( ከ’አባይ’ – ‘ባ’ ጠብቆ ይነበብ፤ ከ’አባዮች’ – ‘ባ’ ላልቶ ይነበብ (ዋሾዎች ለማለት ፈልጌ ነው፡፡)
ይድረስ ለተወደዳችሁ በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንዲሁም ይህን ጽሑፍ ልታነቡ የቻላችሁ ክቡራን የሰው ዘር አባላት በሙሉ፤
ብዙዎች ኢትዮጵያውያን በኃያል መቅሰፍትነቱ የምናውቀው ኢትዮጵያ ላይ የነገሠው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መንግሥት ባጭር አጠራር ‹ወያኔ‹ በመባል የሚታወቀው የወንበዴ ቡድን እየሠራ ያለው ሕዝብን የማራቆት ሥራ ቢያንገበግበኝ ጊዜ ይህችን ማስታወሻ ለታሪክ መታሰቢያት ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ አሁን በምንጽፈውም ሆነ በምንናገረው ነገር ለጊዜው ምንም ዓይነት ፍርድ የምናገኝ አለመሆናችንን ብንረዳም እንደነዚህ ተመዝግበው በሚቀመጡ ታሪካዊ ማስታወሻዎች መነሻነት አጥፊዎች የሥራቸውን እንዲያገኙና ሌሎች ተረኞችም አሁን ከምናሳልፈው ግላዊም ይሁን ማኀበራዊ የሕይወት ገጠመኞች ልምድ ቀስመው አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ ስለሚረዳ እንደዚህ በአደባባይ መጮሃችን ለጊዜው አስፈላጊነቱ አነስተኛ መስሎ ቢታይም ለወደፊቱ በእጅጉ ጠቃሚያችን መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡
በግርድፍ ግምት ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከከፋ የድህነት ወለል በታች በሚኖርበት በአሁኑ ወቅት ችግር የሚባል ሲያልፍ የማይነካውና ስለችግር ምንነትም አንዳችም ግንዛቤ ያለው የማይመስለን የወያኔ መንግሥት በአባይ ግድብ ምክንያት ሕዝቡን በየአቅጣጫው እየዘረፈ ነው፡፡ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ‹ከዚህ በገንዘብ ፍቅር ለይቶለት ካበደ የወያኔ መንግሥት ማን ይታደገን?› የሚለው ነው፡፡
አሁን ህመሙ ባሰበትና ከነአካቴው ቅጥአምባሩ ጠፋበት እንጂ ቀድሞም ቢሆን የወያኔ ጎጠኛ የዘራፊዎች ቡድን የሚሠራው ሥራ ሁሉ ጤናማ መንግሥት ይሠራዋል ተብሎ የሚጠበቅ አልነበረም፤ አይደለምም፡፡ የአሁኑ ግን እጅግ የከፋ ሆኖብናል፡፡ ዜጎች በተለይም አነስተኛ ገቢና ጥቃቅን መተዳደሪያ ያለን በበርካታ ሚሊዮኖች የምንቆጠር ወገኖች የግፉ ቀንበር ሸክሙ ከብዶብን መድረሻ አጥተናል፡፡ እባካችሁ ተሰሚነት ያላችሁ ወገኖቻችን ለሚመለከተው ሁሉ ጩሁልን፡፡
በመሠረቱ እንደወያኔ ያለ አጭበርባሪና ሌባ መንግሥት ሳይሆን ሁነኛ የሕዝብ መንግሥት በሀገራችን ሥልጣን ላይ ወጥቶ በምክክርና በሕዝባዊ ይሁንታ ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ለአንድ ግድብ ቀርቶ ለበርካታ የኒኩሌየር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ(ለሰላማዊ አገልግሎት) አዋጡ ቢባል አንድም ሰው አይከፋውም – በደስታ ጮቤ ይረግጣል እንጂ እንዲያውም፡፡ የአሁኑ የወያኔ ዓላማ ግን ለሀገርና ለሕዝብ ተጨንቆና ተቆርቁሮ ወይም ተጠብቦ ሳይሆን ሕዝብን በ‹ፍቅሩ› ለማማለልና ውዴታን ለማግኘት ታስቦ ከመሆኑም በተጨማሪም የሃሳቡን መነሻ ጊዜ ስናጤነውና የአብዛኛውን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ስንቃኘው እንኩዋንስ ለግድብ ማሠሪያ አዋጣ ሊባል ከእጅ ወደአፍ መሆንም አቅቶት በርሃብ አለንጋ እዬተገረፈ ባለበት ሁኔታ የሚገኝ በመሆኑ ይህን ሕዝብ አፅሙን መጋጥና መቅኒውን መምጠጥ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ይቅርታና ሥርየት የሌለው ኃጢያት መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ የሚያዳግተው ጤናማ ዜጋ የለም፡፡ ይህን አለሁህ ባይ የሌለውን ሕዝብ በግላጭ አገኘሁት ብሎ ይህን ያህል መጨከን የዞረ ድምር እንዳለውና ለልጅ ልጅ የሚተርፍ አበሳ እንደሚያስከትል የወያኔው መንግሥት ቢረዳ ለሁላችን በበጀን ነበር፡፡ እንዲህ ሕዝብን አስለቅሶ እንደዋዛ ተሸሽጎ መቅረትና ተደብቆ ዓለምን መቅጨት የማይታሰብ መሆኑን እነዚህ ሕዝብ አስለቃሽ ወሮበሎች ሊገነዘቡም በተገባቸው – አእምሮኣቸው በጊዜያዊው ዓለማዊ ደስታ ባይታወር ኖሮ፡፡ የሂትለር ጀሌዎች በዘመናቸው በሠሩት ጥፋት የተነሣ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በዓለም ዙሪያ ከየተደበቁበት እየታደኑ ካረጁ ካፈጁ በሁዋላም ቢሆን ለፍርድ ሲቀርቡ ማየታችን ለዚህ እውነት አንዱ ማስረጃችን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ለዚህ መከረኛ ግድብ የምናዋጣበት መንገድ በጣም ብዙ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ በመሥሪያ ቤቴ የአንድ ወር ደመወዜ በአንድ ዓመት ውስጥ ተቆርጦ ገቢ እንዲሆን በግድ አስፈርመውኛል፡፡ አካሄዱ እንዲህ ነው፤ ስብሰባ ተጠራን፡፡ የመሥሪያ ቤታችን ዋና አለቃ በይምሰልና በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ የልግጫ ፈገግታ ተሞልቶ እንዲህ ብሎ ስብሰባውን ጀመረ፤‹ በእውነቱ በዚህ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እንደዛሬ ኮርቼ አላውቅም፡፡ በየዲፓርትመንታችሁ ተወያይታችሁ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአባይ ወንዝ የአንድ ወር ደመወዛችሁን በአንድ ዓመት ውስጥ ለመስጠት መወሰናችሁ ማኔጅመንቱን በደስታ አስፈንድቆኣል፤ ኩራትም አላብሶናል፡፡ … › አድርባይነት ማለት እንዲህ ነው፡፡ ድርጅታዊ አሠራር ማለትም እንደዚህ ነው፡፡ ደርግን ‹በየት ዞረህ ቀደምከኝ?› ብሎ መጠየቅ አሁን ነው – እንደአለቃ ገ/ሃና ቀልድ፡፡ ሁሉም ሠራተኛ አንገቱን ደፍቶ ከአዳራሹ ወጣ – ምርጫ አልነበረውም፤ ጎልያድን በአንደበት ብቻ መጋፈጥ ትርፍ እንደሌለው ከተረዳን ሰነበትን፤ ሌላ ዘዴ መቀየስ ነው የሚያዋጣው፡፡ ወንበዴን በቃላት እሩምታ ማሸነፍ እንደማይቻል ተገንዝበናል፡፡ ወሮበላን ለመርታት የመናገር ችሎታ ብቻ ሳይሆን ውሃ የማያሰኝ ወፍራም ዱላም መያዝ ግድ የሚልበት ጊዜ አለ፡፡ እንዶድ በየዋህነትዋ ወንዝ እንደወሰዳት ለመረዳት የ97 ምርጫን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ያኔ አላሳን ወተራዊ ሥልት ተጠቅመን ቢሆን ኖሮ ዛሬ መለስ ዜናዊ ድመት የአይጥ ግዳይዋን ከመብላትዋ በፊት እንደምትጫወትባት ዓይነት የፉገራ ጨዋታ አይጫወትብንም ነበር፡፡
በነገራችን ላይ የሚሰማንን በገሃድ አውጥተን አለመናገራችን ለወያኔው የተስማማው ይመስላል፡፡ መጥፎነቱ ጫካውን ሁሉ ናፍጣና ቤንዚን እያርከፈከፉ ሳይቀር በሰደድና በጋያ አቃጥለውና መንጥረው ስለጨረሱት ጫካ የለም እንጂ ከኩርፊያው መረዳት እንደሚቻለው ብዙው ሠራተኛ በምናቡ ‹ፋኖ ተሠማራ› የሚል ይመስላል፡፡ ጥቃት መጥፎ ነው፡፡ እንደጥቃት ውስጥን የሚያቃጥል ነገር የለም፡፡ በእውነቱ ሁሉም እዬተቃጠለ ነው፡፡ ምን ማድረግ እንደሚችልም ግራ የተጋባው ዜጋ ብዙ ነው፡፡ በቁምህ ካለውዴታህ ቆዳህን ሲገፉት ስታይ፣ በአራቱም አቅጣጫ ስታማትር የሚደርስልህ አንድም ሰው ስታጣ፣ ተስፋህ ይመነምንና ቅስምህ ይሰበራል፡፡ ወያኔዎች ቅስማችንን ብቻ አይደለም እዬሠበሩት ያሉት ፤ የኀልውና እስትንፋሳችንንም እዬዘጉት ናቸው፡፡ ‹እኔ እምሞት ዛሬ ማታ፤ እህል እሚደርስ በፍልሰታ› እንደተባለው የአባይ ግድብ እውነት እንኩዋን ቢሆን አሁን የምንቀምሰውንና የምንልሰውን አጥተን እነሱው በፈጠሩት የኑሮ ውድነት እየተቆላን እያለን እንደዚህን ያህል ወርደው ኢሰብኣዊ ከሆኑ ዕንባችን ይፋረዳቸው እንጂ ለጊዜው ምንም የምንለው ነገር የለንም፡፡ ግን ወዮ ለቀናቸው! ቀናቸው ሲደርስ ይገቡበትን ቀዳዳ ያጣሉ፡፡
በመሥሪያ ቤቴ ብቻ አይደለም የሚገፉኝ፡፡ (‹ፉ›ን በሁለቱም አገባብዋ ልትወስዱዋት ትችላላችሁ፡፡) በትምህርት ቤት በልጆቼም እንዲሁ ተገድጄ የተጠየቁትን ብር ዛሬ ጥዋት ልኬያለሁ፡፡ በሠፈር ነዋሪነቴም መጥተውብኛል፡፡ በዕድርም ገና ይመጣሉ፡፡ በምገብርባቸው የመንጃ ፈቃድና ሌሎች ካርዶችና መታወቂያ ወረቀቶችም እንደሚመጡ ግልጥ ነው፡፡ እነሱ እንደሆኑ በጽዋ ማኀበሬም ሳይመጡብን አይቀሩም፡፡ አንዴውኑ በወጥመዳቸው ገብቻለሁና ካልሞትኩላ(ባ?)ቸው እንደማይለቁኝ ተረድቻለሁ፡፡
በመሠረቱ ወያኔ ማለት መርዝ ማለት ነው፡፡ የመርዝነት ደረጃውም ኃይለኛው የአናኮንዳና የኮብራ ወይም የእፉኝት ዓይነት ነው፡፡ የወያኔዎች ንድፊያ በምንም ዓይነት መንገድ መድኃኒት አይገኝለትም፡፡ ብቸኛው መዳኛ መንገድ የሕዝብ አንድነትና እምቢ ለነጻነቴ ባይነት ነበር፡፡ ያ ግን እስካሁኒትዋ ቅጽበት በተግባር ሊታይ አልቻለም፡፡ እነሱም የሕዝቡ አለመተባበርና ተለያይቶ መሰባበር የልብ ልብ ስለሰጣቸው ይሄውና ያሰኛቸውን ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡ ዘረፋቸውም ቅጥ አጥቶ የገንዘብ ፍቅር አንድያውን አራዥቶኣቸዋል፡፡ አያያዛቸው ሲታይ በቀላሉ የማይወጡት አፍቅሮተ ንዋይ ውስጥ ተዘፍቀው ራሳቸውም አብደው ሕዝብንም እያሳበዱ ለመሆናቸው በግልጽ የሚታይ ሆንዋል፡፡ እግዚኣብሔር ይሁነን እንጂ አካሄዳችን በፍጹም አያምርም፡፡
እግዜር ያሳያችሁ እንግዲህ፤ ተማሪን ለግድብ ማሠሪያ ገንዘብ አምጣ ማለት ምን ማለት ነው? ከየትስ ያመጣል? ስንቱ ወላጅ ነው የልጆቹን ወስፋት ሳይሸነግል ባዶ ሆዳቸውን ት/ቤት የሚልከውና ምሣ ሰዓት አካባቢ በጠኔ (…) ኦ! ሌላ የቅንጦት ብሶት ላሰማችሁ ፤ ‹በጠኔ› ካልኩ በሁዋላ አሁን በዚህ አንቀጽ ውስጥ በቅንፍ ካስቀመጥኩት ነጠብጣብ በፊት ስንትና ስንት ነገር ጽፌ ነበር፡፡ ነገር ግን መብራት በመሄዱ ያ ሁሉ የለም፡፡ ‹በጠኔ› እስከሚለው ብቻ የጻፍኩትን አገኘሁ፡፡ ግዴለም እሱስ ይሙዋላል፡፡ ግና ተመልከቱ ችግራችንን፡፡ መብራት ያለማስጠንቀቂያ ሲፈልግ በየአሥር ደቂቃና ከዚያም በታች ወይም በላይ በሆነ የጊዜ ርዝማኔ እየሠራህ እያለ ሊጠፋብህ ይችላል፡፡ ለቀናትም ላይኖርህ ቢችል ተጠያቂ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ስትኖር አቡዋራና ትቢያ ነህ፤ ሰው መስለህ የምትታየው በአካል እንጂ በኅሊናዊ ኑባሬህ አይደለም፡፡ እናም እንኩዋንስ ‹መብራት ጠፍቶብኝ ጨለማ ዋጠኝ፣ ውሃዬ ጠፍታ ከነቤተሰቤ በጥም ሞትኩኝ፣ ስልኬ ተጠልፎ ባለዕዳ ሆንኩኝ ወይም በብልሽት ምክንያት አግልግሎት ተቁዋረጠብኝ› ብለህ ልትጮህና ልትደመጥ ቀርቶ እንዲህ በማለትህ ራሱ በቅንጦተኛ ባለአቤቱታነት ተወንጅለህ በጥቂቱ ይሳቅብሃል፤ አለበለዚያ ያልሠራኸው ወንጀልና ጥፋት ተፈልጎልህ ሸቤ ትገባለህ – ከ‹ስህተትህ እስክትማርና እንድትማርም›፡፡ በዚያ ላይ የመብራቱም፣ የውሃውም፣ የስልኩም፣ የነዳጁም፣ የሸቀጡም፣ የአገልግሎቱም፣ የምኑም የምናምኑም ታሪፍ በየጊዜው – በዬደቂቃው – ህልምና ቅዠታቸው በሉ ባላቸው ቁጥር – ጠጥተው ወይም ቅመው በመረቀኑ ጊዜ ገንዘብ የማግኛ ሥልት በነደፉ ቁጥር – ያንተን የድሃውን አቅም ባላገናዘበ መልክ ተመኑን ወደሰማይ ሽቅብ ያሽቀነጥሩትና – እንደወስፈንጠር ወደሰማየ ሰማያት እንደኩዋስ ያጉኑትና በቤትህ የነዚህን አገልግሎቶች አጠቃቀም ለመቀነስ ስትል ቤተሰብህን አፍነህ ለመያዝ ሁሉንም የእመቃ ዘዴዎች እንድትጠቀም ልትገደድ ትችላለህ፡፡ ለውሃው ተነቃይ ቁልፍ፣ ለመብራቱ ጭል ጭል የሚል ኃይል ቆጣቢ አምፖል፣ ለስልኩ አስተማማኝ ጉዋጉንቸር ገዝተህ እያንዳንዱን ትከረችምና ቤተሰብህን ማንጫጫት ትጀምራለህ፡፡ ወያኔ ከላይ አንተን ሲያንጫጫ አንተ ደግሞ በተራህ በሥርህ ያሉ ምሥኪኖች ሚስትህንና ልጆችህን እጥፍ ድርብ የሆነ መብረቃዊ ቁጣህን ታወርድባቸዋለህ – ምርጫ የለህማ! እቶናዊ የሲዖል ኑሮ ይሉሃል ይቺ ናት ታዲያ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ወያኔውንና አድርባይ ነጋዴውን አያካትትም፤ ሙሰኛውንና የወር ደመወዙን በወዳጅ ዘመዶቹ ልመና እዬተጉዋደደ የሚወስደውን ጉቦኛ አይጨምርም፡፡ ሀገር የሚሸጠውንና የሚያሻሽጠውን ወፍ ዘራሽ ትውልድ አይመለከትም፡፡ የወያኔው መንግሥት በሥሩ ያሉትን ዘበናይና ቅንጡ አጫፋሪዎቹንና ባስነጠሰው ቁጥር መሃረብ የሚያቀርቡለትን እንደነእንቶኔ ያሉ ሀብታሞችን የተንደላቀቀ ኑሮ እያየ በሚያወጣው ሕግና የዋጋ ጭማሪ የምንጎዳው እኛ ምንዱባኑ ተራ ዜጎች ነን፡፡ እኛን ለማየት ወደኛ ዝቅ ብሎ ችግራችንን መጠየቅና ኑሮኣችንን መመልከት ይገባል፡፡ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ተቀምጦ ወይም በሚያማምሩ ሆቴሎች እየተንፈላሰሱ ‹ዕድሜ ለወያኔ፣ የኢትጵያ ሕዝብ አልፎለታል› ማለት ከለየለት ነፍሰ ገዳይነት የማይተናነስ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡
ለማንኛውም የጀመርኩትን ሃሳብ ልቁዋጭና ብሶቴን ላብቃ፡፡ … ምሣ ሰዓት አካባቢ በጠኔ ምክንያት እዬተዝለፈለፉ በየት/ቤቶች ቅጽር ግቢዎች የሚወድቁትን የድሃ ቤተሰብ ልጆችን ሃያና ሠላሣ ብር አምጡ ማለት ምን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል? በበርካታ ት/ቤቶች በበጎ ፈቃደኞች የተደራጁ የድሃ ቤተሰብ ልጆች ተማሪዎችን የሚመግቡ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች አሉ፡፡ ከነሱ የምንሰማው ወሬ በሚዘገንን ሁኔታ ያስደነግጣል፡፡ አብዛኛው ተማሪ እንኩዋንስ ለግድብ ገንዘብ ሊከፍል ይቅርና የራሱም ነፍስ ከግድቡዋ ልትወጣና እስትንፋሱ በርሃብ ልታልፍ አንድ ሀሙስ ነው የቀራት፡፡ ተማሪውም ሆነ ወላጁ የግዳቸውን ነው የሞት ሞታቸውን በጠኔ እዬተንጠራወዙ የሚኖሩት፡፡ ‹እኔ እምሞት ዛሬ ማታ እህል እሚደርስ በፍልሰታ› ይባላል፡፡ ወያኔ የሚቀልድበትና የሚያፌዝበት የአባይ ግድብ ሥራ ተጠናቅቆ ኃይል ወደውጭ ሀገራት በመሸጥ ገንዘብ የምናገኝበት ጊዜ በዕቅዱ መሠረት ይከናወናል ቢባል እንኩዋ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለት በመቶ የማይሆነው ተንደላቅቆ እዬኖረ ሰፊውን ድሃ ሕዝብ በዚያች ባለችው ሽርፍራፊ ሣንቲምና ለምኖም ሆነ ተመጽውቶ በሚያገኛት እጅግ አነስተኛ ‹ገቢ› የዕለት ጉሮሮውን እንዳይዘጋ ከሌለው ላይ እነኚያ በሚሊዮንና በቢሊዮን ደረጃ ያላቸው ኀሊናቢስ ዜጎች በፈረዱበት ግፈኛ ፍርድ ምክንያት የማይወጣው ዕዳ ውስጥ እየተዘፈቀ ይገኛል፡፡ ይህ የግፍ ግፍ ፍርድ እንደጤዛ የሚረግፍ ወይም እንደጉም የሚበንን ሳይሆን ተጠራቅሞ የልጅ ልጅ ድረስ የሚወራረድ የኃጢያትና የመርገምት ቁልል የሚያስከትል መሆኑን የአሁኖቹ የሀገር መሪ ተብዬዎች በቅጡ ሊገነዘቡት በተገባ ነበር፡፡ ግፍን ለትውልድ ማስቀመጥ ደግሞ ኩነኔ ነው፤ በቀጣይ ትውልዶች ክፉኛ ያስወቅሳል፡፡ የአሁኑን ትውልድም መቅኖ ያሳጣል፡፡
ስለዚህ የተወደዳችሁ በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ወንድምና እህቶቻችን እባካችሁ ይህንን ብሶታችንን ሰው ለሆኑ ሰዎች አሰሙልን፡፡
ምሬታችን የሰማይን በሮች ከአንኩዋኩዋ ዘመን የለውም፡፡ ዕንባችን ኩሬና ምንጮችን ሞልቶ ሀይቅና ባህርም ሆኖ ወደ ውቅያኖሶች እየፈሰሰ ነው፡፡ በላያችን ላይ የወደቀው ወያኔያዊ የግፍ አገዛዝ ቀምበር ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ሆኖብን ትከሻችን ጎብጦ እንደ ክርስቶስ ኤሎሄ ማለት ከጀመርን ሃያ ዓመት አስቆጥረናል፡፡ የእስካሁኑን ልቅሶና ዋይታችንን ያዳመጠን የለም፡፡ ለወትሮው ‹የእስራኤል አምላክ፤ የኢትዮጵያ አምላክ፤ የአንድዬ እናት ወለለዋ …› እያልን በራሱና በቅዱሳኑ አማካይነት የምንለምነው እግዚኣብሔርም የኃጢያታችን ብዛት ከኛ ስላራቀው ይመስላል ፊቱን ሊያዞርልን አልቻለም፡፡ የኛ እርግማን ለወያኔዎች እንደምርቃት እዬተቆጠረ ኃይላቸውና ብርታታቸው ሳይዝል በብረት እንደወገሩን እስካሁን አሉ፡፡ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው አንድ ብቸኛ መታደጊያችን የኛ መተባበርና በአንድነት መነሣት ነበር፡፡ አሁን ለጊዜው ግን ያ እውን እንዳይሆን የያዘን ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ይህን እኛን የሚለያዩበትን ድግምት መሰል መሠሪ ተንኮላቸውንና ደንቃራቸውን በጋራ ሆነን መክረን መፍትሔ በመፈለግ ትብታባቸውን ካልሻርን ወይም ካላከሸፍን ወዮልን! ሌትና ቀን በሚያካሂዱዋቸው ስብሰባዎች የሚማከሩት ለኛ ሳይሆን የሚመሣጠሩት በኛ ላይ ነው፡፡ ከምድረ ገጽ ሊያጠፉን የቀራቸው ጊዜ በጣም ኢምንት መሆኑን ተረድተን አሁኑኑ አንዳች የመፍትሔ እርምጃ ልንወስድ ጊዜው ያስገድደናል፡፡ እየተፈራራንና አንዳችን አንዳችንን እዬተጠራጠርን ብዙ ጊዜ አባክነናል፤ ያም ሊቆጨን ይገባል፡፡ ከአሁን ወዲያ ግን የመጣው ይምጣ ይለይልንና በክቡር ሞታችን ክቡር ነጻነታችንን እንጎናጸፍ፡፡ ሞቱ እንደሆነ አሁንም ቢሆን አልቀረልንም፡፡ ተበታትነን በድህነትና በውርደት ከምንጠፋ ተባብረን ለብልጽግናና ለጋራ ዕድገት የክብር ሞትን እንሙት፡፡ በዚያውም የፍርሀትንና የትግስትን ገደብ ለነዚህ ፈሪዎች እናሳያቸው፡፡ ፈሪዎች ስል እውነቴን ነው፡፡ ፈሪ ብቻ ነው ያሸነፈውንና ጠላቴ ነው ብሎ የፈረጀውን ካሸነፈውም በሁዋላ እንኩዋን ማሸነፉን ስለማይተማመን እስከመጨረሻው የሚያሰቃዬው፡፡ ወያኔ ጀግና ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ይሄኔ የት ትደርስ ነበር? ብለን መጠየቅ እንችላለን፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ጀግና መሐሪ ነው፤ ጀግና ታጋሽ ነው፤ ጀግና ባገኘው ድል በከንቱ አይታበይም፤ ጀግና አብሮ የሚበላና የሚጠጣ ትሁትና በቃኝን የሚያውቅ እንጂ እንደወያኔ ስግብግብና እሱቅ ውስጥ እንደገባ ሕጻን በዓይን ዐዋጅ ሁሉንም እኔ ልውሰድ የሚል ባሕርይ የለውም፡፡ ጀግና በራሱ ስለሚተማመን ‹እንዲህ ባደርግ እንዲህ ያደርጉኝ ይሆናል› በሚል ከንቱ ጥርጣሬና የራስ ሥሪት ዓለም ውስጥ ተቀምብቦ ዕድሜ ልኩን በምርኮኞቹ ላይ ተንኮል ሲሸርብና ሤራ ሲጎነጉን አይኖርም፡፡ ስለዚህ ወያኔ አንድም የጀግንነት ባሕርይ የሌለው የተራ ወሮበሎችና ወንጀለኞች ጥርቅም መሆኑን ለማጠየቅ በግድ ፍርድ ቤት ሄዶ ነቃሽ መቁጠርና ማስመስከር አያስፈልግም፡፡ ወያኔዎች ከሕዝብ ተዘርፎ በተገኘ ገንዘብ የተገዛ የፈሪ ዱላ አላቸው እንጂ ሌላ የአስተዳደር ዕውቀትም ሆነ ጥበብ፣ ፈሪሃ እግዚኣብሔርም ሆነ ሰብኣዊነት፣ ሕጋዊነትም ሆነ ፍትሃዊነት ፈጹሙን የላቸውም፡፡ እነሱ የቀን ጅቦችና ዓሣማዎች ናቸው፡፡ አእምሮም ሆነ ኀሊና የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም፡፡ ከአፍ እስካፍንጫ የማያስብ ትንሽዬ የዶሮ ጭንቅላትና እንደፊኛ የሚለጠጥ እምብርት የሌለው አንዳች እሚያህል ቀፈት ብቻ ነው ያላቸው፡፡ በዚህ ማንም ይወራርድ – ያሸንፋል፡፡ የሁሉም ዓሣሞች አንደበት መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እሱ ባለብላቢት ምላሱ እንደሥራዬ ቤት ነገርን እየመለሰ እዬቀለሰ ያሸሙርላቸዋል፤ በአግቦ መግነጢስና በድርቅና እንዲሁም በ‹ሞኝ እንዴት ያሸንፋል?› ቢሉት ‹እምቢ ብሎ› ዓይነት የሞኝ ጉልበተኞች ፈሊጥ እየተመራ ተቃዋሚዎቻቸውን ያነጉድላቸዋል፤ በብልጥነትና በመሠሪነት ከመለስ ያነሱቱ ሌሎቹ የምርም ሆኑ የተጋቦት ወያኔዎች በትልቁ ጋንኤል በመለስ ዜናዊ ብብት ሥር ተወትፈው በርሱ ቡራኬ ሀገሪቱን ይመዘብራሉ፤ በእጃቸው የገባን ገንዘብ ወደውጭ ያሸሻሉ፤ ባገር ውስጥም ሕንጻና ፋብሪካ ይገነባሉ፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው፤ እስኪ ሲኖሩበት ያሳየን … ቻው፡፡
ወቅታዊ ልዩ ማሳሰቢያ፤ ምዕመናን እባካችሁ ለማንበብና ያነበባችሁትን ላላነበበ ለማካፈል አትሰልቹ! ጊዜው ደርሶኣል፡፡ የመኸሩ ወቅት እዬተቃረበ መሆኑን የሚያመላክቱ ከዋክብት በሰማይ ላይ እየታዩ መሆናቸውን ‹ዐውደ ነገሥቱ›ንያነበቡ ሊቃውንት እዬጠቆሙ ስለሆነ ከፖለቲካችን ብዙም አንራቅ፡፡ ከሀገር እንዴት ይራቃል? እናት ሀገር እንዴት እስከወዲያኛው ትተዋለች? ኩርፊያው ይብቃንና ለራሳችን ጉዳይ እኛም እንደሚያገባን ተገንዝበን ቀጥተኛ ተሣታፊ እንሁን፡፡ ‹ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በዕጅ›ንም እናስወግድና በሙሉ ልብ ለአንድ ዓላማ እንረባረብ፡፡ ያገር ጉዳይ ለጥቂቶች ብቻ የሚተውአለመሆኑንም እንረዳ፡፡ አክብሮት ከሞላበት ምሥጋና ጋር፡፡
(netsanetzegeye3@gmail.com)