"ሚስቴን የአንተን ሲዲ ሰጥቻት፤ ልኬላት ነው የተጋባነው ሲሉ አንድ ሁለት ሶስት ሰዎች ነግረውኛል" ገረመው አሰፋ

የዛሬውን እንግዳችንን ድምጻዊ ገረመው አሰፋን ለእናንተ ለአንባቢያን ማስተዋወቁ ለቀባሪው ማርዳት ስለሆነብኝ አልሞክረውም፡፡ ምክንያቱም ሁሌም አይሰለቼ የሆኑት ዘፈኖቹ ስለ ድምፃዊው ብዙ ብለዋልና፡፡
በተለያየ የሙያ ዘርፍ አንዱ አንዱን ዘመዱን ቤተሰቡን ማስከተሉ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በአትሌቲክሱ ቀነኒሳ ታሪኩ በቀለን፣ ጥሩነሽ ዲባባ ገንዘቤ ዲባባን ሲያስከትሉ በሙዚቃውም ብርቱካን ዱባለ እና የሺእመቤት፣ ማዲንጎ አፈወርቅ እና ትዕግስት አፈወርቅ፣ ማለፊያ ተካ አዳነ ተካን እያስከተሉ እነሆ ገረም ታናሸ ወንድሙ የሆነውን ተረፈ አሰፋን አስከትሎ ሁለት ነጠላ ዜማዎችን በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ብንሰማ ስለ ሁኔታው ልናነጋግረው ፈለግንና ተሳካቶልን ጀርመን ሀገር ስለሚኖረው ወንድሙ እንዲሁም ስለ ራሱም ምን በመስራት ላይ እንዳለ አዲስ እየሰራው ስላለው ኮሌክሽንና አልበም ያካፈለንን እንደሚከተለው አቀርብንላችኋል፡፡
ጥያቄ፡- ገሬ ለፈቃደኝነትህ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
ገረመው፡- እንግዳችሁ እንድሆን ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ እኔም፡፡
ጥያቄ፡- ተወዳጅ የሆነልህን አልበም ከሰራህ ቆየት ብለሃል አሁን በምን አይነት እንቅስቃሴ ላይ ነህ?
ገረመው፡- አሁን እንግዲህ ያው ሁለተኛውን አልበሜን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ አንድ አዲስ ኮሌክሽንም እየሰራሁ ነው፡፡ አማኑኤል ይልማ ጋር ኮሌክሽን ስራ እየተሰራ ነው፡፡ እሱ ውስጥም አለሁበት፡፡
ጥያቄ፡- የኮሌክሽን ስራ ከአንተ ጋር እነማን ተካተቱበት?
ገረመው፡- ብዙ ታዋቂ አርቲስቶች አሉበት፡፡ በስም እነ እገሌ ባልልህም ተወዳጅ ድምፃዊያን የተሳተፉበት ነው፡፡ እና ጥሩ ኮሌክሽን ነው፡፡
ጥያቄ፡- የአንተ ዘፈን በኮሌክሽኑ ላይ የተካተተው ከአንድ በላይ ወይስ…?
ገረመው፡- አዎን፡፡ አንድ ነው የኔ ዘፈን፡፡ አንድ ስራ ነው፡፡ እንግዲህ በቅርቡ ይለቀቃል፡፡
ጥያቄ፡- አንተን የምናውቅህ እነ ንፁህ ነሽ፣ ከአይን የራቀ፣ ቀርበሽ እይኝ፣ ሰላም ነሽ፣ እና በመሳሰሉት በማይሰለቹት ዘፈኖችህ ነው፡፡ እና ይሄም ኮሌክሽን ላይ የተካተተው ዘፈንህ አሪፊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ገረመው፡- አማኑኤል በጣም ጥሩ ስራ ነው የሰጠኝ፡፡ ጥሩ ዜማ ነው የሰጠኝ፡፡ አሬንጀመንቱ ቆንጆ ነው፡፡ እኔ ወድጄዋለሁ፡፡ በጣም ተደስቼበታለሁ፡፡ እና ከእግዚአብሔር ጋር አሪፍ እንደሚሆን ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
ጥያቄ፡- ግጥም ላይ የምትሰጠው ትኩረት አለ፡፡ አሁንስ በግጥሙ በኩል ምን ያክል ትኩረት አድርገሀል?
ገረመው፡- ግጥም ላይ ግድ ነው፤ ያው ትኩረት ማድረግ አለብህ፡፡ በፊትም በደንብ አስቤበት ነው የሰራሁ፡፡ አሁንም ደግሞ ከዛ በተሻለ በደንብ አስቤበት ነው የምሰራው፡፡ ምክንያቱም ግጥም ሰውን ማሸነፍ አለበት፡፡ ዜማ ሰርተህ ዝም ብለህ ስለ ዘፈንክ ሳይሆን ግጥሙም ሰውን ሊነካው ይገባል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ስለማስብ ግጥም ላይ በጣም ነው የማተኩረው፡፡
ጥያቄ፡- ስለሆነም አንተን ይሄ ግጥም አሳምኖሀላ?
ገረመው፡- አዎን ደስ ብሎኛል፡፡
ጥያቄ፡- በዛውም ደግሞ ገሬ ጠፍቷል አንድ አልበም ሰርቶ ድምፁ ጠፋብን ለሚሉትም አድናቂዎችህ መልስ ይሰጣል ብዬ አስባለሁ ካልተሳሳትኩ?
ገረመው፡- ልክ ነህ፡፡ በእርግጥ ቆይቻለሁ፡፡ ግን ያው ጥሩ ነገር ለመስራት ነው የቆየሁት፡፡ ያው እየሰራሁም ነው ያለሁት፡፡ እግዚአብሔር ይጨምርበት ጥሩ ነገር ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የመጀመሪያ አልበምህ ተወዳጅ ሲሆን ሁለተኛ ለመስራት እጅግ ያስጨንቃል፡፡ አልበም ሰርቼ ባላውቅም የምቀርባቸው አንዳንዶች ችግራቸው ሆኖ ስለማይ ነው፡፡ እና የሁለተኛ ስራ ክብደቱ እንዴት ነው?
ገረመው፡- ክብደቱ የሚገርምህ ነገር ከበፊቱ የባሰ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰው በመጀመሪያ ስራዬ ጥሩ ምላሽ ስለሰጠኝ ሁለተኛም ላይ የተሻለ ነው ከእኔ የሚጠብቀው፡፡ ስለዚህ አንተም ያንን ምላሽ አዎንታዊ ለማድረግ ለአድማጮችህ እርካታና ደስታ መልስ ለመስጠት ትለፋለህ፡፡ በትኩረት ትሰራለህ፡፡ ስለዚህ ጥሩ ነገር እየፈለኩ ነው ያለሁት፡፡ እና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጥሩ ነገር እሰራለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ከሙዚቃ ውጪ አዋዋልህ እንዴት ነው? የምትመርጣቸው ለየት ያሉ መዝናኛ ስፍራዎች አሉ?
ገረመው፡- እኔ ምንም የምመርጠው ቦታ የለም፡፡ ደስ ያለኝ ቦታ ነው የምዝናናው፡፡ ክለብ እሄዳለሁ፡፡ የተመቸኝ ቦታ ላይ እዝናናለሁ፡፡ እኔን ወይም ደግሞ ጓደኞቼን አብረውኝ ያሉትን ሰዎች ያስደሰታቸው ቦታ እገባለሁ፡፡ እንጂ እዚህ ቤት አልገባም እዚህ ቤት እገባለሁ የምለው ቦታ የለም፡፡
ጥያቄ፡- ወደ ወንድምህ ስራ ላምራ፣ ከሁለታችሁ ማን ቀደሞ አልበም በመስራት ሳይሆን ሙዚቃን በመምረጥ፣ እሱ አንተን ተከተለ ወይስ ተቀድመሃል?
ገረመው፡- እኔን ተከትሎ ነው፡፡ አንደኛ ነገር ታናሼም ነው፡፡ ቤት ያው ትንሽ ሆነን እንዘፍን ነበር፡፡ እኛ ቤት ብዙዎቹ ይሞክራሉ፡፡ ግን ሌሎቹ ብዙም ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው፡፡ እሱ ግን ገፍቶበት አሁን ነጠላ ዜማዎችን ለቋል፡፡ ጀርመን ሀገር ነው የሚኖረው፡፡ እዛ በተለያዩ ክለቦች ይዘፍናል፡፡ እንደገና ደግሞ እዛው ኤርፖርት ውስጥ አንዳንድ ሀገሮች እየሄደ ይሰራል፡፡ ከታዋቂ ድምፃዊያን ከብዙዎች ጋር ሰርቷል፡፡ ግን ያው እኔ ነኝ የቀደምኩት፡፡ ቤት ውስጥ እኔና እሱ የእሱ ታናሽ ሆነን እንዘፍን ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ሶስተኛው ወንድማችሁስ?
ገረመው፡- ያን ጊዜ እንዲሁ ቤት ውስጥ አብሮን ይዝፈን እ ንጂ ብዙም ፍላጎቱ አልነበረውም፡፡ ይኼኛው ግን በፊትም ቤት ውስጥ በዲጄነት ይሰራ ነበር፡፡ ሙዚቃ በደንብ ያውቃል፡፡ ጎበዝ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ ወንድማማቾች ወይም አንድ ቤተሰብ የሆኑ ሰዎች ድምፃቸው ይመስላል፡፡ የእናንተስ እንዴት ነው?
ገረመው፡- እኔ እንጃ ሰዎች አንዳንድ ቦታ ላይ ይመስላል ይላሉ፡፡ እኔ ግን ብዙ የሚመሳሰል አልመሰለኝም፡፡
ጥያቄ፡- ዜማዎቹን በለቀቀበት ሰዓት የአንተ እገዛ በምን መልኩ ነበር?
ገረመው፡- እዚህ መጥቶ ነው የሰራው፡፡ እሱ በሰራበት ወቅ ት እኔ አልነበርኩም፡፡ በዛን ጊዜ አሜሪካ ነበርኩ፡፡ ስመጣ ነው ለትንሽ ጊዜ የተገናኘነው፡፡ ከዛ በኋላ ሰርቶት ሄደ፡፡ እኔ ነኝ ሲዲውን አሳትሜ ምን ብዬ የበተንኩት፡፡ ወደ 500 ሲዲዎች አሰር ቼ ክልልም እዚህም ለሚዲያም ተሰጥቶት እየተመደመጠ ይገኛል፡፡ እና እዚህ ያለውን የሲዲውን ኃላፊነት የወሰድኩት እኔ ነኝ፡፡
ጥያቄ፡- በጥበቡ ዙሪያ ላይስ? ይሄን እንዲህ ብታደርገው ስትል የምትሰጠው አስተያት የለም?
ገረመው፡- በሱ በኩልም እናወራለን፡፡ የሚገርምህ በጣም ጥሩ ጆሮ አለው፡፡ ዘፈን በደንብ ያውቃል፡፡ ጎበዝ ነው፡፡ ዜማ ላይ እንደውም ከእኔ የተሻለ ሳያውቅ ይቀራል ብለህ ነው፤ ጎበዝ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ እሱ ሙዚቃ በጣም ይሰማል፡፡ ጎበዝ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አንዳንድ ድምፃዊያን በእነሱ ሙያ የቤተሰባቸው አንድም አካል እንዲከተላቸው አይፈልጉም፡፡ አንተስ ምን ያክል ደስተኛ ነህ?
ገረመው፡- እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ወንድሜ ነው፡፡ እሱ ደስ ያለው ነገር ደስ ይለኛል፡፡ ስለዚህ እንደውም እሱን ለማገዝ ነው የምሞክረው፡፡ በብዙ ነገር ላይም እየተጋገዝን ነው፡፡
ጥያቄ፡- ተደማጭነቱ ምን ያክል ነው የተወሰነ ጊዜ ሰምቼዋለሁ፤ እኔም፡፡
ገረመው፡- ሁለት ስራ ነው የሰራው፡፡ ሁለቱም በተለያዩ ሚዲያዎች ይቀርባሉ፡፡ ያለው ነገር ጥሩ ነው፡፡ ብዙ ሚዲያ ላይ የእኔ ወንድም መሆኑ ተገልጿል፡፡ ያልተገለፀና ዘፈኑ የሚተላ ለፍበትም ጊዜ አለ፡፡ ያን ጊዜ በሰው ዘንድ ያለው አስተያየት ጥሩ ነው፡፡ የአንተን ድምፅ የሚመስል ልጅ ዘፍኗል የሚሉኝም አንዳንድ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ እና ገና አዲስ ቢሆንም የሰሙት ሰዎች ግን ጥሩ አስተያየት ነው እየሰጡን ያሉት፡፡
ጥያቄ፡- በአልበም በኩልስ ምን እያሰበ ነው?
ገረመው፡- አልበም እየሰራ ነው፡፡ ያው ውጪ ሀገር ከባድ ነው፡፡ እኛ እዚህ ሆነንም ይከብደናል፡፡ እኔ አሁን አልበሜን ካወጣሁ አራት ዓመት ሆነኝ፡፡ እሱ ደግሞ ውጪ እየኖረ በጣም ይከብደዋል፡፡ ብዙው ነገር ግጥምና ዜማ ከዚህ እየተላከለት ነው ራሱም ቢሰራም፤ እና በጣም ጊዜ ይወስድበታል፡፡
ጥያቄ፡- ወደፊት በጋራ አልበም ለመስራት ያሰባችሁት ነገር የለም?
ገረመው፡- እስካሁን ምንም አላወራንም በዚህ ጉዳይ ላይ፡፡ ምክንያቱም ገና የእሱን ነገር ነው አሁን እየሰራን ያለነው፡፡ የሱ ስራ አንድ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ምናልባት ልናወራበት እንችል ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡- ግን በቅብብልም ቢሆን አንድ ነጠላ ዜማ ብትሰሩ በጋራ ለእሱም ስኬት አንድ በር ከፋች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ገረመው፡- አዎን ልክ ነህ፡፡ እስካሁን በዚህ ጉዳይ አላወራንም፡፡ አሁን በሱ ስራ ላይ ነው ያለነው፡፡ እኔም እዚህ ከግጥምና ዜማ ደራሲዎች ጋር እየተገናኘሁ እልክለታለሁ፡፡ በፊትም ከሱ ቀድሜ ስለሆነ ክለብ የጀመርኩት የክለብ ዘፈኖችን ግጥሞችን እየፃፍኩ እነዚህን ስራ እያልኩ እልክለት ነበር፡፡ በተለይ ጉራጊኛ፣ ሱዳንኛ፣ ዐረቢኛ ዘፈኖችን ግጥሞቹን እየጻፍኩ እልክለት ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ጀርመን ሀገር ከከተመ ምን ያህል ጊዜ ሆነው?
ገረመው፡- ዘጠኝ ዓመት ሆኖታል፡፡
ጥያቄ፡- ከእሱ የምታደንቅለት አለ? እሱስ ከአንተ የሚያደንቀው መቼም ዘፈኖችህን ይሰማቸዋል አይደል?
ገረመው፡- ከሙያ ውጪም ተረፈን በጣም ነው የምወደው፡፡ ተረፈ አሰፋ ነው የሚባለው፡፡ በጣም የምወደው ወንድሜነው፡፡ ከቤተሰቤ ሁሉ ለሱ ያለኝ ነገር ከፍ ይላል፡፡
ጥያቄ፡- በመዙቃው አንተን ስለመሰለ?
ገረመው፡- በሙዚቃ እኔን ስለተከተለ ሳይሆን በአስተሳሰቡ ጥሩ ልጅ ስለሆነ ነው፡፡ በጣም ጥሩ ልጅ ነው፡፡ ዘፈኖቼን ይወዳቸዋል ከማውጣቴም በፊት ያውቃቸዋል፡፡ ግን ስለሱ አሁን እሱ ጀማሪ ስለሆነና ተለያይተንም ስላለን ስለተራራቅን ስለ እሱ መናገር ይከብደኛል፡፡ ከባህሪ አንጻር በጣም ጥሩ እና የምወደው ወንድሜ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ሁለታችሁም ወደ ሙዚቃው ስትገቡ ቤተሰባችሁ ያለው አስተያየት ምን ይመስላል?
ገረመው፡- ገና አሁን ብዙ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ በተለይ ደግሞ እናትና አባታችን ጋር ያለው ነገር ገና ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በሬዲዮም ሰምተውት ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ያው ፋዘር ደስተኛ አይሆንም፡፡ ጭራሽ የአንዱ ሲገርመኝ ሁለተኛውም ሊገባ ነው የሚል ነገር እንዳለው ወሬውን ሰምቻለሁ፡፡ ለሰዎች ነግሯቸው፡፡ እና እሱ ደስተኛ አይሆንም፡፡
ጥያቄ፡- እነሱስ ቤት ውስጥ አያንጎራጉሩም? አሁን እንኳን ባይሆን በፊት የምታውቀው ነገር ካለ?
ገረመው፡- አይ አያንጎራጉሩም፡፡ ትልልቅ ሰዎች ናቸው፡፡ ወደ መንፈሳዊው ነገር እንጂ አለማዊውን ነገር አይደግፉትም፡፡
ጥያቄ፡- ያንተንስ ዘፈን አይሰሙትም?
ገረመው፡- በአጋጣሚ በቲቪ ሲለቀቅ ወይም በሬዲዮ ሲሰማው እንጂ ፋዘር ትልቅ ሰው ስለሆነ ስራዬ ብሎ ለመስማት ከፍቶ ሰምቶት አያውቅም፡፡ የቤተክርስቲያን ሰው ነው፡፡
ጥያቄ፡- በመዚቃው ገሬ የወደፊት ዓላማው ምንድን ነው?
ገረመው፡- ያው አልበም መስራት ነው እንግዲህ፡፡ ሌላ ምን ይታሰባል ብለህ ነው፡፡ ያው ሁለተኛ አልበም ይሰራል፡፡ ከዛ ሶስተኛው ይቀጥላል፡፡ በዛ ውስጥ ግን ጥሩ ስራ ለመስራት መጣርንና ሙዚቃችን የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ማድረግን በተመለከተ ያለው ፍላጎትና ጥረት እንዳለ ነው፡፡ ከዛ ደግሞ ከየአልበሞችህ የምትማረው ነገር አለ፡፡ ከመጀመሪያው የተማርኩት ነገር አለ፡፡ እሱን ሁለተኛው ላይ አሻሽላለሁ፡፡ ከሁለተኛውም የተማርኩትን ነገር ሶስተኛው ላይ አሻሽላለሁ፡፡ ከሁለተኛውም የተማርኩትን ነገር ሶስተኛው ላይ አሻሽላለሁ፡፡ ለሰው ጥሩ ነገርን ማቅረብ ነው የምፈልገው፡፡ አሁን ለጊዜው ያለን አላማ ይሄ ነው፡፡
ጥያቄ፡- በርከት ባሉ ሀገራት በመዘዋወር ዘፈኖችህን አቅርበሃል የት የት ሀገር ሄደሀል?
ገረመው፡- የተወሰኑ ሀገሮች ሄጃለሁ፡፡ ከዐረብ ሀገር ብጀምር ዱባይ፣ አቡዳቢ፣ ባህሬን፣ ኩዌት ሄጃለሁ፡፡ ኤሮፕ ደግሞ ጀርመን፣ ሲዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ጣሊያን፣ ግሪክ እንዲሁም ደግሞ አሜሪካም ሰርቻለሁ፡፡
ጥያቄ፡- ከነዚህ ሀገሮች ላንተ ልዩ የስራ ቦት የት ሀኖ ተገኘ?
ገረመው፡- አቡዳቢ የሰራሁት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ አንደኛ ኦዲየንሱ በጣም ብዙ ነበር፡፡ ማናጀሩ ራሱ ደስ ብሎት አመስግኖኝ ጋብዞን ከሙዚቀኞቹ ጋር ማለት ነው፡፡ ሙዚቀኞቹ እዛው ያሉ ናቸው፡፡ እኔ ብቻዬን ነበር የሄኩት፡፡ ደስ ብሎት ለአንድ ስራ ብሄድም ሁለተኛ ስራ አስደግሞኝ ሰርቼ ሁለቱም አረፊ ሆነው ነው የተመለስኩት፡፡ እና የአቡዳቢውን ስራ ሁሌም አልረሳውም፡፡
ጥያቄ፡- የመድረክ ገጠመኝ የለህም?
ገረመው፡- የመድረክ ገጠመኞች ብዙ የሉኝም፡፡
ጥያቄ፡- ዘፈንህን ወደውት በፍቅር የጠየቁህ ሴቶች አልገጠሙህም?
ገረመው፡- /ሳቅ/እንደሱ አልገጠመኝም፡፡ ግን እኔና ሚስቴ የተጋባነው በአንተ ዘፈን ነው ያሉኝ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ በአድ ናቆት እንጂ በፍቅር ደረጃ በዘፈኔ አፍቅሮኝ የጠየቀኝ ሰው የለም፡፡
ጥያቄ፡- ዘፍኖ ሰውን ከማስደሰት ባለፈ በዘፈንህ ሰዎች ስታጋባ ወይም ለጋብቻ መንስኤ ስትሆን የሚፈጥርብህ ስሜት እንዴት ነው ታዲያ?
ገረመው፡- ደስ ይላል፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ እኔ ሚስቴን የአንተን ሲዲ ሰጥቻት ልኬላት ነው የተጋባነው ሲሉ አንድ ሁለት ሶስት ሰዎች ነግረውኛል፡፡ በተለይ ንፁህ ነሽን ደግሞ እያለቀሰ ይሄን ዘፈን ለእኔ ነው የዘፈንከው በድያለሁ ያለኝ ሰውም አለ፡፡ እና ደስታ ነው የሚፈጥርብኝ፡፡
ጥያቄ፡- የህገወጥ ኮፒው ነገር ረገብ ብሏል እየተባለ አይደል ?
ገረመው፡- አይ አይ የተረጋጋ አይመስለኝም፡፡ የተረጋጋ ቢሆ ን ኖሮ ሙዚቃ ቤቶቹ ይገዙ ነበር፡፡ ስለማያተርፋቸው እኮ ነው፡፡ አሁን ይገባሉ ወዲያው በህገ ወጥ ኮፒ ይቸበቸባል፡፡ ስለ ዚህ ሙዚቃ ቤቱ ያወጣውን ወጪ ራሱ ላይሸፍን ይችላል፡፡ ስላላዋጣቸው ነው ከስራው የወጡት እና በዚህ ከቀጠለ አስፈሪ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ድምፃዊያን በህብረት ስብስብ ብላችሁ በችግሩ ላይ የተወያያችሁበት ጊዜ የለም?
ገረመው፡- ሁሌ ተሰብስበን እናወራለን፡፡ ከመንግስትም አካል የሚመለከታቸው ሰዎች ብዙ ጊዜ መጥተው ስብሰባ ተደርጓል፡፡ እንግዲህ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ ያው የሙዚቃ ኮሚቴዎች አሉ፡፡ እነሱ ናቸው በማህበሩ በኩል ጉዳዩን የሚከታተሉት፡፡አንድ ነገር ሲኖር የሚያሳውቁን እነሱ ናቸው፡፡
ጥያቄ፡- ይህን ስታስቡ ወጪ ላይ መሰሰት ይመጣል?
ገረመው፡- በእኛ በኩል እንዲህ አይነት ነገር የለም፡፡ ወጪ የሚባለው ነገር አርት እስከሆነ ድረስ ውስጥህ በስራው መርካት አለበት፡፡ ገንዘቡ ላይ ሳይሆን ስራው ላይ ማተኮር ነው ያለብን፡፡ ገንዘቡ ኖሮን አይደለም፡፡ ግን አንተ በስራው ሳትረካ ለሰው ብታቀርበው ዝም ብሎ ልፋት ስለሚሆንና ሰውም ስለማይረካበት ነው፡፡ መጀመሪያ በምትሰራው ስራ አንተ መደሰት አለብህ፡፡ አንተ ስትደሰትበት ነው ሰውም ሊደሰትበት የሚችለው፡፡ ስለዚህ በአልበም ስራ ላይም ሆነ ክሊፕ ላይ ወጪና ጉልበትን ማሰብ የለብንም፡፡µ
ጥያቄ፡- በመጨረሻ ለአንባቢዎቻችን ከአንተም ሆነ ከወንድምህ ዘፈን የቱን ትጋብዛለህ?
ገረመው፡- የእኔን ያው ብዙ ጋብዣለሁ፡፡ ከወንድሜ ግን ብዙ ነገር አለ የምወድልሽ የሚለውን እወደዋለሁ፡፡ እሱን እጋብዛለሁ፡፡
ብዙ ነገር አለ የምወድልሽ
የትኛውን ትቼ የቱን ልንገርሽ
ይላል፡፡ ግጥሙን መሰለ ነው የጻፈው፤ ዜማው የሱራፌን ነው፡፡
ጥያቄ፡- ገሬ በቀናነት እንግዳችን በመሆን ላሳየኸን ፈቃደኝነት እናመስግናለን በጣም፡፡
ገመረው፡- እኔም በጣም ነው የማመሰግነው፡፡ µ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአባይ ግድብ በግብጽ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ መገንባቱ ወያኔ ምን ያህል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ያሳያል
Share