‹‹የማሸነፍ አዕምሮ›› የዘንድሮው የማንቸስተር ጠንካራ ጎን ሆኗል

ማንቸስተር ዩናይትድ ኤቨርተንን 1ለ0 የረታበት ግጥሚያ ለሊግ ሻምፒዮንነት ለመብቃት እውነተኛው ኃይል እንዳለው በትክክል ለማረጋገጥ የተቻለበት ነው፡፡ የቡድኑ ተሰላፊዎች ወሳኝ የማሸነፊያ ጎልን ለማስቆጠር አብዛኛውን የጨዋታ ክፍል ጊዜ ጥረት በማድረግ ማሳለፍ መቻላቸውም በመጨረሻው ፍሬያማ እንዲሆኑ ምክንያት ሲሆናቸው ታይቷል፡፡ ይህንን ባህል የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቡድን በሲዝኑ ወሳኝ ወቅት መድገም መቻሉም ለ19ኛ ጊዜ ለሊጉ ሻምፒዮንነት በመብቃት የእንግሊዝፉ ትቦል ታሪክ አዲስ ሪከርድን ለማስመዝገብ እንዲቀርብ ምክንያት እንደሆነው በማመን የፉትቦል አናሊስቱ ግሬግ ስቶባርት ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ሙያዊ ዳሰሳውን አስነብቧል፡፡
የቅዳሜው የኦልድትራፎርድ ግጥሚያ ከመደረጉ በፊት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ለክለባቸው ደጋፊዎች ባስተላለፉት መልዕክት የቡድናቸው የውድድር ዘመን አጨራረስ ባሰቡት መልኩ ያማረ እንደሚሆን ቃል ገብተዋል፡፡ የ69 ዓመቱ ስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ እርግጠኝነት መንፈስን አሳድረው ይህንን ቃል የገቡት ማንቸስተር ዩናይትድ በሲዝኑ በዚህ ወሳኝ ወቅት ለፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነት ለመብቃት ያገኘው የተመቻቸ እድልን አሳልፎ የመስጠት ባህል እንዳለው ለማስገንዘብ በመፈለጋቸው ጭምር ነው፡፡ በእርግጥ ማንቸስተር ዩናይትድ በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስር ከዚህ በፊት ለፕሪሚየር ሺፕ ሻምፒዮንነት ለመብቃት በቻለባቸው የውድድር ዘመኖች የነበረው እጅግ ታላቅ ፕሮፎርማንስ በዘንድሮው ሲዝን ለማበርከት ችሏል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ነገር ግን በሲዝኑ ወሳኝ ወቅት በጥሩ አቋም የመገኘት ባህሉን ዘንድሮም ለመድገም መቻሉን ኤቨርተንን 1ለ0 የረታበት ግጥሚያ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በጨዋታው 83ኛ ደቂቃ ሃቪየር ሄርናዴዝ ያስቆጠራት ጎልን አስከብረው ለመውጣት እያንዳንዱ የቡድኑ ተሰላፊዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴን ማሳየታቸውም በማንቸስተር ዩናይትድ እና በሌሎቹ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ቼልሲና አርሴናል መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቡድን ከፍተኛ የማሸነፍ አዕምሮን የተላበሰ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ዩናይትድ ይህንን ከፍተኛ ወሳኝነት ያለው ድልን ለማስመዝገብ የቻለበት ጎልን ለማስቆጠር የቻለው ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃዎች እስከ ቀሩት ድረስ በኤቨርተን ተሰላፊዎች በጠንካራ ሁኔታ የመከላከል ተግባርን በመፈፀም መዝለቃቸው በምዕራብ ለንደኑ ክለብ ደጋፊዎች ዘንድ የሻምፒዮንነት ፉክክራቸው ተስፋ የለመለመ የመሰለበት መንፈስ መፈጠር የጀመረበት ወቅት ነው፡፡ በተግባር እንደታየውም ኤቨርተን በሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠቀስ የሚችል ጎል ለማስቆጠር ሙከራን በጃክ ሮድዌል አማካይነት በአንድ አጋጣሚ ከማድረጉ አንፃር ከግጥሚያው ነጥብ የመጋራት እድልን ማግኘት ተገቢው አልነበረም፡፡
በአንፃሩ ግን የአርሴናል ተሰላፊዎች እንደ ዩናይትድ ሁሉ ጠንካራ የማሸነፍ አዕምሮ እንደሚጎላቸው ከሊቨርፑል፣ ከቶተንሃምና ከቦልተን ጋር ባደረጓቸው ያለፉት ሶስት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ማሳካታቸው በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ይህ ችግር የቼልሲም ጭምር ነው ለማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም የካርሎ አንቼሎቲ ቡድን እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሁሉ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ የሚመስል ግጥሚያ በድል ለማጠናቀቅ ሲቸገር የታየበት በርካታ አጋጣሚዎች ሲከሰቱበት ታይተዋል፡፡ ግጥሚያዎችን በድል ማጠናቀቅ መቻል ደግሞ ከአንድ እውነተኛ ለሊግ ሻምፒዮንነት ክብር ከሚጫወት ቡድን የሚጠበቅ ኳሊቲ ነው፡፡ ከኤቨርተን ጋር በተደረገው ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ አጀማመሩ ላይ ቀዝቅዞ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ግን በአጭሩ አቋም በመግባት የጨዋታ እንቅስቃሴ የበላይነትን በመያዝ በርካታ ጎል የማስቆጠር ዕድሎችን ለመፍጠር ችሏል፡፡ በተለይም ሀቪዬር ሄርናዴዝ በበርካታ አጋጣሚዎች የቲም ሃዋርድ መረብን ለመድፈር ሲቃረብ በታየበት ግጥሚያ ነው፡፡
ቺቻሪቶ ከኤቨርተን የመሀል ተከላካዮች ስር ባለመራቅ ጎል ለማስቆጠር ያደረገው ያላሰለሰለ ጥረት በመጨረሻም ፍሬያማ ሲሆንለት የታየው አሜሪካዊያን ግብ ጠባቂ ቲም ሀዋርድን በከፍተኛ ደረጃ የተፈታተኑ ሶስት አደገኛ ጎል የማስቆጠር ሙከራዎችን ካደረገ በኋላ ነው፡፡ እነዚህ ሶስት ተደናቂ ሙከራዎቹ በግራ እግሩ፣ በቀኝ እግሩና በግንባሩ በመግጨት የተደረጉ መሆናቸው ደግሞ የ22 ዓመቱ ሜክሲኮዋዊ አጥቂ ሁሉንም አይነት ጎል የማስቆጠር ኳሊቲዎችን የተላበሰ መሆኑን የሚያሳይነው፡፡ ዋይኒ ሩኒም የቀድሞ ክለቡ ላይ ትልቅ አደጋን ሲፈጠር የታየበት ጥሩ እንቅስቃሴን ያደረገበት ግጥሚያ ነው፡፡ በተለይም በተደጋጋ በትክክለኛው ስፍራ በመገኘትና ለሄርናንዴዝ ለእያንዳንዱ አጋጣሚዎች ፓሶችን ለማድረስ ያደረገው ጥረት ሊደነቅለት የሚገባ ነው፡፡ የኢኳዶሩ ኢንተርናሽናል አንቶኒዮ ቫሌንሲያም በርካታ ክሮሶቹ በኤቨርተን ተከላካዮች ሲመለሱ መታየቱ ሳያስጨንቀው ተስፋ ባለመቁረጥ መንፈስ ሆኖ ያገኛቸው ኳሶችን በጠቅላላ ወደ ኤቨርተን ፔናሊቲ ቦክስ እንዲያስገባ ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን የተሰጠው መመሪያን በአግባ ሲፈፅም ታይቷል፡፡ ይህ ጥረቱ የሰመረ እንደሚሆን ተቀይሮ የገባው ማይክል ኦዌን ከኤቨርተን በር ቅርብ ርቀት ላይ ያደረጋት ጎል የማስቆጠር ሙከራ ተጨራርፋ በኤቨርተን ጎል ቋሚን በመታከክ ወደ ውጪ መውጣቷ የጠቆመው ሆኗል፡፡ የኤቨርተን ተሰላፊዎችም በቲም ሃዋርድና የፊል ጃጌልካ በጥሩ አቋም መገኘት የማንቸስተር ዩናይትድን ጠንካራ ኃይል ሙሉውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመቋቋም ለመቻል የሚረዳቸው አለመሆኑን እንዲገነዘቡለት አድርጓቸዋል፡፡
ሰር አሌክስ ሰዓታቸውን በማየት የቡድናቸው ሌላ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ማጂክን መመኘት የጀመሩትም ያኔ ነው፡፡ በእርግጥም የኤቨርተን ተሰላፊዎች ሙሉውን 90 ደቂቃ ከመዘናጋት መንፈስ ነፃ ለመሆን እንዳይችሉ የዩናይትድ የማያቋርጥ ከፍተኛ ጫና ተፅዕኖን ሲፈጥርባቸው የታየበት አጋጣሚ ቺቻሪቶ የቫሌንሲያ ክሮስን ከጎሉ አፋፍ ላይ በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረበት ተግባሩ ሲከሰት ታይቷል፡፡
ማንቸስተር በዘንድሮው ሲዝን በሊጉ ውድድር በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ውስጥ ጎል ለማስቆጠር ሲችል ይህን ለ15ኛ ጊዜ ነው፡፡ በአጠቃላይም ዩናይትድ በዘንድሮው ሲዝን ከመረብ ካሳረፋቸው የፕሪሚየር ሊግ ጎሎቹ ውስጥ 21 ፐርሰንቱ የተገኙት ከ80ኛ ደቂቃ ባሉት የጨዋታ ክፍለ ጊዜዎች ውስጥ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የሰር አሌክስ ቡድን ወሳኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች መሆናቸውን ነው፡፡ የቡድኑ ተሰላፊዎች ይህንን ባህል ማዳበራቸው እያንዳንዱ ግጥሚያን እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ጎል ለማስቆጠር እንደሚችሉ ሙሉ እምነትን አሳድረው እንዲዘልቁ የሚረዳቸው ነው፡፡ ይህንን ባለፈው ወር ከቦልተን ጋር ባደረጉት ግጥሚያ ደግመውታል፡፡
ያኔ በኦልድትራፎርድ የተደረገው ግጥሚያ 0ለ0 በሆነ ውጤት ወደ ጭማሪዎቹ ደቂቃዎች የሚገባ በመሰለበት ወቅት ዲሚታር ቤርባቶቭ በ89ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል ዩናይትድ 1ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል፡፡ በቅዳሜው ግጥሚያም ኤቨርተንን በተመሳሳይ ውጤት ያሸነፈው ቺቻሪቶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠራት ጎል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቡድንን ለ19ኛ ጊዜ ለሊጉ ሻምፒዮንነት በመብቃት በእንግሊዝ ፉትቦል አዲስ ታሪክን ለመስራት እንዲመቻች ምክንያት ሆኖታል፡፡
ምክንያቱም በቀሪው ሲዝን ከአርሰናል፣ ከቼልሲ፣ ከብላክበርንና ከብላክፑል ጋር በሚያደርጋቸው ግጥሚያዎች ማግኘት ከሚገባው 12 ነጥቦች ሰባቱን ለማሳካት መቻል ለሻምፒዮንነት ክብር ለመብቃት በቂው ይሆንለታል፡፡ የፈርጉሰን አላማም ከፊታቸው ከአርሰናልና ከቼልሲ ጋር የሚያደርጉት ግጥሚያዎችን በድል በማጠናቀቅ ለሻምፒዮንነት መብቃታቸውን ማረጋገጥ መቻል ነው፡፡ በዘንድሮው ሲዝን በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በርካታ ጎሎችን ለማስቆጠር የቻሉት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከዚህ በታች ያሉት ናቸው፡፡
በመጨረሻዎቹ 10 ዲቂቃዎች
1ኛ/ ማንቸስተር ዩናይትድ 15 ጎል
2ኛ/ ቼልሲ 13
ስቶክ ሲቲ – 13
3ኛ/ ኤቨርተን 11
4ኛ/ አርሴናል 10
ቦልተን 10
ብላክፑል 10
ዌስትብሮም 10
5ኛ/ ኒውካስል ዩናይትድ 10
ቶተንሃም 9

ተጨማሪ ያንብቡ:  Ethiopia names 22 players for Nigerian Encounter
Share