By Wanaw
አንቺ የምሽት ኮከብ ጨረቃ
ድንገት በሕልሜ አይቼሽ ብነቃ …
የዳዊትን ዜማ ጮክ ብላ ታዜማለች : ስታዜም ወደጨረቃዋ አንጋጣ ነው ከጀርባዋ የተከፈተው የመጠጡ ቤት የሚንቦገቦግ መብራት ከፊል የፊቷን ገፅ እየቀያየረ ያሳየኛል ከፊል ፊቷን ደግሞ በጨለማው ውስጥ ያበራችው የምታዜምላት ጨረቃ ብረሐን ታሳየናለች :: ሲጋራዋን አንዴ ስትስበው እሳቱ ፈመ :: ከሷ ጎን አንዲት ሌላ ሴት ፀጉሯን እንደማስተካከል እያለች ድራፍቷን ትጎነጫለች ከመጠጥ ቤቱ ውስጥ ”ልጁን ያያችሁ አዬ እስቲ ን .ገ .ሩኝ …” ‘ሚለውን ዜማ ብዙ ድምፆች አጅበው ያዜማሉ :: የምሽቱ አየር ሞቅ ያለ ስለሆነ ከውስጥ ይልቅ በረንዳው ተመችቶኛል :: እዚህ ናዝሬት ከመጣው 1ሣምንት ሆነኝ የመጣዉበት ዓላማ ስላልተሳካ ዛሬ በተለይ ምርር ብሎኝ ነው የዋልኩት እዚች ቤት ሆኜ የምሽቱን ንግስቶች መልክ ሳጠናና ሳስተውል ይሄው ዛሬ 3ኛ ቀኔ ነው ::
አንዲት አጭር ሞንዳላ ሴት ከማጨሠው ሲጋራ ‘ወጋው ‘ ስትለኝ ሌላ ሲጋራ ስሰጣት
”ፍሬንድ ምነው አንተ ደግሞ ቺክህ ጥላህ ኮበለለች እንዴ … የሆነ ትካዜ ምናምን ነገር … አቦ ግባና ወዝወዝ በልበት ካስፈለገም ድብርቱን ….”
አለችና ሌባ ጣቷን ካጣበቀቻቸው ሁለት ጣቶቿ ጋር ጧ ! አድርጋ እያማታች
”እኛ እንነቅልልሀለን ”
ብላኝ ወደ ውስጥ ገባች : በፈገግታዬ ሸኘዋት ያቺ ልጅ አሁንም ታዜማለች ሢጋራው አልቆ አመድና ቁራሽ ስፖንጅ ሆኖ ተወርውሮዋል …
”መስኮት ከፍቼ ውጪ ባይሽ
ጨረቃም የለች አንቺም ጠፋሽ
ዳግም አልተኛ ምን አደርጋለሁ
እስክትመጪ እጠብቃለሁ ”
ስታዜም ወደ ጆሮዎቿ ጥግ ተንጋደው ቀልበስ ያሉ ዓይኖቿ ይጨፈናሉ ቀለም የቃሙ ከናፍርቷ ይሾላሉ … የምጠጣዉን ድራፍት ያዝኩና አጠገቧ ሄድኩኝ
”ይቻላል …?”
አልኳት አጠገቧ ያለዉን ወንበር ድራፍት በያዘ እጄ እያመላከትኳት አልመለሰችልኝም …
ከራሷ ጨማምራበት ካልሆነ መቼም የዳዊት ግጥም እንደሆን አልቅዋል ተቀመጥኩኝ
”ጨረቃ ትወጂያለሽ ?”
አልኳት እንደመፍራት ብዬ : ያቺ የቅድሟ ከመፀዳጃ ቤት ስትመለስ ገላምጣኝ ፈንጠር ብላ ተቀመጠች :
”እ … እኔን ነው ?”
አለችኝ ያቺ ጨረቃ አፍቃሪ
”እንግዲያ … ጨረቃዋማ እንኳንስ እኔን ልትሰማ አንቺንም ስታዋራ አላየዋት ለሷ ማወራው ”
አልኳት : ሳቀች ስትስቅ ሸራፋ ጥርሷ ሳቋን ቄንጠኛ አደረገላት :
”ከመጣህ 1 ሠዓት አልፎሀል እንዴት አሁን ታየውህ ?”
አለችኝ ተቀምጬ የነበርኩበትን ወምበር ገልመጥ አድርጋ ቀይ ፊቷ ስጠጋው እንደቅድሙ ሲጋራዋ ፍም ቦግ ብሎ ታየኝ :
”አሁን አይደለም የታየሽኝ ቅድም ነው ዘፈንሽን ማቋረጥ አልፈለኩም ነበር ”
አልኳት
”እዚህ ቤት ሳይህ 3ተኛ ቀኔ ነው ሁሌም ብቻህን ሆነህ ሲጋራህን እያቦነንክ ድራፍትህ ላይ ተተክለህ ነው ….. ሸርሙጣ ማትወድ ነህ ብዬ ደምድሜ ነበር ”
አለችኝ አገጯን በመዳፏ ጥግ እንደደገፈች
”እንዴት አስተዋልሽኝ ?”
”እኛ ሸርሙጣዎች ነን ስጋችንን ምንቸረችርለት ሠው በዓይናችን የመፈለግ ግዴታ አለብን ”
ድምጿ ይርገበገባል ዝም አልኳት ከደረት ኪሴ የሲጋራ ፓኬት አወጣዉና አቀብያት ለራሴም ለሷም አቀጣጠልኩኝ
”ጅን ግዛልኝ ዛሬ አባቴ በታም ናፍቆኛል እንዲህ ሙሉ ጨረቃ ስትወጣ አባቴ ይናፍቀኛል ;”
ገብቼ ለኔ ድራፍት ለርሷ ጅን ይዤ መጣው ከውስጥ የቦብ ማርሊ ሙዚቃ ይጮኻል ጎረምሶች አንድ እግራቸውን እያፈራረቁ አንድ እጃቸውን ወደጣሪያው ዘርግተው ሌባ ጣታቸዉን ቀስረው ይወዛወዛሉ
”ሰካራምም አጫሽም አትመስልም ”
አለችኝ ጅኑን ተቀብላ ከኔ ድራፍት ጋር አግጭታ እየጠጣች ስታንቆረቁረው አንገቷን ቀና ስታደርግ አይቼያት አንገቷ ረጅም ነው :
”የጠጣ ሁሉ ሰካራም ሲጋራ ያጨሰ ሁሉ አጫሽ አይባልም ”
አልኳት : ሳቀች እነኚያን ቅርጻቸው ደስ ያሉኝን ዓይኖቿን እየጨፈነች
”ምናለ ለብር ስትል ጭኗን ከፍታ …… የሰጠች ሸርሙጣ አይደለችም …… የሚል ውሸት ቢጀመር ….. ምናለ ጠላቶቻቸዉን በቢላ ወግተው የገደሉ … ነብሠገዳይ አይደሉም የሚል ውሸት ቢመጣ …..”
ያጠላለፈችው እግሯን ስታቀያይር የባቷን ቅርፅ አየውት … አሸራሟጭ በሆነ ስሜት ይሁን ተፈጥሮን በማድነቅ ስሜት ብቻ አደነቅኩት ጎመዠዉትም ::
”ሳይህ ደደብ አትመስልም ብዙ ወንዶች ደደቦች ናቸው ለምንድነው ?”
”እኔንጃ ….”
ሲጋራዋን የያዘችበት የጇ አውራ ጣት ዓይኖቿን አበሰችና ወደጨረቃዋ እያየች
”ጨረቃ ትወዳለህ ?”
አለችኝ
”አስቤው አላውቅም ማለተ ልውደድ ልጥላ ስሜቱን አላውቀዉም ”
አልኳት : የጡቶቿን ቅርፅ አሳምሮ የሚያሳይ ልብሷን ወደ ዳሌዋ ቁልቁል ሳብ አድርጋ
”ለፉገራ እወዳለሁ ብትለኝ ደደብ ነህ ልልህ ነበር ምክኒያቱም ለጨረቃ ግድ እንደሌለህ ታስታውቃለህ … አባቴ ሲነግረኝ የተፀነስኩትም የተወለድኩትም በሙሉ ጨረቃ ነው ይሄው እኔም በጨረቃ ሸርሙጨ በጨረቃ ፍም ስንዴ ዳቦ እጋግራለሁ … የአስቴርን ዘፈን ታውቀዋለህ ?”
እስክመልስላት አልጠበቀችኝም የአስቴርን ዘፈን ቀጠለች
”ስንዴ ዳቦ ጋገርኩ በጨረቃ ፍም ….”
አንድ ጡንቻው የለበሠዉን ጠባቃ ሸሚዝ ያስጨነቀ ወጣት ደረጃዉን አልፎ ወደ በረንዳው ብቅ አለ እንደሚፈልጋት ነግሯት ወደውስጥ ገባ የልጁ የራስ ፀጉር በተልባ ተዘፍዝፎ እንደከረመ ሁሉ ሉጭጭ ብሎ እዛው ተጠቅልሏል ::
”ዛሬ ሽቀላ ካላገኘው እሱን አቅፌ የመተኛት ግዴታ አለብኝ ”
አለች ምርር እንዳላት ሁሉ ዘፈኗን አቋርጣ
”ለምን …?”
ጥያቄዉን ለምን እንደጠየቅኳት ከጠየቅኳት በኌላ ራሴም ግራ ገባኝ
”እሱ የቤቱ ጋርድ ነው የፈለገዉን እንዲያደርግ የቤቱ ሕግ ይፈቅድለታል ”
ወዲያው ያ ፈርጣማ አንዱን እየጠፈጠፈ ይዞት ወጣ
”እና እስከመቼ ….?”
አልኳት እየተጠፈጠፈ ሚፈራገጠዉን ልጅ አይቼ
”ምን እስከመቼ አለው እሱ ቢሄድም ሌላው ጉልበተኛ ይተካል … አየህ ምግብ ቤት ‘ሚሠሩ ሠዎች ቤታቸው እየሄዱ አይበሉም ከሚሠሩበት ምግብ ቤት ውስጥ ያለዉን ምግብ ይበላሉ … ልክ እንደዛ ነው :”
ሲጋራዋን ወርውራ
”አናግሬው ልምጣ ”
ብላ ተነሳች ስትሄድ መቀመጫዋን ቃኘት ሳደርግ የቅድሟ ሴት ዓይኖቼን አይታ እንደማሽሟጠጥ ብላ አብሯት ወዳለው ሠውዬ ዞረች ሠውዬው ጥምብዝ ብሎ ሰክሯል ይለፈልፋል ይጠጣል … ከዛ የሷን ጭን ይዳብሳል እያመናጨቀች እጁን ስትገፈትረው ምንም አይላትም ይስቅና ድጋሚ መጠጡን ያነሳል : ከትንሽ ቆይታ በኌላ ልጅቷ
”ይቅርታ ሳልጠይቅህ አመጣው ”
አለችና ድራፍትና ጅን ይዛ መጥታ ተቀመጠች
”ምንሽ ነው ? አይለኝም …”
”ምን አልሽው ?”
” ምን እለዋለሁ ምኔም እዳልሆንክና አንተ ይዘህኝ እንደማታድር ነግሬው መጣዋ …?”
ሲጋራ ጠይቃኝ አቀጣጠልኩላት
”ይዤሽ እንደማልሄድ በምን አወቅሽ ?”
”አወቅኩዋ !”
በወፍራም ሳቋ ጥያቄዬን ከአፌ ቀማችኝ
”…ይልቅ ስለጨረቃ ላውራልህ ሚሰማኝ አግኝቼ ስለማላውቅ እኮ ነው … ምክኒያቱም አንተ ደደብ አይደለህም ታስታውቃለህ … እናልህ ……ልጅ ሆኜ አባቴ በረንዳችን ላይ ይዞኝ ይወጣና ጨረቃን ያሳየኛል ስለኳክብት ይነግረኛል ….”
ትልና ምስጥ ብላ ወደ ሠማዩ አንጋጣ ትቀራለች ጨረቃዋ ደመና ውስጥ ተወሽቃለች ለዚች የምሽት ንግስት መፅናኛ ወይም መተከዣ ለመሆን የኮራች ይመስላል : ትኩር ብዬ ሳያት ጨቅላ ዕድሜዋ ፈክቶ ታየኝ
”ስንት ዓመትሽ ነው ?”
አልኳት ከሃሣቧም ለማባነን
”አሁን 18 ሞልቶኛል … ምነው ፂፂ ሆንኩብህ ….? ቀጫጫ ነኝ አይደል ? ግን ‘ኮ ተማመን የሆነ ሼፕ ነው ያለኝ ስማ ይሄንን ፉራ ማይቋምጥበት የለም ….ኽ ?”
እያለች ከተቀመጠችበት ወንበር ሠውነቷን ጋደል አድርጋ መቀመጨዋን ባንድ ጎኑ ብድግ አድርጋ እያዞረች አሳየችኝ ::ወዲያው ሀዘኗ ወደቀልድ ተቀየረ : ሳቅኩ
”ቆንጆ ነሽ :”
አልኳት
”አባቴ … ግን ‘ኮ ቁንጅናሽ ፈተና እናድይሆንብሽ እፈራለሁ … እያለኝ ነው የሞተው ”
የሆነ ስሜት ተሰማኝ : አሁን ጊዜ ማባከን አልፈለግኩም እየተጣደፍኩ ድራፍቱን ጠጣውና
”ይቅርታ አብረን ማደር እንችላለን ?”
አልኳት
”ከምርህ ነው ?”
አለች ፍጥጥ ብላ እያየችኝ
”አዎ … የጀመርሽልኝን ወሬ ለብቻችን ሆነን ትጨርሺልናለሽ እሺ …?”
ተያይዘን ስንወጣ ያ ወጠምሻ በቢጫ ዓይኖቹ ገላምጦ ሸኘን
”እንዴት ግን በፍራቻ ከማትወጂው ሠው ጋር ትተኚያለሽ ?”
”ምን ማለትህ ነው ነብሱ ከምወደው ሠው ጋር ተኝቼ አላውቅም መዋደድ ሚባለውን ነገር ሳላውቅ ነው የሸረሞጥኩት ”
ሽቶዋ መኪናዬን አጠነው
”የት ነው አልጋ የያዝከው ?”
ነገርኳት :
”ነጋዴ ነህ ?”
አለችኝ መኪናዬን በደንብ ቃኝታው
”አይደለሁም …ምነው ?”
”አማኑኤል ሆስፒታል ለቀሻል ብለው ያስተኙኝ ጊዜ እዛ የተዋወቅኩት አንድ ዶክተር ነበር ልክ ሳይህ እሱን መስለህኝ ነበር ”
(‘ኝለቀሻል ‘ ምትለዋን ቃል ስትጠራት በሌባ ጣቷ የአናቷን ጎን ጠቁማ አሽከረከረች /በጨ … ለማለት / ) አንዱን ርዕስ ጀምራ ወደሌላ የመሄዷን ነገር እያሰብኩት በአሕምሮ መታመም ምክኒያት ሆስፒታል መተኛቷን ስትነግረኝ እንደምፍራትም እንደ ማዘንም አደረገኝ : በርግጥ አሳዝናኛለች በጣም ታሳዝናለች : ገና በእምቡጥ ዕድሜዋ ተቀጥፋ ዝሙት ውስጥ መወርወሯ አሳዝኖኛል ::
ሆቴል እንደደረስን መጠጥ አዘዝኩኝ : መኝታ ክፍሌ ስንገባ ሲጋራ ተቀብላኝ አልጋው ጫፍ ቁጭ አለች : አሁን ትኩር ብዬ አያዋት ጉንጯ ላይ ጠባሳ አለባት ጥርት ያለች ቆንጆ ናት
”እስቲ ስለ አባትሽ ንገሪኝ …”
አልኳት ….. የሸሚዜን ሁለት ቁልፎች ከላይ ከፈትኩና ዘና ብዬ ከፊትለፊቷ እግሬን ደራርቤ ወምበሩ ላይ ቁጭ አልኩኝ
”አባቴ … ”
ፀጥ አለች ….. ከዛም አነባች :: ስቅስቅ ብላ አነባች
”ለምን ታለቅሺያለሽ ?”
”ብዙ ጊዜ ሃዘኔን ያዩ ሠዎች ሃዘኔን ጠይቀው እያነባው መጥፎ ትዝታዬን ስነግራቸው ‘ተባኖብሻል የእኛን ሆድ አባተሽ የሠው ሙድ ከስክሰሽ ሳትንፊ ልታመልጪ ነው ‘ እያሉ ቅጥቅጥ አድርገው እንደፈለጉ ያደርጉኛል ….”
ዕምባዎቿ ሲፈሱ አልጠረገቻቸዉም …………………. የመኝታ ክፍላችንን በር ቀብቅቅቦ ጥርሱ ያለውበት ከተማ ነዋሪነቱን ሚመሰክር አስተናጋጅ መጥጥና ብርጭቆዎች ይዞ መጣ ቀድቼ አቀበልኳት ቀጠለች ታሪኳን
”አባቴን ፊትለፊቴ ገደሉት … ወንድሜ አመለጠ … አባቴ ግን በደም የተለወሰ እጆቹን ዘርግቶ የኔን እርዳታ እየጠየቀ ሞተ … እናትም ጓደኛም ሆኖ ያሳደገን አባታችን …”
በእንባ ሙላት የቀሉ እነኚያ ዓይኖቿን ወደመጠጡ ስታይ ደገምኳት :
”ወንድሜንም ገለዉት ይሆናል አላውቅም ደደቦች አይደሉ … እኔን በዛ እድሜዬ ራሴን እስክስት ደፈሩኝ …”
ንግግሯን የሚያቋርጥ ሳግ ልቧን እያፈነው ሲጋራ ጠየቀችኝ ሰጠዋት መጠጥ ድጋሚ ስትጠይቀኝ ከለከልኳት …
”ይሄንን ሀዘኔን ልቀይርልህ ከፍለህ እስካመጣህኝ ድረስ በሀዘን የተጨማደደ ስሜት ማግኘት የለብህም … ”
እጆቿን ስትዘረጋ ከለከልኳት ታገለችኝ : ሠውነቷ ከሠውነቴ ሲነካካ አንዳች ስሜት ነዘረኝ ምናልባትም እሷ ደደቦች ብላ የሰየመቻቸው ዓይነት ድድብናን መውረስ የፈልግኩ መሰለኝ : እንደ እብድ ስትጮህ ጠርሙሱን አቀበልኳት ጠጣችው ፊቷን እያኮማተረች ጠጣች :
ከዚህ በኌላ ታሪኳን የመስማት ዕድሉ አልነበረኝም : ግን በጣም ተደስቺያለሁ : :
ሲነጋ የናዝሬት ፀሐይ በንፋስ ታጅቦ መኝታቤታችን ገባ :: ልብሷን ለባብሳ ወምበሩ ላይ ቁጭ ብላለች ስካሩ ሙሉ በሙሉ እንዳልለቀቃት ታስታውቃለች
”ምነው ?”
አልኳት ሠዓቴን እያየው
”ብር ስጠኝና ልሂድ …”
”የት ነው ምትሄጂው ገና ጠዋት እኮ ነው …”
”ተጠይፈህኝ ነው አይደል አንተ መሬት ተኝተህ ያደርከው ?”
እጆቿን አጣምራ በተቀመጠችበት እግሮቿን ትወዘውዛለች
”ይቅርታ ስምሽ ማነው ?”
አልኳት
”ስሜ ምን ያደርግልሀል … አሀ ለካስ ማታ ስሜን እንኳን አልጠየቅከኝም ”
ፊቷ ባንድ ጊዜ ቲማቲም መሰለ : ቆመች አንጠልጥላው የነበረ ቦርሳዋን አጥልቃው
”ለነገሩ ሁሉንም ነገር የማድረግም ያለማድረግም መብትህ ነው …. ግን … ግን …”
ስቅስቅ ያለ ለቅሶዋ ንግግሯን አቋረጠው
”…. ሠው ሚፀየፈኝ ያህል ደረጃ መድረሴ ታውቆኝ አያውቅም …”
ንግግሯ አስደነገጠኝ በእርግጥ ማታ ከስሜቴ ጋር ክፉኛ ስንሟገት ነበር በተለይ ከቦርሳዋ ውስጥ የሌሊት ልብሷን አውጥታ ፊትለፊቴ ስትቀይር ገላዋ ተገላልጦ ሳየው መስከር ፈልጌ ነበር ስክር ብዬ ራሴን ስቼ እዛ ገላ ውስጥ ተጣብቄ ማደርን ፈልጌ ነበር :
ለቅሶዋንም ለማባበል ተጠግቺያት
”ረጋ በይ ሂሩት ….”
ስላት ቦርሳዋን በቁሟ ለቀቀችው ዓይኖቿ ፈጠጡ
”ስ …ስ … ሜን እንዴት አወቅከው … በዚህ ስም …”
ስጠጋት ፈራችኝ ወደበሩ መሸሽ ጀመረች
”አትጠጋኝ ……. አትጠጋኝ … አን …ተ … ማነህ ?”
”ይሄውልሽ ሂሩት ቁጭ በይ ስለ ሁሉም አስረዳሻለሁ … እዚህ ናዝሬት የመጣውት አንቺን ፍለጋ ነው አንቺን ስፈልግ ወደ 3 ወር ፈጅቶብኛል … ወንድምሽ በሕይወት አለ እሱ እንድፈልግሽ ሠው ልኮብኝ ነው ….”
”ምን …….?”
”ውጪ አገር ነው ያለው …”
አልኳትና ደብዳቤዉን ከኪሴ አውጥቼ ሠጠዋት ማንበብ ቀጠለች …
‘ሂሩትዬ … ከአባታችን ገዳይ ውስጥ አንዱ ገለሽ መሠወርሽን ሠማው ………..’’
የተሠጠኝን ኃላፊነት በትክክል የተወጣውት መሠለኝ : ዛሬ ወንድሜ ጋር ደውዬ የሂሩትን ወንድም ማናገር አለብኝ : ከሸሚዝ ኪሴ ፎቶግራፏን ስሰጣት ደብዳቤዉን በለቅሶ አንብባ ጨርሰዋለች ….
ተፈፀመ