የፕሪሚየር ሊጉ ኃያላን በአሁኑ ዝውውር መስኮት እነማንን ያጣሉ?

የዘንድሮው የፕሪሲዝን ዝውውር መስኮት የፊታችን ኦገስት 31 እስኪዘጋ ድረስ እንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ክለቦች ቡድናቸውን ለማጠናከር የሚችሉላቸው አዲስ ተጨዋቾችን ለማግኘት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረትን ማድረጋቸውን እንደሚገፉበት ይታመናል፡፡ ከወዲሁም የዘንድሮውን ሲዝን ከ1ኛ-6ኛ ደረጃ ከጨረሱት ክለቦች ውስጥ ቶተንሀም አሜሪካዊው አንጋፋ ብራድ ፍሪድልን በማስፈረም የግብ ጠባቂ ችግርን የመቅረፍ ውሳኔን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ስድስቱ ኃያላን ክለቦች ከሁለት ወራት በላይ የሚዘልቀው የዝውውሩ መስኮት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ይታመናል፡፡
ሻምፒዮኑ ማንቸስተር ዩናይትድ ከጨዋታ ዓለም የተገለሉት ኤድዊን ቫንደርሳርና ፖል ስኮልስን ለመተካት የሚችሉት ተጨዋቾችን ማግኘትን ዋነኛው አላማው ሲያደርግ አርሴናል በበኩሉ ለባርሴሎና ለመፈረም ጫፍ ደረሰው ሴስክ ፋብሪጋስንና ሌሎች የቡድኑ ቁልፍ ተሰላፊዎችን በሚተኩለት ተጨዋቾችን በማግኘት ለድፍን ስድስት ዓመታት የዘለቀው ዋንጫ ጥማቱን ለመቅረፍ የሚችልበት ጠንካራ ቡድንን የመፍጠር አላማ አለው፡፡ ቼልሲም አዲስ በሚሾመው አሰልጣኝ ስር ሌላ የትልቅ ዋጋ የግዢ ውልን እንደሚፈፅም ይጠብቃል፡፡ ከወዲሁም የበርካታ ታላላቅ ፉትቦለሮች ስም ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በመያያዝ ላይ ነው፡፡
ለአዲስ ተጨዋች ግዢ እስከ 75 ሚሊን ፓውንድ የሚደርስ በጀትን የመደበው ሊቨርፑልም ሌላው በዝውውሩ መስኮት ሰፊ እንቅስቃሴን እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ክለብ ነው፡፡ የቶተንሃም ዋነኛ አላማ ደግሞ የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋቾች የሆኑት ሉካ ሞድሪችና ጋሬዛ ቤልን ማቆየት ነው፡፡ ለማንኛውም የጎል ዌብሳይት የፕሪሚየር ሊግ ፉትቦል አናሊስቶች የእንግሊዝ ኃያላን ክለቦች በአሁኑ የዝውውር መስኮት ሊያጧቸው የሚችሏቸው ተጨዋቾችን ከዚህ በታች ባለው መልኩ ዳስሷቸዋል፡፡
ጋሬዝ ቤል /ቶተንሃም/
የጨዋታ ሚና፡- ሚድፊልደርና ግራ ተመመላሽ
ዕድሜ፡- 21
በተጠናቀቀው ሲዝን፡- ግጥሚያ 41
ጎል፡- 11
አሲስትስ፡- 3
ኮንትራቱ የሚያበቃው፡- በ2015
የሽያጩ ዋጋ፡- 50 ሚሊዮን ፓውንድ
የሚፈልጉት ክለቦች፡- ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማን ሲቲ፣ ቼልሲ፣ ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎናና ኢንተርሚላን
ስፐርስን የመልቀቁ ተስፋ፡- 15 ፐርሰንት ዌልሳዊው የመስመር ተጨዋች በዘንድሮው ሲዝን በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለማበርከት የቻለው ታላቅ ፐርፎርማንስን ስሙ በአውሮፓ ከሚገኙ በርካታ ታላላቅ ክለቦች ጋር እንዲያያዝ ምክንያት ሆኖታል፡፡ በተለይም በሳንሲሮ በተደረገው ግጥሚያ በኢንተር ሚላን ላይ ሀትሪክ የሰራበት ታላቅ ፐርፎርማንሱ የዘንድሮው የ/PFA/ ኮከብ ተጨዋችን በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ አድርጎታል፡፡ የዛሬ ዓመት ማንቸስተር ዩናይትድና ሪያል ማድሪድ የ21 ዓመቱ ዌልሳዊ ስታርን ለማስፈረም ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በማርች ወር ለቶተንሃም ለአራት ዓመት ተኩል የሚቆይበት የኮንትራት ውልን ማራዘሙን ተከትሎ ዋጋው ወደ 50 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍ ብሏል፡፡ ከዚህ አንፃር ይህንን ከፍተኛ ሂሳብን ለመክፈል ፈቃደኛ የሚመስሉት ክለቦች ማንቸስተር ሲቲና ቼልሲ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቤል ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ቢያንስ ለአንድ ተጨማሪ ሲዝን በቶተንሃም በመቆየት ለክለቡ ያለውን ታማኝነት ለመግለፅ ፍላጎት ማሳደሩን ተናግሯል፡፡
ዴሚታር ቤርባቶቭ /ማን.ዩናይትድ/
የጨዋታ ሚና፡- አጥቂ
ዕድሜ፡- 30
በተጠናቀቀው ሲዝን፡- ግጥሚያ 41
ጎል፡- 20
አሲስትስ፡- 6
ኮንትራቱ የሚያልቀው፡- በ2012
የሽያጭ ዋጋው፡- 12 ሚሊዮን ፓውንድ
የሚፈልጉት ክለቦች፡- ባየር ሙኒክ፣ ፒ.ኤስ.ጂ፣ ጁቬንቱስና ቶተንሃም
ዩናይትድን የመልቀቅ ተስፋው፡- 70 ፐርሰንት
ቡልጋሪያዊው አጥቂ የፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አግቢነትን ሽልማት ከካርሎስ ቴቬስ ጋር በመጋራት የዘንድሮን ሲዝን ለማጠናቀቅ ቢችልም በኦልድትራፎርድ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት የመቻሉ ተስፋ ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ በተለይም ማንቸስተር ዩናይትድ በባርሴሎና 3ለ1 ከተረታበት የቻምፒየንስ ሊግ ፋይናል ውጪ መሆኑ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን እቅድ ውጪ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ቤርባቶቭ በዘንድሮው ሲዝን ካለፉት ዓመታት አንፃር ለማንቸስተር ዩናይትድ በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ጎሎችን ለማስቆጠር ቢችልም እስካሁንም ድረስ ግን የክለቡ ሪከርድን በመስበር በ30.75 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ በ2008 ከቶተንሃም ከተገዛ ወዲህ በኦልድትራፎርድ የተረጋጋ የፉትቦል ህይወት ሊኖረው አልቻለም፡፡ በተለይም በዘንድሮው ሲዝን የ30 ዓመቱ ቡልጋሪያዊ ከፍተኛ ወሳኝነት ባላቸው ግጥሚያዎች ከዩናይትድ መደበኛ ቋሚ አሰላለፍ ውጪ መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ፈርጉሰን ለሀቪዬር ሄርናንዴዝ የተሻለ የመሰለፍ እድልን መስጠታቸው ነው፡፡ የቤርባቶቭ የኮንትራት ውል የሚጠናቀቀው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በመሆኑም የዩናይትዱ አሰልጣኝ በአሁኑ የዝውውር መስኮት በመሸጥ መጠነኛ ገቢን ሊያገኙበት የወሰኑ ይመስላሉ፡፡ ከወዲሁም ባየር ሙኒክ የቀድሞው የሌቨርኩዘንና የቶተንሃም የፊት አጥቂን ለመግዛት ፍላጎትን አሳይቷል፡፡ ሆኖም ግን ተጨዋቹ እስካሁንም ድረስ በኦልድትራፎርድ ለአንድ ዓመት በመቆየት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያለውን ኮንትራት ለማጠናቀቅ እንደሚመኝ በመናገር ላይ ነው፡፡ እንደ ብዙዎች አምነትም የቤርባቶቭ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ማንቸስተር ዩናይትድ በጁላይ ወር በፕሪ ሲዝን ዝግጅት ፕሮግራምን በሚጀምርበት ወቅት ነው፡፡
ሴስክ ፋብሪጋዝ /አርሴናል/
የሚጫወትበት ቦታ፡- ሚድፊልደር
ዕድሜ፡- 24
በተጠናቀቀው ሲዝን፡- ግጥሚያ 35
ጎል፡- 9
አሲስትስ፡- 14
ኮንትራቱ የሚጠናቀቀው፡- በ2014
የሽያጭ ዋጋው፡- 45 ሚሊዮን ፓውንድ
የሚፈልጉት ክለቦች፡- ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድና ማን.ሲቲ
አርሴናልን የመልቀቁ ተስፋ፡- 60 ፐርሰንት
የአርሰናሉ አምበል ወደ ቀድሞው ክለቡ ባርሴሎና ተመልሶ የመጫወት ከፍተኛ ጉጉት ባለፈው ፕሪ ሲዝን የዝውውር መስኮት ታላቅ አጀንዳ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮም ይህ ጉዳይ የዝውውሩ ገበያ ትልቅ የመወያያ ርዕስ ሆኗል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ፋብሪጋስ እስካሁንም ድረስ ለአውሮፓ ሻምፒዮኖቹ ለመፈረም ከፍተኛ የሆነ ጉጉትን ማሳደሩ ነው፡፡ ዛሬ 12 ወራት ገደማ ፋብሪጋስ አርሴናልን የመልቀቅ ፍላጎትን ያሳደረው ከስሜታዊነት በመነሳሳት ይመስል ነበር፡፡ አሁን ግን ከስምንት ያላነሱ የስፔን ብሔራዊ ቡድን ጓደኞቹ ያሉበት ባርሴሎናን መቀላቀል ሊፈፅመው የሚገባ ግዴታው በማድረግ ቆጥሮታል፡፡ ትልቁ ችግር ግን እስካሁን ድረስ ባርሴሎናና አርሴናል በተጨዋቹ የዋጋ መጠን ሊቀራረቡ አለመቻላቸው ነው፡፡ ባርሳ ከ30 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ በላይ ለማቅረብ አይሻም፡፡ የአርሴናል ኃላፊዎች ግን የዝውውር ድርድሩን ለመጀመር ፈቃደኛ የሚሆኑት ከ45 ሚሊዮን ፓውንድ ያላነሰ ሂሳብ ከባርሳ ሲቀርብላቸው ብቻ መሆኑን በመናገር ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአርሴናል ኃላፊዎች የተጨዋቹ ፍላጎት ምን እንደሆነ በመረዳታቸው ምኞቱን ለማሳካት እንዳይችል ተፅዕኖን ሊፈጥሩበት የሚመኙ አይመስሉም፡፡ ነገር ግን በርካሽ ዋጋ የቡድናቸው ቁልፍ ተጨዋችን ላለመልቀቅ የተቻላቸውን ሁሉ ትግል ማድረግን ምርጫቸው አድርገውታል፡፡ የተጨዋቹ ኤጀንትና አባት ምናልባትም ከዚህ የተለየ ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ከሚኖራቸው አማራጭ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ ፋብሪጋስ ለሁለት ዓመታት ለማይበልጥ ጊዜ ለማንቸስተር ሲቲ ከተሰለፈ በኋላ የባርሴሎና ስኳድን የመቀላቀል አላማውን ለማሳካት የሚችልበት ነው የሚል እምነት አለ፡፡
ሉካ ሞድሪች /ቶተንሃም/
የሚጫወትበት ቦታ፡- ሚድፊልደር
ዕድሜ፡- 25
በተጠናቀቀው ሲዝን፡- ግጥሚያ 43
ጎል፡- 4
አሲስት፡- 3
ኮንትራቱ የሚጠናቀቀው፡- በ2016
የሽያጭ ዋጋው፡- 35 ሚሊዮን ፓውንድ
የሚፈልጉት ክለቦች፡- ዩናይትድና ቼልሲ
ስፐርስን የመልቀቅ ተስፋው፡- 25 ፐርሰንት
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን የ2010-11 ሲዝን የፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ተጨዋችን እንዲመርጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸውን የሰጡት ሉካ ሞድሪች በማለት ነው፡፡ ይህ የዩናይትዱ አሰልጣኝ ለ25 ዓመቱ ክሮኤሺያዊ ኢንተርናሽናል ብቃት ሙሉ እምነት እንዳላቸው በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የሰር አሌክስ እምነትም ሞድሪች ከጨዋታ ዓለም ለተገለለው ፖል ስኮልስ ትክክለኛው ምትክ ይሆናል የሚል ነው፡፡ የክሮኤሺያዊው ሚድፊልደር በአማካይ ክፍል በርካታ የኳስ ቁጥጥሮችን በመያዝ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴን በተደናቂ ሁኔታ የመምራት ብቃት ከዩናይትድ ባሻገር የቼልሲዎችንም ቀልብ በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የፕሪሚየር ሊግ ዘመቻቸውን በ1ኛና በ2ኛ ስፍራ ተቀምጠው ያጠናቀቁት ሁለቱ ኃያላን ክለቦች የአማካይ ክፍላቸው የክሬኤቲቭ ሚናን ከፍ የሚያደርግላቸው ተጨዋችን ማግኘትን ዋነኛ አላማቸው አድርገውታል፡፡ ከወዲሁም ሞድሪች ባለፈው ሳምንት ውስጥ በሰጠው መግለጫው በቻምፒየንስ ሊግ ውድድር የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው በመናገር ራሱን ለዝውውር ዝግጁ ማድረጉን ጠቁሟል፡፡
ቶተንሃም ቀጣዩ ሲዝን የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ተሳትፎ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን አሰልጣኝ ሀሪ ሬድናፕ ከቶተንሃም ስኳድ እጅግ ወሳኙ ተጨዋች ያሉትን ሞድሪች ለመሸጥ የሚገደዱ ከሆነ በከፍተኛ ዋጋ የታጀበ ጥሪ እንዲቀርብላቸው ይመኛሉ፡፡ ክለባቸው ከዚህ በፊት በክሮኤሺያው ሚድፊልደር ላይ ያወጣው ዋጋ 25 ሚሊየን ፓውንድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የበርካታ ትላልቅ ክለቦችን ልዩ ትኩረትን እየሳበ መምጣቱን በመገንዘብ በያዝነው ሳምንት ውስጥ ከ35 ሚሊየን ፓውንድ በታች እንዲቀርብላቸው እንደማይፈልጉ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ መልኩ በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥም የሞድሪች ዋጋ እየናረ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡
ካርሎስ ቴቪስ /ማን.ሲቲ/
የሚጫወትበት ቦታ፤- አጥቂ
ዕድሜ፡- 27
በተጠናቀቀው ሲዝን፡- ግጥሚያ 44
ጎል፡- 24
አሲስት፡- 9
ኮንትራቱ የሚጠናቀቀው፡- በ2014
የሽያጭ ዋጋው፡- 45 ሚሊዮን ፓውንድ
የሚፈልጉት ክለቦች፡- ኢንተር ሚላንና ሪያል ማድሪድ
ሲቲን የመልቀቅ ተስፋው፡- 50 ፐርሰንት ካርሎስ ቴቬስ በጃንዋሪው የዝውውር መስኮት ማንቸስተር ሲቲን ለመልቀቅ የነበረው ሀሳብን በመሰረዝ እስከ ሲዝኑ መጨረሻ በኢስትላንድ ለመቆየት ይወስን እንጂ በአሁኑ የዝውውር መስኮት ወደ ሌላ አገር ትልቅ የሊግ ውድድር የማምራት ፍላጎትን አሳድሯል፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባትም ኢንተር ሚላንና ሪያል ማድሪድ ፊርማውን የማግኘት ፍላጎትን አሳድረዋል፡፡ ነገር ግን የ27 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂ ዝውውር የማድረግ ፍላጎትን ማሳደሩን ሲናገር የነበረው በርካታ አማራጭ ክለቦች ይኖሩኛል የሚል ግምቱ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ ምክንያቱም ስሙ በመያያዝ ላይ ያለው ከኢንተር ሚላንና ከሪያል ማድሪድ ዝውውር ጋር ብቻ ነው፡፡ የማንቸስተር ሲቲ ኃላፊዎች ቀድሞውንም ቢሆን ክለባቸው የቀጣዩ ሲዝን የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር የቀጥታ ተሳትፎን ያስገኘላቸው የቡድናቸው ከፍተኛ ጎል አግቢን የመሸጥ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ በዚህም ቴቬስ ዝውውር የማድረግ ፍላጎትን ማሳደርን አልወደዱትም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቴቬስን ለማግኘት በርካታ ክለቦች ጉጉትን ሲያሳድሩ አለመታየታቸው የሚያስፀፅት ሆኖባቸዋል፡፡ የአርጀንቲናዊው አጥቂ የዋጋ መጠንን በ45 ሚሊዮን ፓውንድ ሂሳብ ሊገድቡት የተገደዱትም ከዚህ በመነጨ ምክንያት ነው፡፡ የ27 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ማንቸስተር ዩናይትድን በመልቀቅ ለማንቸስተር ሲቲ በአወዛጋቢ ሁኔታ ከፈረመ ወዲህ የኢስትላንድ የሁለት ሲዝን ቆታውን ያሳለፈው ውጤታማ ፉትቦልን በማበርከት ቢሆንም ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቱ ግን የማንቸስተር ከተማ ቆይታው ደስተኛ ሳያደርገው ቆይቷል፡፡ ባለፈው ዲሴምበር ወር በይፋ ደብዳቤ በመፃፍ በክለቡ እንዲለቀቅ ጥያቄ እስከማቅረብ የደረሰውም በማንቸስተር ሲቲ መገኘቱ ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቱ ደስተኛ እንዳይሆን ምክንያት እንደሆነው በመግለፅ ነው፡፡ የማንቸስተር ሲቲ ኃላፊዎች በቅርቡ ያቀረቡለት በሳምንት 25 ሚሊዮን ፓውንድ ደሞዝን የሚያገኝበት የኮንትራት ማራዘሚያ ውልን ሳይቀበለውም ቀርቷል፡፡ ከወዲሁም ቴቬዝ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ደመወዝ ከሚከፈላቸው ሶስት ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡ ዝውውር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ባረጋገጠበት በአሁኑ ወቅት ከኢንተር ሚላንና ከሪያል ማድሪድ በስተቀር ሌሎቹ ክለቦች ጥሪ ሊያቀርቡለት ያልፈለጉትም ይህንን ከፍተኛ ደመወዝ የማግኘት ፍላጎቱን ከግምት በማስገባታቸው ነው፡፡
አሽሊ ያንግ /አስቶንቪላ/
የሚጫወትበት ቦታ፡- በክንፍና የፊት አጥቂ
ዕድሜ፡- 25
በተጠናቀቀው ሲዝን
ግጥሚያ፡- 37
ጎል፡- 13
አሲስቶች፡- 13
ኮንትራቱ የሚያልቀው፡- በ2012
የሽያጩ ዋጋ 15 ሚሊዮን ፓውንድ
የሚፈልጉት ክለቦች፡- ማን.ዩናይትድ፣ ሊቨርፑልና ማን.ሲቲ
ቪላን የመልቀቁ ተስፋ፡- 90 ፐርሰንት
የኢንግላንድ ኢንተርናሽናል በአሁኑ የዝውውር መስኮት አስቶንቪላን እንደሚለቅ ከመናገር የተቆጠበበት ወቅት የለም፡፡ ከወዲሁም ሁለቱ ታሪካዊ ተቀናቃኞች ማንቸስተር ዩናይትድና ሊቨርፑል አሽሊ ያንግን ለማግኘት ተፋጥጠዋል፡፡ የሰር አሌክስ ፈርጉሰንና የኬኒ ዳግሊሽ ልዩ ትኩረትን እንዲስብ ምክንያት የሆናቸው በከፍተኛ ፍጥነት የታጀበ የማጥቃት እንቅስቃሴን በሁለቱም ክንፎች በኩል የማድረግ ብቃቱ በተጠናቀቀው ሲዝን የበለጠ አድጎ በመታየቱ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት አስቶንቪላ በ9.75 ሚሊየን ፓውንድ ከዋትፎርድ ከገዛው ወዲህም እያንዳንዱ ሲዝን ፐርፎርማንሱን በማሳደግ በማሳለፍ ላይ ነው፡፡ ያንግ ከአስቶንቪላ ጋር ያለው ኮንትራት የሚጠናቀቀው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢሆንም የዋጋ መጠኑ ከ15 ሚሊየን ፓውንድ እንደማይበልጥ ይታመናል፡፡ በተጨዋቹ የቅርብ ወዳጆች እንደሚጠቁሙት አሽሊ ያንግ በቀጣዩ ሲዝን በፉትቦል ህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ተሳትፎን ለማግኘት ሲል የኦልድትራፎርድ ጉዞን ለማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ምርጫው ነው፡፡ ነገር ግን ሊቨርፑል ከማንቸስተር ዩናይትድ የተሻለ የደመወዝ ክፍያ በማዘጋጀትና የመደበኛ ቋሚ ተሰላፊነት እድል እንዲኖረው ቃል በመግባት ሀሳቡን ለማስቀየር ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን የአሽሊ ያንግ የወደፊት እጣ ፈንታ በቀጣዮቹ ሰባት ቀናት እንደሚወሰን ይጠበቃል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ነገሰ
Share