‹‹አርሴን ቬንገር እራሳቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው ትክክል ነው›› ኢያን ራይት

አርሴናል ለ6ተኛ አመት በተከታታይ የዋንጫ ሽልማት ማጣቱን ተከትሎ አርሴን ቬንገር ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ራሳቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡ ‹‹ችግሩ የተሰላፊዎቹ ሳይሆን እኔ ነኝ›› ማለታቸውም ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት የቀድሞው የአርሴናል ዝነኛ ጎል አዳኝ ኢያን ራይት በዘ-ሰን ጋዜጣ ‹‹ቬንገር እራሳቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው ትክክል ነው›› በሚል እምነቱን ከዚህ በታች ባለው መልኩ አስነብቧል፡፡

አርሴናል ሌላ የውድድር ዓመትን ካለዋንጫ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኑን ተከትሎ አርኔን ቬንገር እራሳቸውን በጥፋተኝነት መውቀሳቸው ትክክል ናቸው፡፡ ቬንገር የአርሰናልን ስራ እንዳይለቁ ከሚፈልጉ ሰዎች እኔ አንዱ ነኝ፡፡ ነገር ግን ቬንገር እራሳቸውን ለለውጥ እርምጃ እስካላዘጋጁ ድረስ የዛሬ አመትም በኤሚሬትስ ሌላ ፀፀት መኖሩ አይቀርም፡፡ የቡድናቸው ተሰላፊዎች ቬንገርን ያሳፈሩበት የራሳቸው የሆኑ ድክመቶች እንዳሉባቸው ባምንም ትልቁ ስህተት ያለው በፈረንሳዊው አሰልጣኝ እጅ ነው፡፡
ስህተታቸውን ለማረም የሚችሉበት በዝውውሩ መስኮት ጋሪ ካሂል፤ ስኮት ፓርከር፤ ፊል ጃጌልካና ሮጀር ጆንሰንን የመሳሰሉት ሰፊ ልምድና እውነተኛ የማሸነፍ ወኔ ያላቸው ተጨዋቾችን ማስፈረም ሲችሉ ነው፡፡ አርሴናል ቡድንን ለመምራት የሚችሉ ልምድና ብቃት የተላበሱ ተጨዋቾችን ማግኘት እስካልቻለ ድረስ ከኒውካስልና ከቶተንሃም ጋር ባደረጋቸው ግጥሚያዎች እንደታየው ሁሉ የሰፊ ውጤት መሪነትን ይዞ በአቻ መለያየት የተገደደበትን ችግሩን ለመቅረፍ አይችልም፡፡ የጠቀስኳቸው እንደዚህ አይነቱ ተጨዋቾች ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ በእኔ የጨዋታ ዘመን ሬይ ፓርከር፤ ፓትሪክ ቪየራ፤ ኢማኑኤል ጉቲና ዳቪድ ሮከስትልን የመሳሰሉት እውነተኛ የማሸነፍ ወኔ ያላቸው ተጨዋቾችን አርሴናል ይዞ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በአርሴናል ቡድን ውስጥ ቡድኑን የመምራት ብቃት ያላቸው ተጨዋቾች አይታዩኝም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቬንገር ከወዲሁ ችሎታቸውን ትልቅ ደረጃ ያደረሱ ተጨዋቾችን የማስፈረም ፍላጎት አጥተው መቆየታቸው ነው፡፡ በእኔ የጨዋታ ዘመን የቬንገርን ሃሳብ ለማሻሻል ያለባቸውን ነገሮችን የሚጠቁሟቸው በርካታ ተጨዋቾች እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደዚህ አይነት ባህርይ ያላቸው ተጨዋቾች በአርሰናል ውስጥ የሉም፡፡ አብዛኛዎቹ የቡድኑ ተሰላፊዎች ቬንገር የእግር ኳስ ህይወታቸውን ትልቅ ደረጃ ያደረሱላቸው በመሆናቸው ይህንን ውለታቸውን በመጋፋት በአንዳንድ ነገሮች ቅሬታቸውን ሊገልፁላቸውም ሆነ ሃሳባቸውን ሊያካፍሏቸው አይደፍሩም፡፡
የቬንገር 2ተኛ አሰልጣኝ ከዘንድሮው የውድድር አመት መጠናቀቅ በኋላ ራሳቸውን ከሃላፊነቱ ሲያገሉ የሚተኳቸው ረዳት አሰልጣኝ ለአርሰናል ቁልፍ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ የሚለውም ከዚህ በመነጨ ምክንያት ነው፡፡ ቬንገር ረዳታቸው አድርገው አድርገው የሚቆጥሩት ባለሙያ ሁሉንም ሃሳባቸውን የሚቀበልላቸው ሳይሆን ያላመነበት ነገሮች በሚኖሩበት ወቅት ሃሳቡን የሚያካፍል ሊሆን ይገባዋል፡፡ የአርሴናል ደጋፊዎች የሚፈልጉት በአለም የታወቁ ችሎታ የተካኑ ስመ ጥር ተጨዋቾች ለቡድናቸው ሲሰለፉ ማየት እንጂ የክለባቸው የፋይናንስ አቅም የተረጋጋ መሆኑን መመልከት አይደለም፡፡ ‹‹የዋንጫ ሽልማት ባይኖረንም ክለባችን ከዕዳ ነፃ ነው›› ብለው የሚፅናኑ የአርሴናል ደጋፊዎች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ የሁሉም ምኞት የዋንጫ ድሎችን ማየት ብቻ ነው፡፡ በርካታ ቀንደኛ የአርሰናል ቀንደኛ ደጋፊዎች ከሆኑ ሰዎች ጋር በየጊዜው ስለምገናኝ ሁል ጊዜ የሚነግሩኝ ይሄንኑ ነው፡፡ የክለባቸው በተረጋጋ የፋይናንስ ሁኔታ መገኘት ለአርሰናል ደጋፊዎች የሚሰጠው ምንም ጥቅም የለም፡፡ ለምሳሌ ማንችስተር ዩናይትድ በእዳ ቁልል ተዘፍቆ በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቡድን በየአመቱ የዋንጫ ሽልማቶችን ስለሚያገኝ ደጋፊዎቹ ምንጊዜም ደስተኞች ናቸው፡፡ ቼልሲ ባለፉት አመታት ውስጥ በኪሳራ ቢንቀሳቀስም ቢያንስ ግን የፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮንነትን ክብር ለሶስት ጊዜ ለማግኘት ከመቻልም አልፎ ለሻምፒዮን ሊግ ፍፃሜ ደርሷል፡፡ ይህንን ስል ግን ‹‹ቬንገር የአርሰናልን ካዝና በማራቆት በከፍተኛ ዋጋ ውድ ተጨዋቾችን መግዛት ይኖርባቸዋል፡፡›› የሚል ግትር አቋም የለኝም፡፡ ነገር ግን በአነስተኛ ሚሊዮኖች ለቡድኑ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ተጨዋቾችን ለማግኘት ይችላል፡፡
ከዘንድሮው የውድድር ጊዜ መጠናቀቅ በኋላ ቼልሲ ብቻ ሳይሆን ማንችስተር ሲቲም ለአዲስ ተጨዋቾች ከፍተኛ ሂሳብ እንደሚያወጣ ለመገመት አስቸጋሪ አይሆንብኝም፡፡ ሊቨርፑል ለተጨዋቾች ግዢ በቂ ገንዘብ መድቧል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድና ቶተንሃም በየአመቱ ቡድናቸውን በአዲስ ተጨዋቾች የማጠናከር ባህላቸውን ይገፉበታል፡፡ ነገር ግን ቬንገር የአሁኑ የዝውውር ፖሊሲያቸውን የሚገፉበት ከሆነ አርሰናል በቀጣዩ አመትም ቢሆን በሚያደርጋቸው የተለያዩ ውድድሮች የዋንጫ ሽልማቶችን ለማግኘት ትልቅ ችግር እንደሚፈጠርበት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡ አርሰናል ካለፉት አመታት አንፃር የዘንድሮው አመት ውድድር ከ2004 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን በሻምፒዮንነት ማጠናቀቅ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮለት ነበር፡፡ ምክንያቱም ማንችስተር ዩናይትድ ለፕሪምየር ሊጉ ሻምፒዮንነት ለመብቃት የተቃረበው በአብዛኛው በውድድር አመቱ የወትሮውን ታላቅ ብቃቱን ባላሳየበት ሁኔታ ነው፡፡ ቼልሲም በበርካታ ግጥሚያዎች ብዛት ያላቸውን ነጥቦች ያባከኑበት የውድድር ዘመን ነው፡፡ ነገር ግን አርሰናል ከእነዚህ ሁለት ተቀናቃኞቹ የአቋም አለመረጋጋት በአግባቡ ተጠቃሚ በመሆን በደረጃው ሰንጠረዥ አልፏቸው ሲሄድ አልታየም፡፡ በቬንገር ላይ የአርሰናል ተጨዋቾች ባላቸው ጥልቅ እምነት እኔም እስማማለሁ፡፡ ምክንያቱም ቬንገር ከሀላፊነታቸው መልቀቃቸው ለአርሰናል ውጤታማነት የመፍትሄ እርምጃ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ ይልቅ ቬንገር የዝውውር ፖሊሲያቸውን በመቀየር ለበርካታ አመታት ለዘለቀው የክለባቸው ደጋፊዎች የዋንጫ ሽልማት ጉጉት በቀላሉ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የደስታችን ምንጭ ሜዳሊያው ብቻ ሳይሆን አትሌቶቻችን ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ ያሳዩት ትብብርና ህብረት ነው- ሻለቃ አትሌት ኃይሌ
Share