በግላቸው የሚሰሩ እንዴት ለጡረታቸው ገንዘብ ማጠራቀም ይችላሉ? – ጉዳዩ ለትናንሽ ድርጅቶች የሚሰሩትንም ያጠቃልላል

ከዮሃንስ አለማየሁ
በዚህ ጽሁፌ ለግላቸው የሚሰሩ ሰዎችና የትንንሽ ድርጅቶች ባለቤቶችና ሠራተኞች ለጡረታ ጊዜ የሚሆናቸውን ሃብት ለማጠራቀም ምን ማድረግ እንዳለባቸው አንዳንድ ሃሳቦችን ለመጠቆም እወዳለሁ:: በመጀመሪያ ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው የህብረተሰባችን አባላት ለጡረታ የመዘጋጀት ጥቅሙን በመጠኑ እጠቁማለሁ።

1. ለመንግስት የሚከፍሉትን ቀረጥ ለመቀነስ ወይም ጭራሽ ለማስወገድ
2. ለጡረታ የሚሆናቸውን ሃብት ከሌላው ሃብታቸው በመለየት ከግልም ሆነ ከድርጅት ጋር ከተያያዘ እዳ ለመከላከል
3. ለቤተሰቦቻቸው ከድርጅታቸው ወይም ከሥራቸው ጋር ያልተያያዘ የጡረታ ጊዜ የሃብት ዋስትና ለመስጠት
በተለይ የግል ድርጅት ባለቤቶች የሚሰሩላቸውን ሠራተኞች ለጡረታ እንዲዘጋጁ በመርዳት ሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ማበረታታትና በሚያገለግሉበትም ህብረተሰብ አካባቢ ጥሩ ሃሳቢና ደግ በመባል የበለጠ ደንበኞችን ለመሰብሰብ ይረዳል።
ጥቅሞቹ በከፊሉ ከላይ የተጠቀሱት ከሆነ በግላቸው የሚሰሩ ሰዎችን የትንንሽ ድርጅቶች ባለቤቶችና ሰራተኞች ለጡረታ ለመዘጋጀት የምጠቀሙባቸው ዘዴዎችን በከፊሉ እንደሚከተለው አመለክታለሁ። እነዚህ ሰዎች መጠቀም ካለባቸው የጡረታ ሃብት ሃብትማጠራቀሚያ ዘዴዎች ውስጥ ዲፋይንድ ኮንትሪቢውሽን (Defined contribution) በሚለው ውስጥ የሚጠቃለሉትን እናያለን።
Simplified Employee Pention (SEP):- በዚህ ዘዴ ለግላቸው የሚሰሩ ከገቢያቸው በዓመት 20%ን እስከ 45 ሺ ዶላር በ2009 እና እስከ 46 ሺ ዶላር በ2010 ለጡረታቸው ከታክስ ነጻ በሆነ መንገድ ማስቀመጥ ይችላሉ።
ለትናንሽ ድርጅት ባለቤቶችም ይህ ዘዴ ይጠቅማል፣ እሱም ከላይ የጠቀስኩትን መጠን ከገቢያቸው ቀንሰው ለጡረታ ማስቀመጥ ይችላሉ። የድርጅቱ ባለቤት በዚህ ዘዴ ተጠቅሞ ለራሱ የጡረታ ገንዘብ ካስቀመጠ ለሠራተኞቹም ከደሞዛቸው ከ1% – 15%የሚደርስና ከ24 ሺ ዶላር የማይበልጥ ለጡረታ የሚሆን ገንዘብ ማስቀመጥ ይገባዋል። ሠራተኛው ራሱ ተጨማሪ SEP ውስጥ ማስቀመጥም ይችላል። በዚህ ዘዴ የድርጅቱም ባለቤት ሆኑ ሠራተኞቹ የሚከፍሉትን ታክስ ይቀንሳሉ። SEP ለመክፈትና ለመጠቀም በጣም ቀላል ነው።
SOLO 401K:- በዚህ ዘዴ ለግላቸው የሚሰሩ ግለሰቦች በዓመት እስከ 46 ሺ እድሜ ደግሞ ከ50 በላይ ከሆነ እስከ 51ሺ ዶላር ለጡረታ ጊዜ ከታክስ ነጻ ማስቀመጥ ይችላሉ። በዚህ ዘዴ አነስተኛ ለሆኑ የግል ድርጅቶች የሚሰሩ ሰራተኞች በዓመት እስከ 10ሺ ከታክስ ነጻ የሆነ ገንዘብ ለጡረታ ማስቀመጥ ይችላሉ። በዚህ ላይ የድርጅቱ አሰሪ ወይም ባለቤት ከጨመረ (ማች ካረገ) የጡረታም ጊዜ ሲመጣ ብዙ ገንዘብ ሊሆን ይችላል።
ROTH IRAs:- SEP ወይም 401K ውስጥ ከሚያስቀምጡት ገንዘብ ሌላ ROTH IRAs ውስጥ በዓመት 4 ሺ (በ2007) እንዲሁም 5 ሺ (በ2008) ማስቀመጥ ይችላሉ። ሮት አይ አር ኤ ውስጥ ማስቀመጥ የሚችሉት ታክስ ከከፈሉበት ገንዘብ ላይ ስለሆነና ወደፊት ገንዘቡ ሳያድግ የሚያገኙት ትርፍ ላይ ምንም ታክስ ስለማይከፍሉ ጠቀሜታው በጣም ከፍ ያለ ነው። ስለዚህ ይህ የጡረታ ሃብት ማከማቻ ዘዴ በጣም ተመራጭ የሆነ ዘዴ ነው፤
Payroll Deduction IRAs:- አነስተኛ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች በዚህ ዘዴ ከደሞዛቸው እየተቆረጠ በዓመት እስከ 2000 ዶላር ከታክስ ነጻ የሆነ ገንዘብ ለጡረታ ጊዜ እንዲሆናቸው ማስቀመጥ ይችላሉ። ይህን ዘዴ ለመጠቀም አይ አር ኤ አካውንት መክፈትና ከደመወዝ ተቆራጭ በማድረግ እንዲቀመጥ ማድረግ ብቻ ስለሆነ ቀላል ግን የአሰሪዎችን በጎ ፈቃድ የሚጠይቅ ነው።
ከላይ የዘረዘርኳቸው ለግላቸው ለሚሰሩም ሆነ ለትናንሽ ድርጅቶች ባለቤቶችና ሰራተኞች ለሆኑ ግለሰቦች የጡረታ ጊዜ ሃብት ማከማቻ ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ምክሮች ነው። እነዚህ ዘዴዎች ሁሉንም ያጠቃለሉ ባይሆኑም ዋና ዋናዎቹና ለኛ ህብረተሰብ ይጠቅማሉ ያልኳቸው ናቸው። ተጨማሪ ምክር ለማግኘት በዚህ መስክ እውቀቱና ልምዱ ያላቸውን በማነጋገር ታክስ የሚከፍሉትን በመቀነስና ለጡረታ ጊዜ የሚያስፈልጎትን ሃብት በሚገባ ማከማቸት ይችላሉ።
__________________________________________
* አቶ ዮሃንስ አለማየሁ በሙያቸው ሲ ፒ ኤ የሂሳብ ሰራተኛ ሲሆኑ ለአንድ ፎርቹን 100 ትላልቅ ኩባንያዎች ካላቸው ለአንዱ ተቀጥረው በመስራት ላይ ይገኛሉ::S

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዓብይ አህመድ ኃይሎች በዓድዋ ድል በዓል ህዝቡ በምኒሊክ አደባባይ እንዳያከብር ግፍ ሲፈጽሙ ዋሉ
Share