By Wannaw
ንፋሱ የፒያሳን ጎዳናዎች ከጥግ እስከጥግ አዳርስ ተብሎ ከላይ እንደተላከ ሁሉ የላስቲክና የኮተት መዐት እያንኳኳ ያልፋል :: ቀሚስ ይገልባል … በእድሜ ብዛት የተጣፈ ሻንጥላን እያወላገደ ይታገላል :: ሚጡ ዓይኖቿ ውስጥ የገባዉን አዋራ በትናንሽ ጣቶቿ እንደጨፈንች እያሸችው በእንባዋ ታሟሟዋለች : ከዛም ዓይኖቾ ይቀላሉ :: ቀይ ፊቷን በብርድ ፊርማ ተዥጎርጉሮም ውብ ገጿ እንዳለ ነው :: ካፍንጫዋ ስር የደረቀው የንፍጧ ቅርፋፊ እርብትብት ከናፍርቷን ያመላክታል ::
ሚመጸወት ሲመጣ ልክ እንደፒያሳው ነፋስ እሷም በሚጢጢ ባዶ እግሯ እየሮጠች ትንሽ መዳፏን ትዘረጋና አንገቷን ዘመም ታደርጋለች :: ከተጎነጎነ መቆየቱን በመቦዘዙና በመበታተኑ ሚያስታውቅ ፀጕሯን ባንደኛው እጇ እያከከች በኮልታፋ አንደበቷ ትለምናለች : ግን አልተሳካላትም እንደሠውም የቆጠራት የለም :: እሷም ሆድ አይብሳትም ወዲያው ወደጨዋታዋ ትሮጣለች የተንከረፈፈ ቀሚሷን እያዘናፈለች ወደሞነጫጨረችው መሬት ላይ ድንጋይ እየወረወረች እናጣጥ እንጣጥ ትላለች … ወዲያው ደግሞ መዳፏን ዘርግታ ራሷን ጋደድ አድርጋ አላፊ አግዳሚዉን ትለምናለች ::
”ዛሬ ምነው አንቺም እንደመስከረም ንፋስ ቅልብልብ አደረገሽ ሚጡዬ …?”
አሏት ጋሽ አስቻለው የተወረወረላቸዉን ሣንቲም ባንድ እጃቸው እየቆጠሩ አንደኛው እጃቸው የለም … ወይም አልነበረም :: ሁለቱ እግራቸዉም እንደዚሁ … የመጸዋቹ አንጀት ጨክኖ ሚቆጥሩት ቀርቶ ብድግ ሚያደርጓት ሳንቲም ‘ንኳን ሲያጡ የተሸበሸበ የፊታቸው ቆዳ ላይ ሚንጠባጠበዉን እንባ በትከሻው አንገታቸዉን ቆልመመው እየጠረጉ
”አይ ፈጣሪ ለዚች ግማሽ በስባሳ ስጋዬን ‘ንኳን መሆን አቃተህ …?”
እያሉ ያለቃስሉ ::
ከርሳቸው ፈንጠር ብላ የሚጡ እናት ሎሚዎቿን ዘርግታ ገቢያ ትጠብቃለች :: ቀጫጫ ሠዉነቷ እጥፍጥፍ ብሎ ትንሽ ሆናለች : በጊዜ ጠባሳ የተደበቀ ውበቷ ዳመና እንደጋረደው የማታ ጀንበር ሆኗል ::
”ምነው ዛሬ ደግሞ ልጅሽ እንዲያ ስትፈነጥዝ አንቺ መተከዝሽ …?”
አሉ ጋሽ አስቻለው ወደሚጡ እናት እያዩ : ቀሚሷን ለመግለብ ከሚታገላት ንፋስ በክንዷ እንደመመንጨቅ ብላ ያጠፈች እግሯ መሀል ሸጎጠችና
”አይ አባት … መቼ ሳልተክዝ ውዬ አውቅና ነው …? ነው ወይስ ዛሬ ነው በመስከረሙ ብረሐን ያስተዋሉኝ …?”
ፈገግ ለማለት ስትል ብልጭ ያሉ ጥርሶቿ እውነትም በቁጠባ ብቻ እንደሚከፈቱ … ለክት ብቻ እንደሚታዩ ሁሉ በረዶ ናቸው ::
”ኤዲያ ምን ቢተክዙ ቢያብሰለስሉ አይሞላ ….. እንዳስቻለው ገላ ጎዶሎ ለሆነ ሕይወት ደግሞ …”
መፅዋቹ ጠብ ሚያደርግላቸዉን ሣንቲም አይተው ቀና ይሉና የምርቃት መዐቱን ያወርዱታል :: ሚጡ ለርሳቸው የመፀወተዉን እየተከተለች ስትለምን መፅዋቹ 10 ሣንቲም ትንሽ መዳፏ ላይ አቀበላት ሳንቲሙን በስስት አይታው ወደናቷ ስታመራ
”ምነው ሚጡዬ አሳሳሽ እንዴ ?”
አለቻት በአዋራው የቀሉ ዓይኖቿን አይታ
”ከለሜላ ልግዛበት …?”
አለቻት ሣንቲሙን ወደጀርባዋ እንደመደበቅ እያደረገች
”ግዢበት …”
አለቻት እናትየው በከረሜላ ጉጉት የበሩ ድፍርስ ዓይኖቿን በሀዘን አይታ : ሚጡ ሮጣ ማስቲካ ሲጋራና ከረሜላ ወደሚቸረችረው ጫማ ጠራጊ ሄደች ::
”ይሄ ከረሜላ አይገዛም …”
አላት ድንገት ጉልበቱ መሀል አጣብቆ የያዘዉን ያረጀ ጫማ በጅማት ወስውሶ በወረንጦ መጎልጎሉን ገታ አድርጎ እጇ ላይ ያለዉን ድፍን አስርሣንቲም እያየ ..
ሚጡ ሣንቲሙን አገላብጣ አየችዉና ሸንኮራ ወደሚሸጠው ደግሞ ሄደች
”እናትሽን 10ሣንቲም ጨምሪ …. በያት ::”
አላት ሸንኮራ ሻጩ :: በጨርቅ እንደቁስለኛ የተበተበ ቢላዉ የሸንኮራ ፍርፍሪ በመያዙ ዝምቦች ሊወሩት ያንዣብባሉ :: ከሻጩ ይልቅ ያልተነኩት አገዳዎች በኩራት የመዘጋጃ ጊቢን ግንብ ተደግፈዋሉ :: አሁንም ሚጡ 10ሣንቲሙን አይታው ወደመፋቂያ ሻጩ ሄደችና ቀልቧ የወደደዉን መፋቂያ ስታነሳ ሻጩ እጇን ቀብ አደረጋት ::
”… ልገዛ ነው ….”
አለች እንደማልቀስ ብላ
”ለየትኛው ጥርስሽ እስቲ እኝኝኝኝ በይ ::”
አላት መፋቂያ ሻጩ : እጇን ሳይለቃት የጉንጩ ከፊቱ አጥንት ላይ መለጠፍ የዓይኖቹ መጎድጎድ የከንፈሩ መድረቅ … እሕል ቀምሶ ሚያውቅም አይመስልም ::
”እኝኝ ”
አለች ሚጡ ትንንሽ ጥርሶቿን ለማሳየት ቀይ ድዷን እያበራች
”… ለኔእኮ አይደለም ለእማዬ ነው …”
አለች እኝኝ በማለቷ እንዳፈረች ሁሉ አንገቷን ደፍታ
”ለናትሽ ወተት ጥርስማ እኔ በነጻ እሰጥሻለው ታዲያ ንገሪያት እሱ ነው የላከልሽ ብለሽ …”
አላት የተከናነበችዉን ሎሚ ሻጭ እናቷን እያየ
ሚጡ መፋቂያው ቢሰጣትም ለምና ያመጣችው ሣንቲም ምንም የመግዛት አቅም እንደሌለው አይታ ተናዳለች …
”ልመዘን …?”
አለች ሚዛን ስሩ አኑሮ ቀጫጫና ወፍራም በመለካት ዳቦዉን ሚጠብቀዉን ወጣት …. 10ሣንቲሟን እያሳየችው : በቁጣ
”ሂጂ ወደዚያ እቺ ሳትፈለግ ተፈልፍላ …”
ከተናገረ ሣምንት ያልፈው ሚመስል ድምፁን ትንሿ ሚጡ ላይ ሞረደ … በሞረድ ዓይኖቹም እያፈጠጠባት …. ሚጡ እንደንፋስ በርግጋ ወደናቷ ሮጠች
”እማዬ መፋቂያ አመጣዉልሽ …”
አለቻት ለናቷ ቅርፊቱ በቄንጥ የተቀረፀ ረጅም መፋቂያዉን እያቀበለቻት
”አይ ሚጢዬ …. ላንቺ ከረሜላ ብለሽ … ለኔ መፋቂያ ገዛሽ ?”
አለቻት አቅፋ አንገቷ ስር እየሳመቻት እንዲህ አድርጋ ስትስማት የሚጡ አባት ትዝ ይላታል እሱም በፍቅራቸው ጊዜ ተላፍቷት ካደከማት በኌላ አንገቷ ስር ነበር ሚስማት
”እስቲ … ባክህ … ምን እንደድመት አንገቴን …”
ትላለች ስሜት ባወረዛው ፊቷ የውሸት ቁጣ እየሞከረች
”ለዛሬ ድመት ብንሆን ምን አለበት ውሻ እያረጉን ስንት ጊዜ እንኖር የለ …?”
ይላታል በቀን ስራ የጠነከረ መዳፉን ወገቧ ላይ እየጠመጠመ …
አንድ ቀን እንዲሁ በድሕነት ፍቅራቸው ሐሤትን እያገኙ በመዋደዳቸው ድሕነትን ድል እየነሡ እንዲህ አለችው
”እኔ ያንተ ልፊያ በቃኝ አሁንማ ምትላፋው ላመጣልህ ነው …”
”አልገባኝም …?”
አላት ዓይኖቹን አፍጥጦ
”አሳድገህ ምትላፋው ላመጣልህ ነዋ …”
”አሁንም አልገባኝም …”
አላት
”ኡፍፍፍፍ አንተ በቃ ይሄ ሢሚንቶ ጆሮህን ደፍኖታል አይደል ?”
አለችው በነኚያ ጥርሶቿ ፈገግ ብላ የጎን እያየችው
”ጆሮዬማ እየሠማ ነው ግን ….”
ይሄኔ መዳፉን ይዛ ሆዷ ላይ አኖረችው : ፈነጠዘ
”እውነት እርጉዝ ነሽ ?”
”እና በቅሎ መሰልኩህ ….?”
ፈነጠዘ ማንቆርቆሪያ ጠላ አስልኮ ዋንጫዉን አጋጨ ::
”ግን ሤት መሆን አለባት …”
”እሱን አንተ አትወስንም እኔ ደግሞ ምፈልገው ወንድ ነው …”
ትላለች እሷም
”በጭራሽ … አቤት …. ፓ ! እንደምንም ጥሩ አድርጌ ነው ማሳድጋት ”
”እስቲ ልጁ ይምጣ መጀመሪያ … እሳቸው በመጡና አፈር በበሉ አለች አክስቴ ….”
ግን ልጁን አላየም :: ሚጡ ልትወለድ 3 ሣምንታት ሲቀረው ከሚሠራበት ፎቅ ላይ ድንጋይ ወደቀበት … ያ ቀን የጣለው ድንጋይ የሚጡ አባትንም ሕይወት ጣለው ::
”እማዬ … ያ ከቻቻው ልጅ ‘ኮ ነው የሰተሽ የኔ 10ሳንቲም ምንም አልገዛ አለኝ …”
አለቻትና ሳንቲሙን እንደመደበቅ እያደረገች አሳየቻት እናትየው ፊቷ በሀዘን ቀጭሟል
”… አስል ሳንቲም ምንም አይገዛም ?”
አለች ሚጡ ለማትሠማት እናቷ
”አባባ አስል ሳንቲም ምን ይገዛል ?”
አለች ለጋሽ አስቻለው
”አዬ ልጄ ትንሽ አርፈድሽ ተፈጠርሽ እንጂ … ብዙ ነገር ይገዛ ነበር …”
አሏት ::
ከማዶ የጊዮርጊስ ቤ /ቲያን ቅዳሴ ከታክሲዎች ጥሩንባና ከአውቶብስ ፍሬን ቡጥጫ ጋር እየተሻማ ይሠማል ::
”አባባ … በካ ምንም አይገዛም ?”
አለች ሚጡ : ሁሉም ዝም ብሏል ያ ሣንቲም የመግዛት አቅሙን ሊነግራት የቻል የለም :: እናቷ ወደትላንትና ትዝታዎቿ ነጉዳለች
ሚጡ ሣንቲሙን ጋሽ አስቻለው ግማሽ እግሮች ስር ወርውራ ወደ እናቷ ሮጠች
”ለምን ታልክሺያለሽ መፋኪያውን ልመልስለት ….?”
አለቻት እንባዋን በሚጢጢ እጇ እያበሠች
”ሚጡ …”
አሉ ጋሽ አስቻለው : ሚጡ ዞር ብላ አየቻቸው
”10 ሣንቲም ምርቃት ይገዛል …”
አሏት
”ምንድነው ምንድነው …?”
ብላ ሮጠች
”እግዚያብሔር ፊቱን አያዙርብሽ …”
አሏት :: ሚጡ ሣንቲሙን መስጠቷን ረስታው ሚጢጢ መዳፏን አየች :
የጊዮርጊስ ደወል …. የመዘጋጃ የሠዓት ደወል …. ይሠማል ጊዜ በማንኛዉም ቅፅበት ስልጣን እንዳለው ለመናገር ሚያሾፍ መሠላቸው ጋሽ አስቻለው ::
______________________////__________________________
መጀመሪያ
ተፃፈ በኢት አቆጣጠር 19 91