ክፍል አንድ
ትላንት፣እሁድ፣ ግንቦት 14′2ዐዐ3 ዓ.ም፣ የእናቴን አርባ አወጣኹ፡፡ ውስጤ የፈጠረውን ስሜት ልገልፀው አልችልም፡፡ ደስታ አይደለም፡፡በውስጤ ያለው ባዶነት ደስታን ውጦ የሚያስቀር ጨለማ ጉድጓድ ነው፡፡ እርካታ ብለው የተሻለ ይመስለኛል፡፡ የእናቴ ነፍስ ከእንግዲህ የፍርድ ቀንን በሰላም መጠበቅ ትችላለች ብዬ አስባለኹ፡፡
በባህላችን ለቅሶ ይከበራል፡፡ ሙታንን እንደ ኢትዮጵያዊያን የሚያከብር ሕዝብ የለም፡፡ ከ3 እስከ 7 ቀናት እያለቀስንላቸው እንቀመጣለን፡፡ በ12 እና በ 3ዐኛው ቀናት በቅዳሴ ግዜ ምልጃ ይሰማላቸዋል፡፡ በ4ዐኛው ቀን ሰፋ ባለ ዝግጅት ይታሰባሉ፡፡ ለሙት ዓመታቸው ፀበል ፀዲቅ ይዘጋጃል፡፡ የሚችል፣ ሰባተኛውን ዓመት ድንኳን ጥሎ እየፀለየ፣ እየበላና እየጠጣ ያስታውሳቸዋል፡፡
ይህንን ሁሉ እንደኋላ ቀር ባህል የሚቆጥሩት እንዳሉ አውቃለኹ፡፡ እኔ ግን አልስማማም፡፡ ለሚወዱት አይበዛም፡፡ ከእኛ ኋላቀርነት ይልቅ፣የፈረንጆቹ ጭካኔ ነው የሚሰቀጥጠኝ፡፡ቀብረው በነገታው normalcy ወደሚሉት መመለስ ነው፡፡ የሰውነትን ዋጋ በእጅጉ እንዳሳነሰ ባህል እቆጥረዋለኹ፡፡ እነሱ እኛን እንጂ፣ እኛ እነሱን ስንመስል ማየት አልሻም፡፡
እናቴን የቀበርኩ ዕለት የመኪና ታርጋ ሲመዘገብ እንደነበር ሰማኹ፡፡ ለኢሕአዲግ አፈርኹለት፡፡ በባህላችን ለቅሶ አይደፈርም፡፡ ይከበራል፡፡ ደመኛ እንኳን ፀቡን ያበርዳል፡፡ በመንገድ የሚያልፍ አስክሬንን፣ ሕዝብ እጅ ይነሳል፣ ወታደር ሰላምታ ይሰጣል፡፡ የሰልስቱ ዕለት ግን ኢሕአዴግ በጋዜጣ የስድብ ናዳ አወረደብኝ፡፡(#ዛሬ እናቱ ከሞቱ 3ኛው ቀን ነው$ እየተባለ፡፡) ሌላ ነውር፡፡ለ4ዐውም አላረፈም፣ታርጋ ሲመዘገብ እንደነበር ሰማኹ፡፡
#ኢሕአዴግ ቀይ መስመር የለውም;$ ብዬ አንድ የሚቀርባቸውን ሰው ባለፈው ሰሞን ጠይቄው ነበር፡፡
#የለውም፣$ ብሎመለሰልኝ ፊቱን ቅጭም አድርጎ፡፡
#ቀይ መሥመር መኖርማ አለበት፡፡ ከፖለቲካ የሚበልጥ እኮ ብዙ ነገር አለ፣$ ብዬ በስሜት መለስኹለት፡፡
ቀይ መስመር ከሌለ ህሊና የለም ማለት ነው፡፡ ህሊና በብዙ ምክንያቶች ይጠፋል፡፡ ጥላቻ አንዱ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ሌላው ነው፡፡ ክፋትም መንስዔ ነው፡፡እንዲህ እንዲህ እያሉ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ የኢሕአዴግን መሪዎች በሚመለከት ግን፣ እስከቅርብ ግዜ ፍርሃታቸው ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ ሕዝብን ያንገላቱ ሰዎች ናቸው፡፡ ይሄ ግን ቀላሉ ወንጀላቸው ነው፡፡ ሀገራቸው ላይ የፈፀሙት ታሪካዊ በደል አለ፡፡የሚሊኒየሙ ጥፋት ነው የሚሉት ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የነብርን ጭራ መያዝ ነው የሆነባቸው፡፡ የነብርን ጭራ ለያዘ ደግሞ፣ህሊና ቅንጦት ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የልማት ተቋም ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ጥናት ግን፣ ፍርሃታቸውን አቀጭጮብኛል፡፡ ምንም ቦታ የለውም ባይባልም፣ አውራ ነው ብሎ ለመከራከር ከዚህ በኋላ ይከብዳል፡፡
እንደጥናቱ ውጤት ከሆነ፣ በኢትዮጵያ፣ ሥልጣን የሀብት ምንጭ ሆኗል፡፡ የባለሥልጣናቱን ስም ባይዘረዝርም፡፡ ይሄ በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እውን ከሆነ፣ ብዙ አሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያ አንዷ ስላልነበረች ስንደሰት ኖረናል፡፡
የ5 ቢሊዮን ዶላር ባለሀብት ጌታ ለመሆን ስለበቁት የዛየር መሪው ሞቡቱ ሴሴኮ አንብበን ለአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን አዝነንላቸዋል፡፡ ሞቡቱ ሥልጣን ሲይዙ አምስት ሳንቲም አልነበራቸውም፡፡ የናይጄሪያው ሳኒ አባቻ ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ጥቂት ዓመታት ከ2 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ወደ ኪሳቸው እንዳስገቡ ሲሰማ የተፈጠረው ድንጋጤ ትውስ ይለኛል፡፡ ከመቼው; ከአፍሪካ ወጣ ስንል ደግሞ፣የኢንዶኔዢያው ሱሃርቶ አሉ፡፡ ከሀገራቸው ላይ ከ15 እስከ35 ቢሊዮን ዶላር ዘርፈዋል፡፡ ጎረቤታቸው የፊሊፕንሱ ፈርዲናንድ ማርቆስ ከ5 እስከ 1ዐ ቢሊዮን ጭጭ አድርገዋል፡፡ በአውሮፖ ደግሞ፣ የሰርቢያው ሚሊሶቪች እንደምንም ብለው 1ቢሊዮን ሞልተዋል፡፡ይህ ማለት ግን፣ ሁሉም መሪዎች ዘራፊዎች ናቸው ማለት አይደለም፡፡
ይሄ ሁሉ (ከሚሊሶቪች በቀር) ቅድመ ግንቦት 2ዐ 1983 መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የደርግ ባለሥልጣናት ግን፣ ከውስኪና ጥሬ ሥጋ ባሻገር ብዙም አልተጓዙም፡፡ ስኳር የቃሙትም ቢሆኑ፣ የዶላር ሚሊየነር አልሆኑም፡፡ ከአንዲት ሚኒባስ ያለፉት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ደርግ ፈፅሞ ዘራፊ መንግሥት አልነበረም፡፡ ደርግን ያሰከረው የሰው ደም ነበር፣ ገንዘብ ቦታ አልነበረውም፡፡
ሌባ አለመሆኑ ግን ደርግን አያስመሰግነውም፡፡ እኔ በግሌ፣ ሳይሰርቅ ከሚገድል መንግሥት፣ እየሰረቀ የማይገድል መንግሥት እመርጣለኹ፡፡ የሰውን ሕይወት የሚያክል ረቅቅ ፍጥረት በገንዘብ ሊተመን አይችልም፡፡ ደርግ ሳይገድል ቢዘርፍ ይሻል ነበር፡፡ ገንዘብ ይተካል፡፡ ያለቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ግን መቼም አንተካቸውም፡፡
ችግሩ፣ ዘራፊ መንግሥታት ብዙ ጊዜ ገዳይ መሆናቸው ላይ ነው፡፡ የሱሃርቶ መንግሥት በ1ዐሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ፈጅቷል፡፡ከእኛ ቀይሽብር የባሰ ነበር፡፡ የፊሊፒንሱ ማቆርስ መንግሥትም ነፍስ ለማጥፋት አልቦዘነም፡፡ የሞቡቱ ሴሴኮ የግድያ ሥርዓት የተበሰረው ፓትሪስ ሉሙምባን የመሰለ ብርቅዬ መሪ በመቅጠፍ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ መቆሚያ አልነበረውም፡፡ የሳኒ አባቻ መንግሥት ደግሞ ሳዲስት ነበር፡፡ ሰይፉ ለባለቅኔዎች እንኳን አልታጠፈም፡፡
(ይቀጥላል)
ፀሀፊውን ለማግኘት [email protected]