May 20, 2011
46 mins read

በድል ማግስት ሽንፈት እንዳይኾን

(አበበች በላቸው)
መቸም በቱንዝያ እና በግብጽ የተነሳው ሕዝባዊ አብዮት የሁለቱን አገሮች አምባገነን ገዥዎች ከገለበጠ ወዲህ ጭቆናና እና ድህነት በሰፈነበት አገር ሁሉ ስለሕዝባዊ ዐመፅ አስፈላጊነት እና ተገቢነት ብዙ ተጽፏል። ከእነዚህ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ እንደመኾኗ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሕዝባዊ ዐመፅ በአገራችን ሊነሳ እንደሚችል እና መነሳትም እንዳለበት ጽፈዋል። እንዲያውም ሕዝባዊ ዐመፅ አይቀሬነቱ ተተርኮለታል። አልፎ ተርፎም አንዳንዶች መለስ ዜናዊ እንዴት ሊገለበጥ እንደሚችል “የዐመፅ አቡጊዳ” መጻፍ የዳዳቸው አሉ። ይኹን እንጂ ሕዝባዊ ዐመፅ በአገራችን ስለማስፈለጉ ሲነገር አያሌ መሠረታዊ ጥያቄዎች እንደሚነሱ ሊታወቅ ይገባል። “ቢኾን ኖሮ” ደስ ስለሚለን ምኞታዊ እና ነባራዊ ኹኔታ መጻፍ እና ማውራት አንድ ፈርጅ ቢኾንም፣ “ቢኾን ኖሮ” ፖለቲካ ብሎም የፖለቲካ “ትንተና” ሊኖር አይችልም።

የፖለቲካ ትንተና ባንድ ኅብረተሰብ/አገር ውስጥ ካለው ተጨባጭ ኹኔታ ነው መነሳት ያለበት። ተጨባጩን የአገራችንን ኹኔታ ወረድ ብለን እስከምንመለከት ድረስ አንዳንድ ጉዳዮችን እናሳ።

ሕዝባዊ ዐመፅ ለኢትዮጵያ አዲስ ክስተት አይደለም። በየካቲት 1966 ዓ.ም የተነሳው ሕዝባዊ አብዮት የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። ከ37 ዓመት በፊት የተነሳው ይኸው አብዮት ፈላጭ ቆራጩን የኀይለሥላሴን አገዛዝ ሊያስወግድ ቢችልም በሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ግን ግቡን ሳይመታ ቀርቷል። እነዚህም:-

1ኛ) የተፈለገው እና የተጠየቀው ሕዝባዊ መንግሥት እስከዛሬ ሳይቋቋም ቀርቷል፤
2ኛ) ለዐመፁ መነሳት ነባራዊ ምክንያቶች የኾኑት ድህነት እና ኋላ ቀርነት ባሱ እንጂ አልጠፉም፣ ሊቀነሱም አልቻሉም። ይህ ለምን ኾነ ብለን መጠየቅ፣ መወያየት እና መከራከር ያስፈልጋል። አለበለዚያ ከ37 ዓመት በፊት የነበረውን ችግር አሁንም ተሸክመን ዐመፅ ያስፈልጋል ብንል ከታሪክ አለመማራችንን ያሳያል። ከታሪክ አለመማር ደግሞ ውድቀትን መድገም ነው።፡ ይህን ውይይት ካስነሱት ኹኔታዎች አንዱን ማለትም የግብጽን ሕዝባዊ ንቅናቄ ብንወስድ ምንም እንኳ ዐመፁ የሙባረክን አምባገነን አገዛዝ ቢያስወግድም፣ በቦታው እንኳን ሕዝባዊ መንግሥት ሊያቋቁም ቀርቶ የቀድሞን ሥርዐት “ዝንቡንም እሽ” ለማለት ባለመቻሉ፣ እንቅስቃሴው እንደ አዲስ ከትላንት ጀምሮ በታህሪር አደባባይ እንደገና ተነስቷል። ሥልጣን የያዘው ወታደራዊ ኀይል ተመልሶ የሕዝቡን ሰልፍ በድብደባ መበተን ጀምሯል። ይህ ምን ያስተምረናል? “ኀይለሥላሴን ካስወገድኩላችሁ መች አነሳችሁ” ብሎ ሥልጣን የያዘውን ደርግን ያስታውሰናል። ይህ ኹኔታ ደግሞ ለግብጽ አዲስ አይደለም። እ.ኤአ በ1952 የተነሳውን የሕዝብ አብዮት ቀምቶ ሥልጣን ይዞ የነበረውን የኮሎኔል ናስርን ታሪክ ያስታውሷል።

ዐመፅ መቻል አለመቻል የጥያቄው አንድ አካል ሲኾን ዐመፅ ግቡን መምታት አለመምታቱ ደግሞ የጥያቄው ሌላ ጎን ነው። ዐመፅ ግቡን የሚመታው ኅብረተሰባዊ ለውጥ ሲመጣ ነው። ይህን የመሰለ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ደግሞ መጀመርያ በቂ ኅብረተሰባዊ መሠረት/ድጋፍ ያለው ሪፐብሊክ ሲቋቋም ነው። ስለኾነም ስለ ለውጥ የሚያስቡ ሁሉ፣ ስለ አስፈላጊነቱም የሚሰብኩ ሁሉ ይህን ጥያቄ ሊዘሉት አይችሉም። ምክንያቱም በሕዝባዊ ዐመፅ የቆሰለው መንግሥት ጨርሶ ካልተገረሰሰ፣ አንድም እንደቆሰለ አውሬ ይበልጥ ተናካሽ (እንደ ደርግ)፣ ሁለትም መሠረታዊ የድህነት ጥያቄዎችን አድበስባሽ የኾነ መንግሥት ይፈጠራልና ነው። ይህ ኹኔታ ከተፈጠረ ደግሞ “የድሮው መንግሥት ይሻለን ነበር” የሚሉ እንዲነሱ ያደርጋል።
በአሁኑ ጊዜ በተለይም የዳያስፖራውን ድረ ገጾች ስንመለከት ስለ ዐመፅ አስፈላጊነት በሰፊው ይጻፋል። “ምንም ቢኾን ይህ መንግሥት ይውረድ ብቻ” በመሰለ መጣደፍ መሠረታዊ ጉዳዮች ሳይነሱ ላይ ላዩን መጋለብ የተያዘ ይመስላል። ከኻያ ዓመት በፊትም “ምንም ይኹን ደርግ ይውረድ እንጂ” ተብሎ ነበር። ግን ወያኔን የመሰለ የደንቆሮዎች እና የአውሬዎች መንግሥት መጣ። ጥላውን እንኳ የማያምነው ወያኔ ደግሞ በበኩሉ ምንም ነገር ሳይነሳ መርበትበቱን ገሃድ እያደረገው ነው። “ምን . . . .ያለበት ዝላይ አይችልም” ኾነና ኅብረተሰባዊ መሠረቱ ጠብቦ ጠብቦ በወታደሩ ሳንጃ ላይ ብቻ የኾነበት ወያኔ “አንድሽ ትወጭና” በመሰለ የወሮበላ ፉከራ ሕዝቡን በይፋ አስፈራርቷል። መለስም ሊነሳ የሚችለውን ዐመፅ በኤርትራ የተቀሰቀሰ ነው ብሎ “ያገሪቱን ፀጥታ ለማስከበር” ማንኛውንም ርምጃ እንደሚወስድ ከወዲሁ አስታውቋል። በረከት ስምዖን ደግሞ ያወቀና እና የተናገረ መስሎት “በቱኒዝያ እና በግብጽ ለዐመፁ መነሳት ምክንያት የኾነው ነገር በኢትዮጵያ የለም” ብሎ ምንም አለማወቁን አወጀ። ይህን ሲል ሙባረክም “በቱኒዝያ የነበረው ኹኔታ በግብጽ ውስጥ የለም” ብሎ እንደነበር ለበረከት የነገረው ሰው ያለ አይመስልም። ጋዳፊም በበኩሉ “በግብጽ የነበረው ኹኔታ ሊቢያ ውስጥ የለም” ብሎ ያምን ነበር። እንዲያው ጠበቅ ብለን ሳንገባ የድህነቱን መጠን እና የነጻነት መነፈጉን ደረጃ ብናወዳድረው ለመኾኑ የወያኔን ኢትዮጵያ የሚደርስባት አለ? “ ምን ያለበት . . . . .ዝላይ አይችልም” የሚያሰኘውም ይኸው ነው።
ስለ ዐመፅ ተገቢነት ወደሚሰብኩት ፖለቲከኞችም ወደ ዳያስፖራው አባላት መለስ ስንል እንዲያው “ዐመፁ አንዴ ይነሳ እንጂ”፣ “ወያኔ ይውረድ እንጂ” በመሰለ ግልቢያ ይተረካል እንጂ የዐመፅ ጉዳይ በኢትዮጵያ የሚያስነሱትን ዐበይት ጉዳዮች ማንም አላነሳቸውም። የየካቲት 66ቱ ታሪክ እንደሚደገም ማንም ማስታወስ የቻለ ያለ አይመስልም።፡

1) ኅብረተሰባዊ ለውጥ (Social Change) ወይስ የመንግሥት ለውጥ?
ኅብረተሰባዊ ለውጥ ወይስ የመንግሥት ለውጥ? የሚሉት ጥያቄዎች ዝንተዓለም ለውጥ ፈላጊዎችን ሲያከራክር የነበረ የስትራቴጂ ጥያቄ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ “ከሁለቱ አንዱን መምረጥ” የሚለውን ሜታፊዚካዊ አመለካከት ለማንቀሳቀስ ሳይኾን ግንኙነታቸውንም ለማሳየት ነው። አሁን በአገራችን ካለው ኹኔታ ተነስተን በሕዝባዊ ዐመፅ ወያኔ ቢወርድ ምን ኹኔታ ሊፈጠር ይችላል? “ምንም ይምጣ ምንም ብቻ ወያኔ ይውረድ” የሚለውን የሚያጓጓ አመለካከት ለመቀናነቀን ጉልበቱ እንደሚያጥረኝ ለማመን እፈልጋለሁ። የማናውቀውን ሰይጣን ማንገዳገዱ ይሻለናል። ምንም ቢኾን የመናገር እና የመጻፍ ነጻነት በወያኔ ማግስት መከሰቱ የማይቀር ነው። በዚህ መሀል ተቃዋሚ ድርጅቶችም የወያኔ የመከፋፈል ስትራቴጂ ሲነሳላቸው ይተባበሩ ይኾናል። እነዚህ ግን ሊኾኑም ላይኾኑም የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።

በሁለተኛ ደረጃ ግን ከዚህ አልፈን፣ ቀድመን ሄደን መኾን ስላለበትም ማንሳት እና መወያየት አለብን። ከላይ እንደተመለከትነው የፖለቲካ አብዮት በወያኔ መውረድ ሊከሰት ይችላል። መሠረታዊ ጥያቄው ግን የኅብረተሰባዊ ለውጥ ጥያቄ መኾን አለበት። ለወያኔ መውረድ አስፈላጊነት፣ ለሕዝባዊ ዐመፅ መነሳት ዋናዎቹ እና መሠረታዊ የኾኑት የደኅንነት እና የነጻነት መነፈግ ጥያቄዎች ተነስተው መፍትሄያቸው በወያኔ ቀብር ማግስት መፈለግ አለበት። ለምን?
የአገራችን መሠረታዊ ችግሮች (የድህነት፣ ኋለ ቀርነት፣ ድንቁርና፣ ረሃብ፣ በሽታ ወዘተ . . .) እንዲሁም በአስተሳሰብ ደረጃ (PERCEPTION) ያሉ ነቀርሳዎች ሊወገዱ የሚችሉት በኅብረተሰባዊ ለውጥ እንጂ በመንግሥት ለውጥ ብቻ አይደለም። የመንግሥት ለውጥ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችለንን ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ መሠረት ይጥልልናል እንጂ በራሱ አይፈታቸውም። ስለዚህ በመንግሥት ለውጥና (እንደ አንድ ክስትት እና ሂደት) በኅብረተሰባዊ ለውጥ ሂደት መሀል የፋሲል ግምብ የለም። ለምሳሌ ዛሬ ወያኔ ቢወርድ የኢትዮጵያ ችግሮች ወዲያው ይፈታሉን? አይፈቱም። ለዚህ ነው ከመንግሥታት ለውጥ ባሻገር ስለ ኅብረተሰባዊ ለውጥ ማሰብ ያለብን። እንግዲያው ኅብረተሰባዊ ለውጥ ምን ያስከትላል?
አገራችን ኢትዮጵያ በቂ የተፈጥሮ ሀብት ያላት፣ ሕዝቦቿም ትጉህ እና ጠንካራ ሠራተኞች ኾነው ከድህነት እንዳንወጣ ማነቆ የኾነብን ምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልሱ ኢትዮጵያን ፈላጭ ቆራጭ በተራ ሲገዛ የነበረበት አሁንም ከፋሽስታዊ አገዛዝ ባልተናነስ ጭቆና የሚገዛት መንግሥት በመኖሩ ነው። በአገራችን ሕዝቡ ፈልጎና ፈቅዶ የመረጠው መንግሥት ተቋቁሞ አያውቅም። በዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ ዕድገት የልማት መንገዶች ሁሉ ተዘግተው ጥቂቶች ብቻ የሚፈነጩባት አገር ኾናለች። የኢኮኖሚ ዕድገት እና ልማት ከአገዛዙ ጠባይ ጋራ የተቆራኘባት አገር ነች። በዚህም ምክንያት አሁንም ያለው አገዛዝ (ወይም ወደፊትም ሕዝብ ያልመረጠው መንግሥት) የሚገረሰስበት የፖለቲካ አብዮት የመጀመርያው ርምጃ የሚኾነው ለዚህ ነው።

በኅብረተሰባዊ ለውጥ ሊወገዱ የሚገባቸው እና የአገሪቱን ልማት ማነቆ ኾነው የያዙት ችግሮች ምን እንደኾኑ እንመልከት፤
1) ዲሞክራሲ እና ነጻነት ባለመኖሩ የሕዝቡ ተነሳሽነት እና በነጻ መንቀሳቀስ፣ መደራጀት፣ በልማት እና በኢኮኖሚ መስክ መንቀሳቀስ አለመቻል . . . .
2) የገጠር ልማት ፦
ሀ) አርሶ አደሩ በነጻ እና እንደ ልቡ እንዳያመርት መሬት በመንግሥት እጅ መኾን እና ወያኔም የመሬት ሥሪቱን ለመቀየር አለመፈለግ አርሶ አደሩ ባለበት ታፍኖ እንዲረገጥ በመደረጉ፤ ምርታማነቱም እየቀነሰ ሄዷል።
ለ)አርብቶ አደሩም ለኑሮ ዘይቤው ዕውቅና ሳያገኝ ቀርቶ መንግሥት ገበሬ ካልኾንክ እያለ አፍኖ ይዞ የወያኔ መንግሥትም ስለ አርብቶ አደሩ ልማት የሚያውቀውም ባለመኖሩ የአርብቶ አደሩን መሬት ለውጭ ባለ ሀብቶች በሊዝ እየቸበቸበ አርብቶ አደሩን ለክፉ ድህነትም ብቻ ሳይኾን ለዐመፅም እየጋበዘው ነው።
3) የአካባቢ ውድመት፦ ገና ከኀይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የኤክስፐርቶች ማስጠንቀቂያ ሰሚ በማጣቱ ዛሬ የኢትዮጵያ አካባቢ ውድመት እጅግ አስጊ ኹኔታ ላይ ይገኛል። የገጠር ልማት ላይም ከፍተኛ አንደምታ አለው።
4) የሴቶች ጭቆና፦ ሴቶችን የሚጨቁን ኅብረተሰብ ቋጥኝ አንስቶ ራሱ ላይ እንደመጣል እንደሚቆጥረው ሁሉ በሴቶች ጭቆና ላይ የተተበተበው ኅብረተሰባችን የሴቶችን እኩልነት ለማምጣት ገና ብዙ መጓዝ እንዳለበት የታወቀ ነው። ደርግ እና ወያኔ “የሴቶች ጭቆና” እያሉ ከማላዘን አልፈው የፈየዱት ምንም ነገር ባለመኖሩ እና ይብሱኑ ብለው ደግሞ ሴቶች በራሳቸው ጥረው ግረው ለእኩልነታቸው እንዳይታገሉ መንገዱን ሁሉ ዘግተውታል። በኅብረተሰቡ ግማሽ አካል ላይ ጭቆናና እና ጥቃት እየተሰነዘረ ዲሞክራሲ እና ልማት ብሎ ነገር ስለማይኖር የሴቶች እኩልነት ጥያቄ ማእከላዊ ጥያቄ ነው።
5) የዘላቂ ልማት ትኩረት ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይኾን ለወደፊቱም ስለኾነ ምን ዐይነት የፖለቲካ ሥርዐት፣ ኅብረተሰባዊ ትስስር፣ ኢኮኖሚ፣ የአካባቢ ይዞታ ለመጭው ትውልድ እናስተላልፋለን የሚለው ጥያቄም ማእከላዊ የልማት ጥያቄ ነው። ስለኾነም ሕፃናትን እና ወጣቶችን እንዴት እንደምንኮተኩታቸው ማእከላዊ የልማት ጥያቄ ነው።
6) የሕዝብ ብዛት(POPULATION) የማንኛውም አገር የተፈጥሮ ሀብት ሊመግብ እና ሊደግፍ የሚችለው የሕዝብ ብዛት መጠን አለው። በአገራችን የሚታየው የውልደት ምጣኔ (BIRTH RATE) ከአገሪቱ ሀብት ጋራ ሲመጣጠን እጅግ ከፍተኛ በመኾኑ ለድህነትም፣ ለኋላ ቀርነትም አስተዋጽኦ አድርጓል። የሕዝብ ቁጥርን እና የውልደት ምጣኔ ማስተካካል መሠረታዊ የልማት ጥያቄ ነው።
7) የጤንነት ጉዳይ፦ ሕዛባችን አስከፊ ግን በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች እየተመታ የሚሞተው እና የሚሰቃየው ቁጥሩ ከፍተኛ ነው። ኤች.አይቪ.ኤድስ፣ የሳምባ ነቀርሳ፣ ወባ እና ሌሎቹም በሽታዎች ቁጥሩ እጅግ ብዙ የኾነ ሕዝብ እየገደሉ ነው። ሕዝብን ገዳይ ከኾኑ ደዌዎች ነጻ እንዲኾን ማድረግ መሠረታዊ የልማት ጥያቄ ነው።
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ጥያቄዎች ኅብረተሰባዊ ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር የሚፈቱ ጥያቄዎች አይደሉም። የጠቀስነው የፖለቲካ አብዮት (ሕዝባዊ ዐመፅ) ተሳክቶ ወደ ኅብረተሰባዊ ለውጥ ሂደት ለመሸጋገር በሕዝብ ተቀባይነት ያለው ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ቢቋቋምም በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ የአመለካከት ነቀርሳዎች እንቅፋት እና ጋሬጣ ሊኾኑ ስለሚችሉ ከወዲሁ ሊታሰብባቸው በተለይም መልእክት የማስተላለፍ ችሎታ ያላቸው ኀይሎች ትኩረት ሊሰጡበት የሚገባ ጉዳይ ነው። እነዚህ የአመለካከት ነቀርሳዎች ምንድን ናቸው?
ኅብረተሰባዊ ለውጥን በፖለቲካ ለውጥ ብቻ ወስነው ጉዳዩ በወያኔ መውረድ ብቻ የሚፈታ የሚመስላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ይኹን እንጂ በአገራችን ለሚደረገው ኅብረተሰባዊ ለውጥ የቆሙ ሁሉ በግለሰብ ደረጃም ቢኾን ከእያንዳነዱ የሚጠበቅ ይኖራል። ይኸውም የአመለካከት ለውጥ ማድረግን ይመለከታል። በወያኔ አገዛዝ የበገኑ ሁሉ ራሳቸውን ለመቀየር የያዟቸውን ጎጂ አመለካከቶች ለማስወገድ በራሳቸው ላይ “ጦርነት ማወጅ” አለባቸው እላለሁ።

ኢትዮጵያዊነት፦ ኢትዮጵያን ከእነሕዝቦቿ የምናስባት ከኾነ በአገራችን ብዙ ሕዝቦች(ብሔሮች) እንደመኖራቸው መጠን ኢትዮጵያ የእነዚህ ሁሉ ሕዝቦች አገር ልትኾን ይገባታል ብለን መነሳት አለብን። እነዚህ ሕዝቦች “አገሬ ኢትዮጵያ” የሚሉበትን የፖለቲካ ኹኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ ወዘተ . . .ስንል ስለ አንድ ወይም ሁለት ባሕል እና ታሪክ ብቻ መኾን የለበትም የምናስበው። የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚባለው ሁሉ የኦሮሞው፣ የሶማሌው፣ የአፋሩ፣ የሐመሩ፣ የጉምዙ . . .ወዘተ . .ታሪክም እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ መወሰድ አለበት። በቀድሞቹ ነገሥታት የተገፉ እና የተመዘበሩ ሕዝቦች ኢትዮጵያዊነት ሲባል በሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ እኩልነትን ይጠይቃሉ። ይህ ደግሞ ለአገሪቱ አንድነት ዐይነተኛ ጥያቄ ነው። ብዙ ጊዜ በእኛ በኢት ጵያውያን ዘንድ እቅጩን አፍርጠን መወያየት አልተለመደም። አንዳንዴ ደግሞ እቅጩን ካላፈነዳን አይኾንም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን በአማራው ወይም በአማራ-ትግራይ መነጽር ማየት በአስተሳሰብ ረገድ ለኅብረተሰባዊ ለውጥ አንደኛው ነቀርሳ ነው። [ይህ ጥያቄ ብዙ ውይይት እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። እዚህ ላይ ያነሳነው አመለካከት ለአገሪቱ አንድነት ነቃይ መኾኑን ለመጥቀስ ያህል እንጂ ውይይት ውስጥ እንዳልገባን ለማስገንዘብ እወዳለሁ።] (ከታች የሚገኘውን ተጨማሪ ማስታወሻ -1 ይመልከቱ)

የወንዱ ትምክህተኝነት፦ የሴቶችን እኩልነት ጥያቄ ደርግ እና ወያኔ በማያውቁት ጉዳይ ገብተው የራሳቸውን ትምክተኝነት መሸፈኛ ባደረጉት “የሴቶች ጥያቄ” አስከልክለው በማስቀረታቸው የሴቶች እኩልነት ጉዳይ አንድም መቀለጃ አለዚያም የለጋሾችን ጆሮ መሳቢያ ኾኖ ቀርቷል። የፆታ ግንኙነት ጉዳይ ግን እጅግ ከባድ ጥያቄ አንድምታውም ከብዙዎች የኅብረተሰባዊ ለውጥ ዋና ዋና ጥያቄዎች ጋራ ዝምድና ያለው ነው። ከኅብረተሰቡ የግማሹን መብት እና እኩልነት የማያመጣ ለውጥ ኅብረተሰባዊ ለውጥ ሊኾን አይቻለውም። ለኅብረተሰባዊ ለውጥ ቆመናል የሚሉት ሁሉ በርግጥም የትምክህተኛ ካባቸውን ማውለቅ አለማውለቃቸው የሚታወቅበት ጥያቄ የሴቶች እኩልነት ጥያቄ ነው። ከዚያም በላይ የአንድ ግለሰብ ሰብአዊነቱ የሚለካበትም በዚሁ ጥያቄ ነው። በዚህ ረገድ ለኅበረተሰባዊ ለውጥ እንቅፋት ወይም ነቀርሳ የኾነው አስተሳሰብ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ ማየት፣ ሴቶችን የወሲብ ማርኪያ ብቻ አድርጎ ማየት፣ በሴቶች ላይ የተለያዩ ጥቃቶችን ማድረስ፣ የመሳሰሉትም ይገኙበታል። ይህን የመሰለ ነቀርሳ ይዞ ኅብረተሰባዊ ለውጥ ማለት ትርጉም አይኖረውም። “መለስ ወይም ወያኔ ይውረድ” ማለትም የዐይንን ጉድፍ ሳያወጡ ይኾንና ያስተዛዝባል።
“ከእኔ በላይ ላሳር”፦ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለራሳችን በግላጭ እና ዕቅጩን ከመናገር ይልቅ በተዘዋዋሪ እና ከተቻለም በሰም እና ወርቅ መናገር እንወዳለን። ነቀርሳ ይዞ ለውጥ የለምና ከወዲሁ ማራገፍ ካለብን ነቀርሳዎች አንዱ ስለ ራሳችን ያለን ግምት ነው። በተሰማራንበት ሁሉ ፍሬያማ ሲልም ልቆ መገኘት (To Excel) ሳይኾን ኮከብ ኾኖ መታየትን እናስቀድማለን። ኮከብ መኾን መደነቅን( ርግጡ ግን ማዳነቅ ነው) ስለሚያስከትል “መታወቅንም” ያስከትላል። በዚህ ምክንያት በምንሠራው ሁሉ ከይዘቱ ይልቅ ቅርጹ (Form) ላይ ማተኮርን እንወዳለን። ይህ አመለካከት በመሠረቱ ሐቀኝነት ይጎድለዋል። ፖለቲከኛው የሚታየው በሆታ ሲያሸበርቅ፣ በሚዲያ ጠዋት ማታ ሲነገርለት፣ ባጭሩ ኮከብ ኾኖ መታየትን እንጂ እንደ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ አገሩንም ኾነ ሕዝቡን ለማገልገል የተነሳ አድርጎ የሚቆጥረው ትንሽ ነው። ዓላማውና ሕልሙ ጠዋት ማታ ሥልጣን . . . ሥልጣን. . . .ነው። አንዳንድ ጊዜ ሕልሙ ቀድሞት ሄዶ በሌለ ኹኔታ ወይም በማይኾን ስትራቴጂ ሥልጣን ሲይዝ ይታየዋል። በየድረገፁ እና ፓልቶኩ የሚለፈልፉትም በፍጹም ባልተረዱት ጉዳይ ላይ አዋቂ ኾነው ለመቅረብ የሚዳዳቸውም በርካታ ናቸው።፡ (ከታች የሚገኘውን ተጨማሪ ማስታወሻ -2ን ይመልከቱ)

ከዚህ ጋራ የተያያዙ በርካታ የአመለካከት ችግሮች እንዳሉብን የታወቀ ነው። በዚህ ረገድ በፖለቲካ አብዮቱ ማግስት መደረግ ያለበት ነገር ቢኖር ባህላዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ የትምህርት ዘመቻ ማድረግ ነው። ለውጥ በቅርብ ቢቀሰቀስ ምን ሊፈጠር ይችላል? ከሁሉ አስቀድመን የወያኔ መንግሥት መወገድ አለበት የምንለው ወያኔን እንደ ድርጅት በመጥላት ብቻ ሳይኾን በአገራችን ለሚያስፈልገው ኅብረተሰባዊ ለውጥ ዋነኛው እንቅፋት ወያኔ ስለኾነ ነው። ወያኔን ለማስወገድ ሕዝባዊ ለውጥ በቂ ነው። ጥያቄው ግን እንዴት? የሚለው ነው።
አሁን ባለው ተጨባጭ የአገሪቱ ኹኔታ በተለይም በቱንዚያ እና በግብጽ እንዳየነው ሕዝባዊ ዐመፅ በማስነሳት እና ወያኔን ለማውረድ የግምባር ቀደም ድርጅት አስፈላጊነት ዋና ችግር አይደለም። የግለሰቡ ሚና ቦግ ብሎ የሚታይበት ለውጥ ነው የሚኾነው። የግለሰቦችን ሚና በሚመለከት አንዳንድ የጽንፍ አካሄድ ችግሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ መልእክት ማስተላለፍ የሚችሉ ሁሉ ከወዲሁ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ መልእክት ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል።

ሀ) ለውጡ የወያኔ መሠረታዊ ፖሊሲዎችን የሚቃረን መኾን አለበት፤ ከዚህም ዋነኛው “የትግራይ ሕዝብ ተወካይ እና ግምባር ቀደም ነኝ” የሚለው ተረቱን በፍጹም መቃረን ያስፈልጋል። ለውጡ ማነጣጠር ያለበት ወያኔን እንደ መንግሥት እንጂ እንደ ትግራይ ሕዝብ ተወካይ ባለመወሰድ ነው። ነውጡ የወያኔን መንግሥት እና የትግራይን ሕዝብ ለይቶ ማየት አለበት። የትግራይን ሕዝብ የነውጡ አጋር መደረግ አለበት። (በትግራይ ሕዝብ ላይ የተጫነውን የቁጥጥር፣ የጭቆናና የስለላ መዋቅር እንዲፈራርስ ማድረግ ከትግሉ ዋነኛ መልእክቶች አንዱ ሊኾን ይገባዋል። )
ለ) “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት” በርግጥም ሊከሰት የሚችለው ከወያኔ የተለየ ግብረገብነት ሲኖር ነው። በዚህ ረገድ ወያኔ ለአገዛዙ የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች እና አስተሳሰቦች መቃረን አስፈላጊ ነው። ዕቅዶቹንም በሚገባ ማወቅ እና መቃወም። ነውጡ ቢነሳ እንደሌሎቹ የተገረሰሱት አምባገነኖች ፖሊሲ አሻሽላለሁ፣ ይኼን አሻሽላለሁ፣ ነጻ ምርጫ አዘጋጃለሁ ብሎ ቢያላዝን መልሱ አይኾንም መኾን አለበት።
በዚህ ረገድ ዐመፁ እንደተነሳ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ።

የግለሰቦች ሚና፦ ግለሰቦች የሕዝቡ መሠረታዊ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ዐመፅ ማቆም እንደሌለበት ተግተው መታገል ይኖርባቸዋል። ወያኔ እንደተለመደው እንዳይገዛ (UNGOVERNABLE SITUATION) ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ቶሎ ብሎ በየቀበሌው ሕዝባዊ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ማድረግ። እነዚህም ኮሚቴዎች ከወያኔ ጆሮ ጠቢዎች ነጻ መኾናቸውን ማረጋገጥ፣ ቀበሌዎች እንዲፈርሱ ማድረግ።
የሠራዊቱ ሚና፦ ለሕዝባዊ ዐመፁ መሳካትም ኾነ መዳፈን የሠራዊቱ ወሳኝ ሚና የኢትዮጵያ ወታደሮች በርግጥም በአገሪቱ ታሪክ በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ያለውን መንግሥት መጠበቅ ወይም ማውረድ በሚለው ምርጫ ላይ ሊወስኑ ነው። ሠራዊቱ ያለው መንግሥት መውረድ አለበት ብሎ የማመን አማራጩ ከፍተኛ ነው። ለዚህ ነባራዊ ምክንያቱ በሠራዊቱ ውስጥ ያለው የዘር መድልዎ እና የአንድ ብሔር የበላይነት፣ ወታደሩ ዩኒፎርም ይልበስ እንጂ አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ሥራ አጥ ስለኾነ የሕዝቡ በድህነት መማቀቅ የእርሱም መማቀቅ ነው፤ ወያኔ የሕዝብ ተቃውሞ ያለበት በመኾኑ አንድ ነውጥ ቢነሳ ይህን ተቃውሞ ሊያሳይ ስለሚችል ነው። በዐመፁ ጊዜ ሕዝቡ/ሰልፈኛው የወያኔን መንግሥት እና ሠራዊቱን ለያይቶ ማየት አለበት። በሠራዊቱ ውስጥ ያለውን ጉምጉምታ ሰልፈኛው ተረድቶ ድኻው ወታደር አጋሩ እንዲኾን ማድረግ አለበት።
እንግዲህ እስከ አሁን የዘረዘርነው ዐመፅ ማስፈለጉን፣ ዐመፅ በኢትዮጵያ እንደሚቻል እና መነሳትም እንዳለበት፣ እንዲሁም ዐመፁ ወደ ኅብረተሰባዊ ለውጥ ካላመራ ለውጥ እንደማያመጣ እና በተጨባጭም ግለሰቦች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው።

ከዚህ በተረፈ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከኾነላቸው ጥሩ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በሚያስማማቸው የፖለቲካ መድረክ ተስማምተው ለምናልባቱ ሕዝባዊ ዐመፅ ቢነሳ ምን ማድረግ እንዳለባቸው መስማማት ቢችሉ ትግሉን ያግዘዋል። ከዚያም አልፎ ወያኔ በዐመፅ ቢወርድ ሌላ ወታደራዊ አገዛዝ ልክ እንደ ደርግ “የተደራጀ ኀይል ባለመኖሩ” እስከ ጊዜው ሥልጣን ይዣለሁ” ብሎ ሌላ ኻያ ዓመት ከሚፈነጭብን ከአሁኑ አንዳንድ ንቅናቄዎች እንደሚያደርጉት በስደት ላይ ጊዜያዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት አቋቁመው፣ ጊዜያዊ ሸንጎ ሰይመው ቢዘጋጁ ለትግሉ የልብ ልብ ሊሰጠው ይችል ነበር። ይህን ማድረግ ችሎታውም ዝግጁነቱም የሌለው ተቃዋሚ ድርጅት ዓላማው እንደ ኮቲዲቩዋሩ ባግቦ ከወንበሩ ጋራ መሞት የመረጠ ነው።
በመጨረሻም ለማንሳት የምፈልገው ነጥብ መለስ ዜናዊ ወይም የወያኔ መንግሥት “ነውጥ ተነሳብኝ” ብሎ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረገን ህዝብ “ወደፊት ምን ይደርስብኛል ሳይል ሊጨፈጭፍ ይችላልን? የግደል ትዕዛዝ የሚሰጡት መኮንኖችም ኾኑ ባለስልጣናት ከታሪክ ፊት ፍርድ ሳያገኙ ይቀራሉን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱ ከፍርድ እና ከቅጣት አያመልጡም ነው። መለስ ዜናዊ “ነውጥ ተነሳብኝ”፣ “ሕገ መንግስቱን ሊንዱ ተነሱብኝ” የሚለው መዝሙሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያረጀ እና የነጋበት ጅብ ምክንያት እንደኾነ ማንም ስለሚያውቀው ትላንት በተባበሩት መንግሥታት ሳይቀር “አንቱ” የተባሉት እነ ጋዳፊ እንኳን ዛሬ በነፍሰ ገዳይነት ሊከሰሱ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። ሐያላን ለጋሽ መንግስታትም የመለስን አምባገነንነት አገዛዝ የሚፈነገለው ጥፍቶ ነው እንጂ መለስ እንደነጋበት ጅብ በመደናበር ህዝብን ቢጨፈጭፍ ውግዘት እንደሚከተልበት፤ ከስልጣን ከወረደም ከፍርድ እንደማያመልጥ የታወቀ ነው።

ይሁን እንጂ በዳያስፖራው ውስጥ ያለው የተደራጀው ክፍል ከፍተኛ የሎቢ ሥራ መሥራት ይኖርበታል። በዚህ በኩል ዳያስፖራው እጅግ ደካማ ነው።ያ ሁሉ የድረ ገጽ የፖለቲካ ጸሐፊ ገሚሱ ከዚህ ወጣ ብሎ በሰብአዊ መብት መጉድል ዙሪያ የሎቢ እና የአድቮኬሲ ሥራ ቢሠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። ተቃውሞ እና ትግል መግለጫ እና ጽሑፎችን በማውጣት ብቻ አይከናወንም። እንዲያውም ተቃዋሚው የሰከነ ለመኾኑ ማረጋገጫ ከሚኾኑት ጉዳዮች አንዱ የሎቢ እና አድቮኬሲ ሥራ መሥራቱ ነው።
** *

ተጨማሪ ማስታወሻ
1) በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ የሚነገረው “ኢትዮጵያዊነት” የድሮውን፣ የጥንቱን፣ የገለማውን እና በኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ወደ ሙዚየም የተላከውን የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን መመለስ ይመስላል። የዚህ አስተሳሰብ ነጸብራቁ በድሮው ሥርዐት ተጨቁነው እና ተረግጠው የነበሩ ብሔረሰቦችን ወደመናቅ የሚሄድና በተለይም በኀይለሥላሴ መንግሥት ይካሄድ የነበረውን ፀረ ትግሬነት ነው። በአሁኑ ጊዜ በወያኔ መንግሥት ተቃርኖ (REACTION) መልሶ የመጣው ይኸው ፀረ-ትግሬነት ነው። ይኼ አስተሳሰብ ገኖ እያለ ዐመፅ ቢነሳ ፀረ ትግሬ መልክ ይዞ አንዳንድ አጸያፊ ተግባሮች ሊፈጸሙ ይችላሉ። የሕዝባዊ ዐመፅ በርግጥም ሕዝባዊነቱ እና ኢትዮጵያዊነቱ የሚለካው ይህን ወያኔ የፈጠረውን የዘር ፖለቲካ ከአእምሮው አውጥቶ ጭቁኑን የትግራይን ሕዝብ ከጨቋኙ ወያኔ ለይቶ ሲያይ እና የትግራይን ሕዝብ አጋር አድርጎ ሲወስድ ነው። በወያኔ ፕሮፖጋንዳ ካልታወርን በስተቀር የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። ጭቁንም ነው። ለዚህ ነው በጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚቃጣ ዐመፅ ሕዝባዊ ሊኾን የሚችለው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መልእክት የማስተላለፍ ችሎታ ያላቸው ሁሉ (ጋዜጣ ሬድዮ፣ ድረ ገጽ፣ ወዘተ . . .)በዚህ ጥያቄ ላይ ሰፊ ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
2) በአሁኑ ጊዜ በግልጽ የሚታዩ እና ለሕዝባዊ አብዮቱ እንቅፋት ሊኾኑ የሚችሉ የአመለካከት ችግሮች አሉ። እነዚህ ችግሮች በዳያስፖራው በቅጡ ሲነጸባረቁ ይታያሉ። ከእነዚህም መሀል፦
• አለማወቅ፣ ለማወቅም አለመሞከር፦ እንደሚታወቀው ዳያስፖራው የሚኖርበት ክፍለ ዓለም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መጥቆ እና አድጎ ያለበት፣ በዚህም ከኢንፎርሜሽን ብዛት የተነሳ “ኢንፎርሜሽን ግላት” (INFORMATION GLUT) ያለበት ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያውያን (በዳያስፖራ ውስጥ ያሉ) ምን ያህል ራሳቸውን አስተምረዋል ወይም እያስተማሩ ነው ብለን ብንጠይቅ ቁጥሩ እጅግ አድርጎ በሚያስደነግጥ አኳኋን ጥቂት ኾኖ እናገኘዋለን። የዳያስፖራውን ድረ ገጽ ማንበብ አንድ ጥሩ ጎን ቢኾንም ስለኢትዮጵያ፣ ስለ ልማት እና ሌሎችም የተጻፉ ጽሑፎችን በማንበብ ረገድ ግን ሪከርዱ በጣም ዝቅተኛ ነው። በዚህ ረገድ ራሱን በማስተማር መጭውን ሕዝባዊ ዐመፅም ኅብረተሰባዊ ለውጥ ሊደግፍ ሲችል በኢንፎርሜሽን ሐይቅ ውስጥ ቁጭ ብሎ ጆሮውንም ዐይኑንም የደፈነ ይመስላል።
• ትናንሽ እግዜሮች መፍጠር፦ እኛ ኢትዮጵያውያን ካሉብን የአመለካከት በሽታዎች አንደኛው ፖለቲከኞችን እንደ ጣዖት ማምለክ ነው። አንድ ፖለቲከኛ ብቅ ሲል፣ የተወዳጅነቱ መለኪያ የሚኾነው ወያኔን መስደብ እና ማውገዝ ሲጀምር ማምለክ ይጀመራል። ያ ሰው በወያኔ ከታሰረማ ወንድ ከኾነ በፈረደበት ማንዴላ ስም ይጠራል፤ ሴትም ከኾነች አንግ ሳን ሱ ቺ ትባላለች። ይህ አመለካከት የብስለት ምልክት ሳይኾን የተገላቢጦሽ ነው። አሪስቶትል ስለ ልጆች አመለካከት ሲናገር “ሲወዱም ጽንፍ ፤ሲጠሉም ጽንፍ ናቸው” ይላል። በእኛም በኩል አንድ ማንዴላ ተብሎ የነበረ ፖለቲከኛ (ለምሳሌ ልደቱ) ሲጠላ ፅንፍ ተሂዶ የማይባለው ነገር የለም። ይህ አመለካከት ጎጂ ነው።፡የፖለቲከኞችን መልካም ጎን እና ድክመታቸውን በሚዛን ስለማያይ ወይ አምልኮ ወይም እንትን እንደነካው እንጨት ማድረግ ይመጣል። ይህ ፅንፋዊ አመለካከት ሌላው ገጹ ስለምዕራቡ በተለይም ስለ አሜሪካ ያለው ግምት ነው። ዲሞክራሲ ማለት፣ ሰብአዊ ሥርዐት ማለት፣ ብልጽግና ማለት ምዕራቡ በተለይም አሜሪካ እንደኾነ ተደርጎ ውዳሴው ሌላ ነው። የምዕራቡንም ኾነ የአሜሪካን ሥርዐት የሚጠቅሱ ምዕራባውያን ምኞታቸውንም የሚያውቁ አይመስሉም። ስለዲሞክራሲ ሲጽፉ መነሻቸው የእነ ጄፈርሰን፣ የእነ ሊንከለን፣ እና ሌሎችም ናቸው። ጄፈርሰን፣ ጆርጅ ዋሽንግተን እና ሌሎችም ባሮች ከቤታቸው እንደነበሯቸው ግን አይነግሩንም። ሌላም ብዙ ጉድ አለ።

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop