎች ላይ የጀመረውን ውይይት ቀጥሎ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚችልባቸው አግባቦች እንደነበሩ ገልጸው፣ ቅ/ሲኖዶሱ በግለጫው የመጨረሻው አጀንዳው ባደረገው የማኅበሩ ደንብ ላይ “ውይይት ተደርጎበታል” ከማለት በስተቀር ስብሰባውን የቋጨበት አኳኋን ያልተለመደና አደናጋሪ ነው ብለዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን የዘመኑን ኦርቶዶክሳዊ ትውልድ አደራጅቶ ማንነቱን የሚያውቅበትንና በግብረ ገብ የሚታነፅበትን ትምህርተ ሃይማኖት ከማስተማር ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት አገልግሎታቸውን በብቃት የሚወጡበትን ኹለገብ ሞያዊ ድጋፍ የመስጠት ሓላፊነት እንዳለበት በደንብ አጥኚ ኮሚቴው ማሻሻያ ረቂቅ ላይ መስፈሩ ታውቋል፡፡

ይኹንና ‹‹ጥበቃና ጥንቃቄ›› በሚል ፓትርያርኩ እንደ መመሪያ ያቀረቧቸው ድንጋጌዎችና ግዴታዎች እንዲሁም ከልዩ ጽ/ቤታቸው ማኅበሩን አስመልክቶ በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎች የማኅበሩን አገልግሎት የማቀጨጭ፣ በሒደትም አዳክሞ የማስቆም ውጤት ሊኖራቸው እንደሚችል ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡

የማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ፣ ቅ/ሲኖዶሱ የማኅበሩ ደንብ እንዲሻሻል ግንቦት 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ባካሔደው ስብሰባ÷ ማኅበሩ ከጊዜው ጋር የሚሔድ፣ አገልግሎቱና አደረጃጀቱ የደረሰበትን ስፋትና ዕድገት የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ልማት የሚጠቅም ድርጅታዊ መዋቅር እንደሚያስፈልገው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት አምስት ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገለልተኛ የሕግ ባለሞያዎችና የማኅበሩ አባላት በታከሉበት አጥኚ ኮሚቴ የጋራ ጥናት የተዘጋጀ መኾኑ ተመልክቷል፡፡
በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም. በበጎ ፈቃድ በተሰበሰቡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተመሠረተው ማኅበሩ፤ እየተመራ ያለው ቅ/ሲኖዶስ በ1994 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ አሻሽሎ በሰጠው መተዳደርያ ደንብ ሲኾን አሁን የተሻሻለው ረቂቅ ተመርምሮ ባለመጽደቁ በነባሩ ደንብ እየተመራ ለመቀጠል እንደሚገደድ ተመልክቷል፡፡

3 Comments

  1. ቅዱስ መስቀሉን ይዘው ሲታዩ ለቅድስና የቆሙ ይመስላሉ። ጺማቸውን አንዥርገው ሲታዩ የበቁ መንኩሴ ያስመስላቸዋል። ብዙዎቹ አባቶች በዚህ አይነት ለመታየት የቀን ከሌት ህልማቸው ነው። ግን ግን ባዶ ናቸው የተጠሩበትን ሳይሆን በውስጥ ለውስጥ የተመለመሉበትን ስራ ለመስራት ደፋ ቀና ይላሉ ።አንዳንዶች እንዲያውም ካድሬነታቸው ተወቀ አልታወቀ ደንታም የላቸው ።ልባቸው በሞራ የተሸፈነ የክርስቶስን በጎች ለመበተን ሰርገው የገቡ ተናካሽ ተኩላዎች ሆነው የሄው መንጋውን በማተራመስና በመበተን ድፍን 23 አመታት አለፉ። ዋናው ፓትሪያርክ ትብየው ወደዚህ ከመምጣታቸው በፊት በአስነዋሪ ስራ የተትበትቡ እንደሆነ ይታወቃል። እኝህን እንከን በ እንከን የተተበተቡ አባት ተብየን ነው ሌሎች አባት ነን ባዮች የመረጡት አመራረጡ ላይ ጫና ቢኖርባቸውም።
    ግን ግን መነኮሰ ማለት ሞተ እንደሆነ ነው የሚታወቀው ። አባት ተብየዎች ግን ራሳቸውን ሳይገሉ ለክርስቶስ ቅዱስ ጥሪ ሳይበቁ ም እመናንን ያታለሉ መስላቸው በክርስቶስ ቤት ወንጀል እየፈጸሙ አሉ። ለአንድ አባት ስለ እውነት አለመቆም ወይም አለመድፈር በራሱ ህጢያት ነውና። እንደው ከነ እስክንድር ነጋ ፡ ከነ አንዱአለም አራጌ ከነ በቀለ ገርባ ፡ ከነር እዮት አለሙ ከሌሎችም በ እስር ላይ ከሚገኙት የ እውነት አርበኞችን ያክል ወኔ ማጣታቸው ያስተዛዝባል ማለት ብቻ ሳይሆን የኛ አይደላችሁም ሊባሉ ይገባቸዋል። ማህበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ መሮጥ የማንን አላማ ለማጽፈጸም ነው?
    እውነት እውነት እንላለን ቅዱስ መስቀሉ በናንተ ባልተቀድሳችሁት ላይ ተጻራሪ እንደሚሆን ልታውቁት ይገባል። ስለ ቤተክርስቲያናም አንድነት የቆማችሁ አባቶች በአንድነት ሆናችሁ በቤተክርስዪያና ላይ የሚፈጸመውን ደባ ለም እመናን የማሳወቅ መንፈሳዊም ታሪካዊም ግዴታ አለባችሁ።በሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ብቻ ተቃውሞ ማቅረብ በቂ አይደለም። ከምንም በላይ አንድ መንፈሳዊ አባት ትህትና እንጂ እብሪት መገለጫው ሊሆን አይገባም።እናንተ ባታፍሩም እኛ አፍረንባችሃል።

  2. ያሳዝናል አስተያየት ስንሰነዝር ማን መሆንችንን መርሳታችን የሰውን ሀጽያት ስንናገር ማሰብ አለብን ለመሆኑ አንተማን ነህ መጽሀፉ አንድም ጸድቅ የለም ነው ያለው አንተ መሳሪያ ይዘው መዋጋት አለባቸው ነው የምትለው ባክህ በውኑ ክርስትያን ከሆንክ ጸልይላቸው መጀመሪያ ራስህን መርምር አምላክ ካባቶቻችን ጋር ይሁን::

  3. አየሽ እህት ሀይማኖት እንዳንቺ አይነቶቹ የዋሆች ስለበዙ እነዚህ አባት ነን ባዮች አጃቢ እና የሚሰግድላቸው ስላላጡ የሚሰሩት ሁሉ ትክክል እየመሰላቸው ነው በአንድነታ የምትታወቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልትከፋፈል የበቃችው። ስለ እኔ ማንነት ልግለጽልሽ መሰለኝ አንተ ማነህ ስላልሽኝ። በህጢያት ባህር ውስጥ የምዋኝ ህጢያተኛ ነኝ።ግን እንደዛ በመሆኑ አስተያየት አትስጥ ልባል ግን አይገባም።
    ምነው አንቺ ቸኮልሽሳ እኔ መሳሪያ ይዘው ይዋጉ የሚል ወጣኝ እውነተኛ አባቶች ያጋልጡ ነው ያልኩት መሳሪያቸው እኮ ቅዱስ መስቀሉ ነው ግን አረከሱት ነው እያልኩ ያለሁት። ራስህን መርምር ላልሽኝ ህጢያተኛ ነኝ ያልኩት ላይ ተመልሳል። እኔ ሀጢያተኛ ብሆንም ለመንጋው መጥፋት ምክንያት አይደለሁም። አየሽ እነሱ በትልቁ ተራራ ላይ ሆነው በአደባባይ የሚዋሹና እጆቻቸው በደም ከተጨማለቁ ጋር አብረው ቤተክርስቲያና እንድትጠፋ ሲሰሩ ዝም ማለት ሀጢያት ነው የዋልድባ ገዳም ሲታረስና መነኮሳት ሲፈናቀሉ አይቶ እንዳላየ መሆን ሌላው ሀጢያት ነው ብዙ ማለት የቻላል እኔ ምንም ነኝ እነሱ ግን ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጋ ሃዝበ ክርስቲያን አባቶች ናቸው እነሱ የሚታዩ የሚደመጡ ናቸው። እኔ ግን አሁንም ምንም ነኝ ። በጣም በጣም ልዩነት አለን። ይሄ የአንቺ አይነቱ አስተሳሰብ በደንብ እንደጠቀማቸው ያውቃሉ። ህዝበ ም እመናንን ሲጸልያላቸው እነሱ ግን የክርስቶስ ለመሆን አልቻሉም። ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ እንደ ዴማስ አለም የበለጠችባቸው ናቸው፡፤ ልዩነቱ ዴማስ ከቤተክርስቲያን እ ራሱን ሲያገል እነዚህ ቤተክርስቲያና ላይ ተጣብቀው ነው ለም እመን መሰናክል የሆኑ። አንገታቸው ላይ መጅ አስረው ወደ ባህር ቢገቡ የሻላቸዋል የተባሉት እንደነዚህ አይነቶቹ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዋች ናቸው።
    እውነት ለመናገር ምን ሀጢያተኛ ብሆን ለቤተክርስቲያን ቀናተኛ ነኝ የክርስቶስንም ፍቅር የምራብ ነኝ በውስጤ መልካም የሆነውን ሁሉ አልማለሁ ግን ደግሞ መንገዱ የጠፋበት ሰው ታውቂያለሽ በቃ እንደዛ ነኝ በ እርግጠኝነት አሁንም ውስጤ የሚነግረኝ መንገዱ ጠፍቶብኝ የምቀር አለመሆኔን ነው። ይህን ስልሽ በራሴ ሳይሆን ከክርስቶስ የተነሳ እንጂ

Comments are closed.

Melaku Fenta and Gebrewahid Woldegiorgis
Previous Story

በነአቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ 28 ክሶች እንዲሻሻሉ ፍርድ ቤት በየነ

mata manchester united
Next Story

Sport: የማን.ዩናይትዱ ማታ አሻግሮ እየተመለከተ ነው

Latest from Blog

“መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የሚለው የዲያስፖራ ከንቱ አታካራ! – ክፍል ሁለት

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) በአንዳንድ ስብሰባዎችና የሕዝብ መገናኛ መድረኮች የሚታየው የአንዳንድ ዲያስፖራዎች  “መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የበከተ ከንቱ አታካራ በልጅነታችን ወላጆቻችን ትምህርት እንዲሆነን ይተርኩልን የነበረውን ከጫጉላ ወጥተው ጎጆ ለመመስረት የታከቱ ሁለት ያልበሰሉ ባልና ሚስትን ታሪክ

መነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ እና ወያኔያዊ መሠረቱ

የማይወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል። የዛሬን አያድርገውና የትግሬ ልሂቆች “ትግራይ የጦቢያ መሠረት ናት ።  ጦቢያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይ ያለ ጦቢያ ሊታሰቡ አይችሉም” በማለት ጦቢያዊ ከኛ ወዲያ ላሳር እያሉ አለቅጥ ይመጻደቁ፣ ይኩራሩ፣ ይታበዩ ነበር። ወያኔ

አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባሉ

ለአመታት በእረስር ላይ የሚገኙት  አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና የዕርስ በዕርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀሎች ጥፋተኛ መባላቸው ታውቋል፡፡ አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱበት ክሶች በዛሬ ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ

ከ”ችርቻሮ” ድል አልፎ ለመሄድ የአንድነት አስፈላጊነት – ግርማ ካሳ

በአሁኑ ጊዜ ሁለት የፋኖ አሰላለፎች አሉ:: መኖር ያልነበረበት:: አንከር ሜዲያ ከሁለቱም አሰላለፎች፣ ሁለት ፋኖ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ሁለቱን አደመጥኩ፡፡ በሰማሁት ነገር ተደስቻለሁ:: ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅም አድርጎኛል:: የአማራ ህዝባዊ ድርጅት የፖለቲካ
Go toTop