የእስረኛው ‹‹ጋዜጠኝነት›› ሌላ ፈተና

ጽዮን ግርማ
tsiongir@gmail.com
(ፋክት መጽሔት ላይ የታተመ)

የ2012ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳታዊ ምርጫ ከመከናወኑ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ስለምርጫውና የአሜሪካ የጋዜጠኝነት ኹናቴ እንዲወያዩ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት አዳራሽ ከተጋበዙና ከሰማንያ የዓለም አገሮች ከተውጣጡ አንድ መቶ ሠላሣ ተሳታፊ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ነበርኹ፡፡ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ከተጋበዙ የአሜሪካ አንጋፋ ጋዜጠኞች መካከል ታዋቂው የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ቦብ ውድዋርድ አንዱ ነበር፡፡
ቦብ በስቴት ዲፓርትመንት ሕንፃ አዳራሽ ከሌላ አገር ለመጡ ጋዜጠኞች፤ በምርመራ ጋዜጠኝነት ሥር አጨቃጫቂና አንገብጋቢ ጉዳዮችን ሲዘግቡ በአሜሪካ መንግሥት የሚያጋጥማቸውን ፈተና እየዘረዘረ፣ ዓለም የሚደነቅበትን የአገሩን የመናገርና የመጻፍ ነፃነትና ‹ዴሞክራሲያዊ› የምርጫ ሂደት የፕሬዝዳንት ኦባማን ስም ሳይቀር በስም እየጠቀሰ በሒስ ሲሰልቀው ከፍርሃት ነፃ በኾነ ከፍተኛ የራስ መተማመን መንፈስ ተሞልቶ ነበር፡፡
በወቅቱ የስቴት ዲፓርትመንት ከፍተኛ ባለሥልጣናት “The price of politics” የሚለውን ባለሠላሳ ዶላር መጽሐፉን ፈርሞ በቦታው ለተገኘነው ጋዜጠኞች በስጦታ እንዳበረከተልን ተናግረው ሲያስጨበጭቡን ቦብ በስጨት ብሎ በማቋረጥ፣ ‹‹መጽሐፌን ለማንም በነፃ አልሰጠኹም፤ ስቴት ዲፓርትመንቱ ነው ገዝቶ የሰጣችኹ›› በማለት ሲያሸማቅቃቸው በፈገግታ ነበር ያለፉት፡፡ እንግዲህ የዓለም ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አዳራሽ አንድ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ መሪውንና ሥርዓቱን ሲተች በምናብ ማየት ነው!!

ውይይቱ ሲያበቃም ለጋዜጠኛው ክብር ሲባል በየቡድናችን እየተጠራን ባለበት ሔደን የማስታወሻ ፎቶ እንድንነሣ ስንጋበዝ ባለሥልጣናቱ ለጋዜጠኛው ያላቸው ክብር በግልጽ ይታይ ነበር፡፡ ሞጋች ጋዜጠኞች ከሚሰደዱበት፣ ከሚታሰሩበት አልያም በፍራቻ ሥራ ከሚያቆሙበት ወይም ከፍ ዝቅ ተደርገው እየተመናጨቁ መረጃ ከሚከለከሉበት፣ ከፖለቲካዊና ገዢዎችን ከሚነካ ዘገባ ይልቅ ወደ ማኅበራዊና መዝናኛ ጉዳዮች እንዲያተኩሩ በእጅ አዙር ከሚገደድበት አገር ለሔደች ለእንደኔ ዓይነቷ ጋዜጠኛ የስቴት ዲፓርትመንቱ ባለሥልጣናት ለአንጋፋው የዋሽንግትን ፖስት ጋዜጠኛ ቦብ ውድዋርድ የቸሩት አክብሮት ቢያስደምመኝም የጋዜጠኝነት ሞያ እንዲያ ተከብሮ የሚያስከብር መኾኑን አላጣኹትም ነበር፡፡
ጋዜጠኝነት እንደሞያ እጅግ የተከበረ ነው፡፡ ጋዜጠኝነት በአቀራረቡ ባለብዙ መልክ ቢኾንም የብልሹ አስተዳደርና አሠራር ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት፣ ከሕዝብ የተሰወሩ በደሎችን ለማጋለጥ፣ ከሕግና ሥርዓት ውጭ የኾኑ ባለሥልጣናትን በዐደባባይ ለመተቸትና ለማጋለጥ፣ ለሕዝብ ዋስ ጠበቃ በመኾን የሚያገለግል በተለምዶ አጠራር ‹አራተኛ መንግሥት› ነው፡፡
ከሚዛናዊነት፣ እውነትና ፍትሕ ጋር የሚሠራ “ሞያዊ ጋዜጠኛነት” (Professional journalism) ለዴሞክራሲዊ አስተሳሰብና ተግባር ዋናው አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ ከፍርሃትና ስጋት የተጠበቀ፣ ከተገዢነትና አገልጋይነት የጸዳ ጋዜጠኝነት የሚወደድ ሞያ ነው፡፡ ሞያዊ ጋዜጠኝነት አገልጋይነቱ በቀጥታ ለሕዝብ ስለኾነ ኹሌም ለውጥ በማምጣት ሒደት ውስጥ ዋና ተሳታፊ ነው፡፡ ሞያው ነጻ በወጣባቸው አገሮችም ልክ እንደ ቦብ ውድዋርድ ተከብረው የሚያስከብሩ ጋዜጠኞች ይፈጠራሉ፡፡
በጋዜጠኝነት ሞያ የኢትዮጵያን ነባራዊ ኹኔታ ብናይ፤በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በአገሪቱ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንደተከበረ በተለያየ መንገድ ያውጃል፡፡ መልሶ ደግሞ ይህን መብት ገደብ አልባ በኾኑ የተለያዩ መንገዶች ሲያፍነውና ሲጨቁነው ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው አሠራር በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ነጻነት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ወድቋል፡፡ ለግል የተፈቀዱት ከአንድ እጅ ጣቶች የማያልፉ ሬዲዮ ጣቢያዎችም ቢኾኑ ነፃነታቸው የተረጋገጠው በመዝናኛ ዝግጅቶችና በጥቂት የማኅበራዊ ጉዳይ ዘገባዎች ብቻ ነው፡፡ የኅትመት ብዙኃን መገናኛን በሚመለከትም በርካታ ጋዜጣና መጽሔቶች በየወቅቱ ቢታዩም በተለያየ ምክንያት ስለሚቋረጡ በገበያው ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
እስረኛው ‹‹ጋዜጠኝነት›› በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኝነት ሞያ በራሱ ነፃ ያልወጣ እስረኛ ነው፡፡ በገዢው ግንባር ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ብዙኃን መገናኛዎች በመንግሥት ጥቅም ልክ የሚሠሩና ድጋፍ ብቻ የሚሰጡበት ‹‹ጋዜጠኝነት›› ነው፡፡ ከግንባሩ አስተሳሰብና አሠራር የሚነጨው ይኸው የሞያው እስረኝነት ላለፉት ኻያ ሦስት ዓመታት ሲሠራበት የቆየ ነውና አያጠያይቅም፡፡ በግለሰብ ባለቤትነት በሚመሩ የኅትመት ብዙኃን መገናኛዎችና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጀመረው የዲጂታል ሚዲያ ላይ ተግባራዊ የሚደረገው ጋዜጠኝነትም በበርካታ ተጽዕኖች ሥር የወደቀ ጋዜጠኝነት ነው፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 ጀምሮ ጠንካራ ክንድ ተጭኖ ይዞታል፡፡
የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚሰጧቸው መግለጫዎች ጋዜጠኛውን የሚያንቋሽሹ ቃላትን በመጠቀም በግል ብዙኃን መገናኛ ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች አገሪቷን ወደተሳሳተ መንገድ የሚመሩ አጥፊዎች አድርጎ መሣል የተለመደ ነው፡፡ የወንጀል ሕጉ ውስጥ ጋዜጠኛን በሚመለከት የተካተቱት አንቀጾች፣ የመገናኛ ብዙኃን ዐዋጅና የፀረ ሽብር ዐዋጁ ጋዜጠኝነትን አስረው የሚያስቀምጡ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያ አማካይነት በየዕለቱ በጋዜጠኞች ላይ የወቀሳ ናዳ በማውረድ ሞያው ነፃነቱን እንዲያጣ ያደርጉታል፡፡ በመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች የነፃነታቸው ጉዳይ ሳያሳስባቸው በግል የሚሠሩ ጋዜጠኞችን የሚያንኳስስ ተደጋጋሚ ዘገባ ማቅረብን ለአለቆቻቸው እንደ እጅ መንሻ ይጠቀሙበታል፡፡
በኾነው ባልኾነው ጋዜጠኞችን እየጠሩ ማስፈራራት፣ መክሠሥና ማሰር ሞያውን የበለጠ እንዲኮሰምን ያደርገዋል፡፡ መተቸትን አብዝቶ የሚጠላው መንግሥት በአገዛዙና በሥርዓቱ ላይ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች ሲወጡ ‹‹ከጀርባቸው እገሌ የሚባል አሸባሪ ድርጅት አለ›› ወይም ደግሞ ‹‹እገሌ ከሚባል አገሪቱን ለማተራመስ ከሚሠራ አካል ላይ ገንዘብ ተቀብለዋል›› በሚል ፈርጆ ሞያውን አስሮ ያስቀምጠዋል፡፡ ለመረጃ ነፃነትና ለጋዜጠኝነት ሞያ ድጋፍ በመስጠት ከማሳደግ ይልቅ ገና ብቅ ሳይል አናት አናቱን በማለት እዛው ያስቀረዋል፡፡
በሌላ በኩል የመንግሥት ተፎካካሪ የኾኑ የተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶችም ምንም እንኳን ራሳቸው በበርካታ የመንግሥት ጫና ሥር የሚገኙ ቢኾኑም ትችት የሚያቀርብባቸውን ጋዜጠኛ ላይ ተጽዕኖ ለማሳረፍ አይሰንፉም፡፡ እነርሱን የሚተች ጋዜጠኛ ቅጥያ ይለጠፍበትና የመንግሥት ደጋፊ ተደርጎ ይፈረጃል፡፡ በተለይ እርስ በርስ ስምምነት በሚያጡበት ጊዜ ኹሉም ጋዜጠኛውን ወደ ራሳቸው ጎራ ለመጎተት ይሞክራሉ፡፡ እንቢተኝነትን ያሳየ ወይም ደግሞ ድርጊቱን የተቃወመ ጋዜጠኛ ስሙ ከአንዱ ድርጅት ወይም ግለሰብ ጋር ተዳብሎ ሞያዊ ክብሩን ይገፈፋል፡፡
ጥቂት በማይባሉ አንባብያን ዘንድ ደግሞ ጋዜጠኛው ያቀረበውን መረጃ ትክክለኛነት በሒደት መዝኖ እውነቱን ከማወቅ ይልቅ ፍረጃውን ተከትሎ አብሮ የመዝመም ዝንባሌ ይታያል፡፡ በፍረጃ ፍዳውን ባየ ጋዜጠኛ ላይ ውግዘት ይጨምርበታል፡፡ የማንበብ ፍላጎቱም የሚዘልቀውም የኾነውን የተፈጠረውን ሳይኾን እርሱ እንዲኾን የሚፈልገውን ብቻ ነው፡፡ ጉዳያቸው ብዙኃን መገናኛ ላይ ለመቅረብ ብቁ የኾነም ያልኾነም ግለሰቦች፣ የንግድ ተቋማት፣ አርቲስቶችና ሌሎች አካላትም የሚጻፉት ነገሮች ኹሉ በእነርሱ ፍላጎት ልክ እንዲኾን ይወተውታሉ፡፡ ከፍላጎታቸው ውጭ ከተጻፈና ከተዘገበ ደግሞ ከቻሉ መክሰስ ካልኾነ ደግሞ ጋዜጠኛውን ማንቋሸሽና ጠልፎ ለመጣል ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ምንም እንኳን ሕትመቱ ከመውጣቱ በፊት ቅድመ ምርመራ (censorship) ባይኖርም ከማቀድና ከመጻፍ በፊት ጋዜጠኛው በግሉ ፤የራስ በራስ ምርመራ (self censorship) በማድረግ የሞያውን ነጻነት አሳልፎ ይሰጣል፡፡
ሞያው ነጻነት ባጣ ቁጥር ዕድገቱ እየኮሰመነ ስለሚሄድ የሞያው ተፈላጊነት ይቀንሳል፡፡ በዕውቀትና በክህሎት ብቁ የኾኑ አብዛኞቹ ባለሞዎች ሥራቸውን ይቀይራሉ አሊያም አገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡ ዕለት ከዕለት ሞያውን የሚቀላቀሉት ባለሞያዎችም ብቃት አነስተኛ ስለኾነ ቁንጽል የሆኑ የጋዜጠኝነት መርሆዎችን ብቻ አንጠልጥለው በመያዝ ሞያውን የበለጠ ያዘቅጡታል፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ሞያውን በተቀላቀሉ ቁጥር ገዢው ፓርቲ ይደሰታል፡፡ የጋዜጠኝነት መርሕ ተጥሶ ዘገባ ሲቀርብ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት መብት በአገሪቱ ላይ መከበሩንና ጋዜጠኞቹ ግን ይህን መብት እንዴት እየተጠቀሙበት እንደኾነ ለዓለም ሕዝብ ለማሳያነት ይጠቀምበታል፡፡
በጋዜጠኝነት ዘርፍ ወደ ተለያየ የዓለም አገራት ተጉዘው ትምሕርት ቀስመው የመጡ ምሑራንም ስለ ጋዜጠኝነት ሞያ አስተያየት ሲጠየቁ ችግሩ ከሥሩ መርምረው ሞያው ነፃነት ያጣበትን ምክንያት ከእነ መፍትሔው በማስቀመጥ ለመቀየር ከመሞከር ይልቅ በነፃነት ዕጦት በኮሰመነው የግል ብዙኃን መገናኛ የሕትመት ውጤትና ጋዜጠኝነት ላይ ውርጅብኝ ያወርዱበታል፡፡ በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት የጋዜጠኝነትና ሥነ ጹሑፍ ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች እንኳን ሳይቀሩ በአብዛኛው ለመመረቂያ ጹሑፋቸው የሚመርጡት ርእስና የሚሠሩት ጥናት የጋዜጠኝነትን ነፃነት የበለጠ የሚያሳጣ ነው፡፡
እነዚህ ኹሉ ችግሮች ተደማምረው ሞያውን አክስመውታል፡፡ አኹን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጋዜጠኝነት ከእስር፣ከስደት፣ከፍረጃ፣ከፍርኃት የተረፈ ‹‹እስረኛ›› ጋዜጠኝነት ነው፡፡ ጋዜጠኝነት በአብዛኛው የራስ በራስ ቅድመ ምርመራ ራሱን ጠፍንጎ ባሰረ ባለሞያና ለሞያው የጠለቀ ዕውቀት በሌላቸው ሰዎች የመጨረሻ እስትንፋስ እየተንገታገተ ያለ ሞያ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ ይቺኑ ትንሽ እስትፋስ እስከ መጨረሻው ለማጥፋት በሚደረገው ጫና ያሉት ጋዜጠኞች ሞያው የሚጠብቅባቸውን መረጃን ለሕዝብ የማስተላፍ ሥራን ከመሥራት ይልቅ ራስን ወደ መከላከል ሥራ ተሸጋግረዋል፡፡ በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ ያሉት ጋዜጦችና መጽሔቶች የፊት ገጽ ሽፋንና የድረ ገፆች ዋና መነጋገሪያ ርእስ ጋዜጠኞች ላይ የሚደረግ እስርና ጫና ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አንዱ የማዳከሚያ ስልት ሊኾን ይችላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቦሌ አየር መንገድና በጎንደር የሚሰማው ወሬ ጥሩ አይደለም! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

በየአራት ዓመቱ በሚካሄደውና ለሦስተኛ ጊዜ በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ተሳታፊ ኾና ቀርባ ነበር፡፡ ስብሰባው የሚደረገው በ197 የዓለም አገሮች መካከል ሲኾን ሲኾን አገራቱ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን በሚመለከት ሪፖርት የሚያቀርቡበት እንዲኹም የሚቀርብባቸውን ወቀሳና ትችት አዳምጠው የሚያሳሽሉትን ‹‹አሻሽላለሁ›› የሚሉበት ያልተስማሙበትን ደግሞ ያልተስማሙበትን ምክንያት የሚያስረዱበት ስብሰባ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ስብሰባ ላይ በ2010 ላይ ስትሳተፍ የመጀመሪያዋ ቢኾንመ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በሚመለከት 159 ጉዳዮችን እንድታሻሽል ተነግሯት ዘጠኛ ዘጠኙን መቀበሏን ስልሳውን ግን እንደማትቀበለው ተናግራ ነበር፡፡ስብሰባው በቀጥታ ከጄኔቭ በቴሌ ኮንፍረንስ የተመራ ሲኾን እያንዳንዱ አገራት ከሚገኙበት አገር ኾነው በስብሰባው እንደተሳተፉት ኹሉ ማክሰኞ ዕለት በተደረገውና ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት በዚህ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ የተመራና ከአምስት በላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ምክትል ሚኒስትሮችን የያዘ ቡድን አዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት ተገኝተቶ በውይይቱ ተሳትፎ ነበር፡፡
በልኡካን ቡድኑ አማካኝነት የኢትዮጵያ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ፤ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ዐዋጅን በተለመከተና የፀረ ሽብር ሕጉን በሚመለከት በከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟታል፡፡ በስብሰባው ላይ የተሳተፉት አብዛኛው አገራት ኢትዮጵያ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ሕጉን የመናገርና የመጻፍ ነፃነትን እንዲሁም የፖለቲካን ተቃውሞ ለማፈን እየተጠቀመችበት ስለኾነ ሕጉን እንድታሻሽልና ሕጉም ሲሻሻል የፖለቲካ ተቃውሞን ለማፈን እንዳትጠቀምበት ዋስትና የሚሰጥ መኾን እንዳለበት በመግለጽ ጠንካራ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ አባል የነበሩት የኮሚዩኒኬሽን ምክትል ሚኒስትሩ አቶ ሽመልስ ከማል በአገራቱ የቀረበውን ወቀሳ አጣጥለው፤ኢትዮጵያ ውስጥ በሽብር ሕጉ ሰበብ ተደርጎ የታሰረ አንድም ጋዜጠኛ እንደሌለ ጠንከር አድርው በመናገር የሽብር ተግባር ሲፈጽሙ ተይዘው የታሠሩና ከዚህ ቀደም በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ ይሠሩ ነበር የሚባሉ እስረኞች ቢኖሩ እንኳን የታሰሩት ከጋዜጠኝነት ሞያቸው ጋር በተያያዘ ሳይኾን በፈጸሙት የሽብር ወንጀል መኾኑን አበክረው ተናግረዋል፡፡
አቶ ሽመልስ እንዲህ ያለ መከራከሪያ ሲያቀርቡ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አገር ውስጥ ያሉም የውጭ ጋዜጠኞች ሲጠይቋቸውም ይህንኑ ነው የሚመልሱት፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሪፖርት ሲያወጡም የሚመልሱት ይህኑ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የዓለም አገራት ተሰባስበው ኢትዮጵያ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት አፈናን እንድታቆም፣በፖሊስ፣በመከላከያና በደህንንት ሰዎች የሚፈጸመው ‹‹ቶርቸር›› እንዲቆም ፀረ ሽብር ሕጉን ጋዜጠኞችን ለማሠር እንዳትጠቀምበት የዓለም አገራት ተሰባስበው ቢመክሩም የአቶ ሽመልስ ከማል ምላሽ ተመሳሳይ ኾኗል፡፡ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ የሚውተረተረው የእስረኛው ‹‹ጋዜጠኝነት›› ትልቁ ፈታናም እዚህ ጋር ኾኗል፡፡ ጋዜጠኛ ይታሰራል ሲታሰር ደግሞ ‹‹በጻፈው ጹሑፍ ሳይኾን በሽብር ተግባር ላይ ስለተሳተፈ ነው›› የሚል ታፔላ ይለጠፍለታል፡፡ ይህ ደግሞ ሞያውን የበለጠ ችግር ውስጥ ይዘፍቀዋል፡፡ የ‹‹እስረኛው›› ጋዜጠኝነት ሌላ ፈተና ማብቂያ እንደተባለው ኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ሕጉን፣ የመናገርና የመጻፍ ነፃነትን እንዲሁም የፖለቲካን ተቃውሞ ለማፈን እየተጠቀመችበት ነው በሚል እየተወቀሰችበት ያለውን ሕግ ስታሻሻል ይኾን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የቁልቢ ገብርኤል ንግስና የመንግሰት አቅጣጫ (መልካም አስተዳደር፣ ሙስና እና ስደት) በግርማ ሠይፉ ማሩ
Share