May 31, 2014
17 mins read

Sport: የማን.ዩናይትዱ ማታ አሻግሮ እየተመለከተ ነው

ዓመቱ ለማንቸስተር ዩናይትድ አስከፊ ነበር፡፡ ሪከርድ በሆነ ዋጋ ዩናይትድን ለተቀላቀለው ሁዋን ማታም ቢሆን የተሻለ አልነበረም፡፡ ስፔናዊው ፕሌይሜከር የቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ነበር፡፡ ለሁለቱ ተከታታይ ዓመታትም የቼልሲ ምርጥ ተጨዋችነት ክብርን ተቀዳጅቷል፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆ ግን በዋናው ቡድን የመሰለፍ ዕድል ነፈጉት፡፡ በኋላ ላይም ውጤቱን እያሽቆለቆለ ለነበረው ዩናይትድ ተሸጠ፡፡ በዚህም ምክንያት ማታ ገና ከአሁኑ መጪውን የውድድር ዘመን አሻግሮ መመልከት ጀምሯል፡፡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ዩናይትድ በአውሮፓ መድረክ አለመሳተፉ በሊጉ ከአናት የመቀመጥ ዕድሉን ያሰፋዋል ብሎም ያምናል፡፡ ክለቡንም ሆነ እርሱን መከራ እንደመከራቸውም ያስባል፡፡ ‹‹በቼልሲ ያለፍኩበት ሁኔታ ከዚህ ቀደም በተጨዋችነት ዘመኔ አጋጥሞኝ የማያውቅ ነገር ነው፡፡ በቋሚነት አልሰለፍም ነበር፡፡ ነገር ግን ይበልጥ ጠንካራ እንዳደረገኝ አስባለሁ፡፡ በመከራ ውስጥ ስታልፍ በራስህ ያለህን እምነት ልታጣ ትችላለህ፡፡ እኔ ግን በልበ ሙሉነቴ ፀናሁ፡፡ ዓላማዎቼንም አልሳትኩም›› በማለት በሰማያዊዎቹ ቤት ያጋጠመውን ያስታውሳል፡፡

ሊቨርል በዚህ የውድድር ዘመን ተነቃቅቷል፡፡ ወጥ አቋምም አበርክቷል፡፡ ለዚህ ስኬት በዋናነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ በአውሮፓ መድረክ ተሳትፎ አለማድረጉ ነው፡፡ ይህን የተገነዘበው ማታ ዩናይትድ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የሊቨርፑልን ገድል ይደግማል ብሎ ያምናል፡፡ ‹‹እርግጥ በቻምፒዮንስ ሊግ ብጫወት እመርጥ ነበር፡፡ ያ አለመሆኑ ግን በሊጉ የተሻለ ዕድል እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ሊቨርልን እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል፡፡ በቻምፒዮንስ ሊግ ባለመጫወቱ እስከ ውድድር ዘመኑ ፍፃሜ ድረስ ለዋንጫ በሚደረገው ትንቅንቅ ዋነኛ ተዋናይ መሆን ችሏል›› ሲል ሃሳቡን በምሳሌ ያጠናክራል፡፡

ማታ ቻምፒዮንስ ሊግን አሸንፏል፡፡ ይህንንም የሚያረጋግጥ ሜዳሊያ በእጁ ላይ ይገኛል፡፡ በሙኒክ የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ዲዲዬ ድሮግባ በግንባሩ ገጭቶ ላስቆጠራት ጎል ኳሷን አመቻችቶ ያቀበለውም እርሱ ነበር፡፡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ወደዚህ ዝነኛ ውድድር ዳግም ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት የሚመራው ማን እንደሆነ ግን በእርግጠንነት መናገር አይቻልም፡፡

በልንቱ እንደ አርአያ ይመለከተው ከነበረው ሪያን ጊግስ ጋር የጠበቀ ትስስር እንዳላቸው ግልፅ ነው፡፡ ‹‹አርአያ የሆኑህን ሰዎች ልታገኛቸው አይገባም›› የሚለው ያረጀ ያፈጀ አባባል በዚህ አውድ የሚሰራ አይመስልም፡፡ ‹‹ክለቡን እንደተቀላቀልኩ በልጅነቴ የእኔ አርአያ እርሱ እንደነበር ነገርኩት፡፡ እርሱም ወደዚህ በመምጣትህ ደስ ብሎኛል፡፡ በመጠኑም ቢሆን ግን ቅሬታ አለብኝ፡፡ ምክንያቱም አንተ በዚህ በመገኘትህ እኔ በክለቡ ሁለተኛው ምርጥ የግራ እግር ተጨዋች ሆንኩ አለኝ፡፡ ያ ሊሆን እደማይችል ነገርኩት፡፡ በታዳጊነቱ በቅርበት እከታተለው የነበረ ተጨዋች ነው፡፡ ኳስን የሚቆጣጠርበትን እና የሚገፋበትን መንገድ እወድደዋለሁ፡፡ እውነተኛ የግራ እግር የክንፍ ተጨዋች ነው፡፡ ፈጣን ነው፡፡ አንድ ለአንድ በምትገናኝበት ወቅት ደግሞ ለማቆም ትቸገራለህ፡፡ በዚያ ላይ ጎሎችን ያስቆጥራ፡፡ አሁን ግን የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ሆኖ የቡድን አጋሬ እና አሰልጣኜ ሆኗል›› ሲል ለዌልሳዊው ያለውን ክብር ይገልፃል፡፡
ማታ ጊግስ በዩናይትድ አሰልጣኝነት ብዙም እንደማይቆይ ያውቃል፡፡ መጪው ጊዜ ይዞት የሚመጣውንም ነገር በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ ስለ ሉዊ ቫን ሃል ሲጠየቅ ‹‹ከእርሱ ጋር ተገናኝቼ አላውቅም፡፡ ምን አይነት ታሪክ እንዳለው ግን አውቃለሁ፡፡ ስላሸነፋቸው ዋንጫዎች እና የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኛችን ስላልሆነ ሰው ማውራት ተገቢ አይመስለኝም›› ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡
ሆላንዳዊው ጊግስን ተክተው የኦልድ ትራፎርዱን ክለብ የሚረከቡ ከሆነ በሶስት የውድድር ዘመን ማታን ያሰለጠኑ ሰባተኛው አሰልጣን ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሱት ትዕግስት አልባ የሆነው የእንግሊዝ እግርኳስ እና ለትንሿ ነገር የተጋነነ ምላሽ በመስጠት የሚታወቁት የስፔን ክለቦች ፕሬዝዳንቶች ናቸው፡፡

ታዲያ ማታ እነዚህን አሰልጣኞች እንዴት ያነፃፅራቸዋል? ‹‹ወደ እንግሊዝ ያመጣኝ አንድሬ ቪያስ ቦአስ ነው፡፡ በእኔ ላይም ትልቅ እምነት ነበረው፡፡ ወጣት ነው፡፡ ትልቅ ራዕይም ነበረው፡፡ ቡድኑ ማራኪ እና አሸናፊ የሆነ እግርኳስን እንዲጫወት ይፈልግ ነበር፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ለእርሱ ክብር አለኝ፡፡ ሮቤርቶ ዲ ማቴዮ በመጠኑ ከጊግስ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የቀድሞ ተጨዋች እና ረዳት አሰልጣኝ ነበር፡፡ ቪያስ ቦአስ ሲለቀቅ እርሱ ክለቡን ተረከበ፡፡ ታላቅ ስኬትም አስመዘገበ፡፡ የቻምፒዮንስ ሊግ እና የኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችን ማንሳት ቻልን፡፡ ከእኔ ጋርም ሆነ ከተቀሩት የቡድኑ አባላት ጋር መልካም ግንኙነት ነበረው፡፡ ህብረት እና ቁርጠኝነት እንዲኖረንም አድርጓል፡፡

‹‹ከዚያም ከራፋኤል ቤኒቴዝ ጋር በመሆን የዩሮፓ ሊግን አሸነፍን፡፡ በቀደመው ታሪኩ የተነሳ መጀመሪያ አካባቢ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሆነውበት ነበር፡፡ ነገር ግን ያህንን ሁሉ ተቋቁሞ መልካም ስራ እንደሰራ አስባለሁ፡፡ ፕሮፌሽናል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ክለቡ ከዚህ ቀደም አሸንፎት የማያውቀውን ዋንጫ እንዲያነሳ አስቻለ›› በማለት አብሯቸው ውጤታማ መሆን ስለቻላቸው አሰልጣኞች በአድናቆት ይናገራል፡፡

ዘንድሮ ደግሞ ጆዜ ሞውሪንሆን ዳግም ሰማያዊዎቹን ተቀላቀሉ፡፡ ነገር ግን ከማታ ጋር ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ ለምን? ወሳኙ ነገር ግንኙነት አለመመስረታቸው ይመስላል፡፡ ነገር ግን እርሱም ቢሆን የአለመግባባቱ ምልክት እንጂ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ ለምን ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ እንዳደረጉት ሞውሪንሆን ጠይቋቸው ያውቅ እንደሆነ ሲጠየቅ በፍፁም፡፡ አስፈላጊ መስሎም አልታየኝም ሲል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ሞውሪንሆስ ቢሆኑ ለምን በቡድኑ ውስጥ ቦታ እንዳጣ አብራርተውለት ይሆን? በጭራሽ በማለት ስፔናዊው አጭር መልስ ይሰጣል፡፡
በመጨረሻም ቼልሲ እና ዩናይትድ ከተደራደሩ በኋላ በጃንዋሪ 25 በሄሊኮፕተር ካሪንግተን ደረሰ፡፡ ‹‹ለቼልሲ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ዳይሬክተሮቹ፣ ባለቤቱ እና ደጋፊዎቹ ከመጀመሪያዋ ቀን አንስቶ እስከ መጨረሻዋ ዕለት ለእኔ መልካሞች ነበሩ፡፡ መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ፡፡ በዚያ በርካታ ወዳጆች አሉኝ፡፡ ሴዛር አዝፒሊኩኤታ፣ ፈርናንዶ ቶሬስ፣ ዴቪድ ልዊዝ እና ኦስካር ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከላምፓርድ እና ቴሪ ጋርም በብዛት እንነጋገራለን፡፡ ወደ ሶስት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አብሬያቸው ነበርኩ፡፡ በመሆኑም በጎ በጎው ነገር እንዲገጥማቸው እመኛለሁ›› ሲል የቀድሞ ክለቡን በመልካም ያነሳል፡፡

ክለቡን ለቅቆ በሄደበት ወቅት ለደጋፊዎች በፃፈው የስንብት እና የምስጋና ደብዳቤም ኩራት ይሰማዋል፡፡ ‹‹ያንን ያደረግኩት ገፅታዬን ለመገንባት አይደለም፡፡ በጥሩ ሁኔታ ሲንከባከቡኝ ስለነበሩ ደጋፊዎች እና ስለ ቼልሲ የሚሰማኝን መግለፅ በመፈለጌ ከልብ የመነጨ ነበር›› በማለት ያንን ለማድረግ የተነሳሳበትን ምክንያት ይገልፃል፡፡

እንደህ በይፋ ለባላንጣ ክለብ ደጋፊዎች ያለውን ፍቅር መግፁ ከቀያይ ሰይጣናቱ ደጋፊዎች ጋር ሊያቃቅረው ይችላል ተብሎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ድርጊቱ የሚያሳየው የሰውነቱን ልክ ነው፡፡ ከቀዮቹ ጋር ዋንጫዎችን ለማሸነፍ ጓጉቷል፡፡ የሚሰለፍበትን ቦታ አስመልክቶ ተንታኞች ብዙ ማውራታቸውንም የወደደው አይመስልም፡፡

‹‹እራሴን የቀኝ ክፍን ተጨዋች አድርጌ እንደማልቆጥር የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በግራ እግሬ ወደ ውስጥ ሰብሬ የምገባበትን ዕድል ያጎናፅፈኛል፡፡ ቫሌንሲያ በነበርኩበት ወቅት በግራ መስመር ተጫውቼ አውቃለሁ፡፡ በብሔራዊ ቡድኑም እንደዚው ምርጥ ብቃቴን የማሳየው ግን ከአጥቂዎቼ ጀርባ ስሰለፍ ነው፡፡ ነገር ግን በሌሎቹም ሁለት ቦታዎችም መልካም እንቅስቃሴ እንደማደርግ አስባለሁ፡፡

ማታ ከዩናይትድ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴ ሂያ ጋር ሆኖ የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮናን አሸንፏል፡፡ የዩናይትድ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው ዴ ሂያ ከኦልድት ትራፎርድ ታላላቅ ተጨዋቾች ተርታ ሊያሰልፈው የሚችል የአዕምሮ ዝግጅት እንዳለውም ያምናል፡፡ ‹‹በራሱ ከፍተኛ እምነት አለው፡፡ ያ ደግሞ እጅግ አስፈላጊ ፀጋ ነው፡፡ ምንም ነገር ተፅዕኖ እንዲያሳድርበት አይፈቅድም፡፡ ስህተት በሚፈፅምበት ወቅት ማጥፋቱን ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን ስህተቱን በማምሰልሰል ለዳግም ጥፋት አይዳረግም፡፡ ስህተቱን የሚጠቀመው ሌላ ስህተት ላለመፈፀም እንደመማሪያ አድርጎ ነው፡፡ በዚያ ላይ በጣም የተረጋጋ ነው›› በማለት ለአገሩ ልጅ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡

‹‹በዚህ ዙሪያ ከጓደኞቼ ጋር ሳወራ የሊዮኔል ሜሲን ባህሪይን እንደ ምሳሌ ጠቀሱልኝ፡፡ ስለምንም ነገር የሚጨነቅ አይመስልም ሲሉም በአንድ አረፍተ ነገር ገለፁት፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ጎሎችን ያስቆጥራል፡፡ ነገር ግን ምንም የተለየ ነገር እንዳልተፈጠረ ሁሉ ዘና ይላል፡፡ ምናልባት ያ መልካም ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ የምትኖረው በከፍተኛ ጫና ውስጥ ነው፡፡ ሁልጊዜም ለራስህ ብለህ እንደሆንክ የምትነግረው ከሆነ በሆነ አጋጣሚ ስህተት ስትሰራ ለክፉ ጉዳት ትጋለጣለህ፡፡ በመሆኑም ሁሉም ነገር የተለመደ አድርጎ መመልከት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህም የታላላቅ ተጨዋቾች ብቃት እንደሆነ አስባለሁ››

በቀዩ የስፔን ማልያ እንዳደረጉት ሁሉ ዴ ሂያ እና ማታ በቀዩ የዩናይትድ ማልያ ያሸንፉ ይሆን? በራስ መተማመን ከኦልድ ትራፎርድ ርቋል፡፡ ከ13 ወራት በፊት ዩናይትድ በኦልድ ትራፎርድ 3-0 እየተመራ ቆይቶ 4-3 ማሸነፍ ይችል ነበር፡፡ አሁን ግን እንዲህ አይነቱን ውጤት ማስመዝገብ ተስኖታል፡፡ ቡድኑ በዚህ የውድድር ዘመን የጎደለው ዋነኛው ነገር በራስ መተማመን ነው፡፡ ነገር ግን ተጫዋቾቹም ሆነ ክለቡ እንደዚሁም ደጋፊዎች ይህንን የአሸናፊነት ስነ ልቦና መልሰው እንደሚያገኙት አምናለሁ፡፡ ይህ ክለብ ውጤት እንዲያስመዝግብ ከፍተኛ ጫና ይደረግበታል፡፡ በዚህ የውድድር ዘመን ዋንጫዎችን ማንሳት ካልቻልክ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ስኬታማ እንድትሆን ይጠበቃል፡፡ በመጪው የውድድር ዘመን ይህን ባህላችንን አላማጣታችን ማስመስከር አለብን፡፡ ክለቡ ተወዳዳሪነቱን እና ማንነቱን እንዳላጣ ማሳያት ይኖርብናል በማለት ሃሳቡን ቋጭቷል፡፡

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop