July 7, 2011
14 mins read

ድምፃዊት ፀደኒያ ገ/ማርቆስ (የመጀመሪያዋ የኮራ አዋርድ አሸናፊ ኢትዮጵያዊት)

‹‹ገዴ›› እና ‹‹ቢሰጠኝ›› በሚሉት አልበሞች እናውቃታለን፡፡ ሁለተኛ አልበሟ ላይ ባለው ‹‹እወድሃለሁ›› በሚለው ዜማዋ የኮራ የሙዚቃ አዋርድ ማሸነፍ የቻለችው አቀንቃኟ በአሁኑ ሰዓት ሦስተኛ አልበሟን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ‹‹ዜማ ፍቅር›› የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ከልብ ጓደኛዋ አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ ጋር አዘጋጅታ ታቀርባለች፡፡ በተጨማሪም ሲዲና ካሴት የሚያመርት ፋብሪካ ለመክፈት ባቀደችው ‹‹ሼባ ሲስተም አክሲዮን ማህበር›› በማስተባበር ስራ ላይ ትገኛለች፡፡ ‹‹ህገ-ወጥ ቅጂን መከላከል የሚያስችል ሲዲ የማምረት እቅድ አንግበናል›› የምትለው ፀደኒያ ‹‹ዘና ብላ›› በሰውነት እንቅስቃሴ ጭምር እያስረዳች ላነሳንላት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ዘሃበሻ፡- ስራ እንዴት ነው?
ፀደኒያ፡- ስራ ምንም አይልም፣(ገብስ) ነው፡፡ ቀለል ያለ ነው፡፡
ዘሃበሻ፡- የአክሲዮን ማህበራችሁ የመጨረሻ ጎል ምንድነው?
ፀደኒያ፡- ሀገሪቱ ውስጥ ያለው አንድ የካሴት ማምረቻ (Super shine) ብቻ ነው፡፡ እኛ የካሴትና የሲዲ ፋብሪካን በኢንዱስትሪ ደረጃ አቋቁመን የውጪ ምንዛሪን መቀነስ እንፈልጋለን፡፡ ስራው አዋጪ በመሆኑ ራሳችንንም ጠቅመን ህገ-ወጥ ቅጂን መከላከል የሚያስችል ሲዲን የማምረት እቅድ አንግበናል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገርን በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ የጥበብ አባላት በተለይ ደግሞ የጥበብ ቤተሰቦች በብዛት እየተመዘገቡ ነው፡፡


ዘሃበሻ፡- የምትሄጂበት መንገድ የስኬት ጎዳናን እየጠረገ ስለመሆኑና አለመሆኑ ቆም ብለሽ ራስሽን የመቃኘት ልማድ አለሽ?
ፀደኒያ፡- ሙዚቃን ብዙ ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ታየዋለህ፡፡ የማያምር ከሆነ ያስታውቅሃል፡፡ መስመርን እየጠረግክ የምትሄደው አንተው አይደለህ? ሁሌ ግርግዳ፤ ሁሌ ድንጋይ ከበዛብህ ያ ነገር ወይም ላንተ አልተፈጠረም አሊያ ስህተት እየሰራህ ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሁለትና ሶስት ቅርንጫፍ ዘርግተህ እንቅፋትም ቢኖረው ቀስ እያለ የሚጠረግ ይሆናል፡፡ መንገድህ ሁሌ አልጋ በአልጋ አይሆንም፤ የምታየውን ጭላንጭል ለማስፋት መስራት አለብህ፡፡ ጭለማ ግን ከሆነ ትዘጋዋለህ፡፡ ሁሌም መንገዴን እቃኛለሁ፡፡ ‹‹ገገገገ…›› ብለው የሚመጡ ነገሮችን ሳልደናገጥና ተስፋ ሳልቆርጥ እሰራዋለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- ሶቅራጥስ ‹‹ራስን ማወቅና መሆን የእውቀቶች ሁሉ መሰረት ነው›› ይላል፡፡ አንቺ ራስሽን ምን ያህል ታውቂዋለሽ?
ፀደኒያ፡- በተወሰነ ደረጃ ራስህን ታውቀዋለህ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ግን፣ እምነኝ ሰው ራሱን አያውቅም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ‹‹አደርጋቸዋለሁ›› የማትላቸውን ነገሮች ስታደርግ በራስህ ትገረማለህ፡፡ ‹‹አብደሀል… አደርገዋለሁ›› ብለህ ሳታደርገው ተልፈስፍሰህ የምትቀርበት አጋጣሚ አለ፡፡ የማታውቀውን የራስህን ፀባይ እየቆየ ልታየው ትችላለህ፡፡ የሰውን ፀባይ ከማስተካከል ይበልጥ የራስን ፀባይ ማወቅና መቆጣጠር ከባድ ነው፡፡ ያንን ማድረግ ከቻልክ ከሰው ጋር ያለህ ግንኙነት የቀለለ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ ሰውን ራስ ወዳድነት ሲገለው ታያለህ፡፡ እያደሩ የሚወጡ ነገሮች አሉ፡፡ ራሴን አውቃለሁ እያልክ የማታውቀው ነገር ይኖራል፡፡ በተወሰነ መልኩ ራሴን አውቃለሁ፡፡ አስደንግጣኝም ታውቃለች፡፡ አስደናቂ ነገሮች ሳደርግ በተለይ እደነግጣለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- ‹‹አስደናቂ›› ያልሽውን ነገሮች ስታደርጊ የምትደናገጪው ፀደኒያ ይህንን የማድረግ ብቃት የላትም ብለሽ ስለምታስቢ ነው?
ፀደኒያ፡- ብቃት የላትም ብዬ አስቤ ሳይሆን ‹‹ዋው! ይህንን ማድረግ ትችላለች›› ብዬ በመደነቅ ነው፡፡ ወይም ያንን ማድረግ እንደምችል ገብቶኝ ስለማያውቅ ነው፡፡ አደርገዋለሁ ብዬ፣ ልፍስፍስ ብዬ ‹‹ምን ሆኜ ነው?›› ብዬ ተሸማቅቄ አውቃለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- ሙዚቃ፣ የሬዲዮ ፕሮግራም፣ አክሲዮን ማህበርን ለመስራት መሰረተ ሐሳብ ያስፈልጋል፡፡ ለህይወታችንስ ይህ ይጠቅማል?
ፀደኒያ፡- ስትኖር ምክንያት ሊኖርህ ይገባል፡፡ እንደ እንስሳ እየበላሁና እየጠጣሁ ብቻ መኖር አልፈልግም፡፡ ኑሮን ‹‹ቅርፅ›› አድርገህ መኖር አይቻልም፡፡ ኑሮ በራሱ መልኩን ይቀያይራል፡፡ የሆነ ቢዝነስ ለመስራት ስትነሳ በነደፍከው እቅድ መሰረት አይሄድም፡፡ የምተነሳበት መሰረተ ሀሳብ ቢኖርም መንገዱን ስትሄደው ቀላል አይደለም፡፡ እቅድ አውጥቼ ያላሳካሁት ነገር ባልተጠበቀ ሁኔታ ደግሞ ሲሳካ ታየዋለህ፡፡ ‹‹እቅድ ማውጣት አያስፈልግም ማለት ነው?›› ብዬ ከራሴ ጋር የምነታረከው ነገር አለ፡፡ ስለምታደርገው ነገር መሰረተ ሀሳብ ቢኖርህም ምንችክ አለማለት ጥሩ ነው፡፡ ‹‹Flexible›› መሆን አለብህ፡፡ ነገሮች በራሳቸው ሂደት ስለሚያልፉ ክፍት መሆንና አለመደናገጥ ተገቢ ነው፡፡

ዘሃበሻ፡- ፀደኒያ ለምን የተፈጠረች ይመስልሻል?
ፀደኒያ፡- ‹‹I don’t know›› በቃ አሁን ያለሁበትን ዓይነት ህይወት ይኖረኛል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ ሙዚቃ እንደምወድ አውቅ ነበር፡፡ እንዴት እንደማሳካው ግን አላውቅም፡፡ ቤተሰብ አሳምኜ ‹‹ዘፋኝ እሆናለሁ?›› የሚለውን ሳስበው ከባድ ነበር፡፡ ደስታ የሚሰጠኝ ሙዚቃ መውደድ ብቻ ነበር፡፡ ተምሬ ዩኒቨርስቲ ገብቼ በትምህርት ስኬታማ የሚባሉት ዶ/ር፣ ኢንጂነር የመሆን እቅድ አልነበረኝም፡፡ ማትሪክ ስፈተን አጥንቼ አልተፈተንኩም፡፡ ዲግሪ ይዤ ቢሮ ልቀመጥ? ብዬ ማጥናትን አቁሜ ነበር፡፡ (አልፈልገውም በሚመስል ስሜት ውስጥ ሆና) የሚሆነው ይሆናል ብዬ ዘግቻለሁ፡፡ የተፈጠርኩት ለመዚቃ ነው ብዬ ብቻ አስብ ነበር፡፡ አሳካዋለሁ፣ አላሳካውም የሚለው የእኔ ችግር አይደለም፡፡
ዘሃበሻ፡- ሬዲዮ ላይ ‹‹ሆስት›› ነሽ፡፡ አክሲዮን ማህበር ለማቋቋም እየሰራሽ ነው፡፡ ግን የተፈጠርኩት ለሙዚቃ ነው እያልሺኝ ነው፡፡ አይጋጭም?
ፀደኒያ፡- ሙዚቃን እርግፍ አድርጌ ትቼ ሌላ ስራ ብሰራ ይጋጭ ነበር፡፡ የሬዲዮ ስራ ያለው የመዝናኛ ዝግጅት ነው፡፡ አክሲዮኑም አሳስቦት የሚሰራው ለሙዚቃ ነው፡፡ ሌላ ታሪክ የለውም፡፡ ዞሮ ዞሮ እዚያው ክበብ ውስጥ ነኝ፡፡ ዘፋኝ ሆንኩኝ፣ የተወሰነ ደረጃ ላይ ደረስኩ፡፡ ትንሽ ስም አገኘሁ፡፡ ሰው ነኝና ሌላ ነገር እፈልጋለሁ፡፡ ያገኘሁትን ስም ለሙዚቃ ብቻ መጠቀም አልፈለኩም፡፡
ዘሃበሻ፡- በሙዚቃ ተጽዕኖ ፈጥረሻል?
ፀደኒያ፡- ገና ነኝ፡፡ ፀደኒያ ሲባል ሰው የሚያስታውሰው የተወሰነ ነገር ይኖራል፡፡ የኮራ የሙዚቃ ሽልማትን ታያይዛለህ፡፡ ይህ በራሱ አንድ ዕድል ነው፡፡ የሚፈጥረውም መጠነኛ ተፅዕኖ ይኖራል፡፡
ዘሃበሻ፡- ነፃነት የሚሰጥሽ ትርጉም ምንድን ነው?
ፀደኒያ፡- ያለምንም ውጫዊ ተፅዕኖ በራስህ አመዛዝነህ አንድ ነገርን ማድረግ ነው፡፡ ‹‹ዝናን እንዴት ትቆጣጠሩታላችሁ?›› ብለው ይጠይቁኛል፡፡ ዝናን መቆጣጠር ካልቻልክ የተጠመደ ፈንጂ ማለት ነው፡፡ እኛ ሀገር ብዙ ችግር የለም፡፡ ውጪ ሀገር ስታይ ራሳቸውን በጣም ይኮፍሱና ከኢንዱስትሪው ይጠፋሉ፡፡ መቅበጥም ሰው መናቅ ይጀምሩና ከማህበረሰቡ ይገለላሉ፡፡ እኔ ነጻነቴን በጣም እፈልጋለሁ፡፡ የትም ቦታ ልታገኘኝ ትችላለህ፡፡ የመብራት ቢል ስከፍል ልታገኘኝ ትችላለህ፡፡ የኢትዮያ ህዝብ ደግሞ አይረብሽህም፡፡ ነፃነት የምታሳጣው ራስን በራስህ ነው፡፡
ዘሃበሻ፡- ለምሳሌ ቸኩለሽ፣ ዝናብ ቢሆን እና አንበሳ አውቶቢስ ቢመጣ ትሳፈሪያለሽ?
ፀደኒያ፡- ይቅርታ መኪና አለኝ፡፡ (ሳቅ) ድሮም ቢሆን በባስ አልሄድም፡፡ የነፃነት ጉዳይ ሳይሆን መጨናነቅ ስለምፈራ ነው፡፡ ዘፋኝም ሳልሆን በፊት ባስን አልጠቀምም ነበር፡፡ ታክሲ ግን ውይይትም ሆነ ሚኒባስ አስቁሜ እሄድ ነበር፡፡
ዘሃበሻ፡- ነፃ ሴት ትመስይኛለሽ፡፡ አንድ የተመቸሽ ቦታ ገብተሸ ቢራ አዘሽ ልትጠጪ ትችያለሽ፡፡ ትሰሪበት የነበረ የምሽት ክበብ ውስጥ ባንኮኒ ላይ ቁጭ ብለሽ የፈለግሽውን አስቀድተሸ ስትጠጪ፣ ሰዎች በተሰበሰቡበት ‹‹እያጨበጨብ ሽ›› አስተናጋጅ ስትጠሪና ነፃ ሆነሽ ስትጫወቺ አይቼሽ አውቃ ለሁ፡፡ ብዙዎች አርቲስቶች ላይ የማይታየው ይህን ነፃነት ከየት አገኘሽው?
ሲመስለኝ አስተዳደጋችን ወታደራዊ (ቁጥጥሩ ጠበቅ ያለ) ነበር፡፡ የሴት ጓደኛ እንኳን መያዝ አይፈቀድልኝም ነበር፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ስገባ ግን ሙሉ ለሙሉ ነፃ ሆንኩ፡፡ በልጅነቴ ያጣሁትን ነፃነት ማጣጣምና መፈለግ ይሆናል፡፡ የትም ገብቼ የፈግኩትን ልበላ፣ ልጠጣ እችላለሁ፡፡ ምንም ችግር የለብኝም፡፡S

Go toTop