(አፍሮ ታይምስ) ዘወትር ረቡዕ ምሽት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው የ “ሰው ለሰው” ድራማ ላይ የዶክተሩን ገፀ-ባህሪ የሚጫወተው አርቲስት ልዑል ግርማ ከድራማው ጋር በተያያዘ ችግር እንደገጠመው ገለፀ።
አርቲስቱ ሰሞኑን ለአፍሮ ታይምስ እንደተናገረው በድራማው ውስጥ ዋናው ገፀ-ባህሪ (መስፍን) በደረሰበት ከባድ የመኪና ግጭት አደጋ አካሉ የማይንቀሳቀስ ከመሆኑም በላይ በውጭ አገር ታክሞ የመዳን ተስፋው የተመናመነ መሆኑ በድራማው እየታየ ሲሆን፣ ዶክተሩ “ተስፋ የለውም” ብሎ መናገሩ የችግሩ መነሻ ነው።
“ሜክሲኮ የሚገኘው ኬኬ ህንፃ ላይ ለግል ጉዳይ በተገኘሁበት ወቅት ሁለት ወጣቶች ከላይኛው ደረጃ ላይ ሆነው ‘ሌባ ዶክተር’ በማለት ጉዳት አድርሰውብኛል፤ የምኖርበት አካባቢ ሰዎችም ‘አንተ ከመቼ ወዲህ ነው ዶክተር የሆንከው?’ በሚል ‘አጭበርባሪ’ እና ‘ሌባ’ እያሉ ሰድበውኛል፤ ዘመዶቼም ለእናቴ ‘ክፉ ልጅ ከመውለድ ቢቀር ይሻል ነበር’ እያሉ መውጫ መግቢያ አሳጥተውናል” ያለው አርቲስት ልዑል ግርማ፣ “ሰዎች ገፀ-ባህሪን እና እውነተኛ ማንነትን ነጣጥለው ባለማየታቸው ለችግር ተዳርጌያለሁ” ሲል ተናግሯል።
“የድራማው ፅሁፍ ሲሰጠኝ ቀድሞውኑ እንዲህ አይነት ነገር ሊከሰት እንደሚችል ገምቼ ደራሲዎቹን አነጋግሬ ነበር” ያለው አርቲስት ልዑል፣ ይሁንና ከህክምና አማካሪያቸው ጋር ተነጋግረው የፃፉት በመሆኑ ምንም “የሚመጣ ነገር አይኖርም” በሚል አሳምነውት ስራውን እንደቀጠለ ይገልፃል። በድራማው
ላይ ለአቶ መስፍን የመዳን ተስፋ እንደሌለው መንገሩ ከአቶ አስናቀ ጋር ተሻርኮ ያደረገው የመሰላቸው የድራማው ተከታታዮች ብዙ መሆናቸውንና በዚህም በእውነተኛ ኑሮው ላይ ተፅዕኖ መፈጠሩንና ለችግር መጋለጡን የሚገለፀው አርቲስቱ “መጠየቅ ካለባቸው እንኳን ተጠያቂዎቹ ደራሲዎቹ እንጂ እኔ ልሆን
አይገባም፤ የሰራሁትም እምቢ ማለት ህዝብን መናቅ ይሆንብኛል በሚል ነው።
ደግሞም ገፀ-ባህሪው እና እውነተኛ ማንነቴ የማይገናኙ በመሆናቸው ሰዎች በእኔ ላይ ያሳደሩትን የጥላቻ መንፈስ ሊያነሱልኝ ይገባል” በማለት ለአፍሮ ታይምስ ቃሉን ሰጥቷል።